በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

‘በመንፈስ እየኖርክ’ ነው?

‘በመንፈስ እየኖርክ’ ነው?

‘በመንፈስ እየኖርክ’ ነው?

“በመንፈስ ኑሩ . . . የሥጋንም ምኞት አትፈጽሙም።”—ገላትያ 5:16

1. በመንፈስ ቅዱስ ላይ ኃጢአት እሠራ ይሆናል ከሚለው ስጋት መላቀቅ የምንችለው እንዴት ነው?

 በይሖዋ ቅዱስ መንፈስ ላይ ኃጢአት እሠራ ይሆናል ከሚለው ስጋት መላቀቅ የምንችልበት መንገድ አለ። ይኸውም ሐዋርያው ጳውሎስ “በመንፈስ ኑሩ . . . የሥጋንም ምኞት አትፈጽሙም” ሲል የሰጠውን ምክር በተግባር በማዋል ነው። (ገላትያ 5:16) የአምላክ መንፈስ እንዲመራን የምንፈቅድ ከሆነ ተገቢ ባልሆኑ የሥጋ ምኞቶች አንሸነፍም።—ሮሜ 8:2-10

2, 3. በመንፈስ መኖራችን ሕይወታችንን የሚነካው እንዴት ነው?

2 ‘በመንፈስ የምንኖር’ ከሆነ የአምላክ ኃይል ይሖዋን እንድንታዘዘው ያነሳሳናል። በአገልግሎት፣ በጉባኤ፣ በቤታችንና በማንኛውም ቦታ አምላካዊ ባሕርያትን እናንጸባርቃለን። ከትዳር ጓደኛችን፣ ከልጆቻችን፣ ከክርስቲያን ባልንጀሮቻችንና ከሌሎች ጋር ባለን ግንኙነት የመንፈስ ፍሬ እንዳፈራን በግልጽ ይታያል።

3 ‘እንደ አምላክ ፈቃድ በመንፈስ መኖራችን’ ከኃጢአት እንድንርቅ ይረዳናል። (1 ጴጥሮስ 4:1-6) በመንፈስ ቅዱስ የምንመራ ከሆነ ይቅርታ የማይደረግለት ኃጢአት አንፈጽምም። ሆኖም በመንፈስ መመላለሳችን በየትኞቹ ሌሎች የሕይወታችን ዘርፎች ላይ በጎ ተጽዕኖ ይኖረዋል?

ከአምላክና ከክርስቶስ ጋር ያለህን ዝምድና ጠብቀህ ኑር

4, 5. በመንፈስ መመላለሳችን ስለ ኢየሱስ ባለን አመለካከት ላይ ለውጥ የሚያመጣው እንዴት ነው?

4 በመንፈስ ቅዱስ የምንመራ በመሆናችን ከአምላክና ከልጁ ጋር ያለንን የቅርብ ዝምድና ጠብቀን መኖር ችለናል። ጳውሎስ ቀደም ሲል ጣዖት አምላኪ ለነበሩትና በኋላ ላይ ግን ተለውጠው የእምነት ባልንጀሮቹ ለሆኑት በቆሮንቶስ ለሚገኙ ክርስቲያኖች ስለ መንፈስ ቅዱስ ስጦታ ሲጽፍላቸው እንዲህ ብሏል:- “ማንም በእግዚአብሔር መንፈስ የሚናገር፣ ‘ኢየሱስ የተረገመ ነው’ የሚል የለም፤ እንደዚሁም በመንፈስ ቅዱስ ካልሆነ በቀር፣ ማንም ‘ኢየሱስ ጌታ ነው’ የሚል እንደሌለ እነግራችኋለሁ።” (1 ቆሮንቶስ 12:1-3) ሰዎች ኢየሱስን እንዲሰድቡ የሚያነሳሳ ማንኛውም መንፈስ ከሰይጣን ዲያብሎስ የመነጨ መሆን አለበት። እኛ ግን በመንፈስ ቅዱስ የምንመላለስ ክርስቲያኖች እንደመሆናችን መጠን ይሖዋ ኢየሱስን ከሞት እንዳስነሳውና ከፍጥረታት ሁሉ የበላይ እንዳደረገው እናምናለን። (ፊልጵስዩስ 2:5-11) በክርስቶስ ቤዛዊ መሥዋዕት የምናምን ከመሆኑም ሌላ ኢየሱስ በአምላክ የተሾመ ጌታችን መሆኑን እንቀበላለን።

