በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

“በቋንቋ ብንለያይም ፍቅር አንድ አድርጎናል”

“በቋንቋ ብንለያይም ፍቅር አንድ አድርጎናል”

“በቋንቋ ብንለያይም ፍቅር አንድ አድርጎናል”

መዳን። ነጻ መውጣት። ለበርካታ ዘመናት ሰዎች ከችግርና ከጭንቀት የሚገላገሉበትን ጊዜ ሲናፍቁ ኖረዋል። በሕይወት ውስጥ የሚያጋጥሙንን ችግሮች እንዴት መወጣት እንችላለን? መዳን የምናገኝበት ጊዜ ይመጣ ይሆን? ከሆነስ እንዴት?

ግንቦት ወር 2006 የተጀመሩት በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጁ የሦስት ቀን የአውራጃ ስብሰባዎች በዚህ ርዕሰ ጉዳይ ላይ ያተኮሩ ነበሩ። የእነዚህ ስብሰባዎች ጭብጥ “መዳናችን ቀርቧል!” የሚል ነበር።

ከእነዚህ የአውራጃ ስብሰባዎች መካከል በዘጠኙ ላይ ከተለያዩ አገሮች የመጡ በሺዎች የሚቆጠሩ ልዑካን ተገኝተው ነበር። በሐምሌና በነሐሴ 2006 የተደረጉት እነዚህ ዘጠኝ ስብሰባዎች የተካሄዱት የቼክ ሪፑብሊክ ዋና ከተማ በሆነችው በፕራግ፣ የስሎቫኪያ ዋና ከተማ በሆነችው በብራቲስላቫ፣ ፖላንድ ውስጥ በቾርዞና በፖዝናን ከተሞች a እንዲሁም ዶርትሙንት፣ ፍራንክፈርት፣ ሀምበርግ፣ ላይፕሲግና ሙኒክ በተባሉት አምስት የጀርመን ከተሞች ውስጥ ነው። በእነዚህ የአውራጃ ስብሰባዎች ላይ በአጠቃላይ ከ313,000 በላይ ተሰብሳቢዎች ተገኝተዋል።

በስብሰባው ወቅት የነበረው መንፈስ ምን ይመስል ነበር? ታዛቢዎችስ ስለ ስብሰባዎቹ ምን አስተያየት ሰጥተዋል? ተሰብሳቢዎቹስ ከስብሰባው በኋላ ምን ተሰምቷቸዋል?

ለስብሰባው የተደረጉ ዝግጅቶች

ወደ ስብሰባው የሄዱት ልዑካንም ሆኑ ስብሰባው በሚካሄድባቸው አገሮች ውስጥ የሚገኙት የይሖዋ ምሥክሮች በዚህ የማይረሳ መንፈሳዊ ዝግጅት ላይ ለመገኘት ጓጉተው ነበር። ወደ ስብሰባው ለሚመጡት ልዑካን የተሟላ ማረፊያ ማዘጋጀት ቀላል ሥራ አልነበረም። ለአብነት ያህል፣ በፖላንድ የሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮች በቾርዞ በሚካሄደው የአውራጃ ስብሰባ ላይ ለመገኘት ከምሥራቅ አውሮፓ የሚመጡ ወደ 13,000 የሚጠጉ እንግዶችን በቤታቸው ለመቀበል ፈቃደኛ መሆናቸውን ገልጸው ነበር። ከሊትዌኒያ፣ ከላትቪያ፣ ከሞልዶቫ፣ ከሩሲያ፣ ከቤላሩስ፣ ከቱርክሜኒስታን፣ ከታጂኪስታን፣ ከአርሜኒያ፣ ከኡዝቤኪስታን፣ ከኤስቶኒያ፣ ከኪርጊስታን፣ ከካዛክስታን፣ ከዩናይትድ ስቴትስ፣ ከዩክሬንና ከጆርጂያ የመጡ ልዑካን በዚህ የአውራጃ ስብሰባ ላይ ተገኝተዋል።

