በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በመንፈስ ቅዱስ ላይ ኃጢአት ሠርተሃል?

በመንፈስ ቅዱስ ላይ ኃጢአት ሠርተሃል?

በመንፈስ ቅዱስ ላይ ኃጢአት ሠርተሃል?

‘ለሞት የሚያበቃ ኀጢአት አለ።’—1 ዮሐንስ 5:16

1, 2. አንድ ሰው በአምላክ ቅዱስ መንፈስ ላይ ኃጢአት ሊሠራ እንደሚችል እንዴት እናውቃለን?

 በጀርመን አገር የምትኖር አንዲት ሴት የአምላክ አገልጋይ ብትሆንም እንኳ፣ “በመንፈስ ቅዱስ ላይ ኃጢአት ሠርቼ ይሆን እያልኩ ስጨነቅ ኖሬያለሁ” በማለት ጽፋለች። በእርግጥ አንድ ክርስቲያን በአምላክ ቅዱስ መንፈስ ላይ ኃጢአት ሊሠራ ይችላል?

2 አዎን፣ አንድ ሰው በይሖዋ ቅዱስ መንፈስ ላይ ኃጢአት ሊሠራ ይችላል። ኢየሱስ ክርስቶስ እንዲህ ብሏል:- “ኀጢአት መሥራትና የስድብ ቃል ሁሉ መናገር ለሰዎች ይቅር ይባልላቸዋል፤ ነገር ግን በመንፈስ ቅዱስ ላይ የሚነገር የስድብ ቃል ይቅር አይባልም።” (ማቴዎስ 12:31) “የእውነትን ዕውቀት ከተቀበልን በኋላ ሆን ብለን በኀጢአት ጸንተን ብንመላለስ፣ ከእንግዲህ ለኀጢአት የሚሆን ሌላ መሥዋዕት አይኖርም፤ የሚቀረው ግን የሚያስፈራ ፍርድ . . . ብቻ ነው” የሚል ማስጠንቀቂያም ተሰጥቶናል። (ዕብራውያን 10:26, 27) ከዚህም በተጨማሪ ሐዋርያው ዮሐንስ ‘ለሞት የሚያበቃ ኀጢአት አለ’ ሲል ጽፏል። (1 ዮሐንስ 5:16) ይሁንና ከባድ ኃጢአት የፈጸመ አንድ ሰው፣ ‘ለሞት የሚያበቃ ኀጢአት’ ሠርቻለሁ ወይም አልሠራሁም ብሎ ራሱ መወሰን ይችላል?

ንስሐ መግባት ይቅርታ ያስገኛል

3. በፈጸምነው ኃጢአት ከልብ ማዘናችን ምን የሚያሳይ ሊሆን ይችላል?

3 ኃጢአት በሠሩ ሰዎች ላይ የመጨረሻውን ዳኝነት የሚሰጠው ይሖዋ ነው። በእርግጥም ሁላችንም ለአምላክ መልስ እንሰጣለን፤ እሱም ሁልጊዜ ትክክል የሆነውን ያደርጋል። (ዘፍጥረት 18:25፤ ሮሜ 14:12) ይቅር የማይባል ኃጢአት መሥራት አለመሥራታችንን የሚወስነውም ሆነ መንፈሱን ሊወስድብን የሚችለው ይሖዋ ብቻ ነው። (መዝሙር 51:11) ሆኖም በፈጸምነው ኃጢአት ከልብ ካዘንን፣ ይህ እውነተኛ ንስሐ መግባታችንን የሚያሳይ ሊሆን ይችላል። እውነተኛ ንስሐ ሲባል ምን ማለት ነው?

4. (ሀ) ንስሐ መግባት ሲባል ምን ማለት ነው? (ለ) መዝሙራዊው በመዝሙር 103:10-14 ላይ የተናገረው ሐሳብ እጅግ የሚያጽናና የሆነው እንዴት ነው?