5 በመጀመሪያው መቶ ዘመን ይኖሩ የነበሩ ክርስቲያን ነን የሚሉ አንዳንድ ሰዎች ክርስቶስ በሥጋ መምጣቱን ይክዱ ነበር። (2 ዮሐንስ 7-11) አንዳንዶች ይህን የተሳሳተ አመለካከት በመቀበላቸው መሲሕ ስለሆነው ስለ ኢየሱስ የሚናገሩትን ትክክለኛ ትምህርቶች ሳያምኑባቸው ቀርተዋል። (ማርቆስ 1:9-11፤ ዮሐንስ 1:1, 14) በመንፈስ መመላለሳችን እንዲህ በመሰለው የክህደት ትምህርት ከመወሰድ ይጠብቀናል። ይገባናል የማንለውን የይሖዋን ደግነት ማግኘትና ‘በእውነት መመላለሳችንን’ መቀጠል የምንችለው በመንፈሳዊ ንቁ ሆነን ስንኖር ብቻ ነው። (3 ዮሐንስ 3, 4) በመሆኑም ማንኛውንም ዓይነት የክህደት አስተሳሰብ ለመቃወም ቁርጥ ውሳኔ እናድርግ። ይህን ካደረግን በሰማይ ከሚኖረው አባታችን ጋር የመሠረትነውን ጠንካራ ዝምድና ጠብቀን መኖር እንችላለን።

6. የአምላክ ኃይል በመንፈስ የሚመላለሱ ሰዎች ምን ዓይነት ፍሬ እንዲያፈሩ ይረዳቸዋል?

6 ጳውሎስ፣ በክህደት ጣዖት ማምለክንም ሆነ አድመኝነትን እንደ ዝሙትና መዳራት ካሉ ‘የሥጋ ሥራዎች’ ጋር ፈርጇቸዋል። ይሁንና “የክርስቶስ ኢየሱስ የሆኑት ሥጋን ከክፉ ምኞቱና መሻቱ ጋር ሰቅለውታል” በማለት ገልጿል። አክሎም “በመንፈስ የምንኖር ከሆን፣ በመንፈስ እንመላለስ” ብሏል። (ገላትያ 5:19-21, 24, 25) የአምላክ ኃይል በመንፈስ የሚኖሩና የሚመላለሱ ሰዎች ምን ዓይነት ፍሬ እንዲያፈሩ ይረዳቸዋል? ጳውሎስ “የመንፈስ ፍሬ ፍቅር፣ ደስታ፣ ሰላም፣ ትዕግሥት፣ ደግነት፣ ጥሩነት፣ እምነት፣ ገርነት፣ ራስን መግዛት ነው” ሲል ጽፏል። (ገላትያ 5:22, 23 NW) እስቲ እነዚህን የመንፈስ ፍሬ የተለያዩ ገጽታዎች እንመርምር።

‘እርስ በርሳችን እንዋደድ’

7. ፍቅር ምንድን ነው? ፍቅር የሚገለጽባቸው አንዳንድ መንገዶችስ ምንድን ናቸው?

