በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ዘረኝነት—መፍትሔው ምንድን ነው?

ዘረኝነት—መፍትሔው ምንድን ነው?

ዘረኝነት—መፍትሔው ምንድን ነው?

አንድ ዳኛ በስፔን ይካሄድ የነበረውን የእግር ኳስ ጨዋታ ለማስቆም ተገደው ነበር። እንዲህ ያደረጉት ለምን ይሆን? በርካታ ተመልካቾች በአንድ ካሜሩናዊ ተጫዋች ላይ የስድብ ናዳ ስላወረዱበት ተጫዋቹ ሜዳውን ለቆ እንደሚወጣ በመግለጹ ነበር። በሩስያ፣ በአፍሪካውያንና በእስያውያን እንዲሁም ከላቲን አሜሪካ በመጡ ሰዎች ላይ የሚደርሰው ጥቃት የተለመደ ነገር እየሆነ መጥቷል፤ በ2004 በዘር ጥላቻ ምክንያት የተደረጉ ጥቃቶች በ55 በመቶ በመጨመራቸው በ2005 ቁጥሩ ወደ 394 ከፍ ብሏል። በብሪታንያ በአንድ ጥናት ከተካፈሉት የእስያ ተወላጆችና ጥቁሮች መካከል አንድ ሦስተኛ የሚሆኑት ሥራቸውን ያጡት በዘር መድሎ የተነሳ እንደሆነ ይሰማቸዋል። እነዚህ ምሳሌዎች በዓለም ዙሪያ እየተንጸባረቀ ያለውን ዝንባሌ የሚጠቁሙ ናቸው።

ዘረኝነት፣ ቅር በሚያሰኝ ወይም የሌሎችን ስሜት በሚጎዳ ንግግር አሊያም በብሔራዊ ፖሊሲ ደረጃ አንድን ዘር ለማጥፋት በመሞከር ሊገለጽ ይችላል። የዘረኝነት መንስኤ ምንድን ነው? እኛስ ከዘረኝነት መራቅ የምንችለው እንዴት ነው? የሰው ዘር በሙሉ በሰላም አብሮ የሚኖርበት ጊዜ እንደሚመጣ ተስፋ ማድረጋችን ምክንያታዊ ይሆን? መጽሐፍ ቅዱስ ይህን ጉዳይ በማስመልከት ትኩረት የሚስብ ሐሳብ ይሰጣል።

ጭቆናና ጥላቻ

መጽሐፍ ቅዱስ “ሰው ገና ከልጅነቱ ጀምሮ ሐሳቡ ወደ ክፋት ያዘነበለ” እንደሆነ ይናገራል። (ዘፍጥረት 8:21) በመሆኑም አንዳንዶች ሌሎችን በመጨቆን ይደሰታሉ። ከዚህም በላይ መጽሐፍ ቅዱስ “የተገፉትን ሰዎች እንባ ተመለከትሁ፤ የሚያጽናናቸውም አልነበረም፤ ኀይል በሚገፏቸው ሰዎች እጅ ነበረ” ይላል።—መክብብ 4:1

ከዚህም በተጨማሪ መጽሐፍ ቅዱስ የዘር ጥላቻ ከጥንት ጀምሮ እንደነበረ ይገልጻል። ለምሳሌ ያህል፣ በ18ኛው መቶ ዘመን ከክርስቶስ ልደት በፊት የግብጹ ፈርዖን ዕብራዊውን ያዕቆብንና ብዙ ቁጥር ያላቸውን የቤተሰቡን አባላት ወደ ግብጽ መጥተው እንዲኖሩ ጋብዟቸው ነበር። ይሁን እንጂ ከጊዜ በኋላ መግዛት የጀመረ ሌላ ፈርዖን በርካታ ቁጥር ያላቸውን እነዚህን ከባዕድ አገር የመጡ ሰዎች ስለፈራቸው ምን እንዳደረገ የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ ሲገልጽ እንዲህ ይላል:- “እርሱም ሕዝቡን እንዲህ አላቸው፤ ‘እነሆ፤ እስራኤላውያን በቍጥር በልጠውናል፤ ከእኛም ይልቅ እየበረቱ ነው፤ ቍጥራቸው እንዳይጨምር፣ . . . ዘዴ እንፈልግ።’ ስለዚህ እያስጨነቁ የግዳጅ ሥራ የሚያሠሯቸውን አሠሪ አለቆች ሾሙባቸው።” (ዘፀአት 1:9-11) እንዲያውም ግብጻውያን የያዕቆብ ዘሮች ሲወልዱ ሕፃናቱ ወንዶች ከሆኑ እንዲገደሉ ትእዛዝ ሰጥተው ነበር።—ዘፀአት 1:15, 16

ዘረኝነት መንስኤው ምንድን ነው?

