በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

‘እቅድህ ሁሉ ይሳካልሃል’

‘እቅድህ ሁሉ ይሳካልሃል’

‘እቅድህ ሁሉ ይሳካልሃል’

መዝሙራዊው ዳዊት ባቀናበረው መዝሙር ላይ እንዲህ ሲል ጸልዮአል:- “አምላኬ ሆይ፤ ንጹሕ ልብ ፍጠርልኝ፤ ቀና የሆነውንም መንፈስ በውስጤ አድስ። የማዳንህን ደስታ መልስልኝ፤ በእሽታ መንፈስም ደግፈህ ያዘኝ።” (መዝሙር 51:10, 12) ከቤርሳቤህ ጋር ከፈጸመው ኃጢአት ንስሐ የገባው ዳዊት እዚህ ጥቅስ ላይ ይሖዋ አምላክ ልቡን እንዲያነጻለትና ትክክል የሆነውን ማድረግ እንዲችል መንፈሱን ማለትም የአእምሮ ዝንባሌውን እንዲያድስለት ለምኗል።

ይሖዋ በእርግጥ ንጹሕ ልብ በመፍጠር ቀናና እሺ ባይ የሆነውን መንፈስ በውስጣችን ሊያድስልን ይችላል? ወይስ እያንዳንዳችን ንጹሕ ልብ ለማግኘትና ይዘን ለመኖር ጥረት ማድረግ ይኖርብናል? እርግጥ ነው፣ ይሖዋ “ልብን ይመረምራል።” ይሁን እንጂ በልባችን ውስጥ ያለውን ሐሳብ ለመለወጥ ጣልቃ የሚገባው ምን ያህል ነው? (ምሳሌ 17:3፤ ኤርምያስ 17:10) ይሖዋ በሕይወታችን፣ በውስጣዊ ግፊታችንና በድርጊታችን ላይ ምን ያህል ተጽዕኖ ያሳድራል?

ምሳሌ ምዕራፍ 16 ከ1-9 ‘እቅዶቻችን እንዲሳኩ’ ለአምላክ ሕይወታችንን ማስገዛት የምንችለው እንዴት እንደሆነ ይጠቁመናል። (ምሳሌ 16:3) ከቁጥር 10-15 ደግሞ አንድ ንጉሥ ወይም ገዢ ባለበት ኃላፊነት ላይ ያተኩራል።

‘ልብን ማዘጋጀት’ ያለበት ማን ነው?

ምሳሌ 16:1ሀ “የልብ ዕቅድ [“ዝግጅት፣” NW] የሰው ነው” በማለት ይናገራል። ከዚህ በግልጽ ማየት እንደሚቻለው ‘ልብን ማዘጋጀት’ የእያንዳንዳችን ኃላፊነት ነው። ይሖዋ በተአምራዊ መንገድ ልባችንን አያዘጋጅልንም ወይም የእሺ ባይነት መንፈስ አይሰጠንም። ከቃሉ ከመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ትክክለኛ እውቀት ለማግኘት፣ በተማርነው ላይ ለማሰላሰልና አስተሳሰባችንን ከእርሱ አስተሳሰብ ጋር ለማስማማት ጥረት ማድረግ ያስፈልገናል።—ምሳሌ 2:10, 11

ዳዊት “ንጹሕ ልብ” እና ‘ቀና መንፈስ’ እንዲሰጠው መጠየቁ የኃጢአት ዝንባሌ እንዳለውና ልቡን ከዚህ ለማንጻት መለኮታዊ እርዳታ እንደሚያስፈልገው መገንዘቡን የሚያሳይ ነው። ፍጽምና የጎደለን ሰዎች በመሆናችን ‘የሥጋ ሥራዎችን’ እንድንፈጽም ልንፈተን እንችላለን። (ገላትያ 5:19-21) እንደ ‘ዝሙት፣ ርኩሰት፣ ፍትወት፣ ክፉ ምኞትና መጐምጀት የመሳሰሉትን ምድራዊ ምኞቶቻችንን ለመግደል’ የይሖዋ እርዳታ ያስፈልገናል። (ቈላስይስ 3:5) ወደ መጥፎ ድርጊቶች ከሚመሩ ፈተናዎች ለመጠበቅና የኃጢአት ዝንባሌዎችን ከልባችን ለማስወገድ እንዲረዳን ወደ ይሖዋ መጸለያችን ምንኛ አስፈላጊ ነው!

