በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

አገልግሎታችንን ለመፈጸም ቁርጥ ውሳኔ አድርገናል

አገልግሎታችንን ለመፈጸም ቁርጥ ውሳኔ አድርገናል

የሕይወት ታሪክ

አገልግሎታችንን ለመፈጸም ቁርጥ ውሳኔ አድርገናል

ሊና ዳቪሰን እንደተናገረችው

የአውሮፕላኑ አብራሪ “ማየት እያቃተኝ ነው። ምንም ነገር ማየት አልቻልኩም” በማለት በግልጽ በማይሰማ መንገድ ተናገረ። ከጥቂት ደቂቃዎች በኋላ እጆቹ የአውሮፕላኑን መቆጣጠሪያዎች ለቅቀው ተዝለፈለፉና ራሱን ሳተ። አውሮፕላን የማብረር ችሎታ ያልነበረው ባለቤቴ አብራሪው እንዲነቃ ለማድረግ ይታገል ጀመር። ከሞት እንዴት እንደተረፍን ከመግለጼ በፊት በምድር ላይ በጣም ሩቅ ከሆኑት ቦታዎች አንዱ በሆነው በፓፑዋ ኒው ጊኒ የአየር ክልል ላይ በሚበርር ትንሽ አውሮፕላን ለምን እንደተሳፈርን ልንገራችሁ።

የተወለድኩት በ1929 አውስትራሊያ ውስጥ ሲሆን ያደግሁት የኒው ሳውዝ ዌልስ ዋና ከተማ በሆነችው በሲድኒ ነው። አባቴ ቢል ሙስካት ይባላል፤ ኮሚኒስት ቢሆንም በአምላክ ያምን ነበር። እንዲያውም በ1938፣ ከይሖዋ ምሥክሮች ዋና መሥሪያ ቤት የመጣው ጆሴፍ ፍራንክሊን ራዘርፎርድ በሲድኒ ከተማ ምክር ቤት አዳራሽ ውስጥ ለመስበክ እንዲፈቀድለት በሚጠይቀው አገር አቀፍ ማመልከቻ ላይ ለመፈረም ተስማምቶ ነበር።

በወቅቱ አባዬ “የሚናገረው አንድ ቁም ነገር ይኖረዋል” ብሎን ነበር። ከስምንት ዓመታት በኋላ የዚያን መልእክት ፍሬ ሐሳቦች ተማርን። አባዬ፣ ኖርማን ቤሎቲ የተባለውን አቅኚ ወይም የሙሉ ጊዜ ወንጌላዊ የሆነ የይሖዋ ምሥክር ቤታችን መጥቶ ስለ መጽሐፍ ቅዱስ እንዲያወያየን ጋበዘው። ከዚያም ቤተሰባችን ወዲያው የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ተቀበለና ብዙም ሳይቆይ በክርስቲያናዊ አገልግሎት በቅንዓት መሳተፍ ጀመረ።

በ1940ዎቹ አጋማሽ ላይ በጠና የታመመችውን እናቴን ለመርዳት ስል ትምህርቴን አቋረጥኩ። በወቅቱ ኑሯችንን ለመደጎም ስል ልብስም እሰፋ ነበር። ሁልጊዜ ቅዳሜ አመሻሹ ላይ እኔና እህቴ ሮዝ ከተወሰኑ አቅኚዎች ጋር ሆነን በሲድኒ ከተማ ምክር ቤት አዳራሽ አካባቢ መንገድ ላይ እንመሰክር ነበር። በ1952 ታላቅ ወንድሜ ጆን በዩናይትድ ስቴትስ ከሚገኘው ጊልያድ የሚስዮናውያን ማሠልጠኛ ትምህርት ቤት ተመረቀና ፓኪስታን ውስጥ እንዲያገለግል ተመደበ። እኔም አገልግሎት በጣም እወድ ስለነበር የእርሱን ፈለግ የመከተል ፍላጎት አደረብኝ። በመሆኑም በቀጣዩ ዓመት የዘወትር አቅኚ ሆንኩ።

