የክፋት ምንጭ ተጋለጠ!
የክፋት ምንጭ ተጋለጠ!
በመጀመሪያው መቶ ዘመን አብዛኞቹ አይሁዳውያን ተስፋ የተሰጠበትን መሲሕ ይጠባበቁ ነበር። (ዮሐንስ 6:14) ኢየሱስ ሲመጣ ሕዝቡ መጽናኛ እንዲያገኙ እንዲሁም የእውቀት ብርሃን እንዲፈነጥቅላቸው ረድቷቸዋል። የታመሙትን ፈውሷል፣ የተራቡትን መግቧል እንዲሁም አስቸጋሪ የአየር ሁኔታዎችን ተቆጣጥሯል፤ የሞቱ ሰዎችንም እንኳ አስነስቷል። (ማቴዎስ 8:26፤ 14:14-21፤ 15:30, 31፤ ማርቆስ 5:38-43) ኢየሱስ የይሖዋን ቃል ከመናገሩም በላይ ለሰዎች የዘላለም ሕይወት ተስፋ ሰጥቷል። (ዮሐንስ 3:34) ኢየሱስ የሰው ልጆችን ከኃጢአትና ኃጢአት ካስከተላቸው መጥፎ ውጤቶች ሁሉ ነጻ የሚያወጣቸው መሲሕ እርሱ መሆኑን በንግግሩም ሆነ በድርጊቱ በሚገባ አሳይቷል።
የአይሁድ የሃይማኖት መሪዎች ኢየሱስን ለመቀበል፣ የሚናገረውን ለማዳመጥና መመሪያዎቹን በደስታ ለመታዘዝ የመጀመሪያዎቹ ሊሆኑ ይገባ ነበር። እነርሱ ግን እንዲህ ከማድረግ ይልቅ ኢየሱስን ጠሉት፣ አሳደዱት እንዲሁም ሊገድሉት አሴሩ!—ማርቆስ 14:1፤ 15:1-3, 10-15
በእርግጥም ኢየሱስ እነዚህን ክፉ ሰዎች ማውገዙ ተገቢ ነበር። (ማቴዎስ 23:33-35) ሆኖም ኢየሱስ በእነዚህ ሰዎች ልብ ውስጥ ክፋት እንዲኖር ያደረገ ሌላ አካል እንዳለ በመገንዘብ እንዲህ ብሏቸዋል:- “እናንተ የአባታችሁ የዲያብሎስ ናችሁ፤ የአባታችሁንም ፍላጎት ለመፈጸም ትሻላችሁ። እርሱ ከመጀመሪያ ነፍሰ ገዳይ ነበር፤ በእርሱ ዘንድ እውነት ስለሌለ በእውነት አልጸናም፤ እርሱ ሐሰተኛ፣ የሐሰትም አባት በመሆኑ ሐሰትን ሲናገር፣ የሚናገረው ከራሱ አፍልቆ ነው።” (ዮሐንስ 8:44) ኢየሱስ፣ የሰው ልጆች የክፋት ድርጊቶችን መፈጸም እንደሚችሉ ቢያምንም የክፋት ዋነኛ ምንጭ ሰይጣን ዲያብሎስ መሆኑን ጠቁሟል።
ኢየሱስ፣ ሰይጣን “በእውነት አልጸናም” ብሎ ሲናገር ይህ መንፈሳዊ ፍጡር በአንድ ወቅት የአምላክ ታማኝ አገልጋይ የነበረ ቢሆንም በኋላ ከትክክለኛው ጎዳና እንደወጣ መግለጹ ነበር። ሰይጣን በይሖዋ ላይ ያመጸው ለምን ነበር? ለራሱ ከሚገባው በላይ ከፍ ያለ ግምት በመስጠቱ ለአምላክ ብቻ የሚገባውን አምልኮ የማግኘት ምኞት ስላደረበት ነው። a—ማቴዎስ 4:8, 9
ሰይጣን፣ በኤድን የአትክልት ሥፍራ ሔዋን የተከለከለውን ፍሬ እንድትበላ ባታለላት ጊዜ በአምላክ ላይ ማመጹ በግልጽ ታየ። በአጽናፈ ዓለም ውስጥ የመጀመሪያውን ውሸት በመናገርና የይሖዋን ስም በማጥፋት ሰይጣን ራሱን ‘የሐሰት አባት’ አደረገ። ከዚህም በላይ አዳምንና ሔዋንን አታልሎ እንዲያምጹ በማድረግ ኃጢአት በእነርሱ ላይ እንዲገዛ መንገድ ከፈተ፤ ይህም ውሎ አድሮ በራሳቸውም ሆነ በዘሮቻቸው ላይ ሞት አስከተለ። በዚህ መንገድ ሰይጣን ራሱን “ነፍሰ ገዳይ” አደረገ፤ እውነትም በዘመናት ከታዩት ሁሉ የከፋ ነፍሰ ገዳይ ነው!—ዘፍጥረት 3:1-6፤ ሮሜ 5:12
