በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

“ክፉን በመልካም አሸንፍ”

“ክፉን በመልካም አሸንፍ”

“ክፉን በመልካም አሸንፍ”

“ክፉን በመልካም አሸንፍ እንጂ በክፉ አትሸነፍ።” —ሮሜ 12:21

1. ክፉን ማሸነፍ እንደምንችል እርግጠኞች መሆን የምንችለው ለምንድን ነው?

 እውነተኛውን አምልኮ አጥብቀው የሚቃወሙ ሰዎችን በጽናት መቋቋም ይቻላል? ከአምላክ ወደራቀው ዓለም ሊመልሱን የሚታገሉንን ተጽዕኖዎችስ ማሸነፍ ይቻላል? ለሁለቱም ጥያቄዎች መልሱ አዎን ይቻላል የሚል ነው! እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው? ሐዋርያው ጳውሎስ ለሮም ክርስቲያኖች ከጻፈው “ክፉን በመልካም አሸንፍ እንጂ በክፉ አትሸነፍ” ከሚለው ሐሳብ በመነሳት ነው። (ሮሜ 12:21) በይሖዋ ከታመንንና ዓለም እንዳያሸንፈን ቁርጥ ውሳኔ ካደረግን በዓለም ላይ ያለው ክፋት አያሸንፈንም። ከዚህም በላይ “ክፉን በመልካም አሸንፍ” ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛው አገላለጽ ክፉን ለመቋቋም መንፈሳዊ ውጊያ ማካሄዳችንን ከቀጠልን ክፉን ማሸነፍ እንደምንችል ያሳያል። በዚህ ክፉ ዓለምና ክፉ በሆነው ገዢው በሰይጣን ዲያብሎስ የሚሸነፉት ተዘናግተው ውጊያውን የሚያቆሙ ብቻ ናቸው።—1 ዮሐንስ 5:19

2. በነህምያ ሕይወት ውስጥ የተከናወኑ አንዳንድ ሁኔታዎችን የምንመረምረው ለምንድን ነው?

2 ጳውሎስ ከኖረበት ዘመን 500 ዓመታት ገደማ ቀደም ብሎ በኢየሩሳሌም ይኖር የነበረ አንድ የአምላክ አገልጋይ፣ ጳውሎስ ክፉን ስለመዋጋት የተናገረውን ሐሳብ እውነተኝነት አረጋግጧል። ነህምያ የተባለው ይህ የአምላክ ሰው ይሖዋን የማይፈሩ ሰዎች ያደረሱበትን ተቃውሞ ከመቋቋሙም በላይ ክፉን በመልካም አሸንፏል። ነህምያ ምን አስቸጋሪ ሁኔታዎች ገጥመውት ነበር? እንዲሳካለት የረዳውስ ምንድን ነው? የእርሱን ምሳሌ መኮረጅ የምንችለው እንዴት ነው? ለእነዚህ ጥያቄዎች መልስ ለማግኘት ነህምያ በሕይወቱ ውስጥ ያጋጠሙትን አንዳንድ ሁኔታዎች እንመርምር። a

3. ነህምያ በኖረበት ወቅት ምን ዓይነት ሁኔታ ነበር? እሱስ ምን ታላቅ ሥራ አከናውኗል?

3 ነህምያ በፋርስ ንጉሥ በአርጤክስስ ቤተ መንግሥት ውስጥ ያገለግል ነበር። ነህምያ የኖረው በማያምኑ ሰዎች መካከል ቢሆንም በወቅቱ የነበረውን ‘ዓለም አልመሰለም።’ (ሮሜ 12:2) በይሁዳ መከናወን ያለበት ተግባር እንዳለ ባወቀ ጊዜ የተደላደለ ኑሮውን መሥዋዕት በማድረግ ወደ ኢየሩሳሌም ለመሄድ አስቸጋሪ የሆነውን ጉዞ ተያያዘው፤ ከዚያም የከተማዋን ቅጥር እንደገና የመገንባቱን ከባድ ሥራ ማከናወን ጀመረ። (ሮሜ 12:1) ነህምያ የኢየሩሳሌም አገረ ገዥ የነበረ ቢሆንም “ጎሕ ሲቀድ ጀምሮ ከዋክብት እስኪወጡ ድረስ” ወገኖቹ ከሆኑት እስራኤላውያን ጋር አብሮ ይሠራ ነበር። በዚህም የተነሳ ሥራው በሁለት ወራት ውስጥ ተጠናቀቀ! (ነህምያ 4:21፤ 6:15) በግንባታው ወቅት እስራኤላውያን የተለያዩ ተቃውሞዎች ስላጋጠሟቸው ሥራው መጠናቀቁ አስደናቂ ነበር! ነህምያን ይቃወሙት የነበሩት እነማን ናቸው? ዓላማቸውስ ምን ነበር?

