ጊዜ በማይሽራቸው የሥነ ምግባር ደንቦች መመራት
ጊዜ በማይሽራቸው የሥነ ምግባር ደንቦች መመራት
እያንዳንዱ ኅብረተሰብ የራሱ የሆኑ የሥነ ምግባር ደንቦች አሉት። ለምሳሌ ያህል፣ ሐቀኝነት፣ ደግነት፣ ርኅራኄና የራስን ጥቅም መሥዋዕት ማድረግ በሁሉም ሰዎች ዘንድ ከፍ ተደርገው የሚታዩና ብዙዎቻችንም የምንወዳቸው ባሕርያት ናቸው ቢባል አትስማማም?
የእነዚህ ባሕርያት ምንጭ ማን ነው?
በመጀመሪያው መቶ ዘመን ከክርስቶስ ልደት በኋላ የኖረ ሳውል የተባለ አንድ ምሁር ነበር። ሳውል የኖረው የአይሁድ፣ የግሪክ እንዲሁም የሮም ባሕሎችና የሥነ ምግባር ደንቦች ከፍተኛ ተጽዕኖ በሚያሳድሩበት ማኅበረሰብ ውስጥ ሮሜ 2:14, 15
ነበር። ይህ ማኅበረሰብ ከነበሩት የተወሳሰቡ ወጎችና ሕጎች በተጨማሪ ሳውል የሰው ልጅ በተፈጥሮ ባገኘው የሥነ ምግባር ሕግ እንደሚመራ ተገንዝቧል። ይህ በተፈጥሮ ያገኘነው የሥነ ምግባር ሕግ ሕሊናችን ነው። ሳውል ክርስትናን ተቀብሎ ሐዋርያው ጳውሎስ ተብሎ መጠራት ከጀመረ በኋላ እንዲህ ሲል ጽፏል:- “ሕግ የሌላቸው አሕዛብ ሕግ የሚያዝዘውን ነገር በተፈጥሮ [“በደመ ነፍስ፣” ዘ ኒው ቴስታመንት ኢን ሞደርን ስፒች] ሲያደርጉ፣ ሕግ ባይኖራቸውም እነርሱ ለራሳቸው ሕግ ናቸው። ኅሊናቸው ስለሚመሰክር . . . የሕግ ትእዛዝ በልባቸው የተጻፈ መሆኑን ያሳያሉ።”—ይሁን እንጂ ትክክልና ስህተት የሆነውን ለመለየት በደመ ነፍስ ወይም በተፈጥሮ ባገኘነው ሕሊና ብቻ መመራት በቂ ነው? የሰው ልጅ ታሪክ በግለሰብም ሆነ በቡድን ደረጃ በተፈጸሙ ስህተቶች የተሞላ መሆኑን ሳታስተውል አልቀረህም። ይህ ሁኔታ ብዙ ሰዎች፣ ሕይወታችንን የምንመራባቸው ከሁሉ የተሻሉ የሥነ ምግባር ደንቦች ለማግኘት ከእኛ የላቀ ችሎታ ካለው አካል እርዳታ ማግኘት ያስፈልገናል ብለው እንዲያስቡ አድርጓቸዋል። ብዙዎች፣ ጊዜ የማይሽራቸው የሥነ ምግባር መሥፈርቶችን በማውጣት ረገድ ከሰው ልጆች ፈጣሪ የተሻለ እንደማይገኝ ይስማማሉ። ዶክተር ካርል ጀንግ ዚ አንዲስከቨርድ ሰልፍ በተባለው መጽሐፋቸው ላይ “የአምላክን መመሪያ በጥብቅ የማይከተል ሰው በዚህ ዓለም የሚያጋጥሙትን ሥጋዊም ሆኑ ሥነ ምግባራዊ ፈተናዎች በራሱ ኃይል ሊቋቋም አይችልም” ሲሉ ተናግረዋል።
