አረጋውያን ለወጣቶች በረከት ናቸው
አረጋውያን ለወጣቶች በረከት ናቸው
“አምላክ ሆይ፤ ሳረጅና ስሸብትም አትተወኝ፤ ክንድህን ለመጭው ትውልድ፣ ኀይልህን ኋላ ለሚነሣ ሕዝብ ሁሉ፣ እስከምገልጽ ድረስ።” —መዝሙር 71:18
1, 2. በዕድሜ የገፉ የአምላክ አገልጋዮች ሊገነዘቡት የሚገባው ነገር ምንድን ነው? ከዚህ ቀጥሎ ምን እየተመለከትን እንሄዳለን?
በምዕራብ አፍሪካ፣ አንድ ክርስቲያን ሽማግሌ አንድን በዕድሜ የገፉ ቅቡዕ ወንድም “እንዴት ነዎት?” በማለት ጠየቃቸው። አረጋዊው ወንድምም “መሮጥ፣ ዱብ ዱብ ማለትና መዝለል እችላለሁ” በማለት ይህን ማድረግ እንደሚችሉ አሳዩት። አክለውም “መብረር ግን አልችልም” በማለት ተናገሩ። እኚህ አረጋዊ ወንድም ምን ማለት እንደፈለጉ ግልጽ ነበር። ‘ማድረግ የምችለውን ነገር በደስታ አደርገዋለሁ፤ የማልችለውን ግን ለማድረግ አልታገልም’ ማለታቸው ነበር። አረጋዊውን ቅቡዕ ወንድም ለመጠየቅ ሄዶ የነበረው የጉባኤ ሽማግሌ በአሁኑ ጊዜ በ80ዎቹ ዕድሜ ውስጥ የሚገኝ ሲሆን ታማኝና ተጫዋች ስለነበሩት ስለ እኚህ ወንድም አስደሳች ትዝታዎች አሉት።
2 በዕድሜ የገፉ ሰዎች የሚያንጸባርቋቸው አምላካዊ ባሕርያት በሌሎች ላይ ዘላቂ የሆነ በጎ ተጽዕኖ ሊያሳድሩ ይችላሉ። እርግጥ ነው፣ አንድ ሰው በዕድሜ ስለገፋ ብቻ ጥበበኛ መሆንና የክርስቶስ ዓይነት ባሕርያት ማፍራት ይችላል ማለት አይደለም። (መክብብ 4:13) መጽሐፍ ቅዱስ “ሽበት የክብር ዘውድ ነው፤ የሚገኘውም በጽድቅ ሕይወት ነው” ይላል። (ምሳሌ 16:31) በዕድሜ የገፋህ ክርስቲያን ከሆንክ የምትናገራቸውና የምታደርጋቸው ነገሮች በሌሎች ላይ ምን ያህል በጎ ተጽዕኖ ሊያሳድሩ እንደሚችሉ ተገንዝበሃል? አረጋውያን ለወጣቶች ምን ያህል በረከት እንደሆኑ የሚያሳዩ አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሳሌዎችን እንመልከት።
ከፍተኛ ጥቅም ያስገኘ እምነት
3. ኖኅ ታማኝ መሆኑ በዚህ ዘመን የሚኖሩ ሰዎችን በሙሉ የጠቀመው እንዴት ነው?
3 ኖኅ ያሳየው እምነትና ጽናት በዚህ ዘመን የምንኖር ሰዎችንም ጭምር ጠቅሞናል። ኖኅ መርከብ ሲሠራ፣ እንስሳቱን ሲሰበስብ እንዲሁም ለሰዎች ሲሰብክ ዕድሜው ወደ 600 ዓመት ተጠግቶ ነበር። (ዘፍጥረት 7:6፤ 2 ጴጥሮስ 2:5) ኖኅ አምላካዊ ፍርሃት የነበረው ሰው በመሆኑ እርሱና ቤተሰቡ ከታላቁ የጥፋት ውኃ መትረፍ ችለዋል፤ ከዚህም በላይ ኖኅ በዛሬው ጊዜ በምድር ላይ ለሚኖሩ ሰዎች ሁሉ ቅድመ አያት ለመሆን በቅቷል። እርግጥ ነው፣ ኖኅ የኖረው አብዛኞቹ ሰዎች ረዥም ዘመን በሚኖሩበት ወቅት ነበር። ያም ሆኖ ዕድሜው በጣም በገፋበት ወቅትም እንኳ በታማኝነት ማገልገሉን የቀጠለ ሲሆን ይህም ታላቅ በረከት አስገኝቷል። እንዴት?