ትዳርና የሚስዮናዊነት አገልግሎት

ከዚያ ብዙም ሳይቆይ አውስትራሊያ በሚገኘው የይሖዋ ምሥክሮች ቅርንጫፍ ቢሮ ውስጥ ከሚያገለግለው ጆን ዳቪሰን ጋር ተዋወቅሁ። ትሕትናው፣ ቆራጥነቱና ጠንካራ የሥነ ምግባር አቋሙ ማረከኝ። በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት ክርስቲያናዊ የገለልተኝነት አቋሙን በመጠበቁ ምክንያት ሦስት ጊዜ ታስሮ ነበር። አንድ ላይ ሆነን በክርስቲያናዊው አገልግሎት ዕድሜያችንን በሙሉ ለመካፈል ወሰንን።

ሰኔ 1955 ከጆን ጋር ተጋባን። ከዚያም በአውስትራሊያ አካባቢ በሚገኙ ገለልተኛ ቦታዎች ለመስበክ እንዲረዳን በማሰብ አንድ አውቶብስ ገዛን፤ አውቶብሱን የገዛነው ተንቀሳቃሽ ቤት እንዲሆነን ልንቀይረው አስበን ነው። በቀጣዩ ዓመት ኒው ጊኒ በመሄድ እንዲሰብኩ ለይሖዋ ምሥክሮች ጥሪ ቀረበ፤ ኒው ጊኒ ያለው በሰሜን አውስትራሊያ በሚገኝ አንድ ትልቅ ደሴት ላይ በስተ ሰሜን ምሥራቅ ነው። a በወቅቱ የመንግሥቱ መልእክት በዚህ የዓለም ክፍል አልተሰበከም ነበር፤ እኛም ወዲያውኑ ራሳችንን በፈቃደኝነት አቀረብን።

በወቅቱ አንድ ሰው ወደ ኒው ጊኒ ለመግባት የሚችለው ሙሉ ቀን ለመሥራት ከተዋዋለ ብቻ ነበር። በመሆኑም ጆን ሥራ ለማግኘት ጥረት ማድረግ ጀመረ። ብዙም ሳይቆይ በኒው ብሪትን አንድ ጣውላ ፋብሪካ ውስጥ ሥራ አገኘ፤ ኒው ብሪትን የኒው ጊኒ ክፍል የሆነች በጣም ትንሽ ደሴት ናት። ከበርካታ ሳምንታት በኋላ ወደ አዲሱ ምድባችን የተጓዝን ሲሆን ሐምሌ 1956 ራባውል፣ ኒው ብሪትን ደረስን። በራባውል አንድ ጀልባ መጥቶ ወደ ዋተርፎል የባሕር ወሽመጥ እስኪወስደን ድረስ ለስድስት ቀናት መጠበቅ ነበረብን።

በዋተርፎል የባሕር ወሽመጥ ያከናወንነው አገልግሎት

ከበርካታ ቀናት አስቸጋሪ የጀልባ ጉዞ በኋላ ከራባውል በስተ ደቡብ 240 ኪሎ ሜትር ገደማ ርቆ ወደሚገኘው ዋተርፎል የባሕር ወሽመጥ ደረስን። በዚያም ጫካው ተመንጥሮ ትልቅ የጣውላ ፋብሪካ ተቋቁሟል። የዚያን ቀን ማታ የድርጅቱ ሠራተኞች በጠቅላላ በእራት መመገቢያው ጠረጴዛ ዙሪያ ተቀምጠው ሳለ ሥራ አስኪያጁ “በነገራችን ላይ አቶ ዳቪሰንና ወይዘሮ ሊና፣ ድርጅታችን ሠራተኞቹ በሙሉ ሃይማኖታቸውን እንዲያሳውቁ የሚያዝዝ መመሪያ አለው” በማለት ተናገረ።

እንዲህ ዓይነት መመሪያ እንዳልነበረ እርግጠኞች ነበርን፤ ይሁን እንጂ ቀደም ሲል ሲጋራ ለማጨስ ፈቃደኞች ስላልነበርን ጠርጥረውን ነበር። የሆነው ሆኖ ጆን “የይሖዋ ምሥክሮች ነን” በማለት መለሰ። በዚህ ጊዜ ፍጹም ጸጥታ ሰፈነ። እዚያ የነበሩት ሰዎች በሁለተኛው የዓለም ጦርነት የተካፈሉ ከመሆኑም በላይ የይሖዋ ምሥክሮች በጦርነቱ ወቅት በወሰዱት የገለልተኝነት አቋም ምክንያት ለእነርሱ ጥላቻ ነበራቸው። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ሰዎቹ ሁኔታዎች አስቸጋሪ እንዲሆኑብን ለማድረግ አጋጣሚ ይፈልጉ ጀመር።

