በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ዮፍታሔ ለይሖዋ የተሳለውን ፈጽሟል

ዮፍታሔ ለይሖዋ የተሳለውን ፈጽሟል

ዮፍታሔ ለይሖዋ የተሳለውን ፈጽሟል

ንድ ድል አድራጊ ተዋጊ አገሩን ከወራሪዎች ነፃ አውጥቶ ወደ ቤቱ መመለሱ ነው። በዚህ ጊዜ ሴት ልጁ በደስታ እየጨፈረችና አታሞ እየመታች ልትቀበለው ወጣች። አባቷ ሲያያት ከመደሰት ይልቅ በሐዘን ልብሱን ቀደደ። ይህን ያደረገው ለምንድን ነው? በሰላም ወደ ቤቱ መመለሱ ልክ እንደ እርሷ ሊያስደስተው አይገባም ነበር? ድል ያደረገው በየትኛው ጦርነት ነው? ይህ ሰው ማን ነው?

ይህ ሰው ከጥንቷ እስራኤል መሳፍንት መካከል አንዱ የሆነው ዮፍታሔ ነው። ይሁንና ለተቀሩት ጥያቄዎች መልስ ለማግኘትና ታሪኩ ለእኛ ምን ትምህርት እንደያዘ ለመረዳት፣ ዮፍታሔና ልጁ በዚህ ሁኔታ ከመገናኘታቸው በፊት የተከሰቱትን ነገሮች እንመርምር።

በእስራኤል የነበረ አስቸጋሪ ሁኔታ

ዮፍታሔ የኖረው በአስቸጋሪ ዘመን ነው። ወገኖቹ የሆኑት እስራኤላውያን ንጹሑን አምልኮ ትተው የሲዶናን፣ የሞዓብን፣ የአሞንንና የፍልስጥኤማውያንን አማልክት ያመልኩ ነበር። በመሆኑም ይሖዋ ሕዝቡን ለ18 ዓመት በጭቆና ለገዟቸው ለአሞናውያንና ለፍልስጥኤማውያን አሳልፎ ሰጣቸው። በዚህ ወቅት በተለይም ከዮርዳኖስ ወንዝ በስተ ምሥራቅ የሚኖሩት የገለዓድ ምድር ነዋሪዎች ብዙ መከራ ደርሶባቸዋል። a በመጨረሻም እስራኤላውያን ወደ ልቦናቸው ተመልሰው ንስሐ በመግባት የይሖዋን እርዳታ ጠየቁ። እንዲሁም ባዕድ አማልክትን ከመካከላቸው በማስወገድ ይሖዋን ማምለክ ጀመሩ።—መሳፍንት 10:6-16

አሞናውያን ሠራዊታቸውን በገለዓድ አሰፈሩ፤ እስራኤላውያንም ሊገጥሟቸው ተሰበሰቡ። ሆኖም ግን እስራኤላውያን የጦር አዛዥ አልነበራቸውም። (መሳፍንት 10:17, 18) በዚህ ወቅት ዮፍታሔ የራሱ ችግሮች ነበሩት። ስስታም የሆኑት የአባቱ ልጆች ውርሱን ለመንጠቅ በማሰብ ስላባረሩት ጦብ ወደተባለ ምድር መጥቶ መኖር ጀመረ። ይህ አካባቢ ከገለዓድ በስተ ምሥራቅ የሚገኝ ሲሆን ለእስራኤል ጠላቶች ጥቃት የተጋለጠ ነበር። በኋላም፣ ጨቋኞቻቸው ከሥራ ያባረሯቸው ወይም በደረሰባቸው በደል ምክንያት ያመጹ አንዳንድ “ወሮበሎች” ወደ ዮፍታሔ ተሰባስበው ‘ይከተሉት’ ጀመር። ዮፍታሔን ‘ተከተሉት’ የተባለው ክፉ ጎረቤቶቻቸውን ለመዝረፍ በሚሄድበት ጊዜ አብረውት ይሄዱ እንደነበር ለማመልከት ሊሆን ይችላል። ዮፍታሔ ጎበዝ ተዋጊ በመሆኑ ሳይሆን አይቀርም ቅዱሳን መጻሕፍት “ኀያል ጦረኛ” በማለት ይጠሩታል። (መሳፍንት 11:1-3) ታዲያ ከአሞናውያን ጋር በሚያደርጉት ውጊያ እስራኤላውያንን ማን ይመራቸው ይሆን?