ሌሎች ልባቸውን ‘እንዲያዘጋጁ’ መርዳት እንችል ይሆን? መጽሐፍ ቅዱስ “ግድ የለሽ ቃል እንደ ሰይፍ ይወጋል፤ የጠቢብ አንደበት ግን ፈውስን ያመጣል” በማለት ይናገራል። (ምሳሌ 12:18) አንደበታችን ሌሎችን የሚፈውሰው መቼ ነው? “የአንደበት መልስ ግን ከእግዚአብሔር ዘንድ ነው” በሚለው መሠረት ትክክል የሆነውን የመጽሐፍ ቅዱስ ቃል ለሌሎች ስንናገር ነው።—ምሳሌ 16:1ለ

መጽሐፍ ቅዱስ “የሰው ልብ ከሁሉ ይልቅ ተንኰለኛ ነው፤ ፈውስም የለውም” ይላል። (ኤርምያስ 17:9) ምሳሌያዊው ልባችን ራሱን የማጽደቅና ራሱን የማታለል ዝንባሌ ያጠቃዋል። የጥንቷ እስራኤል ንጉሥ የነበረው ሰሎሞን እንዲህ ዓይነቱ ዝንባሌ ስላለው አደጋ ሲያስጠነቅቅ “የሰው መንገድ ሁሉ በዓይኖቹ ፊት ንጹሕ ነው፤ እግዚአብሔር ግን መንፈስን ይመዝናል” ብሏል።—ምሳሌ 16:2 የ1954 ትርጉም

ራስን መውደድ ለሠራናቸው ስህተቶች ሰበብ እንድንፈላልግ፣ መጥፎ ባሕርዮቻችንን እንድንደብቅ እንዲሁም የራሳችን ክፋት ፈጽሞ እንዳይታየን ሊያደርገን ይችላል። ይሁን እንጂ ይሖዋን ማታለል አንችልም። እርሱ መንፈስን ይመዝናል። መንፈስ የአንድን ሰው የአእምሮ ዝንባሌ የሚያመለክት ሲሆን ከልብ ጋር የተያያዘ ነው። በመሆኑም መንፈሳችን እየጠነከረና እየጎለበተ መሄድ አለመሄዱ በከፍተኛ ሁኔታ የተመካው ምሳሌያዊ ልባችን በሚያደርገው እንቅስቃሴ ላይ ነው። ምሳሌያዊው ልባችን አስተሳሰባችንን፣ ስሜታችንንና ውስጣዊ ግፊታችንን የሚያጠቃልል ነው። ‘ልብን የሚመረምረው’ አምላክ የሚመዝነው ይህንን መንፈስ ሲሆን ፍርዶቹም ከአድሎ የጸዱ ናቸው። መንፈሳችንን በመጠበቅ ጥበበኞች መሆን እንችላለን።

‘የምታደርገውን ሁሉ ለይሖዋ ዐደራ ስጥ’

እቅድ ማውጣት ቆም ብሎ ማሰብን የሚጠይቅ ሲሆን ይህ ደግሞ የልባችን ሥራ ነው። ብዙውን ጊዜ ከሥራ እቅድ ይቀድማል። ታዲያ ጥረታችን ይሳካ ይሆን? ሰሎሞን “የምታደርገውን ሁሉ ለእግዚአብሔር ዐደራ ስጥ፤ ዕቅድህም ሁሉ ይሳካልሃል” ብሏል። (ምሳሌ 16:3) የምናደርገውን ሁሉ ለይሖዋ አደራ መስጠት ሲባል ትምክህታችንን በእርሱ ላይ መጣል፣ በእርሱ መታመን እንዲሁም ራሳችንን ለእርሱ ሥልጣን ማስገዛት ማለት ሲሆን በምሳሌያዊ ሁኔታ የከበደንን ነገር ከትከሻችን ላይ አውርደን በእርሱ ትከሻ ላይ መጣል ማለት ነው። መዝሙራዊው “መንገድህን ለእግዚአብሔር ዐደራ ስጥ፤ በእርሱ ታመን፤ እርሱም ያከናውንልሃል” በማለት ዘምሯል።—መዝሙር 37:5