4. የኖኅ ጽናት በአሁኑ ጊዜ ለሚገኙ የአምላክ አገልጋዮች ጠቃሚ የሆነው እንዴት ነው?
4 ናምሩድ፣ ይሖዋ ለሰው ልጆች ‘ምድርን እንዲሞሏት’ የሰጠውን ትእዛዝ በመቃወም የባቤልን ግንብ መሥራት በጀመረበት ወቅት ኖኅ 800 ዓመት ገደማ ይሆነው ነበር። (ዘፍጥረት 9:1፤ 11:1-9) ይሁን እንጂ ኖኅ ከናምሩድ ጋር ተባብሮ አላመጸም። በመሆኑም ይሖዋ የዓመጸኞቹን ቋንቋ ሲደበላልቀው የኖኅ ቋንቋ አልተለወጠ ይሆናል። ኖኅ ዕድሜው ሲገፋ ብቻ ሳይሆን በሕይወቱ ሙሉ ያሳየው እምነትና ጽናት በማንኛውም ዕድሜ የሚገኙ የአምላክ አገልጋዮች ሊኮርጁት የሚገባ ባሕርይ ነው።—ዕብራውያን 11:7
በቤተሰባቸው ላይ የሚያሳድሩት በጎ ተጽዕኖ
5, 6. (ሀ) አብርሃም 75 ዓመት ሲሆነው ይሖዋ ምን እንዲያደርግ አዘዘው? (ለ) አብርሃምስ ለአምላክ ትእዛዝ ምን ምላሽ ሰጠ?
5 ከኖኅ በኋላ ከኖሩት የእምነት አባቶች ሕይወት እንደምንመለከተው አረጋውያን፣ የቤተሰባቸው አባላት በሚኖራቸው እምነት ላይ ተጽዕኖ ማሳደር ይችላሉ። አምላክ ለአብርሃም የሚከተለውን ትእዛዝ በሰጠው ወቅት አብርሃም 75 ዓመቱ ነበር:- “አገርህን፣ ወገንህንና የአባትህን ቤት ትተህ እኔ ወደማሳይህ ምድር ሂድ። ታላቅ ሕዝብ አደርግሃለሁ፤ ደግሞም እባርክሃለሁ።”—ዘፍጥረት 12:1, 2
6 ቤትህን፣ ጓደኞችህን፣ የትውልድ ቀዬህን ትተህ እንዲሁም በዘመድ አዝማድ መካከል ያለ ስጋት መኖር ስትችል ይህን ሁሉ ጥለህ ወደማታውቀው አገር እንድትሄድ ቢነገርህ ምን ሊሰማህ እንደሚችል አስብ። አብርሃም እንዲህ እንዲያደርግ የተነገረው ሲሆን እርሱም “እግዚአብሔር እንዳዘዘው ወጣ።” ከዚያ በኋላም ቀሪውን የሕይወት ዘመኑን በከነዓን ምድር እንደ መጻተኛና ስደተኛ ሆኖ በድንኳን ውስጥ ኖሯል። (ዘፍጥረት 12:4፤ ዕብራውያን 11:8, 9) ይሖዋ፣ ለአብርሃም “ታላቅ ሕዝብ” እንደሚሆን የነገረው ቢሆንም አብርሃም የሞተው ዘሮቹ ከመብዛታቸው ከረጅም ጊዜ በፊት ነበር። ባለቤቱ ሣራም ለአብርሃም የወለደችለት ይስሐቅን ብቻ ሲሆን ይህም የሆነው በተስፋይቱ ምድር ለ25 ዓመታት ከኖሩ በኋላ ነበር። (ዘፍጥረት 21:2, 5) ያም ቢሆን ግን አብርሃም ተስፋ ቆርጦ ወደመጣበት ከተማ አልተመለሰም። አብርሃም እንዴት ያለ የእምነትና የጽናት ምሳሌ ነው!
7. የአብርሃም መጽናት በልጁ በይስሐቅ ላይ ምን ተጽዕኖ አሳድሯል? ለሰው ልጆችስ ምን ጥቅም አስገኝቷል?