“መጥተህ ምራን

የገለዓድ አለቆች ዮፍታሔን “መጥተህ ምራን” በማለት ተማጸኑት። እነዚህ ሰዎች ዮፍታሔ ወዲያውኑ እሺ ብሎ ወደ አገሩ ይመለሳል ብለው ከጠበቁ ተሳስተዋል። ዮፍታሔ “ምነው ጠልታችሁኝ ከአባቴ ቤት አሳዳችሁኝ አልነበረምን? ታዲያ አሁን ችግር ሲገጥማችሁ ነው የምትፈልጉኝ?” ሲል ጠየቃቸው። እነዚህ ሰዎች ዮፍታሔን በማባረር ፍትሕ የጎደለው ድርጊት ከፈጸሙ በኋላ አሁን የእርሱን እርዳታ ለመጠየቅ መምጣታቸው እንዴት የሚያሳፍር ነው!—መሳፍንት 11:4-7

ዮፍታሔ ገለዓድን የሚመራው የጠየቃቸውን ነገር ከፈጸሙለት ብቻ ነው። ዮፍታሔ፣ ይሖዋ ‘አሞናውያንን በእጄ አሳልፎ ቢሰጣቸው በእርግጥ አለቃችሁ እሆናለሁ’ አላቸው። ድል ማድረጋቸው የአምላክ ድጋፍ እንዳላቸው የሚያረጋግጥ ቢሆንም ዮፍታሔ ሕዝቡ ችግሩ ካለፈ በኋላም ይሖዋን እንደማይተዉ ቃል እንዲገቡለት ፈልጎ ነበር።—መሳፍንት 11:8-11

ዮፍታሔ ከአሞናውያን ጋር የነበረው ግንኙነት

ዮፍታሔ ከአሞናውያን ጋር ለመደራደር ሞከረ። አሞናውያን እስራኤላውያንን ለማጥቃት የተነሱበትን ምክንያት እንዲያጣሩ መልእክተኞችን ወደ ንጉሣቸው ላከ። የአሞናውያን ንጉሥም፣ እስራኤላውያን ከግብፅ በወጡ ጊዜ የአሞናውያንን መሬት ስለወሰዱ ሊመልሱልን ይገባል በማለት ክስ ያዘለ መልእክት ላከ።—መሳፍንት 11:12, 13

ዮፍታሔ የእስራኤልን ታሪክ አሳምሮ ያውቅ ስለነበር የአሞናውያን ክስ ትክክል አለመሆኑን በዘዴ አስረዳ። እስራኤላውያን ግብፅን ለቅቀው በወጡ ጊዜ አሞንን፣ ሞአብን ወይም ኤዶምን እንዳልበደሉ ነገራቸው። በተጨማሪም ተወስዶብናል የሚሉት መሬት እስራኤላውያን ወደ ተስፋይቱ ምድር በተጓዙበት ወቅት በአሞናውያን ይዞታ ሥር አልነበረም። በወቅቱ መሬቱን ይዘውት የነበሩት አሞራውያን ሲሆኑ አምላክ ሴዎን የተባለውን ንጉሣቸውን ለእስራኤላውያን አሳልፎ ሰጥቷቸዋል። ከዚህም በላይ እስራኤላውያን በዚህ አካባቢ ለ300 ዓመታት ኖረዋል። ታዲያ አሞናውያን ይህን ጥያቄ አሁን ያነሱት ለምንድን ነው?—መሳፍንት 11:14-22, 26

በተጨማሪም ዮፍታሔ ለእስራኤላውያን መከራ ዋነኛ ምክንያት በሆነው ጉዳይ ላይ አተኩሯል። እውነተኛው አምላክ ማን ነው? ይሖዋ ነው ወይስ እስራኤላውያን በያዙት ምድር ላይ የነበሩት አማልክት? ካሞሽ ኃይል ቢኖረው ኖሮ ምድራቸው እንዳይወሰድ ማድረግ አይችልም ነበር? ይህ አጋጣሚ አሞናውያን ከሚከተሉት የሐሰት ሃይማኖትና ከእውነተኛው አምልኮ ድል የሚያደርገው የትኛው እንደሆነ የሚታይበት ነበር። በመሆኑም ዮፍታሔ “ፈራጁ እግዚአብሔር በእስራኤላውያንና በአሞናውያን መካከል ዛሬ ይፍረድ” ሲል ሐሳቡን ቋጨ።—መሳፍንት 11:23-27