4 ንስሐ መግባት ሲባል ከዚህ ቀደም ስለሠራነው ወይም ልንሠራው ስላሰብነው ኃጢአት ያለንን አመለካከት መለወጥ ማለት ነው። በሌላ አባባል፣ ባደረግነው ነገር ከልብ አዝነን ወይም ተጸጽተን ከኃጢአት ጎዳና መመለስ ማለት ነው። ከባድ ኃጢአት የፈጸምን ብንሆንም እውነተኛ ንስሐ መግባታችንን ለማሳየት አስፈላጊ እርምጃዎችን ከወሰድን መዝሙራዊው እንዲህ ሲል የተናገረው ሐሳብ ያጽናናናል:- “[ይሖዋ] እንደ ኀጢአታችን አልመለሰልንም፤ እንደ በደላችንም አልከፈለንም። ሰማይ ከምድር ከፍ እንደሚል፣ እንዲሁ ለሚፈሩት ምሕረቱ ታላቅ ናት። ምሥራቅ ከምዕራብ እንደሚርቅ፣ መተላለፋችንን በዚያው መጠን ከእኛ አስወገደ። አባት ለልጆቹ እንደሚራራ፣ እግዚአብሔር ለሚፈሩት እንዲሁ ይራራል። እርሱ አፈጣጠራችንን ያውቃልና፤ ትቢያ መሆናችንንም ያስባል።”—መዝሙር 103:10-14

5, 6. አንደኛ ዮሐንስ 3:19-22 የያዘው ፍሬ ሐሳብ ምንድን ነው? የሐዋርያው ዮሐንስ ቃላት ምን ትርጉም እንዳላቸው አብራራ።

5 በተጨማሪም ሐዋርያው ዮሐንስ የተናገራቸው የሚከተሉት ቃላት የሚያጽናኑ ናቸው:- “እኛ የእውነት ወገን መሆናችንን በዚህ እናውቃለን፤ ልባችንንም በፊቱ እናሳርፋለን፣ ይህም ልባችን በእኛ ላይ በሚፈርድብን ነገር ሁሉ ነው። እግዚአብሔር ከልባችን ይልቅ ታላቅ ነውና ሁሉን ነገር ያውቃል። ወዳጆች ሆይ፤ ልባችን የማይፈርድብን ከሆነ በእግዚአብሔር ፊት ድፍረት አለን፤ ትእዛዛቱንም ስለምንጠብቅና በፊቱም ደስ የሚያሰኘውን ስለምናደርግ የምንለምነውን ሁሉ ከእርሱ እንቀበላለን።”—1 ዮሐንስ 3:19-22

6 ለወንድሞቻችን ፍቅር ስለምናሳይና ኃጢአት የመሥራት ልማድ ስለሌለን ‘የእውነት ወገን መሆናችንን እናውቃለን።’ (መዝሙር 119:11) በሆነ ምክንያት በጥፋተኝነት ስሜት የምንሠቃይ ከሆነ ‘አምላክ ከልባችን ይልቅ ታላቅ እንደሆነና ሁሉን ነገር እንደሚያውቅ’ ማስታወሳችን የተገባ ነው። ይሖዋ፣ ‘ለወንድሞቻችን ግብዝነት የሌለበት ፍቅር’ እንደምናሳይ፣ ኃጢአት ላለመሥራት ትግል እንደምናደርግና ፈቃዱን ለመፈጸም እንደምንጥር ስለሚገነዘብ ምሕረት ያደርግልናል። (1 ጴጥሮስ 1:22 የ1954 ትርጉም) በይሖዋ ከታመንን፣ ለወንድሞቻችን ፍቅር ካለንና ሆን ብለን ኃጢአት ካልፈጸምን ልባችን ‘አይፈርድብንም።’ እንዲያውም ወደ አምላክ በጸሎት ለመቅረብ የሚያስችል “ድፍረት” የምናገኝ ከመሆኑም ሌላ ትእዛዛቱን ስለምንጠብቅ ለጸሎታችን መልስ ይሰጠናል።

በመንፈስ ቅዱስ ላይ ኃጢአት ሠርተዋል

7. አንድ ኃጢአት ይቅርታ የሚደረግለት ነው ወይስ አይደለም የሚለውን የሚወስነው ምንድን ነው?