በዓለም ላይ የሚገኙ ሃይማኖቶች ዘረኝነትን በመቃወም ረገድ ይህ ነው የሚባል ሥራ አላከናወኑም። አንዳንድ ግለሰቦች በሌሎች ዘሮች ላይ የሚደርሰውን ጭቆና በድፍረት ቢቃወሙም ሃይማኖት በአጠቃላይ ግን አብዛኛውን ጊዜ ከጨቋኞቹ ጋር ወግኗል። በዩናይትድ ስቴትስ እንዲህ ዓይነት ሁኔታ ነበር፤ በዚህች አገር የነበረው ሕግ ጥቁር የቆዳ ቀለም ባላቸው ሰዎች ላይ የሚደርሰውን ጭቆና ይፈቅድ የነበረ ከመሆኑም በላይ ጥቁሮች ለፍርድ ሳይቀርቡ ይገደሉ ነበር፤ ከዚህም በላይ የተለያየ ዘር ባላቸው ሰዎች መካከል ጋብቻ እንዳይከናወን የሚከለክለው ሕግ እስከ 1967 ድረስ ይሠራ ነበር። በደቡብ አፍሪካም ቢሆን በአፓርታይድ አገዛዝ ወቅት አነስተኛ ቁጥር ያላቸው ሰዎች የበላይነታቸውን ለማስጠበቅ ካወጧቸው ሕግጋት መካከል የተለያየ ዘር ያላቸው ሰዎች እንዳይጋቡ የሚከለክለው ሕግ ይገኝበት ነበር። ከላይ ባየናቸው በሁለቱም ሁኔታዎች፣ አጥባቂ ሃይማኖተኛ የሚባሉ አንዳንድ ሰዎች ዘረኝነትን ደግፈዋል።

መጽሐፍ ቅዱስ የዘረኝነትን ዋና መንስኤ ይገልጽልናል። አንዳንድ ዘሮች ሌላውን የሚጨቁኑበትን ምክንያት እንዲህ በማለት ይነግረናል:- “የማይወድ ግን እግዚአብሔርን አያውቅም፤ እግዚአብሔር ፍቅር ነውና። ማንም፣ ‘እግዚአብሔርን እወደዋለሁ’ እያለ ወንድሙን ቢጠላ፣ እርሱ ሐሰተኛ ነው፤ ያየውን ወንድሙን የማይወድ ያላየውን እግዚአብሔርን መውደድ አይችልምና።” (1 ዮሐንስ 4:8, 20) ይህ ጥቅስ የዘረኝነት ዋነኛ መንስኤ ምን እንደሆነ ግልጽ ያደርግልናል። ሃይማኖተኛ እንደሆኑ የሚናገሩትም ሆነ ሃይማኖተኛ ያልሆኑት ሰዎች ዘረኝነትን የሚያስፋፉት አምላክን ስለማያወቁት ወይም ለእርሱ ፍቅር ስለሌላቸው ነው።

አምላክን ማወቅ ሁሉም ዘሮች ተስማምተው መኖር እንዲችሉ መሠረት ነው

አምላክን ማወቅና መውደድ ሁሉም ዘሮች ተስማምተው እንዲኖሩ የሚያደርጋቸው እንዴት ነው? የአምላክ ቃል፣ ሰዎች ከእነርሱ የተለዩ የሚመስሉ ግለሰቦችን ከመጉዳት እንዲቆጠቡ የሚያደርግ ምን እውቀት ይዟል? መጽሐፍ ቅዱስ፣ ይሖዋ የሰው ዘሮች በሙሉ አባት እንደሆነ ይናገራል። የአምላክ ቃል “ለእኛ ግን ሁሉም ነገር ከእርሱ የሆነ፣ . . . አንድ አምላክ አብ አለን” ይላል። (1 ቆሮንቶስ 8:6) በተጨማሪም “የሰውን ዘር ሁሉ ከአንድ ወገን [እንደፈጠረ]” ይናገራል። (የሐዋርያት ሥራ 17:26) በመሆኑም የሰው ዘሮች በሙሉ ወንድማማቾች ናቸው ማለት ይቻላል።

