ለልጆች የሚሆን አስፈላጊ ትምህርት
ለልጆች የሚሆን አስፈላጊ ትምህርት
ግላዲስ በሜንዶዛ፣ አርጀንቲና በአንድ ትምህርት ቤት ውስጥ ትሠራለች። አንድ ቀን በአንድ ክፍል አጠገብ ስታልፍ አንዲት መምህርት ለአራተኛ ክፍል ተማሪዎች የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች መማሪያ መጽሐፌ ከተባለው መጽሐፍ ላይ ስታነብላቸው ተመለከተች። a ግላዲስም ለዚህች መምህርት የይሖዋ ምሥክር እንደሆነች ከነገረቻት በኋላ መጽሐፉን ይበልጥ ልትጠቀምበት የምትችለው እንዴት እንደሆነ ልታሳያት እንደምትፈልግ ገለጸችላት። መምህርቷም፣ ግላዲስ ባብራራችላት ነገር በጣም ስለተገረመች መጽሐፉ በትምህርት ቤቱ ሥርዓተ ትምህርት ውስጥ እንዲካተት ፈለገች። ይሁን እንጂ ይህን ለማድረግ ከትምህርት ቤቱ አስተዳደር ፈቃድ ማግኘት ያስፈልጋት ነበር። ጥያቄዋ ተቀባይነት ሲያገኝ ተደሰተች።
ብዙም ሳይቆይ ትምህርት ቤቱ መጽሐፍ ማንበብን ለማበረታታት በመደበው ቀን ይህች መምህርት ተማሪዎቿ በትምህርት ቤት ጓደኞቻቸው ፊት ከመጽሐፉ ውስጥ አንድ ምዕራፍ እንዲያነቡ አደረገች። ይህ ፕሮግራም ጥሩ ምላሽ በማግኘቱ መምህርቷ በአገሪቱ በሚሠራጭ የቴሌቪዥን ፕሮግራም ላይ እንግዳ ሆና ተጋብዛ ነበር። ከፕሮግራሙ አቅራቢ ጋር ስለ ተማሪዎች ባሕርይ አንስተው ሲወያዩ “በምታስተምሪበት ክፍል ውስጥ ያሉት ልጆች ጥሩ ምግባር እንዲኖራቸው የምታደርጊው እንዴት ነው?” በማለት ጠየቃት። መምህርቷም በክፍሏ ውስጥ የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች መማሪያ መጽሐፌ የተባለውን መጽሐፍ ለማስተማሪያነት እንደምትጠቀምበት ነገረችው። አክላም የሃይማኖት ትምህርት በክፍል ውስጥ እያስተማረች እንዳልሆነች ከተናገረች በኋላ በዚህ መጽሐፍ አማካኝነት ልጆቹ ሰውን ማክበርን፣ መቻቻልን፣ አንድነትን፣ ትብብርን፣ ታዛዥነትን እንዲሁም ፍቅርን የመሰሉ የሥነ ምግባር እሴቶችን እንዲያዳብሩ እየረዳቻቸው እንደሆነ ገልጻለች። እነዚህ ባሕርያት ደግሞ ልጆች ሊማሯቸው የሚገቡ አስፈላጊ ትምህርቶች እንደሆኑ ሁሉም ተስማምተዋል።
አንተስ ልጆችህ እነዚህን ባሕርያት እንዲያዳብሩ ትፈልጋለህ? የይሖዋ ምሥክሮች የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች መማሪያ መጽሐፌ የተባለውን ግሩም መጽሐፍ እንዲሰጡህ መጠየቅ ትችላለህ።
[የግርጌ ማስታወሻ]
a በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀ።