በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በጆርጂያ በአንድ የአውራጃ ስብሰባ ላይ የተከናወኑ ሁለት “ተአምራት”

በጆርጂያ በአንድ የአውራጃ ስብሰባ ላይ የተከናወኑ ሁለት “ተአምራት”

በጆርጂያ በአንድ የአውራጃ ስብሰባ ላይ የተከናወኑ ሁለት “ተአምራት”

በ2006 በጆርጂያ ሁለት ተአምራት የተፈጸሙበት የማይረሳ ክንውን ታይቶ ነበር። “መዳናችን ቀርቧል!” የተባለው የይሖዋ ምሥክሮች የአውራጃ ስብሰባ ከሐምሌ 7 እስከ 9 ባሉት ሦስት ቀናት ውስጥ በአገሪቱ በጠቅላላ በስድስት ቦታዎች ተከናውኗል። በዚህ መንፈሳዊ ድግስ ላይ ወደ 17,000 የሚጠጉ ተሰብሳቢዎች ተገኝተዋል።

በጥር ወር 2006 የጆርጂያ ዋና ከተማ በሆነችው በተብሊሲ በሚደረገው የአውራጃ ስብሰባ ላይ የሚገኙትን በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች የሚይዝ ምቹ ቦታ ለማግኘት ጥረት ማድረግ ተጀመረ። የአውራጃ ስብሰባው የሚካሄድባቸው ሌሎች ቦታዎች ደግሞ በተብሊሲ ዋናው ስብሰባ ከሚደረግበት ቦታ ጋር በስልክ አማካኝነት እንዲገናኙ ይደረጋል።

ባለፉት ዓመታት ውስጥ በጆርጂያ የአምልኮ ነፃነት ቀስ በቀስ ተገኝቷል። በዚህ ምክንያት ወንድሞች ቀደም ባሉት ዓመታት በብዙ ቦታዎች ተቃውሞ ያጋጠማቸው ቢሆንም በዋና ከተማዋ ውስጥ የአውራጃ ስብሰባ የሚያደርጉበት ቦታ እንደሚያገኙ በመተማመን ፍለጋቸውን ተያያዙት። የጆርጂያ ሕዝብ ወዳጃዊ መንፈስ ያለውና እንግዳ ተቀባይ ቢሆንም አንዳንድ ባለ ሥልጣናት ለሃይማኖት ሥር የሰደደ መሠረተ ቢስ ጥላቻ አላቸው። ታዲያ እነዚህ ባለ ሥልጣናት ይህን ጥላቻቸውን ዋጥ አድርገው የይሖዋ ምሥክሮች መሰብሰቢያ ቦታ እንዲከራዩ ይፈቅዱላቸው ይሆን?

በአውራጃ ስብሰባው ኮሚቴ ውስጥ የሚሠሩት ወንድሞች የሚሰበሰቡበት ቦታ ለማግኘት የተለያዩ ስታዲየሞችንና ሰፊ የስፖርት አዳራሾችን ተመለከቱ። የእነዚህ ቦታዎች ሥራ አስኪያጆች፣ የይሖዋ ምሥክሮች በቦታው ሊጠቀሙ እንደሚችሉ ቃል ቢገቡም ወንድሞች ቦታውን የሚፈልጉበትን ቀን ሲነግሯቸው ግን ሊያከራዩዋቸው ፈቃደኞች አልነበሩም። በመሆኑም በተብሊሲ የሚገኘው የሙዚቃ ትርዒት የሚታይበት አዳራሽ አስተዳደር፣ የይሖዋ ምሥክሮች አዳራሹን እንዲከራዩ ሲፈቅድ የአውራጃ ስብሰባው ኮሚቴ በጣም ተገረመ። አዳራሹ የሚገኘው መሃል ከተማ ሲሆን ታላላቅ ዝግጅቶች የሚከናወኑት በዚህ ቦታ ነው።

