“ጌታ ሆይ፣ ምነው ዝም አልህ?”
“ጌታ ሆይ፣ ምነው ዝም አልህ?”
ይህን ጥያቄ ያነሱት ሊቀ ጳጳስ ቤነዲክት አሥራ ስድስተኛ ሲሆኑ ግንቦት 28, 2006 ኦሽዊትዝ፣ ፖላንድ የሚገኘውን የቀድሞ የማጎሪያ ካምፕ በጎበኙበት ወቅት የተሰማቸውን ስሜት የሚያንጸባርቅ ነው። ናዚዎች በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ አይሁዳውያንንና ሌሎች ሰዎችን በጨፈጨፉበት በዚህ ቦታ ሊቀ ጳጳሱ አክለው እንዲህ ብለዋል:- “እዚህ ቦታ በርካታ ጥያቄዎች ይነሳሉ! ብዙውን ጊዜ ‘በዚያን ጊዜ አምላክ የት ነበር? ለምንስ ዝም አለ? ሰዎች ያለ ምንም ገደብ እርስ በርስ እንዲተራረዱና ክፋት እንዲህ እንዲነግሥ ለምን ፈቀደ?’ እንደሚሉት ያሉ ጥያቄዎች ይነሳሉ። . . . ‘አንድ እርምጃ ውሰድ! ፍጥረትህ የሆነውን የሰው ዘር አትርሳ!’ እያልን ወደ አምላክ በትሕትና ሆኖም ያለ ማቋረጥ መጮሃችንን መቀጠል ይኖርብናል።”
የጳጳሱ ንግግር የተለያዩ አስተያየቶችን አስነስቷል። አንዳንዶች ጳጳሱ የተወሰኑ ርዕሰ ጉዳዮችን ላለማንሳት እንደመረጡ ተሰምቷቸዋል። ለምሳሌ በኦሽዊትዝ ለተፈጸመው ግፍ ምክንያት የሆነውን ፀረ-ሴማዊነት መጥቀስ እንዳልፈለጉ አስተውለዋል። ሌሎች ደግሞ ንግግራቸው ጳጳስ ዳግማዊ ጆን ፖል ቤተ ክርስቲያኗ ስለፈጸመችው ኃጢአት ይቅርታ መጠየቃቸው ያን ያህል አስፈላጊ አይደለም የሚል አንድምታ እንዳለው ተሰምቷቸዋል። ፊሊፖ ጄንቴሎኒ የተባለ አንድ የካቶሊክ ጋዜጠኛ እንዲህ ሲል ገልጿል:- “ብዙ ተንታኞች ‘አምላክ የት ነበር?’ የሚለው ፈጽሞ መልስ የሌለው ከባድ ጥያቄ ሲነሳባቸው ‘ፓየስ አሥራ ሁለተኛስ የት ነበሩ?’ የሚለውን ጥያቄ መልሰው መጠየቃቸው የተገባ ነው።” ተንታኞቹ ይህን ሲሉ ‘ሊቀ ጳጳስ ፓየስ አሥራ ሁለተኛ ሆሎኮስት ተብሎ በሚጠራው የናዚ እልቂት ወቅት ዝምታን የመረጡት ለምን ነበር?’ ማለታቸው ነው።
ሆሎኮስትን ጨምሮ በሰው ዘር ታሪክ ውስጥ የተፈጸሙት ሌሎች የዘር ማጥፋት ድርጊቶች “ሰው ሰውን ለመጕዳት ገዥ” እንደሆነ አረጋግጠዋል። (መክብብ 8:9) ከዚህም በላይ የሰው ልጆች ፈጣሪ እንዲህ ዓይነት የጭካኔ ድርጊቶች በተፈጸሙበት ወቅት ዝምታን አልመረጠም። ከዚህ ይልቅ ክፋት እንዲኖር የፈቀደበትን ምክንያት በመጽሐፍ ቅዱስ አማካኝነት በግልጽ ተናግሯል፤ በተጨማሪም ሰዎችን እንዳልረሳ ማረጋገጫ ሰጥቶናል። እንዲያውም አምላክ ሰዎች ራሳቸውን በራሳቸው እንዲያስተዳድሩ የፈቀደላቸው ጊዜ በቅርቡ ያበቃል። (ኤርምያስ 10:23) አምላክ ለእኛ ስላለው ዓላማ ይበልጥ ማወቅ ይፈልጋሉ? የይሖዋ ምሥክሮች፣ ሊቀ ጳጳስ ቤነዲክት አሥራ ስድስተኛን ግራ ያጋቧቸውን ጥያቄዎች አስመልክቶ መጽሐፍ ቅዱስ የሚሰጠውን መልስ ሊያብራሩልዎት ፈቃደኞች ናቸው።
[በገጽ 32 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
Oświęcim Museum