የትንሣኤ ተስፋ እውን ሆኖልሃል?
የትንሣኤ ተስፋ እውን ሆኖልሃል?
‘ሙታን ይነሳሉ።’—የሐዋርያት ሥራ 24:15
1. ሞት የማይቀር ነገር መስሎ የሚታየው ለምንድን ነው?
“በዚህ ዓለም ላይ ሞትና ቀረጥ የማይቀሩ ነገሮች ናቸው።” አሜሪካዊው የፖለቲካ ሰው ቤንጃሚን ፍራንክሊን በ1789 የጻፏቸው እነዚህ ቃላት በአንዳንዶች ዘንድ አድናቆት አትርፈዋል። ይሁንና ታማኝነት የጎደላቸው ብዙ ሰዎች ቀረጥ በአግባቡ ባለመክፈል ያጭበረብራሉ። ከሞት ግን ማምለጥ የሚቻል አይመስልም። ውሎ አድሮ ከሚመጣብን ሞት በራሳችን ኃይል ልናመልጥ አንችልም። ሞት ሁላችንንም ያገኘናል። የሰው ልጆች መቃብር የሆነው የማይጠግበው ሲኦል የምንወዳቸውን ሰዎች ሲነጥቀን ቆይቷል። (ምሳሌ 27:20) ይሁንና የሚከተለውን የሚያጽናና ሐሳብ ተመልከት።
2, 3. (ሀ) ብዙዎች እንደሚያስቡት መሞት የማይቀር ነው ሊባል የማይችለው ለምንድን ነው? (ለ) በዚህ ርዕስ ውስጥ ምን እንመረምራለን?
2 የይሖዋ ቃል የሞቱ ሰዎች ዳግመኛ ሕያው እንደሚሆኑ የሚገልጸውን አስተማማኝ የሆነ የትንሣኤ ተስፋ ይሰጣል። ይህ ተስፋ እንዲያው ሕልም ብቻ አይደለም። እንዲሁም በአጽናፈ ዓለም ውስጥ ያለ ማንኛውም ኃይል ይሖዋ ይህን ተስፋ እንዳይፈጽም ሊያግደው አይችልም። ይሁን እንጂ በዛሬው ጊዜ ያሉ ብዙዎች፣ ሞትን የማያዩ በርካታ ሰዎች መኖራቸውን አይገነዘቡም። ሞትን የማያዩ ይኖራሉ የምንለው ለምንድን ነው? ምክንያቱም ቁጥራቸው በውል የማይታወቅ ‘እጅግ ብዙ ሕዝቦች’ በቅርቡ ከሚመጣው ‘ታላቅ መከራ’ ስለሚተርፉ ነው። (ራእይ 7:9, 10, 14) ከዚያም የዘላለም ሕይወት ተስፋ ይዘው ይኖራሉ። በመሆኑም ሞት ለእነዚህ ሰዎች የማይቀር ነገር ነው ሊባል አይችልም። እንዲያውም ‘ሞት ይደመሰሳል።’—1 ቆሮንቶስ 15:26
3 ‘ጻድቃንና ኀጥአን ከሙታን ይነሳሉ’ ሲል እንደተናገረው እንደ ሐዋርያው ጳውሎስ እኛም ትንሣኤ እንደሚኖር እርግጠኞች ልንሆን ይገባል። (የሐዋርያት ሥራ 24:15) ትንሣኤን በተመለከተ የሚነሱ ሦስት ጥያቄዎችን እንመርምር። አንደኛ፣ ይህ ተስፋ መፈጸሙ አይቀርም እንድንል የሚያደርገን ምንድን ነው? ሁለተኛ፣ የትንሣኤ ተስፋ አንተን በግልህ ሊያጽናናህ የሚችለው እንዴት ነው? ሦስተኛ፣ ይህ ተስፋ አሁን ሕይወትህን በምትመራበት መንገድ ላይ ተጽዕኖ የሚያሳድረው እንዴት ነው?
ትንሣኤ—እርግጠኛ የሆነ ተስፋ
4. ትንሣኤ በይሖዋ ዓላማ ውስጥ ወሳኝ ሚና የሚጫወተው እንዴት ነው?