የኮሚቴው አባላት ያደረጉት ጥረት የተፈለገውን ውጤት ማስገኘቱ ስላበረታታቸው በተብሊሲም ሆነ በመላ አገሪቱ በሚገኙ ሌሎች ከተሞች የሚካሄዱትን የአውራጃ ስብሰባዎች ማደራጀት ጀመሩ፤ ስብሰባው ከሚካሄድባቸው ሌሎች ከተሞች መካከል ስኖሪ፣ ኩታኢሲ፣ ዙግዲዲ፣ ካስፒና ጎሪ ይገኙበታል። ወንድሞች ፕሮግራሙን በተመሳሳይ ሰዓት ለማድረግ እንዲቻል ስብሰባው የሚካሄድባቸውን እነዚህን ቦታዎች በስልክ ለማገናኘት ብዙ ደክመዋል። ለስብሰባው ሁሉም ነገር ተዘጋጅቶ ነበር። ሆኖም ስብሰባው ሊጀምር አንድ ሳምንት ሲቀረው የተብሊሲ የሙዚቃ ትርዒት አዳራሽ አስተዳደር ምንም ምክንያት ሳይሰጥ ውሉን በድንገት አፈረሰው።

የመጀመሪያው “ተአምር”

ወንድሞች በዚህ አጭር ጊዜ ውስጥ ምን ማድረግ ይችላሉ? ያላቸው ብቸኛ አማራጭ ከተብሊሲ 40 ኪሎ ሜትር ርቆ ወደሚገኘው ማርነኡሊ የተባለ ከተማ ስብሰባውን ማዛወር ነበር። ማኅበረሰቡ በግብርና ሥራ በሚተዳደርበት በዚህ ከተማ ውስጥ የይሖዋ ምሥክር በሆኑ አንድ ቤተሰብ ቦታ ላይ በርካታ የአውራጃ ስብሰባዎች ሲደረጉ ቆይተዋል። ቦታው በአንድ ወቅት ሰፊ የአትክልት ሥፍራ ነበር። ላለፉት አሥር ዓመታት በተብሊሲ የሚገኙ ጉባኤዎች የአውራጃ ስብሰባ ማድረግ የሚችሉት እዚያ ብቻ ነበር። የይሖዋ ምሥክሮች ከባድ የሕዝብ ዓመጽ ያጋጠማቸውም በማርነኡሊ ከተማ ነበር።

በይሖዋ ምሥክሮች ላይ እንዲህ ዓይነት ጥቃት ከተሰነዘረባቸው ወቅቶች አንዱ መስከረም 16, 2000 ነበር። የማርነኡሊ ከተማ ፖሊሶች፣ ወንድሞች ወደ ስብሰባው ቦታ እንዳይደርሱ ለማድረግ መንገዱን ዘጉባቸው። ከዚያም በመጥፎ ምግባሩ ምክንያት ከቅስና የወረደው ቫሲሊ ምካላቪሽቪሊ የተባለ የኦርቶዶክስ ቄስ የሚመራቸው ዓመጸኞች በአውቶቡሶች ሞልተው ወደ ቦታው መጡ። እነዚህ ዓመጸኞች በማርነኡሊ ወደሚካሄደው ስብሰባ የሚጓዙ መኪኖችንና አውቶቡሶችን አስቁመው በርካታ ተሰብሳቢዎችን ከመኪኖቹ ጎትተው እያወጡ ያለ አንዳች ምሕረት ደበደቧቸው፤ ሌሎች ተሳፋሪዎችን ደግሞ መጽሐፍ ቅዱሶቻቸውንና መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎቻቸውን ጨምሮ ንብረቶቻቸውን ዘረፏቸው።

በማርነኡሊ በሚገኘው መሰብሰቢያ ቦታም 60 ያህል ሰዎች ጥቃት አድርሰዋል። በዚህ ወቅት 40 የሚያህሉ የይሖዋ ምሥክሮች ጉዳት የደረሰባቸው ሲሆን አንድ ወንድም ደረቱ ላይ በቢላዋ ተወግቷል። በወንድሞች ላይ ጥቃት ከሰነዘሩት ሰዎች አንዳንዶቹ በያዙት ሽጉጥ ያስፈራሯቸውና ወደ ሰማይ ይተኩሱ ነበር። ከእነዚህ ሰዎች መካከል አንዱ የእርሻ ቦታው ባለቤት ላይ ሽጉጥ ደግኖ ገንዘቧንና ጌጣጌጦቿን እንድታመጣ ጠየቃት። ዓመጸኞቹ ስብሰባው በሚደረግበት ቦታ በአንደኛው ጥግ ወደሚገኘው ቤቷ ገብተው ምስቅልቅሉን ያወጡት ከመሆኑም በላይ ውድ የሆኑ ንብረቶቿን ዘረፏት። በቤቷ ውስጥ ያሉትን መስኮቶች በሙሉ ከሰባበሩ በኋላ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችንና ለስብሰባው ተብለው የተሠሩ አግዳሚ ወንበሮችን አቃጠሉ። በዚህ ጊዜ አሥራ አምስት ኩንታል የሚመዝኑ ጽሑፎች ወድመዋል። በቦታው የነበሩት ፖሊሶች ረብሻውን ከማስቆም ይልቅ በይሖዋ ምሥክሮች ላይ በተፈጸመው ዓመጽ ተባብረዋል። a

