ግርዘት የወንድነት ምልክት ነው?
ግርዘት የወንድነት ምልክት ነው?
በበርካታ የዓለም ክፍሎች ለጤንነት ተብሎ ሕፃናት ወንዶች ይገረዛሉ። በሌሎች የዓለም ክፍሎች ደግሞ ወንዶች ዕድሜያቸውን ሙሉ ሳይገረዙ መኖራቸው የተለመደ ነው። ለአይሁዳውያንና ለሙስሊሞች ግን ግርዘት ለጤንነት ተብሎ ብቻ የሚደረግ ሳይሆን ከሃይማኖት ጋር ግንኙነት ያለው ነገር ነው።
ይሁን እንጂ በአንዳንድ አገሮች የግርዘት ሥነ ሥርዓት የሚከናወነው አንድ ልጅ የልጅነት ዕድሜውን ጨርሶ ጉርምስና ደረጃ ላይ ሲደርስ ነው። ይህ ደግሞ ልጁን ወደሚገረዝበትና ቁስሉ እስኪድንለት ድረስ ከኅብረተሰቡ ተገልሎ ለበርካታ ሳምንታት ወደሚቆይበት ባሕላዊ ትምህርት ቤት መላክን ይጨምራል። በዚህ ወቅት ልጁ አንዳንድ ሃይማኖታዊ ሥነ ሥርዓቶችን እንዲከተል የሚደረግ ከመሆኑም በላይ ከወንዶች ምን እንደሚጠበቅ ይማራል። ይሁንና አንድ ልጅ የጉርምስና ዕድሜ ላይ መድረሱን ለማረጋገጥ ይህ ዓይነቱ ግርዘት አስፈላጊ ነው? እስቲ አምላክ ስለዚህ ጉዳይ ያለውን አመለካከት መጽሐፍ ቅዱስ ምን እንደሚል እንመልከት።—ምሳሌ 3:5, 6
አምላክ ስለ ግርዘት ያለው አመለካከት
እንደ ግብፃውያን ያሉ በጥንት ጊዜ የነበሩ አንዳንድ ሕዝቦች የመግረዝ ማለትም የወንድን የጾታ ብልት ሸለፈት የመቁረጥ ልማድ ነበራቸው። ይሁን እንጂ አብርሃም የተወለደው እንዲህ ዓይነት ባሕል በሚከተል ኅብረተሰብ ውስጥ አልነበረም። እንዲያውም አብርሃም አብዛኛውን የሕይወት ዘመኑን ያሳለፈው ሳይገረዝ ነበር። ከዚህም በላይ አብርሃም ሳይገረዝ በቆየባቸው ዓመታት ጀግና መሆኑን አስመስክሯል። የወንድሙን ልጅ ሎጥን የማረኩትን የአራት ነገሥታት ሠራዊት አሳድዶ ድል ያደረገው ጥቂት ቁጥር ባላቸው ሰዎች ነበር። (ዘፍጥረት 14:8-16) ይህን ካደረገ ከ14 ዓመታት ገደማ በኋላ አምላክ፣ አብርሃም ራሱ እንዲገረዝ ብሎም በቤቱ የሚኖሩትን ሁሉ እንዲገርዝ ትእዛዝ ሰጠው። አምላክ እንዲህ እንዲያደርግ ያዘዘው ለምን ነበር?
አምላክ ለአብርሃም ይህንን ትእዛዝ የሰጠው ልጅነቱን ጨርሶ ጉርምስና ዕድሜ ላይ መድረሱን ለማሳየት እንዳልነበረ ግልጽ ነው። ምክንያቱም በወቅቱ አብርሃም 99 ዓመቱ ነበር! (ዘፍጥረት 17:1, 26, 27) አምላክ ይህንን ትእዛዝ የሰጠበትን ምክንያት ሲገልጽ “ስለዚህ ሁላችሁም ሸለፈታችሁን ትገረዛላችሁ፤ ይህም በእኔና በእናንተ መካከል ላለው ኪዳን ምልክት ይሆናል” ብሏል። (ዘፍጥረት 17:11) አምላክ ከአብርሃም ጋር