በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ የምንገኘው ለምንድን ነው?
በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ የምንገኘው ለምንድን ነው?
ክሪስቲን ለ20 ዓመት በትዳር አብሯት የኖረው ባሏ በድንገት ጥሏት ሄደ። በመሆኑም ከ7 እስከ 18 ባለው የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ አንድ ሴትና ሰባት ወንዶች ልጆቿን የማሳደግ ኃላፊነት በእርሷ ትከሻ ላይ ወደቀ። እንዲህ ብላለች:- “ከዚህ በኋላ ከባድ ውሳኔዎችን በሙሉ ራሴ ማድረግ ይኖርብኛል። ይህ ኃላፊነት አስጨንቆኝ ስለነበር ድጋፍና መመሪያ ማግኘት የምችልበት መንገድ አሳስቦኝ ነበር።” ታዲያ ይህንን እርዳታ ከየት አገኘች?
ክሪስቲን እንዲህ ብላለች:- “ክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ለእኔም ሆነ ለቤተሰቤ እምነት ምሰሶ ነበሩ። በስብሰባዎች ላይ ከወንድሞቻችን ማበረታቻ ከአምላክ ቃል ደግሞ መመሪያ እናገኝ ነበር። በስብሰባዎች ላይ አዘውትረን መገኘታችን በእያንዳንዱ የሕይወት ዘርፍ ረድቶናል።”
በዚህ ‘አስጨናቂ የመጨረሻ ጊዜ’ ውስጥ ሁላችንም የተለያዩ ችግሮች ያጋጥሙናል። (2 ጢሞቴዎስ 3:1) እንደ ክሪስቲን ሁሉ አንተም ለይሖዋ የምታቀርበው አምልኮ ዓብይ ክፍል የሆነውን የጉባኤ ስብሰባ የእምነትህ ምሰሶ እንደሆነ አድርገህ ትመለከተው ይሆናል። በእርግጥም በየሳምንቱ የምትገኝባቸው አምስት የጉባኤ ስብሰባዎች ለአምላክ ያለህን ፍቅር እንደሚጨምሩልህ፣ ስለ ወደፊቱ ጊዜ ያለህን ተስፋ እንደሚያጠናክሩልህ አልፎ ተርፎም ችግሮችህን ለመቋቋም የሚያስችል መጽሐፍ ቅዱሳዊ መመሪያ እንደሚያስገኙልህ ምንም ጥርጥር የለውም።
ይሁን እንጂ በስብሰባዎች ላይ አዘውትሮ መገኘት አስቸጋሪ የሚሆንባቸው አንዳንድ ወንድሞች አሉ። ምሽት ላይ በጣም ስለሚደክማቸው ለስብሰባ ተስማሚ የሆነ ልብስ ቀይረው ወደ ጉባኤ የመጓዙን ጉዳይ ሲያስቡት ሁኔታው ዳገት ይሆንባቸዋል። ሌሎች ደግሞ ሥራቸው ከጉባኤ የስብሰባ ሰዓት ጋር ይጋጭባቸዋል። በሁሉም ስብሰባዎች ላይ ለመገኘት በደሞዛቸው ላይ መፍረድ ይኖርባቸዋል አሊያም ሥራቸውን የማጣት አደጋ ሊደቀንባቸው ይችላል። ጥቂቶች ደግሞ ከጉባኤ የሚቀሩት ከጉባኤው ጋር ከሚፈጥሩት ቅርርብ ይልቅ በአንዳንድ የመዝናኛ ዓይነቶች ላይ መካፈል ይበልጥ ዘና እንደሚያደርጋቸው ስለሚሰማቸው ይሆናል።
ታዲያ በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ እንድትገኝ የሚገፋፉህ ዋና ዋና ምክንያቶች ምንድን ናቸው? እነዚህ ስብሰባዎች ለአንተ አስደሳች እንዲሆኑልህ ማድረግ የምትችለው እንዴት ነው? ለእነዚህ ጥያቄዎች መልስ ለማግኘት ኢየሱስ በማቴዎስ 11:28-30 ላይ ያቀረበውን ፍቅራዊ ግብዣ እንመርምር። ኢየሱስ እንዲህ ብሏል:- “እናንት ሸክም የከበዳችሁና የደከማችሁ ሁሉ ወደ እኔ ኑ፤ እኔም ዕረፍት እሰጣችኋለሁ። ቀንበሬን ተሸከሙ፤ ከእኔም ተማሩ፤ እኔ በልቤ የዋህና ትሑት ነኝና፤ ለነፍሳችሁም ዕረፍት ታገኛላችሁ፤ ቀንበሬ ልዝብ ሸክሜም ቀላል ነውና።”