7 ፍቅር ከመንፈስ ፍሬ ገጽታዎች አንዱ ሲሆን ብዙውን ጊዜ ጥልቅ የመውደድ ስሜትን፣ ለሌሎች ከራስ ወዳድነት ነፃ የሆነ አሳቢነት ማሳየትንና ከእነሱ ጋር ጥብቅ ዝምድና መመሥረትን ያመለክታል። አምላክ የፍቅር ተምሳሌት በመሆኑ መጽሐፍ ቅዱስ ‘አምላክ ፍቅር ነው’ ሲል ይናገራል። የኢየሱስ ክርስቶስ ቤዛዊ መሥዋዕት አምላክና ልጁ ለሰው ዘር ያላቸውን ታላቅ ፍቅር ያሳያል። (1 ዮሐንስ 4:8፤ ዮሐንስ 3:16፤ 15:13፤ ሮሜ 5:8) የኢየሱስ ተከታዮች መሆናችን ተለይቶ የሚታወቀው እርስ በርሳችን ባለን ፍቅር ነው። (ዮሐንስ 13:34, 35) እንዲያውም “እርስ በርሳችን እንድንዋደድ” ታዝዘናል። (1 ዮሐንስ 3:23) ጳውሎስም ፍቅር ታጋሽና ቸር መሆኑን ተናግሯል። ከዚህም በተጨማሪ ፍቅር አይመቀኝም፣ አይመካም፣ ተገቢ ያልሆነ ነገር አያደርግም ወይም ራስ ወዳድ አይደለም። ፍቅር አይበሳጭም ወይም በደልን አይቆጥርም። ፍቅር ከእውነት ጋር እንጂ በዓመጽ ደስ አይሰኝም። ፍቅር ሁሉን ይታገሣል፣ ሁሉን ያምናል፣ ሁሉን ተስፋ ያደርጋል እንዲሁም ሁልጊዜ ጸንቶ ይኖራል። ከዚህም በላይ ፍቅር ከቶ አይወድቅም።—1 ቆሮንቶስ 13:4-8

8. ለእምነት ባልንጀሮቻችን ፍቅር ማሳየት የሚገባን ለምንድን ነው?

8 የአምላክ መንፈስ በውስጣችን የፍቅርን ፍሬ እንዲያፈራ የምንፈቅድ ከሆነ ይህ ባሕርይ ከአምላክና ከሰዎች ጋር በሚኖረን ግንኙነት ላይ ይንጸባረቃል። (ማቴዎስ 22:37-39) ሐዋርያው ዮሐንስ እንዲህ ሲል ጽፏል:- “ፍቅር የሌለው ሁሉ በሞት ይኖራል። ወንድሙን የሚጠላ ነፍሰ ገዳይ ነው፤ ነፍሰ ገዳይም የዘላለም ሕይወት እንደሌለው ታውቃላችሁ።” (1 ዮሐንስ 3:14, 15) አንድ ነፍሰ ገዳይ በእስራኤል በሚገኙት የመማጸኛ ከተሞች ውስጥ መሸሸግ የሚችለው ሟቹን በጥላቻ ተነሳስቶ እስካልገደለው ድረስ ብቻ ነው። (ዘዳግም 19:4, 11-13) በመንፈስ ቅዱስ የምንመራ ከሆነ ለአምላክ፣ ለእምነት ባልንጀሮቻችንና ለሌሎች ሰዎች ፍቅር እናሳያለን።

የይሖዋ ‘ደስታ ብርታታችሁ ነው’

9, 10. ደስታ ምንድን ነው? ደስተኛ እንድንሆን የሚያደርጉን አንዳንድ ምክንያቶች ምንድን ናቸው?

9 ደስታ ከልብ የመነጨ የእርካታ ስሜት ነው። ይሖዋ “ደስተኛ አምላክ” ነው። (1 ጢሞቴዎስ 1:11 NW፤ መዝሙር 104:31) ኢየሱስም የአባቱን ፈቃድ መፈጸም ያስደስተዋል። (መዝሙር 40:8፤ ዕብራውያን 10:7-9) የይሖዋ ‘ደስታ ለእኛም ብርታታችን ነው።’—ነህምያ 8:10