4 ትንሣኤ እርግጠኛ የሆነ ተስፋ ነው እንድንል የሚያደርጉን በርካታ ምክንያቶች አሉ። ከሁሉም በላይ፣ ትንሣኤ በይሖዋ ዓላማ ውስጥ ወሳኝ ሚና አለው። ሰይጣን የሰው ልጆችን ወደ ኃጢአት እንደመራቸውና ይህም ለሞት እንደዳረጋቸው አስታውስ። በዚህም ምክንያት ኢየሱስ ስለ ሰይጣን ሲናገር “እርሱ ከመጀመሪያ ነፍሰ ገዳይ ነበር” ብሏል። (ዮሐንስ 8:44) ይሁንና ይሖዋ “ሴቲቱ” ወይም በሚስት የተመሰለችው ሰማያዊ ድርጅት ‘የጥንቱን እባብ’ ራስ የሚቀጠቅጥ ማለትም ሰይጣንን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ የሚያጠፋ ዘር እንደምታስገኝ ቃል ገብቷል። (ዘፍጥረት 3:1-6, 15፤ ራእይ 12:9, 10፤ 20:10) ይሖዋ መሲሐዊውን ዘር በተመለከተ ያለውን ዓላማ ደረጃ በደረጃ ሲገልጥ ዘሩ ሰይጣንን ከማጥፋት የበለጠ ነገር እንደሚያከናውን ግልጽ ሆነ። የአምላክ ቃል “የእግዚአብሔር ልጅ የተገለጠውም የዲያብሎስን ሥራ ያፈርስ ዘንድ ነው” ሲል ይገልጻል። (1 ዮሐንስ 3:8) ይሖዋ በኢየሱስ ክርስቶስ አማካኝነት ከሚያፈርሳቸው የሰይጣን ሥራዎች መካከል፣ ከአዳም የወረስነው ኃጢአት ያመጣብን ሞት በዋነኝነት ይጠቀሳል። በዚህ ረገድ የኢየሱስ ቤዛዊ መሥዋዕትና ትንሣኤ ወሳኝ ሚና ይጫወታሉ።—የሐዋርያት ሥራ 2:22-24፤ ሮሜ 6:23
5. ትንሣኤ የይሖዋን ስም የሚያስከብረው እንዴት ነው?
5 ይሖዋ ቅዱስ ስሙን ለማስከበር ወስኗል። ሰይጣን የአምላክን ስም ሲያጠፋና ውሸትን ሲያዛምት ኖሯል። አዳምና ሔዋን አምላክ ከከለከለው ፍሬ ቢበሉ ‘እንደማይሞቱ’ በመግለጽ ሐሰት ተናግሯል። (ዘፍጥረት 2:16, 17፤ 3:4) ከዚያን ጊዜ አንስቶ ሰይጣን ከዚህ ጋር የሚመሳሰሉ የሐሰት ትምህርቶችን አስፋፍቷል። ከእነዚህ መካከል ‘አንድ ሰው ሲሞት ነፍሱ በሕይወት ትቀጥላለች’ የሚለው ትምህርት ይገኝበታል። ሆኖም ይሖዋ በትንሣኤ አማካኝነት ይህን የመሰሉት ትምህርቶች በሙሉ ሐሰት መሆናቸውን ያጋልጣል። ሕይወትን የሚያድነውም ሆነ መልሶ የሚሰጠው እርሱ ብቻ መሆኑን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ያረጋግጣል።
6, 7. ይሖዋ ሙታንን ስለ ማስነሳት ምን ይሰማዋል? እንዲህ እንደሚሰማውስ ማወቅ የምንችለው እንዴት ነው?
6 ይሖዋ የሞቱ ሰዎችን ለማስነሳት ይናፍቃል። ይሖዋ በዚህ ረገድ ያለውን ስሜት መጽሐፍ ቅዱስ በግልጽ ይናገራል። ለምሳሌ ያህል፣ ታማኙ ኢዮብ በመንፈስ ቅዱስ አነሳሽነት የተናገረውን የሚከተለውን ሐሳብ ተመልከት:- “ሰው ከሞተ በኋላ ተመልሶ በሕይወት ይኖራል? እድሳቴ እስከሚመጣ ድረስ፣ ተጋድሎ የሞላበትን [“የግዳጅ አገልግሎት፣” NW] ዘመኔን ሁሉ እታገሣለሁ። ትጠራኛለህ፤ እኔም እመልስልሃለሁ፤ የእጅህንም ሥራ ትናፍቃለህ።” (ኢዮብ 14:14, 15) እነዚህ ቃላት ምን ትርጉም አላቸው?
