በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ይሖዋ ታዛዥነትህን ከፍ አድርጎ ይመለከተዋል

ይሖዋ ታዛዥነትህን ከፍ አድርጎ ይመለከተዋል

ይሖዋ ታዛዥነትህን ከፍ አድርጎ ይመለከተዋል

“ልጄ ሆይ፤ ጠቢብ ሁን፤ ልቤን ደስ አሰኘው።”—ምሳሌ 27:11

1. በዘመናችን ባለው ኅብረተሰብ ውስጥ ተንሰራፍቶ የሚገኘው የትኛው መንፈስ ነው?

 በዛሬው ጊዜ በራስ የመመራትና ያለመታዘዝ መንፈስ በዓለም ላይ ተንሰራፍቶ ይገኛል። ሐዋርያው ጳውሎስ ለኤፌሶን ክርስቲያኖች በጻፈው ደብዳቤ ላይ ይህ የሆነበትን ምክንያት ሲገልጽ እንዲህ ብሏል:- “የዓለምን ክፉ መንገድ ተከትላችሁ፣ በአየር ላይ ላሉት መንፈሳውያን ኀይላት ገዥ ለሆነውና [“በአየር ላይ ሥልጣን እንዳለው አለቃ ፈቃድ፣” የ1954 ትርጉም] አሁንም . . . በማይታዘዙት ሰዎች ላይ ለሚሠራው መንፈስ እየታዘዛችሁ ትኖሩ ነበር።” (ኤፌሶን 2:1, 2) አዎን፣ ‘በአየር ላይ ሥልጣን ያለው አለቃ’ ማለትም ሰይጣን ዲያብሎስ መላውን ዓለም ባለመታዘዝ መንፈስ በክሎታል ማለት ይቻላል። ሰይጣን በመጀመሪያው መቶ ዘመን እንዲህ ሲያደርግ ነበር፤ በዘመናችንም በተለይ በአንደኛው የዓለም ጦርነት ወቅት ከሰማይ ከተባረረ በኋላ ዓለምን የበለጠ መበከሉን ተያይዞታል።—ራእይ 12:9

2, 3. ይሖዋን ልንታዘዘው ይገባል እንድንል የሚያደርጉን ምክንያቶች ምንድን ናቸው?

2 ይሁንና እኛ ክርስቲያኖች ይሖዋ አምላክ ፈጣሪያችን፣ ተንከባካቢያችን፣ አፍቃሪ ሉዓላዊ ጌታችንና ታዳጊያችን ስለሆነ እርሱን በሙሉ ልባችን መታዘዝ እንዳለብን እናውቃለን። (መዝሙር 148:5, 6፤ የሐዋርያት ሥራ 4:24፤ ቈላስይስ 1:13፤ ራእይ 4:11) በሙሴ ዘመን የነበሩት እስራኤላውያን ይሖዋ ሕይወት ሰጪያቸውና አዳኛቸው መሆኑን ተረድተው ነበር። በመሆኑም ሙሴ “አምላካችሁ እግዚአብሔር ያዘዛችሁን ለመፈጸም ተጠንቀቁ” ብሏቸዋል። (ዘዳግም 5:32) አዎን፣ ይሖዋን መታዘዝ ይገባቸው ነበር። ሆኖም ብዙም ሳይቆይ በሉዓላዊ ጌታቸው ላይ ዓመጹ።

3 ለአጽናፈ ዓለሙ ፈጣሪ መታዘዛችን ምን ያህል አስፈላጊ ነው? በአንድ ወቅት አምላክ በነቢዩ ሳሙኤል አማካኝነት ለንጉሥ ሳኦል፣ ‘መታዘዝ ከመሥዋዕት ይበልጣል’ ብሎት ነበር። (1 ሳሙኤል 15:22, 23) ይህ የሆነው እንዴት ነው?

መታዘዝ ‘ከመሥዋዕት የሚበልጠው’ እንዴት ነው?

4. ለይሖዋ መስጠት የምንችለው ነገር አለ የምንለው ከምን አንጻር ነው?

