በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት እምነትን ይገነባል

የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት እምነትን ይገነባል

የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት እምነትን ይገነባል

“ላለፉት አምስት ወራት ለፈጣሪያችን ሐሳቦች ትኩረት መስጠታችንና ነገሮችን እሱ በሚያይበት መንገድ መመልከትን መማራችን እንዴት ያለ ውድ መብት ነው!” ይህንን የተናገረው የጊልያድ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ቤት የ122ኛው ክፍል ተወካይ ሲሆን በዚህ ዕለትም የጊልያድ ተማሪዎች ተመርቀዋል። በዚህ ዕለት ለተመረቁትና በተመደቡባቸው 26 አገሮች ውስጥ የሚስዮናዊነት አገልግሎታቸውን ለሚጀምሩት 56 ተማሪዎች መጋቢት 10, 2007 የማይረሳ ቀን ነው። 

የበላይ አካሉ አባል የሆነው ወንድም ቴዎዶር ጃራዝ 6,205 ለሚሆኑት ተሰብሳቢዎች ሞቅ ያለ አቀባበል ካደረገላቸው በኋላ እንዲህ በማለት ተናገረ:- “በዚህ የምረቃ ሥነ ሥርዓት ላይ መገኘታችሁ መንፈሳዊነታችሁን እንደሚያጠናክረውና እምነታችሁን እንደሚገነባው እርግጠኞች ነን።” ከዚያም ከእርሱ በኋላ በተከታታይ ንግግር የሚያቀርቡት አራት ተናጋሪዎች፣ ተማሪዎቹ በሚስዮናዊነት ምድባቸው ስኬታማ እንዲሆኑ የሚረዳቸው በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ ወቅታዊ ማበረታቻና ምክር እንደሚሰጧቸው አስተዋወቀ።

በሌሎች ላይ እምነት እንዲጥሉ የተሰጡ ማበረታቻዎች

የዩናይትድ ስቴትስ ቅርንጫፍ ቢሮ ኮሚቴ አባል የሆነው ወንድም ሊዮን ዊቨር “መልካም ማድረጋችሁን ቀጥሉ” በሚል ጭብጥ ንግግር አቀረበ። ወንድም ዊቨር፣ ተማሪዎቹ እያንዳንዳቸው በሙሉ ጊዜ አገልግሎት በአማካይ 13 ዓመታት እንዳሳለፉና በዚህ ጊዜ ውስጥ የመጽሐፍ ቅዱስን ትምህርት በማስፋፋቱ ሥራ ተጠምደው እንደነበር አስታወሳቸው። “ያከናወናችሁት ተግባር፣ የሰዎችን ሕይወት የሚያድንና ከሁሉ በላይ ደግሞ በሰማይ የሚኖረውን አባታችንን ይሖዋን ከፍ ከፍ የሚያደርግ በመሆኑ መልካም ሥራ ነው” ብሏል። ከዚያም ተማሪዎቹ ‘መንፈስን ለማስደሰት መዝራታቸውን’ እንዲቀጥሉና ‘በጎ ነገር ከማድረግ እንዳይታክቱ’ አበረታታቸው።—ገላትያ 6:8, 9

የበላይ አካሉ አባል የሆነው ወንድም ዴቪድ ስፕሌን “ጥሩ ጅምር እንዲኖራችሁ ለማድረግ ጣሩ” በሚል ጭብጥ ላይ ተመሥርቶ ተግባራዊ ሊሆኑ የሚችሉ ማሳሰቢያዎችን አቀረበ። ወንድም ስፕሌን አዲሶቹ ሚስዮናውያን የሚከተሉትን ምክሮች ተግባራዊ በማድረግ በተመደቡበት ቦታ ጥሩ ጅምር እንዲኖራቸው አበረታታቸው:- “አዎንታዊ አመለካከት ይኑራችሁ። ስለ አንድ ነገር መደምደሚያ ላይ ለመድረስ አትቸኩሉ። የወዳጅነት መንፈስ አዳብሩ። ነቃፊዎች አትሁኑ። ትሑቶች ሁኑ፤ እንዲሁም የአካባቢውን ወንድሞች አክብሩ።” አክሎም እንዲህ ብሏል:- “ከአውሮፕላን ከወረዳችሁበት ጊዜ ጀምሮ በተመደባችሁበት ቦታ ጥሩ ጅምር ይኑራችሁ፤ እንዲሁም ለሰዎች ‘መልካም ዜና የሚያበስሩ’ ያማሩ እግሮቻችሁን ይሖዋ ይባርክላችሁ።”—ኢሳይያስ 52:7