ሁሉም ዘሮች ሕይወትን ያገኙት ከአምላክ በመሆኑ ሊኮሩ ቢችሉም የዘር ሐረጋቸውን በተመለከተ ግን ሁሉም ቢሆን የሚያዝኑበት ምክንያት አለ። የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊ የሆነው ጳውሎስ “ኀጢአት በአንድ ሰው በኩል ወደ ዓለም እንደ ገባ” ተናግሯል። በመሆኑም “ሁሉም ኀጢአትን ሠርተዋል፤ የእግዚአብሔርም ክብር ጐድሎአቸዋል።” (ሮሜ 3:23፤ 5:12) ይሖዋ አምላክ ልዩ ልዩ ፍጥረታትን ፈጥሯል፤ ፍጹም አንድ ዓይነት የሆኑ ፍጥረታት የሉም። ያም ቢሆን ግን የትኛውም ዘር ከሌላው እንደሚበልጥ እንዲሰማው ምክንያት የሚሆን ነገር አላደረገም። ብዙዎች የራሳቸው ዘር ከሌላው እንደሚበልጥ ይሰማቸዋል፤ ሆኖም በዓለም ላይ ተስፋፍቶ የሚገኘው ይህ አመለካከት በቅዱሳን መጻሕፍት ላይ ከሰፈረው እውነታ ጋር ይቃረናል። ከዚህ በግልጽ ለመመልከት እንደምንችለው ከአምላክ የምናገኘው እውቀት የተለያየ ዘር ያላቸው ሰዎች ተስማምተው እንዲኖሩ ያበረታታል።

አምላክ ለሁሉም ብሔራት ያስባል

አንዳንዶች፣ አምላክ እስራኤላውያንን አብልጦ በመውደዱና ከሌሎች ብሔራት የተለዩ እንዲሆኑ በማስተማሩ የዘር መድሎ እንዲኖር እንዳደረገ ይሰማቸዋል። (ዘፀአት 34:12) በአንድ ወቅት አምላክ፣ የእስራኤላውያን ቅድመ አያት የሆነው አብርሃም ባሳየው የሚደነቅ እምነት ምክንያት የእስራኤልን ብሔር ለእርሱ የተለየ ሕዝብ እንዲሆን መርጦት ነበር። አምላክ ራሱ ገዢዎችን በመምረጥና ሕግጋትን በመስጠት የጥንቶቹን እስራኤላውያን ያስተዳድራቸው ነበር። እስራኤላውያን በእነዚህ ዝግጅቶች ተስማምተው በሚኖሩበት ወቅት፣ ሌሎች ብሔራት በአምላክ አገዛዝና በሰዎች አገዛዝ መካከል ያለውን ልዩነት ማስተዋል ይችሉ ነበር። በተጨማሪም ይሖዋ፣ የሰው ዘሮች እንደገና ከእሱ ጋር ጥሩ ግንኙነት እንዲኖራቸው መሥዋዕት አስፈላጊ መሆኑን ለእስራኤላውያን አስተምሯቸዋል። በመሆኑም ይሖዋ ከእስራኤላውያን ጋር የነበረው ግንኙነት ሁሉንም ብሔራት ጠቅሟል። ይህ ደግሞ “ቃሌን ስለ ሰማህ የምድር ሕዝቦች ሁሉ በዘርህ ይባረካሉ” በማለት ለአብርሃም ከገባው ቃል ጋር የሚስማማ ነው።—ዘፍጥረት 22:18

ከዚህም በተጨማሪ አይሁዳውያን የአምላክን ቅዱስ ቃል የመቀበልና መሲሑ የሚወለድበት ብሔር የመሆን መብት አግኝተው ነበር። ይህም ቢሆን ሁሉንም ብሔራት የሚጠቅም ነበር። ለአይሁዳውያን የተሰጡት የዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት፣ ሁሉም የሰው ዘሮች ታላቅ በረከት የሚያገኙበትን ጊዜ በተመለከተ ቀጥሎ ያለውን አስደሳች ሐሳብ ይዘዋል:- “ብዙ አሕዛብ መጥተው እንዲህ ይላሉ፤ ‘ኑ፤ ወደ እግዚአብሔር ተራራ፣ ወደ ያዕቆብ አምላክ ቤት እንሂድ፤ በመንገዱ እንድንሄድ፣ መንገዱን ያስተምረናል።’ . . . አንዱ መንግሥት በሌላው መንግሥት ላይ ሰይፍ አያነሣም፤ ከእንግዲህም የጦርነት ትምህርት አይማሩም። እያንዳንዱ ሰው በገዛ ወይኑ ሥር፣ ከገዛ በለሱም ሥር ይቀመጣል፤ የሚያስፈራቸው አይኖርም።”—ሚክያስ 4:2-4