የአውራጃ ስብሰባው ኮሚቴ፣ ወንድሞች እንደዚህ ዓይነቱ ጥቃት እንዳይፈጸምባቸው ከመስጋቱም በላይ ለወትሮው 2,500 ሰዎች የሚይዘው ቦታ ለ5,000 ተሰብሳቢዎች እንዴት ሊበቃ እንደሚችል አሳስቦት ነበር። በዚህ አጭር ጊዜ ውስጥ ይህን ችግር መፍታት የሚቻለው እንዴት ይሆን? በዚህ ጊዜ ስብሰባው ከሚካሄድበት ቦታ አጠገብ ያሉት ሁለት የአትክልት ሥፍራዎች ባለቤት የሆኑት ሰዎች ቦታቸውን ለማከራየት ፈቃደኞች እንደሆኑ ገለጹ፤ ይህ የተአምር ያህል ነበር።

እነዚህን የአትክልት ቦታዎች አመቺ መሰብሰቢያ ማድረጉ ቀላል አልነበረም። የአየሩ ጠባይ ደግሞ ሁኔታውን ይበልጥ አስቸጋሪ አደረገው፤ ከስብሰባው በፊት ሳምንቱን ሙሉ ይዘንብ ነበር። ቦታቸውን ለማከራየት ፈቃደኛ በሆኑት ጎረቤቶች የአትክልት ቦታዎች ላይ ድንች ተተክሎ ስለነበር ድንቹ መሰብሰብ ነበረበት። ኃይለኛ ዝናብ ቢጥልም ፈቃደኛ ሠራተኞች በመጀመሪያ ድንቾቹን ቆፍረው አወጧቸው። ከዚያም አጥሮቹን ካነሱ በኋላ ለፀሐይና ለዝናብ መከላከያ የሚሆን ዳስ ለመሥራት ምሰሶዎች ተከሉ። ከዚህም በላይ ሌሎች የእንጨት አግዳሚ ወንበሮችን መሥራትና ተጨማሪ የድምጽ መሣሪያዎች ማዘጋጀት ያስፈልግ ነበር። ፈቃደኛ ሠራተኞቹ ሌት ተቀን፣ አንዳንዶቹም እንቅልፋቸውንም ጭምር መሥዋዕት አድርገው አስፈላጊ የሆኑትን የእንጨት ሥራዎች በሙሉ ያከናውኑ ነበር።

“ዝናቡ በአውራጃ ስብሰባው ወቅትም ቢቀጥልስ? ጭቃው ተሰብሳቢዎቹን ይውጣቸው ይሆን?” የሚለው ጥያቄ ሁሉንም ሰው አሳስቦት ነበር። በዝናብ የራሰውን መሬት ለመሸፈን ጭድ ተገዛ። በመጨረሻ ግን ፀሐይዋ ወጣች! ስብሰባው በተካሄደባቸው በሦስቱም ቀናት ፀሐይዋ ፍንትው ብላ ወጥታ ነበር።