4 ይሖዋ የሁሉ ነገር ፈጣሪ እንደመሆኑ መጠን እኛ ያለን ቁሳዊ ሀብት ሁሉ የእርሱ ንብረት ነው። ታዲያ እኛ ልንሰጠው የምንችለው ነገር ይኖራል? አዎን አለ፤ አንድ እጅግ ውድ የሆነ ነገር ልንሰጠው እንችላለን። ይህ ነገር ምንድን ነው? የሚከተለው ምክር መልሱን ይሰጠናል:- “ልጄ ሆይ፤ ጠቢብ ሁን፤ ልቤን ደስ አሰኘው፤ ለሚንቁኝ ሁሉ መልስ መስጠት እችል ዘንድ።” (ምሳሌ 27:11) ለአምላክ ልንሰጠው የምንችለው ነገር ታዛዥነታችንን ነው። ያለንበት ሁኔታና አስተዳደጋችን የተለያየ ቢሆንም ታዛዦች በመሆን ዲያብሎስ ‘ሰዎች ችግር ቢገጥማቸው ለአምላክ ታማኝ አይሆኑም’ በማለት ላነሳው የተንኮል ክስ መልስ መስጠት እንችላለን። ይህ እንዴት ያለ ታላቅ መብት ነው!

5. ታዛዥ አለመሆናችን ፈጣሪን የሚነካው እንዴት ነው? በምሳሌ አስረዳ።

5 አምላክ የምናደርጋቸውን ውሳኔዎች በቁም ነገር ይመለከታል። ታዛዥ አለመሆናችን እርሱንም ይነካዋል። እንዴት? አምላክ ማንኛውም ሰው እንዲህ ዓይነቱን ጥበብ የጎደለው እርምጃ እንደወሰደ ሲመለከት ያዝናል። (መዝሙር 78:40, 41) ለምሳሌ ያህል፣ አንድ የስኳር ሕመምተኛ ለጤንነቱ የታዘዘለትን ተስማሚ ምግብ በመተው ጤናውን የሚጎዳ ምግብ ይመገባል እንበል። በዚህ ጊዜ ከልብ የሚያስብለት ሐኪም ምን ይሰማዋል? ይሖዋም የሰው ልጆች ለሕይወታቸው የተሰጣቸውን መመሪያ ቸል ማለታቸው ምን መዘዝ እንደሚያስከትልባቸው ስለሚያውቅ ሳይታዘዙት ሲቀሩ እንደሚያዝን እርግጠኞች መሆን እንችላለን።

6. ለአምላክ ታዛዥ እንድንሆን ምን ሊረዳን ይችላል?

6 በግለሰብ ደረጃ ለአምላክ ታዛዥ እንድንሆን ምን ሊረዳን ይችላል? ንጉሥ ሰሎሞን እንዳደረገው ሁሉ እያንዳንዳችን አምላክ “አስተዋይ [“ታዛዥ፣” NW] ልብ” እንዲሰጠን መጠየቃችን ተገቢ ነው። ሰሎሞን ይሖዋ ታዛዥ ልብ እንዲሰጠው የጠየቀው እስራኤላውያን ወገኖቹን በሚያስተዳድርበት ጊዜ ‘መልካሙን ከክፉው መለየት’ እንዲችል ነበር። (1 ነገሥት 3:9) እኛም ያለመታዘዝ መንፈስ በነገሠበት በዚህ ዓለም ስንኖር መልካሙን ከክፉው መለየት እንድንችል “ታዛዥ ልብ” ያስፈልገናል። አምላክ “ታዛዥ ልብ” እንዲኖረን ለመርዳት መጽሐፍ ቅዱስን፣ ቃሉን ለማጥናት የሚያስችሉንን ጽሑፎች፣ ክርስቲያናዊ ስብሰባዎችንና አሳቢ የሆኑ የጉባኤ ሽማግሌዎችን ሰጥቶናል። እንደነዚህ ባሉት ፍቅራዊ ዝግጅቶች በሚገባ እየተጠቀምን ነው?

7. ይሖዋ ታዛዥነት ከመሥዋዕት እንደሚበልጥ የተናገረው ለምንድን ነው?

