በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የአንባቢያን ጥያቄዎች

የአንባቢያን ጥያቄዎች

የአንባቢያን ጥያቄዎች

ሔዋንን ያነጋገራት እባብ እግሮች ነበሩት?

ዘፍጥረት 3:14 ላይ እንደተዘገበው በኤደን ገነት ሔዋንን ያሳታትን እባብ ይሖዋ አነጋግሮታል። አምላክ እንዲህ አለው:- “ይህን ስለ ሠራህ፣ ‘ከከብቶችና ከዱር እንስሳት ሁሉ ተለይተህ የተረገምህ ሁን፤ በሕይወትህ ዘመን ሁሉ፣ በደረትህ እየተሳብህ ትሄዳለህ፤ ዐፈርም ትበላለህ።’” መጽሐፍ ቅዱስ ሔዋንን ለማሳሳት ያገለገለው እንስሳ እርሷን ባነጋገረበት ጊዜ እግሮች እንደነበሩት የገለጸው ነገር የለም። የዘፍጥረት 3:14 አጻጻፍ አንዳንዶችን እንዲህ ብለው እንዲያስቡ ቢያደርጋቸውም፣ እባቦች ከዚህ እርግማን በፊት እግር ነበራቸው ብለን መደምደም አይኖርብንም። ለምን?

በመጀመሪያ ደረጃ ይሖዋ ፍርዱን ያስተላለፈው በእባቡ ላይ ሳይሆን ይህንን እንስሳ ለመጥፎ ተግባር በተጠቀመበት መንፈሳዊ ፍጡር ማለትም በሰይጣን ላይ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ ሰይጣንን ‘የሐሰት አባት’ እና ‘የጥንቱ እባብ’ በማለት ይጠራዋል። እነዚህ ሁለት መጠሪያዎች ሔዋን የአምላክን ትእዛዝ እንድትተላለፍ ለማድረግ ሰይጣን በሚታይ እንስሳ ይኸውም በእባብ እንደተጠቀመ ይጠቁሙናል።—ዮሐንስ 8:44፤ ራእይ 20:2

እባቦችን የፈጠራቸው አምላክ ነው፤ አዳም ደግሞ ስም ያወጣላቸው ሰይጣን ሔዋንን ለማሳት በእባብ ከመጠቀሙ በፊት ነው። ሔዋንን ያነጋገራት እባብ የማሰብና የማመዛዘን ችሎታ ስለሌለው ለተንኮል ድርጊቱ ተጠያቂ አይሆንም። እባቡ፣ ሰይጣን እየተጠቀመበት እንዳለ የማያውቅ ከመሆኑም ሌላ አምላክ በዓመጸኞቹ ላይ ያስተላለፈውን ፍርድ መረዳት አይችልም።

ታዲያ አምላክ እባቡን ‘በደረትህ ትሳባለህ’ ሲል የረገመው ለምንድን ነው? እባብ መሬት ለመሬት በደረቱ እየተሳበ፣ አፈር የሚልስ ይመስል ምላሱን ቶሎ ቶሎ የሚያወጣ መሆኑ ሰይጣን ያለበትን የተዋረደና ዝቅተኛ ሁኔታ ለመግለጽ ተስማሚ ምሳሌ ነው። ሰይጣን ቀደም ሲል ከፍ ያለ ቦታ የነበረው የአምላክ መልአክ ቢሆንም በአሁኑ ወቅት፣ መጽሐፍ ቅዱስ እንጦርጦስ ብሎ በሚጠራው መዋረድን በሚያመለክት ሁኔታ ውስጥ ይገኛል።—2 ጴጥሮስ 2:4 NW

በተጨማሪም፣ እባብ የሰውን ተረከዝ ሊያቆስል እንደሚችል ሁሉ የተዋረደው ሰይጣንም የአምላክን “ዘር” ‘ተረከዝ ይቀጠቅጣል።’ (ዘፍጥረት 3:15) የዚህ ዘር ዋነኛ ክፍል ኢየሱስ ክርስቶስ ሲሆን የሰይጣን ወኪሎች ጊዜያዊ ጉዳት አድርሰውበታል። የምሳሌያዊው እባብ ራስ ግን ውሎ አድሮ በክርስቶስና ትንሣኤ ባገኙት ቅቡዓን ባልንጀሮቹ አማካኝነት ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ይቀጠቀጣል። (ሮሜ 16:20) በመሆኑም አምላክ እባቡን መርገሙ፣ መንፈሳዊ ፍጡር የሆነው ‘የጥንቱ እባብ’ ማለትም ሰይጣን ዲያብሎስ እንደሚዋረድና በስተ መጨረሻም እንደሚጠፋ የሚያሳይ ተስማሚ ምሳሌ ነው።