በእርጅና ዘመን በመንፈሳዊ ማፍራት
በእርጅና ዘመን በመንፈሳዊ ማፍራት
‘በይሖዋ ቤት ተተክለዋል፤ ባረጁ ጊዜ እንኳ ያፈራሉ።’ —መዝሙር 92:13, 14
1, 2. (ሀ) አብዛኛውን ጊዜ የዕድሜ መግፋት እንዴት ይገለጻል? (ለ) ቅዱሳን መጻሕፍት፣ የአዳም ኃጢአት ያስከተላቸውን ውጤቶች በተመለከተ ምን ተስፋ ይሰጣሉ?
እርጅና ሲባል ወደ አእምሮህ የሚመጣው ምንድን ነው? የተሸበሸበ ቆዳ፣ የመስማት ችሎታ መድከም ወይም አቅም ማጣት? ወይስ በመክብብ 12:1-7 ላይ በዝርዝር የተገለጸው “የጭንቀት ጊዜ” ሌሎች ገጽታዎች ናቸው? እነዚህን ነገሮች የምታስብ ከሆነ በመክብብ ምዕራፍ 12 ላይ የሚገኘው መግለጫ የዕድሜ መግፋትና እርጅና፣ ፈጣሪያችን ይሖዋ አምላክ መጀመሪያ ለሰው ዘር ያሰባቸው ነገሮች አለመሆናቸውን እንደሚያመለክት መገንዘብ ያስፈልግሃል፤ እነዚህ ለውጦች በሰዎች አካል ላይ የሚከሰቱት በአዳም ኃጢአት ምክንያት ነው።—ሮሜ 5:12
2 የዕድሜ መግፋት በራሱ እርግማን አይደለም፤ ምክንያቱም ለረዥም ጊዜ ለመኖር ዓመታት ማለፋቸው የግድ ነው። እንዲያውም ሕይወት ያላቸው ነገሮች በሙሉ እንዲያድጉና ወደ ጉልምስና እንዲደርሱ ይፈለጋል። በቅርቡ ደግሞ ኃጢአትና አለፍጽምና ለስድስት ሺህ ዓመታት በዓለም ላይ ያደረሱት ጥፋት ይስተካከላል፤ እንዲሁም እርጅናም ሆነ ሞት ተወግደው ታዛዥ የሆኑ የሰው ልጆች በሙሉ አምላክ መጀመሪያ እንዳሰበው በደስታ ይኖራሉ። (ዘፍጥረት 1:28፤ ራእይ 21:4, 5) በዚያን ጊዜ “‘ታምሜአለሁ’ የሚል አይኖርም።” (ኢሳይያስ 33:24) አረጋውያን ‘ወደ ወጣትነት’ የሚመለሱ ሲሆን ሥጋቸውም “እንደ ሕፃን ልጅ ገላ ይታደሳል።” (ኢዮብ 33:25) በአሁኑ ዘመን ግን ሁሉም ሰው የአዳም ኃጢአት ካስከተላቸው ውጤቶች ጋር መታገል አለበት። ያም ሆኖ የይሖዋ አገልጋዮች ዕድሜያቸው እየገፋ ሲሄድ ለየት ባሉ መንገዶች በረከት ያገኛሉ።
3. ክርስቲያኖች ‘ባረጁ ጊዜ እንኳ የሚያፈሩት’ በምን መንገዶች ነው?
3 የአምላክ ቃል፣ የይሖዋ አገልጋዮችን በተመለከተ “በእግዚአብሔር ቤት ተተክለዋል፤ . . . ባረጁ ጊዜ እንኳ ያፈራሉ” የሚል ማረጋገጫ ሰጥቶናል። (መዝሙር 92:13, 14) መዝሙራዊው፣ ታማኝ የሆኑ የአምላክ አገልጋዮች በአካላዊ ሁኔታ ቢያረጁም በመንፈሳዊ ሁኔታ እድገት ማድረጋቸውንና ፍሬ ማፍራታቸውን እንደሚቀጥሉ በመግለጽ መሠረታዊ የሆነውን ሐቅ በምሳሌያዊ አነጋገር አስቀምጦታል። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተገለጹም ሆነ በዘመናችን ያሉ በርካታ ምሳሌዎች ይህ እውነት እንደሆነ አረጋግጠዋል።
“ከቤተ መቅደስ ሳትለይ”
4. አረጋዊቷ ነቢይት ሐና ለአምላክ ያደረች መሆኗን ያሳየችው እንዴት ነበር? እንዲህ በማድረጓስ የተባረከችው እንዴት ነው?