እኚህ ሰው የደረሱበት መደምደሚያ በጥንት ዘመን የኖረ አንድ ነቢይ ከጻፈው ሐሳብ ጋር ይስማማል:- “የሰው ሕይወት በራሱ እጅ እንዳልሆነች፣ አካሄዱንም በራሱ አቃንቶ ሊመራ እንደማይችል ዐውቃለሁ።” (ኤርምያስ 10:23) ፈጣሪያችን “የሚበጅህ ምን እንደ ሆነ የማስተምርህ፣ መሄድ በሚገባህ መንገድ የምመራህ ነኝ” ብሏል።—ኢሳይያስ 48:17
እምነት የሚጣልባቸው የሥነ ምግባር ደንቦች የሚገኙበት አስተማማኝ ምንጭ
ከላይ የተጠቀሱት ሐሳቦች የሚገኙት በዓለም ዙሪያ በሰፊው በተሰራጨውና የሥነ ምግባር ደንቦች ምንጭ በሆነው በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ነው። በዓለም ዙሪያ የሚገኙ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች፣ ሌላው ቀርቶ ክርስቲያን ያልሆኑና ሃይማኖት የሌላቸው ሰዎች እንኳ ማስተዋልና ጥበብ ለማግኘት ቅዱሳን መጻሕፍትን ያነብባሉ። ጀርመናዊው ገጣሚ ዮሐን ቮን ጎት አንዲህ ብለዋል:- “እኔ በበኩሌ [መጽሐፍ ቅዱስን] እወደዋለሁ፣ እንዲሁም አከብረዋለሁ፤ ምክንያቱም በሕይወቴ የምመራባቸውን የሥነ ምግባር ደንቦች በሙሉ ያገኘሁት ከዚህ መጽሐፍ ነው ለማለት እችላለሁ።” የሂንዱ መሪ የነበሩት ሞሃንደስ ጋንዲ “በተራራ ስብከት [በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከሚገኙት የኢየሱስ ክርስቶስ ትምህርቶች መካከል አንዱ ነው] የተሰጣችሁን ጥልቅ እውቀት ቅሰሙ፤ . . . ምክንያቱም እነዚህ ትምህርቶች ለሁላችንም የሚጠቅሙ ናቸው” ማለታቸው ተዘግቧል።
ቀደም ሲል የተጠቀሰው ሐዋርያው ጳውሎስ ቅዱሳን መጻሕፍት እምነት የሚጣልባቸው የሥነ ምግባር ደንቦችን በመስጠት ረገድ የሚጫወቱትን ሚና አጉልቶ ሲገልጽ “ቅዱሳት መጻሕፍት ሁሉ የእግዚአብሔር መንፈስ ያለባቸው ናቸው፤ ለማስተማር . . . ይጠቅማሉ” ብሏል። (2 ጢሞቴዎስ 3:16) ይህ በእርግጥ እውነት ነው?
ይህን ለማረጋገጥ ለምን አንተ ራስህ አትመረምርም? በሚቀጥለው ገጽ ላይ የተዘረዘሩትን የሥነ ምግባር ደንቦች ተመልከት። ከዚያም ምን ያህል ጠቃሚ ውጤት እንደሚያስገኙ ለማስተዋል ሞክር። እነዚህ ትምህርቶች የያዟቸው ሐሳቦች የአንተን ሕይወትም ሆነ ከሌሎች ጋር ያለህን ዝምድና እንዴት እንደሚያሻሽሉ አሰላስል።
የአምላክ ቃል ከሚሰጠው ትምህርት ተጠቃሚ መሆን ትፈልጋለህ?