10 ከአምላክ የሚገኘው ደስታ በመከራ፣ በሐዘንና በስደት ውስጥ በምንሆንበት ጊዜም እንኳ መለኮታዊውን ፈቃድ በመፈጸም ጥልቅ እርካታ እንድናገኝ ያስችለናል። ‘የአምላክን እውቀት’ ማግኘት እጅግ ታላቅ ደስታ ያስገኝልናል! (ምሳሌ 2:1-5) ከአምላክ ጋር ያለን አስደሳች ዝምድና የተመሠረተው በእሱም ሆነ በኢየሱስ ቤዛዊ መሥዋዕት ላይ ባለን እምነትና ስለ እነሱ ባገኘነው ትክክለኛ እውቀት ላይ ነው። (1 ዮሐንስ 2:1, 2) የዓለም አቀፉ እውነተኛ የወንድማማች ኅብረት አባል መሆን ሌላው የደስታችን ምንጭ ነው። (ሶፎንያስ 3:9፤ ሐጌ 2:7) የመንግሥቱ ተስፋና ምሥራቹን እንድናውጅ የተሰጠን ታላቅ መብት ለደስታችን ምክንያት ይሆኑናል። (ማቴዎስ 6:9, 10፤ 24:14) የዘላለም ሕይወት ተስፋ ያለን መሆኑም ደስተኞች እንድንሆን ያደርገናል። (ዮሐንስ 17:3) እንዲህ የመሰለ ድንቅ ተስፋ ስላለን ‘ፍጹም ደስተኞች መሆን’ ይገባናል።—ዘዳግም 16:15

ሰላማዊና ታጋሽ ሁን

11, 12. (ሀ) ሰላም ሲባል ምን ማለት ነው? (ለ) ከአምላክ የሚገኘው ሰላም በእኛ ላይ ምን በጎ ተጽዕኖ ይኖረዋል?

11 ሌላው የመንፈስ ፍሬ ገጽታ ሰላም ነው። ሰላም የመረጋጋት መንፈስ መያዝንና ከመረበሽ ስሜት ነፃ መሆንን ያመለክታል። በሰማይ የሚኖረው አባታችን የሰላም አምላክ ነው፤ መጽሐፍ ቅዱስም ይሖዋ “ሕዝቡን በሰላም ይባርካል” የሚል ማረጋገጫ ይሰጠናል። (መዝሙር 29:11፤ 1 ቆሮንቶስ 14:33) ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ “ሰላምን እተውላችኋለሁ፤ ሰላሜን እሰጣችኋለሁ” ብሏቸዋል። (ዮሐንስ 14:27) የኢየሱስ ተከታዮች ይህን ሰላም ማግኘታቸው የሚጠቅማቸው እንዴት ነው?

12 ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ የሰጣቸው ሰላም ልባቸውንና አሳባቸውን ያረጋጋላቸው ሲሆን ፍርሃታቸውንም ቀንሶላቸዋል። በተለይም ደግሞ ቃል የተገባላቸውን መንፈስ ቅዱስን በተቀበሉ ጊዜ ይህን ሰላም አግኝተዋል። (ዮሐንስ 14:26) በዛሬው ጊዜም፣ በመንፈስ ቅዱስ ስንመራና ለጸሎታችን መልስ ስናገኝ ልባችንንና አሳባችንን የሚያረጋጋልንን ተወዳዳሪ የሌለውን ‘የአምላክ ሰላም’ እናገኛለን። (ፊልጵስዩስ 4:6, 7) ከዚህም በተጨማሪ የይሖዋ መንፈስ ከእምነት አጋሮቻችንና ከሌሎች ሰዎች ጋር በተረጋጋ መንፈስና በሰላም እንድንኖር ይረዳናል።—ሮሜ 12:18፤ 1 ተሰሎንቄ 5:13

13, 14. ትዕግሥት ምንድን ነው? ይህን ባሕርይ ማሳየት የሚገባንስ ለምንድን ነው?