ሆኖም የአሞን ንጉሥ የዮፍታሔን ቁርጥ ያለ መልስ ለመስማት ፈቃደኛ አልሆነም። በዚህ ጊዜ “የእግዚአብሔር መንፈስ በዮፍታሔ ላይ ወረደ”፤ ከዚያም ለጦርነት የሚሆኑ ወንዶችን ለመመልመል ሳይሆን አይቀርም “ገለዓድንና ምናሴን አቋርጦ ሄደ።”—መሳፍንት 11:28, 29

የዮፍታሔ ስእለት

ዮፍታሔ መለኮታዊ መመሪያ ለማግኘት ካለው ከፍተኛ ጉጉት የተነሳ እንደሚከተለው ሲል ለይሖዋ ተሳለ:- “አሞናውያንን በእጄ አሳልፈህ ብትሰጠኝ፣ አሞናውያንን ድል አድርጌ በምመለስበት ጊዜ በመጀመሪያ ሊቀበለኝ ከቤቴ ደጅ የሚወጣው ማንኛውም ሰው ለእግዚአብሔር ይሆናል፤ እኔም የሚቃጠል መሥዋዕት አድርጌ አቀርበዋለሁ።” በምላሹም አምላክ ዮፍታሔን 20 የአሞናውያንን ከተሞች ‘ፈጽሞ እንዲያጠፋና’ የእስራኤልን ጠላቶች እንዲያንበረክክ በማድረግ ባረከው።—መሳፍንት 11:30-33

ዮፍታሔ ከጦርነት ሲመለስ ልትቀበለው የወጣችው በጣም የሚወዳት አንድ ልጁ ነበረች! ዘገባው እንዲህ ይላል:- “ባያትም ጊዜ ልብሱን በመቅደድ፣ ‘ወይኔ ልጄ ጕድ አደረግሽኝ! ጭንቅም ላይ ጣልሺኝ፤ ማስቀረት የማልችለውን ስእለት ለእግዚአብሔር ተስያለሁና’ ብሎ በኀዘን ጮኸ።”—መሳፍንት 11:34, 35

በእርግጥ ዮፍታሔ ልጁን መሥዋዕት ያደርጋታል? በፍጹም። ዮፍታሔ ያሰበው ይህን ሊሆን አይችልም። ይሖዋ የከነዓናውያን ርኩስ ልማድ የነበረውን ቃል በቃል ሰውን መሥዋዕት ማድረግን ይጸየፋል። (ዘሌዋውያን 18:21፤ ዘዳግም 12:31) ዮፍታሔ ለአምላክ በተሳለ ጊዜ የይሖዋ መንፈስ የወረደበት ከመሆኑም በላይ ይሖዋ ጥረቱን ሁሉ ባርኮለታል። ዮፍታሔ ባሳየው እምነትና በአምላክ ዓላማ ውስጥ በተጫወተው ሚና በቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ ተመስግኗል። (1 ሳሙኤል 12:11፤ ዕብራውያን 11:32-34) በመሆኑም ዮፍታሔ ሰውን መሥዋዕት ማድረግ ማለትም መግደል ፈጽሞ የሚያስበው ነገር አይደለም። ታዲያ ዮፍታሔ ሊቀበለው የሚወጣውን ሰው ለይሖዋ መሥዋዕት አድርጎ ለማቅረብ ሲሳል ምን ማለቱ ነበር?