7 አብርሃም ያሳየው ጽናት፣ በልጁ በይስሐቅ ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ አሳድሯል፤ ይስሐቅ ዕድሜውን ሙሉ ማለትም 180 ዓመት በከነዓን ምድር እንደ መጻተኛ ሆኖ ኖሯል። ይስሐቅ እንዲጸና የረዳው በአምላክ ተስፋ ላይ የነበረው እምነት ነው፤ እንዲህ ዓይነት እምነት እንዲያዳብር የረዱት አረጋውያን ወላጆቹ ሲሆኑ በኋላ ላይ ደግሞ ይሖዋ ራሱ የተናገረው ነገር እምነቱን አጠናክሮለታል። (ዘፍጥረት 26:2-5) ይስሐቅ ያሳየው ጽናት፣ ይሖዋ የሰው ልጆች በሙሉ የሚባረኩበት ‘ዘር’ በአብርሃም ቤተሰብ በኩል እንደሚመጣ የገባው ቃል እንዲፈጸም ትልቅ ሚና ተጫውቷል። ከብዙ መቶ ዓመታት በኋላ ደግሞ የዚህ ‘ዘር’ ዋነኛ ክፍል የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ በእርሱ የሚያምን ሁሉ ከአምላክ ጋር እንዲታረቅና የዘላለም ሕይወት እንዲያገኝ መንገድ ከፍቷል።—ገላትያ 3:16፤ ዮሐንስ 3:16
8. ያዕቆብ ጠንካራ እምነት እንዳለው ያሳየው እንዴት ነበር? ይህስ ምን ውጤት አስገኝቷል?
8 ይስሐቅ ደግሞ በተራው ልጁ ያዕቆብ እስከ ሽምግልና ዕድሜው ድረስ እንዲጸና የረዳውን ጠንካራ እምነት እንዲያዳብር ረድቶታል። ያዕቆብ በረከት ለማግኘት ሲል ከአንድ መልአክ ጋር ሌሊቱን ሙሉ በታገለበት ወቅት 97 ዓመቱ ነበር። (ዘፍጥረት 32:24-28) በመቶ አርባ ሰባት ዓመቱ ከመሞቱ በፊት ኃይሉን አሰባስቦ 12ቱን ወንዶች ልጆቹን በግለሰብ ደረጃ ባረካቸው። (ዘፍጥረት 47:28) በዘፍጥረት 49:1-28 ላይ ተመዝግበው የሚገኙት ያዕቆብ የተናገራቸው ትንቢት አዘል ሐሳቦች በትክክል የተፈጸሙ ሲሆን በአሁኑ ጊዜም ፍጻሜያቸውን እያገኙ ነው።
9. በመንፈሳዊ የጎለመሱ አረጋውያን በቤተሰባቸው ላይ ስለሚያሳድሩት ተጽዕኖ ምን ማለት ይቻላል?
9 ከዚህ በግልጽ ለመመልከት እንደምንችለው በዕድሜ የገፉ የአምላክ አገልጋዮች በቤተሰባቸው አባላት ላይ በጎ ተጽዕኖ ማሳደር ይችላሉ። እነዚህ ክርስቲያኖች የሚሰጡት ጥበብ ያዘለ ምክርና በጽናት ረገድ የሚተዉት ምሳሌ ከቅዱስ ጽሑፋዊ መመሪያ ጋር ተዳምረው አንድ ወጣት ጠንካራ እምነት እንዲገነባ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ሊያበረክቱ ይችላሉ። (ምሳሌ 22:6) በመሆኑም አረጋውያን በቤተሰባቸው ላይ በጎ ተጽዕኖ ለማሳደር ያላቸውን አጋጣሚ አቅልለው መመልከት የለባቸውም።
በእምነት አጋሮቻቸው ላይ የሚያሳድሩት በጎ ተጽዕኖ
10. ዮሴፍ ‘ስለ ዐጽሙ የሰጠው ትእዛዝ’ ምን ነበር? ይህስ ምን ጥቅም ነበረው?