ይሁንና እቅዶቻችን እንዲሳኩልን ከፈለግን ከአምላክ ቃል ጋር የሚስማሙና ከትክክለኛ የውስጥ ግፊት የመነጩ መሆን ይኖርባቸዋል። ከዚህም በላይ ይሖዋ እንዲረዳንና እንዲያግዘን ወደ እርሱ መጸለይና የመጽሐፍ ቅዱስን ምክር በጥብቅ ለመከተል የቻልነውን ሁሉ ማድረግ ይኖርብናል። በተለይ ደግሞ መከራና አስቸጋሪ ሁኔታዎች ሲያጋጥሙን ‘የከበደንን ነገር በይሖዋ ላይ መጣላችን’ አስፈላጊ ነው፤ ‘እርሱም ደግፎ ይይዘናል።’ እውነት ነው፣ ይሖዋ “የጻድቁንም መናወጥ ከቶ አይፈቅድም።”—መዝሙር 55:22

‘ይሖዋ ሁሉንም ነገር ለራሱ ዐላማ ሠርቶአል’

የምናደርገውን ሁሉ ለይሖዋ አደራ በመስጠታችን ምን ተጨማሪ ውጤት እናገኛለን? ጠቢቡ ንጉሥ “እግዚአብሔር ሁሉንም ነገር ለራሱ ዐላማ ሠርቶአል” ብሏል። (ምሳሌ 16:4ሀ) የአጽናፈ ዓለሙ ፈጣሪ ዓላማ ያለው አምላክ ነው። የምናደርገውን ሁሉ ለእርሱ አደራ ስንሰጥ ሕይወታችን ከንቱና እርባና በሌላቸው ነገሮች ሳይሆን ትርጉም ባለው እንቅስቃሴ የተሞላ ይሆናል። ከዚህም በላይ ይሖዋ ለምድርና በእርሷ ላይ ለሚኖሩ ሰዎች ያወጣው ዓላማ ዘላለማዊ ነው። (ኤፌሶን 3:11) ምድርን የፈጠራት “መኖሪያ” እንድትሆን ነው። (ኢሳይያስ 45:18) በተጨማሪም ይሖዋ የሰው ልጅ በምድር ላይ እንዲኖር ያወጣው የመጀመሪያ ዓላማ መሳካቱ አይቀርም። (ዘፍጥረት 1:28) ለእውነተኛው አምላክ ያደረ ሰው ዘላለማዊና ትርጉም ያለው ሕይወት ይኖረዋል።

ይሖዋ “ክፉዎችንም እንኳ ለጥፋት ቀን አዘጋጅቶአል [“ሠርቷል፣” NW]።” (ምሳሌ 16:4ለ) ይሖዋ ‘ሥራው ፍጹም’ ስለሆነ ክፉዎችን ክፉ አድርጎ አልፈጠረም። (ዘዳግም 32:4) ይሁን እንጂ ክፉዎች ወደ ሕልውና እንዲመጡ የፈቀደ ሲሆን በእነርሱ ላይ የቅጣት ፍርድ የሚፈጽምበት ትክክለኛ ጊዜ እስኪደርስ ድረስ በሕይወት እንዲቆዩ አድርጓል። ለምሳሌ ይሖዋ፣ የግብፁን ፈርዖን “ኀይሌን እንዳሳይህና ስሜም በምድር ዙሪያ ሁሉ እንዲታወቅ ለዚህ አስነሥቼሃለሁ” ብሎት ነበር። (ዘፀአት 9:16) በእርግጥም፣ አሥሩ መቅሰፍቶች እንዲሁም ፈርዖንና ሠራዊቱ ቀይ ባሕር ውስጥ መስጠማቸው አምላክ ተወዳዳሪ የሌለው ኃይል እንዳለው የሚያሳዩ የማይረሱ ማስረጃዎች ናቸው።

በተጨማሪም ይሖዋ ክፉዎች ሳያውቁት ለእርሱ ዓላማ እንዲቆሙ ሁኔታዎችን ሊያመቻች ይችላል። መዝሙራዊው “ሰውን ብትቈጣ [“የሰዎች ቁጣ፣” የ1980 ትርጉም] እንኳ ለክብርህ ይሆናል፤ ከቍጣ የተረፉትንም ትገታቸዋለህ” ብሏል። (መዝሙር 76:10) ይሖዋ ሕዝቦቹን በመቅጣት የሚያስፈልጋቸውን ያህል ሥልጠና ለመስጠት ጠላቶቹ በእነርሱ ላይ ቁጣቸውን እንዲገልጹ የሚፈቅድበት ጊዜ ይኖራል። ቁጣቸው ከመጠን ካለፈ ግን አምላክ ራሱ እርምጃ ይወስድባቸዋል።