4 ታማኝ ነቢይት የነበረችውን ሐናን እንመልከት። ሐና በ84 ዓመቷ “ቀንና ሌሊት ከቤተ መቅደስ ሳትለይ፣ በጾምና በጸሎት [ታገለግል]” ነበር። የሐና አባት “ከአሴር ወገን” በመሆኑ እንደ ሌዋውያን በቤተ መቅደሱ ውስጥ መኖር አትችልም ነበር። በመሆኑም ሐና በማለዳ ከሚቀርበው መሥዋዕት ጀምሮ በምሽት እስከሚቀርበው መሥዋዕት ድረስ በቤተ መቅደሱ ውስጥ በየዕለቱ ለመገኘት ምን ያህል ጥረት ጠይቆባት እንደሚሆን መገመት ትችላለህ! ሆኖም ሐና ለአምላክ ያደረች በመሆኗ የተትረፈረፈ በረከት አጭዳለች። ዮሴፍና ማርያም በሕጉ መሠረት ሕፃኑን ኢየሱስን ለይሖዋ ለማቅረብ ወደ ቤተ መቅደሱ ይዘውት ሲመጡ በዚያ የመገኘት መብት አግኝታለች። ሐና ኢየሱስን ስታየው “እግዚአብሔርን አመሰገነች፤ የኢየሩሳሌምንም መቤዠት ለሚጠባበቁ ሁሉ ስለ ሕፃኑ ተናገረች።”—ሉቃስ 2:22-24, 36-38፤ ዘኍልቍ 18:6, 7
5, 6. በዛሬው ጊዜ የሚገኙ በዕድሜ የገፉ በርካታ ክርስቲያኖች እንደ ሐና ዓይነት መንፈስ ያሳዩት በምን መንገዶች ነው?
5 በዛሬው ጊዜም በመካከላችን የሚገኙ በርካታ አረጋውያን እንደ ሐና አዘውትረው በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ የሚገኙ ከመሆኑም በላይ እውነተኛው አምልኮ እንዲስፋፋ ልባዊ ምልጃ ያቀርባሉ፤ እንዲሁም ምሥራቹን ለመስበክ ከፍተኛ ፍላጎት አላቸው። በ80ዎቹ ዕድሜ ውስጥ የሚገኙና ከባለቤታቸው ጋር አዘውትረው በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ የሚገኙ አንድ ወንድም እንዲህ ብለዋል:- “ወደ ስብሰባዎች የመሄድ ልማድ አዳብረናል። ሌላ የትም ቦታ መሆን አንፈልግም። የአምላክ ሕዝቦች ባሉበት ቦታ መገኘት እንፈልጋለን። እዚያ ስንሆን ደስ ይለናል።” ሁላችንንም የሚያበረታታ እንዴት ያለ ግሩም ምሳሌ ነው!—ዕብራውያን 10:24, 25
