በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ለሌሎች አሳቢ በመሆን ረገድ ይሖዋን እየኮረጅክ ነው?

ለሌሎች አሳቢ በመሆን ረገድ ይሖዋን እየኮረጅክ ነው?

ለሌሎች አሳቢ በመሆን ረገድ ይሖዋን እየኮረጅክ ነው?

“እርሱ ስለ እናንተ ስለሚያስብ የሚያስጨንቃችሁን ሁሉ በእርሱ [በአምላክ] ላይ ጣሉት።” (1 ጴጥሮስ 5:7) እንዴት ያለ ፍቅራዊ ግብዣ ነው! ይሖዋ አምላክ ለሕዝቦቹ በግለሰብ ደረጃ ያስባል። በእቅፉ ውስጥ ስላለን የደህንነት ስሜት ይሰማናል።

እኛም ለሌሎች ተመሳሳይ የሆነ የአሳቢነት መንፈስ ማዳበርና ይህንንም በተግባር ማሳየት ይኖርብናል። ይሁንና ፍጽምና የጎደለን ሰዎች ስለሆንን ለሌሎች በግለሰብ ደረጃ አሳቢነት ስናሳይ ልንጠነቀቅባቸው የሚገቡ አንዳንድ ጉዳዮች አሉ። እነዚህን ነገሮች ከማየታችን በፊት ይሖዋ ለሕዝቦቹ አሳቢ መሆኑን የሚያሳይባቸውን አንዳንድ መንገዶች እንመልከት።

መዝሙራዊው ዳዊት አንድን እረኛ እንደ ምሳሌ አድርጎ በመጠቀም አምላክ ለሰዎች ያለውን አሳቢነት ሲገልጽ እንዲህ ብሏል:- “እግዚአብሔር እረኛዬ ነው፤ አንዳች አይጐድልብኝም። በለመለመ መስክ ያሳርፈኛል፤ በዕረፍት ውሃ ዘንድ ይመራኛል፤ ነፍሴንም ይመልሳታል። . . . በሞት ጥላ ሸለቆ ውስጥ፤ ብሄድ እንኳ፣ አንተ ከእኔ ጋር ስለ ሆንህ፣ ክፉን አልፈራም።”—መዝሙር 23:1-4

ዳዊት ራሱ እረኛ ስለነበር አንድን መንጋ መጠበቅ ምን ነገሮችን እንደሚጨምር ያውቃል። አንድ እረኛ በጎቹን እንደ አንበሳ፣ ተኩላና ድብ ከመሳሰሉ አውሬዎች ጥቃት ይከላከላል። መንጋው እንዳይበተን ይጠብቃል፣ የጠፋ በግ ካለ ይፈልጋል፣ የደከማቸውን ጠቦቶች በእቅፉ ይይዛል፤ እንዲሁም ለታመሙትና ጉዳት ለደረሰባቸው አስፈላጊውን እንክብካቤ ያደርጋል። በተጨማሪም በጎቹን በየቀኑ ውኃ ያጠጣል። ይህ ሲባል ግን እረኛው በጎቹ የሚያደርጉትን እያንዳንዱን እንቅስቃሴ ይቆጣጠራል ማለት አይደለም። በጎቹ እንዳሻቸው ይንቀሳቀሳሉ፤ ቢሆንም አስፈላጊው ጥበቃ ይደረግላቸዋል።