13 ትዕግሥት ሰላማዊ ከመሆን ጋር ይዛመዳል። አንድ ዓይነት በደል ወይም ችግር ሲደርስብን ሁኔታዎች ይስተካከሉ ይሆናል ብለን በተስፋ እንድንጠብቅ የሚያደርገን በጽናት መታገሣችን ነው። አምላክ ታጋሽ ነው። (ሮሜ 9:22-24) ኢየሱስም ቢሆን ይህን ባሕርይ አንጸባርቋል። ጳውሎስ እንደሚከተለው ሲል መጻፉ ኢየሱስ ካሳየው ትዕግሥት ተጠቃሚዎች መሆን እንደምንችል ያሳያል:- “ክርስቶስ ኢየሱስ በእርሱ ለሚያምኑና የዘላለምን ሕይወት ለሚቀበሉ ወሰን የሌለው ትዕግሥቱን ከኀጢአተኞች ዋና በሆንሁት በእኔ እንደ ምሳሌ አድርጎ ያሳይ ዘንድ ምሕረትን አገኘሁ።”—1 ጢሞቴዎስ 1:16

14 ታጋሽ መሆን ሌሎች ሰዎች ደግነት ወይም አሳቢነት የጎደለው ነገር ሲናገሩን አሊያም ሲፈጽሙብን እንድንጸና ይረዳናል። ጳውሎስ ክርስቲያን ባልንጀሮቹን “ሰውን ሁሉ ታገሡ” ሲል መክሯቸዋል። (1 ተሰሎንቄ 5:14) ሁላችንም ፍጽምና የጎደለን በመሆናችን እንሳሳታለን። በመሆኑም ሰዎች ስህተት በምንሠራበት ጊዜ በትዕግሥት እንዲያልፉን እንፈልጋለን። እንግዲያው እኛም ሌሎችን ‘በደስታ ለመታገሥ’ መጣር ይኖርብናል።—ቈላስይስ 1:9-12

ደግነትንና ጥሩነትን አሳይ

15. ደግነት ምንድን ነው? ደግነት በማሳየት ረገድ አርዓያ የሚሆኑን እነማን ናቸው?

15 ለሌሎች ወዳጃዊና አጽናኝ ቃላትን በመናገር እንዲሁም በጎ ነገር በማድረግ እንደምናስብላቸው ስንገልጽ ደግነት እያሳየን ነው። ይሖዋም ሆነ ልጁ ቸርነት ወይም ደግነት ያሳያሉ። (ሮሜ 2:4፤ 2 ቆሮንቶስ 10:1) የአምላክና የክርስቶስ አገልጋዮች ሁሉ የደግነት ባሕርይ እንዲያንጸባርቁ ይጠበቅባቸዋል። (ሚክያስ 6:8 NW፤ ቈላስይስ 3:12 NW) ከአምላክ ጋር ወዳጅነት ያልመሠረቱ አንዳንድ ሰዎች እንኳ ‘የሚያስገርም ደግነት’ ያሳያሉ። (የሐዋርያት ሥራ 27:3፤ 28:2) በመሆኑም ‘በመንፈስ የምንኖር’ ከሆነ ደግነት ማሳየት እንደምንችል ጥርጥር የለውም።

16. ደግነት እንድናሳይ የሚያነሳሱን አንዳንድ ሁኔታዎች የትኞቹ ናቸው?

16 አንድ ሰው ጎጂ ቃላት በመናገሩ ወይም አሳቢነት የጎደለው ድርጊት በመፈጸሙ ለመቆጣት በቂ ምክንያት በሚኖረን ጊዜም እንኳ ደግነት ማሳየት እንችላለን። ጳውሎስ እንዲህ ብሏል:- “ተቈጡ፤ ነገር ግን ኀጢአት አትሥሩ፤ በቊጣችሁ ላይ ፀሓይ አይግባ፤ ለዲያብሎስም ስፍራ አትስጡት። እግዚአብሔር በክርስቶስ ይቅር እንዳላችሁ፣ እናንተም ይቅር ተባባሉ፤ እርስ በርሳችሁ ቸሮችና [“ደጎችና፣” የ1980 ትርጉም] ርኅሩኆች ሁኑ።” (ኤፌሶን 4:26, 27, 32) በተለይ ደግሞ በመከራ ውስጥ ላሉ ሰዎች ደግነት ማሳየታችን ተገቢ ነው። እርግጥ ነው፣ አንድ የጉባኤ ሽማግሌ አንድ ሰው ‘የበጎነት፣ የጽድቅና የእውነትን’ ጎዳና የመተው አደገኛ አዝማሚያ ሲያሳይ ስሜቱን ላለመጉዳት በማሰብ ቅዱስ ጽሑፋዊ ምክር ከመስጠት ወደኋላ ቢል ደግነት አሳይቷል ሊባል አይችልም።—ኤፌሶን 5:9