ይሖዋ ትሑት አገልጋዮቹን ይደግፋቸዋል። ኩሩና ትዕቢተኛ ሰዎችንስ ምን ያደርጋቸዋል? ንጉሡ “እግዚአብሔር በልብ የሚታበዩትን ሁሉ ይጸየፋል፤ እነርሱም ከቅጣት እንደማያመልጡ በእርግጥ ዕወቅ” በማለት ተናግሯል። (ምሳሌ 16:5) ‘በልባቸው የሚታበዩ’ ሰዎች ቢተባበሩ እንኳ ከቅጣት አያመልጡም። በመሆኑም ምንም ዓይነት እውቀት ወይም ችሎታ አሊያም የአገልግሎት መብት ይኑረን የትሕትና መንፈስ ማዳበራችን ይጠቅመናል።

‘ይሖዋን መፍራት’

ሁላችንም ኃጢአተኞች ሆነን ስለተወለድን ስህተት ወደ መሥራት እናዘነብላለን። (ሮሜ 3:23፤ 5:12) ታዲያ ወደ መጥፎ ጎዳና የሚመሩ እቅዶችን እንዳናወጣ ምን ሊረዳን ይችላል? ምሳሌ 16:6 “በፍቅርና በታማኝነት [“በፍቅራዊ ደግነትና በእውነት፣” NW] ኀጢአት ይሰረያል፤ እግዚአብሔርን በመፍራት ሰው ከክፋት ይርቃል” ይላል። ይሖዋ በፍቅራዊ ደግነቱና በእውነቱ ተነሳስቶ ኃጢአታችንን ይቅር ቢልልንም እንኳ ኃጢአት ከመሥራት እንድንቆጠብ የሚያደርገን ለእርሱ ያለን ፍርሃት ነው። አምላክን ከመውደድና ያሳየንን ፍቅራዊ ደግነት ከማድነቅ በተጨማሪ እርሱን ላለማሳዘን የሚስችለንን ፍርሃት ማዳበራችን ምንኛ አስፈላጊ ነው!

አምላክን መፍራት የምንችለው እጅግ ታላቅ ለሆነው ኃይሉ ጥልቅ አክብሮት ስናዳብር ነው። በፍጥረት ሥራው ላይ የተንጸባረቀውን ኃይሉን እስቲ አስብ! ኢዮብ በአምላክ የፍጥረት ሥራዎች ላይ የታየውን ኃይል መለስ ብሎ እንዲያስታውስ መደረጉ አስተሳሰቡን እንዲያስተካክል ረድቶታል። (ኢዮብ 42:1-6) እኛም በተመሳሳይ ይሖዋ ለሕዝቦቹ ያደረጋቸውን ሥራዎች አስመልክቶ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ተመዝግበው የሚገኙትን ታሪኮች ማንበባችንና ማሰላሰላችን አስተሳሰባችንን እንድናስተካክል አይረዳንም? መዝሙራዊው “ኑና፣ እግዚአብሔር ያደረገውን እዩ በሰዎች መካከል ሥራው አስፈሪ ነው!” በማለት ዘምሯል። (መዝሙር 66:5) በመሆኑም የይሖዋን ፍቅራዊ ደግነት አቅልለን መመልከት አይኖርብንም። ይሖዋ እስራኤላውያን ‘ሲያምጹና ቅዱስ መንፈሱን ሲያሳዝኑ እርሱ ራሱ ተመልሶ ጠላት በመሆን ተዋግቷቸዋል።’ (ኢሳይያስ 63:10) በሌላ በኩል ግን “የሰው መንገድ እግዚአብሔርን ደስ ሲያሰኘው፣ ጠላቶቹ እንኳ አብረውት በሰላም እንዲኖሩ ያደርጋል።” (ምሳሌ 16:7) ይሖዋን መፍራት እንዴት ያለ ጥበቃ ነው!