7 ከዚህ ጋር በተያያዘ፣ ይሖዋ በጥንት ዘመን ለነበሩት ሕዝቦቹ መታዘዝ የእንስሳ መሥዋዕት ከማቅረብ የበለጠ አስፈላጊ መሆኑን እንደገለጸላቸው አስታውስ። (ምሳሌ 21:3, 27፤ ሆሴዕ 6:6፤ ማቴዎስ 12:7) ሕዝቡ የእንስሳ መሥዋዕት እንዲያቀርቡ ያዘዛቸው ይሖዋ ራሱ ሆኖ ሳለ እንዲህ ያላቸው ለምን ነበር? አዎን ትእዛዙን የሰጣቸው ይሖዋ ነበር። ይሁንና አንድ ሰው መሥዋዕት እንዲያቀርብ የሚገፋፋው ምንድን ነው? ይህን የሚያደርገው አምላክን ለማስደሰት ነው? ወይስ እንዲያው የአምልኮ ሥርዓት ለመፈጸም ነው? አንድ ክርስቲያን በእርግጥ ይሖዋን ለማስደሰት የሚፈልግ ከሆነ ትእዛዛቱን ሙሉ በሙሉ ይፈጽማል። የእንስሳ መሥዋዕት ለአምላክ የሚያመጣለት ጥቅም የለም፤ ከዚህ ይልቅ ለአምላክ ልንሰጠው የምንችለው የላቀ ዋጋ ያለው ነገር ታዛዥነታችን ነው።

የማስጠንቀቂያ ምሳሌ

8. አምላክ ሳኦልን ንጉሥ እንዳይሆን የናቀው ለምንድን ነው?

8 ስለ ንጉሥ ሳኦል የሚናገረው የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ የታዛዥነትን አስፈላጊነት አጉልቶ ያሳያል። ሳኦል መግዛት በጀመረበት ጊዜ ትሑትና ‘በዓይኑ ፊት ታናሽ’ የሆነ ልኩን የሚያውቅ ንጉሥ ነበር። ይሁንና ከጊዜ በኋላ ኩራትና የተሳሳተ አመለካከት በውሳኔዎቹ ላይ ተጽዕኖ ያሳድሩ ጀመር። (1 ሳሙኤል 10:21, 22፤ 15:17) በአንድ ወቅት ሳኦል ከፍልስጥኤማውያን ጋር ለመዋጋት እየተዘጋጀ ነበር። በዚህ ጊዜ ሳሙኤል እርሱ መጥቶ ለይሖዋ መሥዋዕት እስኪያቀርብና ተጨማሪ መመሪያ እስኪሰጠው ድረስ እንዲጠብቀው ለንጉሡ ነገረው። ይሁንና ሳሙኤል ይመጣል ተብሎ በታሰበበት ጊዜ ሳይመጣ በመቅረቱ ሕዝቡ መበታተን ጀመረ። ሳኦል ይህን ሲመለከት “የሚቃጠለውን መሥዋዕት አቀረበ።” ይህ ይሖዋን የሚያሳዝን ድርጊት ነበር። በመጨረሻ ሳሙኤል ሲመጣ ንጉሡ የሚቃጠል መሥዋዕት ለማቅረብ ‘የተገደደው’ እርሱ በመዘግየቱና የይሖዋን ሞገስ ለማግኘት በመፈለጉ እንደሆነ በመግለጽ ላለመታዘዙ ሰበብ አቀረበ። ንጉሥ ሳኦል ይህን መሥዋዕት ማቅረብ ሳሙኤልን እንዲጠብቅ የተሰጠውን መመሪያ ከመታዘዝ ይበልጥ አስፈላጊ እንደሆነ ተሰምቶት ነበር። ሳሙኤል ግን “የማይገባህን አደረግህ፤ አምላክህ እግዚአብሔር የሰጠህን ትእዛዝ አልጠበቅህም” አለው። ሳኦል ይሖዋን ባለመታዘዙ ንግሥናውን አጥቷል።—1 ሳሙኤል 10:8፤ 13:5-13

9. ሳኦል አምላክን ለመታዘዝ እምቢተኛ መሆኑን ያሳየው እንዴት ነው?