የተዘረዘሩት የሥነ ምግባር ደንቦች ቅዱሳን መጻሕፍት ከያዟቸው ጠቃሚ ምክሮች መካከል ጥቂቶቹ ብቻ ናቸው። ከእነዚህ በተጨማሪ የአምላክ ቃል በሕይወታችን ላይ መጥፎ ተጽዕኖ የሚያሳድሩ ጎጂ አስተሳሰቦችን፣ አነጋገሮችንና ድርጊቶችን እንድናስወግድ ያሳስበናል።—ምሳሌ 6:16-19
አዎን፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶች ከሰው ልጅ ማኅበረሰብ ፈጽሞ ማግኘት የማንችለውን ምክር፣ ይኸውም ሰዎች ከሁሉ የተሻለውን የሥነ ምግባር እሴት እንዲያዳብሩ የሚያስችላቸውን መመሪያ ይሰጣል። እነዚህን ትምህርቶች ተቀብለው በተግባር ላይ የሚያውሉ ሁሉ በሕይወታቸው ላይ ጉልህ ለውጥ ያደርጋሉ። የተሻለ አስተሳሰብ ይኖራቸዋል። (ኤፌሶን 4:23, 24) ውስጣዊ ዝንባሌያቸው ይለወጣል። ብዙዎች በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙትን የአምላክን የሥነ ምግባር ደንቦች መማራቸው ዘረኝነትንና ጭፍን ጥላቻን ከልባቸው ነቅለው እንዲያወጡ ረድቷቸዋል። (ዕብራውያን 4:12) መጽሐፍ ቅዱስና በውስጡ የሚገኙት የሥነ ምግባር እሴቶች ሰዎች ሁሉንም ዓይነት ዓመጽና ክፋት አስወግደው የተሻሉ ግለሰቦች እንዲሆኑ አነሳስተዋቸዋል።
አዎን፣ የመጽሐፍ ቅዱስ የሥነ ምግባር እሴቶች በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች፣ ሥር የሰደዱ ልማዶቻቸውንና በሌሎች ላይ ጉዳት የሚያስከትሉ ድርጊቶቻቸውን እንዲያስወግዱ ረድተዋቸዋል። (1 ቆሮንቶስ 6:9-11) የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶች፣ እነዚህ ሰዎች ልማዶቻቸውን ብቻ ሳይሆን ልባቸውን፣ ተስፋቸውንና የቤተሰባቸውን ሕይወት ጭምር እንዲለውጡ አድርገዋቸዋል። ይህ ዓለም የቱንም ያህል እየተበላሸ ቢሄድ በዓለም ዙሪያ የሚገኙ በርካታ ሰዎች ሕይወታቸው በመሻሻል ላይ ይገኛል። እንዲህ ያለው ለውጥ ለዘላለም የሚቀጥል ይሆናል። መጽሐፍ ቅዱስ “ሣሩ ይደርቃል፤ አበባውም ይረግፋል፤ የአምላካችን ቃል ግን ለዘላለም ጸንቶ ይኖራል” ይላል።—ኢሳይያስ 40:8
ይሁን እንጂ አንተስ “የአምላካችን ቃል” ከሚሰጠው ትምህርት ተጠቃሚ መሆን ትፈልጋለህ? የይሖዋ ምሥክሮች ሕይወትህን በመጽሐፍ ቅዱስ የሥነ ምግባር እሴቶች መምራት የምትችለው እንዴት እንደሆነ ሊያሳዩህ ፈቃደኞች ናቸው። ከእነዚህ የሥነ ምግባር እሴቶች ጋር ተስማምተህ መኖርህ በአሁኑ ጊዜ የአምላክን ሞገስ እንድታገኝ ይረዳሃል። ለወደፊቱ ደግሞ ጊዜ በማይሽራቸው መለኮታዊ ደንቦች እየተመራህ ለዘላለም እንድትኖር ያስችልሃል።
[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
ጊዜ የማይሽራቸው የሥነ ምግባር ደንቦች
ወርቃማው ሕግ። “ሌሎች እንዲያደርጉላችሁ የምትፈልጉትን ነገር እናንተም አድርጉላቸው፤ ኦሪትም፣ ነቢያትም በዚህ ይጠቃለላሉና።”—ማቴዎስ 7:12