በመጀመሪያ፣ ማቀዝቀዣና ምድጃ የማግኘት መብት ቢኖረንም ሥራ አስኪያጁ ሁለቱንም ሊሰጠን ፈቃደኛ አልነበረም። በመሆኑም ከማቀዝቀዣ ውጭ መቆየት የማይችሉት ምግቦቻችን ተበላሹብን፤ ምግባችንንም ለማብሰል ጫካ ውስጥ ባገኘነው አሮጌ ምድጃ መጠቀም ግድ ሆኖብን ነበር። ቀጥሎ ደግሞ የአካባቢው ነዋሪዎች ከተቆረጡ ያልቆዩ አትክልቶችን እንዳይሸጡልን ስለተከለከሉ የተገኘውን መመገብ ነበረብን። በተጨማሪም እንደ ሰላይ ስለምንታይ መጽሐፍ ቅዱስን እንደምናስተምር ለማጣራት በጥንቃቄ ይከታተሉን ነበር። ይህ በእንዲህ እያለ እኔ ደግሞ ወባ ያዘኝ።

ይሁን እንጂ አገልግሎታችንን ለመፈጸም ቁርጥ ውሳኔ አድርገን ነበር። በመሆኑም በእንጨት መሰንጠቂያው ውስጥ የሚሠሩና እንግሊዝኛ የሚናገሩ ሁለት የአገሬው ወጣቶች የአገሪቱ ብሔራዊ ቋንቋ የሆነውን ሜላኒዣን ፒጅን እንዲያስተምሩን ጠየቅናቸው። እኛ ደግሞ እነርሱን መጽሐፍ ቅዱስ አስተማርናቸው። ቅዳሜና እሁድ “አገር ለማየት” ብለን ረጅም ጉዞዎችን እናደርግ ነበር። እግረ መንገዳችንን በየመንደሩ ለምናገኛቸው ሰዎች በጥበብ እንመሰክርላቸው የነበረ ሲሆን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶቻችን ደግሞ በማስተርጎም ይረዱን ነበር። በጉዟችን ላይ ወንዞችን ስናቋርጥ ደራሽ ውኃ ያጋጥመን የነበረ ከመሆኑም በላይ በወንዞቹ ዳርቻ ላይ ፀሐይ የሚሞቁ ትላልቅ አዞዎችን እንመለከት ነበር። ከአደጋ ለጥቂት ከተረፍንበት አንድ አጋጣሚ በስተቀር እነዚህ አስፈሪ እንስሳት አስቸግረውን አያውቁም።

ለማስተማር የሚረዱ መሣሪያዎችን ማዘጋጀት

አገልግሎታችን እየሰፋ ሲሄድ ቀለል ያሉ የመጽሐፍ ቅዱስ መልእክቶችን በጽሕፈት መኪና ጽፈን ፍላጎት ላላቸው ሰዎች ለማሰራጨት ወሰንን። በእንጨት መሰንጠቂያው ውስጥ ይሠሩ የነበሩት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶቻችን በዚህ መንገድ ያዘጋጀነውን የመጀመሪያውን ጽሑፍ ለመተርጎም እንድንችል ረድተውናል። ለበርካታ ምሽቶች በመቶዎች የሚቆጠሩ ትራክቶችን በጽሕፈት መኪና ስንተይብ ከቆየን በኋላ ጽሑፎቹን ለአካባቢው ነዋሪዎችና በዚያ በኩል ለሚያልፉ የጀልባ ሠራተኞች እናሰራጭ ነበር።