የሰይጣን ክፉ ተጽዕኖ ወደ መንፈሳዊው ዓለም ጭምር የተዛመተ ሲሆን በዚያ ያሉ ሌሎች መላእክትም በዓመጹ እንዲተባበሩ አሳደማቸው። (2 ጴጥሮስ 2:4) እንደ ሰይጣን ሁሉ እነዚህ ክፉ መናፍስትም ለሰው ዘሮች ተገቢ ያልሆነ ስሜት ነበራቸው። እነዚህ ክፉ መናፍስት፣ ከሰው ልጆች ጋር የጾታ ግንኙነት የመፈጸም ከተፈጥሮ ውጭ የሆነ ፍላጎት ያደረባቸው ሲሆን ይህም አስከፊ ውጤት አስከትሏል።
ምድር በክፋት ተሞላ
መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል:- “ሰዎች . . . እየበዙ ሲሄዱ ሴቶች ልጆች ተወለዱላቸው። የእግዚአብሔር ወንዶች ልጆች የሰዎችን ሴቶች ልጆች ውብ ሆነው አዩአቸው፤ ከመካከላቸውም የመረጧቸውን አገቡ።” (ዘፍጥረት 6:1, 2) እዚህ ላይ የተገለጹት “የእግዚአብሔር ወንዶች ልጆች” እነማን ናቸው? እነዚህ የእግዚአብሔር ልጆች መንፈሳዊ ፍጥረታት እንጂ ሰዎች አልነበሩም። (ኢዮብ 1:6፤ 2:1 የግርጌ ማስታወሻውን ተመልከት።) ይህን በምን እናውቃለን? አንደኛ ነገር በሰዎች መካከል የሚደረገው ጋብቻ ለ1,500 ዓመታት ያህል ሲከናወን ስለቆየ ለየት ያለ ድርጊት እንደተፈጸመ ተደርጎ መገለጽ አያስፈልገውም። በመሆኑም “የእግዚአብሔር ወንዶች ልጆች” ሥጋዊ አካል ለብሰው ‘ከሰዎች ሴቶች ልጆች’ ጋር የጾታ ግንኙነት መፈጸማቸውን የሚገልጸው ዘገባ ከዚያ በፊት ሆኖ የማያውቅና ከተፈጥሮ ውጭ የሆነ ድርጊት መፈጸሙን የሚያሳይ ነው።
ይህ ድርጊት ተፈጥሯዊ እንዳልሆነ የሚያረጋግጠው ሌላው ማስረጃ ደግሞ ከዚህ ዓይነቱ ጥምረት የተገኙት ልጆች ሁኔታ ነው። ኔፊሊም ተብለው የሚጠሩት እነዚህ ዲቃሎች ሲያድጉ በጣም ግዙፍ ሆኑ። ከዚህም በላይ ሰዎችን የሚጎዱ አረመኔዎች ነበሩ። እንዲያውም “ኔፊሊም” የሚለው ቃል “የሚዘርሩ” ወይም “ሰዎችን አንስተው የሚያፈርጡ” የሚል ትርጉም አለው። እነዚህ ጨካኝ ሰዎች “በጥንቱ ዘመን በጀግንነታቸው ከፍ ያለ ዝና ያተረፉ” እንደነበሩ ተገልጿል።—ዘፍጥረት 6:4
ኔፊሊሞችም ሆኑ አባቶቻቸው ከዚያ በፊት ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ በጣም ክፉዎች ነበሩ። ዘፍጥረት 6:11 “ምድር በእግዚአብሔር ፊት በክፉ ሥራ ረከሰች፤ በዐመፅም ተሞላች” ይላል። ይህ የሆነው የሰው ልጆች የእነዚህን ዲቃሎች እንዲሁም የአባቶቻቸውን የዓመጽና የብልግና ጎዳና መከተል ስለጀመሩ ነበር።
