በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ቤርዜሊ አቅሙን የሚያውቅ ሰው

ቤርዜሊ አቅሙን የሚያውቅ ሰው

ቤርዜሊ አቅሙን የሚያውቅ ሰው

‘ለምን ተጨማሪ ሸክም እሆንብሃለሁ?’ የእስራኤል ንጉሥ ለነበረው ለዳዊት እንዲህ ሲል የተናገረው የሰማንያ ዓመቱ አረጋዊ ቤርዜሊ ነበር። መጽሐፍ ቅዱስ ይህ ሰው “እጅግ ባለ ጸጋ” እንደነበረ ይናገራል። (2 ሳሙኤል 19:32, 35) ቤርዜሊ ይኖር የነበረው ከዮርዳኖስ ወንዝ በስተ ምሥራቅ በሚገኝ ገለዓድ የተባለ ተራራማ አካባቢ ነበር።—2 ሳሙኤል 17:27፤ 19:31

ቤርዜሊ ከላይ እንደተጠቀሰው በማለት ለዳዊት የተናገረው በምን ዓይነት ሁኔታ ውስጥ ሆኖ ነው? ይህ አረጋዊ እንዲህ ሲል የተናገረው ለምንድን ነው?

በንጉሡ ላይ ዓመጽ ተቀሰቀሰ

የዳዊት ሕይወት አደጋ ላይ ወድቆ ነበር። ልጁ አቤሴሎም ‘የእስራኤልን ሰዎች ልብ በመስረቅ’ የአባቱን ዙፋን ቀማ። አቤሴሎም ለአባቱ ታማኝ የሆነን ሰው እንደማይምር የታወቀ ስለነበር ዳዊትና አገልጋዮቹ ከኢየሩሳሌም ሸሹ። (2 ሳሙኤል 15:6, 13, 14) ዳዊት ከዮርዳኖስ በስተ ምሥራቅ ወደምትገኘው ወደ መሃናይም በደረሰ ጊዜ ቤርዜሊ አግኝቶ ረዳው።

ቤርዜሊና ሌሎች ሁለት ሰዎች በደግነት ተነሳስተው ለዳዊት የተትረፈረፈ ቁሳዊ እርዳታ አደረጉለት። እነዚህ ታማኝ ሰዎች “ሕዝቡ በምድረ በዳ ተርቦአል፤ ደክሞአል፤ ተጠምቶአል” ሲሉ መናገራቸው ዳዊትና አብረውት የነበሩት ሰዎች ያሉበትን አስጨናቂ ሁኔታ ተረድተው እንደነበር ያሳያል። ቤርዜሊ፣ ሾቢ እና ማኪር ለመኝታ የሚሆኑ ምንጣፎች፣ ስንዴ፣ ገብስ፣ ዱቄት፣ የተጠበሰ እሸት፣ ባቄላ፣ ምስር፣ ማር፣ ቅቤ፣ በጎችና ሌሎች ነገሮች በመስጠት የዳዊትንና አብረውት የነበሩትን ሰዎች ፍላጎት ለማሟላት የቻሉትን ሁሉ አድርገዋል።—2 ሳሙኤል 17:27-29

በዚህ ጊዜ ዳዊትን መርዳት አደገኛ ነበር። አቤሴሎም ሕጋዊ የሆነውን ንጉሥ የሚደግፍን ማንኛውንም ሰው ከመቅጣት ወደኋላ እንደማይል ግልጽ ነው። በመሆኑም ቤርዜሊ ከዳዊት ጎን በታማኝነት መቆሙ ደፋር መሆኑን የሚያሳይ ነው።

ሁኔታው ተለወጠ

ብዙም ሳይቆይ፣ በአቤሴሎም ይመራ የነበረው ዓማጺ ኃይል ከዳዊት ሰዎች ጋር ውጊያ ገጠመ። ውጊያው የተካሄደው በኤፍሬም ደን ውስጥ ሲሆን ይህ ሥፍራ የሚገኘው በመሃናይም አቅራቢያ ሳይሆን አይቀርም። በመጨረሻም የአቤሴሎም ሰራዊት ተሸነፈ፤ “በዚያም ቀን ታላቅ እልቂት ሆነ።” አቤሴሎም ለመሸሽ የሞከረ ቢሆንም ከሞት ማምለጥ አልቻለም።—2 ሳሙኤል 18:7-15