7 ኢዮብ ከሞተ በኋላ ለተወሰነ ጊዜ አንቀላፍቶ መቆየት እንደሚኖርበት ተገንዝቦ ነበር። ኢዮብ ነፃ እስከሚሆንበት ጊዜ ድረስ በውዴታ ሳይሆን በግዴታ የሚቆይበትን ይህን ዘመን ‘ከግዳጅ አገልግሎት’ ጋር አመሳስሎታል። ኢዮብ ነፃ እንደሚወጣ እርግጠኛ ነበር። የእድሳቱ ጊዜ መምጣቱ እንደማይቀር ተገንዝቧል። እንደዚህ እንዲያስብ ያደረገው ምንድን ነው? ይሖዋ በዚህ ረገድ ያለውን ስሜት ማወቁ ነው። ይሖዋ ታማኝ አገልጋዮቹን እንደገና ለማየት ‘ይናፍቃል።’ አዎን፣ አምላክ ጻድቃንን በሙሉ ዳግም ወደ ሕልውና ለማምጣት ይጓጓል። በተጨማሪም ይሖዋ ከሞት የሚነሱ ሌሎች ሰዎችም ገነት በሆነች ምድር ላይ ለዘላለም እንዲኖሩ አጋጣሚ ይሰጣቸዋል። (ሉቃስ 23:43፤ ዮሐንስ 5:28, 29) ይህ የአምላክ ፈቃድ ነው፤ ታዲያ ማን ሊያስቆመው ይችላል?
8. ይሖዋ የወደፊት ተስፋችን እውን እንደሚሆን ‘ያረጋገጠው’ እንዴት ነው?
8 የወደፊት ተስፋችን በኢየሱስ ትንሣኤ አማካኝነት የተረጋገጠ ሆኗል። ጳውሎስ በአቴና በሰጠው ንግግር ላይ እንዲህ ብሏል:- “[አምላክ] በመረጠው ሰው አማካይነት በዓለም ላይ በጽድቅ የሚፈርድበትን ቀን ወስኖአልና፤ እርሱንም ከሙታን በማስነሣቱ ለሰዎች ሁሉ ይህን አረጋግጦአል።” (የሐዋርያት ሥራ 17:31) ጳውሎስን ያዳምጡት ከነበሩት ሰዎች መካከል አንዳንዶቹ ስለ ትንሣኤ ሲሰሙ አፌዙ። ሌሎች ግን አማኝ ሆኑ። የእነዚህን ሰዎች ትኩረት የሳበው ጳውሎስ የትንሣኤ ተስፋ የተረጋገጠ ስለመሆኑ የተናገረው ሐሳብ ሊሆን ይችላል። ይሖዋ ኢየሱስን ሲያስነሳ ከሁሉ የላቀውን ተአምር ሠርቷል። ልጁን ኃያል መንፈሳዊ ፍጡር አድርጎ ከሞት አስነስቶታል። (1 ጴጥሮስ 3:18) ኢየሱስ ከሞት ከተነሳ በኋላ ያገኘው ክብርም ሆነ ሥልጣን ሰው ሆኖ ወደ ምድር ከመምጣቱ በፊት ከነበረው በእጅጉ የበለጠ ነው። ኢየሱስ የማይሞት ሕይወት በማግኘቱና ከይሖዋ ቀጥሎ ያለውን ከፍተኛ ሥልጣን በመያዙ ይህ ነው የማይባል ኃላፊነት ከአባቱ ለመቀበል ብቁ ሆኗል። ይሖዋ በሰማይም ሆነ በምድር የመኖር ተስፋ ያላቸውን ሰዎች ከሞት ለማስነሳት በኢየሱስ ይጠቀማል። በመሆኑም ኢየሱስ ራሱ “ትንሣኤና ሕይወት እኔ ነኝ” ብሏል። (ዮሐንስ 5:25፤ 11:25) ይሖዋ ልጁን ከሞት በማስነሳት ለታማኝ አገልጋዮቹ የሰጠው ይህ ተስፋ እንደሚፈጸም አረጋግጧል።
9. የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ ትንሣኤ አስተማማኝ ተስፋ መሆኑን የሚያረጋግጠው እንዴት ነው?