የገባው ይህ ቃል ኪዳን “በምድር የሚኖሩ ሕዝቦች” ሁሉ ውሎ አድሮ በአብርሃም አማካኝነት የተትረፈረፉ በረከቶችን እንደሚያገኙ የገባውን ቃል የሚጨምር ነው። (ዘፍጥረት 12:2, 3) በመሆኑም በአምላክ ዓይን ግርዘት ከወንድነት ጋር ምንም ግንኙነት የለውም። ግርዘት ይከናወን የነበረው አንድ ሰው ‘የአምላክን ቃል በዐደራ’ የመያዝ መብት ከተሰጣቸውና የአብርሃም ዝርያዎች ከሆኑት ከእስራኤላውያን ወገን መሆኑን ለማመልከት ነበር።—ሮሜ 3:1, 2
ከጊዜ በኋላ የእስራኤል ብሔር የአብርሃም እውነተኛ ዘር የሆነውን ኢየሱስ ክርስቶስን ባለመቀበሉ አደራውን መወጣት የማይችል መሆኑ ተረጋገጠ። በመሆኑም አምላክ እነርሱን የተዋቸው ሲሆን ከዚያን ጊዜ ጀምሮ መገረዛቸው በአምላክ ፊት ትርጉም አጣ። ይሁን እንጂ በመጀመሪያው መቶ ዘመን ከክርስቶስ ልደት በኋላ የነበሩ አንዳንድ ክርስቲያኖች ግርዘት አምላክ የሚፈልገው ብቃት እንደሆነ ይከራከሩ ነበር። (የሐዋርያት ሥራ 11:2, 3፤ 15:5) በዚህም የተነሳ ሐዋርያው ጳውሎስ በተለያዩ ጉባኤዎች ውስጥ የነበረውን ችግር ‘እንዲያስተካክል’ ቲቶን ላከው። ጳውሎስ ለቲቶ በጻፈለት ወቅት አንደኛው ችግር ምን እንደነበረ ሲገልጽ እንዲህ ብሏል:- “ዐመፀኞች፣ ለፍላፊዎችና አታላዮች የሆኑ ብዙ ሰዎች አሉና፤ በተለይም እነዚህ ከተገረዙት ወገን ናቸው። እነዚህን ዝም ማሰኘት ተገቢ ነው፤ ምክንያቱም ትክክል ባልሆነ መንገድ ጥቅም ለማግኘት ሲሉ ማስተማር የማይገባቸውን ነገር በማስተማር ቤተ ሰብን ሁሉ በመበከል ላይ ናቸውና።”—ቲቶ 1:5, 10, 11
ጳውሎስ የሰጠው ይህ ምክር በዛሬው ጊዜም ይሠራል። አንድ እውነተኛ ክርስቲያን የሌላ ሰው ልጅ መገረዝ እንዳለበት ሐሳብ የሚያቀርብ ከሆነ ይህ ሁኔታ ከቅዱሳን መጻሕፍት ጋር እንደሚጋጭ ምንም ጥርጥር የለውም። አንድ ክርስቲያን “በሰው ነገር ጣልቃ ገቢ” ከመሆን ይልቅ እንዲህ ዓይነት የግል ውሳኔዎችን ለወላጆች ይተዋል። (1 ጴጥሮስ 4:15) ከዚህ በተጨማሪም ጳውሎስ በሙሴ ሕግ ሥር ስለነበረው የግርዘት ሥርዓት በመንፈስ ተነሳስቶ ሲጽፍ እንዲህ ብሏል:- “አንድ ሰው ተገርዞ ሳለ ቢጠራ፣ እንዳልተገረዘ ሰው አይሁን፤ ሳይገረዝም ተጠርቶ ከሆነ አይገረዝ። መገረዝም ሆነ አለመገረዝ አይጠቅምም፤ ዋናው ነገር የእግዚአብሔርን ትእዛዝ መፈጸሙ ነው። እያንዳንዱ ሰው በተጠራበት ሁኔታ ጸንቶ ይኑር።”—1 ቆሮንቶስ 7:18-20
ስለ “ግርዘት ትምህርት ቤቶች” ምን ማለት ይቻላል?
