በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ምላስ ያለው ኃይል

ምላስ ያለው ኃይል

ምላስ ያለው ኃይል

የቀጭኔ ምላስ እስከ 45 ሴንቲ ሜትር የሚደርስ ርዝመት ያለው ሲሆን ቀልጣፋና በዛፍ ቅርንጫፎች ላይ የሚገኙትን ቅጠሎች ለመበጠስ የሚያስችል ኃይል ያለው ነው። ብሉ ዌል የተባለው ዓሣ ነባሪ ምላስ የአንድ ዝሆን ያህል ክብደት አለው። ይህን ምላስ ለማንቀሳቀስ ብቻ እንኳ ምን ያህል ኃይል እንደሚያስፈልግ መገመት ትችላለህ!

የሰው ምላስ በመጠን፣ በክብደትም ሆነ በጥንካሬ ከእነዚህ እንስሳት ጋር ሲወዳደር እዚህ ግባ የሚባል አይደለም። ይሁንና ከእነዚህ እንስሳት የበለጠ ኃይል አለው። መጽሐፍ ቅዱስ ከሰውነታችን ክፍሎች ውስጥ በመጠን ትንሽ የሆነውን ምላስን አስመልክቶ ሲናገር “ሞትና ሕይወት በምላስ እጅ ናቸው” ብሏል። (ምሳሌ 18:21 የ1954 ትርጉም) በእርግጥም ምላስ ውሸት በመፍጠርና የሐሰት ምሥክርነት በመስጠት ንጹሕ ሰዎች እንዲጎዱ ምናልባትም እንዲሞቱ በማድረግ ስላለው የመግደል ኃይል ስንት ጊዜ ሰምተናል?

በተመሳሳይም ለብዙ ዓመታት የዘለቀ ጓደኝነት ጎጂ በሆነ ንግግር የተነሳ ይቋረጣል። እንዲሁም ስሜታችን በሸካራ ቃላት ምክንያት ይጎዳል። በጓደኞቹ አነጋገር በእጅጉ የተጎዳው ኢዮብ “ነፍሴን የምታስጨንቋት፣ በቃልስ የምትደቍሱኝ እስከ መቼ ነው?” በማለት በምሬት ተናግሯል። (ኢዮብ 19:2) ደቀ መዝሙሩ ያዕቆብ “ምላስ ትንሽ የሰውነት ክፍል ሆና ሳለ በታላላቅ ነገሮች ትኩራራለች፤ ትልቅ ጫካ በትንሽ እሳት እንዴት ተቃጥሎ እንደሚጠፋ አስተውሉ፤ ምላስም እንደ እሳት ናት” በማለት የተናገራቸው ቃላት ያልተገታ ምላስ ምን ያህል የመጉዳት ኃይል እንዳለው ቁልጭ አድርገው የሚያሳዩ ናቸው።—ያዕቆብ 3:5, 6

በሌላ በኩል ግን ምላስ ያለው ኃይል ሕይወት ሰጪ ሊሆንም ይችላል። የሌሎችን ችግር የሚረዱ አንዳንድ ሰዎች የተናገሯቸው አጽናኝ ቃላት ሰዎችን ከጭንቀትና የራሳቸውን ሕይወት ከማጥፋት ታድገዋቸዋል። ሰሚ ጆሮ ያገኙ ጠቃሚ ምክሮች የዕፅ ሱሰኞችና ጨካኝ ወንጀለኞች የነበሩ በርካታ ሰዎችን ያለ ዕድሜያቸው ከመቀጨት አድነዋቸዋል። በእርግጥም የጻድቅ ሰው ምላስ “የሕይወት ዛፍ ናት፤” እንዲሁም “ባግባቡ የተነገረ ቃል፣ በብር መደብ ላይ እንደ ተቀረጸ የወርቅ እንኮይ ነው።”—ምሳሌ 15:4፤ 25:11

ይሁን እንጂ ምላሳችንን ከሁሉ በተሻለ መንገድ የምንጠቀመው የአምላክን መንግሥት ምሥራች በመስበክና በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙትን ውድ እውነቶች ለሌሎች በማስተማር ይሖዋ አምላክን ስናወድስበት ነው። እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው? ምክንያቱም ኢየሱስ “እውነተኛ አምላክ የሆንኸውን አንተንና የላክኸውንም ኢየሱስ ክርስቶስን ያውቁ ዘንድ ይህች የዘላለም ሕይወት ናት” ብሏል።—ዮሐንስ 17:3፤ ማቴዎስ 24:14፤ 28:19, 20