7 ይቅርታ የማይደረግላቸው ኃጢአቶች የትኞቹ ናቸው? የዚህን ጥያቄ መልስ ለማግኘት ጥቂት የመጽሐፍ ቅዱስ ምሳሌዎችን እንመልከት። ከባድ ኃጢአት ከሠራን በኋላ ንስሐ የገባን ቢሆንም፣ አሁንም የምንጨነቅ ከሆነ ከእነዚህ ምሳሌዎች ማጽናኛ እንደምናገኝ ጥርጥር የለውም። የአንድ ሰው ኃጢአት ይቅርታ የሚደረግለት ነው ወይስ አይደለም የሚለውን የሚወስነው የሠራው የኃጢአት ዓይነት ሳይሆን ዝንባሌው፣ የልቡ ሁኔታና ኃጢአቱን ለመሥራት ምን ያህል አስተዋጽኦ አድርጓል የሚለው ይሆናል።

8. በመጀመሪያው መቶ ዘመን ይኖሩ የነበሩ አንዳንድ የአይሁድ ሃይማኖታዊ መሪዎች በመንፈስ ቅዱስ ላይ ኃጢአት የሠሩት እንዴት ነው?

8 ኢየሱስን ክፉኛ የተቃወሙት በመጀመሪያው መቶ ዘመን ይኖሩ የነበሩ የአይሁድ ሃይማኖታዊ መሪዎች በመንፈስ ቅዱስ ላይ ኃጢአት ሠርተዋል። ኢየሱስ ይሖዋን የሚያስከብሩ ተዓምራት በፈጸመባቸው ጊዜያት የአምላክ መንፈስ በእሱ ላይ ሲሠራ ተመልክተዋል። ያም ሆኖ እነዚህ የክርስቶስ ጠላቶች፣ ኢየሱስ ኃይሉን ያገኘው ከሰይጣን ዲያብሎስ እንደሆነ አድርገው ተናግረዋል። ኢየሱስ እንደተናገረው፣ የአምላክን ቅዱስ መንፈስ የተሳደቡት እነዚህ ሰዎች “በዚህም ሆነ በወዲያኛው [“በሚመጣው፣” የ1954 ትርጉም] ዓለም” ይቅርታ የማይደረግለት ኃጢአት ሠርተዋል።—ማቴዎስ 12:22-32

9. የስድብ ቃል መናገር ሲባል ምን ማለት ነው? ኢየሱስ ይህን አስመልክቶ ምን ብሏል?

9 የስድብ ቃል መናገር ሲባል ስም ማጥፋት፣ የሚጎዳ ወይም የዘለፋ ንግግር መናገር ማለት ነው። የመንፈስ ቅዱስ ምንጭ አምላክ በመሆኑ በእሱ መንፈስ ላይ ማንኛውንም ዓይነት የስድብ ቃል መናገር ይሖዋን ራሱን ከመሳደብ ተለይቶ አይታይም። አንድ ሰው በይሖዋ ላይ እንደዚህ ዓይነት ንግግር ተናግሮ ንስሐ የማይገባ ከሆነ ይቅርታ አያገኝም። ኢየሱስ ይህን ስለመሰለው ኃጢአት የተናገራቸው ቃላት፣ እየጠቀሰ የነበረው የአምላክን ቅዱስ መንፈስ አሠራር ሆን ብለው ስለሚቃወሙ ሰዎች መሆኑን ያሳያሉ። ተቃዋሚዎቹ የይሖዋ መንፈስ በኢየሱስ ላይ ሲሠራ ቢመለከቱም ይህ ኃይል ከሰይጣን ነው በማለታቸው መንፈስ ቅዱስን ተሳድበዋል። በመሆኑም ኢየሱስ “በመንፈስ ቅዱስ ላይ የስድብ ቃል የሚናገር ሁሉ የዘላለም ኀጢአት ዕዳ ይሆንበታል እንጂ ለዘላለም አይሰረይለትም” በማለት ተናገረ።—ማርቆስ 3:20-29

10. ኢየሱስ ይሁዳን ‘የጥፋት ልጅ’ ሲል የጠራው ለምንድን ነው?

