በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ክፋት—ከቁጥጥር ውጭ ሆኗል?

ክፋት—ከቁጥጥር ውጭ ሆኗል?

ክፋት—ከቁጥጥር ውጭ ሆኗል?

አንድ ትንሽ ልጅ የሆነ ነገር መሬት ላይ ሲመለከት ምንነቱን ለማወቅ በመጓጓት አነሳው፤ ሕፃኑ ያነሳው ነገር ፈንጂ በመሆኑ ዓይኖቹን ያጣ ሲሆን በሰውነቱ ላይም ከባድ ጉዳት ደረሰበት። አንዲት እናት አራስ ልጇን መንገድ ዳር በተጠራቀመ ቆሻሻ ውስጥ ጣለችው። ከሥራ የተባረረ አንድ ሰው ወደ ቀድሞ መሥሪያ ቤቱ ተመልሶ በመሄድ ያገኘውን ሁሉ ከገደለ በኋላ የራሱን ሕይወት አጠፋ። አንድ የተከበሩ ግለሰብ ራሳቸውን መከላከል የማይችሉ ልጆችን በጾታ አስነወሩ።

በዘመናችን እንደነዚህ ያሉ የክፋት ድርጊቶችን መስማት በጣም የተለመደ መሆኑ እጅግ ያሳዝናል። ይበልጥ የሚያሳዝነው ደግሞ እንደ ዘር ማጥፋት ዘመቻዎችና ሽብርተኝነት ያሉት ተግባራት ከላይ ከተገለጹት ድርጊቶች የበለጠ ትኩረት የሚሰጣቸው መሆኑ ነው። በ1995 የታተመ አንድ ጽሑፍ እንዲህ በማለት ዘግቦ ነበር:- “ይህ ምዕተ ዓመት የሰይጣን ዘመን ነበር። ሰዎች በዘር፣ በሃይማኖት ወይም በመደብ ልዩነት የተነሳ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሌሎች ሰዎችን ለመጨፍጨፍ የዚህን ዘመን ያህል በተራቀቀ ዘዴ የተጠቀሙበትና ከፍተኛ ፍላጎት ያሳዩበት ሌላ ወቅት የለም።”

ይህም ሳይበቃ ሰዎች አየሩን እየበከሉ፣ ምድርን እያበላሹ፣ የምድርን የተፈጥሮ ሀብት እያሟጠጡና ሥፍር ቁጥር የሌላቸውን የእንስሳት ዝርያዎች ከምድር ገጽ እያጠፉ ናቸው። የሰው ልጅ እነዚህን የክፋት ድርጊቶች አስወግዶ የምንኖርበት ዓለም የተሻለና አስተማማኝ ቦታ እንዲሆን ማድረግ ይችል ይሆን? ወይስ ይህን ማድረግ ማዕበልን በመጥረጊያ ለመመለስ እንደመሞከር ይሆን? ከክፋት ጋር በተያያዘ በርካታ የሥነ ጽሑፍ ሥራዎችን ያዘጋጁ አንድ ፕሮፌሰር “በዓለም ላይ ለውጥ ለማምጣት ማለትም ዓለምን ለማሻሻል ከፍተኛ ፍላጎት ነበረኝ። ሆኖም በዓለም ላይ የጎላ ለውጥ አይታይም” ብለዋል። አንተም እንዲህ ይሰማህ ይሆናል።

ዓለማችን ያለችበት ሁኔታ፣ ከዕለት ወደ ዕለት ማዕበሉ ወደሚጨምርና ይበልጥ አደገኛ ወደሚሆን ባሕር እያመራች ካለች መርከብ ጋር ሊመሳሰል ይችላል። ማንም ሰው በዚያ በኩል መጓዝ ባይፈልግም የመርከቧን አቅጣጫ ለመቀየር የተደረጉ ጥረቶች በሙሉ መና ሆነው ቀርተዋል። መርከቧን ማንም ሊያቆማት ስላልቻለ አደገኛ ወደሆነው ማዕበል እየተጓዘች ነው።

ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ ላለው ለዚህ ሁኔታ በተወሰነ መጠን ምክንያት የሆነው የሰው ልጆች አለፍጽምና ነው። (ሮሜ 3:23) ያም ሆኖ ግን የክፋት ድርጊቶች ይህን ያህል መብዛታቸው፣ በበርካታ ቦታዎች መስፋፋታቸውና ማቆሚያ የሌላቸው መሆኑ ለእነዚህ ድርጊቶች ተጠያቂ የሚሆኑት የሰው ልጆች ብቻ እንዳልሆኑ የሚጠቁም ነው። ታዲያ የሰው ልጅ በአንድ የማይታይና ኃይለኛ የሆነ ክፉ አካል ቁጥጥር ሥር ይሆን? ከሆነ ይህ ኃይል ምንድን ነው? ራሳችንን ከዚህ ክፉ ኃይል መጠበቅ የምንችለው እንዴት ነው? በሚቀጥለው ርዕስ ላይ ለእነዚህ ጥያቄዎች መልስ እናገኛለን።

[በገጽ 3 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]

© Heldur Netocny/Panos Pictures