የጊልያድ ትምህርት ቤት አስተማሪ የሆነው ወንድም ሎረንስ ቦወን ያቀረበው ንግግር ጭብጥ “እርግጠኛ የሆነ ውርስ” የሚል ነበር። ወንድም ቦወን፣ የጊልያድ ትምህርት ቤት በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት የተቋቋመው የይሖዋ ትንቢታዊ ቃል እንደሚፈጸም ሙሉ በሙሉ በመተማመን እንደነበር ተማሪዎቹን አስታወሳቸው። (ዕብራውያን 11:1፤ ራእይ 17:8) ከዚያን ጊዜ ጀምሮ የጊልያድ ትምህርት ቤት፣ ተማሪዎች እምነታቸውን እንዲያጠናክሩ ጥሩ አጋጣሚ ሰጥቷቸዋል። ተመራቂዎቹ ያላቸው ጠንካራ እምነት ደግሞ እውነትን በቅንዓት እንዲያውጁ ይገፋፋቸዋል።

ሌላው የጊልያድ መምህር የሆነው ወንድም ማርክ ኑሜር “አንድን ሰው ታስታውሱኛላችሁ” በሚል ትኩረት የሚስብ ጭብጥ ላይ የተመሠረተ ንግግር አቀረበ። ንግግሩ፣ የተሰጠውን ተልዕኮ በእምነትና በድፍረት ባከናወነው በነቢዩ ኤልያስ ምሳሌ ላይ ያተኮረ ነበር። ወንድም ኑሜር በ1 ነገሥት 19:21 ላይ የተመሠረተ እንዲህ የሚል ሐሳብ ሰጥቷል:- “ኤልያስ በሕይወቱ ውስጥ ማስተካከያ ለማድረግ ፈቃደኛ ነበር፤ ለራሱ ፍላጎቶች ቅድሚያ አልሰጠም እንዲሁም የይሖዋን ዓላማ አውጇል።” ተመራቂዎቹ የኤልያስ ዓይነት መንፈስ በማሳየታቸው ካመሰገናቸው በኋላ በአዲሱ ምድባቸውም እንዲህ ማድረጋቸውን እንዲቀጥሉ አበረታታቸው።

እምነት በድፍረት ለመናገር ያስችላል

ሚስዮናዊ ለመሆን የሚሠለጥኑት ተማሪዎች በትምህርት ክፍለ ጊዜያቸው እምነታቸውን ይገነቡ የነበረ ሲሆን በሳምንቱ የመጨረሻ ቀናት ደግሞ ምሥራቹን ለሰዎች ይሰብኩ ነበር። እንዲህ በማድረጋቸውም ጥሩ ተሞክሮዎች ያገኙ ሲሆን የጊልያድ አስተማሪ የሆነው ወንድም ዋላስ ሊቨራንስ ባቀረበው ክፍል ላይ እነዚህ ተሞክሮዎች ተነግረዋል፤ እንዲሁም በሠርቶ ማሳያ መልክ ቀርበዋል። ወንድም ሊቨራንስ “እምነት ስላለን እንናገራለን” በሚል ጭብጥ ያቀረበው ክፍል በ2 ቆሮንቶስ 4:13 ላይ የሚገኘውን የሐዋርያው ጳውሎስ አባባል የሚያስታውስ ነበር።