10 አረጋውያን በእምነት አጋሮቻቸው ላይም በጎ ተጽዕኖ ማሳደር ይችላሉ። የያዕቆብ ልጅ የሆነው ዮሴፍ በስተርጅናው የሰጠው እምነቱን የሚያሳይ ቀላል ትእዛዝ ከእርሱ በኋላ በኖሩ በሚሊዮን የሚቆጠሩ እውነተኛ አምላኪዎች ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ አሳድሯል። ዮሴፍ ‘ስለ ዐጽሙ ትእዛዝ በሰጠበት’ ጊዜ ይኸውም እስራኤላውያን ግብጽን ለቅቀው ሲወጡ ዐጽሙን ይዘው እንዲሄዱ በተናገረበት ወቅት የ110 ዓመት ሰው ነበር። (ዕብራውያን 11:22፤ ዘፍጥረት 50:25) ይህ ትእዛዝ እስራኤላውያን ነጻ እንደሚወጡ ማረጋገጫ ይሰጥ ስለነበር ሕዝቡ ዮሴፍ ከሞተ በኋላ በባርነት ባሳለፏቸው በርካታ ዓመታት ውስጥ ተስፋ እንዲኖራቸው ረድቷቸዋል።
11. አረጋዊው ሙሴ በኢያሱ ላይ ምን በጎ ተጽዕኖ አሳድሮ ሊሆን ይችላል?
11 የዮሴፍን እምነት በሚያሳየው በዚህ ንግግር ከተበረታቱት ሰዎች አንዱ ሙሴ ነው። ሙሴ 80 ዓመት ሲሆነው የዮሴፍን ዐጽም ከግብጽ ይዞ የመውጣት መብት አግኝቷል። (ዘፀአት 13:19) በዚሁ ጊዜ አካባቢ ሙሴ በዕድሜ ከእርሱ በጣም ከሚያንሰው ከኢያሱ ጋር ተገናኘ። በቀጣዮቹ 40 ዓመታት ውስጥ ኢያሱ የሙሴ ረዳት ሆኖ አገልግሏል። (ዘኍልቍ 11:28) ሙሴ ወደ ሲና ተራራ በወጣበት ወቅት ኢያሱ የተወሰነ መንገድ አብሮት የሄደ ሲሆን ሙሴ የምሥክሩን ጽላት ይዞ እስኪወርድ ድረስም ተራራው ላይ ሆኖ ጠብቆታል። (ዘፀአት 24:12-18፤ 32:15-17) ኢያሱ የጎለመሰ የአምላክ አገልጋይ ከነበረው ከአረጋዊው ሙሴ ምክርና ጥበብ ያዘለ ትምህርት እንዳገኘ ጥርጥር የለውም!
12. ኢያሱ በሕይወት ዘመኑ ሁሉ በእስራኤል ሕዝብ ላይ በጎ ተጽዕኖ ያሳደረው እንዴት ነበር?
12 ኢያሱ ደግሞ በበኩሉ በሕይወት በነበረበት ጊዜ ሁሉ የእስራኤልን ሕዝብ ያበረታታ ነበር። መሳፍንት 2:7 እንዲህ ይላል:- “ኢያሱ በሕይወት በነበረበት ዘመን ሁሉ እንዲሁም ከእርሱ በኋላ እግዚአብሔር ለእስራኤል ያደረገውን ታላላቅ ነገሮች ሁሉ ያዩ አለቆች በነበሩበት ዘመን ሁሉ ሕዝቡ እግዚአብሔርን አመለከ።” ይሁን እንጂ ኢያሱም ሆነ ሌሎቹ ሽማግሌዎች ከሞቱ በኋላ ነቢዩ ሳሙኤል እስከተነሳበት ጊዜ ድረስ በነበሩት 300 ዓመታት ሕዝቡ በእውነተኛውና በሐሰተኛው አምልኮ መካከል ይወላውል ነበር።
ሳሙኤል ‘በቅን ፈረደ’
13. ሳሙኤል ‘በቅን ለመፍረድ’ ምን አድርጓል?