ዳዊት በድጋሚ ተቀናቃኝ የሌለው የእስራኤል ንጉሥ ለመሆን በቃ። ከዚህ በኋላ ተከታዮቹ በስደት መኖር አያስፈልጋቸውም። ከዚህም በላይ ታማኝነታቸው በዳዊት ዘንድ አክብሮትና አድናቆት አትርፎላቸዋል።

ዳዊት ወደ ኢየሩሳሌም ለመመለስ እየተዘጋጀ ሳለ ‘ገለዓዳዊው ቤርዜሊ ከሮግሊም ወረደ፤ ንጉሡን ለመሸኘትም አብሮት ወደ ዮርዳኖስ’ መጣ። በዚህ ጊዜ ዳዊት ለአረጋዊው ቤርዜሊ “ከእኔ ጋር ተሻገርና በኢየሩሳሌም አብረኸኝ ኑር፤ እኔ እመግብሃለሁ” የሚል ግብዣ አቀረበለት።—2 ሳሙኤል 19:15, 31, 33

ዳዊት ቤርዜሊ ላደረገለት እርዳታ ከፍተኛ አድናቆት እንደነበረው አያጠራጥርም። ሆኖም ዳዊት ቤርዜሊ አብሮት እንዲሄድ የጠየቀው ለተደረገለት እርዳታ ቁሳዊ ነገር በመስጠት ብድሩን መመለስ ስለፈለገ ብቻ አይመስልም። ቤርዜሊ ባለጸጋ ስለነበር እንዲህ የመሰለው እርዳታ አያስፈልገውም። ዳዊት ይህን ያደረገው የዕድሜ ባለጸጋ የሆነው ቤርዜሊ ያለው ግሩም ባሕርይ ስለማረከው በቤተ መንግሥቱ እንዲኖር ፈልጎ ሳይሆን አይቀርም። ቤርዜሊ በቤተ መንግሥቱ መኖሩ የንጉሡ ወዳጅ የመሆን አጋጣሚ ስለሚሰጠው ትልቅ ክብር ነበር።

ልክን ማወቅና እውነታውን መቀበል

ቤርዜሊ ንጉሥ ዳዊት ላቀረበለት ግብዣ መልስ ሲሰጥ እንዲህ አለ:- “ከንጉሡ ጋር ወደ ኢየሩሳሌም የምሄደው ለየትኛው ዕድሜዬ ብዬ ነው? እኔ አሁን የሰማንያ ዓመት ሽማግሌ ነኝ፤ ታዲያ ደግና ክፉውን መለየት እችላለሁ? ከእንግዲህ አገልጋይህ የሚበላውንና የሚጠጣውን ጣዕሙን መለየት ይችላል? የሚዘፍኑትን የወንዶችና የሴቶችን ድምፅ አሁንም መስማት እችላለሁ?” (2 ሳሙኤል 19:34, 35) በዚህ መንገድ ቤርዜሊ የቀረበለትን ግብዣና ግሩም መብት እንደማይቀበል በትሕትና ገለጸ። ይሁንና እንዲህ ያደረገው ለምንድን ነው?

ቤርዜሊ ይህን ያደረገበት አንዱ ምክንያት ዕድሜው ስለገፋና ከዚህ ጋር የተያያዙ አንዳንድ ችግሮች ስለነበሩበት ይሆናል። ምናልባትም ቤርዜሊ በሕይወት ብዙ እንደማይቆይ ተሰምቶት ሊሆን ይችላል። (መዝሙር 90:10) ዳዊትን ለመርዳት የቻለውን ሁሉ አድርጓል፤ ይሁንና የዕድሜ መግፋት ያስከተለበትን የአቅም ገደብም ተገንዝቧል። ቤርዜሊ፣ ክብርና ዝና የማግኘት ሐሳብ እውነታውን ከመመልከት እንዲያግደው አልፈቀደም። የሥልጣን ጥመኛ ከነበረው ከአቤሴሎም በተቃራኒ ቤርዜሊ ልኩን የሚያውቅ፣ ትሑትና ጥበበኛ ሰው መሆኑን አሳይቷል።—ምሳሌ 11:2