ይሖዋም ለሕዝቦቹ እንደሚያስብ የሚያሳያው በዚህ መንገድ ነው። ይህንን ሁኔታ በተመለከተ ሐዋርያው ጴጥሮስ “በእግዚአብሔር ኀይል ተጠብቃችኋል” በማለት ገልጿል። እዚህ ጥቅስ ላይ “ተጠብቃችኋል” የሚለው ቃል በቀጥታ ሲተረጎም “እይታ ውስጥ መሆን” ማለት ነው። (1 ጴጥሮስ 1:5 የአዲስ ዓለም ትርጉም የግርጌ ማስታወሻ) ይሖዋ ለእኛ ካለው ልባዊ አሳቢነት የተነሳ ሁልጊዜ የሚመለከተን ከመሆኑም በላይ እርዳታ በምንጠይቀው ጊዜ ሁሉ እኛን ለመርዳት ዝግጁ ነው። ይሁን እንጂ ይሖዋ የፈጠረን ነፃ ምርጫ እንዲኖረን አድርጎ ስለሆነ በምናደርጋቸው እንቅስቃሴዎችና ውሳኔዎች ውስጥ ጣልቃ አይገባም። በዚህ ረገድ ይሖዋን መኮረጅ የምንችለው እንዴት ነው?

ለልጆቻችሁ አሳቢ በመሆን ረገድ አምላክን ኮርጁ

“ልጆች የእግዚአብሔር ስጦታ ናቸው።” በመሆኑም ወላጆች ልጆቻቸውን መጠበቅና ለእነርሱ ማሰብ ይኖርባቸዋል። (መዝሙር 127:3) ይህ ደግሞ ልጆች ሐሳባቸውንና ስሜታቸውን አውጥተው እንዲናገሩ ማድረግን እንዲሁም ከእነርሱ ጋር ባላቸው ግንኙነት ይህንኑ ግምት ውስጥ ማስገባትን የሚያጠቃልል ይሆናል። ወላጆች የልጆቻቸውን ፍላጎቶች ሙሉ በሙሉ ችላ ብለው እያንዳንዱን እንቅስቃሴያቸውን ለመቆጣጠር የሚሞክሩ ከሆነ በጎቹን በገመድ አስሮ ለመቆጣጠር እንደሚሞክር እረኛ ሆነዋል ማለት ነው። መቼም ቢሆን መንጋውን በዚህ መንገድ መጠበቅ የሚፈልግ እረኛ የለም፤ ይሖዋም ቢሆን የሚጠብቀን በዚህ መንገድ አይደለም።

ማሪኮ a እንደሚከተለው ስትል ተናግራለች:- “ለዓመታት ልጆቼን ‘ይህን ማድረግ አለባችሁ፤ ያንን ማድረግ የለባችሁም’ ስላቸው ቆይቻለሁ። ወላጅ እንደመሆኔ መጠን ይህን የማድረግ ግዴታ እንዳለብኝ ይሰማኝ ነበር። አንድም ቀን አመስግኛቸው አላውቅም፤ እንዲሁም ከእነርሱ ጋር ግልጽ ውይይት አድርጌ አላውቅም።” የማሪኮ ሴት ልጅ ከጓደኞቿ ጋር በስልክ ረዘም ላለ ሰዓት የምታወራ ቢሆንም ከእናቷ ጋር ግን ለረጅም ሰዓት አውርታ አታውቅም። ማሪኮ ቀጥላ እንዲህ ብላለች:- “በኋላ ግን ልጄ ከጓደኞቿ ጋር ረጅም ሰዓት ማውራት የቻለችበትን ምክንያት አስተዋልኩ። ልጄ ከጓደኞቿ ጋር ስታወራ ‘አዎ ልክ ነው’ ወይም ‘እኔም እንደዚያ ይሰማኛል’ እንደሚሉት ያሉ ስሜታቸውን እንደምትጋራ የሚያሳዩ አገላለጾችን ትጠቀማለች። እኔም ልጄ ስሜቷን አውጥታ እንድትናገር ለማድረግ ተመሳሳይ አገላለጾችን መጠቀም ጀመርኩ፤ ብዙም ሳይቆይ ጭውውት የምናደርግበት ጊዜ ረጅምና ይበልጥ አስደሳች እየሆነ መጣ።” ይህ ሁኔታ ሁለቱን ወገን የሚያሳትፍ ጥሩ ውይይት የማድረግን አስፈላጊነት ያጎላል።