9 ንጉሡ ከዚህ ሁኔታ ትምህርት አግኝቷል? በፍጹም! ቆየት ብሎም ይሖዋ ሳኦልን ከዚህ ቀደም ያላንዳች ምክንያት እስራኤላውያንን የወጓቸውን አማሌቃውያንን ፈጽሞ እንዲያጠፋቸው አዘዘው። ሳኦል የቤት እንስሶቻቸውን እንኳ ሳይቀር ማጥፋት ነበረበት። ሳኦል ‘አማሌቃውያንን ከኤውላጥ አንሥቶ እስከ ሱር ድረስ በመውጋት’ ታዛዥነቱን አሳይቷል። እንዲያውም ሳሙኤል ወደ እርሱ በመጣ ጊዜ፣ ባገኘው ድል እጅግ ተደስቶ “እግዚአብሔር ይባርክህ፤ የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ፈጽሜአለሁ” አለው። ሆኖም ሳኦልና ሕዝቡ የተሰጣቸውን ግልጽ መመሪያ በመጣስ ንጉሥ አጋግን እንዲሁም “ምርጥ ምርጡን በግና የቀንድ ከብት፣ የሰባውን ጥጃና ጠቦት፣ መልካም የሆነውን ሁሉ” ሳይገድሉ ቀርተዋል። አሁንም ንጉሥ ሳኦል “ሰራዊቱ . . . ምርጥ ምርጦቹ በጎችና በሬዎች ለእግዚአብሔር ለአምላክህ መሥዋዕት እንዲሆኑ ሳይገድሉ የተዉአቸው ናቸው” በማለት ላለመታዘዙ ሰበብ አቀረበ።—1 ሳሙኤል 15:1-15

10. ሳኦል ሳይማር የቀረው ቁም ነገር ምንድን ነው?

10 በዚህ ጊዜ ሳሙኤል ለሳኦል እንዲህ አለው:- “ለእግዚአብሔር ቃል በመታዘዝ ደስ የሚለውን ያህል፣ እግዚአብሔር፣ በሚቃጠል ቍርባንና መሥዋዕት ደስ ይለዋልን? እነሆ! መታዘዝ ከመሥዋዕት፣ ማዳመጥም ከአውራ በግ ሥብ ይበልጣል።” (1 ሳሙኤል 15:22) ይሖዋ እነዚያ እንስሳት እንዲጠፉ ስለወሰነ ለመሥዋዕትነት ቢቀርቡለት እንኳ ተቀባይነት አይኖራቸውም ነበር።

በሁሉም ነገር ታዛዥ ሁን

11, 12. (ሀ) ይሖዋ በአምልኮታችን እርሱን ለማስደሰት የምናደርገውን ጥረት እንዴት ይመለከተዋል? (ለ) አንድ ሰው ታዛዥ ባይሆንም እንኳ የአምላክን ፈቃድ እየፈጸመ እንዳለ አድርጎ በማሰብ ራሱን ሊያታልል የሚችለው እንዴት ነው?

11 ይሖዋ ታማኝ አገልጋዮቹ ስደትን በጽናት ሲቋቋሙ፣ ሰዎች ደንታ ቢስ ቢሆኑም እንኳ በትጋት ሲሰብኩና የኑሮ ጫና ቢኖርባቸውም በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ ሲገኙ ሲመለከት እጅግ ይደሰታል! እነዚህን በመሳሰሉት በጣም አስፈላጊ በሆኑ መንፈሳዊ እንቅስቃሴዎች ረገድ ታዛዥ መሆናችን የይሖዋን ልብ ደስ ያሰኛል! ይሖዋ ከፍቅር ተነሳስተን እርሱን ለማምለክ የምናደርገውን ጥረት ከፍ አድርጎ ይመለከተዋል። ሰዎች ልፋታችንን ከቁብ ባይቆጥሩትም እንኳ አምላክ ከልብ የምናቀርበውን መሥዋዕት የሚመለከት ከመሆኑም በላይ መቼም ቢሆን አይረሳውም።—ማቴዎስ 6:4

