በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

መንፈሳዊነትን ለማግኘት የሚደረግ ጥረት

መንፈሳዊነትን ለማግኘት የሚደረግ ጥረት

መንፈሳዊነትን ለማግኘት የሚደረግ ጥረት

ኢየሱስ ታዋቂ በሆነው የተራራ ስብከቱ ላይ “መንፈሳዊ ነገሮችን የሚጠሙ ደስተኞች ናቸው” በማለት ተናግሮ ነበር። (ማቴዎስ 5:3 NW) አንተም በዚህ ሐሳብ ትስማማ ይሆናል። በየትኛውም ቦታ የሚኖሩ ሰዎች መንፈሳዊ ነገሮች እንደሚያስፈልጓቸው የሚገነዘቡ ከመሆኑም በላይ እነዚህን ነገሮች ካገኙ ደስተኛ እንደሚሆኑ ይሰማቸዋል። ይሁን እንጂ “መንፈሳዊነት” የሚለው ቃል ምን ትርጉም አለው?

አንድ መዝገበ ቃላት መንፈሳዊነት የሚለውን ቃል “ሃይማኖታዊ እሴቶች እንደሚያስፈልጉ መገንዘብ ወይም እነዚህን ነገሮች መውደድ” እንዲሁም “መንፈሳዊ ሰው መሆን” በማለት ፈቶታል። በዚህም የተነሳ “መንፈሳዊነት፣” “መንፈሳዊ መሆን” ወይም “መንፈሳዊ አስተሳሰብ መያዝ” የሚሉት ሐሳቦች ተመሳሳይ ትርጉም እንዳላቸው ይታሰባል። በሌላ አባባል አንድ ግለሰብ መንፈሳዊ ወይም ሃይማኖታዊ ነገሮችን ከፍ አድርጎ የሚመለከት ከሆነ መንፈሳዊ ሰው ይባላል።

ታዲያ እውነተኛ መንፈሳዊነትን ማግኘት የሚቻለው እንዴት ነው? ሁሉም ሃይማኖቶች ማለት ይቻላል፣ አንድ ሰው መንፈሳዊ ለመሆን ምን ማድረግ እንዳለበት እንደሚያውቁ ቢናገሩም የሚሰጧቸው መመሪያዎች ግን እንደ ሃይማኖቶቹ በርካታ ናቸው። ፕሮቴስታንት የሆነ ሰው፣ የመንፈስ ቅዱስ መነቃቃት ስብሰባዎች ላይ መገኘቱ ለመዳን እንደሚያበቃው ይናገራል። የኦርቶዶክስ እምነት ተከታይ ደግሞ ለመጽደቅ ሲል ይቆርባል። የቡድሂዝም ሃይማኖት ተከታይ የሆነ ሰው፣ በማሰላሰል የተሟላ እውቀት ለማግኘትና ሥቃይም ሆነ ምኞት የሌለበት ሁኔታ ላይ ለመድረስ ይጥራል። የሂንዱ ሃይማኖት ተከታይ ደግሞ ራሱን በመጨቆን እንደገና ከመወለድ ዑደት ነፃ ለመውጣት ይሞክራል። ታዲያ እነዚህ ሁሉ መንገዶች ወይም ከእነዚህ አንዱ ወደ እውነተኛ መንፈሳዊነት ይመራሉ?

ብዙዎች ከላይ ላለው ጥያቄ የሚሰጡት መልስ ‘አይመሩም’ የሚል ነው። እነዚህ ሰዎች፣ መንፈሳዊነት ሲባል “አባል ሳይሆኑ ማመን” ይኸውም የአንድ ቤተ ክርስቲያን አባል ሳይሆኑ በአምላክ ማመን ማለት እንደሆነ ይናገራሉ። ሌሎች ደግሞ መንፈሳዊነት፣ ውስጣዊ ሰላምና የሕይወት ዓላማ የማግኘት ፍላጎትን እንጂ አንድ ሰው ከሃይማኖት ጋር በተያያዘ የተፈጸመለትን ነገር እንደማያመለክት ይሰማቸዋል። እነዚህ ሰዎች፣ መንፈሳዊነትን ለማግኘት የሚጥሩ ግለሰቦች ሃይማኖት ፈጽሞ እንደማያስፈልጋቸው ይናገራሉ። ከዚህ ይልቅ ውስጣዊ ስሜታቸውን ብቻ ማዳመጥ አለባቸው ይላሉ። አንድ ጸሐፊ ይህን በማስመልከት እንዲህ ብለዋል:- “እውነተኛ መንፈሳዊነት በግለሰቡ ውስጥ የሚገኝ ነገር ነው። ዓለምንና በአካባቢህ የሚገኙ ሰዎችን የምታፈቅርበት እንዲሁም እነሱን የምትቀበልበት መንገድ ብሎም ከእነሱ ጋር ያለህ ግንኙነት ነው። እውነተኛ መንፈሳዊነት የአንድ ቤተ ክርስቲያን አባል በመሆን ወይም የተወሰነ ሃይማኖታዊ ትምህርቶችን በማመን ሊገኝ አይችልም።”

በግልጽ መመልከት እንደሚቻለው ሰዎች ስለ መንፈሳዊነት ያላቸው አመለካከት በእጅጉ ይለያያል። በሺህ የሚቆጠሩ መጻሕፍት መንፈሳዊ ሕይወት መምራት የሚቻልበትን መንገድ እንደሚጠቁሙ ቢገልጹም ብዙ ጊዜ አንባቢዎቹ በሚያነቡት ነገር የማይረኩ ከመሆኑም ሌላ ግራ ይጋባሉ። ይሁን እንጂ ስለ መንፈሳዊ ነገሮች አስተማማኝ መመሪያ የያዘ አንድ መጽሐፍ አለ። ይህ መጽሐፍ በአምላክ መንፈስ አነሳሽነት እንደተጻፈ ይናገራል። (2 ጢሞቴዎስ 3:16) የመንፈሳዊነትን ትርጉምና ጠቀሜታ በተመለከተ ይህ መጽሐፍ ማለትም መጽሐፍ ቅዱስ ምን እንደሚል እንመልከት።

[ምንጭ]

COVER: Background: © Mark Hamblin/​age fotostock