ወላጆች ልጆቻቸው ስሜታቸውንና ፍላጎታቸውን አውጥተው እንዲናገሩ ማድረግ ይኖርባቸዋል፤ ልጆችም በበኩላቸው ወላጆች ለእነርሱ ማሰባቸው ጥበቃ የሚሆንላቸው እንዴት እንደሆነ መገንዘብ ይኖርባቸዋል። መጽሐፍ ቅዱስ ልጆች ወላጆቻቸውን እንዲታዘዙ ይመክራል። ከዚያም ምክንያቱን ሲገልጽ “መልካም እንዲሆንልህ፣ ዕድሜህም በምድር ላይ እንዲረዝም” ይላል። (ኤፌሶን 6:1, 3) እሺ ባይ መሆን የሚያስገኘውን ጥቅም በደንብ የተረዱ ልጆች መታዘዝ ቀላል ይሆንላቸዋል።

ለመንጋው አሳቢ በመሆን ረገድ ይሖዋን ኮርጁ

የይሖዋ ፍቅራዊ አሳቢነት በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥም ተንጸባርቋል። ኢየሱስ ክርስቶስ የጉባኤው ራስ እንደመሆኑ መጠን ሽማግሌዎች ለመንጋው አሳቢ እንዲሆኑ መመሪያ ሰጥቷቸዋል። (ዮሐንስ 21:15-17) የበላይ ተመልካች ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ ቃል “ልብ ብሎ መጠበቅ” የሚል ትርጉም ካለው ግስ ጋር ተዛማጅነት አለው። ጴጥሮስ ይህ እንዴት መከናወን እንደሚኖርበት ጎላ አድርጎ ሲጠቅስ ለሽማግሌዎች የሚከተለውን መመሪያ ሰጥቷል:- “በእናንተ ኀላፊነት ሥር ያለውን የእግዚአብሔርን መንጋ ጠብቁ፤ የምትጠብቁትም ከእግዚአብሔር እንደሚጠበቅባችሁ በግድ ሳይሆን በፈቃደኝነት፣ ለጥቅም በመስገብገብ ሳይሆን ለማገልገል ባላችሁ ጽኑ ፍላጎት ይሁን፤ እንዲሁም በዐደራ ለተሰጣችሁ መንጋ መልካም ምሳሌ በመሆን እንጂ በላያቸው በመሠልጠን አይሁን።”—1 ጴጥሮስ 5:2, 3

አዎን፣ ሽማግሌዎች ያለባቸው ኃላፊነት ከእረኞች ተግባር ጋር ተመሳሳይ ነው። ሽማግሌዎች በመንፈሳዊ ለታመሙ ክርስቲያኖች እንክብካቤ ማድረግ የሚኖርባቸው ከመሆኑም በላይ የእነዚህ ሰዎች አኗኗር የጽድቅ መሥፈርቶችን የሚያንጸባርቅ እንዲሆን አስፈላጊውን ማስተካከያ እንዲያደርጉ ይረዷቸዋል። ሽማግሌዎች የጉባኤ እንቅስቃሴዎችን የማደራጀት፣ ለስብሰባ አስፈላጊ ዝግጅቶችን የማድረግና የጉባኤውን ሥርዓት የማስጠበቅ ኃላፊነት አለባቸው።—1 ቆሮንቶስ 14:33

