በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

‘በአምላክ ዘንድ ሀብታም’ ነህ?

‘በአምላክ ዘንድ ሀብታም’ ነህ?

‘በአምላክ ዘንድ ሀብታም’ ነህ?

‘ለራሱ ሀብት የሚያከማች፣ ዳሩ ግን በአምላክ ዘንድ ሀብታም ያልሆነ ሰው መጨረሻው ይኸው ነው።’—ሉቃስ 12:21

1, 2. (ሀ) ሰዎች ምን ለማግኘት ሲሉ ከፍተኛ መሥዋዕትነት ለመክፈል ፈቃደኛ ሆነዋል? (ለ) ክርስቲያኖች ምን አስቸጋሪና አደገኛ ሁኔታ ይገጥማቸዋል?

 ባለፉት ዘመናት በተለያዩ ማኅበረሰቦች ውስጥ የኖሩ ሰዎች ቁሳዊ ሀብት ለማግኘት ሲለፉ ኖረዋል። ለአብነት ያህል፣ በ19ኛው መቶ ዘመን ሰዎች ወርቅ ለማግኘት ሲሉ ራቅ ካሉ ቦታዎች ወደ አውስትራሊያ፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ካናዳና ዩናይትድ ስቴትስ ተጉዘዋል፤ እነዚህ ሰዎች ሀብት ለማግኘት ሲሉ ቤታቸውንና ዘመዶቻቸውን ትተው ወደማያውቋቸው አንዳንድ ጊዜም አስቸጋሪ ወደሆኑ አካባቢዎች ለመሄድ ፈቃደኞች ነበሩ። አዎን፣ ብዙ ሰዎች ልባቸው የቋመጠለትን ሀብት ለማግኘት ሲሉ ሕይወታቸውን ለአደጋ የሚያጋልጥ ነገር ለማድረግም ሆነ ከፍተኛ መሥዋዕትነት ለመክፈል ፈቃደኞች ናቸው።

2 እርግጥ ነው፣ በዛሬው ጊዜ የሚኖሩ በርካታ ሰዎች ቃል በቃል ወርቅ ለማግኘት የዚያን ያህል ጥረት ባያደርጉም ለመኖር ሲሉ ጠንክረው መሥራት አለባቸው። በዚህ ሥርዓት ይህን ማድረግ አስቸጋሪ እንዲሁም ጊዜና ጉልበትን የሚያሟጥጥ አልፎ ተርፎም ጫና የሚፈጥር ሊሆን ይችላል። ምግብ፣ ልብስና መጠለያ ለማግኘት በምናደርገው ጥረት በጣም ከመወጠራችን የተነሳ ይበልጥ አስፈላጊ የሆኑትን ነገሮች ችላ ልንል አልፎ ተርፎም ልንረሳ እንችላለን። (ሮሜ 14:17) ኢየሱስ በሉቃስ 12:16-21 ላይ ይህን የሰዎች ዝንባሌ በትክክል የሚገልጽ ምሳሌ ሰጥቶ ነበር።

3. በሉቃስ 12:16-21 ላይ ያለውን የኢየሱስ ምሳሌ አጠር አድርገህ ተናገር።

3 ኢየሱስ ይህን ምሳሌ የተናገረው፣ ባለፈው ርዕስ ላይ በዝርዝር የተመለከትነውን ከስግብግብነት ስለ መራቅ የሰጠውን ትምህርት ባቀረበበት ወቅት ነበር። ኢየሱስ ከስግብግብነት እንድንርቅ ካስጠነቀቀ በኋላ ስለ አንድ ሀብታም ሰው ተናገረ፤ ይህ ሰው በብዙ ጎተራዎች የተከማቸ ንብረት ቢኖረውም በዚህ ስላልረካ ያሉትን ጎተራዎች አፍርሶ የበለጠ ንብረት መያዝ የሚችሉ ሰፋ ያሉ ጎተራዎችን ሠራ። ሰውየው ይህን ካደረገ በኋላ ዘና ለማለትና የተደላደለ ኑሮ ለመምራት ሲያስብ ሊሞት እንደሆነና ያከማቸው ንብረትም ለሌላ ሰው እንደሚሆን አምላክ ነገረው። ኢየሱስ “ለራሱ ሀብት የሚያከማች፣ ዳሩ ግን በእግዚአብሔር ዘንድ ሀብታም ያልሆነ ሰው መጨረሻው ይኸው ነው” በማለት ንግግሩን ደመደመ። (ሉቃስ 12:21) ከዚህ ምሳሌ ምን ትምህርት እናገኛለን? ትምህርቱን በሕይወታችን ውስጥ ልንሠራበት የምንችለውስ እንዴት ነው?

