በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የአንባቢያን ጥያቄዎች

የአንባቢያን ጥያቄዎች

የአንባቢያን ጥያቄዎች

ምሳሌ 22:6 ክርስቲያን ልጆች ተገቢውን ሥልጠና ካገኙ ከይሖዋ መንገድ እንደማይወጡ ዋስትና ይሰጣል?

ጥቅሱ “ልጅን የሚሄድበትን መንገድ አስተምረው፤ በሚሸመግልበት ጊዜ ከዚያ ፈቀቅ አይልም” ይላል። የአንድ ዛፍ ቀንበጥ ተጣምሞ ወይም ተስተካክሎ መውጣቱ በኋላ ሲያድግ በሚኖረው ቅርጽ ላይ ተጽዕኖ እንደሚያደርግ ሁሉ ተገቢውን ሥልጠና ያገኙ ልጆችም ሲያድጉ ይሖዋን በማገልገል የመቀጠል አጋጣሚያቸው ሰፊ ይሆናል። ማንኛውም ወላጅ እንዲህ ዓይነቱ ሥልጠና ብዙ ጊዜና ጥረት እንደሚጠይቅ ያውቃል። ወላጆች፣ ልጆቻቸውን ክርስቲያን ደቀ መዛሙርት ለማድረግ በጥንቃቄ ሊያስተምሯቸው፣ ሊመክሯቸው፣ ሊያበረታቷቸው እንዲሁም ተግሣጽ ሊሰጧቸውና ጥሩ ምሳሌ ሊሆኑላቸው ይገባል። ይህንንም ለበርካታ ዓመታት ሳያቋርጡ በፍቅር ማድረግ ይኖርባቸዋል።

ይህ ሲባል ታዲያ አንድ ልጅ ይሖዋን ማገልገሉን ቢተው ወላጆቹ የሰጡት ሥልጠና ችግር አለበት ማለት ነው? አንዳንድ ጊዜ ወላጆች፣ ልጆቻቸውን በይሖዋ ምክርና ተግሣጽ ለማሳደግ የሚያደርጉት ጥረት በቂ ላይሆን ይችላል። (ኤፌሶን 6:4) በሌላ በኩል ግን በምሳሌ መጽሐፍ ላይ የሚገኘው ሐሳብ፣ ልጆች ጥሩ ሥልጠና ማግኘታቸው ለአምላክ ታማኝ እንዲሆኑ እንደሚያደርጋቸው ዋስትና አይሰጥም። ወላጆች ልጆቻቸውን በሚፈልጉት መንገድ መቅረጽ አይችሉም። እንደ አዋቂዎች ሁሉ ልጆችም የፈለጉትን የመምረጥ ነጻነት አላቸው፤ እንዲሁም ሕይወታቸውን የሚመሩበትን ጎዳና የሚመርጡት እነርሱ ብቻ ናቸው። (ዘዳግም 30:15, 16, 19) ወላጆች ከፍተኛ ጥረት ቢያደርጉም አንዳንድ ልጆች እየተወያየንበት ያለውን ጥቅስ እንደጻፈው እንደ ሰሎሞን ታማኝ ሳይሆኑ ይቀራሉ። ይሖዋም እንኳ ታማኝነታቸውን ያጎደሉ ልጆች አሉት።

በመሆኑም ይህ ጥቅስ ተገቢውን ሥልጠና ያገኘ ልጅ ሁሉ “ከዚያ ፈቀቅ አይልም” ማለቱ አይደለም፤ ከዚህ ይልቅ ሐሳቡ በአብዛኛው የሚገኘውን ውጤት የሚጠቁም ነው። ይህ ለወላጆች እንዴት የሚያበረታታ ነው! ወላጆች ልጆቻቸውን በይሖዋ መንገድ ለማሠልጠን የሚያደርጉት ከፍተኛ ጥረት ጥሩ ውጤት እንደሚያስገኝ ማወቃቸው ሊያበረታታቸው ይገባል። ወላጆች በዚህ ረገድ የሚጫወቱት ሚና አስፈላጊ ከመሆኑም በላይ በልጆቻቸው ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ የሚያሳድሩ በመሆኑ ኃላፊነታቸውን በቁም ነገር እንዲመለከቱት ተመክረዋል።—ዘዳግም 6:6, 7

ልጆቻቸውን በአግባቡ ለማሠልጠን ጥረት ያደረጉ ወላጆች፣ ልጆቹ ይሖዋን ማገልገላቸውን ቢያቆሙም እንኳ አንድ ቀን ወደ ልባቸው ሊመለሱ እንደሚችሉ ተስፋ ያደርጋሉ። የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ኃይል አለው፤ የወላጆች ሥልጠናም በቀላሉ አይረሳም።—መዝሙር 19:7