በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የሥነ ምግባር ደንቦች የሚለዋወጡበት ዓለም

የሥነ ምግባር ደንቦች የሚለዋወጡበት ዓለም

የሥነ ምግባር ደንቦች የሚለዋወጡበት ዓለም

አንድ በሰፊው የሚታወቅ አፈ ታሪክ፣ ታማኝ ሰው ፍለጋ በጠራራ ፀሐይ ፋኖስ ይዞ ይዞር ስለነበረ አንድ ሰው ይናገራል። ይህ ሰው በአራተኛው መቶ ዘመን ከክርስቶስ ልደት በፊት በአቴንስ ይኖር የነበረው ዳያጀኒዝ የተባለ ፈላስፋ ነው።

ይህ አፈ ታሪክ እውነት ይሁን አይሁን የሚታወቅ ነገር የለም። ይሁንና ዳያጀኒዝ ዛሬ በሕይወት ቢኖር ኖሮ ጥሩ ሥነ ምግባር ያላቸውን ሰዎች ለማግኘት የበለጠ መልፋቱ አይቀርም ነበር። ሰዎች ቋሚ የሥነ ምግባር ደንብ ሊኖራቸው ይገባል የሚለውን ሐሳብ ብዙዎች የሚቀበሉት አይመስልም። መገናኛ ብዙሃን በመንግሥት ደረጃ፣ በሰዎች የግል ሕይወት፣ በሥራውና በስፖርቱ ዓለም፣ በንግዱ ማኅበረሰብ እንዲሁም በተለያዩ ዘርፎች ስለሚታየው የሥነ ምግባር ውድቀት በተደጋጋሚ ይዘግባሉ። ያለፈው ትውልድ ከፍ አድርጎ ይመለከታቸው የነበሩት በርካታ የሥነ ምግባር እሴቶች በአሁኑ ጊዜ ቦታ የላቸውም። ባለፉት ጊዜያት ሲሠራባቸው የቆዩ መሥፈርቶች እንደገና የሚገመገሙ ሲሆን በአብዛኛው ውድቅ እንዲሆኑ ይደረጋል። ሌሎች የሥነ ምግባር ደንቦች ደግሞ በንድፈ ሐሳብ ደረጃ አድናቆት የሚቸራቸው ቢሆኑም በተግባር ላይ አይውሉም።

የሃይማኖት ሶሺዮሎጂስት የሆኑት አለን ዎልፍ እንዲህ ብለዋል:- “ሰፊ ተቀባይነት የነበራቸው የሥነ ምግባር መሥፈርቶች ጊዜ ያለፈባቸው ሆነዋል። የሰዎች የሥነ ምግባር አቋም በባሕል እንዲሁም ተቋማት ባወጧቸው መሥፈርቶች ላይ የተመካ መሆን የለበትም የሚለው አስተሳሰብ ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ ተቀባይነት አግኝቷል።” ሎስ አንጀለስ ታይምስ ያለፉትን 100 ዓመታት አስመልክቶ ጆናታን ግሎቨር የተባሉ ፈላስፋ የታዘቡትን በመጥቀስ በዓለም አቀፍ ደረጃ ለዓመጽ መስፋፋት ትልቁን ሚና የተጫወተው፣ ሃይማኖትና ሰፊ ተቀባይነት የነበራቸው የሥነ ምግባር ደንቦች እየተዳከሙ መሄዳቸው መሆኑን ዘግቧል።

ሰፊ ተቀባይነት ያላቸውን የሥነ ምግባር እሴቶች በተመለከተ የተፈጠረው ግራ መጋባት፣ አንዳንድ ሰዎችን ቋሚ የሥነ ምግባር ደንብ ከመፈለግ አላገዳቸውም። የቀድሞው የዩኔስኮ ዋና ዳይሬክተር ፌዴሪኮ ማዮር ከጥቂት ዓመታት በፊት እንዲህ ብለው ነበር:- “ዓለማችንን ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ የሚያሳስበው የሥነ ምግባር እሴቶች ጉዳይ ነው።” ይሁንና ዓለም መልካም የሆኑ የሥነ ምግባር ደንቦች ሊኖሩት አለመቻሉ ልንመራባቸው የሚገቡ ጤናማ የሥነ ምግባር ደንቦች ከናካቴው እንደሌሉ የሚያሳይ አይደለም።

ይሁን እንጂ ‘የትኛውን መሥፈርት እንከተል?’ ለሚለው ጥያቄ ሁሉም ሰው አንድ ዓይነት መልስ ይኖረዋል? እንደማይኖረው ግልጽ ነው። ታዲያ ትክክልና ስህተት ናቸው ለሚባሉት ነገሮች ተመሳሳይ አቋም ከሌለ፣ አንድ ሰው አንድ የሥነ ምግባር ደንብ ትክክል መሆንና አለመሆኑን እንዴት ማወቅ ይችላል? የሥነ ምግባር ደንብ እንደየሰዉ ይለያያል የሚለው አመለካከት በዛሬው ጊዜ ሰፊ ተቀባይነት አግኝቷል። ሆኖም ይህ አመለካከት ሰዎች የተሻለ የሥነ ምግባር አቋም እንዲኖራቸው እንዳላደረገ ማስተዋል ትችላለህ።

እንዲያውም እንግሊዛዊው ታሪክ ጸሐፊ ፖል ጆንሰን፣ ይህ ፍልስፍና ከ20ኛው መቶ ዘመን በፊት ጎልተው ይታዩ የነበሩት “የግል ኃላፊነትን የመወጣት ስሜት እንዲሁም ቋሚና ትክክለኛ የሆነ የሥነ ምግባር ደንብን የመከተል የሞራል ግዴታ ዝቅ ተደርገው እንዲታዩ ምክንያት አንደሆነ” አጥብቀው እንደሚያምኑ ገልጸዋል።

ታዲያ “ትክክለኛ የሆነ የሥነ ምግባር ደንብ” ማግኘት ወይም ‘ሰፊ ተቀባይነት ባገኙ የሥነ ምግባር ደንቦች’ መመራት ይቻል ይሆን? የተረጋጋ ሕይወት እንድንመራ የሚያስችሉንና ብሩሕ ተስፋ የሚፈነጥቁልን፣ ጊዜ የማይሽራቸው ቋሚ የሥነ ምግባር ደንቦች የማውጣት ሥልጣን ያለው አካል ይኖራል? የሚቀጥለው ርዕስ ለእነዚህ ጥያቄዎች መልስ ይሰጣል።