ቤርዜሊ የቀረበለትን ግብዣ ለመቀበል ያልፈለገበት ሌላው ምክንያት፣ አቅመ ደካማ መሆኑ በአምላክ የተሾመው ንጉሥ የሚያከናውነውን ተግባር እንዲያስተጓጉልበት ስላልፈለገ ሊሆን ይችላል። ቤርዜሊ “ታዲያ አገልጋይህ ለንጉሥ ጌታዬ ለምን ተጨማሪ ሸክም ይሆናል?” ሲል ጠየቀ። (2 ሳሙኤል 19:35) ቤርዜሊ ዳዊትን የረዳው ቢሆንም ከእሱ ይልቅ በዕድሜ ወጣት የሆነ ሰው ነገሮችን በተሻለ ብቃት ሊያከናውን እንደሚችል ተሰምቶት መሆን አለበት። በመሆኑም ልጁን በማመልከት ሳይሆን አይቀርም “አገልጋይህ ከመዓም እነሆ፤ ከጌታዬ ከንጉሡ ጋር ይሻገር፤ ደስ ያለህንም ነገር አድርግለት” አለ። ዳዊት በዚህ ከመከፋት ይልቅ በሐሳቡ ተስማማ። ከዚያም የዮርዳኖስን ወንዝ ከመሻገሩ በፊት “ቤርዜሊን ስሞ መረቀው።”—2 ሳሙኤል 19:37-39

ሚዛናዊ መሆን ያስፈልጋል

የቤርዜሊ ታሪክ ሚዛናዊ የመሆንን አስፈላጊነት ጎላ አድርጎ ያሳያል። በአንድ በኩል ዘና ያለ ሕይወት መምራት ስለምንፈልግና ኃላፊነት ለመሸከም እንደማንበቃ ሆኖ ስለሚሰማን ብቻ አንድ ልዩ መብት ከመቀበል ወይም እንዲህ ያለውን የአገልግሎት መብት ለማግኘት ከመጣጣር ወደኋላ ማለት የለብንም። አምላክ ጥንካሬና ጥበብ እንደሚሰጠን ከታመንን ጉድለታችንን ይሞላልናል።—ፊልጵስዩስ 4:13፤ ያዕቆብ 4:17፤ 1 ጴጥሮስ 4:11

በሌላ በኩል ደግሞ ያለብንን የአቅም ገደብ አምነን መቀበል አለብን። ለምሳሌ ያህል፣ አንድ ክርስቲያን በመንፈሳዊ እንቅስቃሴዎች የተጠመደ ሊሆን ይችላል። በመሆኑም ተጨማሪ ኃላፊነቶችን መቀበሉ የቤተሰቡን መንፈሳዊና ቁሳዊ ፍላጎት ማሟላትን ጨምሮ ሌሎች ቅዱስ ጽሑፋዊ ግዴታዎቹን ችላ ወደማለት ሊመራው እንደሚችል ይገነዘብ ይሆናል። በዚህ ጊዜ የቀረበለትን ተጨማሪ መብት ላለመቀበል መወሰኑ ልኩን እንደሚያውቅና ምክንያታዊ እንደሆነ የሚያሳይ አይደለም?—ፊልጵስዩስ 4:5 NW፤ 1 ጢሞቴዎስ 5:8

ቤርዜሊ ልናሰላስልበት የሚገባን ግሩም ምሳሌ ትቶልናል። ቤርዜሊ ታማኝ፣ ደፋር፣ ለጋስና ልኩን የሚያውቅ ሰው ነበር። ከሁሉም በላይ ከራሱ ጥቅም ይልቅ የአምላክን ፍላጎት ለማስቀደም ቁርጥ ውሳኔ አድርጎ ነበር።—ማቴዎስ 6:33

[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ካርታ]

(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)

የሰማንያ ዓመቱ ቤርዜሊ ዳዊትን ለመርዳት አድካሚ ጉዞ አድርጓል

ገለዓድ

ሮግሊም

ሱኮት

መሃናይም

ዮርዳኖስ ወንዝ

ጌልገላ

ኢያሪኮ

ኢየሩሳሌም

ኤፍሬም

[በገጽ 13 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ቤርዜሊ ዳዊት ያቀረበለትን ግብዣ ያልተቀበለው ለምን ነበር?