የማትሞት ነፍስ አለችህ?
የማትሞት ነፍስ አለችህ?
የተሠራነው ከሥጋና ደም ብቻ ነው? ወይስ ከእነዚህ የተለየ ሌላ ነገር አለን? ሕይወታችን አሁን ታይቶ በኋላ እንደሚጠፋ ጤዛ ነው? ወይስ በውስጣችን የምትኖር አንዲት ረቂቅ ነገር በምንሞትበት ጊዜ ከሥጋችን ተለይታ በሕይወት መኖሯን ትቀጥላለች?
በዓለም ያሉ ሃይማኖቶች ከሞት በኋላ ስላለው ሁኔታ ግራ የሚያጋቡ በርካታ ትምህርቶች ያሏቸው ቢሆንም፣ አብዛኞቹ ‘በውስጣችን ያለች አንዲት ረቂቅ ነገር ከሞትንም በኋላ በሕይወት መኖሯን ትቀጥላለች’ በሚለው መሠረታዊ ሐሳብ ይስማማሉ። ብዙ ሰዎች ይህች የማትሞት “ነገር” ነፍስ ነች ብለው ያምናሉ። አንተስ ምን ብለህ ታምናለህ? የተሠራነው ከሥጋና ከነፍስ ነው? ነፍስ ምንድን ነው? ሰዎች የማትሞት ነፍስ አላቸው? ስለዚህ ጉዳይ እውነቱን ማወቃችን እጅግ አስፈላጊ ነው!
“ሰውም ሕያው ነፍስ ሆነ”
“ነፍስ”፣ አንድ ሰው ሲሞት ከሥጋው ተለይታ በሕይወት መኖሯን የምትቀጥል ነገር ናት? ሆልመን ኢለስትሬትድ ባይብል ዲክሽነሪ “ነፍስ በአብዛኛው የሚያመለክተው ራሱን ሰውን ነው” ብሏል። ለምሳሌ ያህል ዘፍጥረት 2:7 “እግዚአብሔር አምላክ ከምድር ዐፈር ወስዶ ሰውን አበጀው፤ በአፍንጫውም የሕይወት እስትንፋስ እፍ አለበት፤ ሰውም ሕያው ነፍስ ሆነ” ይላል። በመሆኑም የመጀመሪያው ሰው አዳም ነፍስ ነበር።
“ነፍስ” የሚለው ቃል ሰውን እንደሚያመለክት የሚያሳዩ ሌሎች ጥቅሶችም አሉ። ለምሳሌ ያህል፣ መጽሐፍ ቅዱስ ነፍስ ሥራ እንደምትሠራ ይናገራል። (ዘሌዋውያን 23:30 የ1879 ትርጉም) ከዚህም ባሻገር ነፍስ እንደምትጨነቅ፣ እንደምታዝን፣ እንደምትፈራና እንደምትሰደድ ተደርጋ ተገልጻለች። (መሳፍንት 16:16 የ1954 ትርጉም፤ ኢዮብ 19:2፤ መዝሙር 119:28፤ የሐዋርያት ሥራ 2:43 NW፤ መዝሙር 7:5 የ1954 ትርጉም) ሮሜ 13:1 [የ1954 ትርጉም] “ነፍስ ሁሉ በበላይ ላሉት ባለ ሥልጣኖች ይገዛ” በማለት ነፍስ የሚለውን ቃል ሰውን ለማመልከት ተጠቅሞበታል። በተጨማሪም በ1 ጴጥሮስ 3:20 [የ1954 ትርጉም] ላይ ‘ጥቂቶች ማለት ስምንት ነፍስ ከውኃ ጥፋት እንደዳኑ’ እናነባለን። ከእነዚህ ጥቅሶች መካከል አንዳቸውም ቢሆኑ ነፍስ ከሞት በኋላ መኖሯን የምትቀጥል ረቂቅ ነገር እንደሆነች አያመለክቱም።
ዘፍጥረት 1:20, 24) በመሆኑም ሁሉም ሕያዋን ፍጥረታት ማለትም ሰዎችም ሆኑ እንስሳት ነፍስ ናቸው። ዕፅዋት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ነፍስ ተብለው አልተጠሩም።
