በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

አንድ ዓመት ‘በመልካሚቱ ምድር’

አንድ ዓመት ‘በመልካሚቱ ምድር’

አንድ ዓመት ‘በመልካሚቱ ምድር’

በኢየሩሳሌም ምዕራባዊ ክፍል የባሕር ዳርቻ አካባቢ፣ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ስሟ የተጠቀሰ ጌዝር የምትባል ከተማ ትገኛለች። በ1908፣ በአሥረኛው መቶ ዘመን ከክርስቶስ ልደት በፊት እንደተቀረጸ የሚገመት ትንሽ የበሃ ድንጋይ በዚህች ከተማ ተገኘ። በድንጋዩ ላይ የተቀረጸው ጽሑፍ በጥንቱ የዕብራይስጥ አጻጻፍ ስልት የተጻፈ ሲሆን በዓመት ውስጥ ያሉትን የእርሻ ወቅቶችና በእነዚህ ወቅቶች የሚደረጉትን እንቅስቃሴዎች ባጭሩ የሚዘረዝር እንደሆነ ይገመታል። ይህ የበሃ ድንጋይ የጌዝር የቀን መቁጠሪያ የሚል ስያሜ ተሰጥቶታል።

በድንጋዩ ላይ ‘አብያ’ የሚል ፊርማ ሰፍሮበታል። ሁሉም አርኪኦሎጂስቶች ባይስማሙበትም እንኳ ብዙዎቹ አንድ ተማሪ በግጥም መልክ የጻፈው የቤት ሥራ እንደሆነ ያምናሉ። a የመልካሚቱ ምድር የእርሻ ወቅቶች በአንድ ትንሽ ልጅ እይታ ምን እንደሚመስሉ ለማወቅ ትፈልጋለህ? ይህን ማወቅህ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሱ አንዳንድ ክንውኖችን ለማስታወስ ይረዳህ ይሆናል።

ሁለት የመከር ወራት

የዚህ ጥንታዊ የቀን መቁጠሪያ ጸሐፊ መጀመሪያ ላይ ያሰፈረው አጠቃላዩን የመከር ወቅት ነው። ይህ ወቅት በቀን መቁጠሪያው መጀመሪያ ላይ የሰፈረ ቢሆንም እስራኤላውያን ይህን የመከር ጊዜ የዋናው የእርሻ ወቅት ማብቂያ አድርገው ይመለከቱት የነበረው ለምን እንደሆነ መረዳት አያዳግትህም። ኢታኒም (ከጊዜ በኋላ ቲሽሪ ተብሏል) በዘመናችን የቀን አቆጣጠር ከመስከረም አጋማሽ እስከ ጥቅምት አጋማሽ ያለውን ጊዜ ያመለክታል። አብዛኛው የመከር ሥራ የሚጠናቀቀው በእነዚህ ወራት ስለነበር ይህ ወቅት ትንሹን አብያን ጨምሮ ለሁሉም እስራኤላውያን የደስታ ጊዜ ነበር። አብያ ለአንድ ሳምንት የሚቆዩበትን ዳስ ከአባቱ ጋር ሆኖ ሲሠራ ምን ያህል እንደሚደሰት አስብ! በእነዚህ ቀናት ይሖዋን ለሰጣቸው ምርት ያመሰግኑታል።—ዘዳግም 16:13-15

በዚህ ጊዜ አካባቢ የወይራ ፍሬዎች መብሰል ስለሚጀምሩ የአብያ ቤተሰብ ቅርንጫፎቹን በመምታት ያራግፏቸዋል። ይህ ሥራ እንደ አብያ ላለ ትንሽ ልጅ ከባድ ስለሚሆን በሥራው ላይ መካፈል ባይችልም እንኳ ሌሎች ሲሠሩ ማየቱ ግን ሳያስደስተው አይቀርም። (ዘዳግም 24:20) ፍሬዎቹን ከለቀሙ በኋላ ዘይት ለመጭመቅ በአቅራቢያቸው ወደሚገኝ የድንጋይ ወፍጮ ይወስዱታል። አንዳንድ ቤተሰቦች ደግሞ የተፈነከቱ ወይም የተጨፈለቁ የወይራ ፍሬዎችን ውኃ ውስጥ ከዘፈዘፉ በኋላ ከላይ የሚሰፈውን ዘይት በመጨለፍ በቀላሉ ዘይት ያወጣሉ። ዘይቱ የተዘጋጀበት መንገድ ምንም ይሁን ምን፣ ይህ አስፈላጊ ፈሳሽ ለምግብነት ብቻ የሚውል አልነበረም። ከዚህ ይልቅ ለመብራት እንዲሁም እንደ አብያ ያለ ልጅ ሲጫወት ሊያጋጥመው የሚችለውን ጉዳትና ቁስል ለማከም ያገለግላል።