6 በ80ዎቹ ዕድሜ ውስጥ የሚገኙት ጂን የተባሉ አንዲት ክርስቲያን መበለት እንዲህ የሚል መርህ አላቸው:- “ከእውነተኛው አምልኮ ጋር የተያያዘ ማንኛውንም ነገር፣ ላደርገው የምችለው እስከሆነ ድረስ ማድረግ እፈልጋለሁ።” አክለውም “የማዝንባቸው ጊዜያት እንዳሉ አልክድም። ሆኖም እኔ ሳዝን አብረውኝ ያሉትም እንዲያዝኑ ለምን አደርጋለሁ?” በማለት ተናግረዋል። እኚህ እህት በሚያንጹ መንፈሳዊ ዝግጅቶች ላይ ለመገኘት ወደ ሌሎች አገሮች በመሄዳቸው ምን እንደተሰማቸው ሲገልጹ ደስታቸው በፊታቸው ላይ ይነበባል። በቅርቡ ባደረጉት ጉዞ ላይ አብረዋቸው የሚጓዙትን ሰዎች “ከዚህ በኋላ ሌላ ታሪካዊ ቦታ ማየት አልፈልግም፤ ማገልገል እፈልጋለሁ!” ብለዋቸው ነበር። እህት ጂን በአካባቢው የሚነገረውን ቋንቋ መናገር ባይችሉም ሰዎች ለመጽሐፍ ቅዱስ መልእክት ፍላጎት እንዲያድርባቸው ረድተዋል። ከዚህም በተጨማሪ እርዳታ በሚያስፈልገው አንድ ጉባኤ ውስጥ ለማገልገል ሲሉ አዲስ ቋንቋ መማርና ወደ ስብሰባዎች ደርሰው ለመመለስ ለሁለት ሰዓታት መጓዝ ያለባቸው ቢሆንም እንኳ ለብዙ ዓመታት እንዲህ አድርገዋል።
አእምሮን በሥራ ማስጠመድ
7. ሙሴ ዕድሜው ከገፋም በኋላ ከአምላክ ጋር ያለውን ዝምድና ለማጠናከር እንደሚፈልግ የገለጸው እንዴት ነበር?
7 የሕይወት ተሞክሮ የሚገኘው በጊዜ ሂደት ነው። (ኢዮብ 12:12) በሌላ በኩል ግን መንፈሳዊ ጉልምስና ሁልጊዜ ከዕድሜ ጋር ይመጣል ማለት አይደለም። በመሆኑም የአምላክ ታማኝ አገልጋዮች ቀደም ሲል ባከማቹት እውቀት ረክተው ከመቀመጥ ይልቅ ዓመታት ባለፉ ቁጥር ‘ዕውቀታቸውን ለመጨመር’ ጥረት ያደርጋሉ። (ምሳሌ 9:9) ሙሴ፣ ከይሖዋ ተልዕኮ ሲሰጠው 80 ዓመቱ ነበር። (ዘፀአት 7:7) ሙሴ “የዕድሜአችን ዘመን ሰባ ዓመት፣ ቢበዛም ሰማንያ ነው” በማለት ስለጻፈ በእርሱ ዘመን ይህን ያህል ዓመት መኖር ያልተለመደ ነገር ነበር። (መዝሙር 90:10) ያም ቢሆን ግን ይህ የአምላክ አገልጋይ ስላረጀ መማር እንደማይችል አልተሰማውም። ሙሴ በርካታ መብቶች አግኝቶ አምላክን ለብዙ አሥርተ ዓመታት ሲያገለግልና ከበድ ያሉ ኃላፊነቶችን ሲወጣ ከቆየ በኋላ ይሖዋን “አንተን ዐውቅህ . . . ዘንድ መንገድህን አስተምረኝ” በማለት አጥብቆ ለምኖታል። (ዘፀአት 33:13) ሙሴ ምንጊዜም ቢሆን ከይሖዋ ጋር ያለውን ዝምድና ለማጠናከር ይፈልግ ነበር።
8. ዳንኤል በ90ዎቹ ዕድሜ ውስጥ እያለም እንኳ አእምሮውን በሥራ ያስጠመደው እንዴት ነበር? ይህስ ምን ውጤት አስገኝቷል?