ችግር ያጋጠመው ሰው

4. በኢየሱስ ምሳሌ ላይ ስለተገለጸው ሰው ምን ማለት እንችላለን?

4 ኢየሱስ የተናገረው ምሳሌ የታወቀ ነው። ታሪኩን የጀመረው “ዕርሻው እጅግ ፍሬያማ የሆነችለት አንድ ሀብታም ነበረ” በማለት ነው። ኢየሱስ፣ ሰውየው ሀብታም የሆነው በማታለል ወይም በሕገ ወጥ መንገድ እንደሆነ አልተናገረም። በሌላ አነጋገር ግለሰቡ፣ መጥፎ ሰው እንደሆነ ተደርጎ አልተገለጸም። እንዲያውም ኢየሱስ ከተናገረው አንጻር በምሳሌው ላይ የተገለጸው ሰው ታታሪ ሠራተኛ እንደነበር ማሰቡ ምክንያታዊ ይመስላል። ሌላው ቢቀር ይህ ሰው ንብረት ያጠራቀመው ስለ ወደፊቱ ጊዜ አስቀድሞ በማሰብ ሊሆን እንደሚችል መረዳት እንችላለን፤ ምናልባትም ይህን ያደረገው ስለ ቤተሰቡ ደኅንነት በማሰብ ይሆናል። በመሆኑም ከሰብዓዊ አመለካከት አንጻር ሲታይ ይህ ሰው ኃላፊነቱን በቁም ነገር የሚወጣ ታታሪ ሠራተኛ ነው ሊባል ይችላል።

5. በኢየሱስ ምሳሌ ላይ የተገለጸው ሰው ምን ችግር አጋጠመው?

5 ሁኔታው ምንም ይሁን ምን ኢየሱስ በምሳሌው ላይ የጠቀሰውን ሰው ሀብታም ብሎ ስለጠራው ግለሰቡ የተትረፈረፈ ቁሳዊ ንብረት ያለው ባለጠጋ ነበር። ሆኖም ኢየሱስ እንደገለጸው ሀብታሙ ሰው ችግር አጋጥሞት ነበር። እርሻው ፍሬያማ ስለሆነለት ከጠበቀውና ከሚያስፈልገው እንዲሁም በጎተራው ሊያስቀምጠው ከሚችለው በላይ ብዙ ምርት አገኘ። ታዲያ ይህ ሰው ምን ማድረግ ነበረበት?

6. በዛሬው ጊዜ የሚገኙ በርካታ የአምላክ አገልጋዮች ውሳኔ የሚጠይቅ ምን ምርጫ ይደቀንባቸዋል?

6 በዛሬው ጊዜ የሚገኙ በርካታ የይሖዋ አገልጋዮች ከዚህ ሰው ጋር በጣም የሚመሳሰል ሁኔታ ያጋጥማቸዋል። እውነተኛ ክርስቲያኖች ሐቀኛ፣ ታታሪና ጠንቃቃ ሠራተኞች ለመሆን ይጥራሉ። (ቈላስይስ 3:22, 23) ተቀጥረውም ይሥሩ ወይም የራሳቸው ሥራ ይኑራቸው፣ አብዛኛውን ጊዜ ሥራቸውን ጥሩ አድርገው ያከናውናሉ፤ እንዲያውም በሥራቸው ከሌሎች ልቀው ይገኛሉ። በዚህም የተነሳ የሥራ እድገት ወይም አዳዲስ የሥራ አጋጣሚዎች ሲያገኙ ውሳኔ ለማድረግ የሚያስገድዳቸው ሁኔታ ይደቀንባቸዋል። ታዲያ ያገኙትን የሥራ እድገት ተቀብለው በርከት ያለ ገንዘብ ማግኘት ይኖርባቸው ይሆን? የይሖዋ ምሥክሮች የሆኑ በርካታ ወጣቶችም በትምህርት ቤት ጥሩ ውጤት ያመጣሉ። በዚህም የተነሳ ሽልማት ይሰጣቸው ወይም ታዋቂ በሆኑ ተቋማት ውስጥ ገብተው ከፍተኛ ትምህርት ለመከታተል የሚያስችል የነጻ ትምህርት ዕድል ያገኙ ይሆናል። ታዲያ በዚህ ወቅት አብዛኞቹ ሰዎች እንደሚያደርጉት ሁሉ እነሱም የቀረበላቸውን አጋጣሚ መቀበል ይኖርባቸው ይሆን?