13 መጽሐፍ ቅዱስ ሳሙኤል በስንት ዓመቱ እንደሞተ አይናገርም፤ ሆኖም በአንደኛ ሳሙኤል መጽሐፍ ውስጥ ሰፍረው የሚገኙት ዘገባዎች የ102 ዓመት ጊዜ የሚሸፍኑ ሲሆን አብዛኞቹ ክንውኖች ሲፈጸሙ ሳሙኤል በሕይወት ነበር። ዕብራውያን 11:32, 33 ጻድቅ መሳፍንትና ነቢያት ‘በቅን እንደፈረዱ’ ይናገራል። ሳሙኤል በዘመኑ የነበሩት ሰዎች ከክፉ ድርጊት እንዲርቁ ወይም መጥፎ ነገር መሥራታቸውን እንዲያቆሙ ይረዳቸው ነበር። (1 ሳሙኤል 7:2-4) ይህን ያደረገው እንዴት ነው? ሳሙኤል በሕይወት ዘመኑ ሁሉ ለይሖዋ ታማኝ ነበር። (1 ሳሙኤል 12:2-5) ለንጉሡ እንኳ ሳይቀር ጠንከር ያለ ምክር ለመስጠት አልፈራም። (1 ሳሙኤል 15:16-29) ከዚህም በላይ ሳሙኤል ‘ዕድሜው ገፍቶና ጠጕሩ ሸብቶ’ እያለም ስለ ሌሎች በመጸለይ ረገድ ግሩም ምሳሌ ትቷል። እስራኤላውያንን “ለእናንተ ከመጸለይ ወደ ኋላ በማለት እግዚአብሔርን መበደል ከእኔ ይራቅ” ብሏቸዋል።—1 ሳሙኤል 12:2, 23
14, 15. በዛሬው ጊዜ ያሉ አረጋውያን በጸሎት ረገድ ሳሙኤልን መምሰል የሚችሉት እንዴት ነው?
14 ከላይ የተመለከትናቸው ዘገባዎች በሙሉ፣ በዕድሜ የገፉ ሰዎች አብረዋቸው ይሖዋን በሚያገለግሉት ክርስቲያኖች ላይ በጎ ተጽዕኖ ሊያሳድሩ የሚችሉበትን በጣም አስፈላጊ መንገድ ጎላ አድርገው የሚያሳዩ ናቸው። በዕድሜ የገፉ ክርስቲያኖች በጤና ማጣትም ሆነ በሌሎች ምክንያቶች የተነሳ የአቅም ገደብ ቢኖርባቸውም ስለ ሌሎች መጸለይ ይችላሉ። እናንተ አረጋውያን፣ የምታቀርቧቸው ጸሎቶች ጉባኤውን ምን ያህል እንደሚጠቅሙ ትገነዘባላችሁ? በፈሰሰው የክርስቶስ ደም ላይ እምነት በማሳደራችሁ በይሖዋ ፊት ተቀባይነት አግኝታችኋል፤ እንዲሁም ባሳያችሁት ጽናት ምክንያት ‘የተፈተነ’ እምነት አላችሁ። (ያዕቆብ 1:3፤ 1 ጴጥሮስ 1:7) “የጻድቅ ሰው ጸሎት ኀይል አለው፤ ታላቅ ነገርም ያደርጋል” የሚለውን ጥቅስ ፈጽሞ ልትረሱት አይገባም።—ያዕቆብ 5:16
15 የስብከቱን ሥራና የጉባኤ እንቅስቃሴዎችን በመደገፍ የምታቀርቡት ጸሎት አስፈላጊ ነው። አንዳንድ ወንድሞቻችን በክርስቲያናዊ የገለልተኝነት አቋማቸው ምክንያት ወኅኒ ቤት ተጥለዋል። በተፈጥሮ አደጋዎች፣ በጦርነቶች እንዲሁም በእርስ በርስ ግጭቶች የተጎዱም አሉ። ባለንበት ጉባኤ ውስጥ ያሉ ሌሎች ክርስቲያኖችም ፈተና ወይም ተቃውሞ ያጋጥማቸዋል። (ማቴዎስ 10:35, 36) በስብከቱ ሥራም ሆነ ጉባኤዎችን በመምራት ረገድ ቅድሚያውን ወስደው የሚያገለግሉት ክርስቲያኖችም የእናንተ የዘወትር ጸሎት ያሻቸዋል። (ኤፌሶን 6:18, 19፤ ቈላስይስ 4:2, 3) ኤጳፍራ እንዳደረገው ሁሉ እናንተም የእምነት ባልንጀሮቻችሁን ጠቅሳችሁ መጸለያችሁ በጣም ግሩም ነው!—ቈላስይስ 4:12
መጭውን ትውልድ ማስተማር
16, 17. በመዝሙር 71:18 ላይ ምን ትንቢት ተነግሯል? ይህስ ተፈጻሚነት ያገኘው እንዴት ነው?