9 ትንሣኤ ሲፈጸም የተመለከቱ የዓይን ምሥክሮች የነበሩ ሲሆን ስለዚህ የሚናገሩ ዘገባዎችም በአምላክ ቃል ውስጥ ይገኛሉ። መጽሐፍ ቅዱስ ትንሣኤ ስላገኙ ስምንት ሰዎች የሚናገሩ ዝርዝር ዘገባዎችን ይዟል። እነዚህ ተአምራት የተፈጸሙት በድብቅ ሳይሆን በግልጽ፣ ብዙውን ጊዜም የዓይን ምሥክሮች ባሉበት ነበር። ኢየሱስ ለአራት ቀናት ሞቶ የነበረውን አልዓዛርን ያስነሳው በርካታ ለቀስተኞች በተሰበሰቡበት ነው። ከለቀስተኞቹ መካከል የአልዓዛር ቤተሰቦች፣ ወዳጆችና ጎረቤቶች እንደሚገኙበት ግልጽ ነው። ይህ ተአምር ኢየሱስ ከአምላክ የተላከ ለመሆኑ ጠንካራ ማስረጃ ስለነበር ጠላቶቹ እንኳ መፈጸሙን ፈጽሞ ሊክዱት አልቻሉም። ከዚህ ይልቅ ኢየሱስን ብቻ ሳይሆን አልዓዛርንም ጭምር ለመግደል አሴሩ። (ዮሐንስ 11:17-44, 53፤ 12:9-11) አዎን፣ ትንሣኤ እርግጠኛ ተስፋ እንደሆነ ልንተማመን እንችላለን። አምላክ እኛን ለማጽናናትና እምነታችንን ለመገንባት ሲል በጥንት ጊዜ የተፈጸሙት ትንሣኤዎች ተመዝግበው እንዲቆዩልን አድርጓል።
የትንሣኤ ተስፋ የሚሰጠው መጽናኛ
10. ስለ ትንሣኤ ከሚናገሩት የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባዎች መጽናኛ ለማግኘት ምን ማድረግ ይኖርብናል?
10 ከሞት ጋር በመፋጠጥህ ምክንያት መጽናኛ ለማግኘት የተመኘህበት ጊዜ አለ? ስለ ትንሣኤ ከሚናገሩት የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባዎች መጽናኛ እንደምናገኝ አያጠራጥርም። እንደነዚህ ያሉትን ዘገባዎች ማንበብህ፣ ባነበብከው ላይ ማሰላሰልህና ታሪኩን በዓይነ ሕሊናህ መሳልህ የትንሣኤ ተስፋ ይበልጥ እውን ሆኖ እንዲታይህ ያደርጋል። (ሮሜ 15:4) እነዚህ ታሪኮች ልብ ወለድ አይደሉም። በአንድ ወቅት በገሃዱ ዓለም የኖሩ እንደኛው ያሉ ሰዎች ያሳለፏቸው እውነተኛ ታሪኮች ናቸው። እስቲ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከተመዘገቡት ትንሣኤዎች መካከል የመጀመሪያ የሆነውን በአጭሩ እንመልከት።
11, 12. (ሀ) የሰራፕታዋ መበለት ምን የሚያሳዝን ሁኔታ ገጠማት? መጀመሪያ ላይስ ምን ተሰምቷት ነበር? (ለ) ይሖዋ መበለቲቱን ለመርዳት ሲል ለነቢዩ ኤልያስ ምን የማድረግ ኃይል እንደሰጠው አብራራ።
11 ሁኔታውን በዓይነ ሕሊናህ ለማየት ሞክር። ነቢዩ ኤልያስ ሰራፕታ በምትኖረው መበለት ቤት፣ ሰገነት ላይ በሚገኝ ክፍል ውስጥ በእንግድነት ከተቀመጠ ጥቂት ሳምንታት ሆኖታል። ጊዜው አስከፊ ነበር፤ ድርቅና ረሃብ አካባቢውን አጥቅቷል። በዚህም ሳቢያ ብዙዎች እየሞቱ ነው። ይሖዋ፣ ኤልያስ ለረጅም ጊዜ የሚዘልቅ ተአምር እንዲፈጽም በማድረግ ይህች ትሑት መበለት ላሳየችው እምነት ወሮታ ከፍሏታል። አምላክ በኤልያስ ተጠቅሞ ዱቄቱና ዘይቱ በተአምር እንዲበረክት ባደረገ ጊዜ መበለቲቱና ልጇ ያላቸው ምግብ ተሟጥጦ ለረሀብ ሊጋለጡ ነበር። በዚህ ሁኔታ ላይ እያሉ መበለቲቱ አሳዛኝ ነገር ገጠማት። ልጇ በድንገት ታመመና ብዙም ሳይቆይ እስትንፋሱ ቀጥ አለ። መበለቲቱም ክፉኛ አዘነች! ያለ ባል እርዳታና ድጋፍ መኖር በራሱ አስቸጋሪ ሆኖ ሳለ አሁን ደግሞ አንድ ልጇን በሞት ተነጠቀች። እጅግ ከማዘኗ የተነሳ ኤልያስንና አምላኩን ይሖዋን አማረረች! ነቢዩ ምን ያደርግ ይሆን?
