በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የሰቆቃወ ኤርምያስ መጽሐፍ ጎላ ያሉ ነጥቦች

የሰቆቃወ ኤርምያስ መጽሐፍ ጎላ ያሉ ነጥቦች

የይሖዋ ቃል ሕያው ነው

የሰቆቃወ ኤርምያስ መጽሐፍ ጎላ ያሉ ነጥቦች

ነቢዩ ኤርምያስ ለ40 ዓመታት ሲያውጀው የቆየው የፍርድ መልእክት ፍጻሜውን ሲያገኝ ተመለከተ። ነቢዩ የሚወዳት ከተማ ስትጠፋ ሲያይ ምን ተሰምቶት ይሆን? በግሪክኛው ሰብዓ ሊቃናት ትርጉም ላይ የሰቆቃወ ኤርምያስ መጽሐፍ መግቢያ እንዲህ ይላል:- “ኤርምያስ ቁጭ ብሎ ካለቀሰ በኋላ እንደሚከተለው በማለት ስለ ኢየሩሳሌም የሐዘን እንጉርጉሮ አወረደ።” ለአንድ ዓመት ከስድስት ወር የዘለቀው የኢየሩሳሌም ከበባና የከተማዋ መቃጠል ያሳደረበት ስሜት ከኤርምያስ አእምሮ ሳይጠፋ በ607 ከክርስቶስ ልደት በፊት የተጻፈው የሰቆቃወ ኤርምያስ መጽሐፍ ይህ ነቢይ የተሰማውን ጥልቅ ሐዘን በሚገባ ይገልጻል። (ኤርምያስ 52:3-5, 12-14) በታሪክ ውስጥ እንዲህ ያለ አሳዛኝና ልብ የሚነካ የሐዘን እንጉርጉሮ የተጻፈላት ሌላ ከተማ አናገኝም።

የሰቆቃወ ኤርምያስ መጽሐፍ የጸሐፊውን ስሜት የሚገልጹ አምስት ግጥሞች ስብስብ ነው። የመጀመሪያዎቹ አራት ግጥሞች የሐዘን እንጉርጉሮ ወይም ሙሾ ሲሆኑ አምስተኛው ደግሞ ልመና ወይም ጸሎት ነው። የመጀመሪያዎቹ አራት መዝሙራት በፊደል ቅደም ተከተል የተጻፉ ሲሆን እያንዳንዱ ቁጥር የሚጀምረው በ22ቱ የዕብራይስጥ ፊደላት ቅደም ተከተል መሠረት ነው። አምስተኛው መዝሙር ግን 22 ቁጥሮች ቢኖሩትም በዕብራይስጥ ፊደላት ቅደም ተከተል መሠረት አልተቀመጠም።—ሰቆቃወ ኤርምያስ 5:1

“ዓይኔ በእንባ ደከመች”

(ሰቆቃወ ኤርምያስ 1:1 እስከ 2:22)

“በሕዝብ ተሞልታ የነበረችው ከተማ፣ እንዴት የተተወች ሆና ቀረች! በሕዝቦች መካከል ታላቅ የነበረችው፣ እርሷ እንዴት እንደ መበለት ሆነች! በአውራጃዎች መካከል ልዕልት የነበረችው፣ አሁን ባሪያ ሆናለች።” ነቢዩ ኤርምያስ ኢየሩሳሌምን አስመልክቶ ያሰማው የሐዘን እንጉርጉሮ የሚጀምረው በዚህ መንገድ ነው። ነቢዩ በከተማዋ ላይ እንዲህ ያለ መከራ የመጣበትን ምክንያት ሲገልጽ “ከኀጢአቷ ብዛት የተነሣ፣ እግዚአብሔር ከባድ ሐዘን አምጥቶባታል” ብሏል።—ሰቆቃወ ኤርምያስ 1:1, 5

ባሏንና ልጆቿን በሞት ባጣች መበለት የተመሰለችው ኢየሩሳሌም “የእኔን መከራ የመሰለ መከራ አለን?” በማለት ጠይቃለች። ጠላቶቿንም አስመልክታ እንዲህ በማለት ወደ አምላክ ጸልያለች:- “ክፋታቸው ሁሉ በፊትህ ይቅረብ፤ ከኀጢአቴ ሁሉ የተነሣ፣ በእኔ ላይ እንዳደረግኽብኝ፣ በእነርሱም ላይ አድርግባቸው፤ የሥቃይ ልቅሶዬ በዝቶአል፤ ልቤም ደክሞአል።”—ሰቆቃወ ኤርምያስ 1:12, 22