16 በምድር ላይ ለዘላለም የመኖር ተስፋ ያላቸው “ሌሎች በጎች” ወደ ሰማይ የመሄድ ጥሪ ካለው “ታናሽ መንጋ” ታማኝ አባላት ጋር በመተባበራቸው ጠቃሚ ሥልጠና አግኝተዋል። (ሉቃስ 12:32 የ1954 ትርጉም፤ ዮሐንስ 10:16) ይህ ደግሞ “አምላክ ሆይ፤ ሳረጅና ስሸብትም አትተወኝ፤ ክንድህን ለመጭው ትውልድ፣ ኀይልህን ኋላ ለሚነሣ ሕዝብ ሁሉ፣ እስከምገልጽ ድረስ” በሚለው የመዝሙር 71:18 ጥቅስ ላይ አስቀድሞ ተነግሮ ነበር። በመንፈስ የተቀቡት ክርስቲያኖች ከኢየሱስ ጋር ክብር ለመጎናጸፍ ከመሄዳቸው በፊት የሌሎች በጎች አባላት የሆኑ ወዳጆቻቸውን ለተጨማሪ ኃላፊነቶች ለማሠልጠን ከፍተኛ ፍላጎት አላቸው።
17 በመሠረታዊ ሥርዓት ደረጃ፣ በመዝሙር 71:18 ላይ ‘ኋላ የሚነሣውን ሕዝብ’ ስለ ማስተማር የሚናገረው ሐሳብ አምላክ ከቀባቸው ክርስቲያኖች መመሪያ በሚቀበሉት ሌሎች በጎች ላይም ሊሠራ ይችላል። አረጋውያን፣ በአሁኑ ጊዜ እውነተኛውን አምልኮ ለሚቀበሉ ሰዎች ስለ ይሖዋ የመመሥከር መብት ተሰጥቷቸዋል። (ኢዩኤል 1:2, 3) ሌሎች በጎች ከቅቡዓን ትምህርት በማግኘታቸው እንደተባረኩ የሚሰማቸው ከመሆኑም በላይ ያገኙትን ቅዱስ ጽሑፋዊ ትምህርት ይሖዋን ማገልገል ለሚፈልጉ ሰዎች ለማካፈል ይነሳሳሉ።—ራእይ 7:9, 10
18, 19. (ሀ) አረጋውያን የሆኑ በርካታ የይሖዋ አገልጋዮች ምን ውድ ታሪኮች ሊያካፍሉን ይችላሉ? (ለ) በዕድሜ የገፉ ክርስቲያኖች ስለ ምን ነገር እርግጠኞች መሆን ይችላሉ?
18 በመንፈስ የተቀቡም ሆኑ የሌሎች በጎች አባላት የሆኑ በዕድሜ የገፉ የይሖዋ አገልጋዮች ወሳኝ የሆኑ ታሪካዊ ክንውኖች ሲፈጸሙ ተመልክተዋል። “የፍጥረት ፎቶ ድራማ” የተባለው ፊልም መጀመሪያ ላይ በታየበት ወቅት ከነበሩት ክርስቲያኖች መካከል ጥቂቶቹ አሁንም በሕይወት አሉ። አንዳንድ በዕድሜ የገፉ ክርስቲያኖች፣ በ1918 የታሰሩትን ኃላፊነት የነበራቸው ወንድሞች በግለሰብ ደረጃ ያውቋቸዋል። ሌሎች ደግሞ ደብልዩ ቢ ቢ አር በተባለው የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር የሬዲዮ ጣቢያ ውስጥ ፕሮግራም ያስተላልፉ ነበር። በርካታ አረጋውያን ከይሖዋ ምሥክሮች ሃይማኖታዊ ነጻነት ጋር የተያያዙ ጉዳዮች በከፍተኛ ፍርድ ቤቶች የቀረቡበትን ጊዜ ያስታውሳሉ። አምባገነናዊ አገዛዝ ባለባቸው አገሮች ውስጥ እውነተኛውን አምልኮ በመደገፍ ጸንተው የቆሙም አሉ። በእርግጥም በዕድሜ የገፉ ክርስቲያኖች የእውነት እውቀት እንዴት ቀስ በቀስ እንደተገለጠ ማውሳት ይችላሉ። መጽሐፍ ቅዱስ በርካታ ተሞክሮዎች ካላቸው ከእነዚህ አረጋውያን ጥቅም እንድናገኝ ያበረታታናል።—ዘዳግም 32:7