12 ኤልያስ መበለቲቱ የሐሰት ክስ በመሰንዘሯ አልገሠጻትም። ከዚህ ይልቅ “ልጅሽን ስጪኝ” አላት። ኤልያስ ልጁን ተሸክሞ ወደሚኖርበት ሰገነት ከወሰደው በኋላ ሕይወቱ እንዲመለስለት ደጋግሞ ጸለየ። በመጨረሻም ይሖዋ ጸሎቱን ሰማው! ልጁ መተንፈስ ሲጀምር ኤልያስ ምን ያህል ተደስቶ ሊሆን እንደሚችል አስብ። ልጁ በድጋሚ ሕያው ሆነ። ኤልያስ ልጁን ወደ እናቱ ካመጣው በኋላ “ልጅሽ ይኸውልሽ፤ ድኖልሻል!” አላት። ደስታዋ ወደር አልነበረውም። እርሷም “አሁን የእግዚአብሔር ሰው መሆንህን፣ ከአንደበትህም የወጣው የእግዚአብሔር ቃል እውነት መሆኑን ዐወቅሁ” አለችው። (1 ነገሥት 17:8-24) በይሖዋና በወኪሉ ላይ ያላት እምነት ከምንጊዜውም ይበልጥ ተጠናከረ።
13. ኤልያስ የአንዲት መበለትን ልጅ ከሞት እንዳስነሳ የሚገልጸው ዘገባ የሚያጽናናን እንዴት ነው?
13 እንዲህ ባለው ዘገባ ላይ ማሰላሰል እንደሚያጽናናህ እሙን ነው። ይሖዋ ጠላታችን የሆነውን ሞትን ድል ማድረግ እንደሚችል በግልጽ ታይቷል! ሙታን ሁሉ በሚነሱበት ጊዜ፣ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ሰዎች ያቺ መበለት የተሰማት ዓይነት ደስታ ሲያገኙ የሚኖረውን ሁኔታ አስብ! ይሖዋ፣ በልጁ አማካኝነት በምድር ዙሪያ ትንሣኤ እንዲከናወን ሲያደርግ በሰማይም ታላቅ ደስታ ይሆናል። (ዮሐንስ 5:28, 29) የምትወደው ሰው በሞት ተለይቶሃል? ይሖዋ ሙታንን የማስነሳት ችሎታ እንዳለውም ሆነ ይህን እንደሚያደርግ ማወቅ እንዴት የሚያጽናና ነው!
በትንሣኤ ተስፋ ማመንህ በአኗኗርህ ላይ የሚያሳድረው ተጽዕኖ
14. የትንሣኤ ተስፋ በአኗኗርህ ላይ ተጽዕኖ የሚያሳድረው እንዴት ነው?
