በአውሮፓ የሰብዓዊ መብቶች ፍርድ ቤት የተገኘ ድል
በአውሮፓ የሰብዓዊ መብቶች ፍርድ ቤት የተገኘ ድል
በጥር 11, 2007 ስትራዝቡር፣ ፈረንሳይ የሚገኘው የአውሮፓ ሰብዓዊ መብቶች ፍርድ ቤት በሩሲያ የሚኖሩ የይሖዋ ምሥክሮች በሩሲያ ፌዴሬሽን ላይ ላነሱት ክስ በአንድ ድምፅ ፈረደላቸው። ውሳኔው የይሖዋ ምሥክሮች የሃይማኖት ነፃነትና ያለአድልዎ የመዳኘት መብት ሊከበርላቸው እንደሚገባ የሚገልጽ ነበር። እስቲ ለዚህ ክስ መነሻ የሆኑትን ሁኔታዎች እንመልከት።
ቼልያቢንስክ፣ ሩሲያ በሚገኘው የይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤ ውስጥ የሚሰበሰቡት አብዛኞቹ ሰዎች መስማት የተሳናቸው ናቸው። ስብሰባቸውን የሚያካሂዱት ከአንድ የሙያ ማሠልጠኛ ኮሌጅ በተከራዩት አዳራሽ ውስጥ ነበር። እሁድ፣ ሚያዝያ 16, 2000 የአካባቢው የሰብዓዊ መብቶች ሊቀመንበር ወይም ኮሚሽነር፣ ከሁለት ከፍተኛ የፖሊስ ባለ ሥልጣናትና ከአንድ ሲቪል ልብስ የለበሰ ፖሊስ ጋር ሆነው የይሖዋ ምሥክሮቹ ያካሂዱት የነበረው ስብሰባ እንዲቋረጥ አደረጉ። በተለይ ኮሚሽነሯ ለይሖዋ ምሥክሮች ባላቸው ጭፍን ጥላቻ ምክንያት ሕገወጥ ስብሰባ አካሂደዋል በሚል የሐሰት ክስ ስብሰባው እንዲበተን አደረጉ። ከግንቦት 1, 2000 ጀምሮ ደግሞ የመሰብሰቢያ አዳራሹ ኮንትራት እንዲሰረዝ ተደረገ።
የይሖዋ ምሥክሮቹ ለቼልያቢንስክ አቃቤ ሕግ አቤቱታ ቢያቀርቡም ምንም ውጤት ሳይገኝ ቀረ። የሩሲያ ሕገ መንግሥትም ሆነ የአውሮፓ የሰብዓዊና መሠረታዊ መብቶች ድንጋጌ፣ የሃይማኖትና የመሰብሰብ ነፃነት ስለሚሰጡ በአውራጃው ፍርድ ቤት ክስ ተመሠረተ። ከዚያም ለክልሉ ፍርድ ቤት ይግባኝ ተጠየቀ። ቀደም ሲል የሩሲያ ከፍተኛ ፍርድ ቤት፣ በሐምሌ 30, 1999 ባስተላለፈው የፍርድ ብያኔ ላይ እንዲህ ብሎ ነበር:- “የሕሊና ነፃነትንና ሃይማኖታዊ ማኅበራትን አስመልክቶ በወጣው የሩሲያ ሕግ ላይ ‘ያላንዳች እንቅፋት’ የሚለው ሐረግ ቦታው [ለዚህ ዓላማ] የተዘጋጀ እስከሆነ ድረስ ሃይማኖታዊ ሥርዓት ለማካሄድ ከአካባቢው ባለ ሥልጣናት ፈቃድ ማግኘትም ሆነ በቅድሚያ ማሳወቅ እንደማያስፈልግ ያሳያል።” (ቅንፍ የጨመርነው እኛ አይደለንም።) ይህ ውሳኔ እንደ ምሳሌ ሆኖ ሊያገለግል ቢችልም በአውራጃውም ሆነ በክልሉ ፍርድ ቤት የተመሠረተው ክስ ውድቅ ሆነ።
በታኅሣሥ 17, 2001 ጉዳዩ ለአውሮፓ የሰብዓዊ መብቶች ፍርድ ቤት ቀረበ። በመስከረም 9, 2004 ክሱ መታየት ጀመረ። ፍርድ ቤቱ ካስተላለፈው የመጨረሻ ውሳኔ ላይ የተወሰዱ ሐሳቦች ከታች ቀርበዋል:-
“ከሳሾች በሚያዝያ 16, 2000 ሲያከናውኑ የነበረውን ሃይማኖታዊ ስብሰባ የአካባቢው ባለ ሥልጣናት እንዲቋረጥ በማድረግ የሃይማኖት ነፃነታቸውን መጋፋታቸውን ፍርድ ቤቱ አምኖበታል።”
“በሕጋዊ መንገድ ለዚሁ ዓላማ በተከራዩት ቦታ ላይ የሚያካሂዱትን ሃይማኖታዊ ስብሰባ ለመበተን የሚያስችል አንዳች ሕጋዊ መሠረት እንደሌለ በግልጽ ማየት ይቻላል።”
“የሩሲያ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ከዚህ ቀደም በነበረ የፍርድ ውሳኔ ላይ ተመርኩዞ ያረቀቀው ሕግ፣ ሃይማኖታዊ ስብሰባዎችን ለማካሄድ ከባለ ሥልጣናት ፈቃድ ማግኘትንም ሆነ በቅድሚያ ማሳወቅን እንደማይጠይቅ [ፍርድ ቤቱ] ተገንዝቧል።”
“ከሳሾቹ በሚያዝያ 16, 2000 ሲያካሂዱ የነበረው ስብሰባ በኮሚሽነሯና በተባባሪዎቿ መስተጓጎሉ የአውሮፓ የሰብዓዊና መሠረታዊ መብቶች ድንጋጌ አንቀጽ 9ን [የሃይማኖት ነፃነት] የሚጥስ ነው።”
“ፍርድ ቤቱ፣ የአውራጃውና የክልሉ ፍርድ ቤቶች ሁለቱንም ወገኖች ያለአድልዎና ፍትሐዊ በሆነ መንገድ የመዳኘት ኃላፊነታቸውን በአግባቡ እንዳልተወጡ ተረድቷል። በመሆኑም የአውሮፓ የሰብዓዊና መሠረታዊ መብቶች ድንጋጌ አንቀጽ 6 [ያለአድልዎ የመዳኘት መብት] ተጥሷል።”
የይሖዋ ምሥክሮች በአውሮፓ የሰብዓዊ መብቶች ፍርድ ቤት ላገኙት ድል አምላካቸውን ያመሰግናሉ። (መዝሙር 98:1) ፍርድ ቤቱ ያስተላለፈው ውሳኔ ምን ያህል ተጽዕኖ ይኖረዋል? የሃይማኖትና የሕዝብ ጉዳዮች ፖሊሲ ኢንስቲትዩት ፕሬዚዳንት የሆኑት ጆሴፍ ግሪቦስኪ ይህን ጉዳይ አስመልክተው እንዲህ ብለዋል:- “ይህ ብያኔ በአውሮፓ የሰብዓዊ መብቶች ፍርድ ቤት ሥር ባሉት አገሮች ሃይማኖታዊ ነፃነት ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ ያሳድራል። በመሆኑም በመላው አውሮፓ ካለው የሃይማኖት ነፃነት ጋር በተያያዘ ትልቅ ትርጉም ያለው ውሳኔ ነው።”