ዘር የሚዘራባቸው ሁለት ወራት

አብያ የፊተኛው ማለትም የበልግ ዝናብ መዝነብ ሲጀምርና ቀዝቃዛው ውኃ ሰውነቱ ላይ ሲያርፍ ምን ያህል እንደሚደሰት ገምት። በዚህ ጊዜ፣ አባቱ ዝናብ ለመሬት ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ ነግሮት ይሆናል። (ዘዳግም 11:14) ለወራት በዘለቀው ፀሐይ ክው ብሎ የደረቀው አፈር በዝናቡ ስለሚርስ ለመታረስ ምቹ ይሆናል። የጥንቱ እስራኤላዊ ገበሬ የብረት ድግር ያለውን ሞፈር ከብት ላይ ጠምዶ ያርሳል። በተቻለው መጠን ቀጥ ያለ ትልም ለማውጣት ይጥራል። መሬት በጣም ውድ ስለሆነ ገበሬዎቹ ተዳፋት የሆነውን ጨምሮ በቁራሽ መሬት ላይ እንኳ ይዘራሉ። ይሁንና ተዳፋት የሆኑትን ቦታዎች በእጃቸው መቆፈር ይኖርባቸዋል።

በውኃ የራሰው መሬት ከታረሰ በኋላ ስንዴና ገብስ ይዘራበታል። በጌዝር የቀን መቁጠሪያ ላይ ቀጥሎ የተጠቀሰው፣ ሁለት ወር የሚፈጀው ይህ የዘር ወቅት መሆኑ ትኩረት የሚስብ ነው። ገበሬው ዘሩን በልብሱ ይይዝና በእጁ እየዘገነ ይበትነዋል።

የኋለኞቹ ሁለት የዘር ወራት

‘በመልካሚቱ ምድር’ ሰብል የማይመረትበት ወቅት የለም። (ዘዳግም 3:25) የዝናቡ መጠን ከፍተኛ በሚሆንበት በታኅሣሥ ወር መሬቱ አረንጓዴ ይለብሳል። በዚህ ወቅት እንደ አተርና ሽምብራ ያሉ ጥራጥሬዎች የሚዘሩ ሲሆን ሌሎች አትክልቶችም ይተከላሉ። (አሞጽ 7:1, 2 NW) አብያ ይህንን ጊዜ “የግጦሽ ሣር የሚበቅልባቸው የጸደይ ወራት” ወይም እንደ ሌሎች አተረጓጎም “የኋለኛው የዘር ወቅት” በማለት ጠርቶታል። በእነዚህ ወራት ከተለያዩ የአትክልት ዓይነቶች የሚዘጋጁ ጣፋጭ ምግቦች እንደ ልብ ይገኛሉ።

ቅዝቃዜው እየለቀቀ አየሩ መሞቅ ሲጀምር ጸደይ መድረሱን የሚያበስረው የለውዝ ዛፍ ነጭና ሮዝ አበባዎች ያብባል። ይህ ሁኔታ አየሩ ገና ሞቅ ማለት በሚጀምርበት በጥር ወር እንኳ ሊታይ ይችላል።—ኤርምያስ 1:11, 12

ተልባ የሚታጨድበት አንድ ወር

አብያ ቀጥሎ የጠቀሰው ስለ ተልባ ነው። ይህ ደግሞ አብያ ከመወለዱ ከብዙ ዘመናት በፊት ከይሁዳ ኮረብቶች በስተ ምሥራቅ በምትገኘው በኢያሪኮ የተፈጸመውን ሁኔታ አስታውሶህ ይሆናል። በዚህች ከተማ ትኖር የነበረችው ረዓብ ሁለቱን ሰላዮች በቤቷ ጣራ ላይ እንዲደርቅ “በረበረበችው የተልባ እግር ውስጥ” ደብቃቸው ነበር። (ኢያሱ 2:6) ተልባ በእስራኤላውያን ሕይወት ውስጥ ትልቅ ቦታ ነበረው። ቃጫውን ለማውጣት መጀመሪያ የተልባ እግሩ መበስበስ ይኖርበታል። ይህም በጤዛ እርጥበት አማካኝነት ሊደረግ ይችላል። ቶሎ እንዲበሰብስ ከተፈለገ ደግሞ በኩሬ ወይም በምንጭ ውኃ ውስጥ ይዘፈዘፋል። ቃጫው ከተለየ በኋላ ሊኖ የተባለ ጨርቅ ይሠራበታል። ይህ ጨርቅ ደግሞ የመርከብ ሸራ፣ ድንኳንና አልባሳት ለመሥራት ያገለግላል። ከዚህም በተጨማሪ ከተልባ እግር የኩራዝ ክር ይሠራል።