4. የነህምያ ጠላቶች ዓላማቸው ምን ነበር?

4 ዋነኛ ተቃዋሚዎቹ በይሁዳ አቅራቢያ የሚኖሩ ሰንባላጥ፣ ጦቢያና ጌሳም የተባሉ ተደማጭነት ያላቸው ሰዎች ነበሩ። እነዚህ ሰዎች የአምላክ ሕዝብ ጠላቶች በመሆናቸው “ስለ እስራኤላውያን ደኅንነት የሚቈረቈር [ነህምያ የተባለ] ሰው በመምጣቱ እጅግ ተበሳጩ።” (ነህምያ 2:10, 19) የነህምያ ጠላቶች የተንኰል ሴራ በመጠንሰስ የግንባታውን ሥራ ለማጨናገፍ ቆርጠው ነበር። ታዲያ ነህምያ ‘በክፉ ይሸነፍ’ ይሆን?

“ተቈጣ፤ እጅግም ተበሳጨ”

5, 6. (ሀ) የነህምያ ጠላቶች የግንባታውን ሥራ በተመለከተ ምን አሉ? (ለ) ነህምያ በተቃዋሚዎቹ አነጋገር በፍርሃት ያልራደው ለምን ነበር?

5 ነህምያ “የኢየሩሳሌምን ቅጥር እንደ ገና እንሥራ” በማለት ሕዝቡን በድፍረት አበረታታቸው። ሕዝቡም “መሥራቱን እንጀምር” በማለት መለሱለት። ነህምያ፣ ሕዝቡ “እጃቸውንም ለበጎ ሥራ አበረቱ” [የ1954 ትርጉም] ብሏል። አክሎም ተቃዋሚዎቹ “አፌዙብን፤ አንቋሸሹንም፤ እንዲሁም፣ ‘የምታደርጉት ይህ ምንድን ነው? በንጉሡ ላይ ልታምፁ ትፈልጋላችሁን?’ አሉ” በማለት ተናግሯል። የእነዚህ ተቃዋሚዎች ፌዝና የሰነዘሩት የሐሰት ክስ ነህምያ በፍርሃት እንዲርድ አላደረገውም። ለተቃዋሚዎቹ “የሰማይ አምላክ ያከናውንልናል፤ እኛ ባርያዎቹ እንደ ገና ሥራውን እንጀምራለን” በማለት መለሰላቸው። (ነህምያ 2:17-20) ነህምያ በዚህ “በጎ ሥራ” ለመቀጠል ቆርጦ ነበር።

6 ከተቃዋሚዎቹ አንዱ የሆነው ሰንባላጥ ይህን ሲያውቅ “ተቈጣ፤ እጅግም ተበሳጨ።” ከዚህም በላይ የስድብ ናዳ አወረደባቸው። “እነዚህ ደካማ አይሁድ ምን እያደረጉ ነው? . . . የፍርስራሽ ክምር የሆነውን ድንጋይ ነፍስ ሊዘሩበት ይችላሉን?” በማለት አላገጠባቸው። ጦቢያም ተደርቦ “በድንጋይ የሚሠሩት ቅጥር እኮ ቀበሮ እንኳ ብትወጣበት ሊፈርስ ይችላል” ሲል አፌዘባቸው። (ነህምያ 4:1-3) በዚህ ወቅት ነህምያ ምን አድርጎ ይሆን?

7. ነህምያ ተቃዋሚዎቹ ለሰነዘሩት ትችት ምላሽ የሰጠው በየትኞቹ መንገዶች ነው?

7 ነህምያ ፌዛቸውን ችላ ብሎ አለፈው። የአምላክን ሕግ ይከተል ስለነበረ አጸፋውን ለመመለስ አልሞከረም። (ዘሌዋውያን 19:18) ከዚህ ይልቅ ጉዳዩን ለይሖዋ በመተው “አምላካችን ሆይ፤ ተንቀናልና ስማን፤ ስድባቸውን በራሳቸው ላይ አውርድባቸው” ሲል ጸልዮአል። (ነህምያ 4:4) ነህምያ፣ ይሖዋ “በቀል የእኔ ነው፤ እኔ ብድራትን እመልሳለሁ” በማለት በሰጠው ማረጋገጫ ታምኗል። (ዘዳግም 32:35) ከዚህም በላይ ነህምያና ሕዝቡ ‘ቅጥሩን መሥራታቸውን’ ቀጠሉ። ምንም ነገር ከሥራቸው እንዲያዘናጋቸው አልፈቀዱም። እንዲያውም “ቅጥሩም ሁሉ እስከ እኩሌታው ድረስ ተጋጠመ፤ የሕዝቡም ልብ ለሥራው ጨከነ።” (ነህምያ 4:6 የ1954 ትርጉም) የእውነተኛው አምልኮ ጠላቶች የግንባታውን ሥራ ማስቆም አልቻሉም! እኛስ የነህምያን ምሳሌ መከተል የምንችለው እንዴት ነው?

8. (ሀ) ተቃዋሚዎች በሐሰት ሲወነጅሉን የነህምያን ምሳሌ መኮረጅ የምንችለው እንዴት ነው? (ለ) አጸፋ ከመመለስ መራቅ የጥበብ እርምጃ እንደሆነ የሚያሳይ አንተ ያጋጠመህን ወይም የሰማኸውን ተሞክሮ ተናገር።

8 በዛሬው ጊዜ አብረውን የሚማሩ ልጆች፣ የሥራ ባልደረቦቻችን ወይም የቤተሰባችን አባላት ሳይቀሩ እንኳ እኛን በመቃወም ይሳለቁብንና ይወነጅሉን ይሆናል። ሆኖም አብዛኛውን ጊዜ እንዲህ ያሉ የሐሰት ክሶች ሲገጥሙን የተሻለው እርምጃ “ለዝምታ ጊዜ አለው” የሚለውን የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓት ተግባራዊ ማድረግ ነው። (መክብብ 3:1, 7) በመሆኑም እኛም የአሽሙር ቃላት ተጠቅመን አጸፋ ከመመለስ በመቆጠብ የነህምያን ምሳሌ መኮረጅ እንችላለን። (ሮሜ 12:17) “እኔ ብድራትን እመልሳለሁ” ብሎ ቃል በገባልን አምላክ በመታመን ወደ እርሱ እንጸልያለን። (ሮሜ 12:19፤ 1 ጴጥሮስ 2:19, 20) እንዲህ ካደረግን ተቃዋሚዎቻችን በዛሬው ጊዜ መከናወን ካለበት ስለ አምላክ መንግሥት ምሥራች የመስበክና ደቀ መዛሙርት የማድረግ መንፈሳዊ ሥራ እንዲያዘናጉን ፈጽሞ አንፈቅድም። (ማቴዎስ 24:14፤ 28:19, 20) ተቃውሞ እንዲያደናቅፈን ሳንፈቅድ በስብከቱ ሥራ በተካፈልን መጠን እንደ ነህምያ ቆራጥ መሆናችንን እናሳያለን።

‘እንገድላችኋለን’

9. የነህምያ ጠላቶች ተቃውሟቸውን በምን መንገድ ገለጹ? ነህምያስ ምን አደረገ?