ኢየሱስ ክርስቶስ ራሱ ለአይሁዳውያን የሰበከ ቢሆንም “ለሕዝብ ሁሉ ምስክር እንዲሆን፣ ይህ የመንግሥት ወንጌል በዓለም ሁሉ ይሰበካል” ብሏል። (ማቴዎስ 24:14) ስለዚህ ምሥራቹን ሳይሰማ የሚቀር ሕዝብ አይኖርም። በመሆኑም ይሖዋ ለማንም ሳያዳላ ሁሉንም የሰው ዘሮች በእኩል ዓይን በመመልከት ረገድ ፍጹም ምሳሌ ትቷል። “እግዚአብሔር ለማንም [አያዳላም]፤ . . . ነገር ግን እርሱን የሚፈሩትንና ጽድቅን የሚያደርጉትን ሁሉ ከየትኛውም ወገን ቢሆኑ ይቀበላቸዋል።”—የሐዋርያት ሥራ 10:34, 35

አምላክ ለጥንቱ የእስራኤል ብሔር የሰጣቸው ሕግጋትም ለሁሉም ብሔራት እንደሚያስብ ያሳያሉ። በሕጉ መሠረት የአምላክ ሕዝቦች በአገራቸው ከሚኖሩ እስራኤላውያን ያልሆኑ ሰዎች ጋር ተቻችለው ከመኖር የበለጠ ነገር እንዲያደርጉ ይጠበቅባቸው ነበር። አምላክ “አብሮአችሁ የሚኖረው መጻተኛ እንደ ገዛ ወገናችሁ ይታይ፤ እንደ ራሳችሁም ውደዱት፤ እናንተም በግብፅ መጻተኞች ነበራችሁና” የሚል ሕግ ሰጥቷቸው ነበር። (ዘሌዋውያን 19:34) አብዛኞቹ የአምላክ ሕግጋት እስራኤላውያን ለመጻተኞች ደግነት እንዲያሳዩ ያስተምሯቸው ነበር። በመሆኑም የኢየሱስ ቅድመ አያት የሆነው ቦዔዝ፣ ችግረኛ የሆነች አንዲት መጻተኛ በእርሻው ውስጥ ስትቃርም ሲመለከት ከአምላክ ካገኘው ትምህርት ጋር የሚስማማ እርምጃ በመውሰድ አጫጆቹ የምትቃርመው በርከት ያለ ነዶ እንዲተዉላት አዟቸዋል።—ሩት 2:1, 10, 16

ኢየሱስ ደግነትን አስተምሯል

ኢየሱስ ከማንኛውም ሰው የበለጠ የአምላክን እውቀት ገልጿል። የተለየ ዘር ላላቸው ሰዎች እንዴት ደግ መሆን እንደሚቻል ለተከታዮቹ አሳይቷቸዋል። በአንድ ወቅት ከአንዲት ሳምራዊት ጋር ውይይት ጀምሮ ነበር። ሳምራውያን በርካታ አይሁዳውያን የሚንቋቸው ሕዝቦች ስለነበሩ ይህች ሴት እንዲህ በማድረጉ ተገርማ ነበር። ኢየሱስ፣ በውይይታቸው ወቅት የዘላለም ሕይወት እንዴት ማግኘት እንደምትችል በደግነት አስረድቷታል።—ዮሐንስ 4:7-14

ኢየሱስ ስለ ደጉ ሳምራዊ በተናገረው ምሳሌ ላይም ከእኛ የተለየ ዘር ያላቸውን ሰዎች እንዴት ልንይዛቸው እንደሚገባ አስተምሮናል። ይህ ሳምራዊ ዘራፊዎች ክፉኛ የደበደቡት አንድ አይሁዳዊ መንገድ ላይ ወድቆ ተመለከተ። ሳምራዊው ‘አይሁዳውያን ሕዝባችንን እየናቁ፣ እኔ ይህን አይሁዳዊ የምረዳው ለምንድን ነው?’ ብሎ ሊያስብ ይችል ነበር። ሆኖም ኢየሱስ በተናገረው ምሳሌ ላይ ሳምራዊው የእሱ ዓይነት ዘር ለሌላቸው ሰዎች ከዚህ የተለየ አመለካከት እንደነበረው ገልጿል። ሌሎች መንገደኞች የተጎዳውን ሰው እያዩት ዝም ብለው ቢያልፉም ሳምራዊው ‘ስላዘነለት’ ከፍተኛ እርዳታ አድርጎለታል። ኢየሱስ ምሳሌውን ሲደመድም የአምላክን ሞገስ ለማግኘት የሚፈልግ ማንኛውም ሰው እንዲህ ማድረግ እንዳለበት ተናግሯል።—ሉቃስ 10:30-37