10 በተጨማሪም የአስቆሮቱ ይሁዳን ሁኔታ ተመልከት። ይሁዳ በአደራ ከተሰጠው የገንዘብ ከረጢት ውስጥ በመስረቅ ታማኝነት የጎደለው ድርጊት ይፈጽም ነበር። (ዮሐንስ 12:5, 6) በኋላም ወደ አይሁድ መሪዎች በመሄድ ኢየሱስን በሠላሳ ጥሬ ብር አሳልፎ ለመስጠት ተስማማ። እውነት ነው፣ ይሁዳ ኢየሱስን አሳልፎ ከሰጠው በኋላ የጸጸት ስሜት ተሰምቶታል፤ ሆኖም ሆን ብሎ ከሠራው ኃጢአቱ ፈጽሞ ንስሐ አልገባም። ከዚህም የተነሳ ይሁዳ ትንሣኤ የሚገባው ሰው አልሆነም። ኢየሱስም ‘የጥፋት ልጅ’ በማለት የጠራው ለዚህ ነው።—ዮሐንስ 17:12፤ ማቴዎስ 26:14-16

በመንፈስ ቅዱስ ላይ ኃጢአት አልሠሩም

11-13. ንጉሥ ዳዊት ከቤርሳቤህ ጋር በተያያዘ ኃጢአት የሠራው እንዴት ነው? አምላክ ጉዳዩን ከያዘበት መንገድ ምን ማጽናኛ ማግኘት እንችላለን?

11 አንዳንድ ክርስቲያኖች የሠሩትን ከባድ ኃጢአት ከተናዘዙና ከጉባኤ ሽማግሌዎች መንፈሳዊ እርዳታ ካገኙ በኋላም ቀደም ሲል የሠሩትን ኃጢአት በማሰብ በጭንቀት ሊዋጡ ይችላሉ። (ያዕቆብ 5:14) እኛም እንዲህ የሚሰማን ከሆነ ቅዱሳን መጻሕፍት ኃጢአታቸው ይቅር ስለተባለላቸው ሰዎች የሚናገሩትን ሐሳብ መመርመራችን እንደሚጠቅመን ምንም ጥርጥር የለውም።

12 ንጉሥ ዳዊት ከኦርዮ ሚስት ከቤርሳቤህ ጋር በተያያዘ ከባድ ኃጢአት ሠርቷል። ዳዊት ከሰገነቱ ላይ ሆኖ ይህች ውብ ባለትዳር ሴት ሰውነቷን ስትታጠብ ተመለከታት። ከዚያም ወደ ቤተ መንግሥቱ አስመጥቷት ከእርሷ ጋር ምንዝር ፈጸመ። በኋላም ቤርሳቤህ መጸነሷን ስትነግረው ኃጢአቱን ለመሸፋፈን በማሰብ ባሏ ኦርዮ ከእርሷ ጋር እንዲተኛ ለማድረግ ዘዴ ቀየሰ። ይህ ዘዴ አልሳካ ሲለው ኦርዮ በጦርነት ላይ እንዲገደል ሁኔታዎችን አመቻቸ። ከዚያም ቤርሳቤህ የዳዊት ሚስት ሆነች፤ የተወለደው ልጅ ግን ሞተ።—2 ሳሙኤል 11:1-27

13 ይሖዋ የዳዊትንና የቤርሳቤህን ጉዳይ በተገቢው መንገድ ይዞት ነበር። አምላክ የዳዊትን ንስሐ መግባት፣ ከእሱ ጋር የገባውን የመንግሥት ቃል ኪዳንና ሌሎች ጉዳዮችን ከግምት በማስገባት ዳዊትን ይቅር ብሎታል። (2 ሳሙኤል 7:11-16፤ 12:7-14) ቤርሳቤህ የንጉሥ ሰሎሞን እናትና የኢየሱስ ክርስቶስ ቅድመ አያት የመሆን መብት ማግኘቷ የንስሐ ዝንባሌ እንደነበራት ያሳያል። (ማቴዎስ 1:1, 6, 16) ኃጢአት ሠርተን ከሆነ ይሖዋ የምናሳየውን የንስሐ ዝንባሌ በቁም ነገር የሚመለከት መሆኑን ማስታወሳችን ጥሩ ነው።

14. የንጉሥ ምናሴ ታሪክ አምላክ ምን ያህል ይቅር ባይ እንደሆነ የሚያሳየው እንዴት ነው?