12 ሆኖም አምላካችንን ሙሉ በሙሉ ለማስደሰት ከፈለግን በሁሉም የሕይወታችን ዘርፍ ታዛዥ መሆን ይገባናል። በአንዳንድ የሕይወቴ ዘርፎች ለይሖዋ አምልኮ እስካቀረብኩ ድረስ አንዳንዶቹን የአምላክ ትእዛዛት ሳልጠብቅ ብቀር ምንም ማለት አይደለም ብለን ራሳችንን እንዳናታልል መጠንቀቅ አለብን። ለምሳሌ ያህል፣ አንድ ሰው ‘በተለመዱት የአምልኮ እንቅስቃሴዎች እስከተካፈልኩ ድረስ የጾታ ብልግና ወይም ሌላ ከባድ ኃጢአት ብፈጽም ችግር የለውም’ በማለት ራሱን ሊያታልል ይችላል። ይህ እንዴት ያለ ስህተት ይሆናል!—ገላትያ 6:7, 8

13. ብቻችንን በምንሆንበት ጊዜ ለይሖዋ ያለን ታዛዥነት እንዴት ሊፈተን ይችላል?

13 በመሆኑም “የግል ጉዳዮቼን ጨምሮ በዕለት ተዕለት እንቅስቃሴዬ ይሖዋን እየታዘዝኩት ነው?” ብለን ራሳችንን ልንጠይቅ እንችላለን። ኢየሱስ “በትንሽ ነገር ታማኝ የሆነ በትልቁም ይታመናል፤ በትንሽ ነገር ያልታመነ በትልቁም አይታመንም” ብሏል። (ሉቃስ 16:10) ሌሎች ሰዎች በማያዩን ቦታ ማለትም ‘በቤታችን ውስጥ’ በምንሆንበት ጊዜም እንኳ ‘በንጹሕ ልብ እንመላለሳለን?’ (መዝሙር 101:2) አዎን፣ ቤታችን ስንሆን ንጽሕናችን ማለትም ጽኑ አቋማችን ይፈተን ይሆናል። ኮምፒውተር በየቤቱ በሚገኝባቸው አገሮች፣ አስጸያፊ ምስሎችን ማግኘት በጣም ቀላል ነው። ከጥቂት ዓመታት በፊት አንድ ሰው እንዲህ ዓይነት ምስሎችን ለመመልከት የብልግና ድርጊቶች ወደሚታዩባቸው የመዝናኛ ቦታዎች መሄድ ነበረበት። ኢየሱስ “ሴትን በምኞት ዓይን የተመለከተ ሁሉ በልቡ ከእርሷ ጋር አመንዝሮአል” ሲል የሰጠውን ምክር ከልብ እንታዘዛለን? የሥነ ምግባር ብልግና የሚያሳዩ ምስሎችን ለማየት እንኳ እንጸየፋለን? (ማቴዎስ 5:28፤ ኢዮብ 31:1, 9, 10፤ መዝሙር 119:37፤ ምሳሌ 6:24, 25፤ ኤፌሶን 5:3-5) የዓመጽ ድርጊት ስለሚተላለፍባቸው የቴሌቪዥን ፕሮግራሞችስ ምን ለማለት ይቻላል? ‘ዓመጻን የሚወዱትን ከሚጠላው’ አምላካችን ጋር ተመሳሳይ ስሜት አለን? (መዝሙር 11:5) ወይም ለብቻችን በምንሆንበት ጊዜ ከልክ በላይ አልኮል የመጠጣት ልማድ አለን? መጽሐፍ ቅዱስ ስካርን ብቻ ሳይሆን ‘በወይን ጠጅ ሱስ መጠመድንም’ ያወግዛል።—ቲቶ 2:3፤ ሉቃስ 21:34, 35፤ 1 ጢሞቴዎስ 3:3

14. ገንዘብ ነክ በሆኑ ጉዳዮች ረገድ ለአምላክ ታዣዥ መሆናችንን የምናሳይባቸው አንዳንድ መንገዶች ምንድን ናቸው?