በ1957 በተጓዥ የበላይ ተመልካችነት ተሞክሮ ያካበተው ጆን ካትፎርዝ የሚያበረታታ ጉብኝት አደረገልን። b ማንበብ ለማይችሉ ሰዎች የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ለማስተማር በሥዕሎች መጠቀም ውጤታማ ሊሆን እንደሚችል ነገረን። በመሆኑም እርሱና ባለቤቴ መሠረታዊ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶችን ለማብራራት የሚረዱ ቀለል ያሉ ሥዕሎችን ማዘጋጀት ጀመሩ። ከጊዜ በኋላ ለበርካታ ሰዓታት ቁጭ ብለን እነዚህን ለስብከት የሚረዱ ሥዕሎች ወደ መማሪያ ደብተሮች ገለበጥናቸው። እያንዳንዱ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪ ለሌሎች ለመስበክ እንዲጠቀምበት አንድ የዚህ ዓይነት ደብተር እንሰጠው ነበር። ቀስ በቀስ ይህ የማስተማሪያ ዘዴ በመላ አገሪቱ ጥቅም ላይ ዋለ።

በዋተርፎል የባሕር ወሽመጥ ለሁለት ዓመት ተኩል ካገለገልን በኋላ የሥራ ውላችን የተጠናቀቀ ቢሆንም በአገሪቱ እንድንቆይ ተፈቀደልን። በመሆኑም ልዩ አቅኚዎች እንድንሆን የቀረበልንን ግብዣ ተቀበልን።

ወደ ራባውል ተመለስን

ሰሜናዊውን አቅጣጫ ተከትለን ወደ ራባውል ስንጓዝ የኮኮናትና የካካዋ እርሻ በሚገኝበት በዋይድ የባሕር ወሽመጥ አንድ ቀን አደርን። የዚህ እርሻ ባለቤት የሆኑት አረጋውያን ባልና ሚስት ሥራቸውን አቁመው ወደ አውስትራሊያ ለመመለስ ስለፈለጉ ጆን ይህን እርሻቸውን እንዲያስተዳድርላቸው ጠየቁት። ይህ የሥራ ግብዣ በጣም ፈታኝ ነበር፤ ይሁንና የዚያኑ ቀን ማታ ከጆን ጋር ስለ ሁኔታው ስንወያይ ወደ ኒው ጊኒ የመጣነው ቁሳዊ ሀብት ለማሳደድ እንዳልሆነ ተስማማን። በአቅኚነት አገልግሎታችን ለመቀጠል ቆርጠን ነበር። በመሆኑም በቀጣዩ ቀን ለሰዎቹ ውሳኔያችንን አሳወቅንና በጀልባ ጉዟችንን ቀጠልን።

ራባውል ስንደርስ ከተለያዩ አገሮች ወደዚህ ቦታ ከመጡ ጥቂት የይሖዋ ምሥክሮች ጋር ተገናኘን። የአካባቢው ነዋሪዎች ለመንግሥቱ መልእክት ከፍተኛ ፍላጎት ስለነበራቸው በርካታ ሰዎችን መጽሐፍ ቅዱስ ማስጠናት ጀመርን። በአካባቢው በተከራየነው አንድ አዳራሽ ውስጥ ክርስቲያናዊ ስብሰባዎችን ማድረግ የጀመርን ሲሆን በስብሰባዎቹ ላይ እስከ 150 የሚደርሱ ሰዎች ይገኙ ነበር። ከእነዚህ መካከል አብዛኞቹ እውነትን የተቀበሉ ሲሆን የአምላክን መንግሥት ምሥራች ወደ ሌሎቹ የአገሪቱ ክፍሎች ለማዳረስ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ አበርክተዋል።—ማቴዎስ 24:14

በተጨማሪም ከራባውል 50 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው ቩናባል የተባለች መንደር ውስጥ ለመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ከፍተኛ ፍላጎት ያሳዩ ሰዎች ስለነበሩ እየሄድን እንጎበኛቸው ነበር። ብዙም ሳይቆይ እነዚህ ሰዎች በአካባቢው ተደማጭነት ያለውን የአንድ ካቶሊክ ትኩረት መሳባቸው አልቀረም። ይህ ሰው ከቤተ ክርስቲያን ጓደኞቹ ጋር በመሆን ሳምንታዊውን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናታችንን ከመረበሹም በላይ መንደሩን ለቅቀን እንድንወጣ አስገደደን። በቀጣዩ ሳምንት በምናደርገው ስብሰባ ላይም የበለጠ እንደሚያስቸግሩን ስናውቅ ፖሊሶች አብረውን እንዲሄዱ ጠየቅን።