14 ከዚህም በተጨማሪ የይሁዳ ንጉሥ የነበረው የምናሴ ታሪክ ይሖዋ ምን ያህል ይቅር ባይ መሆኑን ያሳያል። ምናሴ በይሖዋ ፊት ክፉ የሆነ ድርጊት ፈጽሟል። ለበኣል መሠዊያዎችን ከመሥራቱም ባሻገር ‘የሰማይ ከዋክብት ሰራዊትን’ አምልኳል። ሌላው ቀርቶ በቤተ መቅደሱ ሁለት አደባባዮች ላይ ለሐሰት አማልክት መሠዊያዎችን አቁሟል። ምናሴ ወንዶች ልጆቹን ለእሳት አሳልፎ ሰጥቷል፤ እንዲሁም መናፍስታዊ ድርጊቶችን አስፋፍቷል። በተጨማሪም የይሁዳና የኢየሩሳሌም ነዋሪዎች ይሖዋ “በእስራኤላውያን ፊት ካጠፋቸው አሕዛብ የባሰ ክፉ ድርጊት” እንዲፈጽሙ አድርጓል። በወቅቱ የአምላክ ነቢያት የተናገሯቸው ማስጠንቀቂያዎች ሰሚ ጆሮ አላገኙም። ከጊዜ በኋላ የአሦር ንጉሥ ምናሴን ምርኮኛ አድርጎ ወሰደው። ምናሴ በግዞት ሳለ ንስሐ የገባ ሲሆን ራሱን እጅግ በማዋረድ ወደ አምላክ ደጋግሞ ጸለየ። አምላክም ይቅር በማለት በኢየሩሳሌም ወደሚገኘው ዙፋኑ መለሰው። ከዚያም ምናሴ እውነተኛውን አምልኮ ማስፋፋት ጀመረ።—2 ዜና መዋዕል 33:2-17

15. የይሖዋ ምሕረት ታላቅ መሆኑን የሚያሳየው በሐዋርያው ጴጥሮስ ሕይወት ውስጥ የተከሰተው የትኛው ሁኔታ ነው?

15 ከብዙ መቶ ዘመናት በኋላ ሐዋርያው ጴጥሮስ ኢየሱስን በመካድ ከባድ ኃጢአት ሠራ። (ማርቆስ 14:30, 66-72) ሆኖም ይሖዋ ለጴጥሮስ ታላቅ ምሕረት አደረገለት። (ኢሳይያስ 55:7) ለምን? ምክንያቱም ጴጥሮስ እውነተኛ ንስሐ ገብቷል። (ሉቃስ 22:62) ይህ ከሆነ ከ50 ቀናት በኋላ ማለትም በጴንጠቆስጤ ዕለት፣ ጴጥሮስ ስለ ኢየሱስ በድፍረት የመመሥከር መብት ማግኘቱ አምላክ ይቅር እንዳለው በግልጽ የሚያሳይ ማስረጃ ነው። (የሐዋርያት ሥራ 2:14-36) በዛሬው ጊዜም ይሖዋ እውነተኛ ንስሐ የገቡ ክርስቲያኖችን ይቅር እንደሚላቸው ለማመን የሚያስችል በቂ ምክንያት አለን። መዝሙራዊው “እግዚአብሔር ሆይ፤ ኀጢአትን ብትቈጣጠር፣ ጌታ ሆይ፤ ማን ሊቆም ይችላል? ነገር ግን በአንተ ዘንድ ይቅርታ አለ” ሲል ዘምሯል።—መዝሙር 130:3, 4

‘በመንፈስ ቅዱስ ላይ ኃጢአት ሠርቼ ይሆን’ ከሚለው ጭንቀት መገላገል

16. አምላክ ይቅር የሚለው ምን ነገሮችን መሠረት በማድረግ ነው?