አንዳንዶች ውኃ እንደልብ በማይገኝበት በጌዝር አካባቢ ተልባ ይበቅል ነበር በሚለው ሐሳብ አይስማሙም። ሌሎች ደግሞ ተልባ የሚመረተው በዓመቱ መጨረሻ ላይ እንደሆነ ይናገራሉ። በዚህም ምክንያት አንዳንዶች በጌዝር የቀን መቁጠሪያ ላይ የተጠቀሰው “ተልባ” ተብሎ የተተረጎመው ቃል “የሣር” ድርቆሽን ያመለክታል ይላሉ።

የገብስ ሰብል የሚሰበሰብበት አንድ ወር

ቀጥሎ አብያ በቀን መቁጠሪያው ላይ ያሰፈረው፣ በየዓመቱ ተልባ ከታጨደ በኋላ የሚደርሰውን የገብስ እሸት ነው። ይህ ወቅት በዕብራይስጥ አቢብ በሚባለው ወር ላይ ይውላል። አቢብ ማለት “እሸት” ማለት ሲሆን፣ ይህም የገብሱ ዛላ ቢደርስም ገና ለጋ መሆኑን የሚያመለክት ሊሆን ይችላል። ይሖዋ “የአቢብን ወር ጠብቅ፤ የአምላክህን የእግዚአብሔርን ፋሲካ አክብርበት” የሚል ትእዛዝ ሰጥቷል። (ዘዳግም 16:1) አቢብ (ከጊዜ በኋላ ኒሳን ተብሏል) በዘመናችን የቀን አቆጣጠር ከመጋቢት አጋማሽ እስከ ሚያዝያ አጋማሽ ያለውን ጊዜ ያመለክታል። የገብሱ መድረስ ይህ ወር የሚጀምርበትን ጊዜ ለይቶ ለማወቅ ሳይረዳ አልቀረም። በዛሬው ጊዜም እንኳ ቀረዓት አይሁዳውያን አዲስ ዓመት የሚጀምርበትን ጊዜ ለመወሰን የገብስ ሰብል ማሸቱን ይጠባበቃሉ። ያም ሆነ ይህ፣ አቢብ ወር በገባ በ16ኛው ቀን ካህኑ የመጀመሪያውን የገብስ ነዶ በይሖዋ ፊት ይወዘውዝ ነበር።—ዘሌዋውያን 23:10, 11

ገብስ በአብዛኞቹ እስራኤላውያን የዕለት ተዕለት ሕይወት ውስጥ ትልቅ ድርሻ ነበረው። ስንዴ ውድ ስለነበር በተለይ ድሆች የገብስ ዳቦ መጋገር ይመርጡ ነበር።—ሕዝቅኤል 4:12

መከር የሚሰበሰብበትና እህል የሚሰፈርበት አንድ ወር

አብያ የኖረበትን ዘመን መለስ ብለህ ብታስብ፣ አንድ ቀን ማለዳ ላይ አብያ ደመናው እየሳሳ እንደሆነ ሲመለከት ለተወሰነ ጊዜ ዝናብ እንደማይኖር ተገንዝቦ እንደሚሆን መገመት ትችላለህ። በዚህ ጊዜ በመልካሚቱ ምድር የሚበቅሉት እፅዋት እድገታቸው የሚመካው በጤዛ ላይ ነው። (ዘፍጥረት 27:28፤ ዘካርያስ 8:12) እስራኤላውያን ገበሬዎች፣ በዓመቱ ውስጥ ፀሐያማ በሆኑት ወራት የሚሰበሰቡት አብዛኞቹ ሰብሎች እስከ ጰንጠቆስጤ በዓል ባለው ጊዜ ውስጥ መጠኑን የጠበቀ ነፋስ እንደሚያስፈልጋቸው ያውቁ ነበር። ከሰሜን አቅጣጫ የሚነፍሰው ቀዝቃዛና እርጥበት አዘል አየር ለጥራጥሬ እህሎች እድገት ጠቃሚ ቢሆንም ላበቡ የፍራፍሬ ዛፎች ግን አደገኛ ነው። ከደቡብ የሚነፍሰው ሞቃታማና ደረቅ አየር ደግሞ የዛፎቹ አበቦች እንዲፈኩ በማድረግ እንዲራቡ መንገድ ይከፍታል።—ምሳሌ 25:23፤ ማሕልየ መሓልይ 4:16