ጎረቤትህን ውደድ። “ጎረቤትህን እንደ ራስህ ውደድ።” (ማቴዎስ 22:39) “ፍቅር በባልንጀራው ላይ ክፉ አያደርግም፤ ስለዚህ ፍቅር የሕግ መፈጸሚያ ነው።”—ሮሜ 13:10
ሌሎችን አክብር። “እርስ በርሳችሁ በወንድማማች መዋደድ አጥብቃችሁ ተዋደዱ፤ አንዱ ሌላውን ከራሱ በማስበለጥ እርስ በርሳችሁ ተከባበሩ።”—ሮሜ 12:10
ሰላምን እሻ። “እርስ በርሳችሁ ተስማምታችሁ በሰላም ኑሩ።” (ማርቆስ 9:50 የታረመው የ1980 ትርጉም) “ቢቻላችሁስ በበኩላችሁ ከሰው ሁሉ ጋር በሰላም ኑሩ።” (ሮሜ 12:18) “ሰላም የሚገኝበትን . . . ማንኛውንም ጥረት እናድርግ።”—ሮሜ 14:19
ይቅር ባይ ሁን። “እኛም ደግሞ የበደሉንን ይቅር እንደምንል፣ በደላችንን ይቅር በለን።” (ማቴዎስ 6:12) “ይቅር ተባባሉ፤ እርስ በርሳችሁ ቸሮችና ርኅሩኆች ሁኑ።”—ኤፌሶን 4:32
ታማኝ ሁን። ‘ለሚስትህ ታማኝ በመሆንና እርስዋን ብቻ በመውደድ እርካ። በወጣትነት ባገባሃት ሚስትህ ደስ ይበልህ። ውበትዋ ሁልጊዜ ያርካህ፤ በፍቅርዋም ዘወትር ደስ ይበልህ። በአመንዝራይቱ ሴት ለምን ትማረካለህ? ለምንስ ከሌላው ሰው ሚስት ጋር ትባልጋለህ?’ (ምሳሌ 5:15-20 የታረመው የ1980 ትርጉም) “በትንሽ ነገር ታማኝ የሆነ በትልቁም ይታመናል፤ በትንሽ ነገር ያልታመነ በትልቁም አይታመንም።” (ሉቃስ 16:10) “ባለ ዐደራዎችም ታማኝ ሆነው መገኘት አለባቸው።”—1 ቆሮንቶስ 4:2
ሐቀኛ ሁን። “በአባይ ሚዛንና በከረጢት ባለ በተንኰል መመዘኛ ንጹሕ እሆናለሁን?” (ሚክያስ 6:11 የ1954 ትርጉም) “በሁሉም መንገድ በመልካም አኗኗር ለመኖር የሚናፍቅ ንጹሕ ኅሊና እንዳለን እርግጠኞች ነን።”—ዕብራውያን 13:18
እውነተኛና ፍትሕ ወዳድ ሁን። “ክፉውን ጥሉ፤ መልካሙንም ውደዱ። በፍርድ አደባባይም ፍትሕን አታጓድሉ።” (አሞጽ 5:15) “እርስ በርሳችሁ እውነትን ተነጋገሩ፤ በአደባባያችሁም እውነትንና ትክክለኛ ፍርድን አስፍኑ።” (ዘካርያስ 8:16) “ውሸትን አስወግዳችሁ፣ እያንዳንዳችሁ ከባልንጀራችሁ ጋር እውነትን ተነጋገሩ።”—ኤፌሶን 4:25
ታታሪና ትጉ ሠራተኛ ሁን። “በሙያው ሥልጡን የሆነውን ሰው አይተሃልን? በነገሥታት ዘንድ ባለሟል ይሆናል።” (ምሳሌ 22:29) “ለሥራ ከመትጋት አትለግሙ።” (ሮሜ 12:11 የ1954 ትርጉም) “የምታደርጉትን ሁሉ ለሰው ሳይሆን ለጌታ እንደምታደርጉት ቈጥራችሁ በሙሉ ልባችሁ አድርጉት።”—ቈላስይስ 3:23
የዋህ፣ ርኅሩኅና ቸር ሁን። “ርኅራኄን፣ ቸርነትን፣ ትሕትናን፣ ጨዋነትንና ትዕግሥትን ልበሱ።”—ቈላስይስ 3:12
ክፉን በመልካም አሸንፍ። “ጠላቶቻችሁን ውደዱ፤ ለሚያሳድዷችሁም ጸልዩ።” (ማቴዎስ 5:44) “ክፉን በመልካም አሸንፍ እንጂ በክፉ አትሸነፍ።”—ሮሜ 12:21
ለአምላክ ምርጥህን ስጥ። “‘ጌታ አምላክህን በፍጹም ልብህ፣ በፍጹም ነፍስህ፣ በፍጹም ሐሳብህ ውደድ፤’ ይህ የመጀመሪያውና ከሁሉ የሚበልጠው ትእዛዝ ነው።”—ማቴዎስ 22:37, 38
[ሥዕሎች]
በመጽሐፍ ቅዱስ የሥነ ምግባር እሴቶች መመራት የተሳካ ትዳር፣ ደስተኛ የቤተሰብ ሕይወትና ጥሩ ወዳጆች እንድናገኝ ያስችለናል