16 ከላይ የተጠቀሱት ምሳሌዎች ‘በመንፈስ ቅዱስ ላይ ኃጢአት ሠርቼ ይሆን’ ከሚለው ጭንቀት ለመላቀቅ እንደሚረዱን አያጠራጥርም። እነዚህ ምሳሌዎች ይሖዋ ንስሐ የገቡ ኃጢአተኞችን ይቅር እንደሚል ያሳያሉ። ዋናው አስፈላጊ ነገር ወደ አምላክ ልባዊ ጸሎት ማቅረብ ነው። ኃጢአት ሠርተን ከሆነ የኢየሱስን ቤዛዊ መሥዋዕት፣ የይሖዋን ምሕረት፣ የወረስነውን አለፍጽምናና ከዚህ ቀደም ያከናወንነውን የታማኝነት አገልግሎት መሠረት አድርገን ይቅርታ ለማግኘት ልባዊ ጸሎት ማቅረብ እንችላለን። ይገባናል የማንለውን የይሖዋን ደግነት ከተረዳን ምሕረቱን እንደምናገኝ በመተማመን ይቅርታ ልንጠይቅ እንችላለን።—ኤፌሶን 1:7 NW

17. ኃጢአት ብንሠራና መንፈሳዊ እርዳታ ቢያስፈልገን ምን ማድረግ ይኖርብናል?

17 ኃጢአት መሥራታችን በመንፈሳዊ እንድንታመም ስላደረገን መጸለይ ቢያቅተንስ? ደቀ መዝሙሩ ያዕቆብ ይህን ጉዳይ አስመልክቶ እንዲህ ሲል ጽፏል:- “[እንዲህ ዓይነቱ ሰው] የቤተ ክርስቲያን ሽማግሌዎችን ይጥራ፤ እነርሱም በጌታ ስም ዘይት ቀብተው ይጸልዩለት። በእምነት የቀረበ ጸሎት የታመመውን ሰው ይፈውሰዋል፤ ጌታም ያስነሣዋል፤ ኀጢአትም ሠርቶ ከሆነ፣ ይቅር ይባላል።”—ያዕቆብ 5:14, 15

18. አንድ ሰው ከጉባኤ ቢወገድም እንኳ ይቅርታ የማይደረግለት ኃጢአት ሠርቷል ሊባል የማይችለው ለምንድን ነው?

18 ኃጢአት የሠራ አንድ ሰው ንስሐ ባይገባና ከጉባኤ ቢወገድ እንኳ ይቅርታ የማይደረግለት ኃጢአት ሠርቷል ሊባል አይችልም። ኃጢአት በመሥራቱ ምክንያት ከቆሮንቶስ ጉባኤ ተወግዶ ስለነበረ አንድ የተቀባ ክርስቲያን ጳውሎስ እንዲህ ሲል ጽፏል:- “እንደዚህ ያለው ሰው ብዙዎች የወሰኑበት ቅጣት በቂው ነው። ደግሞም ከልክ በላይ አዝኖ ተስፋ እንዳይቈርጥ፣ ይቅር ልትሉትና ልታጽናኑት ይገባችኋል።” (2 ቆሮንቶስ 2:6-8፤ 1 ቆሮንቶስ 5:1-5) ኃጢአት የሠሩ ሰዎች ከይሖዋ ጋር ያላቸውን ዝምድና ለማደስ እንዲችሉ ክርስቲያን ሽማግሌዎች የሚሰጧቸውን በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ መንፈሳዊ እርዳታ መቀበልና እውነተኛ ንስሐ መግባታቸውን ማሳየት ያስፈልጋቸዋል። ‘ለንስሓ የሚገባ ፍሬ ማፍራት’ አለባቸው።—ሉቃስ 3:8

19. ‘በእምነት ጤናማ’ ሆነን ለመኖር ምን ሊረዳን ይችላል?