ተሰብሳቢዎቹ ሲመጡ ቦታው ደስ የሚል ሆኖ ነበር። ከከተማ ወጣ ብሎ የሚገኘው ይህ ሰላማዊ አካባቢ የአዲሱ ዓለም ቅምሻ ይመስል ነበር። ተሰብሳቢዎቹ ምቹ መቀመጫ ከማግኘታቸውም በላይ ዙሪያቸውን በበለስና በሌሎች የፍራፍሬ ዛፎች እንዲሁም በበቆሎና በቲማቲም እርሻዎች ተከብበው ነበር። የመድረኩ ጀርባ ደግሞ በወይን ሐረጎች አጊጦ ነበር። አልፎ አልፎ በፕሮግራሙ መሃል አውራ ዶሮዎች ሲጮኹና ሴት ዶሮዎች ደግሞ እንቁላላቸው በሚሰበሰብበት ጊዜ ሲያስካኩ ይሰማ ነበር። በገጠር አካባቢ የተለመዱ ሌሎች ድምፆችም ይሰሙ የነበረ ቢሆንም ለተሰብሳቢዎቹ ግን ይህ ደስ እንደሚል ለስላሳ ሙዚቃ ሆኖላቸዋል። ተሰብሳቢዎቹ እነዚህ ድምፆች ሐሳባቸውን እንዲሰርቁት ከመፍቀድ ይልቅ ግሩም የሆነውን መጽሐፍ ቅዱሳዊ ፕሮግራም በትኩረት ይከታተሉ ነበር። ሆኖም በዚህ የአውራጃ ስብሰባ ላይ የማይረሳ ትዝታ ጥለው ያለፉት ሁኔታዎች እነዚህ ብቻ አልነበሩም።

ሁለተኛው “ተአምር”

ዓርብ ዕለት በተደረገው ስብሰባ የጠዋቱ ክፍለ ጊዜ ማብቂያ ላይ፣ የይሖዋ ምሥክሮች የበላይ አካል አባል የሆነው ወንድም ጄፍሪ ጃክሰን ሙሉው የአዲስ ዓለም የቅዱሳን መጻሕፍት ትርጉም በጆርጂያ ቋንቋ መውጣቱን ሲገልጽ ተሰብሳቢዎቹ በጣም ተገረሙ። b አብዛኞቹ ተሰብሳቢዎች በዚህ በጣም በመደነቃቸው ዓይኖቻቸው እንባ አቅርረው ነበር። አንድ ቤተሰብ እንዲህ በማለት በደስታ ተናግረዋል:- “ለዚህ ተአምር፣ ይሖዋ ለሠራው ተአምር የተሰማን አድናቆት በቃላት ልንገልጸው ከምንችለው በላይ ነው። በዚህ አጭር ጊዜ ውስጥ ይህን ያህል ብዙ ሥራ መከናወኑ አስደናቂ ነው!”

ታሌንጂሃ በተባለችው ከተማ የምትኖርና ፕሮግራሙን በስልክ ሲተላለፍ ያዳመጠች አንዲት እህት እንዲህ በማለት ተናግራለች:- “ሙሉውን መጽሐፍ ቅዱስ በማግኘታችን የተሰማኝን ደስታ ለመግለጽ ቃላቶች ያጥሩኛል። ለዚህ አስደናቂ የሦስት ቀናት የአውራጃ ስብሰባ ላመሰግናችሁ እፈልጋለሁ። ታሪካዊ ክንውን ነበር።” በምዕራብ ጆርጂያ በጥቁር ባሕር ጠረፍ ላይ የሚገኝ አንድ ጉባኤ አባል የሆነ አንድ ቤተሰብ እንዲህ ብሏል:- “እስከ አሁን ድረስ በቤታችን ውስጥ የሚገኘው አንድ መጽሐፍ ቅዱስ ብቻ ነበር፤ አሁን ግን አራታችንም የየራሳችን የአዲስ ዓለም ትርጉም መጽሐፍ ቅዱስ አለን። አሁን እያንዳንዳችን መጽሐፍ ቅዱስን በግላችን ማጥናት እንችላለን።”

ሆኖም ተሰብሳቢዎቹ ያላዩአቸው አንዳንድ ችግሮች ተፈጥረው ነበር። ለአብነት ያህል፣ ሙሉው የአዲስ ዓለም ትርጉም ለስብሰባው እንዲደርስ በጊዜ ታትሞ ወደ ጆርጂያ ቢላክም የጉምሩክ ባለ ሥልጣናት ወደ ጆርጂያ እንዳይገባ ከለከሉ። ወንድሞች ለእንባ ጠባቂ ቢሮ አቤቱታ በማቅረባቸው ቢሮው ከአውራጃ ስብሰባው በፊት መጽሐፍ ቅዱሶቹን ማስለቀቅ ችሏል። እንዲያውም በዚህ ቢሮ የሚሠራው ግለሰብ ለቢሮው መጽሐፍ ቅዱሶችን እንዲያመጣ ረዳቱን በማርነኡሊ ወደሚደረገው የአውራጃ ስብሰባ ልኮታል።