17, 18. ጥሩነት ምን ፍቺ አለው? ይህ ባሕርይ በሕይወታችን ውስጥ ምን ሚና ሊኖረው ይገባል?

17 ጥሩነት ሲባል በጎነትን፣ የላቀ የሥነ ምግባር ደረጃን ወይም መልካም መሆንን ያመለክታል። አምላክ በጥሩነቱ አቻ የለውም። (መዝሙር 25:8 NW፤ ዘካርያስ 9:17 NW) ኢየሱስ በጎ የሆነውን ብቻ የሚያደርግ ሲሆን በሥነ ምግባርም እንከን አይገኝበትም። ያም ሆኖ ኢየሱስ “ቸር [“ጥሩ፣” NW] መምህር” ተብሎ በተጠራ ጊዜ በዚህ ማዕረግ ለመጠራት ፈቃደኛ አልነበረም። (ማርቆስ 10:17, 18) ይህን ያደረገው በጥሩነቱ ተወዳዳሪ የሌለው አምላክ ብቻ መሆኑን በመገንዘቡ እንደሆነ ግልጽ ነው።

18 በወረስነው ኃጢአት ምክንያት ጥሩ ነገር የማድረግ ችሎታችን ውስን ነው። (ሮሜ 5:12) ያም ሆኖ አምላክ ‘ጥሩነትን እንዲያስተምረን’ ከጸለይን ይህን ባሕርይ ማንጸባረቅ እንችላለን። (መዝሙር 119:66 NW) ጳውሎስ በሮም ለሚገኙት የእምነት አጋሮቹ እንዲህ ብሏቸዋል:- ‘ወንድሞቼ ሆይ፤ እናንተ ራሳችሁ በበጎነትና [“በጥሩነትና፣” NW] በዕውቀት ሁሉ እንደተሞላችሁ እኔ ራሴ እርግጠኛ ሆኜአለሁ።’ (ሮሜ 15:14) አንድ ክርስቲያን የበላይ ተመልካች ጥሩ ወይም “በጎ የሆነውን ነገር የሚወድ” መሆን አለበት። (ቲቶ 1:7, 8) በአምላክ መንፈስ የምንመራ ከሆነ በጥሩነታችን የምንታወቅ እንሆናለን። ይሖዋም ‘ያደረግነውን ነገር ሁሉ በበጎነት ያስብልናል።’—ነህምያ 5:19፤ 13:31

‘ግብዝነት የሌለበት እምነት’

19. በዕብራውያን 11:1 መሠረት እምነት ምን ትርጉም አለው?

19 እምነት የመንፈስ ፍሬ አንዱ ገጽታ ሲሆን “ተስፋ ያደረግነው ነገር እንደሚፈጸም እርግጠኛ የምንሆንበት፣ የማናየውም ነገር እውን መሆኑን የምንረዳበት ነው።” (ዕብራውያን 11:1) እምነት ካለን ይሖዋ ቃል የገባልን ነገሮች በሙሉ መፈጸማቸው እንደማይቀር እርግጠኞች እንሆናለን። የማናየው ነገር እውን መሆኑን የሚያረጋግጥልን ማስረጃ በጣም አሳማኝ ስለሆነ እምነት ከዚህ ተጨባጭ ማስረጃ ጋር እኩል እንደሆነ ተደርጎ ተገልጿል። ለምሳሌ ያህል፣ የፍጥረታት መኖር ፈጣሪ እንዳለ በእርግጠኝነት እንድናምን ያደርገናል። በመንፈስ መመላለሳችንን ከቀጠልን ይህ ዓይነቱ እምነት ይኖረናል።

20. ‘በቀላሉ ተብትቦ የሚይዘን ኀጢአት’ ምንድን ነው? ከዚህ ኃጢአትም ሆነ ከሥጋ ሥራዎች መራቅ የምንችለው እንዴት ነው?