የዚያን ቀን የተቃውሞ ጩኸት የሚያሰሙ ካቶሊኮች መንገዱን ሞልተውት ነበር። አብዛኞቹ በድንጋይ ሊወግሩን ተዘጋጅተው ነበር። አንድ ቄስ ደግሞ በመቶዎች የሚቆጠሩ የመንደሩን ነዋሪዎች ሰበሰበ። ፖሊሶች ስብሰባ የማካሄድ መብት እንዳለን የገለጹልን ሲሆን ሰዎቹ መንገድ እንዲለቅቁልን በማድረግ በመካከላቸው አሳለፉን። ይሁን እንጂ ስብሰባችንን እንደጀመርን ቄሱ ሕዝቡን በመቀስቀስ እንዲረብሹን አደረጋቸው። ፖሊሶች ሕዝቡን መቆጣጠር ስላልቻሉ የፖሊስ አዛዡ ቦታውን እንድንለቅ በማሳሰብ በፍጥነት ወደ መኪናችን ወሰደን።

ሰዎቹ ከበውን ሲሰድቡን፣ ሲተፉብን እንዲሁም በጡጫ ሊመቱን ሲዝቱብን ቄሱ እጆቹን አጣምሮ በመቆም ይስቅብን ነበር። ከዚህ ቦታ ካመለጥን በኋላ የፖሊስ አዛዡ የዚህን ያህል የከፋ ሁኔታ አጋጥሞት እንደማያውቅ ተናገረ። አብዛኞቹ የቩናባል ነዋሪዎች በተነሳው የሕዝብ ዓመፅ ምክንያት ፍርሃት ስላደረባቸው ለእውነት አቋም ባይወስዱም አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ግን የመንግሥቱን እውነት በድፍረት ደግፏል። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ በመላው ኒው ብሪትን የሚገኙ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች አቋም ወስደዋል።

ኒው ጊኒ መግባት ቻልን

በኅዳር ወር 1960 በዋናው ደሴት በኒው ጊኒ ሰሜናዊ ጠረፍ በምትገኘው ማዳንግ የተባለች ትልቅ ከተማ ውስጥ እንድናገለግል ተመደብን። በዚህ ቦታ እኔና ጆን በርካታ የሙሉ ቀን ሥራዎችን የማግኘት አጋጣሚዎች ነበሩን። አንድ ድርጅት የልብስ መደብሩን እንድቆጣጠርለት አጥብቆ ጠየቀኝ። ሌላ ድርጅት ደግሞ ደንበኞች የገዟቸውን ልብሶች እንዳስተካክል ፈልጎ ነበር። ከውጭ አገር የመጡ አንዳንድ ሴቶች ሱቅ ከፍቼ የሴቶች ልብስ እንድሰፋ የገንዘብ ድጋፍ ሊያደርጉልኝ ፈልገው ነበር። ዓላማችንን ስላልረሳን እነዚህንም ሆነ ሌሎች የሥራ ግብዣዎችን እንደማንቀበል በትሕትና ገልጸንላቸዋል።—2 ጢሞቴዎስ 2:4

የማዳንግ የአገልግሎት ክልል ፍሬያማ ስለነበር ብዙም ሳይቆይ ጥሩ እድገት የሚያደርግ አንድ ጉባኤ ተቋቋመ። በእግራችንና በሞተር ብስክሌት ራቅ ብለው ወደሚገኙ መንደሮች በመሄድ ለበርካታ ቀናት እንሰብክ ነበር። በጉዟችን ወቅት ሰዎች በማይኖሩባቸው ጎጆ ቤቶች ውስጥ ከጫካው በታጨዱ የሣር ክምሮች ላይ እንተኛ ነበር። ወደዚህ ቦታ ስንሄድ የምንይዘው ነገር ቢኖር የታሸጉ ምግቦች፣ ብስኩቶችና የወባ መከላከያ አጎበር ብቻ ነበር።