ክርስቲያን ወላጆች ወንዶች ልጆቻቸው መገረዝ እንደሚኖርባቸው ቢወስኑስ? ወንዶች ልጆቻቸውን ቀደም ሲል ወደተጠቀሱት ዓይነት የግርዘት ትምህርት ቤቶች መላካቸው ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር ይስማማል? እንዲህ በመሰሉ ትምህርት ቤቶች መግባት ሸለፈትን ከማስወገድ የበለጠ ነገርን የሚጨምር ነው። እንደነዚህ ዓይነት ትምህርት ቤቶች ውስጥ የሚገባ አንድ ልጅ ይሖዋን ከማያመልኩ ልጆችና አስተማሪዎች ጋር ለበርካታ ሳምንታት አብሮ መኖር ግድ ይሆንበታል። በትምህርት ቤቶቹ ውስጥ የሚሰጡት አብዛኞቹ ትምህርቶች ከመጽሐፍ ቅዱስ ከፍተኛ የሥነ ምግባር መሥፈርቶች ጋር የሚጋጩ ናቸው። መጽሐፍ ቅዱስ “መጥፎ ጓደኝነት መልካሙን ጠባይ ያበላሻል” በማለት ያስጠነቅቃል።—1 ቆሮንቶስ 15:33
በእነዚህ ትምህርት ቤቶች ውስጥ የሚገቡ ልጆች ላይ የሚደርሰው አካላዊ ጉዳትም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መጥቷል። በ2003 ሳውዝ አፍሪካን ሜዲካል ጆርናል የተባለ መጽሔት እንዲህ ሲል አስጠንቅቆ ነበር:- “ዘግናኝ የሆኑ የግርዘት ውጤቶች በዚህ ዓመትም የታዩ ሲሆን የሞት አደጋዎችና ከባድ አካላዊ ጉዳቶች እንደደረሱ የሚገልጹ ዘገባዎች በዋና ዋናዎቹ የዜና ማሠራጫዎች አማካኝነት በመላው ዓለም እየተላለፉ ናቸው። . . . በአጭሩ በዛሬው ጊዜ የሚገኙት ‘የግርዘት ትምህርት ቤቶች’ በእርግጥ ትምህርት ቤት ናቸው ሊባሉ የማይገባቸው ከመሆኑም በላይ ግድያ የሚከናወንባቸው ቦታዎች ናቸው።”
በትምህርት ቤቶቹ ውስጥ በወጣቶች ላይ ሊያጋጥም ከሚችለው አካላዊ ጉዳት በተጨማሪ ይበልጥ አደገኛ የሆነ መንፈሳዊ ጉዳትም ይደርሳል። በእነዚህ የግርዘት ትምህርት ቤቶች ውስጥ የሚሰጡት ትምህርቶችና የሚከናወኑት ልማዶች ከመናፍስታዊ ድርጊቶችና ለሞቱ የቀድሞ አባቶች ከሚቀርበው አምልኮ ጋር በቅርብ የተያያዙ ናቸው። ለምሳሌ ያህል፣ በአንድ ልጅ ላይ ጉዳት የሚደርሰው ግድ የለሽ በሆኑ ገራዦችና በንጽሕና ጉድለቶች ምክንያት እንደሆነ አምኖ ከመቀበል ይልቅ ብዙዎች ይህ ዓይነቱ አሳዛኝ ሁኔታ የተከሰተው በድግምት አሊያም በሞቱ የቀድሞ አባቶች ቁጣ ሳቢያ እንደሆነ አድርገው ያምናሉ። መጽሐፍ ቅዱስ ከሐሰት ሃይማኖት ጋር ሊኖረን የሚገባውን ግንኙነት በተመለከተ የሚከተለውን ትእዛዝ ይሰጣል:- “ከማያምኑ ሰዎች ጋር አግባብ ባልሆነ መንገድ አትጠመዱ፤ ጽድቅ ከዐመፅ ጋር ምን ግንኙነት አለው? ብርሃንስ ከጨለማ ጋር ምን ኅብረት አለው? . . . ‘ስለዚህ ከመካከላቸው ውጡ፤ ለእኔም የተለያችሁ ሁኑ፤ ይላል ጌታ። ርኩስ የሆነውን ነገር አትንኩ፤ እኔም እቀበላችኋለሁ።’” (2 ቆሮንቶስ 6:14-17) ከዚህ ምክር አንጻር ክርስቲያን ወላጆች ወንዶች ልጆቻቸውን ወደ ግርዘት ትምህርት ቤት መላካቸው ጥበብ የጎደለው ድርጊት ይሆናል።
አንድን ክርስቲያን ወንድ የሚያደርገው ምንድን ነው?
የአንድ ክርስቲያን ወንድነት የሚለካው በመገረዙ ወይም ባለመገረዙ አይደለም። እውነተኛ ክርስቲያኖችን በዋነኝነት የሚያሳስባቸው ‘ውጫዊ በሆነ ነገር መታየት’ ሳይሆን አምላክን የማስደሰቱ ጉዳይ ነው።—ገላትያ 6:12
ይሁን እንጂ አንድ ክርስቲያን አምላክን ለማስደሰት ከፈለገ ‘ልቡን መግረዝ’ ይኖርበታል። (ዘዳግም 10:16፤ 30:6፤ ማቴዎስ 5:8) ይህ ደግሞ የሚከናወነው የሰውነት ክፍልን በቢላ በመቁረጥ ሳይሆን መጥፎ ምኞቶችንም ሆነ በሥጋ መገረዝ አንድን ሰው ከሌሎች ያስበልጠዋል እንደሚሉት ያሉ የኩራት አስተሳሰቦችን በማስወገድ ነው። አንድ ክርስቲያን ተገረዘም አልተገረዘ መከራዎችን በመቋቋምና ‘በእምነት በመጽናት’ ወንድነቱን ማረጋገጥ ይችላል።—1 ቆሮንቶስ 16:13፤ ያዕቆብ 1:12