8 ነቢዩ ዳንኤል በ90ዎቹ ዕድሜ ውስጥ እያለም እንኳ ቅዱሳን መጻሕፍትን በጥንቃቄ ይመረምር ነበር። የዘሌዋውያንን፣ የኢሳይያስን፣ የኤርምያስን፣ የሆሴዕንና የአሞጽን መጻሕፍት ጨምሮ ‘ቅዱሳት መጻሕፍትን’ በማጥናቱ ያገኘው እውቀት ወደ ይሖዋ ከልብ የመነጨ ጸሎት እንዲያቀርብ አነሳስቶታል። (ዳንኤል 9:1, 2) ይሖዋም ስለ መሲሑ መምጣት እንዲሁም እውነተኛው አምልኮ ወደፊት ምን እንደሚሆን በመንፈሱ አማካኝነት በመግለጽ ለጸሎቱ መልስ ሰጥቶታል።—ዳንኤል 9:20-27
9, 10. አንዳንዶች አእምሯቸውን በሥራ ለማስጠመድ ምን አድርገዋል?
9 እኛም እንደ ሙሴና ዳንኤል፣ አቅማችን እስከፈቀደልን ድረስ ትኩረታችንን በመንፈሳዊ ነገሮች ላይ በማድረግ አእምሯችንን በሥራ ለማስጠመድ መጣር እንችላለን። ብዙዎች ይህንን እያደረጉ ነው። በ80ዎቹ ዕድሜ ውስጥ የሚገኙት ወርዝ የተባሉ ክርስቲያን ሽማግሌ “ታማኝና ልባም ባሪያ” የሚያዘጋጃቸውን መንፈሳዊ ምግቦች በሙሉ በመመገብ ከድርጅቱ ጋር እኩል ለመሄድ ይጥራሉ። (ማቴዎስ 24:45 የ1954 ትርጉም) ወንድም ወርዝ እንዲህ ብለዋል:- “ለመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ከፍተኛ ፍቅር አለኝ፤ የእውነት ብርሃን ከጊዜ ወደ ጊዜ እንዴት እየጨመረ እንደሚሄድ ማየት ያስደስተኛል።” (ምሳሌ 4:18) በተመሳሳይም ከ60 ዓመታት በላይ በሙሉ ጊዜ አገልግሎት የተካፈሉት ወንድም ፍሬድ፣ ከእምነት ባልንጀሮቻቸው ጋር ሲሆኑ ቅድሚያውን ወስደው መጽሐፍ ቅዱሳዊ ውይይት መጀመር በመንፈሳዊ የሚያነቃቃ ሆኖላቸዋል። ወንድም ፍሬድ እንዲህ ብለዋል:- “መጽሐፍ ቅዱስ በአእምሮዬ ውስጥ ሕያው ሆኖ እንዲቀጥል ማድረግ አለብኝ። መጽሐፍ ቅዱስ ሕያው እንዲሆን ማለትም ትርጉም እንዲኖረው ማድረግ ከቻልክ እንዲሁም የምትማረውን ነገር ‘ከጤናማው ትምህርት ምሳሌ’ ጋር ካዛመድከው የተሟላ እውቀት ይኖርሃል። በዚህ መንገድ፣ እያንዳንዱ እውነት በቦታው ተስተካክሎ ሲቀመጥ እንደሚያንጸባርቅ ፈርጥ ሊሆንልህ ይችላል።”—2 ጢሞቴዎስ 1:13
10 አንድ ሰው በዕድሜ ስለገፋ ብቻ አዳዲስና ከበድ ያሉ ነገሮችን ለመማር አይችልም ማለት አይደለም። በ60ዎቹ፣ በ70ዎቹና ሌላው ቀርቶ በ80ዎቹ ዕድሜ ላይ የሚገኙ ሰዎችም እንኳ ማንበብና መጻፍ ወይም አዳዲስ ቋንቋዎችን መማር ችለዋል። አንዳንድ የይሖዋ ምሥክሮች የተለያየ ዜግነት ላላቸው ሰዎች ምሥራቹን ለማካፈል ሲሉ እንዲህ አድርገዋል። (ማርቆስ 13:10) ወንድም ሃሪና ባለቤታቸው የፖርቹጋል ቋንቋ የሚናገሩ ሰዎችን ለመርዳት በወሰኑበት ወቅት በ60ዎቹ ዕድሜ መገባደጃ ላይ ይገኙ ነበር። ወንድም ሃሪ “ዕድሜ እየገፋ ሲሄድ ማንኛውም ተግባር ይበልጥ አስቸጋሪ እንደሚሆን አይካድም” በማለት ተናግረዋል። ያም ቢሆን ግን እነዚህ ባልና ሚስት ያለማቋረጥ ጥረት በማድረግ በፖርቹጋል ቋንቋ ሰዎችን መጽሐፍ ቅዱስ ማስጠናት ችለዋል። ወንድም ሃሪ ላለፉት በርካታ ዓመታት በአውራጃ ስብሰባ ላይ በፖርቹጋል ቋንቋ ንግግር አቅርበዋል።
11. ታማኝ የሆኑ አረጋውያን ያከናወኗቸውን ነገሮች የምንመለከተው ለምንድን ነው?