በአንድ ወቅት እንዲህ ዓይነት ጉዞ ስናደርግ፣ ከማዳንግ በስተ ሰሜን 50 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኝ ታሊዲግ የምትባል መንደር ውስጥ የሚኖሩ ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ለማወቅ ፍላጎት ያላቸው የተወሰኑ ሰዎችን ጎብኝተን ነበር። ይህ ቡድን በመንፈሳዊ እያደገ ሲሄድ በአካባቢው የሚገኝ የአንድ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር የሕዝብ በሆኑ ቦታዎች መጽሐፍ ቅዱስን እንዳያጠኑ ከለከላቸው። በኋላ ላይ ይህ ርዕሰ መምህር፣ ፖሊሶች የእነዚህን ሰዎች ቤት እንዲያፈርሱባቸውና ወደ ጫካ እንዲያባርሯቸው አደረገ። ይሁንና በአቅራቢያው የሚገኝ መንደር አለቃ የሆነው ግለሰብ ቡድኑ በእርሱ መንደር ውስጥ እንዲኖር ፈቀደ። ከጊዜ በኋላ ይህ ደግ አለቃ የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ተቀበለ፤ በአሁኑ ጊዜ በዚያ አካባቢ ዘመናዊ የመንግሥት አዳራሽ ተገንብቷል።

የትርጉምና የጉብኝት ሥራ

በ1956 ኒው ብሪትን ከደረስን ከሁለት ዓመት በኋላ እኔና ጆን የተለያዩ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችን ወደ ሜላኒዣን ፒጅን ቋንቋ በመተርጎም ሥራ እንድንካፈል ተጋበዝን። ይህ ሥራ ለዓመታት የዘለቀ ነበር። ከዚያም በ1970 የፓፑዋ ኒው ጊኒ ዋና ከተማ በሆነችው በፖርት ሞርስቢ በሚገኘው ቅርንጫፍ ቢሮ ውስጥ በትርጉም ሥራ ሙሉ ጊዜ እንድናገለግል ተጋበዝን። ከዚህም በተጨማሪ ቋንቋ እናስተምር ነበር።

በ1975 በጉብኝት ሥራ ለማገልገል ወደ ኒው ብሪትን ተመለስን። ለቀጣዩቹ 13 ዓመታት በእያንዳንዱ የአገሪቱ ክፍል ማለት ይቻላል በአውሮፕላን፣ በጀልባ፣ በመኪና ወይም በእግር ተጉዘናል። በዚህ ርዕስ መግቢያ ላይ የተጠቀሰውን ጨምሮ ከአደጋ ለጥቂት የተረፍንባቸው ሌሎች በርካታ አጋጣሚዎች ነበሩ። መግቢያው ላይ በተገለጸው አጋጣሚ ላይ ካንድሪያን፣ ኒው ብሪትን በሚገኘው አየር ማረፊያ ለመድረስ ጥቂት ሲቀረን አውሮፕላን አብራሪው ጨጓራውን በጣም ከመታመሙ የተነሳ ራሱን ሳተ። አውሮፕላኑ በአውቶማቲክ አብራሪ እየተመራ በጫካው ላይ በሚያንዣብብበት ወቅት ጆን አብራሪውን ለማንቃት ይጥር ነበር። በመጨረሻም አብራሪው ነቃና አጥርቶ ማየት ሲችል እንደምንም ብሎ አውሮፕላኑን አሳረፈው። ከዚያም እንደገና ራሱን ሳተ።

ሌላ የሥራ በር ተከፈተ

በ1988 በቅርንጫፍ ቢሮው ውስጥ እያደገ ለመጣው የትርጉም ሥራ እርዳታ እንድናበረክት እንደገና ፖርት ሞርስቢ ተመደብን። በቅርንጫፍ ቢሮው ውስጥ 50 የምንሆን ሰዎች እንደ አንድ ቤተሰብ ሆነን እንኖርና እንሠራ ነበር፤ እኔና ጆን አዳዲስ ተርጓሚዎችንም እናሠለጥን ነበር። ሁላችንም አነስ ያሉ አንድ አንድ ክፍሎች ውስጥ እንኖር ነበር። እኔና ጆን፣ የቤተሰቡ አባላትም ሆኑ እንግዶች ወደ ክፍላችን ጎራ እንዲሉ ለማበረታታት ስንል በሩን ገርበብ አድርገን ለመተው ወሰንን፤ በዚህ መንገድ ከእነርሱ ጋር ይበልጥ መተዋወቅ ችለናል። እንዲህ በማድረጋችን ከቤተሰባችን ጋር በጣም የተቀራረብን ሲሆን አንዳችን ለሌላው ፍቅር ማሳየትና ድጋፍ ማድረግ ችለን ነበር።