የአየር ሁኔታን መቆጣጠር የሚችለው ይሖዋ፣ ምድራችን የተስተካከለ ሥነ ምህዳር እንዲኖራት አድርጎ ፈጥሯታል። በአብያ ዘመን እስራኤል “ስንዴና ገብስ፣ ወይንና የበለስ ዛፎች፣ ሮማን፣ የወይራ ዘይትና ማር የሚገኝባት ምድር” ነበረች። (ዘዳግም 8:8) ምናልባት አያቱ የይሖዋ በረከት በግልጽ በታየበት በጠቢቡ ንጉሥ ሰሎሞን የግዛት ዘመን ስለነበረው የተትረፈረፈ ብልጽግና ለአብያ ነግረውት ሊሆን ይችላል።—1 ነገሥት 4:20

በቀን መቁጠሪያው ላይ ስለ መከር መሰብሰብ ከተጠቀሰ በኋላ አንዳንዶች “መስፈር” የሚል ፍቺ የሰጡት ቃል ይገኛል። ይህ ቃል ከተሰበሰበው እህል ላይ የተወሰነው ተሰፍሮ ለእርሻው ባለቤቶችና ለሠራተኞች እንደሚሰጥ ወይም ደግሞ ለግብር ክፍያ እንደሚውል የሚያመለክት ሊሆን ይችላል። ይሁንና ሌሎች ምሁራን ይህ የዕብራይስጥ ቃል “ድግስ” የሚል ትርጉም እንዳለውና በሲቫን ወር (ከግንቦት አጋማሽ እስከ ሰኔ አጋማሽ ያለውን ጊዜ ያመለክታል) የሚከበረውን የሰባቱን ሱባዔ በዓል እንደሚያመለክት ይሰማቸዋል።—ዘፀአት 34:22

የወይን ቅጠል የሚመለመልበት ሁለት ወር

አብያ በቀን መቁጠሪያው ላይ ቀጥሎ የጻፈው ለወይን ተክል እንክብካቤ ስለሚደረግባቸው ሁለት ወራት ነው። የወይን ዘለላዎቹ የፀሐይ ብርሃን እንዲያገኙ ሲባል እጅብ ያሉት ቅጠሎች በሚመለመሉበት ጊዜ አብያ በሥራው ላይ ተካፍሎ መሆን አለበት። (ኢሳይያስ 18:5) ከዚያ በኋላ፣ በዚያን ዘመን ለነበሩ ወጣቶች በጣም አስደሳች የሆነው ወቅት ይኸውም የወይን ዘለላ የሚቆረጥበት ጊዜ ይደርሳል። መጀመሪያ የሚደርሱት የወይን ፍሬዎች እጅግ ጣፋጭ ናቸው! አብያ ሙሴ ተስፋይቱን ምድር እንዲሰልሉ ስለላካቸው 12 ሰላዮች ሳይሰማ አይቀርም። እነዚህ ሰላዮች የምድሪቱን መልካምነት ለማየት የሄዱት የወይን ፍሬ መብሰል በጀመረበት ጊዜ ነበር። በዚያን ወቅት፣ የወይን ዘለላዎች ያንዠረገገ አንድ ቅርንጫፍ በጣም ትልቅ ከመሆኑ የተነሳ ሁለት ሰዎች መሸከም ነበረባቸው!—ዘኍልቍ 13:20, 23