በርካታ ልዑካን ለጉዟቸው መዘጋጀት የጀመሩት ከወራት በፊት ነበር። ታቲያና የተባለች የሙሉ ጊዜ ወንጌላዊት የምትኖረው ካምቻትካ በተባለች ከጃፓን በስተ ሰሜን ምሥራቅ የምትገኝ የሩሲያ ባሕረ ገብ መሬት ላይ ነው፤ ታቲያና ለጉዞዋ የሚሆን ገንዘብ ማጠራቀም የጀመረችው ከአንድ ዓመት በፊት ነበር። ይህቺ የሙሉ ጊዜ ወንጌላዊት ወደ ስብሰባው ቦታ ለመድረስ 10,500 ኪሎ ሜትር ያህል መጓዝ ነበረባት። ወደ ቾርዞ ለመሄድ መጀመሪያ ለ5 ሰዓታት በአውሮፕላን፣ ከዚያም ለሦስት ቀናት ገደማ በባቡር በመጨረሻም ለ30 ሰዓታት በአውቶቡስ ተጉዛለች።

ከስብሰባው በፊት በሺዎች የሚቆጠሩ ፈቃደኛ ሠራተኞች ስታዲየሞቹንና አካባቢያቸውን በማጽዳት ለይሖዋ አምልኮ የሚስማማ እንዲሆኑ አድርገዋል። (ዘዳግም 23:14) አንድ ምሳሌ ለመጥቀስ ያህል፣ በላይፕሲግ የሚገኙት የይሖዋ ምሥክሮች ስታዲየሙን ግሩም አድርገው ያጸዱት ሲሆን ከስብሰባው በኋላም እንደገና እንደሚያጸዱት ተናገሩ። በዚህም የተነሳ የስታዲየሙ ባለ ሥልጣናት፣ ለኪራይ ከተዋዋሉት ገንዘብ ውስጥ የጽዳት ወጪዎችን ለመሸፈን ተብሎ የተመደበውን ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ ቀነሱላቸው።

ሰዎችን መጋበዝ

በዓለም ዙሪያ የሚገኙ ጉባኤዎች “መዳናችን ቀርቧል!” ወደተባለው የአውራጃ ስብሰባ ብዙ ሰዎችን ጋብዘዋል። ለየት ባሉ የአውራጃ ስብሰባዎች ላይ ለመገኘት ያሰቡት ወንድሞችም በዚህ ዘመቻ በከፍተኛ ቅንዓት ተካፍለዋል። በስብሰባው ዋዜማ እስከ ምሽት ድረስ ሰዎችን ይጋብዙ ነበር። በቅንዓት ያከናወኑት ሥራ ያስገኘው መልካም ውጤት ይኖር ይሆን?

ቦግዳን የተባለ ፖላንዳዊ የይሖዋ ምሥክር ያነጋገራቸው አንድ አዛውንት በቾርዞ በሚደረገው የአውራጃ ስብሰባ ላይ ለመገኘት ቢፈልጉም 120 ኪሎ ሜትር ለመጓዝ የሚበቃ ገንዘብ እንደሌላቸው ነገሩት። እንደ አጋጣሚ ሆኖ በዚያ አካባቢ የሚገኘው ጉባኤ በተከራየው አውቶቡስ ውስጥ አንድ ክፍት ቦታ ነበረ። ቦግዳን “ከንጋቱ 11:30 ላይ አውቶቡሱ ወደሚነሳበት ቦታ ከመጡ ከእኛ ጋር በነጻ መሄድ እንደሚችሉ ለአዛውንቱ ነገርናቸው” ብሏል። እኚህ አረጋዊ ሰው ግብዣውን ተቀብለው በስብሰባው ላይ ተገኙ። ቆይቶም እኚህ አዛውንት “በዚህ ስብሰባ ላይ ከተገኘሁ በኋላ የተሻልኩ ሰው ለመሆን ቆርጫለሁ” የሚል ደብዳቤ ለወንድሞች ጽፈዋል።

በፕራግ፣ ከብሪታንያ የመጡ ልዑካን ባረፉበት ሆቴል ውስጥ የነበረ ሰው፣ አንድ ምሽት በዚያን ዕለት በተደረገው ስብሰባ ላይ እንደተገኘ ለልዑካኑ ነገራቸው። ግለሰቡ በስብሰባው ላይ እንዲገኝ ያነሳሳው ምንድን ነው? ይህ ሰው መንገድ ላይ አሥር አስፋፊዎች የመጋበዣውን ወረቀት ስለሰጡት ወደ ስብሰባው መሄድ እንዳለበት እንደተሰማው ገልጿል። በስብሰባው ላይ በመገኘቱ በጣም የተደሰተ ከመሆኑም በላይ ይበልጥ ለማወቅ ጓጉቶ ነበር።—1 ጢሞቴዎስ 2:3, 4

ገንቢ የሆነ መንፈሳዊ ፕሮግራም

የተለያዩ ችግሮች ሲያጋጥሙ ምን ማድረግ እንደሚቻል በፕሮግራሙ ላይ ተብራርቶ ነበር። በስብሰባው ላይ የቀረቡት ቀጥተኛ የመጽሐፍ ቅዱስ ምክሮች እነዚህን ችግሮች መፍታት ወይም በጽናት መቋቋም የሚቻለው እንዴት እንደሆነ ጠቁመዋል።

በዕድሜ መግፋት፣ በጤና እክል፣ የሚወዱትን ሰው በሞት በማጣት ወይም በሌሎች የግል ችግሮች የሚሠቃዩ ግለሰቦች ለሕይወት ብሩሕ አመለካከት እንዲኖራቸው የሚረዳ ቅዱስ ጽሑፋዊ ማበረታቻ አግኝተዋል። (መዝሙር 72:12-14) ባሎችና ሚስቶች አስደሳች ትዳር እንዲኖራቸው፣ ወላጆች ደግሞ ልጆቻቸውን በተሳካ ሁኔታ ማሳደግ እንዲችሉ የሚረዳ የመጽሐፍ ቅዱስ ምክር ተሰጥቷቸዋል። (መክብብ 4:12፤ ኤፌሶን 5:22, 25፤ ቈላስይስ 3:21) ወጣት ክርስቲያኖች በትምህርት ቤት ለመጥፎ ተጽዕኖ የተጋለጡ ቢሆኑም በቤትም ሆነ በጉባኤ ጥበብ ያዘለ ቅዱስ ጽሑፋዊ ምክር ይሰጣቸዋል። እነዚህ ወጣቶች እኩዮቻቸው የሚያደርጉባቸውን ተጽዕኖ መቋቋምና ‘ከወጣትነት ክፉ ምኞት መሸሽ’ እንዴት እንደሚችሉ የሚገልጽ ተግባራዊ የሚሆን ምክር አግኝተዋል።—2 ጢሞቴዎስ 2:22

እውነተኛ ዓለም አቀፋዊ የወንድማማች ኅብረት

የይሖዋ ምሥክሮች ተግባራዊ ሊሆኑ የሚችሉ የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያዎችን ሁልጊዜ በስብሰባዎቻቸው ላይ ያገኛሉ። (2 ጢሞቴዎስ 3:16) እነዚህን የአውራጃ ስብሰባዎች ለየት የሚያደርጋቸው ግን ዓለም አቀፋዊ ይዘት ያላቸው መሆኑ ነው። በሁሉም ለየት ያሉ የአውራጃ ስብሰባዎች ላይ ተመሳሳይ መንፈሳዊ ፕሮግራም በተለያዩ ቋንቋዎች ቀርቧል። በእያንዳንዱ ቀን የይሖዋ ምሥክሮች የበላይ አካል አባላት ንግግሮች ያቀረቡ ከመሆኑም በላይ ከሌሎች አገሮች የተገኙ ሪፖርቶች ስብሰባው ይበልጥ አስደሳች እንዲሆን አድርገዋል። በስብሰባው ላይ የተገኙትን የተለያየ ቋንቋ ያላቸው ሰዎች ለመርዳት ሲባል እነዚህ ንግግሮችና ሪፖርቶች ይተረጎሙ ነበር።

ልዑካኑ ከሌሎች አገሮች የመጡ ወንድሞቻቸውንና እህቶቻቸውን ለማግኘት ጓጉተው ነበር። አንድ ልዑክ እንዲህ ብሏል:- “የቋንቋ ልዩነት ከባድ ችግር አልፈጠረም። እንዲያውም ወቅቱ ይበልጥ አስደሳች እንዲሆን አድርጓል። እንግዶቹ የተለያየ ባሕል ያላቸው ቢሆንም ሁሉም አንድ ዓይነት እምነት ስላላቸው አንድ ሆነዋል።” በሙኒክ በተደረገው የአውራጃ ስብሰባ ላይ የተገኙት ተሰብሳቢዎች “በቋንቋ ብንለያይም ፍቅር አንድ አድርጎናል” ብለዋል። ተሰብሳቢዎቹ ከየትኛውም አገር ይምጡ፣ የሚናገሩት ቋንቋ ምንም ይሁን ምን በእውነተኛ ወዳጆቻቸው ማለትም በመንፈሳዊ ወንድሞቻቸውና እህቶቻቸው መካከል እንዳሉ ተሰምቷቸዋል።—ዘካርያስ 8:23

የምስጋና መግለጫዎች

በፖላንድ በተደረጉት የአውራጃ ስብሰባዎች ወቅት የአየሩ ሁኔታ የልዑካኑን ዝንባሌና ጽናት የሚፈትን ነበር። አብዛኛውን ጊዜ ይዘንብ የነበረ ከመሆኑም በላይ የሙቀቱ መጠን ወደ 14 ዲግሪ ሴንቲ ግሬድ በመውረዱ አየሩ በጣም ይቀዘቅዝ ነበር። ከዩናይትድ ስቴትስ የመጣ አንድ ወንድም እንዲህ ብሏል:- “በአውራጃ ስብሰባ ላይ እንዲህ ዓይነት ቀዝቃዛ አየር አጋጥሞኝ አያውቅም፤ አብዛኛው የፕሮግራሙ ክፍል አልገባኝም። ሆኖም ከተለያዩ አገራት የመጡ ሰዎች መኖራቸው የፈጠረው አስደሳች ሁኔታ እንዲሁም ልዩ የሆነው የእንግዳ ተቀባይነት መንፈስ ይህን ሁሉ አካክሶታል። ፈጽሞ የማይረሳ የአውራጃ ስብሰባ ነበር!”

የፖላንድ ቋንቋ ተናጋሪ ለሆኑት ተሰብሳቢዎች ደግሞ ቅዱሳን ጽሑፎችን ጠለቅ ብሎ ማስተዋል የተባለው መጽሐፍ በፖላንድ ቋንቋ መውጣቱ ስብሰባው የማይረሳ እንዲሆንላቸው አድርጓል፤ በእርግጥም ቅዝቃዜውንም ሆነ ዝናቡን ተቋቁመው በመጽናታቸው ተክሰዋል። “መዳናችን ቀርቧል!” በተባለው የአውራጃ ስብሰባ ላይ የተገኙ ሁሉ ሊቭ ዊዝ ጂሆቫስ ዴይ ኢን ማይንድ የተባለው አዲስ መጽሐፍ መውጣቱ በጣም አስደስቷቸዋል።

ብዙዎቹ ተሰብሳቢዎች ደግሞ ስብሰባውን የሚያስታውሱባቸው ሌሎች ምክንያቶች አሏቸው። የቼክ ሪፑብሊክ ዜጋ የሆነችና ከባሕር ማዶ ከመጡት ልዑካን ጋር በአውቶቡስ ለመጓዝ ራሷን በፈቃደኝነት ያቀረበች ክርስቲና የተባለች እህት እንዲህ ብላለች:- “በምንሰነባበትበት ወቅት አንዲት እህት ወደ አንድ ጥግ ወሰደችኝና እቅፍ አድርጋ ‘ጥሩ አድርገሽ ተንከባክበሽናል! የተቀመጥንበት ቦታ ድረስ ምግብና የሚጠጣ ውኃም ሳይቀር አምጥተሽልናል። የራስሽን ጥቅም መሥዋዕት አድርገሽ ፍቅር ስላሳየሽን በጣም እናመሰግንሻለን’ አለችኝ።” ይህች እህት ከባሕር ማዶ ለመጡት ልዑካን ስለተደረገው የምሳ ዝግጅት መግለጿ ነበር። አንድ ወንድም እንዲህ ብሏል:- “እንዲህ ዓይነት ሥራ የማከናወን ልምድ አልነበረንም። በየቀኑ 6,500 ለሚያህሉ ሰዎች ምሳ ማቅረብ ነበረብን። ልጆችን ጨምሮ ብዙዎች እገዛ ለማድረግ በፈቃደኝነት ራሳቸውን ሲያቀርቡ መመልከት ልብ የሚነካ ነበር።”

በአውራጃ ስብሰባው ላይ ለመገኘት ከዩክሬን ወደ ቾርዞ የተጓዘች አንዲት እህት እንዲህ ብላለች:- “የእምነት ባልንጀሮቻችን ባሳዩን ፍቅር፣ ባደረጉልን እንክብካቤና በለጋስነታቸው በጥልቅ ተነክተናል። ምስጋናችንን ለመግለጽ ቃላት ያጥሩናል።” ከፊንላንድ የመጣችው አኒካ የተባለች የስምንት ዓመት ልጅ በፖላንድ ለሚገኘው የይሖዋ ምሥክሮች ቅርንጫፍ ቢሮ እንዲህ በማለት ጽፋለች:- “የአውራጃ ስብሰባው ከገመትኩት በላይ በጣም ግሩም ነበር። በይሖዋ ድርጅት ውስጥ መታቀፍ ልዩ መብት ነው፤ ምክንያቱም በዓለም ዙሪያ ወዳጆች አሉን!”—መዝሙር 133:1

ታዛቢዎች የሰጡት አስተያየት

የአውራጃ ስብሰባዎቹ ከመካሄዳቸው በፊት አንዳንድ ልዑካን የሄዱበትን አገር እንዲጎበኙ ዝግጅት ተደርጎ ነበር። ልዑካኑ በባቫሪያ፣ ጀርመን ገጠራማውን አካባቢ ሲጎበኙ የመንግሥት አዳራሾች ባሉባቸው ቦታዎች ይቆሙ የነበረ ሲሆን በአካባቢው የሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮችም በደስታ ይቀበሏቸው ነበር። አንደኛውን ቡድን ታስጎበኝ የነበረችው የይሖዋ ምሥክር ያልሆነች ሴት በተመለከተችው የወንድማማች ፍቅር በጣም ተደንቃ ነበር። አንድ ልዑክ እንዲህ ብሏል:- “በአውቶቡስ ተሳፍረን ወደ ሆቴላችን ስንመለስ፣ አስጎብኚዋ ከሌሎች ጎብኚዎች በጣም የተለየን እንደሆንን ነገረችን። ጥሩ አለባበስ የነበረን ከመሆኑም በላይ ሁላችንም ቡድኑን ከሚመሩት ሰዎች ጋር እንተባበር ነበር። መሰዳደብም ሆነ ትርምስ አልነበረም። የማይተዋወቁ ሰዎች በአጭር ጊዜ ውስጥ ወዳጆች መሆናቸው አስገርሟታል።”

በፕራግ በተደረገው የአውራጃ ስብሰባ ላይ በዜና አገልግሎት ክፍል ውስጥ የሠራ አንድ ወንድም እንዲህ ብሏል:- “እሁድ ጠዋት፣ በአውራጃ ስብሰባው ላይ የተመደቡት ፖሊሶች ኃላፊ ሊጎበኘን መጣ። ስብሰባው ሰላም የሰፈነበት እንደሆነና ምንም የሚሠራው ነገር እንደሌለ ተናገረ። በስታዲየሙ አካባቢ የሚኖሩ አንዳንድ ሰዎች ስለ ስብሰባው እንደጠየቁትም ገለጸ። ኃላፊው፣ የይሖዋ ምሥክሮች ስብሰባ መሆኑን ሲነግራቸው አብዛኛውን ጊዜ ስጋታቸውን ይገልጻሉ፤ እርሱ ግን ‘ሰዎች በመጠኑ እንኳ እንደ የይሖዋ ምሥክሮች ቢሆኑ ኖሩ ፖሊሶች አያስፈልጉም ነበር’ በማለት ይመልስላቸው ነበር።”

በአሁኑ ጊዜም ብዙ ሰዎች ድነዋል!

የአምላክ ቃል የሆነው መጽሐፍ ቅዱስ በተለያዩ ባሕሎች መካከል እንደ ድልድይ በመሆን ክርስቲያኖች ሰላምና አንድነት እንዲኖራቸው ያደርጋል። (ሮሜ 14:19፤ ኤፌሶን 4:22-24፤ ፊልጵስዩስ 4:7) “መዳናችን ቀርቧል!” በሚል ርዕስ የተደረጉት ለየት ያሉ የአውራጃ ስብሰባዎች ይህንን አረጋግጠዋል። የይሖዋ ምሥክሮች ይህንን ዓለም እያስጨነቁት ካሉት በርካታ መቅሠፍቶች በአሁኑ ጊዜም ድነዋል። በማኅበረሰቡ ውስጥ ከሚገኙት ችግሮች መካከል አለመቻቻል፣ ጠብ አጫሪነትና ዘረኝነት ጥቂቶቹ ሲሆኑ የይሖዋ ምሥክሮች እነዚህን ባሕርያት አስወግደዋል ማለት ይቻላል፤ መላው ዓለም ከእነዚህ ችግሮች ነጻ የሚሆንበትን ጊዜ በናፍቆት ይጠባበቃሉ።

በእነዚህ ስብሰባዎች ላይ የተገኙ ሰዎች ከተለያዩ አገሮችና ባሕሎች በመጡ የይሖዋ ምሥክሮች መካከል ያለውን አንድነት መመልከት ችለዋል። በስብሰባዎቹ መጨረሻ ላይ ይህ በግልጽ ታይቷል። ሁሉም ያጨበጭቡ፣ በስብሰባው ላይ ካገኟቸው አዳዲስ ጓደኞቻቸው ጋር ይተቃቀፉና የመሰነባበቻ ፎቶግራፍ ይነሱ ነበር። (1 ቆሮንቶስ 1:10፤ 1 ጴጥሮስ 2:17) ልዑካኑ ከችግሮችና ከሚያስጨንቋቸው ነገሮች ሁሉ ነጻ የሚወጡበት ጊዜ እንደቀረበ እርግጠኞች ሆነውና ተደስተው ወደመጡበት አገርና ጉባኤ የተመለሱ ሲሆን የአምላክን ‘የሕይወት ቃል’ አጥብቀው ለመያዝም ቁርጥ ውሳኔ አድርገዋል።—ፊልጵስዩስ 2:15, 16

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

a በእነዚህ ቦታዎች በተካሄዱት ስብሰባዎች ላይ ጎብኚ ተናጋሪዎች ያቀረቧቸው ክፍሎች ፖላንድ ውስጥ በሌሎች ስድስት ቦታዎች እንዲሁም በስሎቫኪያ ከዋና ከተማዋ በተጨማሪ በሌላ ቦታ በተደረጉ የአውራጃ ስብሰባዎች ላይ ተላልፈዋል።

[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

ሃያ ስድስት ቋንቋዎች እንደ አንድ ሲነገሩ

በእነዚህ ዘጠኝ የአውራጃ ስብሰባዎች በሙሉ ፕሮግራሙ የቀረበው በአካባቢው በሚነገረው ቋንቋ ነበር። በጀርመን በተደረጉት የአውራጃ ስበሰባዎች ላይ ትምህርቶቹ ከጀርመንኛ በተጨማሪ በሌሎች 18 ቋንቋዎች ተላልፈዋል። በዶርትሙንት ስብሰባው በአረብኛ እንዲሁም በስፔን፣ በፋርስ፣ በፖርቹጋልና በሩሲያ ቋንቋዎች ሲደረግ በፍራንክፈርት ደግሞ በእንግሊዝኛ፣ በፈረንሳይኛና በሰርቢያ/ክሮኤሽያ ቋንቋ ተካሂዷል፤ በሃምበርግ ከተማ ስብሰባው የተካሄደው በዳኒሽ፣ በደች፣ በስዊድንና በታሚል ቋንቋዎች ነው። በላይፕሲግ ከተማ ፕሮግራሙ በቻይንኛ፣ በፖላንድና በቱርክ ቋንቋዎች የቀረበ ሲሆን በሙኒክ ደግሞ በግሪክኛ፣ በጣሊያንኛና በጀርመን የምልክት ቋንቋ ስብሰባው ተካሂዶ ነበር። በፕራግ በተደረገው የአውራጃ ስብሰባ ላይ ትምህርቶቹ ሁሉ የተላለፉት በእንግሊዝኛ፣ በቼክና በሩስያ ቋንቋዎች ነበር። በብራቲስላቫ ፕሮግራሙ በእንግሊዝኛ፣ በሃንጋሪና በስሎቫኪያ ቋንቋዎች እንዲሁም በስሎቫኪያ የምልክት ቋንቋ ተደርጎ ነበር። በቾርዞ ስብሰባው በፖላንድ፣ በሩስያና በዩክሬን ቋንቋዎች እንዲሁም በፖላንድ የምልክት ቋንቋ የተካሄደ ሲሆን በፖዝናን ደግሞ በፖላንድና በፊንላንድ ቋንቋዎች ተደርጓል።

በጠቅላላ ሃያ ስድስት ቋንቋዎች ነበሩ! እውነትም ተሰብሳቢዎቹ በቋንቋ ቢለያዩም ፍቅር አንድ አድርጓቸዋል።

[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በፍራንክፈርት የነበሩ ከክሮኤሽያ የመጡ ልዑካን “የአዲስ ዓለም ትርጉም” በቋንቋቸው ማግኘታቸው እጅግ አስደስቷቸዋል