ሳውል ከድሮ ጓደኞቹና ከቀድሞ ጠላቶቹ ጋር ተገናኘ
ሳውል ከድሮ ጓደኞቹና ከቀድሞ ጠላቶቹ ጋር ተገናኘ
ከጊዜ በኋላ ሐዋርያው ጳውሎስ የተባለው ሳውል ወደ ክርስትና ከተለወጠ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ኢየሩሳሌም የተመለሰው ትንሽ የፍርሃት ስሜት እየተሰማው መሆን አለበት። a ከሦስት ዓመታት በፊት ከተማዋን ለቅቆ የወጣው የኢየሱስን ደቀ መዛሙርት ለመግደል እየዛተ ነበር። በደማስቆ የሚያገኛቸውን ክርስቲያኖች በሙሉ ለማሰር የሚያስችል ሥልጣንም ተሰጥቶት ነበር።—የሐዋርያት ሥራ 9:1, 2፤ ገላትያ 1:18
ሳውል ክርስቲያን ከሆነ በኋላ፣ ከሞት በተነሳው መሲሕ ላይ ያለውን እምነት በድፍረት አውጇል። በመሆኑም በደማስቆ የሚገኙ አይሁዳውያን ሊገድሉት ፈለጉ። (የሐዋርያት ሥራ 9:19-25) በኢየሩሳሌም ከሚገኙት የቀድሞ አይሁዳውያን ጓደኞቹ ሞቅ ያለ አቀባበል ይደረግልኛል ብሎ ሊጠብቅ ይችላል? ይሁን እንጂ ሳውልን ይበልጥ ያሳሰበው በኢየሩሳሌም ካሉት የክርስቶስ ተከታዮች ጋር የመገናኘቱ ጉዳይ ነበር። ምክንያቱም ይህን ማድረግ ቀላል አልነበረም።
“ወደ ኢየሩሳሌም በመጣ ጊዜ፣ ከደቀ መዛሙርት ጋር ለመቀላቀል ሞከረ፤ እነርሱ ግን በእርግጥ ደቀ መዝሙር መሆኑን ስላላመኑ ሁሉም ፈሩት።” (የሐዋርያት ሥራ 9:26) ለምን እንደፈሩት መረዳት አያዳግትህም። ከጥቂት ጊዜያት በፊት ይህንን ሰው የሚያውቁት በጨካኝ አሳዳጅነቱ ነበር። ክርስቲያን ነኝ ማለቱ ወደ ጉባኤ ሰርጎ ለመግባት የፈጠረው የማታለያ ዘዴ ሊመስላቸው ይችላል። በመሆኑም በኢየሩሳሌም የነበሩት ክርስቲያኖች ሊያቀርቡት አልፈለጉም።
ይሁንና ከመካከላቸው አንዱ ሳውልን ረዳው። በርናባስ፣ ቀደም ሲል አሳዳጅ የነበረው ይህ ሰው መለወጡንና በደማስቆ መስበኩን በመንገር “ወደ ሐዋርያት” ማለትም ወደ ጴጥሮስ (ኬፋ) እና የኢየሱስ ወንድም ወደሆነው ወደ ያዕቆብ እንዳመጣው መጽሐፍ ቅዱስ ይገልጻል። (የሐዋርያት ሥራ 9:27፤ ገላትያ 1:18, 19) በርናባስ ሳውልን እንዴት ሊያምነው እንደቻለ ምንም የተገለጸ ነገር የለም። ምናልባት ሁለቱ ትውውቅ ኖሯቸው በርናባስ ሳውልን በጥንቃቄ ከመረመረው በኋላ በእርግጥ መለወጡን አምኖ ይሆን? ወይስ ደግሞ በርናባስ በደማስቆ የሚያውቃቸው ክርስቲያኖች ይኖሩ ይሆን? የሳውልን መለወጥ እነዚህ ክርስቲያኖች ነግረውት ይሆን? ምክንያቱ ምንም ይሁን ምን በርናባስ፣ ሐዋርያት በሳውል ላይ የነበራቸው ጥርጣሬ እንዲወገድ አድርጓል። በመሆኑም ሳውል ለ15 ቀን ሐዋርያው ጴጥሮስ ጋር ሰነበተ።
ከጴጥሮስ ጋር አሥራ አምስት ቀን ቆየ
ሳውል ለገላትያ ሰዎች ጠበቅ አድርጎ እንደገለጸው ተልዕኮውን የተቀበለው ከማንም ሰው ሳይሆን በቀጥታ ከኢየሱስ ነበር። (ገላትያ 1:11, 12) ይሁን እንጂ ሳውል ስለ ኢየሱስ አገልግሎት ይበልጥ ማወቅ እንደሚያስፈልገው እንደተገነዘበ ምንም ጥርጥር የለውም። ሳውል፣ ከጴጥሮስ ጋር መቆየቱ ደግሞ ስለ ኢየሱስ አገልግሎት ለማወቅ ሰፊ አጋጣሚ ከፍቶለታል። (ሉቃስ 24:12፤ 1 ቆሮንቶስ ) ሳውል፣ ጴጥሮስንና ያዕቆብን የሚጠይቃቸው ብዙ ነገሮች እንደሚኖሩት ሁሉ እነርሱም የተመለከተውን ራእይና የተሰጠውን ተልዕኮ በተመለከተ የሚጠይቁት ጥያቄ ይኖራቸዋል። 15:3-8
ከቀድሞ ጓደኞቹ ያመለጠው እንዴት ነበር?
እስጢፋኖስ የመጀመሪያው ክርስቲያን ሰማዕት ተብሎ ተጠርቷል። ቀደም ሲል እስጢፋኖስ የተከራከረው “‘የነጻ ወጪዎች ምኵራብ’ ተብሎ የሚጠራው ምኵራብ አባላት የሆኑ ከቀሬናና ከእስክንድርያ፣ እንዲሁም ከኪልቅያና ከእስያ” ከመጡ ሰዎች ጋር ነበር። አሁን ደግሞ ሳውል የተከራከረው “ከግሪክ አገር ከመጡት አይሁድ ጋር” ሲሆን በድፍረት ይመሠክርላቸው ነበር። ውጤቱ ምን ሆነ? ሰዎቹ ሊገድሉት ፈለጉ።—የሐዋርያት ሥራ 6:9፤ 9:28, 29
ሳውል በሕይወቱ ውስጥ ስላደረገው ከፍተኛ ለውጥ ለመናገር መፈለጉና ለቀድሞ ጓደኞቹ ስለ መሲሑ ለማብራራት ጥረት ማድረጉ ምክንያታዊ ነበር። ይሁን እንጂ ከግሪክ አገር የመጡት እነዚህ አይሁዳውያን እንደ ከሐዲ ስለቆጠሩት ለሳውል ጥላቻ አድሮባቸው ነበር።
ሳውል አደገኛ ሁኔታ ውስጥ መግባቱን አስተውሎ ነበር? ሳውል በቤተ መቅደስ ውስጥ ሲጸልይ ሳለ እንደተመሰጠና ኢየሱስን እንዳየው እርሱም “ፈጥነህ ከኢየሩሳሌም ውጣ! ስለ እኔ የምትመሰክረውን አይቀበሉህምና” እንዳለው በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ እናነባለን። ሳውልም የሚከተለውን ምላሽ ሰጠ:- “ጌታ ሆይ፤ በአንተ የሚያምኑትን ሰዎች ለማሰርና ለመደብደብ፣ በየምኵራቡ ስዞር እንደ ነበር እነዚህ ሰዎች ያውቃሉ፤ ደግሞም የአንተን ሰማዕት የእስጢፋኖስን ደም በሚያፈሱበት ጊዜ፣ በድርጊታቸው ተስማምቼ በቦታው ቆሜ . . . ነበር።”—የሐዋርያት ሥራ 22:17-20
አንዳንዶች ሳውል ይህን ሲል አደገኛ ሁኔታ ውስጥ መግባቱን የተረዳ መሆኑን መግለጹ እንደነበር ተሰምቷቸዋል። ሌሎች ደግሞ ሳውል፣ ‘እኔም እንደ እነርሱ አሳዳጅ ነበርኩ፤ ይህንን እነርሱም ያውቁታል። በመሆኑም መለወጤን በቁም ነገር ሊመለከቱት ይገባል። ምናልባትም ልረዳቸው እችል ይሆናል’ ማለቱ እንደነበር ይናገራሉ። ኢየሱስ ግን እነዚያ አይሁዳውያን እንደ ‘ከሐዲ’ የሚያዩትን ሰው ምሥክርነት እንደማይሰሙ አውቋል። ሳውልን “ሂድ፤ በሩቅ ወዳሉት አሕዛብ እልክሃለሁ” ያለው በዚህ ምክንያት ነው።—የሐዋርያት ሥራ 22:21, 22
የእምነት አጋሮቹ ጳውሎስ አደገኛ ሁኔታ ውስጥ መግባቱን ሲገነዘቡ በፍጥነት ወደ ቂሳርያ ወደብ በመውሰድ የትውልድ ከተማው ወደሆነችው ወደ ጠርሴስ ላኩት፤ ይህቺ ከተማ ከቂሳርያ ወደብ በ500 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ትገኛለች። (የሐዋርያት ሥራ 9:30) ሳውል እንደገና ወደ ኢየሩሳሌም የተመለሰው ከበርካታ ዓመታት በኋላ ነው።