11 እርግጥ ነው፣ እንደነዚህ ዓይነት ከበድ ያሉ ተግባሮችን ለማከናወን ሁኔታው ወይም ጤንነቱ የሚፈቅድለት ሁሉም ሰው ላይሆን ይችላል። ታዲያ አንዳንድ አረጋውያን ያከናወኗቸውን ነገሮች ማንሳቱ ለምን አስፈለገ? እንዲህ የምናደርገው ሁሉም ሰው ከላይ ያየናቸውን ነገሮች ለማከናወን መጣር እንዳለበት ሐሳብ ለማቅረብ አይደለም። ከዚህ ይልቅ ሐዋርያው ጳውሎስ “የኑሮአቸውን ፍሬ ተመልከቱ፤ በእምነታቸውም ምሰሉአቸው” በማለት ታማኝ የሆኑ የጉባኤ ሽማግሌዎችን በተመለከተ ለዕብራውያን ክርስቲያኖች የሰጠው ዓይነት ማበረታቻ ለማቅረብ ነው። (ዕብራውያን 13:7) እንደነዚህ ያሉ በቅንዓታቸው ምሳሌ የሚሆኑ አረጋውያንን ስንመለከት ለአምላክ በሚያቀርቡት አገልግሎት እንዲቀጥሉ የሚገፋፋቸውን ጠንካራ እምነት ለመምሰል ልንበረታታ እንችላለን። አሁን 87 ዓመት የሆናቸው ወንድም ሃሪ በይሖዋ አገልግሎት የበለጠ ተሳትፎ ለማድረግ ምን እንዳነሳሳቸው ሲገልጹ “የቀሩኝን ዓመታት በጥበብ በመጠቀም በይሖዋ አገልግሎት የምችለውን ያህል መሥራት እፈልጋለሁ” በማለት ተናግረዋል። ቀደም ብለው የተጠቀሱት ወንድም ፍሬድ ደግሞ በቤቴል ውስጥ በተመደቡበት ቦታ በማገልገል ከፍተኛ እርካታ አግኝተዋል። “ይሖዋን ከሁሉ በተሻለ ሁኔታ ማገልገል የምትችልበትን መንገድ መፈለግና በዚሁ ጎዳና ላይ ጸንተህ መቀጠል አለብህ” በማለት ተናግረዋል።
ሁኔታዎች ቢለዋወጡም ለአምላክ ያደሩ ሆኖ መቀጠል
12, 13. ቤርዜሊ በዕድሜው መግፋት የተነሳ ሁኔታዎቹ ቢለወጡም ለአምላክ ያደረ መሆኑን ያሳየው እንዴት ነበር?