14 የትንሣኤ ተስፋ ሕይወትህን በምትመራበት መንገድ ላይ ተጽዕኖ የሚያሳድረው እንዴት ነው? መከራ፣ ችግር፣ ስደትና አደገኛ ሁኔታ ሲገጥምህ የትንሣኤ ተስፋ ሊያበረታህ ይችላል። ሰይጣን ሞትን በጣም ከመፍራትህ የተነሳ፣ ሕይወትህን እንደምታተርፍ በሚገልጽ ከንቱ ተስፋ ተደልለህ ጽኑ አቋምህን እንድታላላ ይፈልጋል። ሰይጣን “ሰው ለሕይወቱ ሲል ያለውን ሁሉ ይሰጣል” ብሎ ለይሖዋ መናገሩን አትዘንጋ። (ኢዮብ 2:4) ሰይጣን እንዲህ በማለት የአንተን ጨምሮ የሁላችንንም ስም አጥፍቷል። አደገኛ ሁኔታ ቢያጋጥምህ አምላክን ማገልገልህን ትተዋለህ? በትንሣኤ ተስፋ ላይ በማሰላሰል የሰማዩ አባትህን ፈቃድ መፈጸምህን ለመቀጠል ባደረግከው ቁርጥ ውሳኔ መጽናት ትችላለህ።
15. በማቴዎስ 10:28 ላይ የሚገኙት የኢየሱስ ቃላት አደገኛ ሁኔታ በሚያጋጥመን ጊዜ የሚያጽናኑን እንዴት ነው?
15 ኢየሱስ እንዲህ ብሏል:- “ሥጋን መግደል እንጂ ነፍስን መግደል የማይችሉትን አትፍሩ፤ ይልቁንስ ነፍስንና ሥጋን በገሃነም ማጥፋት የሚቻለውን ፍሩ።” (ማቴዎስ ) ሰይጣንንም ሆነ ሰብዓዊ ወኪሎቹን ከልክ በላይ መፍራት የለብንም። እውነት ነው፣ አንዳንዶች እኛን ለመጉዳት ሌላው ቀርቶ ለመግደል የሚያስችል ኃይል ይኖራቸው ይሆናል። ይሁንና የሚያደርሱብን ጉዳት ምንም ያህል ቢከፋ ጊዜያዊ ነው። ይሖዋ ታማኝ አገልጋዮቹን ከሞት እንኳ በማስነሳት የደረሰባቸውን ማንኛውንም ጉዳት ማስወገድ ይችላል፤ ደግሞም ያደርገዋል። ልንፈራውና በጥልቅ ልናከብረው የሚገባው ይሖዋ ብቻ ነው። ከእርሱ በቀር ሕይወትን ሊያጠፋ ወይም ሥጋንም ሆነ ነፍስን በገሃነም በማጥፋት ትንሣኤ የማግኘት ተስፋን መንፈግ የሚችል አካል የለም። የሚያስደስተው ግን ይሖዋ እንዲህ ያለ ሁኔታ እንዲደርስብህ አይፈልግም። ( 10:282 ጴጥሮስ 3:9) የአምላክ አገልጋዮች እንደመሆናችን መጠን የትንሣኤ ተስፋ አለን። በመሆኑም ሁልጊዜም የደህንነት ስሜት ሊሰማን ይገባል። ታማኝነታችንን እስከጠበቅን ድረስ የዘላለም ሕይወት ከፊታችን ይጠብቀናል። ሰይጣንም ይሁን የእርሱ ግበረ አበሮች ይህን ሊነጥቁን አይችሉም።—መዝሙር 118:6፤ ዕብራውያን 13:6
16. ስለ ትንሣኤ ያለን አመለካከት በሕይወታችን ውስጥ ቅድሚያ በምንሰጣቸው ነገሮች ላይ ለውጥ የሚያመጣው እንዴት ነው?
16 የትንሣኤ ተስፋ እውን ከሆነልን፣ ስለ ሕይወት ባለን አመለካከት ላይ ለውጥ ያመጣል። ‘ብንኖርም ብንሞትም የጌታ [“የይሖዋ፣” NW] መሆናችንን’ እንገነዘባለን። (ሮሜ 14:7, 8) በሕይወታችን ውስጥ ቅድሚያ የምንሰጣቸውን ነገሮች በተመለከተ የሚከተለውን የጳውሎስን ምክር በተግባር እናውላለን:- “መልካም፣ ደስ የሚያሰኝና ፍጹም የሆነውን የእግዚአብሔር ፈቃድ ምን እንደ ሆነ ፈትናችሁ ታውቁ ዘንድ በአእምሮአችሁ መታደስ ተለወጡ እንጂ ይህን ዓለም አትምሰሉ።” (ሮሜ 12:2) ብዙ ሰዎች ልባቸው የተመኘውንና አእምሯቸው ያሰበውን ሁሉ ለማግኘት ሲጣደፉ ይታያሉ። ሕይወት አጭር እንደሆነ ስለሚሰማቸው በተቻላቸው መጠን ደስታና እርካታ ለማግኘት ይባክናሉ። እነዚህ ሰዎች ሃይማኖት አለን የሚሉ ከሆነም እምነታቸው ‘ፍጹም ከሆነው የአምላክ ፈቃድ’ ጋር እንደማይጣጣም ግልጽ ነው።
17, 18. (ሀ) የይሖዋ ቃል የሰው ሕይወት አጭር መሆኑን የሚገልጸው እንዴት ነው? አምላክ ለእኛ ያለው ዓላማ ምንድን ነው? (ለ) ይሖዋን በየዕለቱ ለማወደስ የምንገፋፋው ለምንድን ነው?