የበጋ ፍራፍሬ የሚደርስበት አንድ ወር

አብያ በቀን መቁጠሪያው መጨረሻ ላይ ያሰፈረው የበጋ ፍራፍሬዎች የሚደርሱበትን ጊዜ ነው። በጥንት ጊዜ በመካከለኛው ምሥራቅ በበጋ ወቅት ትኩረት የሚደረገው በፍራፍሬ ምርት ላይ ነበር። አብያ ከኖረበት ዘመን በኋላ ይሖዋ ‘በሕዝቡ በእስራኤል ላይ ፍጻሜ መምጣቱን’ ለማመልከት ‘የጎመራ [“የበጋ፣” NW] ፍሬ የሞላበትን ቅርጫት’ እንደ ምሳሌ ተጠቅሟል። በዚህ ምሳሌ ላይ ‘ፍጻሜው’ ‘ከበጋ ፍሬ’ ጋር ተነጻጽሯል። (አሞጽ 8:2) ይህ ምሳሌ ታማኝ ያልሆኑትን እስራኤላውያን ፍጻሜው መቅረቡንና የይሖዋ ፍርድ መድረሱን አስገንዝቧቸው መሆን አለበት። አብያ ከጠቀሳቸው የበጋ ፍራፍሬዎች መካከል የበለስ ፍሬ እንደሚኖር ግልጽ ነው። የበለስ ጥፍጥፍ ለምግብነትና ለቁስል ማከሚያ ያገለግላል።—2 ነገሥት 20:7

የጌዝር የቀን መቁጠሪያ ለአንተ ምን ትርጉም አለው?

ወጣቱ አብያ በአካባቢው ስለሚከናወነው የግብርና ሥራ በደንብ ያውቅ እንደነበር ግልጽ ነው። በዚያን ዘመን የአብዛኞቹ እስራኤላውያን ሕይወት ከግብርና ጋር የተቆራኘ ነበር። ስለ እርሻ ብዙም የምታውቀው ነገር ባይኖርም በጌዝር በተገኘው ድንጋይ ላይ ስለተቀረጸው ጽሑፍ ማወቅህ፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብህ ግልጽና ትርጉም ያለው እንዲሁም ሕያው እንዲሆንልህ ያደርጋል።

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

a በጌዝር የቀን መቁጠሪያ ላይ የሰፈረው የወቅቶች ዝርዝር በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከተጠቀሰው የቀን አቆጣጠር የተወሰነ ልዩነት አለው። ከዚህም በላይ አንዳንድ የእርሻ ሥራዎች የሚከናወኑበት ጊዜ እንደየአካባቢው ሁኔታ በመጠኑ ሊለያይ ይችላል።

[በገጽ 11 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

የጌዝር የቀን መቁጠሪያ ያመለክታቸዋል ተብለው የሚታሰቡት ወቅቶች:-

“ምርጥ እህል የሚመረትባቸውና የወይራ ፍሬ የሚሰበሰብባቸው ወራት፤

ዘር የሚዘራባቸው ወራት፤

የግጦሽ ሣር የሚበቅልባቸው የጸደይ ወራት፤

ተልባ የሚታጨድበት ወር፤

የገብስ ሰብል የሚሰበሰብበት ወር፤

መከር የሚሰበሰብበትና እህል የሚሰፈርበት ወር፤

ወይን የሚገረዝባቸው ወራት፤

የበጋ ፍራፍሬ የሚደርስበት ወር።”

[ፊርማ:-] አብያ b

b [የግርጌ ማስታወሻዎች]

በ1971፣ ጆን ሲ ኤል ጊብሰን ባዘጋጀው ቴክስትቡክ ኦቭ ሲሪያን ሴሜቲክ ኢንስክሪፕሽንስ በተባለ መጽሐፍ ጥራዝ 1 ላይ የተመሠረተ።

[ምንጭ]

Archaeological Museum of Istanbul

[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሰንጠረዥ/ሥዕሎች]

(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)

ኒሳን (አቢብ)

መጋቢት​—ሚያዝያ

ኢያር (ዚቭ)

ሚያዝያ​—ግንቦት

ሲቫን

ግንቦት​—ሰኔ

ታሙዝ

ሰኔ​—ሐምሌ

አብ

ሐምሌ​—ነሐሴ

ኤሉል

ነሐሴ​—መስከረም

ቲሽሪ (ኢታኒም)

መስከረም​—ጥቅምት

ሄሽቫን (ቡል)

ጥቅምት​—ኅዳር

ካሴሉ

ኅዳር​—ታኅሣሥ

ቴቤት

ታኅሣሥ​—ጥር

ሳባጥ

ጥር​—የካቲት

አዳር

የካቲት​—መጋቢት

ቬአዳር

መጋቢት

[ምንጭ]

ገበሬ:- Garo Nalbandian

[በገጽ 8 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በጌዝር የተካሄደው የመሬት ቁፋሮ

[ምንጭ]

© 2003 BiblePlaces.com

[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የለውዝ ዛፍ

[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የተልባ ተክል

[ምንጭ]

Dr. David Darom

[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ገብስ

[ምንጭ]

U.S. Department of Agriculture