ስለ ወደፊቱ ጊዜ ማሰብ ያስፈራሃል?
ስለ ወደፊቱ ጊዜ ማሰብ ያስፈራሃል?
ለፍርሃት መንስኤ የሚሆኑ ብዙ ነገሮች አሉ። ለምሳሌ ያህል፣ አንዳንድ ሰዎች ‘የምድር የወደፊት ዕጣ ምን ይሆን?’ እያሉ ይጨነቃሉ። ታይም መጽሔት በሚያዝያ 3, 2006 እትሙ ላይ እንዲህ ብሏል:- “የሙቀት መጠን መጨመር፣ ዝናብ የቀላቀለ አውሎ ነፋስ፣ የጎርፍ መጥለቅለቅ፣ ሰደድ እሳት፣ የግግር በረዶዎች መቅለጥና እነዚህን የመሳሰሉት ክስተቶች የምድራችን የአየር ንብረት በከፍተኛ ሁኔታ መዛባቱን ያሳያሉ።”
የተባበሩት መንግሥታት የአካባቢ ጥበቃ ፕሮግራም በግንቦት 2002፣ “ግሎባል ኢንቫይሮሜንት አውትሉክ-3” በሚል ርዕስ ሪፖርት አውጥቶ ነበር። አንድ የዜና ዘገባ እንደገለጸው በ1,000 ሰዎች ትብብር የተዘጋጀው ይህ ሪፖርት እንደሚከተለው ይላል:- “ዛሬ የሚወሰዱት እርምጃዎች፣ የአሁኑም ሆነ የወደፊቱ ትውልድ ሕልውና በተመካባቸው በደኖች፣ በውቅያኖሶች፣ በወንዞች፣ በተራሮች፣ በዱር አራዊትና ለሕይወት አስፈላጊ በሆኑ ሌሎች ነገሮች ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ የሚያሳድሩ ስለሆኑ ፕላኔታችንን በተመለከተ ትልቅ ውሳኔ የሚጠይቅ ሁኔታ ከፊታችን ተደቅኗል።”
ይሁንና የምድር ከባቢያዊ ሁኔታ ሰዎችን ከሚያስጨንቋቸው ነገሮች ውስጥ አንዱ ብቻ ነው። በዓለም ዙሪያ የሚገኙ ሰዎች የአሸባሪዎች ጥቃት ይደርስብናል በሚል ፍርሃት ተውጠዋል። የካናዳ የስለላ ድርጅት ምክትል ዳይሬክተር “ገና ለገና ጥቃት ይሰነዘርብናል በሚል ስጋት እንቅልፍ አጥተን እናድራለን” ሲሉ ተናግረዋል። ሌላው ቀርቶ የምሽቱን ዜና በቴሌቪዥን ማየት ብቻ እንኳ ለጭንቀት ሊዳርግ ይችላል!
በርካታ ጠንካራ ሠራተኞች ከሥራ እንፈናቀላለን የሚል ስጋት አለባቸው። የሠራተኛ ቅነሳ፣ የፋብሪካ መዘጋት፣ በሥራ ቦታ ያለ የፉክክር መንፈስና አሠሪዎች ከሠራተኞቻቸው ከአቅማቸው በላይ የሚጠብቁ መሆኑ የሥራው ዓለም አስተማማኝ እንዳይሆን አድርገውታል። በአሥራዎቹ ዕድሜ ላይ የሚገኙ ወጣቶች የእኩዮቻቸውን ተቀባይነት እንዳያጡ ይፈራሉ። ትንንሽ ልጆች ወላጆቻችን ከልብ አይወዱን ይሆናል ብለው ይሰጋሉ። እነዚህ ልጆች በአካባቢያቸው ስላለው ሁኔታስ ምን ይሰማቸዋል? ሁኔታዎች የሚያሳስቧት አንዲት
እናት እንዲህ ትላለች:- “በዕድሜ ለጋ ለሆኑትና ምንም ለማያውቁት ልጆች ከቤታቸው ውጪ ያለው ዓለም አንዳንድ ጊዜ በጣም የሚያስፈራ ቦታ ሳይሆንባቸው አይቀርም።” ከዚህም ባሻገር ብዙ ወላጆች በዚህ ዓለም የሚታየው የሥነ ምግባር ዝቅጠት በሚወዷቸው ሰዎች በተለይም በልጆቻቸው ላይ የሚያሳድረው ተጽዕኖ ያስጨንቃቸዋል።ብዙውን ጊዜ አረጋውያን ከደረጃ ላይ እንዳይወድቁ ወይም በመንገድ ላይ ጥቃት እንዳይሰነዘርባቸው ይሰጋሉ። አዎን፣ ‘ዳገት መውጣት ያርዳቸዋል፤ መንገድም ያስፈራቸዋል።’ (መክብብ 12:5) በከባድ በሽታ የመያዝ ፍርሃትም አለ። ገዳይ ስለሆኑ የኢንፍሉዌንዛ ቫይረሶች፣ ስለ ካንሰርና ስለ ተላላፊ በሽታዎች የሚናገሩ ዜናዎችን ስንሰማ፣ እኛን ወይም የቤተሰባችንን አባል ለአካል ጉዳት ወይም ለሞት የሚዳርጉ እንግዳ የሆኑ በሽታዎች እንዳይዙን እንሰጋለን። ጤነኛና ጠንካራ የሆነ ሰው ሲታመምና አቅመ ቢስ ሲሆን ስንመለከት፣ ይህ ሁኔታ በእኛ ወይም በምንወዳቸው ሰዎች ላይ ሊደርስ ይችላል ብለን መጨነቃችን ያለ ነገር ነው። የታመሙ ሰዎች ተስፋቸው ተሟጦ ማየት እንዴት የሚያሳዝን ነው!
ለፍርሃት መንስኤ የሚሆኑ ብዙ ነገሮች በዙሪያችን ቢኖሩም የወደፊቱ ጊዜ የተሻለ ይሆናል ብለን እንድንጠብቅ የሚያደርግ በቂ ምክንያት ይኖረናል? ተስፋ እንዳንቆርጥ የሚረዳን ነገር ይኖር ይሆን? የሚቀጥለው ርዕስ ለእነዚህ ጥያቄዎች መልስ ይሰጣል።
[በገጽ 3 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]
© Jeroen Oerlemans/Panos Pictures