“ወደ እኔ ኑ”
ኢየሱስ “ወደ እኔ ኑ” ብሏል። ለዚህ ግብዣ ምላሽ ከምንሰጥባቸው መንገዶች መካከል አንዱ በስብሰባዎች ላይ አዘውትረን መገኘት ነው። ኢየሱስ በሌላ ጊዜ “ሁለት ወይም ሦስት ሆነው በስሜ ማቴዎስ 18:20
በሚሰበሰቡበት መካከል በዚያ እገኛለሁ” ማለቱ በስብሰባዎች ላይ ለመገኘት በቂ ምክንያት ይሆነናል።—ኢየሱስ በመጀመሪያው መቶ ዘመን የተለያዩ ሰዎችን ተከታዮቹ እንዲሆኑ በግለሰብ ደረጃ በመጋበዝ ከእርሱ ጋር የቅርብ ወዳጅነት የመመሥረት አጋጣሚ ከፍቶላቸው ነበር። አንዳንዶች ግብዣውን ወዲያውኑ ተቀብለዋል። (ማቴዎስ 4:18-22) ሌሎች ግን ቁሳዊ ነገሮችና እነዚህን የመሳሰሉ ሁኔታዎች ግብዣውን ከመቀበል ወደኋላ እንዲሉ አድርገዋቸዋል። (ማርቆስ 10:21, 22፤ ሉቃስ 9:57-62) ኢየሱስ ግብዣውን ተቀብለው የተከተሉትን ሰዎች “እኔ መረጥኋችሁ እንጂ እናንተ አልመረጣችሁኝም” በማለት የሚያጽናና ሐሳብ ነግሯቸዋል።—ዮሐንስ 15:16
ክርስቶስ ከሞት ከተነሳ በኋላ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር በአካል አልነበረም። ይሁንና ለሚያደርጉት እንቅስቃሴ አመራር ይሰጣቸውና ለምክሩ የሚያሳዩትን ምላሽ ይከታተል ስለነበር ከእነርሱ ጋር ነበር ለማለት ይቻላል። ለምሳሌ ኢየሱስ ከሞት ከተነሳ 70 የሚያህሉ ዓመታት ካለፉ በኋላ በትንሿ እስያ ለሚገኙ ሰባት ጉባኤዎች ምክርና ማበረታቻ ሰጥቷል። ኢየሱስ የሰጠው ሐሳብ በእነዚያ ጉባኤዎች ውስጥ ስለሚገኙት ግለሰቦች ጥንካሬና ድክመት ጠንቅቆ ያውቅ እንደነበር የሚያሳይ ነው።—ራእይ 2:1 እስከ 3:22
ኢየሱስ ዛሬም እያንዳንዱ ደቀ መዝሙር ለሚያደርገው እንቅስቃሴ ትኩረት ይሰጣል። “እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር ነኝ” በማለት ቃል ገብቷል። (ማቴዎስ 28:20) የምንኖረው በመጨረሻው ጊዜ ውስጥ በመሆኑ ኢየሱስ እንድንከተለው ካቀረበው ግብዣ ጋር ተስማምተን መኖር ያስፈልገናል። ይህ ደግሞ በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ አዘውትሮ መገኘትንም ይጨምራል። ኢየሱስ የስብሰባ ክፍል በሆኑት በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ ትምህርቶችና ንግግሮች አማካኝነት እንድናዳምጠውና ከእርሱ ‘እንድንማር’ ይፈልጋል። (ኤፌሶን 4:20, 21) ታዲያ ኢየሱስ “ወደ እኔ ኑ” በማለት ላቀረበው ግብዣ ምላሽ እየሰጠህ ነው?