ከዚህ ቀጥሎ ደግሞ የቤቴል ቤተሰብ አባላት የሆኑት ወንድም ዳንኤል ባርንዝ እና ወንድም ቻርልስ ዉዲ በአሁኑ ጊዜ በሚስዮናዊነት ለሚያገለግሉና ቀደም ሲል ሚስዮናዊ ለነበሩ ወንድሞች ቃለ መጠይቅ አደረጉላቸው። እነዚህ ወንድሞች፣ ይሖዋ በታማኝነት የሚያገለግሉትን እንደሚንከባከባቸውና እንደሚባርካቸው ጎላ አድርገው ገልጸዋል። (ምሳሌ 10:22፤ 1 ጴጥሮስ 5:7) አንድ ሚስዮናዊ እንዲህ ብሏል:- “እኔና ባለቤቴ በጊልያድ በነበርንበት ጊዜ ያገኘነው ትምህርት ይሖዋ እየተንከባከበን እንዳለ እንድንመለከት አድርጎናል። ያገኘነው ትምህርት እምነታችንን ገንብቶልናል። ሚስዮናውያንን ጨምሮ ሁሉም የአምላክ አገልጋዮች ፈተናዎች፣ ችግሮችና የሚያስጨንቁ ነገሮች ስለሚያጋጥሟቸው እምነት አስፈላጊ ነው።”

እምነት የሚገነባውን የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ማስፋፋታችሁን ቀጥሉ

የበላይ አካሉ አባል የሆነው ወንድም ሳሙኤል ኸርድ “ወንድሞቻችሁን መገንባታችሁን ቀጥሉ” በሚል ርዕስ ለተሰብሳቢዎቹ ያቀረበው ንግግር ለምረቃ ፕሮግራሙ ግሩም መደምደሚያ ነበር። ተማሪዎቹ ያገኙት ትምህርት ዓላማው ምን ነበር? ወንድም ኸርድ “የትምህርቱ ዓላማ፣ ይሖዋን ለማወደስ፣ አዲስ በተመደባችሁበት ክልል ውስጥ የእሱን እውነት ለሰዎች ለማስተማር እንዲሁም የወንድሞቻችሁን እምነት ለመገንባት አንደበታችሁን እንዴት መጠቀም እንዳለባችሁ ማሠልጠን ነው” ብሏል። ይሁን እንጂ አንደበት የማያንጽ ነገርም ሊያስተላለፍ እንደሚችል አስታወሳቸው። (ምሳሌ 18:21፤ ያዕቆብ 3:8-10) ወንድም ኸርድ፣ ተማሪዎቹ በአንደበት አጠቃቀማቸው ረገድ የኢየሱስን ምሳሌ እንዲኮርጁ አበረታታቸው። በአንድ ወቅት የክርስቶስ ደቀ መዛሙርት ኢየሱስ ሲናገር ካዳመጡ በኋላ “ቅዱሳት መጻሕፍትንም ገልጦ ሲያስረዳን፣ ልባችን እንደ እሳት ይቃጠልብን አልነበረምን?” ብለዋል። (ሉቃስ 24:32) ወንድም ኸርድ “ንግግራችሁ የሚያንጽ ከሆነ በተመደባችሁበት ቦታ ያሉትን ወንድሞችና እህቶች ልብ ይነካል” ብሏል።