ዮፍታሔ መጀመሪያ የተቀበለውን ሰው ለአምላክ አገልግሎት ሙሉ በሙሉ የተወሰነ እንዲሆን ለመስጠት ቃል መግባቱ እንደሆነ እሙን ነው። የሙሴ ሕግ አንድን ሰው ለይሖዋ ለመስጠት መሳል ይቻል እንደነበር ይጠቁማል። ለምሳሌ ያህል ሴቶች ውኃ በመቅዳት ሳይሆን አይቀርም በመገናኛው ድንኳን ያገለግሉ ነበር። (ዘፀአት 38:8፤ 1 ሳሙኤል 2:22) እንደዚህ ስለመሰለው አገልግሎትም ይሁን በቋሚነት የሚደረግ ስለመሆኑ ብዙም የሚታወቅ ነገር የለም። ዮፍታሔ ስእለቱን የተሳለው ይህን መሰሉን ልዩ አገልግሎት በአእምሮው ይዞ ሊሆን ይችላል፤ ከዚህም ባሻገር ስእለት ሆኖ የሚቀርበው ግለሰብ ዕድሜውን በሙሉ ይህን አገልግሎት እንደሚያከናውን አስቦ የነበረ ይመስላል።

የዮፍታሔ ልጅም ሆነች በኋላ ላይ ሕፃኑ ሳሙኤል ፈሪሃ አምላክ ያላቸው ወላጆቻቸው የተሳሉትን ስእለት ለመፈጸም ፈቃደኞች ሆነዋል። (1 ሳሙኤል 1:11) ታማኝ የይሖዋ አምላኪ እንደመሆኗ መጠን የዮፍታሔ ልጅ ልክ እንደ አባቷ ስእለቱ ሊፈጸም እንደሚገባ ተሰምቷታል። ሕይወቷን በሙሉ ባል ስለማታገባ የምትከፍለው መሥዋዕትነት ቀላል አይደለም። ማንኛውም እስራኤላዊ ልጅ ወልዶ የቤተሰቡን ስም የማስጠራትና ርስት የማቆየት ጉጉት ስለነበረው ለድንግልናዋ ወይም ባል ባለማግባቷ አለቀሰች። ለዮፍታሔ ደግሞ ቃሉን መጠበቅ ማለት፣ ከሚወዳት አንድ ልጁ መለየት ማለት ነው።—መሳፍንት 11:36-39

የዚህች ታማኝ ልጃገረድ ሕይወት ከንቱ ሆኖ አልቀረም። በይሖዋ ቤት ሙሉ ጊዜ ማገልገል፣ አምላክን ለማክበር የሚያስችል ግሩምና አስደሳች አጋጣሚ የሚከፍትላት ከመሆኑም ባሻገር የሚያስመሰግናት ነበር። በመሆኑም “የእስራኤል ወጣት ሴቶች የገለዓዳዊውን የዮፍታሔን ልጅ በማሰብ በየዓመቱ እየወጡ የአራት ቀን ኀዘን ያደርጉላታል [‘ለአራት ቀን ያመሰግኗታል፣’ የ1879 ትርጉም]።” (መሳፍንት 11:40) ዮፍታሔም ቢሆን ይሖዋን በማገልገሏ እንደተደሰተ ምንም ጥርጥር የለውም።

በዛሬው ጊዜ ከሚገኙት የአምላክ ሕዝቦች መካከል ብዙዎች አቅኚዎች፣ ሚስዮናውያን፣ ተጓዥ የበላይ ተመልካቾች ወይም የቤቴል ቤተሰብ አባላት በመሆን ሕይወታቸውን በሙሉ ጊዜ አገልግሎት ለማሳለፍ መርጠዋል። በዚህም ምክንያት ከቤተሰቦቻቸው ጋር እንደልብ መገናኘት አይችሉ ይሆናል። ያም ሆኖ ለይሖዋ ቅዱስ አገልግሎት ማቅረባቸው እነርሱንም ሆነ ቤተሰቦቻቸውን ያስደስታል።—መዝሙር 110:3፤ ዕብራውያን 13:15, 16

በመለኮታዊ መመሪያ ላይ ማመጽ

ዮፍታሔ ስለኖረበት ዘመን መለስ ብለን ስናስብ ብዙ እስራኤላውያን የይሖዋን መመሪያ ለመቀበል አሻፈረኝ ብለው እንደነበር እናስተውላለን። ዮፍታሔ መለኮታዊ ድጋፍ እንዳገኘ የሚያሳዩ ማስረጃዎች ቢኖሩም እንኳ ኤፍሬማውያን ለጠብ ተጋብዘዋል። ለጦርነት ሲወጣ ያልጠራቸው ለምን እንደሆነ ማወቅ ፈልገው ነበር። እንዲያውም ቤቱን ‘በላዩ ላይ’ ለማቃጠል አስበው ነበር!—መሳፍንት 12:1