“እናንት ሸክም የከበዳችሁና የደከማችሁ”
በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ ከምንገኝባቸው ዋና ዋና ምክንያቶች መካከል አንዱ ማበረታቻ ለማግኘት ነው። (ዕብራውያን 10:24, 25) ብዙዎቻችን በተለያዩ መንገዶች ‘ሸክም የከበደንና የደከመን’ መሆናችን እሙን ነው። አንተም ጤና ማጣትን የመሳሰሉ የተለያዩ ችግሮች ይኖሩብህ ይሆናል። ቢሆንም ከክርስቲያናዊ ስብሰባዎች በሚገኘው ማበረታቻ ጥቅም ማግኘት ትችላለህ። (ሮሜ 1:11, 12) ለምሳሌ በስብሰባ ላይ ስትገኝ እምነትህን የሚያጠነክር ሐሳብ ትሰማለህ፣ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተውን ተስፋህን ታስታውሳለህ እንዲሁም የተለያዩ ችግሮችን በጽናት የተቋቋሙ ወንድሞችን እምነት መመልከት ትችላለህ። ይህ ሁሉ፣ ችግሮችን እንድትቋቋም ብሎም ስላሉብህ ችግሮች ሚዛናዊ አመለካከት እንድትይዝ ይረዳሃል።
ሥር በሰደደ በሽታ የተያዘች አንዲት እህት የሰጠችውን ሐሳብ ተመልከት። እንዲህ ብላለች:- “በሽታዬ የተወሰኑ ጊዜያት በሆስፒታል እንድተኛ ያስገድደኛል። ከሆስፒታል ከወጣሁ በኋላ ወደ ጉባኤ ስብሰባዎች መሄድ ትንሽ አስቸጋሪ ይሆንብኛል። ይሁን እንጂ አልቀርም። የወንድሞችና እህቶች ደግነትና ፍቅር የደስተኝነት ስሜቴን የሚያድስልኝ ሲሆን ከይሖዋና ከኢየሱስ የማገኘው ትምህርትና መመሪያ ደግሞ ሕይወቴ ትርጉም ያለው እንዲሆን አድርጎልኛል።”
“ቀንበሬ ልዝብ ሸክሜም ቀላል ነው”
እየመረመርነው ባለው በዚህ ጥቅስ ላይ ኢየሱስ “ከእኔም ተማሩ” እንዳለ ልብ በል። የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት የምንሆነው ከእርሱ በመማር ሲሆን ቀንበሩን የምንሸከመው ደግሞ ራሳችንን ለአምላክ ወስነን በምንጠመቅበት ጊዜ ነው። (ማቴዎስ 28:19, 20) የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ሆነን ለመቀጠል በስብሰባዎች ላይ አዘውትረን መገኘታችን በጣም አስፈላጊ ነው። ለምን? ምክንያቱም ስለ ኢየሱስ፣ ስለ ትምህርቶቹና ስላስተማረበት መንገድ የምንማረው በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ ነው።
ክርስቶስ እንድንሸከመው የሚፈልገው ሸክም ምንድን ነው? ይህ ሸክም የአምላክን ፈቃድ እንድናደርግ የተሰጠን መብት ሲሆን ኢየሱስ ራሱም ይህን ሸክም ተሸክሟል። (ዮሐንስ 4:34፤ 15:8) የአምላክን ሕግጋት መጠበቅ ጥረት የሚጠይቅ ቢሆንም ይህን ኃላፊነት መወጣት ግን ከአቅማችን በላይ አይደለም። እርግጥ ይህን ሸክም በራሳችን ኃይል ለመሸከም ከሞከርን ከባድ ሊሆን ይችላል፤ ይሁንና አምላክ መንፈሱን እንዲሰጠን በመጸለይና በስብሰባዎች ላይ የሚቀርብልንን መንፈሳዊ ምግብ በመመገብ እርሱ የሚሰጠውን “እጅግ ታላቅ ኀይል” ማግኘት እንችላለን። (2 ቆሮንቶስ 4:7) ለስብሰባዎች ስንዘጋጅና በጉባኤ ስንሳተፍ ለይሖዋ ያለን ፍቅር እያደገ ይሄዳል። ለሥራ የሚያንቀሳቅሰን ውስጣዊ ግፊት ፍቅር ከሆነ ደግሞ የአምላክ ትእዛዛት ‘ከባድ አይሆኑብንም።’—1 ዮሐንስ 5:3
በጥቅሉ ሲታይ ሰዎች የገንዘብ፣ የጤና እንዲሁም ሌሎች የግል ችግሮች አሉባቸው። ይሁንና እነዚህን ችግሮች ለመፍታት ውስን በሆነው የሰው ጥበብ መታመን የለብንም። ይሖዋ የሚያስፈልገንን ይሰጠናል እንዲሁም ችግሮቻችንን እንድንቋቋም ያስችለናል፤ የጉባኤ ስብሰባዎች ደግሞ ይህን እውነታ በመገንዘብ ‘እንዳንጨነቅ’ ይረዱናል። (ማቴዎስ 6:25-33) በእርግጥም ክርስቲያናዊ ስብሰባዎች የአምላክ ፍቅር መግለጫዎች ናቸው።