7. በኢየሱስ ምሳሌ ላይ ያለው ሰው ያጋጠመውን ችግር የፈታው እንዴት ነበር?

7 ኢየሱስ ወደተናገረው ምሳሌ ስንመለስ፣ ሀብታሙ ሰው ምርቱን የሚያስቀምጥበት ቦታ እስኪያጣ ድረስ እርሻው ፍሬያማ በሆነለት ጊዜ ምን አደረገ? ያሉትን ጎተራዎች አፍርሶ የተትረፈረፈ ምርቱንና ንብረቱን የሚያስቀምጥባቸው ትልልቅ ጎተራዎች ለመሥራት ወሰነ። ያወጣው ዕቅድ እንዲረካና ሕይወቱ አስተማማኝ እንደሆነ እንዲሰማው ሳያደርገው አልቀረም፤ በዚህም የተነሳ እንዲህ ብሎ አሰበ:- “ነፍሴንም፣ ‘ነፍሴ ሆይ፤ ለብዙ ዘመን የሚበቃሽ ሀብት አከማችቼልሻለሁ፤ እንግዲህ ዕረፊ፤ ብዪ፤ ጠጪ፤ ደስም ይበልሽ’ እላታለሁ።”—ሉቃስ 12:19

“ሞኝ” የተባለው ለምንድን ነው?

8. በኢየሱስ ምሳሌ ላይ የተጠቀሰው ሰው የዘነጋው አስፈላጊ ነገር ምን ነበር?

8 ከኢየሱስ አነጋገር መመልከት እንደሚቻለው ግን የሀብታሙ ሰው ዕቅድ አስተማማኝ አልነበረም። ዕቅዱ ጥሩ ቢመስልም በጣም አስፈላጊ የሆነውን ነገር ይኸውም የአምላክን ፈቃድ ከግምት ያስገባ አልነበረም። ሰውየው ያሰበው ስለራሱ ብቻ ነበር፤ ለማረፍ፣ ለመብላት፣ ለመጠጣትና ለመደሰት እንደሚችል አስቦ ነበር። ብዙ “ሀብት” ስላለው “ለብዙ ዘመን” መኖር እንደሚችልም ተሰምቶት ነበር። የሚያሳዝነው ግን ነገሮች እንዳሰበው አልሆኑለትም። ኢየሱስ አስቀድሞ እንደተናገረው:- “የሰው ሕይወቱ በሀብቱ ብዛት የተመሠረተ [አይደለም]።” (ሉቃስ 12:15) የዚያኑ ዕለት ሌሊት አምላክ ይህን ሰው “አንተ ሞኝ፤ ነፍስህን በዚህች ሌሊት ከአንተ ሊወስዱ ይፈልጓታል፤ እንግዲህ፣ ለራስህ ያከማቸኸው ለማን ይሆናል?” አለው፤ በመሆኑም ሰውየው የለፋበት ነገር ሁሉ በድንገት ከንቱ ሆነ።—ሉቃስ 12:20

9. በኢየሱስ ምሳሌ ላይ የተጠቀሰው ሰው ሞኝ የተባለው ለምን ነበር?

9 ኢየሱስ የተናገረው ምሳሌ ዋና ነጥብ ይህ ነው። አምላክ ሰውየውን ሞኝ ብሎ ጠርቶታል። እዚህ ላይ ሰውየውን ለመግለጽ የተሠራበት የግሪክኛ ቃል “ሁልጊዜ የሚያመለክተው ማስተዋል የሌለውን” ሰው እንደሆነ ኤክሴጄቲካል ዲክሽነሪ ኦቭ ዘ ኒው ቴስታመንት አብራርቷል። ይኸው መዝገበ ቃላት እንደሚጠቁመው በምሳሌው ላይ “ሀብታሙ ሰው ለወደፊቱ ጊዜ ያወጣው ዕቅድ ዋጋ እንደሌለው” ለማሳየት አምላክ በዚህ ቃል እንደተጠቀመ ተደርጎ ተገልጿል። ሞኝ የሚለው ቃል የሚያመለክተው እውቀት የሌለውን ግለሰብ ሳይሆን ሕይወቱ “በአምላክ እጅ እንደሆነ ለመቀበል ፈቃደኛ ያልሆነን ሰው” ነው። ኢየሱስ ስለ ሀብታሙ ሰው የሰጠው መግለጫ ከጊዜ በኋላ በመጀመሪያ መቶ ዘመን በትንሿ እስያ በሎዶቅያ ጉባኤ ውስጥ ይኖሩ ለነበሩ ክርስቲያኖች እንደሚከተለው በማለት የተናገረውን ያስታውሰናል:- “‘ሀብታም ነኝ፤ ባለጠጋ ነኝ አንዳችም አያስፈልገኝም’ ትላለህ፤ ነገር ግን ጐስቋላ፣ ምስኪን፣ ድኻ፣ ዕውርና፣ የተራቈትህ መሆንህን አታውቅም።”—ራእይ 3:17