14 ጥንቃቄ ልናደርግበት የሚገባን ሌላው ነገር ገንዘብ ነክ የሆኑ ጉዳዮችን የምንይዝበት መንገድ ነው። ለምሳሌ ያህል፣ ከማጭበርበር በማይተናነሱ በአጭር ጊዜ ለመክበር ያስችላሉ በሚባሉ ውጥኖች ውስጥ እንሳተፋለን? ቀረጥ ከመክፈል ለማምለጥ ስንል ሕገወጥ የሆኑ መንገዶችን እንከተላለን? ወይስ “ለእያንዳንዱ የሚገባውን ስጡ፤ ቀረጥ ከሆነም ቀረጥን . . . ስጡ” የሚለውን መመሪያ ለመታዘዝ እንጠነቀቃለን?—ሮሜ 13:7

ከፍቅር የሚመነጭ ታዛዥነት

15. የይሖዋን መመሪያዎች የምትታዘዘው ለምንድን ነው?

15 ለመለኮታዊ መመሪያዎች መታዘዝ በረከት ያስገኛል። ለምሳሌ ያህል፣ ከትንባሆ በመራቅ፣ በሥነ ምግባር የታነጸ ሕይወት በመምራትና የደምን ቅድስና በማክበር በአንዳንድ በሽታዎች ከመያዝ እንጠበቃለን። በተጨማሪም ከመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ጋር ተስማምቶ መኖር በኢኮኖሚ፣ በማኅበራዊ ወይም በቤተሰብ ሕይወታችን ሊጠቅመን ይችላል። (ኢሳይያስ 48:17) እንደነዚህ ያሉት ተጨባጭ ጥቅሞች የአምላክን ሕግጋት በተግባር በማዋላችን ያገኘናቸው በረከቶች እንደሆኑ አድርገን ልናስብ እንችላለን። ሆኖም ይሖዋን የምንታዘዝበት ዋነኛው ምክንያት ለእርሱ ፍቅር ስላለን ነው። ይሖዋን የምናገለግለው ለግል ጥቅማችን ስንል አይደለም። (ኢዮብ 1:9-11፤ 2:4, 5) አምላክ የፈለግነውን ለመታዘዝ እንድንመርጥ ነፃነት ሰጥቶናል። እኛም ይሖዋን ማስደሰትና ትክክል የሆነውን ማድረግ ስለምንፈልግ እርሱን ለመታዘዝ መርጠናል።—ሮሜ 6:16, 17፤ 1 ዮሐንስ 5:3

16, 17. (ሀ) ኢየሱስ ከልብ በመነጨ ፍቅር አምላክን እንደታዘዘ ያሳየው እንዴት ነው? (ለ) እኛስ ኢየሱስን ልንኮርጅ የምንችለው እንዴት ነው?

16 ይሖዋን ከልብ በመነጨ ፍቅር በመታዘዝ ረገድ ኢየሱስ ፍጹም ምሳሌ ይሆነናል። (ዮሐንስ 8:28, 29) ኢየሱስ በምድር በነበረበት ጊዜ ‘ከተቀበለው መከራ መታዘዝን ተምሯል።’ (ዕብራውያን 5:8, 9) እንዴት? ኢየሱስ ‘ራሱን ዝቅ በማድረግ፤ እስከ ሞት፣ ያውም በመስቀል [“በመከራ እንጨት፣” NW] ላይ እስከ መሞት ድረስ ታዛዥ ሆኗል።’ (ፊልጵስዩስ 2:7, 8) በሰማይ ሳለ ታዛዥ የነበረ ቢሆንም ወደ ምድር ከመጣ በኋላም ታዛዥነቱ ተፈትኗል። ኢየሱስ መንፈሳዊ ወንድሞቹንም ሆነ በእርሱ የሚያምኑ ሌሎች ሰዎችን ሊቀ ካህን ሆኖ ለማገልገል ብቃት እንዳለው እርግጠኞች መሆን እንችላለን።—ዕብራውያን 4:15፤ 1 ዮሐንስ 2:1, 2