“እኔ በልቤ የዋህና ትሑት ነኝ”
ኢየሱስ የአምላክ ቃል ወደሚብራራበት ወደ ምኩራብ የመሄድ ልማድ ነበረው። እንዲህ ባለ አንድ አጋጣሚ የኢሳይያስን ጥቅልል አንስቶ እንዲህ ሲል አነበበ:- “የጌታ መንፈስ በእኔ ላይ ነው፤ ለድኾች ወንጌልን እንድሰብክ፣ እርሱ ቀብቶኛልና፤ ለታሰሩት መፈታትን፣ ለታወሩትም ማየትን እንዳውጅ፣ የተጨቈኑትን ነጻ እንዳወጣ፣ የተወደደችውንም የጌታን ዓመት እንዳውጅ ልኮኛል።” (ሉቃስ 4:16, 18, 19) ኢየሱስ እነዚህ ቃላት በእርሱ ላይ ፍጻሜያቸውን እንደሚያገኙ ለመጠቆም “ይህ በጆሮአችሁ የሰማችሁት የመጽሐፍ ቃል ዛሬ ተፈጸመ” በማለት ሲናገር መስማቱ ምንኛ የሚያስደስት ነበር!—ሉቃስ 4:21
የዋህ “የእረኞች አለቃ” የሆነው ኢየሱስ ለተከታዮቹ የሚደረገውን እንክብካቤ አሁንም በበላይነት ይከታተላል። (1 ጴጥሮስ 5:1-4) በእርሱ አመራር ሥር የሚንቀሳቀሰው “ታማኝና ልባም ባሪያ” በዓለም ዙሪያ በሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤዎች ውስጥ እረኞች ሆነው የሚያገለግሉ ወንዶችን ይሾማል። (ማቴዎስ 24:45-47 የ1954 ትርጉም፤ ቲቶ 1:5-9) እነዚህ ወንዶች ‘የአምላክን ጉባኤ’ በየዋህነት የሚጠብቁ ሲሆን በስብሰባዎች ላይ አዘውትረው በመገኘት ለሌሎች ጥሩ ምሳሌ ይሆናሉ። አንተም በስብሰባዎች ላይ በመገኘትና በመሳተፍ ሌሎችን ማበረታታት የምትችል ከመሆኑም በላይ ለእነዚህ “የወንዶች ስጦታ” አድናቆት እንዳለህ ማሳየት ትችላለህ።—የሐዋርያት ሥራ 15:30-33፤ 20:28 NW፤ ኤፌሶን 4:8 NW, 11, 12
“ለነፍሳችሁም ዕረፍት ታገኛላችሁ”
በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ ስትካፈል እረፍት ማግኘት የምትችለው እንዴት ነው? ይህን ማድረግ የምትችልበት አንዱ መንገድ ኢየሱስ “እንዴት እንደምትሰሙ ተጠንቀቁ” በማለት የሰጠውን ምክር በሥራ ላይ በማዋል ነው። (ሉቃስ 8:18) ከኢየሱስ ለመማር ከፍተኛ ፍላጎት የነበራቸው ሰዎች በትኩረት ይከታተሉት ነበር። በተጨማሪም የሚነግራቸውን ምሳሌዎች እንዲያብራራላቸው ይጠይቁት የነበረ ሲሆን በውጤቱም ጥልቀት ያለው ማስተዋል አግኝተዋል።−ማቴዎስ 13:10-16
አንተም በስብሰባዎቻችን ላይ የሚሰጡትን ንግግሮች በትኩረት በማዳመጥ እነዚያን በመንፈሳዊ የተራቡ ሰዎች መኮረጅ ትችላለህ። (ማቴዎስ 5:3, 6) ትኩረትህ እንዳይሰረቅ ተናጋሪው የሚያስረዳበትን መንገድ ለመከታተል ሞክር። ራስህን እንዲህ የመሳሰሉ ጥያቄዎችን ጠይቅ:- ‘ይህን ትምህርት በሕይወቴ ውስጥ ተግባራዊ ማድረግ የምችለው እንዴት ነው? ሌሎችን ለመርዳት በምን መንገድ ልጠቀምበት እችላለሁ? ይህን ነጥብ ማብራራት የምችለው እንዴት ነው?’ ከዚህ በተጨማሪ ተናጋሪው፣ የሚሰጣቸውን ሐሳቦች ለመደገፍ የሚጠቅሳቸውን ጥቅሶች አውጥተህ ተከታተል። ከፍተኛ ትኩረት ሰጥተህ ባዳመጥክ መጠን ስብሰባዎቹም የዚያኑ ያህል እረፍት የሚሰጡ ይሆኑልሃል።
ከስብሰባው በኋላ ስለተማርካቸው ነገሮች ከሌሎች ጋር ተወያይ። በትምህርቱና ተግባራዊ በሚሆንበት መንገድ ላይ አተኩር። ገንቢ ጭውውት ማድረግ ስብሰባዎች ይበልጥ እረፍት የሚሰጡ እንዲሆኑ ያደርጋሉ።
በእርግጥም አንድ ላይ እንድንሰበሰብ የሚገፋፉ በቂ ምክንያቶች አሉን። ከላይ የተገለጹትን ጥቅሞች ከከለስክ በኋላ ‘ኢየሱስ “ወደ እኔ ኑ” በማለት ላቀረበው ግብዣ ምላሽ የምሰጠው እንዴት ነው?’ ብለህ ራስህን ለምን አትጠይቅም?
[በገጽ 11 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በስብሰባዎች ላይ እንዳትገኝ እንቅፋት የሚሆኑብህ ነገሮች አሉ?