ጠቢቡ ንጉሥ “ከጽድቅ ጋር ጥቂቱ ነገር፣ በግፍ ከሚገኝ ብዙ ትርፍ ይሻላል” በማለት ተናገረ። (ምሳሌ 16:8) ምሳሌ 15:16 “እግዚአብሔርን ከመፍራት ጋር ያለ ጥቂት ነገር፣ ሁከት ካለበት ትልቅ ሀብት ይበልጣል” ይላል። ለአምላክ ጥልቅ አክብሮት ማሳየት በጽድቅ ጎዳና ላይ መመላለሳችንን እንድንቀጥል የሚረዳን እጅግ አስፈላጊ ባሕርይ ነው።

“ሰው በልቡ መንገዱን ያቅዳል”

ሰው የተፈጠረው ትክክልና ስህተት የሆነውን መምረጥ የሚያስችል ነፃነት እንዲኖረው ተደርጎ ነው። (ዘዳግም 30:19, 20) ምሳሌያዊው ልባችን የተለያዩ አማራጮችን በማመዛዘን በአንዱ ወይም ከዚያ በላይ በሆኑት ላይ የማተኮር ችሎታ አለው። ሰሎሞን እያንዳንዱ ሰው የራሱን ምርጫ የማድረግ ኃላፊነት እንዳለበት ሲጠቁም “ሰው በልቡ መንገዱን ያቅዳል” ብሏል። አንድ ጊዜ ይህን እርምጃ ከወሰደ በኋላ ግን “እግዚአብሔር . . . ርምጃውን ይወስንለታል” ወይም ያቀናለታል። (ምሳሌ 16:9) ይሖዋ እርምጃችንን መምራት ስለሚችል ‘እቅዶቻችን እንዲሳኩ’ የእርሱን እርዳታ መፈለጋችን ጥበብ ነው።

ልብ ተንኮለኛ እንደሆነና ሰበብ አስባቦችን የመደርደር ችሎታ እንዳለው ቀደም ሲል ተመልክተናል። ለምሳሌ አንድ ሰው ኃጢአት ከፈጸመ በኋላ ልቡ ጥፋቱን አምኖ ላለመቀበል ሰበብ ይፈላልግ ይሆናል። ግለሰቡ የኃጢአት መንገዱን ከመተው ይልቅ አምላክ አፍቃሪ፣ ደግ፣ መሐሪና ይቅር ባይ እንደሆነ በመናገር ምክንያት ይደረድር ይሆናል። እንዲህ ዓይነቱ ሰው በልቡ “‘እግዚአብሔር ረስቶአል፤ ፊቱን ሸፍኖአል፤ ፈጽሞም አያይም’ ይላል።” (መዝሙር 10:11) ይሁንና የአምላክን ምሕረት በዚህ መንገድ ማሰብ ስህተት ከመሆኑም በላይ አደገኛ ነው።

‘ሐቀኛ መስፈሪያና ሚዛን ከይሖዋ ናቸው’

ሰሎሞን ስለ ሰው ልብና ድርጊት ከተናገረ በኋላ ትኩረቱን ወደ ንጉሥ በማዞር እንዲህ አለ:- “የንጉሥ ከንፈሮች እንደ አምላክ ቃል ይናገራሉ፤ አንደበቱ ፍትሕን ያዛባ ዘንድ አይገባም።” (ምሳሌ 16:10) ይህ ጥቅስ በዙፋን ላይ በተቀመጠው በንጉሡ በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ እንደሚፈጸም ምንም ጥርጥር የለውም። ምድርን የሚያስተዳድረው ከመለኮታዊው ፈቃድ ጋር በሚስማማ መንገድ ነው።

ጠቢቡ ንጉሥ የፍትሕንና የጽድቅን ምንጭ ሲገልጽ “ሐቀኛ መስፈሪያና ሚዛን ከእግዚአብሔር ናቸው፤ በከረጢት ውስጥ ያሉት መመዘኛዎችም ሁሉ ሥራዎቹ ናቸው” በማለት ተናግሯል። (ምሳሌ 16:11) ሐቀኛ መስፈሪያንና ሚዛንን ያዘጋጀው ይሖዋ ነው። እንዲህ ዓይነት መመዘኛዎች በአንድ ንጉሥ ምርጫ የሚወሰኑ አይደሉም። ኢየሱስ ምድር ላይ በነበረበት ጊዜ “እኔ ብቻዬን ከራሴ ምንም ማድረግ አልችልም፤ የምፈርደው የምሰማውን ብቻ ነው፤ የላከኝን እንጂ የራሴን ፈቃድ ስለማልሻም ፍርዴ ትክክል ነው” ብሎ ነበር። አብ፣ ለልጁ ‘ፍርድን ሁሉ አሳልፎ ስለሰጠው’ ከእርሱ ፍጹም ፍትሕ መጠበቅ እንችላለን።—ዮሐንስ 5:22, 30