17 እኛስ? ከሁሉ አስቀድመን ለአምላክ ፈቃድ በመታዘዝ የኢየሱስን ምሳሌ እንኮርጃለን። (1 ጴጥሮስ 2:21) መታዘዝ አስቸጋሪ ወይም ፈታኝ በሚሆንበት ጊዜም እንኳ ለአምላክ ካለን ፍቅር ተነሳስተን ትእዛዛቱን መጠበቃችን እርካታ ያስገኝልናል። (ሮሜ 7:18-20) ይህም በእውነተኛው አምልኮ ውስጥ ግንባር ቀደም ሆነው የሚያገለግሉ ወንድሞች፣ ፍጹማን ባይሆኑም እንኳ የሚሰጧቸውን መመሪያዎች ለመታዘዝ ፈቃደኛ መሆንን ይጨምራል። (ዕብራውያን 13:17) ብቻችንን በምንሆንበት ጊዜም መለኮታዊ መመሪያዎችን መታዘዛችን በይሖዋ ዘንድ ከፍ ያለ ዋጋ አለው።

18, 19. አምላክን ከልብ መታዘዛችን ምን ውጤት ያስገኝልናል?

18 በአሁኑ ጊዜ ይሖዋን መታዘዝ ፍጹም አቋማችንን ለመጠበቅ ስንል በስደት መጽናትን ይጨምራል። (የሐዋርያት ሥራ 5:29) ከዚህም በተጨማሪ፣ ይሖዋ ቃሉን እንድንሰብክና እንድናስተምር የሰጠንን ትእዛዝ ለመፈጸም እስከዚህ ሥርዓት መደምደሚያ ድረስ መጽናት ይኖርብናል። (ማቴዎስ 24:13, 14፤ 28:19, 20) የዚህ ዓለም ጫና ቢበረታብንም ከወንድሞቻችን ጋር መሰብሰባችንን ለመቀጠል ጽናት ያስፈልገናል። አፍቃሪው አምላካችን በእነዚህ ዘርፎች ታዛዥ ለመሆን የምናደርገውን ጥረት በሚገባ ያውቃል። ይሁንና ሙሉ በሙሉ ታዛዥ ለመሆን ኃጢአተኛ ከሆነው ሥጋችን ጋር መታገልና መልካም ለሆኑ ነገሮች ያለንን ፍቅር በማሳደግ ክፉን መጥላት ይኖርብናል።—ሮሜ 12:9

19 በፍቅርና በአድናቆት ስሜት ተገፋፍተን ይሖዋን ካገለገልነው ‘ከልብ ለምንሻው [ለእኛ] ዋጋ ይሰጠናል።’ (ዕብራውያን 11:6) በተገቢው መንገድ የሚቀርቡ መሥዋዕቶች አስፈላጊና የሚደገፉ ቢሆኑም ከሁሉም በላይ ይሖዋን የሚያስደስተው በፍቅር ተነሳስተን እርሱን ሙሉ ለሙሉ መታዘዛችን ነው።—ምሳሌ 3:1, 2

ምን ብለህ ትመልሳለህ?

• ለይሖዋ ልንሰጠው የምንችለው ነገር አለ የምንለው ለምንድን ነው?

• ሳኦል የሠራቸው ስህተቶች ምንድን ናቸው?

• መታዘዝ ከመሥዋዕት የሚበልጥ መሆኑን እንደምታምን እንዴት ማሳየት ትችላለህ?

• ይሖዋን እንድትታዘዝ የሚገፋፋህ ምንድን ነው?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

አንድ አሳቢ ሐኪም፣ ታካሚው የተሰጠውን ምክር ችላ እንዳለ ሲመለከት ምን ይሰማዋል?

[በገጽ 28 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ይሖዋ በንጉሥ ሳኦል ያዘነው ለምንድን ነው?

[በገጽ 30 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ቤትህ ውስጥ ለብቻህ በምትሆንበት ጊዜ የአምላክን መመሪያዎች ትታዘዛለህ?