20 ‘በቀላሉ ተብትቦ የሚይዘን ኀጢአት’ የእምነት ማጣት ነው። (ዕብራውያን 12:1) እምነታችንን ሊያጠፉ ከሚችሉት ከሥጋ ሥራዎች፣ ከፍቅረ ንዋይና ከሐሰት ትምህርቶች ለመራቅ በአምላክ መንፈስ መታመን ይኖርብናል። (ቈላስይስ 2:8፤ 1 ጢሞቴዎስ 6:9, 10፤ 2 ጢሞቴዎስ 4:3-5) የአምላክ መንፈስ፣ በዛሬው ጊዜ የሚገኙ የአምላክ አገልጋዮች ከክርስትና ዘመን በፊትም ሆነ በኋላ የኖሩት የይሖዋ አምላኪዎች የነበራቸውን ዓይነት እምነት እንዲያዳብሩ ይረዳቸዋል። (ዕብራውያን 11:2-40) በተጨማሪም ‘ግብዝነት የሌለበት እምነታችን’ ሌሎች እምነታቸውን እንዲያጠነክሩ ይረዳቸዋል።—1 ጢሞቴዎስ 1:5 የ1954 ትርጉም፤ ዕብራውያን 13:7

ገርነትንና ራስን የመግዛት ባሕርይ አሳይ

21, 22. ገርነት ምን ፍቺ ተሰጥቶታል? ይህን ባሕርይ ማሳየት የሚኖርብንስ ለምንድን ነው?

21 ገርነት ሻካራ ያልሆነ ተፈጥሮንና ባሕርይን ያመለክታል። ገር ወይም የዋህ የሆነው ኢየሱስ የይሖዋን ባሕርይ ፍጹም በሆነ መልኩ ስላንጸባረቀ ገርነት ከአምላክ ባሕርያት መካከል አንዱ መሆኑን እናውቃለን። (ማቴዎስ 11:28-30፤ ዮሐንስ 1:18፤ 5:19) ታዲያ የአምላክ አገልጋዮች እንደመሆናችን መጠን ምን ይጠበቅብናል?

22 ክርስቲያኖች እንደመሆናችን መጠን ‘ለሰው ሁሉ ገርነትን ማሳየት’ ይጠበቅብናል። (ቲቶ 3:1, 2 የ1980 ትርጉም) በአገልግሎት ላይ ስንሆን ገርነትን እናሳያለን። ኃላፊነት ያላቸው መንፈሳዊ ወንድሞች ስህተት የሠራን ክርስቲያን “በገርነት” መንፈስ እንዲያቀኑ ተመክረዋል። (ገላትያ 6:1) ሁላችንም “ትሑታንና ገሮች” በመሆን ለክርስቲያናዊ አንድነትና ለሰላም አስተዋጽኦ ማበርከት እንችላለን። (ኤፌሶን 4:1-3) በመንፈስ የምንመላለስና ራሳችንን የምንገዛ ከሆነ ገርነትን ማሳየት እንችላለን።

23, 24. ራስን መግዛት ምንድን ነው? ይህን ባሕርይ ማዳበራችን እንዴት ይጠቅመናል?