ይሁን እንጂ ከላይ የተጠቀሱት የጴጥሮስ ቃላት አንድ አደጋ እንዳለ ይጠቁማሉ፤ ይኸውም ሽማግሌዎች በጉባኤው ላይ ‘ከመሠልጠን’ መቆጠብ እንደሚኖርባቸው ያስጠነቅቃቸዋል። አንድ ሽማግሌ አላስፈላጊ ሕጎችን ሊያወጣ ይችላል፤ ይህ ደግሞ በመንጋው ላይ ‘እየሠለጠነ’ እንዳለ ከሚጠቁሙት ምልክቶች ውስጥ አንዱ ነው። አንድ ሽማግሌ መንጋውን የመጠበቅ ግዴታውን በጣም አክብዶ ከመመልከቱ የተነሳ ከገደብ አልፎ አንዳንድ ነገሮችን ያደርግ ይሆናል። በሩቅ ምሥራቅ አገሮች በሚገኝ አንድ ጉባኤ ውስጥ ሽማግሌዎች በመንግሥት አዳራሽ ውስጥ ሌሎችን ሰላም ማለት የሚቻልበትን መንገድ በተመለከተ ሕጎችን አውጥተው የነበረ ሲሆን ከእነዚህም መካከል መጀመሪያ ማን መናገር እንደሚኖርበትና የመሳሰሉት ይገኙበታል። ሽማግሌዎቹ ይህን ያደረጉት እነዚህን ሕጎች መከተል ለጉባኤው ሰላም አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት ስለተሰማቸው ነው። ሽማግሌዎቹ ይህን ሕግ ያወጡት ከጥሩ ዓላማ ተነሳስተው መሆኑ ባያጠያይቅም ይሖዋ ሕዝቡን የሚይዝበትን መንገድ ኮርጀዋል ሊባል ይችላል? ሐዋርያው ጳውሎስ ስለዚህ ጉዳይ የነበረው አመለካከት በተናገራቸው ቃላት በግልጽ ተንጸባርቋል። ጳውሎስ “ጸንታችሁ የምትቆሙት በእምነት ስለ ሆነ፣ ደስ እንዲላችሁ ከእናንተ ጋር እንሠራለን እንጂ በእምነታችሁ ላይ ለመሠልጠን አይደለም” ብሏል። (2 ቆሮንቶስ 1:24) ይሖዋ በሕዝቦቹ ላይ እምነት ይጥላል።

አሳቢ የሆኑ ሽማግሌዎች መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሠረት የሌላቸውን ሕጎች ከማውጣት የሚቆጠቡ ከመሆኑም በተጨማሪ ምስጢር ጠባቂ በመሆን ለመንጋው አባላት ከልባቸው እንደሚያስቡ ማሳየት ይችላሉ። “የሌላውን ሰው ምስጢር አታውጣ” የሚለውን መለኮታዊ ማስጠንቀቂያ ልብ ይላሉ።—ምሳሌ 25:9

ሐዋርያው ጳውሎስ የቅቡዓን ክርስቲያኖችን ጉባኤ ከሰውነት ክፍል ጋር በማመሳሰል “እግዚአብሔር ግን የአካል ብልቶችን አንድ ላይ [ያገጣጠመው] . . . በአካል ብልቶች መካከል መለያየት ሳይኖር፣ እርስ በርሳቸው እኩል እንዲተሳሰቡ ነው” በማለት ተናግሯል። (1 ቆሮንቶስ 12:12, 24-26) “እርስ በርሳቸው እኩል እንዲተሳሰቡ” የሚለው ሐረግ ከግሪክኛ ቃል በቃል ሲተረጎም ‘አንዳቸው ለሌላው መጨነቅ ይገባቸዋል’ የሚል ሐሳብ ያስተላልፋል። የክርስቲያን ጉባኤ አባላት አንዳቸው የሌላው ጉዳይ ሊያሳስባቸው ይገባል።—ፊልጵስዩስ 2:4

