በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

“ሄደህ በሰሊሆም መጠመቂያ ታጠብ”

“ሄደህ በሰሊሆም መጠመቂያ ታጠብ”

“ሄደህ በሰሊሆም መጠመቂያ ታጠብ”

ኢየሱስ ማየት የተሳነውን ሰው ዓይን ጭቃ ከቀባ በኋላ “ሄደህ በሰሊሆም መጠመቂያ ታጠብ” አለው። ሰውየው እንደተባለው ያደረገ ሲሆን “እያየም ተመልሶ መጣ።” (ዮሐንስ 9:6, 7) የሰሊሆም መጠመቂያ የሚገኘው የት ነበር? በቅርብ ጊዜ የተደረገ የመሬት ቁፋሮ ይህ መጠመቂያ የሚገኝበትን ቦታ በተመለከተ አዲስ እውቀት ፈንጥቋል።

በርካታ ጎብኚዎች በኢየሩሳሌም የሚገኝን የሰሊሆም መጠመቂያ በመባል የሚታወቅ ቦታ፣ በዮሐንስ 9:7 ላይ የተጠቀሰው መጠመቂያ እንደሆነ በማሰብ ሲጎበኙት ኖረዋል። ይህ ቦታ የሚገኘው ሕዝቅያስ በስምንተኛው መቶ ዘመን ከክርስቶስ ልደት በፊት ባሠራው 530 ሜትር ርዝመት ያለው የውኃ መውረጃ ቦይ መጨረሻ ላይ ነው። እንደ እውነቱ ከሆነ ግን፣ ይህ መጠመቂያ የተገነባው በአራተኛው መቶ ዘመን ከክርስቶስ ልደት በኋላ ሲሆን የገነቡትም ክርስቲያን ነን ይሉ የነበሩት የባይዛንታይን ሰዎች ናቸው። እነዚህ ሰዎች በዮሐንስ ወንጌል ላይ የተጠቀሰው መጠመቂያ የሚገኘው ሕዝቅያስ በገነባው ቦይ መጨረሻ ላይ መሆን አለበት የሚል እምነት ነበራቸው።

ይሁን እንጂ በ2004 አርኪኦሎጂስቶች ኢየሱስ በምድር ሳለ የነበረው የሰሊሆም መጠመቂያ እንደሆነ ያመኑበትን ፍርስራሽ አገኙ። ይህ ፍርስራሽ የሚገኘው የሰሊሆም መጠመቂያ ነው ተብሎ በስህተት ይታሰብ ከነበረው ቦታ በስተ ደቡብ ምሥራቅ 100 ሜትር ገደማ ራቅ ብሎ ነው። ይህን ቦታ እንዴት ሊያገኙት ቻሉ? የከተማው ባለ ሥልጣናት በአካባቢው የሚገኝን የፍሳሽ ማስወገጃ መስመር መጠገን አስፈልጓቸው ነበር። ስለዚህ ትላልቅ መሣሪያዎች የያዙ ሠራተኞችን ጥገና ወዳስፈለገበት ቦታ ላኩ። በአቅራቢያው እየሠራ የነበረ አንድ አርኪኦሎጂስት ሠራተኞቹ ሲቆፍሩ ይመለከት ጀመር። ይህ ሰው አፈሩ በመነሳት ላይ እያለ ሁለት ደረጃዎችን አየ። በዚህም ምክንያት ሥራው እንዲቆም ተደረገ፤ የእስራኤል ቅርስ ጥበቃ ባለ ሥልጣንም በቦታው ላይ አርኪኦሎጂያዊ ቁፋሮ እንዲካሄድ ፈቃድ ሰጠ። አርኪኦሎጂስቶቹ በዚህ ቁፋሮ አማካኝነት 70 ሜትር ገደማ ርዝመት ያለውን የመጠመቂያውን አንድ ግርግዳና ሁለት ማዕዘኖች ማውጣት ችለዋል።

በቁፋሮው ወቅት ጥቂት ሳንቲሞች ተገኝተው ነበር። እነዚህ ሳንቲሞች አይሁዳውያን በሮማውያን ላይ ባመጹ በሁለተኛው፣ በሦስተኛውና በአራተኛው ዓመት ይገበያዩባቸው የነበሩ ናቸው። ይህ ዓመጽ የቆየው ከ66 እስከ 70 ከክርስቶስ ልደት በኋላ ነበር። በመሆኑም እነዚህ ሳንቲሞች፣ መጠመቂያው ኢየሩሳሌም በሮማውያን እስከተደመሰሰችበት እስከ 70 ከክርስቶስ ልደት በኋላ ድረስ አገልግሎት ይሰጥ እንደነበር ያሳያሉ። ቢብሊካል አርኪኦሎጂ ሪቪው የተባለው መጽሔት የሚከተለውን ሐሳብ ሰጥቷል:- “ዓመጹ እስካበቃበት ጊዜ ድረስ ሰዎች መጠመቂያውን ይጠቀሙበት የነበረ ሲሆን ከዚያ በኋላ ግን አገልግሎት መስጠቱን አቁሟል። በኢየሩሳሌም ከሚገኙት ቦታዎች ሁሉ በጣም ዝቅተኛ የሆነው ይህ አካባቢ እስከ ባይዛንታይን ዘመን ድረስ ሰው አልኖረበትም። በየዓመቱ የሚዘንበው የክረምት ዝናብ ከፍተኛ ከሆኑ ቦታዎች ሸርሽሮ የሚያመጣው አፈር መጠመቂያውን ይሞላዋል። በተጨማሪም ከተማዋ በሮማውያን ከጠፋች በኋላ መጠመቂያው ተጸድቶ አያውቅም። በመሆኑም ለበርካታ መቶ ዓመታት የተከማቸው ደለል ቀስ በቀስ መጠመቂያውን ቀበረው። አርኪኦሎጂስቶቹ ገንዳውን ለማውጣት በአንዳንድ ቦታዎች ላይ ሦስት ሜትር ያህል ወደታች መቆፈር አስፈልጓቸዋል።”

የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች የሰሊሆም መጠመቂያ የነበረበትን ቦታ ማወቃቸው ምን ይጠቅማቸዋል? ይህን የመሰለው እውቀት በመጀመሪያው መቶ ዘመን ኢየሩሳሌም የነበራትን የቦታ አቀማመጥ በበለጠ ለመረዳት ያስችላቸዋል። ይህም ስለ ኢየሱስ ሕይወትና አገልግሎት የሚናገሩት የወንጌል ዘገባዎች በተደጋጋሚ የሚጠቅሷቸው ቦታዎች የት እንደሚገኙ ለማወቅ ይረዳቸዋል።

[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በቅርቡ በመሬት ቁፋሮ የተገኘው የሰሊሆም መጠመቂያ

[ምንጭ]

© 2003 BiblePlaces.com