23 ራስን የመግዛት ባሕርይ አሳባችንን፣ ንግግራችንን እና ድርጊታችንን ለመቆጣጠር ያስችለናል። ይሖዋ ኢየሩሳሌምን ባድማ ካደረጓት ከባቢሎናውያን ጋር በተያያዘ ‘ራሱን ገቷል።’ (ኢሳይያስ 42:14) የአምላክ ልጅ በመከራ ውስጥ በነበረበት ጊዜ ራሱን በመግዛት ‘ምሳሌ ትቶልናል።’ በተጨማሪም ሐዋርያው ጴጥሮስ የእምነት አጋሮቹን ‘በእውቀት ላይ ራስን መግዛት እንዲጨምሩ’ መክሯቸዋል።—1 ጴጥሮስ 2:21-23፤ 2 ጴጥሮስ 1:5-8

24 ክርስቲያን ሽማግሌዎች ራሳቸውን የሚገዙ እንዲሆኑ ይጠበቅባቸዋል። (ቲቶ 1:7, 8) ሕይወታቸውን በመንፈስ ቅዱስ የሚመሩ ሁሉ ራስን የመግዛት ባሕርይ ማዳበር ይችላሉ፤ እንዲህ ማድረጋቸው የሥነ ምግባር ብልግናንና ጸያፍ ንግግርን ጨምሮ የአምላክን ሞገስ ሊያሳጣቸው ከሚችል ከማንኛውም ነገር እንዲርቁ ይረዳቸዋል። የአምላክ መንፈስ ራስን የመግዛት ባሕርይ እንድናዳብር እንዲረዳን ከፈቀድን ይህ ባሕርይ በንግግራችንና በድርጊታችን ግልጽ ሆኖ ይታያል።

በመንፈስ መኖራችሁን ቀጥሉ

25, 26. በመንፈስ መመላለሳችን በአሁኑ ጊዜ ከሰዎች ጋር ባለን ግንኙነትም ሆነ በወደፊት ተስፋችን ላይ ምን በጎ ተጽዕኖ ያሳድራል?

25 በመንፈስ የምንኖር ከሆነ ቀናተኛ የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች እንሆናለን። (የሐዋርያት ሥራ 18:24-26) በተጨማሪም ሰዎች በተለይም ለአምላክ ያደሩ የእምነት ባልደረቦቻችን ከእኛ ጋር መሆን ያስደስታቸዋል። በመንፈስ ቅዱስ እንደሚመሩ ሰዎች ሁሉ እኛም ለክርስቲያን ባልንጀሮቻችን የብርታት ምንጭ እንሆናለን። (ፊልጵስዩስ 2:1-4) ሁሉም ክርስቲያን መሆን የሚፈልገው እንዲህ ዓይነት ሰው አይደለም?

26 በሰይጣን ቁጥጥር ሥር ባለው በዚህ ዓለም ውስጥ ስንኖር በመንፈስ መመላለስ ቀላል አይደለም። (1 ዮሐንስ 5:19) ያም ሆኖ በዛሬው ጊዜ የሚኖሩ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች በመንፈስ በመመላለስ ላይ ይገኛሉ። በሙሉ ልባችን በይሖዋ የምንታመን ከሆነ በአሁኑ ጊዜ አርኪ ሕይወት ይኖረናል። ወደፊት ደግሞ፣ በፍቅር ተገፋፍቶ መንፈስ ቅዱስን በሚሰጠን አምላክ የጽድቅ መንገዶች ላይ ለዘላለም መጓዝ እንችላለን።—መዝሙር 128:1፤ ምሳሌ 3:5, 6

መልስህ ምንድን ነው?

• በመንፈስ መኖር ከአምላክና ከልጁ ጋር ባለን ዝምድና ላይ በጎ ተጽዕኖ የሚያሳድረው እንዴት ነው?

• የመንፈስ ፍሬ የትኞቹን ባሕርያት ያካትታል?

• የአምላክን መንፈስ ፍሬ የምናሳይባቸው አንዳንድ መንገዶች ምንድን ናቸው?

• በመንፈስ መመላለሳችን በአሁኑ ሕይወታችንም ሆነ በወደፊት ተስፋችን ላይ ምን ተጽዕኖ ያሳድራል?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የይሖዋ ቅዱስ መንፈስ ለእምነት ባልንጀሮቻችን ፍቅር እንድናሳይ ይገፋፋናል

[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በቃልም ሆነ በድርጊት ሌሎችን በማጽናናት ደግነት አሳይ