ኔፊሊሞችም ሆኑ አባቶቻቸው በሰዎች ላይ እንዲህ ያለ ክፉ ተጽዕኖ ሊያሳድሩ የቻሉት እንዴት ነበር? የሰው ልጆችን ኃጢአት የመሥራት ዝንባሌና ፍላጎት በመጠቀም ነው። ውጤቱስ ምን ሆነ? መጽሐፍ ቅዱስ “ሰው ሁሉ አካሄዱን አበላሽቶ ነበር” ይላል። በመጨረሻም ይሖዋ ጻድቁን ኖኅንና ቤተሰቡን ብቻ አድኖ በወቅቱ የነበሩትን ሰዎች ዓለም አቀፍ በሆነ የጥፋት ውኃ ደመሰሳቸው። (ዘፍጥረት 6:5, 12-22) ሥጋ ለብሰው ወደ ምድር የመጡት መላእክት ግን ኃፍረት ተከናንበው ወደ መንፈሳዊው ዓለም ተመለሱ። እነዚህ የተዋረዱ አጋንንት አምላክንና ታማኝ መላእክትን ያቀፈውን ጻድቅ ቤተሰቡን መቃወማቸውን ቀጠሉ። ከዚያን ጊዜ ወዲህ አምላክ፣ እነዚህ ክፉ መናፍስት ሥጋ መልበስ እንዳይችሉ ያደረጋቸው ይመስላል። (ይሁዳ 6) እንደዚያም ሆኖ በሰዎች ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ ያሳድራሉ።
ክፉው ሙሉ በሙሉ ተጋለጠ!
በ1 ዮሐንስ 5:19 ላይ የሚገኘው “መላው ዓለምም በክፉው ሥር” እንደሆነ የሚገልጸው ጥቅስ ሰይጣን ምን ያህል ክፉ ተጽዕኖ እንደሚያሳድር ያሳያል። ዲያብሎስ፣ የሰው ልጆች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የሚሄድ ወዮታ እንዲያጋጥማቸው እያደረገ ነው። እንዲያውም ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ የሰው ልጆችን ለማጥፋት ቆርጧል። ለምን? እርሱም ሆነ አጋንንቱ በ1914 የአምላክ መንግሥት ከተቋቋመ በኋላ ከሰማይ በመባረራቸው ምክንያት ነው። መጽሐፍ ቅዱስ ይህንን ሁኔታ እንዲህ በማለት አስቀድሞ ተናግሯል:- “ምድርና ባሕር ግን ወዮላችሁ! ምክንያቱም ዲያብሎስ ጥቂት ዘመን ብቻ እንደ ቀረው ስላወቀ፣ በታላቅ ቊጣ ተሞልቶ ወደ እናንተ ወርዶአል።” (ራእይ 12:7-12) ታዲያ ሰይጣን በዛሬው ጊዜ በሰው ልጆች ላይ ተጽዕኖ እያሳደረ ያለው እንዴት ነው?
ሰይጣን በዋነኝነት ይህን የሚያደርገው በሰዎች አስተሳሰብና ድርጊት ላይ ተጽዕኖ የሚያሳድር መንፈስ በማስፋፋት ነው። በመሆኑም በኤፌሶን 2:2 ላይ ዲያብሎስ ‘በአየር ላይ ላሉት መንፈሳውያን ኀይላት ገዥ የሆነውና አሁንም ለእግዚአብሔር በማይታዘዙት ሰዎች ላይ የሚሠራው መንፈስ’ ተብሎ ተጠርቷል፤ ይህ መንፈስ በሰፊው ተንሰራፍቶ የሚታየው ዝንባሌ ነው። ይህ አጋንንታዊ “አየር” ሰዎች አምላካዊ ፍርሃትንና በጎነትን እንዲያዳብሩ ከማበረታታት ይልቅ በአምላክና በመሥፈርቶቹ ላይ እንዲያምጹ ያነሳሳቸዋል። ሰይጣንና አጋንንቱ፣ ሰዎች የሚፈጽሟቸው የክፋት ድርጊቶች እንዲስፋፉና እንዲባባሱ ያደርጋሉ።
“ልብህን ጠብቅ”