ኤርምያስ በጣም ስለተጨነቀ እንዲህ ብሏል:- “በጽኑ ቍጣው፣ የእስራኤልን ቀንድ ሁሉ ሰበረ፤ ጠላት በተቃረበ ጊዜ፣ ቀኝ እጁን ወደ ኋላ መለሰ፤ በዙሪያው ያለውን ሁሉ እንደሚበላ እሳት፣ በያዕቆብ ላይ የእሳት ነበልባል ነደደ።” ይህ ነቢይ የተሰማውን ጥልቅ ሐዘን ሲገልጽ “ዓይኔ በእንባ ደከመች፣ አንጀቴም ታወከ፤ . . . ጉበቴ በምድር ላይ ተዘረገፈ (የ1954 ትርጉም)” ብሏል። መንገድ ተላላፊዎች እንኳ “የውበት መደምደሚያ፣ የምድር ሁሉ ደስታ፣ የተባለች ከተማ ይህች ናትን?” በማለት መገረማቸውን ገልጸዋል።—ሰቆቃወ ኤርምያስ 2:3, 11, 15

ቅዱስ ጽሑፋዊ ጥያቄዎችና መልሶቻቸው:-

1:15 NW—ይሖዋ ‘የድንግሊቱን የይሁዳ ሴት ልጅ የወይን መጭመቂያ የረገጠው’ እንዴት ነው? ባቢሎናውያን እንደ ድንግል ተደርጋ የተገለጸችውን ከተማ ሲያጠፉ በጣም ብዙ ደም በማፍሰሳቸው ሁኔታው በመጭመቂያ ውስጥ ወይን ከመርገጥ ጋር ተመሳስሏል። ይሖዋ ይህንን ሁኔታ አስቀድሞ የተናገረ ከመሆኑም በላይ ትንቢቱ እንዲፈጸም በመፍቀዱ እርሱ ‘የወይን መጭመቂያውን እንደረገጠው’ ተደርጎ ሊገለጽ ይችላል።

2:1 የ1954 ትርጉም—‘የእስራኤል ውበት ከሰማይ ወደ ምድር የተጣለው’ እንዴት ነበር? ‘ሰማያት ከምድር ከፍ ያሉ’ በመሆናቸው የተከበሩ ነገሮች መዋረዳቸውን ለማመልከት ‘ከሰማይ ወደ ምድር እንደተጣሉ’ ተደርጎ አንዳንድ ጊዜ ይገለጻል። ‘የእስራኤል ውበት’ የተባለው ከተማዋ የይሖዋን ሞገስ አግኝታ በነበረችበት ወቅት የነበራት ክብርና ኃይል ሲሆን ኢየሩሳሌም ስትጠፋና ይሁዳ ባድማ ስትሆን ይህ ክብሯና ኃይሏ እንዳልነበረ ሆኗል።—ኢሳይያስ 55:9

2:1, 6—የይሖዋ ‘የእግር መቀመጫ’ እና ‘ማደሪያ [“ዳስ፣” NW]’ ተብሎ የተገለጸው ምንድን ነው? መዝሙራዊው “ወደ ማደሪያው እንግባ፤ እግሮቹ በሚቆሙበት ቦታ እንስገድ” በማለት ዘምሯል። (መዝሙር 132:7) በመሆኑም በ⁠ሰቆቃወ ኤርምያስ 2:1 ላይ የተገለጸው ‘የእግሩ መቀመጫ’ የይሖዋን የአምልኮ ቤት ወይም ቤተ መቅደሱን ያመለክታል። ባቢሎናውያን “የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ” በአትክልት ሥፍራ እንዳለ ዳስ ወይም ተራ ጎጆ ‘በእሳት አቃጥለውታል።’—ኤርምያስ 52:12, 13

2:17—ይሖዋ፣ ከኢየሩሳሌም ጋር በተያያዘ የፈጸመው ‘ቃል’ ምንድን ነው? እዚህ ላይ የተገለጸው ቃል በ⁠ዘሌዋውያን 26:17 ላይ የሚገኘውን “በጠላቶቻችሁ ድል እንድትሆኑ ፊቴን በእናንተ ላይ አከብድባችኋለሁ፤ የሚጠሏችሁ ይገዟችኋል፤ ማንም ሳያሳድዳችሁም ትሸሻላችሁ” የሚለውን ሐሳብ የሚያመለክት ሳይሆን አይቀርም።

ምን ትምህርት እናገኛለን?