ሞቅ ያለ አቀባበል፣ የጆርጂያውያን ባሕል

በማርነኡሊ የተከናወነው የአውራጃ ስብሰባ በጆርጂያ ለሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮች የጎላ ቦታ የሚሰጠው ስብሰባ የሆነበት ሌላም ምክንያት ነበር። የይሖዋ ምሥክሮች የበላይ አካል አባል በፕሮግራሙ ላይ በመገኘቱ ተሰብሳቢዎቹ በሙሉ በጣም ስለተደሰቱ እያንዳንዳቸው ሞቅ ያለ ባሕላዊ ሰላምታ ሊያቀርቡለት ፈለጉ። ወንድም ጃክሰን ወንድሞችንና እህቶችን ሰላም ለማለት ለረጅም ሰዓታት መቆም የነበረበት ቢሆንም ይህን በደስታ አድርጎታል።

በ1903 በተደረገ የአውራጃ ስብሰባ ማብቂያ ላይ አንድ ወንድም “ድሃ ብሆንም ከዚህ የአውራጃ ስብሰባ ያገኘሁትን ጥቅም በአንድ ሺህ ዶላር አልለውጠውም” በማለት ተናግሮ ነበር። ወንድም ይህን ከተናገረ ከአንድ ምዕተ ዓመት በላይ ቢያልፍም በ2006 በጆርጂያ በተደረጉት የማይረሱ የአውራጃ ስብሰባዎች ላይ የተገኙት የይሖዋ ምሥክሮችም ተመሳሳይ ስሜት ነበራቸው።

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

a በጆርጂያ በሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮች ላይ ስለደረሰው ስደት ሰፋ ያለ ሐሳብ ለማግኘት የጥር 22, 2002 ንቁ! (እንግሊዝኛ) ገጽ 18-24ን ተመልከት።

b በ2004 የአዲስ ዓለም ትርጉም የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት በጆርጂያ ቋንቋ ተተርጉሞ ወጥቷል።

[በገጽ 19 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

“ታናሽ የሆነው” ጭማሪ አግኝቷል

በኢሳይያስ 60:22 ላይ የሚገኘው የሚከተለው ጥቅስ በጆርጂያ እየተፈጸመ ነው:- “ከአንቺ ታናሽ የሆነው ሺህ፣ ከሁሉም የመጨረሻው ታናሽ ኀያል መንግሥት ይሆናል፤ እኔ እግዚአብሔር ነኝ፤ ጊዜውም ሲደርስ ይህን በፍጥነት አደርጋለሁ።” በጆርጂያ ከ100 በታች የነበረው የመንግሥቱ አስፋፊዎች ቁጥር ከ20 ዓመት ባነሰ ጊዜ ውስጥ ወደ 16,000 ገደማ ደርሷል። እነዚህ ቀናተኛ የአምላክ ቃል አገልጋዮች በየሳምንቱ ወደ 8,000 የሚጠጉ ሰዎችን የሚያስጠኑ ሲሆን ይህም በጆርጂያ ተጨማሪ እድገት እንደሚኖር ይጠቁማል።

[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ ሥዕላዊ መግለጫ/ካርታ]

(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)

የሩስያ ፌደሬሽን

ጆርጂያ

⇨ ዙግዲዲ

⇨ ኩታኢሲ

ማርነኡሊ ⇨ ጎሪ

⇨ ካስፒ

⇨ ስኖሪ

ተብሊሲ

ቱርክ

አርሜኒያ

አዘርባጃን

[ምንጭ]

ሉል:- Based on NASA/Visible Earth imagery

[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በተብሊሲ የሚገኝ ሐውልት

[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በማርነኡሊ የተደረገው የአውራጃ ስብሰባ በሞባይል ስልክ አማካኝነት ወደ ሌሎች አምስት ቦታዎች ተላልፎ ነበር

[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ተሰብሳቢዎቹ ሙሉው “የአዲስ ዓለም ትርጉም” በጆርጂያ ቋንቋ በመውጣቱ በጣም ተደስተዋል