በ1993 ጆን በልብ በሽታ ምክንያት ሞተ። የሰውነቴ ክፍል የሞተ ያህል ተሰምቶኝ ነበር። ከጆን ጋር በትዳር 38 ዓመታትን አብረን ያሳለፍን ሲሆን በእነዚህ ጊዜያት ሁሉ በአገልግሎት አብረን ነበርን። ያም ቢሆን ይሖዋ በሚሰጠኝ ኃይል በመታገዝ በአገልግሎቴ ለመቀጠል ቆርጬ ነበር። (2 ቆሮንቶስ 4:7) የክፍሌን በር አሁንም ገርበብ አድርጌ የምተወው ሲሆን ወጣቶችም እኔን ለመጠየቅ መምጣታቸውን አላቋረጡም። እንዲህ ያለው መቀራረብ አዎንታዊ አመለካከት ይዤ እንድቀጥል ረድቶኛል።

ጤንነቴ እያሽቆለቆለ ስለመጣ በ2003 በሲድኒ፣ አውስትራሊያ በሚገኘው ቅርንጫፍ ቢሮ ውስጥ እንዳገለግል ተመደብኩ። በአሁኑ ወቅት 77 ዓመት ቢሆነኝም በትርጉም ሥራ በሙሉ ጊዜ አገለግላለሁ፤ እንዲሁም በስብከቱ ሥራ በትጋት እሳተፋለሁ። ጓደኞቼ፣ መንፈሳዊ ልጆቼና የልጅ ልጆቼ ሁልጊዜ ያስደስቱኛል።

ቤቴል ውስጥ የሚገኘውን የክፍሌን በር አሁንም ክፍት የማደርገው ሲሆን በአብዛኞቹ ቀናት ወንድሞች እየመጡ ይጠይቁኛል። እንዲያውም የክፍሌ በር ከተዘጋ ሰዎች ምን እንደሆንኩ ለማወቅ ያንኳኳሉ። በሕይወት እስካለሁ ድረስ አገልግሎቴን ለመፈጸምና አምላኬን ይሖዋን ለማገልገል ቆርጫለሁ።—2 ጢሞቴዎስ 4:5

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

a በዚያን ጊዜ የደሴቱ ምሥራቃዊ ክፍል በሁለት ተከፍሎ የነበረ ሲሆን በስተ ደቡብ ያለው ፓፑዋ ሲባል በስተ ሰሜን ያለው ደግሞ ኒው ጊኒ ይባል ነበር። በዛሬው ጊዜ በኢንዶኔዥያ የሚተዳደረው የደሴቱ ምዕራባዊ ክፍል ፓፑዋ ተብሎ የሚጠራ ሲሆን ምሥራቃዊው ክፍል ደግሞ ፓፑዋ ኒው ጊኒ ይባላል።

b የጆን ካትፎርዝን የሕይወት ታሪክ በሰኔ 1, 1958 መጠበቂያ ግንብ (እንግሊዝኛ) ከገጽ 333-336 ላይ ተመልከት።

[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በ1973 በሌ፣ ኒው ጊኒ በተካሄደ የአውራጃ ስብሰባ ላይ ከጆን ጋር

[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ካርታ]

(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)

ኒው ጊኒ

አውስትራሊያ

ሲድኒ

ኢንዶኔዥያ

ፓፑዋ ኒው ጊኒ

ታሊዲግ

ማዳንግ

ፖርት ሞርስቢ

ኒው ብሪትን

ራባውል

ቩናባል

ዋይድ የባሕር ወሽመጥ

ዋተርፎል የባሕር ወሽመጥ

[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ካርታና ሉል:- NASA/Visible Earth imagery

[በገጽ 20 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ፓፑዋ ኒው ጊኒ በሚገኘው ቅርንጫፍ ቢሮ በ2002