1:1-9 ኢየሩሳሌም በሌሊት አምርራ ታለቅሳለች፤ እንባዋም በጉንጮቿ ላይ ይወርዳል። በበሮቿ የሚገባና የሚወጣ የለም፤ ካህናቷም ይቃትታሉ። ደናግሏ ክፉኛ አዝነዋል፤ እርሷም በምሬት ትሠቃያለች። ይህ የሆነው ለምንድን ነው? ኢየሩሳሌም ከባድ ኀጢአት በመሥራቷ ነው። ርኵሰቷ በቀሚሷ ላይ ታይቷል። ኃጢአት ደስታ አያስገኝም፤ ከዚህ ይልቅ እንባ፣ መቃተት፣ ሐዘንና ምሬት ያስከትላል።

1:18 ይሖዋ ኃጢአተኞችን በመቅጣት ረገድ ምንጊዜም ቢሆን ትክክለኛና ጻድቅ ነው።

2:20 እስራኤላውያን ይሖዋን ካልታዘዙ እርግማን እንደሚደርስባቸው ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷቸው ነበር፤ ከእርግማኖቹ መካከል ‘የወንዶችና የሴቶች ልጆቻቸውን ሥጋ መብላት’ ይገኝበታል። (ዘዳግም 28:15, 45, 53) አምላክን ላለመታዘዝ መምረጥ ምንኛ ጥበብ የጎደለው አካሄድ ነው!

“ከመስማት ጆሮህን አትከልክል”

(ሰቆቃወ ኤርምያስ 3:1 እስከ 5:22)

በ⁠ሰቆቃወ ኤርምያስ ምዕራፍ 3 ላይ የእስራኤል ብሔር እንደ አንድ “ሰው” ተደርጎ ተገልጿል። ይህ ሰው መከራ ቢደርስበትም “እርሱን ተስፋ ለሚያደርጉት፣ ለሚፈልገውም ሰው እግዚአብሔር መልካም ነው” በማለት ዘምሯል። ግለሰቡ ለእውነተኛው አምላክ ባቀረበው ጸሎት ላይ “ልመናዬን ሰምተሃል፤ ‘ርዳታም ፈልጌ ስጮኽ፣ ከመስማት ጆሮህን አትከልክል’” በማለት ጠይቋል። ይሖዋ የጠላቶቻቸውን ወቀሳ ትኩረት ሰጥቶ እንዲሰማ ሲጠይቅም “እግዚአብሔር ሆይ፤ እጆቻቸው ላደረጉት፣ የሚገባውን መልሰህ ክፈላቸው” ብሏል።—ሰቆቃወ ኤርምያስ 3:1, 25, 56, 64

ኤርምያስ፣ ለአንድ ዓመት ከስድስት ወራት የዘለቀው የኢየሩሳሌም ከበባ ያስከተለውን ሰቆቃ በተመለከተ ምን እንደተሰማው ሲገልጽ የሚከተለውን የሐዘን እንጉርጉሮ አሰምቷል:- “በሕዝቤ ላይ የደረሰው ቅጣት፣ የማንም እጅ ሳይረዳት፣ በድንገት ከተገለበጠችው፣ ሰዶም ላይ ከደረሰው ቅጣት ይልቅ ታላቅ ነው።” ኤርምያስ አክሎም “በራብ ከሚሞቱት ይልቅ፣ በሰይፍ የተገደሉት ይሻላሉ፤ ምግብ በሜዳ ላይ ካለማግኘታቸው የተነሣ፣ በራብ ደርቀው ያልቃሉ” ብሏል።—ሰቆቃወ ኤርምያስ 4:6, 9

በአምስተኛው ግጥም ላይ የኢየሩሳሌም ነዋሪዎች እንደሚናገሩ ተደርጎ ተገልጿል። ሕዝቡ “እግዚአብሔር ሆይ፤ በእኛ ላይ የደረሰውን አስብ፤ ውርደታችንን እይ፤ ተመልከትም” ብለዋል። ከዚያም የደረሰባቸውን መከራ በማውሳት የሚከተለውን ልመና አቅርበዋል:- “አቤቱ እግዚአብሔር ሆይ፤ አንተ ለዘላለም ትገዛለህ፤ ዙፋንህ ከትውልድ እስከ ትውልድ ይኖራል። እግዚአብሔር ሆይ፤ ወደ አንተ መልሰን፤ እኛም እንመለሳለን፤ ዘመናችንን እንደ ቀድሞው አድስ።”—ሰቆቃወ ኤርምያስ 5:1, 19, 21