የዚህ “አየር” መገለጫ ከሆኑት ነገሮች መካከል እንደ ወረርሽኝ የተስፋፉት ወሲባዊ ድርጊቶችን የሚያሳዩ ጽሑፎች ወይም ፊልሞች ይገኙበታል። እንደነዚህ ያሉ ጽሑፎችና ፊልሞች ደግሞ ተገቢ ያልሆነ የጾታ ፍላጎት ከማነሳሳታቸውም በላይ ከተፈጥሮ ውጭ የሆኑ የጾታ ድርጊቶች አስደሳች እንዲመስሉ ያደርጋሉ። (1 ተሰሎንቄ 4:3-5) እነዚህ ወሲባዊ ጽሑፎች ወይም ፊልሞች እንደ መዝናኛ አድርገው ከሚያሳዩአቸው ነገሮች መካከል አስገድዶ መድፈር፣ ሌሎችን በማሰቃየት መደሰት፣ በቡድን ሆኖ አስገድዶ መድፈር፣ ከእንስሳ ጋር የጾታ ግንኙነት መፈጸምና በልጆች ላይ የሚፈጸም ወሲባዊ ጥቃት ይገኙበታል። ከጾታ ብልግና ጋር የተያያዙ ነገሮች ጎጂ እንዳልሆኑ በሚያስመስል መንገድ በሚቀርቡበት ጊዜም እንኳ ሰዎችን ሱሰኞች የሚያደርጉ ከመሆኑም በላይ እነዚህን ነገሮች የሚያነቡ ወይም የሚመለከቱ ሰዎች የብልግና ምሥሎችን በመመልከት የመደሰት ልማድ እንዲያዳብሩ ስለሚያደርጓቸው ጎጂ ናቸው። b እንዲህ ዓይነቱ ልማድ ከሰዎች ጋር ያለንን ግንኙነትም ሆነ ከአምላክ ጋር ያለንን ዝምድና የሚያበላሽ ክፉ ድርጊት ነው። ወሲባዊ ጽሑፎችና ፊልሞች፣ እንዲህ ያለውን ድርጊት የሚያስፋፉትን አጋንንት የረከሰ አስተሳሰብ ያንጸባርቃሉ፤ እነዚህ ዓመጸኞች ተገቢ ያልሆነ የጾታ ፍላጎታቸው የጀመረው ከጥፋት ውኃ በፊት በኖኅ ዘመን ነበር።
ጠቢቡ ሰሎሞን “ከሁሉም በላይ ልብህን ጠብቅ፤ የሕይወት ምንጭ ነውና” የሚል ምክር መስጠቱ ተገቢ ነው። (ምሳሌ 4:23) ይህን ምክር ተግባራዊ በማድረግ ወሲባዊ ጽሑፎችና ፊልሞች ከሚያስከትሉት ወጥመድ ልብህን ለመጠበቅ፣ የጾታ ፍላጎትን የሚያነሳሳ ምሥል ሲታይ የቴሌቪዥኑን ጣቢያ መቀየር ወይም ኮምፒውተሩን ማጥፋት ሊኖርብህ ይችላል። ደግሞም በፍጥነት ቆራጥ እርምጃ መውሰድህ አስፈላጊ ነው! በልቡ ላይ የተነጣጠረበትን መሣሪያ ለመከላከል እንደሚጥር ወታደር አድርገህ ራስህን አስብ። በተመሳሳይም ሰይጣን ዝንባሌዎችህና ፍላጎቶችህ በሚገኙበት በምሳሌያዊ ልብህ ላይ በማነጣጠር ሊበክለው ይፈልጋል።
ከዚህም በላይ ለዓመጽ ድርጊቶች ፍቅር እንዳታዳብር ልብህን መጠበቅ አለብህ፤ ዲያብሎስ ‘ዐመፃን የሚወዱትን ይሖዋ እንደሚጠላቸው’ ያውቃል። (መዝሙር 11:5) ሰይጣን፣ ከአምላክ ጋር እንድትጣላ የሚያደርግህ የዓመጽ ተግባሮችን እንድትፈጽም በማድረግ ብቻ አይደለም፤ የዓመጽ ድርጊቶችን እንድትወድ ካደረገህም ከአምላክ ጋር ትጣላለህ። ታዋቂ የሆኑ የመገናኛ ብዙኃን አብዛኛውን ጊዜ ከአስማት ጋር በተያያዙ የዓመጽ ድርጊቶች የተሞሉ የሆኑት እንዲሁ በአጋጣሚ አይደለም። ኔፊሊሞች ከሕልውና ውጭ ቢሆኑም እነርሱ ያሳዩት የነበረው ባሕርይ ግን አሁንም በጣም ተስፋፍቶ ይገኛል! የመዝናኛ ምርጫህ፣ ሰይጣን ሰዎችን ለማጥቃት የሚጠቀምባቸው ዘዴዎችን ለመቋቋም እንደምትጥር ያሳያል?—2 ቆሮንቶስ 2:11
የሰይጣንን ክፉ ተጽዕኖ መቋቋም የሚቻለው እንዴት ነው?