10. አንድ ሰው ብዙ “ሀብት” ያለው መሆኑ “ለብዙ ዘመን” እንደሚኖር ዋስትና የማይሆነው ለምንድን ነው?

10 እኛም በዚህ ትምህርት ላይ ማሰላሰላችን ጠቃሚ ነው። በምሳሌው ላይ እንደተጠቀሰው ሰው፣ ብዙ “ሀብት” ለማካበት ተግተን በመሥራት ተጠምደን “ለብዙ ዘመን” መኖር እንድንችል ማድረግ ያለብንን ነገር ሳናደርግ እንቀር ይሆን? (ዮሐንስ 3:16፤ 17:3) መጽሐፍ ቅዱስ “በቍጣ ቀን ሀብት ፋይዳ የለውም” እንዲሁም “በሀብቱ የሚታመን ሁሉ ይወድቃል” ይላል። (ምሳሌ 11:4, 28) በመሆኑም ኢየሱስ “ለራሱ ሀብት የሚያከማች፣ ዳሩ ግን በእግዚአብሔር ዘንድ ሀብታም ያልሆነ ሰው መጨረሻው ይኸው ነው” በሚለው ምክር ምሳሌውን ደምድሟል።—ሉቃስ 12:21

11. በቁሳዊ ነገሮች ላይ መተማመንና በእነዚህ ተስፋ ማድረግ ከንቱ የሆነው ለምንድን ነው?

11 ኢየሱስ “መጨረሻው ይኸው ነው” ሲል፣ በቁሳዊ ንብረቶች ላይ ብቻ የሚተማመኑና ተስፋቸውን በእነዚህ ነገሮች ላይ የሚጥሉ ሰዎች በምሳሌው ላይ የተገለጸው ሀብታም ያጋጠመው ዓይነት ሁኔታ እንደሚደርስባቸው መጠቆሙ ነበር። ችግሩ ‘ለራስ ሀብት ማከማቸት’ ሳይሆን ‘በአምላክ ዘንድ ሀብታም’ አለመሆን ነው። ደቀ መዝሙሩ ያዕቆብ እንደሚከተለው በማለት ተመሳሳይ ማስጠንቀቂያ ሰጥቷል:- “እናንተ ‘ዛሬ ወይም ነገ ወደዚህች ወይም ወደዚያች ከተማ እንሄዳለን፤ በእርሷም አንድ ዓመት እንቈያለን፤ እንነግዳለን፤ እናተርፋለንም’ የምትሉ እንግዲህ ስሙ። ነገ የሚሆነውን እንኳ አታውቁም።” እነዚህ ሰዎች ምን ማድረግ ነበረባቸው? “የጌታ ፈቃድ ቢሆን እንኖራለን፤ ይህን ወይም ያንን እናደርጋለን” ማለት እንደሚገባቸው ያዕቆብ ነግሯቸዋል። (ያዕቆብ 4:13-15) አንድ ሰው ምንም ያህል ሀብታም ቢሆን ወይም ብዙ ንብረት ቢኖረው በአምላክ ዘንድ ሀብታም ካልሆነ ሁሉ ነገር ከንቱ ነው። ታዲያ በአምላክ ዘንድ ሀብታም መሆን ሲባል ምን ማለት ነው?

በአምላክ ዘንድ ሀብታም መሆን

12. በአምላክ ዘንድ ሀብታም እንድንሆን የሚያስችለን ምን ማድረግ ነው?

