በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የአንባቢያን ጥያቄዎች

የአንባቢያን ጥያቄዎች

የአንባቢያን ጥያቄዎች

መከር የሚሰበሰብበት ጊዜ የሚጀምረው ሁሉም እስራኤላውያን ወንዶች የቂጣ በዓል በሚያከብሩበት ወቅት ስለነበር ወደ ቤተ መቅደስ የሚገባውን በኩሩን የገብስ ነዶ የሚሰበስበው ማን ነበር?

በሙሴ ሕግ ላይ እስራኤላውያን እንደሚከተለው የሚል ትእዛዝ ተሰጥቷቸው ነበር:- “ወንዶችህ ሁሉ በዓመት ሦስት ጊዜ፣ በቂጣ በዓል፣ በመከር በዓልና በዳስ በዓል ላይ፣ እርሱ በሚመርጠው ስፍራ በአምላክህ በእግዚአብሔር ፊት ይቅረቡ።” (ዘዳግም 16:16) ከንጉሥ ሰሎሞን የግዛት ዘመን ጀምሮ አምላክ የመረጠው ቦታ በኢየሩሳሌም የሚገኘው ቤተ መቅደስ ነበር።

ከሦስቱ በዓላት መካከል የመጀመሪያው የሚከበረው ጸደይ ሲጠባ ነው። የቂጣ በዓል ተብሎ የሚጠራው ይህ በዓል መከበር የሚጀምረው የማለፍ በዓል ኒሳን 14 በተከበረ ማግስት ሲሆን እስከ ኒሳን 21 ድረስ ለሰባት ቀናት ያህል ይቆያል። በአይሁዳውያን ቅዱስ የቀን መቁጠሪያ መሠረት የመጀመሪያው የዓመቱ መከር መሰብሰብ የሚጀምረው የቂጣ በዓል መከበር በጀመረ በሁለተኛው ቀን ማለትም በኒሳን 16 ላይ ነው። በዚያን ዕለት ሊቀ ካህናቱ ከገብሱ መከር “የመጀመሪያውን ነዶ” ወስዶ በቤተ መቅደሱ ውስጥ ‘በይሖዋ ፊት መወዝወዝ’ ነበረበት። (ዘሌዋውያን 23:5-12) በዚህ ጊዜ ሁሉም ወንዶች በቂጣ በዓል ላይ እንዲገኙ ይጠበቅባቸው ነበር፤ ታዲያ በኩሩን የገብስ ነዶ የሚሰበስበው ማን ነው?

በቂጣ በዓል ላይ የመከሩን በኩር ለይሖዋ እንዲያቀርቡ የሚያዘው ሕግ የተሰጠው ለመላው የእስራኤል ብሔር ነው። በመሆኑም እያንዳንዱ እስራኤላዊ ሰብሉን መሰብሰብ እንዲጀምርና የበኩሩን ነዶ ወደ ቤተ መቅደሱ እንዲያመጣ አይጠበቅበትም። ከዚህ ይልቅ ጥቂት ግለሰቦች ብሔሩን ወክለው ይህን ትእዛዝ ይፈጽሙ ነበር። ስለዚህ ብሔሩን የሚወክሉ ጥቂት ሰዎች በቅርብ ወደሚገኝ የገብስ ማሳ ሄደው በቂጣ በዓል ላይ የሚቀርበውን ነዶ ያጭዳሉ። ኢንሳይክሎፒዲያ ጁዳይካ በዚህ ጉዳይ ላይ አስተያየት ሲሰጥ እንዲህ ብሏል:- “በኢየሩሳሌም አካባቢ ያለው የገብስ አዝመራ ከደረሰ ከዚያው ይወሰዳል፤ አለዚያም ከየትኛውም የእስራኤል ምድር እንዲመጣ ሊደረግ ይችላል። ሦስት ሰዎች የየራሳቸውን ማጭድና ቅርጫት ይዘው በመሄድ ገብሱን ያጭዳሉ።” ከዚያም የገብሱ ነዶ ለሊቀ ካህናቱ የሚመጣለት ሲሆን እሱም በይሖዋ ፊት ያቀርበዋል።

እስራኤላውያን የመከሩን በኩር ለይሖዋ እንዲያቀርቡ መታዘዛቸው አምላክ ምድራቸውንና ሰብላቸውን ስለባረከ አመስጋኝነታቸውን እንዲገልጹ ግሩም አጋጣሚ ይከፍትላቸዋል። (ዘዳግም 8:6-10) ይሁንና የበኩሩን ነዶ የማቅረቡ ሥነ ሥርዓት “ወደ ፊት ለሚመጡት መልካም ነገሮች ጥላ” በመሆኑ ከዚህ የላቀ ትርጉም አለው። (ዕብራውያን 10:1) ኢየሱስ ክርስቶስ ከሞት የተነሳው፣ በኒሳን 16, 33 ከክርስቶስ ልደት በኋላ ሲሆን ይህም የመከሩ በኩር ለይሖዋ የሚቀርብበት ዕለት ነው። ሐዋርያው ጳውሎስ ኢየሱስን አስመልክቶ እንዲህ ሲል ጽፏል:- “ክርስቶስ ላንቀላፉት ሁሉ በኵራት ሆኖ በእርግጥ ከሙታን ተነሥቶአል። . . . ነገር ግን እያንዳንዱ በራሱ ተራ ይሆናል፤ መጀመሪያ በኵራት የሆነው ክርስቶስ፣ ከዚያም በኋላ እርሱ ሲመጣ የክርስቶስ የሆኑት።” (1 ቆሮንቶስ 15:20-23) ሊቀ ካህናቱ በይሖዋ ፊት የሚወዘውዘው የበኩር ነዶ፣ የዘላለም ሕይወት ለማግኘት ከሞት ከሚነሱት የመጀመሪያው ለሆነው ለኢየሱስ ክርስቶስ ጥላ ነበር። በመሆኑም ኢየሱስ የሰው ልጆች ከኃጢአትና ከሞት ባርነት ነፃ የሚሆኑበትን መንገድ ከፍቷል።

[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

© 2003 BiblePlaces.com