17 ሕይወት አጭር መሆኑ እሙን ነው። በ70 ቢበዛ በ80 ዓመታት ውስጥ ‘ቶሎ ያልፋል፤ እኛም ወዲያው እንነጕዳለን።’ (መዝሙር 90:10) የሰው ልጆች እንደ ሣር፣ ፈጥኖ እንደሚያልፍ ጥላና እንደ እስትንፋስ አላፊ ጠፊ ናቸው። (መዝሙር 103:15፤ 144:3, 4) አምላክ ከሕይወት ዘመናችን ጥቂቶቹን አሥርተ ዓመታት በማደግና የተወሰነ እውቀትና ተሞክሮ በማካበት እንድናሳልፍ፣ በተቀረው ደግሞ ወደ እርጅናና ሞት እንድናዘግም ዓላማው አይደለም። ይሖዋ የሰው ልጆችን የፈጠራቸው ለዘላለም የመኖር ፍላጎት እንዲኖራቸው አድርጎ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ ስለዚህ ሲናገር “በሰዎችም ልብ ዘላለማዊነትን አኖረ” ይላል። (መክብብ 3:11) ታዲያ ይሖዋ ይህንን ምኞት በውስጣችን ካኖረ በኋላ፣ ፍላጎታችንን ማሟላት እንዳንችል የሚያደርግ ጨካኝ አምላክ ነው? በፍጹም አይደለም። ‘አምላክ ፍቅር ስለሆነ’ እንደዚህ አያደርግም። (1 ዮሐንስ 4:8) አምላክ የሞቱ ሰዎች በትንሣኤ አማካኝነት የዘላለም ሕይወት የሚያገኙበትን አጋጣሚ ይከፍትላቸዋል።
18 የትንሣኤ ተስፋ በመኖሩ የወደፊት ሕይወታችን አስተማማኝ ሆኖልናል። ማድረግ የምንችለውን ነገር ሁሉ አሁኑኑ ማከናወን እንዳለብን በማሰብ መጨነቅ አይኖርብንም። ይህንን ያበቃለት ዓለም ሙሉ ለሙሉ ልንጠቀምበት አይገባም። (1 ቆሮንቶስ 7:29-31፤ 1 ዮሐንስ 2:17) ለይሖዋ አምላክ ታማኝ ሆነን እስከቀጠልን ድረስ እውነተኛ ተስፋ ከሌላቸው ሰዎች በተለየ መልኩ፣ እርሱን ለዘላለም የማወደስና በሕይወታችን የመደሰት ግሩም አጋጣሚ እንዳለን እናውቃለን። እንግዲያው በተቻለን መጠን የትንሣኤ ተስፋ የተረጋገጠ እንዲሆን ያደረገውን ይሖዋ አምላክን በየዕለቱ እናወድሰው!
ምን ብለህ ትመልሳለህ?
• ስለ ትንሣኤ ምን አመለካከት ሊኖረን ይገባል?
• የትንሣኤን ተስፋ እርግጠኛ የሚያደርጉት ምክንያቶች የትኞቹ ናቸው?
• ከትንሣኤ ተስፋ መጽናኛ ለማግኘት ምን ማድረግ ይኖርብናል?
• የትንሣኤ ተስፋ ሕይወታችንን በምንመራበት መንገድ ላይ ምን ለውጥ ሊያመጣ ይችላል?
[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]
[በገጽ 28 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ኢዮብ ይሖዋ ጻድቃንን ከሞት ለማስነሳት እንደሚናፍቅ ያውቅ ነበር
[በገጽ 29 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
“ልጅሽ ይኸውልሽ፤ ድኖልሻል!”