ስለ እንስሳትና ስለ ዕፅዋትስ ምን ማለት ይቻላል? እነሱስ ነፍስ ናቸው? መጽሐፍ ቅዱስ ስለ እንስሳት አፈጣጠር ምን እንደሚል ተመልከት። አምላክ “ውሆች ሕይወት ባላቸው በሕያዋን ፍጡራን [“ነፍሳት፣” NW] ይሞሉ” ሲል ተናግሯል። በቀጣዩ የፍጥረት ቀን አምላክ እንዲህ ብሏል:- “ምድር ሕያዋን ፍጡራንን [“ነፍሳትን፣” NW] እንደየወገናቸው፣ ከብቶችን፣ በምድር ላይ የሚሳቡ ፍጡራንንና የዱር እንስሳትን እያንዳንዱን እንደ ወገኑ ታስገኝ።” (“ነፍስ” የሚለው ቃል በሌላም መንገድ ተሠርቶበታል። በኢዮብ 33:22 ላይ “ነፍሱ ወደ ጕድጓድ፣ ሕይወቱም ወደ ሞት መልእክተኞች ትቀርባለች” የሚል ሐሳብ እናነባለን። በዚህ ጥቅስ ላይ ‘ነፍስ’ እና ‘ሕይወት’ የሚሉት ቃላት ጎን ለጎን የተሠራባቸው ሲሆን አንዱ የሌላውን ትርጉም ይበልጥ ግልጽ ያደርጋል። በመሆኑም “ነፍስ” የአንድን ሰው ሕይወት ሊያመለክት ይችላል። ከዚህ የተነሳ መጽሐፍ ቅዱስ የሙሴን ሕይወት ሊያጠፉ የፈለጉትን ጠላቶቹን ‘ነፍሱን የሚሹ ሰዎች’ ሲል ጠርቷቸዋል። (ዘፀአት 4:19 የ1954 ትርጉም) ኢየሱስ ክርስቶስን በተመለከተ ደግሞ “የሰው ልጅ . . . ነፍሱንም [ሕይወቱን] ለብዙዎች ቤዛ አድርጎ ለመስጠት መጥቶአል” ብሏል።—ማቴዎስ 20:28
መጽሐፍ ቅዱስ “ነፍስ” ለሚለው ቃል የሚሰጠው ትርጉም ያልተወሳሰበና የማያሻማ ነው። ቃሉ ሰውን አሊያም እንስሳን ወይም ደግሞ የአንድን ፍጡር ሕይወት ያመለክታል። ቀጥለን እንደምናየው ይህ ሐሳብ መጽሐፍ ቅዱስ አንድ ሰው ሲሞት ነፍስ ምን እንደምትሆን ከሚሰጠው ማብራሪያ ጋር ይስማማል።
‘ኀጢአት የምትሠራ ነፍስ ትሞታለች’
መጽሐፍ ቅዱስ “ኀጢአት የምትሠራ ነፍስ እርሷ ትሞታለች” በማለት ይናገራል። (ሕዝቅኤል 18:4) በተጨማሪም በጭንቀት ስለተዋጠው ስለ ነቢዩ ኤልያስ ሲናገር “ነፍሱም ሞት ተመኘች” ይላል። (1 ነገሥት 19:4 የ1879 ትርጉም) በተመሳሳይም ያዕቆብ 5:20 “ኀጢአተኛን ከተሳሳተበት መንገድ የሚመልስ ሰው ነፍሱን ከሞት ያድነዋል” ይላል። እውነት ነው፣ አንድ ሰው ሲሞት ነፍሱ ይሞታል፤ ነፍስ የማይሞት ነገር አይደለም። ሰው ራሱ ነፍስ ስለሆነ አንድ ሰው ሞተ ሲባል ነፍሱ ሞተ ማለት ነው።
ታዲያ ነፍስ እንደወጣች ወይም እንደተመለሰች የሚናገሩት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች ምን ትርጉም አላቸው? ራሔል ወንድ ልጅ በወለደች ጊዜ ያጋጠማትን ሁኔታ መጽሐፍ ቅዱስ ሲገልጽ እንዲህ ይላል:- “ስትሞት ነፍስዋ በምትወጣበት ጊዜ ስሙን ቤንኦኒ ብላ ጠራችው፤ አባቱ ግን ብንያም አለው።” (ዘፍጥረት 35:18 የ1954 ትርጉም) አንደኛ ነገሥት 17:22 የአንዲት መበለት ልጅ ትንሣኤ እንዳገኘ ሲናገር “እግዚአብሔርም የኤልያስን ጩኸት [ጸሎት] ሰማ፤ የልጁም ነፍስ ተመለሰችለት፤ እርሱም ዳነ” ብሏል። እነዚህ ጥቅሶች ነፍስ ከሥጋ ተለይታ የምትወጣ ወይም ወደ ሰውነት የምትገባ የማትታይ ረቂቅ ነገር እንደሆነች የሚያሳዩ ናቸው?