የክፋት ኃይሎችን መቋቋም በጣም አስቸጋሪ ሊመስል ይችላል። አምላክን ለማስደሰት የሚጥሩ ሰዎች ከራሳቸው አለፍጽምና ጋር ከሚያደርጉት ትግል በተጨማሪ “ከርኩሳን መናፍስት ሰራዊት ጋር” እንደሚጋደሉ መጽሐፍ ቅዱስ ይገልጻል። በትግሉ ለማሸነፍና የይሖዋን ሞገስ ለማግኘት አምላክ ከሚያቀርብልን በርካታ ዝግጅቶች መጠቀም አለብን።—ኤፌሶን 6:12፤ ሮሜ 7:21-25
ከእነዚህ ዝግጅቶች መካከል የአምላክ ቅዱስ መንፈስ ይገኝበታል፤ ይህ መንፈስ በአጽናፈ ዓለም ውስጥ ተወዳዳሪ የሌለው ኃይል ነው። ሐዋርያው ጳውሎስ በመጀመሪያው መቶ ዘመን ለነበሩት ክርስቲያኖች “ከእግዚአብሔር የሆነውን መንፈስ እንጂ፣ የዓለምን መንፈስ አልተቀበልንም” በማለት ጽፎላቸዋል። (1 ቆሮንቶስ 2:12) በአምላክ መንፈስ የሚመሩ ሰዎች አምላክ የሚወደውን ይወዳሉ፤ የሚጠላውንም ይጠላሉ። (አሞጽ 5:15) አንድ ሰው መንፈስ ቅዱስን ማግኘት የሚችለው እንዴት ነው? በዋነኝነት በመጸለይና መጽሐፍ ቅዱስን በማጥናት ነው፤ መጽሐፍ ቅዱስ ራሱ በመንፈስ ቅዱስ የተጻፈ በመሆኑ ይህንን መጽሐፍ ማጥናት መንፈሱን ለማግኘት ይረዳል። ከዚህም በተጨማሪ አምላክን ከልባቸው ከሚወዱ ሰዎች ጋር መወዳጀትም ጠቃሚ ነው።—ሉቃስ 11:13፤ 2 ጢሞቴዎስ 3:16፤ ዕብራውያን 10:24, 25
በእነዚህ መለኮታዊ ዝግጅቶች በመጠቀም፣ “የዲያብሎስን የተንኰል ሥራ” ለመቋቋም የሚያስችልህን ብቸኛ አስተማማኝ መከላከያ ማለትም “የእግዚአብሔርን ሙሉ የጦር ዕቃ” መልበስ ልትጀምር ትችላለህ። (ኤፌሶን 6:11-18) ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ ዛሬ በእነዚህ ዝግጅቶች ሙሉ በሙሉ መጠቀሙ አጣዳፊ ነው። እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው?
ክፋት የሚወገድበት ጊዜ ቀርቧል!