9 በነህምያ ዘመን የነበሩት የእውነተኛው አምልኮ ተቃዋሚዎች “የኢየሩሳሌም ቅጥር ሥራ እየተፋጠነ” እንደሆነ ሲሰሙ ሰይፋቸውን ይዘው “ኢየሩሳሌምን ይወጉ ዘንድ” መጡ። ለአይሁዳውያን ሁኔታው ተስፋ አስቆራጭ ነበር። በስተ ሰሜን ሳምራውያን፣ በስተ ምሥራቅ አሞናውያን፣ በስተ ደቡብ አረቦችና በስተ ምዕራብ ደግሞ የአሽዶድ ሕዝቦች ተነስተውባቸው ነበር። ኢየሩሳሌም ስለተከበበች ቅጥሩን የሚገነቡት ሰዎች መውጫ አልነበራቸውም! ምን ያደርጉ ይሆን? ነህምያ “እኛ ግን ወደ እግዚአብሔር ጸለይን” ብሏል። ጠላቶቻቸው ‘እንገድላቸዋለን፤ ሥራውንም እናስቆመዋለን’ ብለው ዛቱ። ነህምያም ቅጥሩን የሚገነቡት ሰዎች “ሰይፋቸውን፣ ጦራቸውንና ቀስታቸውን” ይዘው ከተማዋን እንዲከላከሉ አደረገ። እርግጥ ነው፣ በሰብዓዊ አመለካከት ሲታይ አነስተኛ የሆኑት አይሁዳውያን ከፍተኛ ቁጥር ያለውን የጠላቶቻቸውን ሠራዊት የሚቋቋሙት አይመስልም ነበር። ሆኖም ነህምያ “አትፍሯቸው፤ ታላቁንና የተፈራውን እግዚአብሔርን አስቡ” በማለት አደፋፈራቸው።—ነህምያ 4:7-9, 11, 13, 14

10. (ሀ) የነህምያ ጠላቶች በድንገት ዕቅዳቸውን የለወጡት ለምን ነበር? (ለ) ነህምያ ምን እርምጃዎች ወሰደ?

10 በድንገት ሁኔታዎቹ ተለዋወጡ። የአምላክ ሕዝብ ጠላቶች ጥቃቱን ከመሰንዘር ታቀቡ። ነህምያ፣ ይህ የሆነው ‘እግዚአብሔር ዕቅዳቸውን ከንቱ ስላደረገባቸው’ እንደሆነ ገልጿል። ሆኖም ነህምያ ጠላቶቻቸው አሁንም ቢሆን እንደሚያሰጓቸው ተገንዝቦ ነበር። በመሆኑም ቅጥሩን የሚገነቡት ሰዎች ሥራቸውን በሚያከናውኑበት መንገድ ላይ ማስተዋል የታከለበት ለውጥ አደረገ። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ሠራተኞቹ “በአንድ እጃቸው ሥራቸውን ሲሠሩ፣ በሌላው እጃቸው የጦር መሣሪያቸውን ይዘው ነበር።” ከዚህም በተጨማሪ ነህምያ፣ ጠላቶች ቢመጡ ግንበኞቹን ለማስጠንቀቅ “መለከት የሚነፋ” ሰው መድቦ ነበር። ከሁሉ በላይ ደግሞ ነህምያ “አምላካችን ስለ እኛ ይዋጋል” በማለት ሕዝቡን አበረታቷቸዋል። (ነህምያ 4:15-20) ቅጥሩን የሚገነቡት ሰዎች ጥቃት ቢሰነዘርባቸው ምን እንደሚያደርጉ ተዘጋጅተውና ተበረታትተው ሥራቸውን ቀጠሉ። ከዚህ ዘገባ ምን ትምህርት ማግኘት እንችላለን?

11. እውነተኛ ክርስቲያኖች የአምላክ መንግሥት ሥራ በታገደባቸው አገሮች ውስጥ ክፉን እንዲቋቋሙ የሚረዳቸው ምንድን ነው? ክፉን በመልካም የሚያሸንፉትስ እንዴት ነው?

11 አንዳንድ ጊዜ እውነተኛ ክርስቲያኖች ከባድ ተቃውሞ ይገጥማቸዋል። እንዲያውም በአንዳንድ አገሮች እውነተኛውን አምልኮ አጥብቀው የሚቃወሙት ሰዎች ከፍተኛ ኃይል አላቸው። ከሰብዓዊ አመለካከት አንጻር ሲታይ በእነዚህ አገሮች ውስጥ ያሉት የእምነት ባልንጀሮቻችን ጠላቶቻቸውን መቋቋም አይችሉም። ያም ቢሆን ግን እነዚህ የይሖዋ ምሥክሮች ‘አምላክ ስለ እነርሱ እንደሚዋጋ’ እርግጠኞች ናቸው። በእርግጥም በእምነታቸው ምክንያት የሚሰደዱ ሁሉ ይሖዋ ጸሎታቸውን እንደሚሰማና የኃያል ጠላቶቻቸውን ዕቅድ ‘ከንቱ እንደሚያደርገው’ በተደጋጋሚ ጊዜያት ተመልክተዋል። የአምላክ መንግሥት ሥራ በታገደባቸው አገሮችም እንኳ ክርስቲያኖች ምሥራቹን መስበካቸውን ለመቀጠል አጋጣሚዎች ይፈልጋሉ። በኢየሩሳሌም የነበሩት ግንበኞች ሥራቸውን የሚያከናውኑበትን መንገድ እንደለወጡ ሁሉ በዛሬው ጊዜ ያሉ የይሖዋ ምሥክሮችም ጥቃት ሲደርስባቸው የሚሰብኩበትን መንገድ በጥበብ ይለውጣሉ። እርግጥ ነው፣ የጦር መሣሪያ አይጠቀሙም። (2 ቆሮንቶስ 10:4) ሆኖም ተቃዋሚዎች አካላዊ ጥቃት እንደሚሰነዝሩባቸው ቢያስፈራሯቸውም እንኳ የስብከት እንቅስቃሴያቸውን አያቆሙም። (1 ጴጥሮስ 4:16) ከዚህ በተቃራኒ እነዚህ ደፋር ወንድሞችና እህቶች ‘ክፉን በመልካም ያሸንፋሉ።’

‘ናና እንገናኝ’

12, 13. (ሀ) የነህምያ ተቃዋሚዎች ምን ዓይነት ዘዴ ተጠቀሙ? (ለ) ነህምያ ከተቃዋሚዎቹ ጋር እንዲገናኝ የቀረበለትን ግብዣ ያልተቀበለው ለምን ነበር?

12 የነህምያ ጠላቶች የሰነዘሩት ቀጥተኛ ጥቃት እንደከሸፈ ሲገነዘቡ ይበልጥ ስውር በሆኑ ዘዴዎች መጠቀም ጀመሩ። እንዲያውም ሦስት የተለያዩ መሠሪ ዘዴዎችን ለመጠቀም ሞክረዋል። እነዚህ ዘዴዎች ምን ነበሩ?

13 በመጀመሪያ የነህምያ ጠላቶች ሊያታልሉት ሞከሩ። “ናና በኦኖ ሜዳ ከሚገኙት መንደሮች በአንዲቱ እንገናኝ” አሉት። ኦኖ በኢየሩሳሌምና በሰማሪያ መካከል የሚገኝ ቦታ ነው። በመሆኑም የነህምያ ጠላቶች ችግሩን ለመፍታት በሁለቱ ከተሞች መካከል ባለ ቦታ ላይ እንዲገናኙ ጠየቁት። ነህምያ ‘ይህ ምክንያታዊ ይመስላል፤ ከመዋጋት መወያየት ይሻላል’ ብሎ ሊያስብ ይችል ነበር። ሆኖም ነህምያ በሐሳባቸው አልተስማማም። “እኔን ለመጕዳት ዐቅደው ነበር” በማለት በሐሳባቸው ያልተስማማበትን ምክንያት ገልጿል። ተንኰላቸውን ስለነቃባቸው አልተታለለም። ተቃዋሚዎቹ አራት ጊዜ ያህል እንዲህ ያለ መልእክት ቢልኩበትም እርሱ ግን “ወዳላችሁበት ስፍራ መውረድ አልችልም፤ ትቼው ወደ እናንተ ወርጄ ሥራው ለምን ይቆማል?” በማለት መልሶላቸዋል። የነህምያ ጠላቶች አቋሙን እንዲያላላ ያደረጉት ሙከራ አልተሳካም። ነህምያ ትኩረት ያደረገው በግንባታው ሥራ ላይ ነበር።—ነህምያ 6:1-4

14. ነህምያ በሐሰት ክስ ለሰነዘሩበት ሰዎች ምን ምላሽ ሰጠ?

14 የነህምያ ጠላቶች የተጠቀሙበት ሁለተኛ ዘዴ ደግሞ ይህ የአምላክ አገልጋይ በንጉሥ አርጤክስስ ላይ ‘ለማመፅ እንደሚዶልት’ የሚገልጽ የሐሰት ወሬ ማናፈስ ነበር። ጠላቶቹ “በአንድነት እንመካከር” የሚል መልእክት በድጋሚ ላኩበት። በዚህ ጊዜም ቢሆን ነህምያ የጠላቶቹ ዓላማ ስለገባው ጥሪውን አልተቀበለም። “ሁሉም፣ ‘እጃቸው መሥራት እስኪሳነው ድረስ ይዝላል፤ ሥራውም ሳይጠናቀቅ ይቀራል’ ብለው በማሰብ ሊያስፈራሩን ሞከሩ” በማለት ተናግሯል። በዚህ ጊዜ ግን ነህምያ “አንተ የምትለውን የመሰለ ምንም ነገር አልተደረገም፤ ይህ አንተ በአእምሮህ የፈጠርኸው ነው” በማለት የጠላቶቹን ክስ ውድቅ አደረገው። ከዚህም በላይ “እጄን አበርታ” በማለት ለእርዳታ ወደ ይሖዋ ጸለየ። በይሖዋ እርዳታ ይህንን ክፉ ሴራ ማክሸፍ እንደሚችልና የግንባታውን ሥራ እንደሚቀጥል ተማምኖ ነበር።—ነህምያ 6:5-9

15. አንድ የሐሰት ነቢይ ነህምያን ምን ብሎ መከረው? ነህምያስ ምክሩን ያልተቀበለው ለምን ነበር?

15 በሦስተኛ ደረጃ፣ ጠላቶቹ ነህምያ የአምላክን ሕግ እንዲጥስ ለማድረግ ከሃዲ በሆነው ሸማያ የተባለ እስራኤላዊ ተጠቀሙ። ሸማያ፣ ነህምያን እንዲህ አለው:- “ሰዎች ሊገድሉህ ይመጣሉ፤ . . . በእግዚአብሔር ቤት ባለው በቤተ መቅደሱ ውስጥ እንገናኝ፤ የቤተ መቅደሱንም በሮች እንዝጋቸው።” ሸማያ፣ ነህምያ ሊገደል እንደሆነና በቤተ መቅደሱ ውስጥ በመደበቅ ሕይወቱን ሊያተርፍ እንደሚችል ነገረው። ሆኖም ነህምያ ካህን ስላልነበረ በአምላክ ቤት ውስጥ ቢደበቅ ኃጢአት ይሆንበታል። ታዲያ ሕይወቱን ለማዳን ሲል የአምላክን ሕግ ይጥስ ይሆን? ነህምያ “እንደ እኔ ያለ ሰው . . . ሕይወቱን ለማዳን ሲል ወደ ቤተ መቅደስ መግባት ይገባዋልን? አልሄድም!” በማለት መለሰለት። ይህ የአምላክ አገልጋይ በተዘጋጀለት ወጥመድ ውስጥ ያልገባው ለምን ነበር? ሸማያ እስራኤላዊ ቢሆንም “እግዚአብሔር . . . እንዳልላከው” ያውቅ ስለነበረ ነው። ደግሞም እውነተኛ ነቢይ የአምላክን ሕግ እንዲጥስ ፈጽሞ አይመክረውም። በዚህ ጊዜም ቢሆን ነህምያ በክፉ ተቃዋሚዎቹ አልተሸነፈም። ይህ ከሆነ ከጥቂት ጊዜ በኋላ “ቅጥሩም ኤሉል በተባለው ወር ሃያ አምስተኛ ቀን፣ በአምሳ ሁለት ቀን ውስጥ ተጠናቀቀ” ብሎ ሊናገር ችሏል።—ነህምያ 6:10-15፤ ዘኍልቍ 1:51፤ 18:7

16. (ሀ) ወዳጅ መስለው የሚቀርቡና በሐሰት የሚወነጅሉ ግለሰቦች እንዲሁም ሐሰተኛ ወንድሞች ሲያጋጥሙን ምን ልናደርግ ይገባል? (ለ) በቤት ውስጥ፣ በትምህርት ቤትና በሥራ ቦታ አቋምህን እንደማታላላ ማሳየት የምትችለው እንዴት ነው?

16 እኛም እንደ ነህምያ ወዳጅ መስለው ከሚቀርቡን ሰዎች፣ በሐሰት ከሚወነጅሉን ግለሰቦች እንዲሁም ከሐሰተኛ ወንድሞች ተቃውሞ ሊያጋጥመን ይችላል። የነህምያ ጠላቶች አቋሙን እንዲያላላ ሐሳብ እንዳቀረቡ ሁሉ በዛሬው ጊዜም አንዳንድ ሰዎች አቋማችንን እንድናላላ ለማድረግ ይጥሩ ይሆናል፤ ይህንንም የሚያደርጉት ለይሖዋ አገልግሎት ያለንን ቅንዓት በመጠኑ ብንቀንስ አምላክን እያገለገልን ዓለማዊ ግቦችንም መከታተል እንደምንችል ሊያሳምኑን በመሞከር ሊሆን ይችላል። ይሁን እንጂ በሕይወታችን ውስጥ የመጀመሪያውን ቦታ የሚይዘው የአምላክ መንግሥት በመሆኑ አቋሟችንን አናላላም። (ማቴዎስ 6:33፤ ሉቃስ 9:57-62) ተቃዋሚዎች በእኛ ላይ የሐሰት ክስም ይሰነዝሩብናል። ነህምያ በንጉሡ ላይ ዓመጽ እንደሚያነሳሳ የሚገልጽ ውንጀላ እንደተሰነዘረበት ሁሉ እኛም በአንዳንድ አገሮች ውስጥ ለመንግሥት አስጊ እንደሆንን ተደርገን እንከሰሳለን። አንዳንዶቹን ውንጀላዎች በፍርድ ቤት ቀርበን እውነት እንዳልሆኑ ማረጋገጥ ችለናል። እንደዚህ ባሉ ሁኔታዎች ውስጥ ውጤቱ ምንም ይሁን ምን ይሖዋ ነገሮችን እንደ ፈቃዱ እንደሚመራቸው በመተማመን እንጸልያለን። (ፊልጵስዩስ 1:7 NW) ይሖዋን እንደሚያገለግሉ ከሚናገሩ ሰዎችም ተቃውሞ ሊመጣ ይችላል። አንድ አይሁዳዊ፣ ነህምያ ሕይወቱን ለማዳን የአምላክን ሕግ እንዲጥስ ሊያሳምነው እንደሞከረ ሁሉ የይሖዋ ምሥክር የነበሩ ከሃዲዎችም አቋሟችንን እንድናላላ ለማድረግ በተለያየ መንገድ ተጽዕኖ ሊያሳድሩብን ይሞክሩ ይሆናል። እኛ ግን ሕይወታችን የሚድነው የአምላክን ሕግጋት በመጣስ ሳይሆን በመታዘዝ እንደሆነ ስለምናውቅ ከሃዲዎችን በፍጹም አንቀበላቸውም! (1 ዮሐንስ 4:1) አዎን፣ በይሖዋ እርዳታ ማንኛውንም ዓይነት ክፉ ነገር ማሸነፍ እንችላለን።

ክፉ ቢያጋጥመንም ምሥራቹን ማወጅ

17, 18. (ሀ) ሰይጣንና ወኪሎቹ ምን ለማድረግ ይጥራሉ? (ለ) አንተስ ምን ለማድረግ ቆርጠሃል? ለምንስ?

17 የአምላክ ቃል፣ የክርስቶስን ቅቡዓን ወንድሞች በተመለከተ “እነርሱም . . . በምስክርነታቸውም ቃል፣ [ሰይጣንን] ድል ነሡት” በማለት ይናገራል። (ራእይ 12:11) ከዚህ መመልከት እንደምንችለው የክፉ ነገሮች ሁሉ ምንጭ የሆነውን ሰይጣንን ድል በማድረግና የመንግሥቱን መልእክት በማወጅ መካከል ቀጥተኛ ግንኙነት አለ። ሰይጣን በቅቡዓን ቀሪዎችም ሆነ ‘በእጅግ ብዙ ሕዝብ’ ላይ ተቃውሞ በማስነሳት ያለማቋረጥ ጥቃት መሰንዘሩ አያስደንቅም!—ራእይ 7:9፤ 12:17

18 ቀደም ብለን እንደተመለከትነው ተቃዋሚዎች ሊሰድቡን ወይም አካላዊ ጥቃት እንደሚያደርሱ ሊያስፈራሩን አሊያም ደግሞ ሌሎች ስውር ዘዴዎችን ሊጠቀሙ ይችላሉ። የሚጠቀሙበት ዘዴ ምንም ይሁን ምን የሰይጣን ዓላማ ምንጊዜም አንድ ነው፤ ይኸውም የስብከቱን ሥራ ማስቆም ነው። ሆኖም የአምላክ ሕዝቦች፣ በጥንት ጊዜ የነበረውን የነህምያን ምሳሌ በመከተል ‘ክፉን በመልካም ለማሸነፍ’ ስለቆረጡ የሰይጣን ጥረት ሁሉ መና ሆኖ ይቀራል። ይሖዋ ሥራው ተፈጽሟል እስከሚልበት ጊዜ ድረስ ምሥራቹን መስበካቸውን በመቀጠል ክፉን በመልካም ያሸንፋሉ!—ማርቆስ 13:10፤ ሮሜ 8:31፤ ፊልጵስዩስ 1:27, 28

[የግርጌ ማስታወሻ]

a ስለ እነዚህ ሁኔታዎች ለማወቅ ነህምያ 1:1-4፤ 2:1-6, 9-20፤ 4:1-23፤ 6:1-15ን አንብብ።

ታስታውሳለህ?

• በጥንት ጊዜ የአምላክ አገልጋዮች ምን ተቃውሞ አጋጥሟቸው ነበር? በዘመናችን የሚገኙ ክርስቲያኖችስ ምን ያጋጥማቸዋል?

• የነህምያ ጠላቶች ዋና ዓላማቸው ምን ነበር? በዛሬው ጊዜ የሚገኙ የአምላክ ጠላቶችስ ዓላማቸው ምንድን ነው?

• በዛሬው ጊዜ ክፉን በመልካም ማሸነፍ የምንችለው እንዴት ነው?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 29 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

ከነህምያ መጽሐፍ የምናገኘው ትምህርት

የአምላክ አገልጋዮች የሚያጋጥሟቸው ነገሮች

• ፌዝ

• ዛቻና

• ማታለያ

ማታለያ የሚቀርብባቸው መንገዶች

• ወዳጅ መስለው ከሚቀርቡን ሰዎች

• በሐሰት ከሚወነጅሉን ግለሰቦች

• ከሐሰተኛ ወንድሞች

የአምላክ አገልጋዮች

• አምላክ የሰጣቸውን ሥራ በመሥራት

ክፉን ያሸንፋሉ

[በገጽ 27 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ነህምያና አብረውት ይሠሩ የነበሩት ሰዎች ከፍተኛ ተቃውሞ ቢያጋጥማቸውም የኢየሩሳሌምን ቅጥር መልሰው ገንብተዋል

[በገጽ 31 ላይ የሚገኝ ሥዕል1]

እውነተኛ ክርስቲያኖች ምሥራቹን በድፍረት ይሰብካሉ