ሐዋርያው ጳውሎስ አምላክን ለማስደሰት የሚፈልጉ ሰዎች ባሕርያቸውን መለወጥና ከሰዎች ጋር ባላቸው ግንኙነት ረገድ አምላክን መምሰል እንዳለባቸው ሲያስተምር እንዲህ በማለት ጽፏል:- “አሮጌውን ሰው ከሥራው ጋር አውልቃችሁ ስለ ጣላችሁ . . . የፈጣሪውን መልክ እንዲመስል በዕውቀት የሚታደሰውን አዲሱን ሰው ለብሳችኋል፤ በዚያ ግሪክ ወይም ይሁዲ፣ የተገረዘ ወይም ያልተገረዘ፣ አረማዊ ወይም እስኩቴስ . . . ብሎ ልዩነት የለም፤ . . . በእነዚህ ሁሉ ላይ ሁሉን በፍጹም አንድነት የሚያስተሳስረውን ፍቅርን ልበሱት።”—ቈላስይስ 3:9-14

አምላክን ማወቅ ሰዎችን ሊለውጥ ይችላል?

በእርግጥ ሰዎች ይሖዋ አምላክን ማወቃቸው ለሌሎች ዘሮች ያላቸውን አመለካከት ሊለውጥ ይችላል? በካናዳ የምትኖርና በዚያ በደረሰባት የዘር መድሎ ተበሳጭታ የነበረች የአንዲት እስያዊት ስደተኛን ሁኔታ እንመልከት። ይህች ሴት የይሖዋ ምሥክሮችን አግኝታ ከእነሱ ጋር መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ጀመረች። ከጊዜ በኋላ በጻፈችው የአድናቆት ደብዳቤ ላይ እንዲህ ብላለች:- ‘በጣም ጥሩና ደግ ሰዎች ናችሁ። እንደ እናንተው ዓይነት ነጭ የቆዳ ቀለም ካላቸው ሌሎች ሰዎች ለምን እንደተለያችሁ ሳስብ ነበር። በጉዳዩ ላይ ብዙ ካወጣሁና ካወረድሁ በኋላ የአምላክ ምሥክሮች ስለሆኑ ነው ብዬ ደመደምኩ። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እንዲህ እንድትሆኑ ያደረጋችሁ አንድ ነገር መኖር አለበት። በስብሰባዎቻችሁ ላይ የተመለከትኳቸው ሰዎች ነጭ፣ ጥቁር፣ ቡናማና ቢጫ የቆዳ ቀለም ቢኖራቸውም የልባቸው ቀለም ተመሳሳይ ነው፤ ምክንያቱም ወንድማማችና እህትማማች ናቸው። እንደዚህ ጥሩ ሰዎች እንድትሆኑ ያደረጋችሁ አምላካችሁ እንደሆነ አሁን አውቄያለሁ።’

የአምላክ ቃል ‘ምድር ሁሉ እግዚአብሔርን በማወቅ የምትሞላበት’ ጊዜ እንደሚመጣ ይናገራል። (ኢሳይያስ 11:9) በአሁኑ ጊዜም እንኳ “ከሕዝብ፣ ከነገድ፣ ከወገን፣ ከቋንቋም ሁሉ” የተውጣጡ በሚሊዮን የሚቆጠሩ እጅግ ብዙ ሰዎች በእውነተኛው አምልኮ አንድ በመሆናቸው የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት እየተፈጸመ ነው። (ራእይ 7:9) እነዚህ ሰዎች በዓለም ዙሪያ ጥላቻ በፍቅር ሲተካ ለመመልከት ይጓጓሉ፤ በዚያ ወቅት ይሖዋ “የምድር ወገኖች ሁሉ ይባረካሉ” በማለት ለአብርሃም የገለጸው ዓላማ ይፈጸማል።—የሐዋርያት ሥራ 3:25

[በገጽ 4 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የአምላክ ሕግ፣ እስራኤላውያን መጻተኞችን እንዲወዱ አስተምሯቸዋል

[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ስለ ደጉ ሳምራዊ ከሚናገረው ምሳሌ ምን መማር እንችላለን?

[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

አምላክ የትኛውም ዘር ከሌላው እንደሚበልጥ እንዲሰማው ምክንያት የሚሆን ነገር አላደረገም