12 በሰውነታችን ላይ የሚታዩ ለውጦችን መቀበልና ከእነዚህ ለውጦች ጋር ራስን አስማምቶ መኖር ቀላል አይደለም። ሆኖም እነዚህ ለውጦች እያሉም ለአምላክ ያደሩ መሆን ይቻላል። ገለዓዳዊው ቤርዜሊ በዚህ ረገድ ግሩም ምሳሌ ነው። ይህ ሰው፣ አቤሴሎም ባመጸበት ወቅት ለዳዊትና ለሠራዊቱ ምግብ እንዲሁም ማረፊያ በማቅረብ በ80 ዓመት ዕድሜው ግሩም የሆነ የእንግዳ ተቀባይነት መንፈስ አሳይቷል። ዳዊት ወደ ኢየሩሳሌም በተመለሰበት ወቅት ቤርዜሊ የዳዊትን ሠራዊት እስከ ዮርዳኖስ ወንዝ ድረስ ሸኝቷል። ከዚያም ዳዊት፣ ቤርዜሊ የንጉሣዊው ቤተሰብ አባል እንዲሆን ግብዣ አቀረበለት። ቤርዜሊ ምን ምላሽ ሰጠ? “እኔ አሁን የሰማንያ ዓመት ሽማግሌ ነኝ፤ . . . ከእንግዲህ አገልጋይህ የሚበላውንና የሚጠጣውን ጣዕሙን መለየት ይችላል? የሚዘፍኑትን የወንዶችና የሴቶችን ድምፅ አሁንም መስማት እችላለሁ? . . . አገልጋይህ ከመዓም እነሆ፤ ከጌታዬ ከንጉሡ ጋር ይሻገር፤ ደስ ያለህንም ነገር አድርግለት” በማለት መለሰ።—2 ሳሙኤል 17:27-29፤ 19:31-40
13 ቤርዜሊ ሁኔታዎቹ ቢለወጡም ይሖዋ የቀባውን ንጉሥ ለመደገፍ የተቻለውን ሁሉ አድርጓል። የመቅመስና የመስማት ችሎታው እንደ ቀድሞው እንዳልሆነ ቢያምንም በሁኔታው አልተማረረም። ከዚህ ይልቅ ለእርሱ የቀረበለትን ግብዣ ከመዓም እንዲወስደው ሐሳብ በማቅረብ ራስ ወዳድ አለመሆኑን እንዲሁም ውስጣዊ ማንነቱን በግልጽ አሳይቷል። እንደ ቤርዜሊ ሁሉ በዛሬው ጊዜ የሚገኙ በርካታ አረጋውያንም ከራስ ወዳድነት የራቀ የለጋስነት መንፈስ ያሳያሉ። እውነተኛውን አምልኮ ለመደገፍ የተቻላቸውን ሁሉ ያደርጋሉ፤ ምክንያቱም “እግዚአብሔር ደስ የሚሰኘው እንደዚህ ባለው መሥዋዕት” እንደሆነ ያውቃሉ። ታማኝ ክርስቲያኖች በመካከላችን መኖራቸው እንዴት ያለ በረከት ነው!—ዕብራውያን 13:16
14. ዳዊት በዕድሜ መግፋቱ በመዝሙር 37:23-25 ላይ ያለው ሐሳብ ይበልጥ ትርጉም እንዲኖረው ያደረገው እንዴት ነው?
14 ዳዊት በሕይወቱ ውስጥ ሁኔታዎቹ ብዙ ጊዜ ቢለዋወጡም ይሖዋ ለታማኝ አገልጋዮቹ የሚያደርገው እንክብካቤ ፈጽሞ እንደማይለወጥ እርግጠኛ ነበር። ዛሬ መዝሙር 37 ተብሎ የሚታወቀውን መዝሙር ያቀናበረው በሕይወቱ መገባደጃ አካባቢ ነው። ዳዊት በገና እየተጫወተ የሚከተለውን መዝሙር በተመስጦ ሲዘምር በአእምሮህ መሳል ትችላለህ:- “የሰው አካሄድ በእግዚአብሔር ይጸናል፤ በመንገዱ ደስ ይለዋል። ቢሰናከልም አይወድቅም፤ እግዚአብሔር በእጁ ደግፎ ይይዘዋልና። ጐልማሳ ነበርሁ፤ አሁን አርጅቻለሁ፤ ነገር ግን ጻድቅ ሲጣል፣ ዘሩም እንጀራ ሲለምን አላየሁም።” (መዝሙር 37:23-25) ይሖዋ፣ በመንፈስ አነሳሽነት በተጻፈው በዚህ መዝሙር ላይ የዳዊት ዕድሜ መጠቀሱ አስፈላጊ እንደሆነ ተሰምቶታል። ይህ ሐሳብ ዳዊት ከልብ በመነጨ ስሜት በዘመረው መዝሙር ውስጥ መካተቱ የዚህን የአምላክ አገልጋይ ስሜት እንዴት ግሩም አድርጎ ይገልጸዋል!