ቀጥሎም ተመራቂዎቹ ዲፕሎማቸውን ተቀበሉ። ከዚያም የ122ኛው ክፍል ተማሪዎች የጻፉት የአድናቆት ደብዳቤ ተነበበ። ደብዳቤው በከፊል እንዲህ ይላል:- “የሚስዮናዊነት ተልእኳችንን በታማኝነት ለመወጣት በተማርናቸው ነገሮች የመጠቀም ከባድ ኃላፊነት እንዳለብን ይሰማናል። እስከ ምድር ዳር ድረስ ለመሄድ ዝግጁ ሆነን የምናደርገው ጥረት ታላቁ አስተማሪያችን የሆነውን ይሖዋ አምላክን ለማወደስ እንዲያስችለን እንጸልያለን።” የተሰብሳቢዎቹ ጭብጨባ ከዳር እስከ ዳር አስተጋባ። በእርግጥም ይህ የምረቃ ሥነ ሥርዓት የሁሉንም ተሰብሳቢዎች እምነት ገንብቷል።

[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

“ንግግራችሁ የሚያንጽ ከሆነ በተመደባችሁበት ቦታ ያሉትን ወንድሞችና እህቶች ልብ ይነካል”

[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ተማሪዎቹን የሚመለከት አኃዛዊ መረጃ

ተማሪዎቹ የተውጣጡባቸው አገሮች ብዛት:- 9

የተመደቡባቸው አገሮች ብዛት:- 26

የተማሪዎቹ ብዛት:- 56

አማካይ ዕድሜ:- 33.4

በእውነት ውስጥ የቆዩባቸው ዓመታት በአማካይ:- 16.8

በሙሉ ጊዜ አገልግሎት የቆዩባቸው ዓመታት በአማካይ:- 13

[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የጊልያድ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ቤት 122ኛ ክፍል ተመራቂዎች

ከዚህ በታች ባለው ዝርዝር ለእያንዳንዱ ረድፍ ቁጥር የተሰጠው ከፊት ወደ ኋላ ሲሆን ስሞቹ የሰፈሩት ከግራ ወደ ቀኝ ነው።

(1) ሬጂኒ ሃዊት፣ ፖላ ስሚዝ፣ አሊሰን ማርቲኔዝ፣ ሲልቭያ ፖትሶቦን፣ ዩኮ ኪታሙራ፣ ሴሲል ሎድ፤ (2) ኢሊንካ ፊድለር፣ ኬት ቢስሊ፣ ሼርሊን ማትኮቪች፣ ዶን ቤል፣ ዌንዲ ሊፐንከት፤ (3) ዌንዲ ሳይትስ፣ አን አንደርሰን፣ ሊሳ ቶቭስ፣ ጂና ፉሳኖ፣ ካርመን ሮትሪገስ፣ ጂክዮን ዩ፤ (4) ሞኒክ ሶቦሜሂን፣ ሊሳ ቶማስ፣ ሳባ ጋሰን፣ ቬሮኒክ ዶባ፣ አንዤሊክ ቤርቶ፣ ሲንዲ ዊን፣ ማጊ ዶብረቮልስኪ፤ (5) ጂሶን ዩ፣ ዤሮም ዶባ፣ ሃይዲ ሚክሰር፣ ሜሊሳ ኒውተን፣ ፍራንቺስኮ ሮትሪገስ፣ ኔተን ሚክሰር፤ (6) ማርቲን ሎድ፣ ካይል ሊፐንከት፣ ሪኪ ማርቲኔዝ፣ አባይጃ ሆብ፣ ሪና ስካምፕ፣ ሉቾ ፖትሶቦን፣ ሼን ቶቭስ፤ (7) ሴባስትየን ሃዊት፣ ዪቺሮ ኪታሙራ፣ ደስትን ኒውተን፣ ጆሽ ሆብ፣ ጆ ሳይትስ፣ ዳር ቶማስ፤ (8) ላዴ ሶቦሜሂን፣ ጄሲ ማትኮቪች፣ ብራንደን ፉሳኖ፣ ጆን ዊን፣ ጄሰን ስካምፕ፣ ዴኒስ አንደርሰን፣ ያሬክ ዶብረቮልስኪ፤ (9) ፒተር ፊድለር፣ ዩዢን ቤል፣ ብሬት ቢስሊ፣ ብሬንደን ስሚዝ፣ ፊሊፕ ቤርቶ፣ ማርክ ጋሰን