12 ኢየሱስ በሰጠው ንግግር ላይ በአምላክ ዘንድ ሀብታም መሆን ለራስ ቁሳዊ ሀብት ከማከማቸት ወይም ራስን በቁሳዊ ነገሮች ከማበልጸግ ጋር ተነጻጽሯል። በመሆኑም ኢየሱስ፣ በሕይወታችን ውስጥ በዋነኝነት ሊያሳስበን የሚገባው ቁሳዊ ሀብት ማከማቸት ወይም በንብረታችን መደሰት መሆን እንደሌለበት እየተናገረ ነበር። ከዚህ ይልቅ ሀብታችንን ከይሖዋ ጋር ያለንን ዝምድና ለማሻሻል ወይም ለማጠናከር ልንጠቀምበት ይገባል። ይህን ማድረጋችን በአምላክ ዘንድ ሀብታም እንደሚያደርገን ጥርጥር የለውም። እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው? ከአምላክ የተትረፈረፈ በረከት እንድናገኝ መንገድ ስለሚከፍት ነው። መጽሐፍ ቅዱስ “የእግዚአብሔር በረከት ብልጽግናን ታመጣለች፤ መከራንም አያክልባትም” ይላል።—ምሳሌ 10:22

13. የይሖዋ በረከት “ብልጽግና” የምታመጣው እንዴት ነው?

13 ይሖዋ ለሕዝቡ በረከቱን ሲያፈስ ሁልጊዜ የሚሰጣቸው ምርጡን ነው። (ያዕቆብ 1:17) ለምሳሌ ያህል፣ ለእስራኤላውያን የሰጣቸው ‘ምድር ማርና ወተት የምታፈስ’ ነበረች። የግብጽ ምድርም በዚህ መንገድ ተገልጾ የነበረ ቢሆንም ይሖዋ ለእስራኤላውያን የሰጣቸው ምድር ግን ቢያንስ በአንድ ወሳኝ መንገድ የተለየች ነበረች። ሙሴ ለእስራኤላውያን “ይህች ምድር አምላክህ እግዚአብሔር የሚንከባከባት . . . ናት” ብሏቸው ነበር። በሌላ አባባል ሕዝቡ፣ ይሖዋ ይንከባከባቸው ስለነበር ባለጠጎች ነበሩ። እስራኤላውያን ለይሖዋ ታማኝ ሆነው እስከቀጠሉ ድረስ ይሖዋ አትረፍርፎ ይባርካቸው የነበረ ሲሆን በዙሪያቸው ከሚገኙት ብሔራት ሁሉ የተሻለ ሕይወት እንዳላቸው በግልጽ ይታይ ነበር። በእርግጥም የይሖዋ በረከት “ብልጽግናን” ታመጣለች!—ዘኍልቍ 16:13፤ ዘዳግም 4:5-8፤ 11:8-15

14. በአምላክ ዘንድ ሀብታም የሆኑ ሰዎች ምን ያገኛሉ?

14 ‘በአምላክ ዘንድ ሀብታም መሆን’ የሚለው አገላለጽ ‘በአምላክ ፊት ሀብታም መሆን’ (ቱዴይስ ኢንግሊሽ ቨርሽን) ወይም ‘በአምላክ ዓይን ሀብታም መሆን’ (በጄ. ቢ. ፊሊፕስ የተዘጋጀው ዘ ኒው ቴስታመንት ኢን ሞደርን ኢንግሊሽ) ተብሎም ተተርጉሟል። በቁሳዊ ነገሮች ረገድ ሀብታም የሆኑ ሰዎች በአብዛኛው ሌሎች ስለ እነሱ ያላቸው አመለካከት ያሳስባቸዋል። ይህ ደግሞ ብዙ ጊዜ በአኗኗራቸው ይንጸባረቃል። በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተገለጸው ዓይነት “የኑሮ ትምክሕት” ወይም ኑሮዬ ይታይልኝ የሚል መንፈስ በማንጸባረቅ ሰዎችን ለማስደመም ይፈልጋሉ። (1 ዮሐንስ 2:16) ከዚህ በተቃራኒ ግን በአምላክ ዘንድ ሀብታም የሆኑ ሰዎች፣ በይሖዋ ዘንድ ተቀባይነትና ሞገስ የሚያገኙ ከመሆኑም በላይ ከእሱ ጋር የቅርብ ዝምድና ይመሠርታሉ፤ እሱም ይገባናል የማንለውን ደግነቱን በላቀ መንገድ ያሳያቸዋል። ይህ ዓይነቱ ውድ ዝምድና ማንኛውም ቁሳዊ ሀብት ሊያስገኝ ከሚችለው በላይ አስተማማኝና ደስተኛ ሕይወት ለማግኘት እንደሚያስችላቸው ጥርጥር የለውም። (ኢሳይያስ 40:11) አሁን የሚነሳው ጥያቄ፣ በአምላክ ዓይን ሀብታም ለመሆን ምን ማድረግ ይኖርብናል? የሚል ነው።

በአምላክ ዘንድ ሀብታም መሆን የሚቻለው እንዴት ነው?