ሳውል በፍጥነት አካባቢውን ለቅቆ መሄዱ ለክርስቲያን ጉባኤ ጥበቃ ሳይሆን አልቀረም። የቀድሞው አሳዳጅ በዚያ ቦታ መገኘት ከፍተኛ ችግር ሊያስከትል ይችላል። ሳውል ከዚያ ከሄደ በኋላ “በይሁዳ፣ በገሊላና በሰማርያ ያለችው ቤተ ክርስቲያን በሰላም መኖር ጀመረች፤ ተጠናከረችም። ደግሞም እግዚአብሔርን በመፍራት እየተመላለሰችና በመንፈስ ቅዱስ እየተጽናናች በቁጥር እየበዛች ሄደች።”—የሐዋርያት ሥራ 9:31
ጥንቃቄ ማድረግን በተመለከተ የምናገኛቸው ትምህርቶች
እንደ መጀመሪያው መቶ ዘመን ሁሉ ዛሬም ጥንቃቄ ማድረግ ተገቢ የሚሆንባቸው ሁኔታዎች ይኖራሉ። እንግዶችን ከልክ በላይ የምንጠረጥርበት ምንም ምክንያት የለንም። ይሁን እንጂ ይሉኝታ የሌላቸው ግለሰቦች ለግል ጥቅማቸው አሊያም ጉባኤውን ለመጉዳት ሲሉ የይሖዋን ሕዝቦች ለመበዝበዝ የሞከሩባቸው ጊዜያት አሉ። በመሆኑም በአስመሳዮች እንዳንታለል የማስተዋል ችሎታችንን መጠቀም ያስፈልገናል።—ምሳሌ 3:27፤ 2 ጢሞቴዎስ 3:13
ሳውል በኢየሩሳሌም ለመስበክ ያደረገው ሙከራ ክርስቲያኖች ጥንቃቄ ማድረግ የሚችሉበትን ሌላም መንገድ ይጠቁማል። በአንዳንድ አካባቢዎች አሊያም የቀድሞ ጓደኞቻችንን ጨምሮ ለአንዳንድ ግለሰቦች መመሥከር አካላዊ፣ መንፈሳዊና ሥነ ምግባራዊ ጉዳት ሊያስከትል ይችላል። በምንመሠክርበት ጊዜ አስፈላጊውን ጥንቃቄ ማድረጋችን ለምሳሌ ያህል ጊዜውንና ቦታውን መምረጣችን ተገቢ ነው።—ምሳሌ 22:3፤ ማቴዎስ 10:16
የዚህ ክፉ ሥርዓት ፍጻሜ ከመምጣቱ በፊት የአምላክ መንግሥት ምሥራች እንደሚሰበክ እርግጠኞች መሆን እንችላለን። ሳውል ለድሮ ጓደኞቹና ለቀድሞ ጠላቶቹ እንኳ ሳይቀር ለማንኛውም ሰው ‘በጌታ ስም በድፍረት በመናገር’ ረገድ እንዴት ያለ ግሩም ምሳሌ ትቷል!—የሐዋርያት ሥራ 9:28
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
a ሳውል በዛሬው ጊዜ ይበልጥ የሚታወቀው ሐዋርያው ጳውሎስ በሚለው ስሙ ነው። ይሁን እንጂ በዚህ ርዕስ ላይ በተጠቀሱት በአብዛኞቹ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች ላይ የተገለጸው፣ ሳውል በሚለው የአይሁድ ስሙ ነው።—የሐዋርያት ሥራ 13:9
[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ሳውል ኢየሩሳሌም እንደደረሰ ግሪክኛ ተናጋሪ ለሆኑ አይሁዳውያን በድፍረት መሥክሯል