በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

አምላክ ይመለከትሃል?

አምላክ ይመለከትሃል?

አምላክ ይመለከትሃል?

ታላቅ ፈጣሪ የሆነው ይሖዋ ማየት ይችላል? እንዴታ! መጽሐፍ ቅዱስ “ዐይንንስ የሠራ እርሱ አያይምን?” በማለት በግልጽ ይናገራል። (መዝሙር 94:9) የይሖዋ እይታ ከሰው ልጆች በእጅጉ የላቀ ነው። ይሖዋ የሚመለከተው ውጫዊ ገጽታችንን ብቻ ሳይሆን ‘ልባችንንም ይመረምራል’ እንዲሁም ‘ልባችንን ይመዝናል።’ (ምሳሌ 17:3፤ 21:2) በእርግጥም አስተሳሰባችንንና ውስጣዊ ፍላጎቶቻችንን እንዲሁም አንድ ነገር እንድናደርግ የሚገፋፋንን ዝንባሌ የማወቅ ችሎታ አለው።

ይሖዋ፣ በሕይወታችን ውስጥ የሚያጋጥሙንን ችግሮች የሚያውቅ ከመሆኑም በላይ የምናቀርበውን ልመና ይሰማል። መዝሙራዊው እንዲህ በማለት ጽፏል:- “የእግዚአብሔር ዐይኖች ወደ ጻድቃን ናቸው፤ ጆሮዎቹም ለጩኸታቸው ክፍት ናቸው። እግዚአብሔር ልባቸው ለተሰበረ ቅርብ ነው፤ መንፈሳቸው የተሰበረውንም ያድናቸዋል።” (መዝሙር 34:15, 18) ይሖዋ ያለንበትን ሁኔታ እንደሚረዳና ከልብ የምናቀርበውን ልመና እንደሚሰማ ማወቃችን እንዴት ያጽናናል!

ይሖዋ አምላክ በስውር የሚፈጸሙ ድርጊቶችን ሳይቀር ይመለከታል። አዎን፣ “ከእግዚአብሔር ዐይን የተሰወረ ምንም ፍጥረት የለም፤ ስለ ራሳችን መልስ መስጠት በሚገባን በእርሱ ፊት ሁሉም ነገር የተራቈተና የተገለጠ ነው።” (ዕብራውያን 4:13) ስለዚህ ድርጊታችን ጥሩም ይሁን መጥፎ፣ አምላክ ሁሉንም ይመለከታል። (ምሳሌ 15:3) ለምሳሌ ያህል፣ ዘፍጥረት 6:8, 9 ‘ኖኅ በይሖዋ ፊት ሞገስን እንዳገኘና አካሄዱን ከይሖዋ ጋር እንዳደረገ’ ይናገራል። አዎን፣ ኖኅ ታዛዥ በመሆኑና የአምላክን የጽድቅ ሥርዓቶች በመጠበቁ በይሖዋ ፊት ተቀባይነት ያገኘ ከመሆኑም በላይ ተባርኳል። (ዘፍጥረት 6:22) ከዚህ በተቃራኒ ግን በኖኅ ዘመን የነበሩ ሰዎች ዓመጸኞችና በሥነ ምግባር የረከሱ ነበሩ። አምላክም ይህንን ሁኔታ በቸልታ አልተመለከተውም። ይሖዋ “የሰው ዐመፅ በምድር ላይ የበዛና የልቡም ሐሳብ ዘወትር ወደ ክፋት ብቻ ያዘነበለ መሆኑን ተመለከተ።” በመጨረሻም ይሖዋ በክፉዎች ላይ ጥፋት ያመጣ ሲሆን ኖኅንና ቤተሰቡን ግን በሕይወት ጠብቋቸዋል።—ዘፍጥረት 6:5፤ 7:23

ታዲያ ይሖዋ ለአንተንስ ጥሩ አመለካከት አለው? በእርግጥም፣ “በፍጹም ልባቸው የሚታመኑበትን ለማበርታት የእግዚአብሔር ዐይኖች በምድር ሁሉ ላይ ይመለከታሉ።” (2 ዜና መዋዕል 16:9) አምላክ በቅርቡ ከምድር ላይ ክፉዎችን ሁሉ እንደገና የሚያጠፋ ሲሆን ገሮችን ግን ያድናቸዋል።—መዝሙር 37:10, 11