15. በአምላክ ዘንድ ሀብታም ለመሆን ምን ማድረግ ይኖርብናል?

15 ኢየሱስ በተናገረው ምሳሌ ላይ ሀብታሙ ሰው ዕቅድ ያወጣውና የሠራው ራሱን ለማበልጸግ ብቻ ስለነበር ሞኝ ተብሎ ተጠርቷል። በመሆኑም በአምላክ ዘንድ ሀብታም ለመሆን በእሱ ዓይን ዋጋ ባላቸው ሥራዎች በትጋት መካፈልና የተሟላ ተሳትፎ ለማድረግ መጣር አለብን። ከእነዚህ ሥራዎች መካከል ኢየሱስ “ሂዱና ሕዝቦችን ሁሉ . . . ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው” በማለት የሰጠው ተልእኮ ይገኝበታል። (ማቴዎስ 28:19) ጊዜያችንን፣ ጉልበታችንንና ተሰጥዎቻችንን ኑሯችንን ለማሻሻል ሳይሆን ስለ አምላክ መንግሥት ለመስበክና ደቀ መዛሙርት ለማድረግ መጠቀም፣ ሀብታችንን ለአንድ ተግባር ከማዋል ጋር ሊመሳሰል ይችላል። ከዚህ ቀጥሎ ያሉት ተሞክሮዎች እንደሚያሳዩት እንዲህ ያደረጉ ሰዎች በመንፈሳዊ ብዙ ትርፍ አግኝተዋል።—ምሳሌ 19:17

16, 17. በአምላክ ዓይን ሀብታም የሚያደርገው ምን ዓይነት አኗኗር እንደሆነ የሚያሳዩ ምን ተሞክሮዎች መናገር ትችላለህ?

16 የኮምፒውተር ቴክኒሽያን ሆኖ ይሠራ የነበረን የአንድ ክርስቲያን ሁኔታ እንመልከት። ይህ ወንድም ዳጎስ ያለ ደመወዝ ይከፈለው የነበረ ቢሆንም ሥራው ጊዜውን በሙሉ ስለሚይዝበት በመንፈሳዊ እንደደከመ ይሰማው ነበር። በዚህም ምክንያት፣ በሥራው ከፍተኛ ደረጃ ለመድረስ ከመሞከር ይልቅ በመንፈሳዊ ለሚያስፈልጉት ነገሮችና ለክርስቲያናዊ ኃላፊነቶቹ የበለጠ ጊዜ ለማግኘት ሲል ሥራውን አቁሞ አይስክሬም እየሠራ መንገድ ላይ መሸጥ ጀመረ። የቀድሞ የሥራ ባልደረቦቹ ቢያሾፉበትም ወንድም እንዲህ ብሏል:- “የሚገርመው ነገር፣ በገንዘብ ረገድ በቀድሞው ሥራዬ አገኘው ከነበረው የተሻለ ገቢ አለኝ። አሁን እንደ ድሮው ውጥረትና ጭንቀት ስለሌለብኝ ይበልጥ ደስተኛ ነኝ። ከሁሉም በላይ ደግሞ ወደ ይሖዋ የበለጠ እንደቀረብኩ ሆኖ ይሰማኛል።” ይህ ክርስቲያን ወንድም ያደረገው ለውጥ ወደ ሙሉ ጊዜ አገልግሎት እንዲገባ ያስቻለው ሲሆን በአሁኑ ጊዜ በአገሩ በሚገኘው የይሖዋ ምሥክሮች ቅርንጫፍ ቢሮ ውስጥ ያገለግላል። በእርግጥም የይሖዋ በረከት “ብልጽግናን ታመጣለች።”