መዝሙራዊው “ክፉዎች እንደ ሣር ቢበቅሉ፣ ክፉ አድራጊዎች ቢለመልሙ፣ ለዘላለሙ ይጠፋሉ” ብሏል። (መዝሙር 92:7) አዎን፣ ልክ እንደ ኖኅ ዘመን ሁሉ በጊዜያችንም ክፋት ይህን ያህል መስፋፋቱ የአምላክ ፍርድ መቅረቡን ያሳያል። አምላክ የሚፈርደው በክፉ ሰዎች ላይ ብቻ ሳይሆን በሰይጣንና በአጋንንቱም ላይ ነው፤ ሰይጣንና አጋንንቱ ምንም ማድረግ በማይችሉበት ጥልቅ ውስጥ ተጥለው ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ የሚጠፉበትን ጊዜ ይጠባበቃሉ። (2 ጢሞቴዎስ 3:1-5፤ ራእይ 20:1-3, 7-10) ይህንን ፍርድ የሚያስፈጽመው ማን ነው? “የእግዚአብሔር ልጅ የተገለጠውም የዲያብሎስን ሥራ ያፈርስ ዘንድ ነው” ከተባለለት ከኢየሱስ ክርስቶስ ሌላ ማንም ሊሆን አይችልም።—1 ዮሐንስ 3:8
ክፋት የሚወገድበትን ጊዜ ለመመልከት ትጓጓለህ? ከሆነ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙት ተስፋዎች ሊያጽናኑህ ይችላሉ። የክፋት ምንጭ ሰይጣን እንደሆነና እርሱም ሆነ ክፉ ሥራዎቹ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ እንዴት እንደሚጠፉ የሚገልጸው መጽሐፍ ቅዱስ ብቻ ነው። በአሁኑ ጊዜ ከሰይጣን የክፋት ተጽዕኖዎች ራስህን ለመጠበቅ እንድትችልና ወደፊት ደግሞ ከክፋት በጸዳ ዓለም ውስጥ የመኖር ተስፋ እንዲኖርህ የመጽሐፍ ቅዱስን ትክክለኛ እውቀት እንድታገኝ እናበረታታሃለን።—መዝሙር 37:9, 10
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
a ከጊዜ በኋላ ሰይጣን የሆነው መልአክ መጀመሪያ ላይ ስሙ ማን እንደነበር አይታወቅም። መጽሐፍ ቅዱስ መጀመሪያ በተጻፈበት ቋንቋ “ሰይጣን” እና “ዲያብሎስ” የሚሉት ስሞች “ተቃዋሚ” እና “ስም አጥፊ” የሚል ትርጉም አላቸው። ሰይጣን የተከተለው አካሄድ በተወሰነ ደረጃ ከጥንቱ የጢሮስ ንጉሥ ጋር ይመሳሰላል። (ሕዝቅኤል 28:12-19) ሁለቱም መጀመሪያ ላይ በመንገዳቸው ነቀፋ የሌለባቸው የነበሩ ሲሆን ከጊዜ በኋላ ግን ትዕቢታቸው ለውድቀት ዳርጓቸዋል።
b “የብልግና ሥዕሎች—ጎጂ ናቸው ወይስ አይደሉም?” የሚለውን በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀውን የጥቅምት 2003 ንቁ! መጽሔት ተመልከት።
[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]
በእውነተኛ ታሪክ ላይ የተመሠረቱ አፈ ታሪኮች
ከፊል ሰው ከፊል አምላክ ስለሆኑ አካላትና ግዙፍ ሰዎች እንዲሁም ከፍተኛ ውድመት ስላስከተለ የውኃ መጥለቅለቅ የሚያወሱ ጥንታዊ አፈ ታሪኮች በዓለም ዙሪያ ይነገራሉ። ለአብነት ያህል፣ ስለ ጊልጋሜሽ የሚናገረው የአካዲያን የጀግንነት ግጥም ስለ ውኃ መጥለቅለቅ፣ ስለ መርከብና ከጥፋቱ ስለተረፉት ሰዎች ይጠቅሳል። ጊልጋሜሽ ራሱ ዘማዊና ጨካኝ የሆነ ከፊል አምላክ ከፊል ሰው እንደነበረ ተገልጿል። የአዝቴኮች አፈ ታሪክ ደግሞ በጥንቱ ዓለም ግዙፍ ሰዎች ይኖሩ እንደነበረና ታላቅ የጥፋት ውኃ እንደመጣ ይናገራል። በአንድ ወቅት ግዙፍ ሰዎች እንዲሁም ባርገልሚር የተባለ ጠቢብ ይኖሩ እንደነበረና ባርገልሚር ትልቅ መርከብ ሠርቶ ራሱንና ሚስቱን እንዳዳነ የሚናገር የኖርሶች አፈ ታሪክም አለ። እነዚህ ሁሉ አፈ ታሪኮች፣ የሰው ዘሮች በሙሉ የመጡት በጥንት ዘመን የነበረው ክፉ ዓለም በውኃ መጥለቅለቅ ከጠፋ በኋላ ከተረፉት ሰዎች እንደሆነ የሚናገረው የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ እውነተኛ መሆኑን ያረጋግጣሉ።
[ሥዕል]
ስለ ጊልጋሜሽ የሚናገረው የአካዲያን የጀግንነት ግጥም የሰፈረበት ጽላት
[ምንጭ]
The University Museum, University of Pennsylvania (neg. # 22065)
[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በዛሬው ጊዜ ያሉ ሰዎች የኔፊሊሞች ዓይነት ባሕርይ ያንጸባርቃሉ
[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ትክክለኛ እውቀት ከክፉ ተጽዕኖ ይጠብቀናል