እውነተኛ ክርስቲያኖች ‘አንዳቸው ለሌላው እንደሚጨነቁ’ የሚያሳዩት እንዴት ነው? ለሌሎቹ የጉባኤ አባላት በመጸለይና ለችግረኞች ተግባራዊ እርዳታ በማድረግ ነው። እንዲህ ማድረጋችን እነርሱም ለሌሎች መልካም እንዲያደርጉ ያበረታታቸዋል። እንዲህ ዓይነቱ ፍቅራዊ አሳቢነት ታዳታካን እንዴት እንደጠቀመው ተመልከት። በ17 ዓመቱ ሲጠመቅ ከቤተሰቡ ውስጥ ይሖዋን የሚያገለግለው እርሱ ብቻ ነበር። ሁኔታውን እንዲህ በማለት ይገልጻል:- “በጉባኤያችን የሚገኝ አንድ ቤተሰብ አብሬአቸው እንድመገብና ግብዣዎች ላይ እንድገኝ ብዙ ጊዜ ይጠሩኝ ነበር። በየቀኑ ማለት ይቻላል ጠዋት ጠዋት ወደ ትምህርት ቤት ስሄድ እግረ መንገዴን የዕለት ጥቅሱን ለመወያየት እነርሱ ቤት እሄዳለሁ። በትምህርት ቤት የሚያጋጥሙኝን ፈተናዎች መቋቋም የምችልበትን መንገድ በተመለከተ ምክር የሚሰጡኝ ከመሆኑም በላይ እነዚህን ጉዳዮች አንስተን አንድ ላይ እንጸልያለን። ከዚህ ቤተሰብ የልግስናን መንፈስ ተምሬአለሁ።” ታዳታካ በአሁኑ ወቅት በአንድ የይሖዋ ምሥክሮች ቅርንጫፍ ቢሮ ውስጥ በማገልገል የተማረውን በሥራ ላይ እያዋለ ነው።

ሐዋርያው ጳውሎስ ለሌሎች አሳቢ ከመሆን ጋር በተያያዘ ጥንቃቄ የሚያሻውን አንድ ለየት ያለ ጉዳይ ጠቅሷል። ‘የማይገባ ነገር ስለሚናገሩ ሐሜተኞችና በሰው ጉዳይ ጣልቃ ስለሚገቡ’ አንዳንድ ሴቶች ጠቅሶ ነበር። (1 ጢሞቴዎስ 5:13) የሌሎች ጉዳይ የሚያሳስበን መሆኑ ተገቢ ቢሆንም በግል ጉዳዮቻቸው ውስጥ ጣልቃ እንዳንገባ መጠንቀቅ ይኖርብናል። ‘የማይገባንን መናገራችን’ ለምሳሌ ያህል፣ ሌሎች ትክክል እንዳልሆኑ የሚገልጽ ሐሳብ መሰንዘራችን ለሌሎች አሳቢ በመሆን ረገድ ሚዛናችንን እንደሳትን ሊያሳይ ይችላል።

ክርስቲያኖች የግል ጉዳዮቻቸውን በሚያከናውኑበት መንገድ፣ በምግብ ምርጫቸው፣ በሚመርጡት ጤናማ የመዝናኛ ዓይነት ሊለያዩ እንደሚችሉ ማስታወስ ይኖርብናል። እያንዳንዱ ሰው በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተገለጹትን መሠረታዊ ሥርዓቶች እስካልጣሰ ድረስ የራሱን ውሳኔ የማድረግ ነፃነት አለው። ጳውሎስ በሮም ይኖሩ የነበሩትን ክርስቲያኖች “እርስ በርሳችን፣ አንዱ በሌላው ላይ ከመፍረድ እንቈጠብ፤ . . . ሰላም የሚገኝበትንና እርስ በርሳችንም የምንተናነጽበትን ማንኛውንም ጥረት እናድርግ” በማለት አሳስቧቸዋል። (ሮሜ 14:13, 19) በጉባኤ ውስጥ አንዳችን ለሌላው ከልባችን እንደምናስብ የምናሳየው በእነርሱ ጉዳይ ውስጥ ጣልቃ በመግባት ሳይሆን ችግር በሚኖርበት ጊዜ እነርሱን ለመርዳት ምንጊዜም ዝግጁ በመሆን ነው። በዚህ መንገድ እርስ በርስ መተሳሰባችን በቤተሰባችንም ሆነ በጉባኤያችን ውስጥ ፍቅርና አንድነት እንዲሰፍን ያደርጋል።

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

a አንዳንዶቹ ስሞች ተቀይረዋል።

[በገጽ 19 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

አመስጋኝ በመሆንና ራሳችሁን በእነርሱ ቦታ በማስቀመጥ ልጆቻችሁ ሐሳባቸውንና ስሜታቸውን አውጥተው እንዲናገሩ አድርጉ