15. ሐዋርያው ዮሐንስ ሁኔታዎቹ ከመለዋወጣቸውም በላይ ዕድሜው ቢገፋም በታማኝነት አምላክን በማገልገል ረገድ ግሩም ምሳሌ የተወልን እንዴት ነው?
15 ሐዋርያው ዮሐንስም ሁኔታዎቹ ከመለዋወጣቸውም በላይ ዕድሜው ቢገፋም በታማኝነት አምላክን በማገልገል ረገድ ግሩም ምሳሌ ትቶልናል። ዮሐንስ ወደ 70 ለሚጠጉ ዓመታት አምላክን ካገለገለ በኋላ “ስለ እግዚአብሔር ቃልና ስለ ኢየሱስ ምስክርነት” በመስጠቱ ፍጥሞ ወደተባለች ደሴት በግዞት ተላከ። (ራእይ 1:9) ይሁን እንጂ ይህ ሐዋርያ የሚሠራው ሥራ ገና አላለቀም ነበር። እንዲያውም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙት እርሱ ያሰፈራቸው መጻሕፍት ሁሉ የተጻፉት በዕድሜው መገባደጃ ላይ ነበር። ዮሐንስ በፍጥሞ ደሴት እያለ አስደናቂ ራዕይ የተመለከተ ሲሆን ያየውን ነገር በሙሉ በጥንቃቄ አስፍሮታል። (ራእይ 1:1, 2) ሐዋርያው፣ ኔርቫ በተባለው የሮም ንጉሠ ነገሥት ግዛት ወቅት ከግዞት እንደተመለሰ ይታመናል። ከዚያም በ98 ከክርስቶስ ልደት በኋላ አካባቢ፣ ዮሐንስ ምናልባትም ከ90 እስከ 100 ዓመት ባለው ዕድሜ ውስጥ ሆኖ በስሙ የተሰየመውን ወንጌልና መልእክቶቹን ጻፈ።
የማይፋቅ የጽናት መዝገብ
16. ሐሳባቸውን የመግለጽ ችግር ያጋጠማቸው አረጋውያን ለአምላክ ያደሩ መሆናቸውን ማሳየት የሚችሉት እንዴት ነው?
16 የሚያጋጥሙን የአቅም ገደቦች የተለያየ መልክና ደረጃ ይኖራቸው ይሆናል። ለምሳሌ አንዳንድ ሰዎች ዕድሜያቸው እየገፋ ሲሄድ ሐሳባቸውን መግለጽ እንኳ ያስቸግራቸው ይሆናል። ያም ቢሆን አምላክ ፍቅሩንና ይገባናል የማንለውን ደግነቱን እንዴት እንዳሳያቸው በማስታወስ ይደሰታሉ። እነዚህ አረጋውያን ብዙ መናገር ባይችሉም በልባቸው ይሖዋን “አቤቱ፤ ሕግህን ምንኛ ወደድሁ! ቀኑን ሙሉ አሰላስለዋለሁ” ይሉታል። (መዝሙር 119:97) ይሖዋም በበኩሉ ‘ስሙን የሚያከብሩ’ ወይም የሚያስቡ ሰዎችን ያውቃቸዋል፤ ከዚህም በላይ እነዚህ ሰዎች ለመንገዶቹ ደንታ ቢስ ከሆነው አብዛኛው የሰው ዘር ምን ያህል የተለዩ እንደሆኑ ይገነዘባል። (ሚልክያስ 3:16፤ መዝሙር 10:4) ይሖዋ በልባችን ሐሳብ እንደሚደሰት ማወቁ ምንኛ የሚያጽናና ነው!—1 ዜና መዋዕል 28:9፤ መዝሙር 19:14
17. ለረጅም ጊዜ ይሖዋን ያገለገሉ ክርስቲያኖች ምን ልዩ ነገር አግኝተዋል?