17 ሌላዋ ምሳሌ የምትሆነን ደግሞ ለትምህርት ከፍተኛ ቦታ በሚሰጥ ቤተሰብ ውስጥ ያደገች ሴት ናት። በፈረንሳይ፣ በሜክሲኮና በስዊዘርላንድ በሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ የተማረች ሲሆን ጥሩ ሥራ የማግኘት አጋጣሚም ነበራት። “በሕይወቴ ስኬታማ ነበርኩ፤ በኅብረተሰቡ ዘንድ እከበር የነበረ ከመሆኑም ሌላ ለየት ያሉ አጋጣሚዎች አገኝ ነበር። ያም ሆኖ ግን ባዶነት ይሰማኝ ነበር፤ እንዲሁም ውስጣዊ እርካታ አልነበረኝም” በማለት ተናግራለች። ከዚያም ስለ ይሖዋ ተማረች። ይህች ሴት እንዲህ ብላለች:- “በመንፈሳዊ እድገት እያደረግኩ ስሄድ እሱን ለማስደሰትና በጥቂቱም ቢሆን አመስጋኝነቴን ለመግለጽ ያለኝ ፍላጎት ምን ማድረግ እንዳለብኝ እንድገነዘብ ይኸውም እሱን በሙሉ ጊዜ ለማገልገል እንድነሳሳ አደረገኝ።” ሰብዓዊ ሥራዋን ከለቀቀች ብዙም ሳይቆይ ተጠመቀች። ላለፉት 20 ዓመታት በሙሉ ጊዜ አገልግሎት በደስታ ስትካፈል ቆይታለች። “አንዳንዶች ችሎታዬን እንዳባከንኩት ይሰማቸዋል። በሌላ በኩል ግን ደስተኛ እንደሆንኩ ይመለከታሉ፤ እንዲሁም የምመራባቸውን መሠረታዊ ሥርዓቶች ያደንቃሉ። ይሖዋ ትሑት ሆኜ በእሱ ዘንድ ተቀባይነት ማግኘት እንድችል እንዲረዳኝ በየዕለቱ ወደ እሱ እጸልያለሁ” በማለት ተናግራለች።

18. እኛም እንደ ጳውሎስ በአምላክ ዘንድ ሀብታም ልንሆን የምንችለው እንዴት ነው?

18 ቀድሞ ሳውል ተብሎ ይጠራ የነበረው ሐዋርያው ጳውሎስ ጥሩ ሥራ የማግኘት አጋጣሚ ነበረው። ሆኖም ከጊዜ በኋላ እንዲህ ሲል ጽፏል:- “ለእርሱ ብዬ ሁሉን ነገር የተውሁለትን፣ ወደር የሌለውን ጌታዬን ክርስቶስ ኢየሱስን ከማወቅ ታላቅነት ጋር ሳነጻጽር፣ ሁሉንም ነገር እንደ ጒድለት እቈጥረዋለሁ።” (ፊልጵስዩስ 3:7, 8) ጳውሎስ፣ በክርስቶስ በኩል ያገኘው ሀብት ዓለም ሊያቀርብለት ከሚችለው ከማንኛውም ነገር ይበልጥበት ነበር። እኛም በተመሳሳይ ማንኛውንም የራስ ወዳድነት ምኞት በማስወገድና ለአምላክ ያደርን ሆነን በመኖር በአምላክ ዘንድ ሀብታም መሆን እንችላለን። የአምላክ ቃል “ትሕትናና እግዚአብሔርን መፍራት፣ ሀብትን፣ ክብርንና ሕይወትን ያስገኛል” የሚል ማረጋገጫ ይሰጠናል።—ምሳሌ 22:4

ልታብራራ ትችላለህ?

• በኢየሱስ ምሳሌ ላይ የተጠቀሰው ሰው ምን ችግር አጋጥሞት ነበር?

• በምሳሌው ላይ የተገለጸው ሰው ሞኝ የተባለው ለምንድን ነው?

• በአምላክ ዘንድ ሀብታም መሆን ሲባል ምን ማለት ነው?

• በአምላክ ዘንድ ሀብታም መሆን የምንችለው እንዴት ነው?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ሀብታሙ ሰው ሞኝ ተብሎ የተጠራው ለምን ነበር?

[በገጽ 27 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

እድገት ለማግኘት የሚያስችሉ አጋጣሚዎች ከባድ ፈተና ሊሆኑብን የሚችሉት እንዴት ነው?

[በገጽ 28 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

“የእግዚአብሔር በረከት ብልጽግናን ታመጣለች”