ቅዱስ ጽሑፋዊ ጥያቄዎችና መልሶቻቸው:-

3:16—“ጥርሴን በድንጋይ ሰበረ” የሚለው አገላለጽ ምን ትርጉም አለው? አንድ የማመሳከሪያ ጽሑፍ እንዲህ ይላል:- “አይሁዳውያን በግዞት በሚወሰዱበት ወቅት ዳቧቸውን ጉድጓድ ውስጥ ለመጋገር ስለተገደዱ የሚበሉት ዳቦ ከአሸዋ ጋር የተቀላቀለ ነበር።” አንድ ሰው እንዲህ ዓይነቱን ዳቦ ሲመገብ ጥርሱ ሊሰበር ይችላል።

4:3, 10 የ1954 ትርጉም—ኤርምያስ ‘የወገኑን ልጅ ከምድረ በዳ ሰጎን’ ጋር ያመሳሰላት ለምንድን ነው? ኢዮብ 39:16 ሰጎን “የእርሷ እንዳልሆኑ ሁሉ በልጆቿ ትጨክናለች” ይላል። ለምሳሌ፣ እንቁላሎቹ ከተፈለፈሉ በኋላ እንስቷ ሰጎን ከሌሎች እንስት ሰጎኖች ጋር ለመቀላቀል ስትል እንቁላሎቿን ትታ ትሄዳለች፤ በዚህ ወቅት ልጆቹን የመንከባከቡ ኃላፊነት አባትየው ላይ ይወድቃል። ሰጎኖች አደጋ በሚያጋጥማቸው ጊዜስ ምን ያደርጋሉ? ወንዱም ሆነ ሴቷ ሰጎን ልጆቻቸውን ትተው ይሸሻሉ። በባቢሎናውያን ከበባ ወቅት የኢየሩሳሌም ነዋሪዎች በጣም በመራባቸው፣ በተፈጥሮ ለልጆቻቸው የሚራሩት እናቶች እንኳ እንደ ምድረ በዳ ሰጎን በልጆቻቸው ላይ ጨክነው ነበር። ይህም እንስት ቀበሮዎች ለልጆቻው ከሚያደርጉት እንክብካቤ ፈጽሞ ተቃራኒ ነበር።

5:7—ይሖዋ በአባቶች ኃጢአት ልጆችን ይቀጣል? በፍጹም፤ ይሖዋ አባቶች በሠሩት ኃጢአት የተነሳ ልጆችን በቀጥታ አይቀጣም። መጽሐፍ ቅዱስ “እያንዳንዳችን ስለ ራሳችን ለእግዚአብሔር መልስ እንሰጣለን” ይላል። (ሮሜ 14:12) ይሁን እንጂ ኃጢአት መሥራት በሚያስከትላቸው መዘዞች የተነሳ ቀጣዩ ትውልድም የችግሩ ገፈት ቀማሽ ሊሆን ይችላል። ለአብነት ያህል፣ የጥንቶቹ እስራኤላውያን ጣዖት ማምለካቸው ከእነርሱ በኋላ የኖሩት ታማኝ እስራኤላውያንም ጭምር በጽድቅ መንገድ መጓዝ አስቸጋሪ እንዲሆንባቸው አድርጓል።—ዘፀአት 20:5

ምን ትምህርት እናገኛለን?

3:8, 43, 44 በኢየሩሳሌም ላይ መከራ በደረሰበት ወቅት የከተማዋ ነዋሪዎች ለእርዳታ ወደ ይሖዋ ቢጮኹም እርሱ አልሰማቸውም። ለምን? ሕዝቡ ታዛዥ አልነበረም፤ ንስሐም አልገባም። ይሖዋ ለጸሎታችን ምላሽ እንዲሰጠን ከፈለግን እርሱን መታዘዝ ይገባናል።—ምሳሌ 28:9

3:21-26, 28-33 ከባድ ሥቃይ ቢደርስብንም እንኳ መጽናት የምንችለው እንዴት ነው? ኤርምያስ መልሱን ይነግረናል። ይሖዋ ፍቅራዊ ደግነቱና ምሕረቱ ብዙ እንደሆነ መዘንጋት አይኖርብንም። ከዚህም በላይ በሕይወት መኖራችን በራሱ፣ ተስፋ ላለመቁረጥ በቂ ምክንያት እንደሆነና ሳናጉረመርም ዝም ብለን በትዕግሥት የይሖዋን ማዳን መጠባበቅ እንዳለብን ማስታወስ ይገባናል። እንዲሁም ‘አፋችንን በአፈር ውስጥ ማኖር’ (የ1954 ትርጉም) ማለትም አምላክ ፈተና እንዲደርስብን የፈቀደበት በቂ ምክንያት እንዳለው በመገንዘብ ራሳችንን ዝቅ አድርገን የሚደርሱብንን ፈተናዎች መቀበል ይኖርብናል።