ይሖዋን ከሚወክል ንጉሥ ምን ተጨማሪ ነገር መጠበቅ ይቻላል? የእስራኤል ንጉሥ “ክፋትን ማድረግ ለነገሥታት አጸያፊ ነው፤ ዙፋን የሚጸናው በጽድቅ ነውና” በማለት ተናግሯል። (ምሳሌ 16:12) መሲሐዊው መንግሥት የሚተዳደረው በአምላክ የጽድቅ ሕጎች መሠረት ነው። ይህ ዓይነቱ መንግሥት ‘ከጥፋት ዙፋን’ ጋር ምንም ኅብረት የለውም።—መዝሙር 94:20፤ ዮሐንስ 18:36፤ 1 ዮሐንስ 5:19

የንጉሥን መልካም ፈቃድ ማግኘት

የንጉሥ ተገዢዎች ምላሽ መስጠት የሚኖርባቸው እንዴት ነው? ሰሎሞን “ነገሥታት በታማኝ ከንፈሮች ደስ ይላቸዋል፤ እውነት የሚናገረውን ሰው ይወዱታል። የንጉሥ ቍጣ የሞት መልእክተኛ ነው፤ ጠቢብ ሰው ግን ቍጣውን ያበርዳል” ብሏል። (ምሳሌ 16:13, 14) በዛሬው ጊዜ የሚገኙት የይሖዋ አምላኪዎች ከእነዚህ ቃላት ጋር የሚስማማ እርምጃ በመውሰድ በስብከቱና ደቀ መዛሙርት በማድረጉ ሥራ በትጋት ይሳተፋሉ። (ማቴዎስ 24:14፤ 28:19, 20) ከንፈሮቻቸውን በዚህ መንገድ መጠቀማቸው መሲሐዊውን ንጉሥ ኢየሱስ ክርስቶስን እንደሚያስደስተው ያውቃሉ። ይህን ኃያል ንጉሥ ላለማሳዘንና የእርሱን ሞገስ ለማግኘት ጥረት ማድረግ በእርግጠኝነት የጥበብ አካሄድ ነው። በመሲሐዊው ንጉሥ ዘንድ ተቀባይነት ለማግኘት ጥረት ማድረግ እንዴት ያለ ብልህነት ነው!

ሰሎሞን በመቀጠል “የንጉሥ ፊት ሲፈካ ሕይወት አለ፤ በጎነቱም ዝናብ እንዳዘለ የበልግ ደመና ነው” በማለት ተናግሯል። (ምሳሌ 16:15) የይሖዋ ‘ፊት መብራቱ’ መለኮታዊ ተቀባይነትን እንደሚያመለክት ሁሉ ‘የንጉሥ ፊት መፍካቱም’ በእርሱ ዘንድ ሞገስ ማግኘትን ያመለክታል። (መዝሙር 44:3፤ 89:15) የጠቆረ ደመና ለእህል መብቀል ወሳኝ የሆነው ዝናብ መምጣቱን እንደሚጠቁም ሁሉ የንጉሥ በጎነትም ጥሩ ነገሮች እንደሚመጡ የሚያሳይ ነው። በመሲሐዊው ንጉሥ የግዛት ዘመን የሚኖረው ሕይወት በንጉሥ ሰሎሞን የግዛት ዘመን በመጠኑ እንደታየው በደስታና በብልጽግና የተሞላ ይሆናል።—መዝሙር 72:1-17

የአምላክ መንግሥት ከፀሐይ በታች ያለውን እያንዳንዱን ሁኔታ የሚቆጣጠርበትን ጊዜ እየተጠባበቅን ሁላችንም ልባችንን ለማንጻት የአምላክን እርዳታ እንፈልግ። በተጨማሪም ትምክህታችንን በይሖዋ ላይ እንጣል እንዲሁም አምላካዊ ፍርሃት እናዳብር። እንዲህ ካደረግን ‘እቅዶቻችን ሁሉ እንደሚሳኩ’ እርግጠኞች መሆን እንችላለን።—ምሳሌ 16:3

[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ይሖዋ ‘ክፉዎችን ለጥፋት ቀን’ የሠራው በምን መልኩ ነው?