ዮፍታሔም ኤፍሬማውያንን እንደጠራቸው እነርሱ ግን ምላሽ እንዳልሰጡት ነገራቸው። ያም ሆነ ይህ አምላክ ድል ተቀዳጅቷል። የኤፍሬም ሰዎች የተቆጡት የገለዓድ ሰዎች ዮፍታሔን መሪያቸው እንዲሆን ሲመርጡት ስላላማከሯቸው ይሆን? እንደ እውነቱ ከሆነ የኤፍሬማውያን ተቃውሞ በይሖዋ ላይ ማመጻቸውን የሚያሳይ ነበር፤ በመሆኑም ከእነርሱ ጋር ከመዋጋት በቀር ሌላ አማራጭ አልነበረም። በውጊያውም የኤፍሬም ሰዎች ተሸነፉ። በሽሽት ላይ የነበሩት ኤፍሬማውያን “ሺቦሌት” የሚለውን ቃል በትክክል መጥራት ባለመቻላቸው ማንነታቸው በቀላሉ ይታወቅ ነበር። በዚህ ግጭት ምክንያት በአጠቃላይ 42,000 ኤፍሬማውያን ሞቱ።—መሳፍንት 12:2-6

ይህ በእስራኤል ታሪክ ውስጥ እንዴት የሚያሳዝን ጊዜ ነበር! ጎቶንያል፣ ናዖድ፣ ባርቅና ጌዴዎን የተባሉት መሳፍንት ያገኟቸው ድሎች ለእስራኤል ሰላም አስገኝተዋል። በዚህ ጊዜ ግን ሰላም ስለመገኘቱ የተጠቀሰ ነገር የለም። ዘገባው እንዲህ በማለት ይደመድማል:- “ዮፍታሔ በእስራኤል ላይ ለስድስት ዓመት ፈራጅ ሆነ። ገለዓዳዊው ዮፍታሔ ሞተ፤ ከገለዓድም ከተሞች በአንዲቱ ተቀበረ።”—መሳፍንት 3:11, 30፤ 5:31፤ 8:28፤ 12:7

ከዚህ ምን እንማራለን? የዮፍታሔ ሕይወት በችግር የተሞላ ቢሆንም ለአምላክ ታማኝ ነበር። ይህ ኃያል ሰው ከገለዓድ አለቆች፣ ከአሞናውያን፣ ከልጁና ከኤፍሬማውያን ጋር ሲነጋገር እንዲሁም ስእለቱን በተሳለ ጊዜ ስለ ይሖዋ ተናግሯል። (መሳፍንት 11:9, 23, 27, 30, 31, 35፤ 12:3) አምላክ እርሱንም ሆነ ልጁን ንጹሑን አምልኮ እንዲያስፋፉ የተጠቀመባቸው መሆኑ፣ ዮፍታሔ ላሳየው ለይሖዋ የማደር ባሕርይ ወሮታ እንደተከፈለው ያሳያል። ሌሎች የአምላክን የአቋም ደረጃዎች ችላ ባሉበት ጊዜ ዮፍታሔ የይሖዋን መመሪያዎች በጥብቅ ተከትሏል። ልክ እንደ ዮፍታሔ ዘወትር ይሖዋን ትታዘዛለህ?

[የግርጌ ማስታወሻ]

a አሞናውያን አረመኔያዊ ድርጊት ከመፈጸም ወደኋላ የሚሉ አልነበሩም። ከ60 ዓመት ገደማ በኋላ እንኳ በገለዓድ ከተሞች የሚኖሩትን ሰዎች ቀኝ ዓይን እንደሚያወጡ ዝተው እንደነበር ተዘግቧል። ነቢዩ አሞጽ አሞናውያን የገለዓድን ነፍሰ ጡር ሴቶች ሆድ የቀደዱበት ጊዜ እንደነበር ተናግሯል።—1 ሳሙኤል 11:2፤ አሞጽ 1:13