3:27 በወጣትነት የሚያጋጥሙ የእምነት ፈተናዎችን ለመቋቋም መከራዎችንና ፌዝን በጽናት መወጣት ያስፈልግ ይሆናል። ያም ቢሆን “ሰው በወጣትነቱ፣ ቀንበር ቢሸከም መልካም ነው።” እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው? አንድ ሰው በወጣትነቱ የመከራ ቀንበርን መሸከም መማሩ በኋለኞቹ ዓመታት የሚያጋጥሙትን ችግሮች ለመቋቋም ያዘጋጀዋል።

3:39-42 ኃጢአት መሥራታችን መከራ ሲያስከትልብን ‘ማጉረምረም’ የጥበብ አካሄድ አይደለም። ኃጢአት መሥራታችን ያስከተላቸውን መዘዞች በማጨዳችን ከማጉረምረም ይልቅ “መንገዳችንን እንመርምር፤ እንፈትን፤ ወደ እግዚአብሔርም እንመለስ።” ንስሐ ገብተን መንገዳችንን ማስተካከላችን የጥበብ መንገድ ነው።

ይሖዋን መታመኛህ አድርገው

የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል የሆነው የሰቆቃወ ኤርምያስ መጽሐፍ፣ ባቢሎናውያን ኢየሩሳሌምን ካቃጠሉና የይሁዳን ምድር ባድማ ካደረጉ በኋላ ይሖዋ ስለ ከተማዋና ስለ ምድሪቷ ምን እንደተሰማው ይገልጻል። በመጽሐፉ ውስጥ ተመዝግበው የሚገኙት ሕዝቡ ኃጢአት መሥራታቸውን የሚገልጹ ሐሳቦች፣ በይሖዋ አመለካከት እስራኤላውያን መከራ የደረሰባቸው በጥፋታቸው እንደሆነ በግልጽ ያሳያሉ። በመንፈስ አነሳሽነት የተጻፉት በዚህ መጽሐፍ ውስጥ የሚገኙት መዝሙራት በይሖዋ ተስፋ ማድረግንና ወደ ትክክለኛው አቅጣጫ የመመለስ ፍላጎትን የሚገልጹ ግጥሞችም ይዘዋል። በኤርምያስ ዘመን የነበሩት አብዛኞቹ ሰዎች በመዝሙሮቹ ውስጥ የተገለጸው ዓይነት አመለካከት ባይኖራቸውም ኤርምያስና ንስሐ የገቡት ቀሪዎች ግን እንዲህ ዓይነት ስሜት ነበራቸው።

በሰቆቃወ ኤርምያስ መጽሐፍ ውስጥ እንደተገለጸው ይሖዋ የኢየሩሳሌምን ሁኔታ መገምገሙ ሁለት አስፈላጊ ትምህርቶች ይሰጠናል። አንደኛ፣ የኢየሩሳሌም መጥፋትና የይሁዳ ባድማ መሆን ለይሖዋ እንድንታዘዝ ያሳስበናል፤ እንዲሁም መለኮታዊውን ፈቃድ ቸል እንዳንል ማስጠንቀቂያ ይሆነናል። (1 ቆሮንቶስ 10:11) ሁለተኛውን ትምህርት የምናገኘው ደግሞ ኤርምያስ ከተወው ምሳሌ ነው። (ሮሜ 15:4) ተስፋ አስቆራጭ በሚመስሉ ሁኔታዎች ውስጥም እንኳ በጥልቅ ያዘነው ነቢዩ ኤርምያስ የይሖዋን ማዳን ይጠባበቅ ነበር። በይሖዋና በቃሉ ሙሉ በሙሉ መታመናችን ምንኛ አስፈላጊ ነው!—ዕብራውያን 4:12

[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ነቢዩ ኤርምያስ ሲያውጀው የቆየው የፍርድ መልእክት ፍጻሜውን ሲያገኝ ተመልክቷል

[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ከክርስቲያናዊ የገለልተኝነት አቋም ጋር በተያያዘ በኮሪያ የሚገኙት እነዚህ የይሖዋ ምሥክሮች እምነታቸው ተፈትኗል