19 በመንፈስ ቅዱስ ላይ ኃጢአት ሠርተናል ብለን እንድናስብ የሚያደርገን ምን ሊሆን ይችላል? ለምን ተሳሳትኩ በሚል ከልክ በላይ መጨነቅ እንዲሁም የአካልና የአእምሮ ጤንነት ችግር አስተዋጽኦ ሊያደርጉ ይችላሉ። በዚህ ጊዜ ጸሎትና በቂ እረፍት ማድረግ ሊረዳ ይችላል። በተለይ ደግሞ ሰይጣን ተስፋ አስቆርጦን አምላክን ከማገልገል እንዲያስቆመን መፍቀድ የለብንም። ይሖዋ በክፉዎች ሞት የሚያዝን ከሆነ ከአገልጋዮቹ መካከል አንዳቸውም ቢሆኑ እንዲጠፉ እንደማይፈልግ እሙን ነው። በመሆኑም በመንፈስ ቅዱስ ላይ ኃጢአት ሠርቼ ይሆናል በማለት የምንጨነቅ ከሆነ አጽናኝ የሆኑትን መዝሙራት ጨምሮ የአምላክን ቃል መመገባችንን መቀጠል አለብን። በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ አዘውትረን መገኘታችንና በመንግሥቱ የስብከት ሥራ ሳናቋርጥ መካፈላችን አስፈላጊ ነው። እንዲህ ማድረጋችን ‘በእምነት ጤናማ’ እንድንሆንና ይቅርታ የማይደረግለት ኃጢአት ሠርቻለሁ ከሚለው ጭንቀት እንድንገላገል ይረዳናል።—ቲቶ 2:2

20. አንድ ሰው በመንፈስ ቅዱስ ላይ ኃጢአት አለመሥራቱን እንዲገነዘብ ራሱን ምን ብሎ መጠየቁ ሊረዳው ይችላል?

20 በመንፈስ ቅዱስ ላይ ኃጢአት ሠርቻለሁ ብለው የሚያስቡ ሰዎች እንዲህ እያሉ ራሳቸውን መጠየቅ ይችላሉ:- ‘መንፈስ ቅዱስን ተሳድቤያለሁ? እውነተኛ ንስሐ ገብቻለሁ? አምላክ ይቅርታ እንደሚያደርግልኝ እምነት አለኝ? መንፈሳዊውን ብርሃን የምቃወም ከሃዲ ነኝ?’ በአምላክ መንፈስ ላይ ኃጢአት ሠርቼ ይሆናል እያሉ የሚጨነቁ አብዛኞቹ ሰዎች መንፈስ ቅዱስን አለመስደባቸውንም ሆነ ከሃዲ አለመሆናቸውን መገንዘባቸው አይቀርም። እነዚህ ሰዎች ንስሐ ገብተዋል፤ እንዲሁም ይሖዋ ይቅር ባይ ስለመሆኑ ጽኑ እምነት አላቸው። በመሆኑም በይሖዋ ቅዱስ መንፈስ ላይ ኃጢአት አልሠሩም።

21. በሚቀጥለው ርዕስ ውስጥ የትኞቹን ጥያቄዎች እንመረምራለን?

21 በመንፈስ ቅዱስ ላይ ኃጢአት እንዳልሠራን ማወቃችን ታላቅ እፎይታ ያስገኝልናል! ሆኖም ከመንፈስ ቅዱስ ጋር በተያያዘ በሚቀጥለው ርዕስ ሥር የምንመረምራቸው ሌሎች ጥያቄዎችም ይኖራሉ። ለምሳሌ ያህል፣ ራሳችንን እንዲህ እያልን ልንጠይቅ እንችላለን:- ‘በእርግጥ በአምላክ ቅዱስ መንፈስ እየተመራሁ ነው? የመንፈስ ቅዱስ ፍሬ በሕይወቴ ውስጥ በግልጽ ይታያል?’

ምን ብለህ ትመልሳለህ?

• አንድ ሰው በአምላክ ቅዱስ መንፈስ ላይ ኃጢአት ሊሠራ ይችላል የምንለው ለምንድን ነው?

• ንስሐ መግባት ሲባል ምን ማለት ነው?

• ኢየሱስ ምድር ላይ በነበረበት ጊዜ በመንፈስ ቅዱስ ላይ ኃጢአት የሠሩት እነማን ናቸው?

• ይቅርታ የማይደረግለት ኃጢአት ሠርቻለሁ የሚለውን ጭንቀት መቋቋም የምንችለው እንዴት ነው?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ኢየሱስ ተዓምራት ያደረገው በሰይጣን ኃይል ነው ብለው የተናገሩት ሰዎች በአምላክ ቅዱስ መንፈስ ላይ ኃጢአት ሠርተዋል

[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ጴጥሮስ ኢየሱስን ቢክደውም ይቅርታ የማይደረግለት ኃጢአት አልፈጸመም