19 አረጋውያን ክርስቲያኖች ለወጣቶች ግሩም ምሳሌ እንዲሆኑ ተመክረዋል። (ቲቶ 2:2-4) እናንተ አረጋውያን የምታሳዩት ጽናት፣ የምታቀርቧቸው ጸሎቶች እንዲሁም የምትሰጧቸው ምክሮች በሌሎች ላይ የሚያሳድሩትን በጎ ተጽዕኖ በአሁኑ ጊዜ አትመለከቱ ይሆናል። ኖኅ፣ አብርሃም፣ ዮሴፍ፣ ሙሴና ሌሎች የአምላክ አገልጋዮች ያሳዩት ታማኝነት በሚመጣው ትውልድ ላይ ምን ያህል በጎ ተጽዕኖ እንዳሳደረ ማወቅ አይችሉም ነበር። ያም ሆኖ በእምነትና በጽናት ረገድ የተዉልን ውርስ ከፍተኛ ተጽዕኖ አሳድሯል፤ የእናንተም ምሳሌነት በመጭው ትውልድ ላይ ተመሳሳይ ተጽዕኖ ያሳድራል።
20. ተስፋቸውን እስከ መጨረሻው አጽንተው የሚይዙ ምን በረከት ያገኛሉ?
20 ‘ታላቁን መከራ’ በሕይወት አልፋችሁም ሆነ ትንሣኤ አግኝታችሁ “እውነተኛ የሆነውን ሕይወት” ማጣጣም ምንኛ አስደሳች ይሆናል! (ማቴዎስ 24:21፤ 1 ጢሞቴዎስ 6:19) በክርስቶስ የሺህ ዓመት ግዛት ወቅት፣ ይሖዋ እርጅና ያስከተላቸውን ውጤቶች የሚያስወግድበት ጊዜ ይታያችሁ። ሰውነታችን ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሽቆለቆለ መሄዱ ይቀርና በየዕለቱ ጠዋት ስንነሳ ኃይላችን፣ የማየትና የመስማት ችሎታችን እንዲሁም መልካችን ይታደሳል! (ኢዮብ 33:25፤ ኢሳይያስ 35:5, 6) በአምላክ አዲስ ዓለም ውስጥ የመኖር መብት ያገኙ ሁሉ ወደፊት ከሚኖራቸው ዘላለማዊ ሕይወት አንጻር ሁልጊዜ ወጣት ሊባሉ ይችላሉ። (ኢሳይያስ 65:22) እንግዲያው ሁላችንም ተስፋችንን እስከ መጨረሻው አጽንተን እንያዝ፤ እንዲሁም ይሖዋን በሙሉ ነፍስ ማገልገላችንን እንቀጥል። ይሖዋ ቃል የገባልንን ነገሮች ምንም ሳያስቀር እንደሚፈጽምና የሚያደርግልን ነገሮችም ከጠበቅነው በላይ እንደሚሆኑ እርግጠኞች መሆን እንችላለን።—መዝሙር 37:4፤ 145:16
ምን ብለህ ትመልሳለህ?
• አረጋዊው ኖኅ ያሳየው ጽናት ለሰው ዘሮች በሙሉ በረከት ያስገኘው እንዴት ነው?
• የጥንት የአምላክ አገልጋዮች ያሳዩት እምነት በልጆቻቸው ላይ ምን በጎ ተጽዕኖ አሳድሯል?
• ዮሴፍ፣ ሙሴ፣ ኢያሱና ሳሙኤል በዕድሜ በገፉበት ወቅት የእምነት አጋሮቻቸውን ያበረታቱት እንዴት ነበር?
• አረጋውያን ምን ውርስ ማስተላለፍ ይችላሉ?
[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]
[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የአብርሃም መጽናት በይስሐቅ ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ አሳድሯል
[በገጽ 28 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ሙሴ የሰጠው ብስለት የተንጸባረቀበት ምክር ኢያሱን አበረታትቶታል
[በገጽ 29 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ስለ ሌሎች የምታቀርቧቸው ጸሎቶች ጥሩ ውጤት ሊያስገኙ ይችላሉ
[በገጽ 30 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ወጣቶች ታማኝ የሆኑ አረጋውያንን በማዳመጥ ይጠቀማሉ