17 ሳንጠቅሰው ልናልፍ የማይገባው ሌላ ነገር ደግሞ፣ ይሖዋን ለበርካታ አሥርተ ዓመታት በታማኝነት ሲያገለግሉ የቆዩ ክርስቲያኖች ልዩ የሆነና በሌላ በምንም መንገድ ሊገኝ የማይችል ነገር የሚያገኙ መሆኑን ነው፤ ስማቸው በማይፋቅ የጽናት መዝገብ ሰፍሯል። ኢየሱስ “ጸንታችሁም በመቆም ነፍሳችሁን ታተርፋላችሁ” ብሏል። (ሉቃስ 21:19) የዘላለም ሕይወት ለማግኘት ጽናት አስፈላጊ ነው። “የእግዚአብሔርን ፈቃድ ፈጽማችሁ” በአኗኗራችሁ ታማኝነታችሁን ያሳያችሁ ሁሉ ‘የተስፋ ቃሉን እንደምትቀበሉ’ መጠባበቅ ትችላላችሁ።—ዕብራውያን 10:36
18. (ሀ) አረጋውያንን በተመለከተ ይሖዋ ምን ማየት ያስደስተዋል? (ለ) በሚቀጥለው ርዕስ ላይ ምን እንመለከታለን?
18 ይሖዋ፣ በሙሉ ነፍስ የምታቀርቡትን አገልግሎት ይነስም ይብዛ ከፍ አድርጎ ይመለከተዋል። ዕድሜ እየገፋ ሲሄድ ‘በውጫዊው ሰውነት’ ላይ ለውጦች ቢከሰቱም ‘ውስጣዊው ሰውነት’ በየዕለቱ እየታደሰ ሊሄድ ይችላል። (2 ቆሮንቶስ 4:16) ይሖዋ ከዚህ ቀደም ያከናወናችሁትን ነገር ከፍ አድርጎ እንደሚመለከተው ምንም ጥርጥር የለውም፤ ለስሙ ስትሉ በአሁኑ ጊዜ እያቀረባችሁ ያላችሁትን አገልግሎት እንደሚያደንቀውም ግልጽ ነው። (ዕብራውያን 6:10) እንዲህ ያለው ታማኝነት የሚያስገኘውን ከፍተኛ ጥቅም በሚቀጥለው ርዕስ ላይ እንመለከታለን።
ምን ብለህ ትመልሳለህ?
• ሐና በዛሬው ጊዜ ለሚገኙ አረጋውያን ክርስቲያኖች ምን ግሩም ምሳሌ ትታለች?
• አንድ ሰው በዕድሜ ስለገፋ ብቻ ሊያከናውነው የሚችለው ነገር ይገደባል የማንለው ለምንድን ነው?
• አረጋውያን ለአምላክ ያደሩ መሆናቸውን ማሳየታቸውን መቀጠል የሚችሉት እንዴት ነው?
• ይሖዋ አረጋውያን የሚያቀርቡለትን አገልግሎት እንዴት ይመለከተዋል?
[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]
[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
አረጋዊው ዳንኤል ‘ቅዱሳት መጻሕፍትን’ በማጥናቱ አይሁዳውያን በግዞት የሚቆዩበትን ጊዜ ለማወቅ ችሏል
[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በዕድሜ የገፉ በርካታ ክርስቲያኖች አዘውትረው በስብሰባዎች በመገኘት፣ በቅንዓት በመስበክና ለመማር ባላቸው ጉጉት ምሳሌ የሚሆኑ ናቸው