በፍጹም አይደሉም። “የነፍስ” አንዱ ትርጉም “ሕይወት” ማለት እንደሆነ አትዘንጋ። በመሆኑም የራሔል ነፍስ ወጣች መባሉ የሕይወቷን ፍጻሜ የሚያመለክት ነው። እንዲያውም አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች “ነፍስዋ በምትወጣበት ጊዜ” የሚለውን ሐረግ “ሕይወቷ ልታልፍ በማጣጣር ላይ ሳለች” (ኖክስ) እና “የመጨረሻዋን እስትንፋስ ከመሳቧ በፊት” (ጀሩሳሌም ባይብል) በማለት ተርጉመውታል። በተመሳሳይም የመበለቲቷ ልጅ ትንሣኤ ባገኘ ጊዜ ሕይወቱ ተመልሶለታል።—1 ነገሥት 17:23 የ1954 ትርጉም
ሰው ምንድን ነው?
መጽሐፍ ቅዱስ ለዚህ ጥያቄ የማያሻማ መልስ ይሰጣል። ሰው በውስጡ ነፍስ ያለው ሳይሆን ራሱ ነፍስ ነው። ይህን ሐቅ ማወቃችን የሙታን የወደፊት ተስፋ የተመካው በትንሣኤ ላይ መሆኑን እንድንገነዘብ ይረዳናል። መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ የሚል ተስፋ ይሰጣል:- “በዚህ አትደነቁ፤ መቃብር ውስጥ ያሉ ሁሉ ድምፁን የሚሰሙበት ጊዜ ይመጣል፤ መልካም የሠሩ ለሕይወት ትንሣኤ፣ ክፉ የሠሩ ለፍርድ ትንሣኤ ይወጣሉ።” (ዮሐንስ 5:28, 29) ሙታን ያላቸው እውነተኛ ተስፋ የተመሠረተው የማትሞት ነፍስ አለች በሚለው ትምህርት ላይ ሳይሆን በትንሣኤ ተስፋ ላይ ነው።
ስለ ትንሣኤ ምንነትና ይህ ተስፋ ለሰው ልጆች ስላለው ትርጉም በትክክል ማወቃችን በጣም አስፈላጊ ነው! በተጨማሪም ኢየሱስ በጸሎቱ ላይ “አንተ ብቻ እውነተኛ አምላክ የሆንኸውንና የላክኸውን ኢየሱስ ክርስቶስን ያውቁ ዘንድ ይህች የዘላለም ሕይወት ናት” በማለት ስለተናገረ አምላክንና ክርስቶስን ማወቅ አስፈላጊ ነው። (ዮሐንስ 17:3) በአካባቢህ የሚኖሩ የይሖዋ ምሥክሮች ስለ አምላክና እሱ ስለሰጣቸው ተስፋዎች እንዲሁም ስለ ልጁ በበለጠ እንድታውቅ ለመርዳት መጽሐፍ ቅዱስን ሊያስጠኑህ ፈቃደኞች ናቸው። ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር እንድትገናኝ ወይም ለዚህ መጽሔት አዘጋጆች እንድትጽፍ እንጋብዝሃለን።
[በገጽ 4 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ሁሉም ነፍስ ናቸው
[ምንጭ]
ፍየል:- CNPC—Centro Nacional de Pesquisa de Caprinos (Sobral, CE, Brasil)