እውነተኛ መንፈሳዊነት—እንዴት ልታገኘው ትችላለህ?
እውነተኛ መንፈሳዊነት—እንዴት ልታገኘው ትችላለህ?
ሐዋርያው ጳውሎስ “የሥጋን ነገር ማሰብ ሞት ነው፤ የመንፈስን ነገር ማሰብ ግን ሕይወትና ሰላም ነው” በማለት ጽፏል። (ሮሜ 8:6) ሐዋርያው እንዲህ ብሎ ሲናገር መንፈሳዊ ሰው መሆን ከግል ምርጫ ወይም ስሜት ያለፈ ነገር እንደሆነ መጠቆሙ ነበር። እንደ እውነቱ ከሆነ ይህ የሕይወትና የሞት ጉዳይ ነው። ሆኖም መንፈሳዊ የሆነ ሰው “ሕይወትና ሰላም” የሚያገኘው እንዴት ነው? መጽሐፍ ቅዱስ፣ እንዲህ ያለው ሰው በአሁኑ ጊዜ ከራሱም ሆነ ከአምላክ ጋር ሰላም እንደሚኖረውና ወደፊት ደግሞ የዘላለም ሕይወት በማግኘት እንደሚባረክ ይናገራል። (ሮሜ 6:23፤ ፊልጵስዩስ 4:7) ኢየሱስ “መንፈሳዊ ነገሮችን የሚጠሙ ደስተኞች ናቸው” ማለቱ አያስገርምም!—ማቴዎስ 5:3 NW
ይህን መጽሔት እያነበብክ መሆንህ በራሱ መንፈሳዊ ፍላጎት እንዳለህ የሚያሳይ ሲሆን ይህ ደግሞ ጥበብ የሚንጸባረቅበት አካሄድ ነው። ሆኖም መንፈሳዊነትን በተመለከተ የተለያየ አመለካከት በመኖሩ ‘እውነተኛ መንፈሳዊነት ምንድን ነው? እንዴትስ ሊገኝ ይችላል?’ ብለህ ትጠይቅ ይሆናል።
“የክርስቶስ አሳብ”
ሐዋርያው ጳውሎስ፣ መንፈሳዊ ሰው መሆን ያለውን አስፈላጊነትና ጠቀሜታ ከመጠቆሙም በተጨማሪ እውነተኛ መንፈሳዊነት ምን ትርጉም እንዳለው ሰፋ ያለ ሐሳብ ሰጥቷል። ጳውሎስ፣ በጥንት የቆሮንቶስ ከተማ ይኖሩ ለነበሩት ክርስቲያኖች በጻፈው ደብዳቤ ላይ መንፈሳዊ ባልሆነ ሰው ማለትም ሥጋዊ ፍላጎቶቹን በሚከተል ግለሰብና በመንፈሳዊ ሰው ማለትም መንፈሳዊ ነገሮችን ከፍ አድርጎ በሚመለከት ግለሰብ መካከል ያለውን ልዩነት ገልጿል። ጳውሎስ እንዲህ ሲል ጽፏል:- “መንፈሳዊ ያልሆነ ሰው ከእግዚአብሔር መንፈስ የሆነውን ነገር ሊቀበል አይችልም፤ ምክንያቱም እንዲህ ያለው ነገር ለእርሱ ሞኝነት ነው።” በሌላ በኩል ግን መንፈሳዊ የሆነ ሰው “የክርስቶስ አሳብ [የ1879 ትርጉም]” አለው።—1 ቆሮንቶስ 2:14-16
አንድ ሰው “የክርስቶስ አሳብ” አለው ሲባል ‘በክርስቶስ ኢየሱስ የነበረውን አስተሳሰብ’ ያንጸባርቃል ማለት ነው። (ሮሜ 15:5 NW፤ ፊልጵስዩስ 2:5) በሌላ አባባል መንፈሳዊ ሰው የሚባለው እንደ ኢየሱስ የሚያስብና ፈለጉን የሚከተል ነው። (1 ጴጥሮስ 2:21፤ 4:1 የ1954 ትርጉም) የአንድ ሰው አስተሳሰብ የክርስቶስን አስተሳሰብ በመሰለ መጠን መንፈሳዊነቱ ይበልጥ ይጠናከራል፤ እንዲሁም “ሕይወትና ሰላም” ማግኘቱ የበለጠ አስተማማኝ ይሆናል።—ሮሜ 13:14
‘የክርስቶስን አሳብ’ ማወቅ የሚቻለው እንዴት ነው?
አንድ ሰው የክርስቶስ አሳብ እንዲኖረው በመጀመሪያ የኢየሱስን አስተሳሰብ ማወቅ አለበት። በመሆኑም መንፈሳዊነትን ለማዳበር የመጀመሪያው እርምጃ ኢየሱስ የሚያስብበትን መንገድ ማወቅ ነው። ይሁንና ከ2,000 ዓመታት በፊት በምድር ላይ ይኖር የነበረን ሰው አስተሳሰብ ማወቅ የምትችለው እንዴት ነው? ለአብነት ያህል፣ በአገርህ ይኖሩ የነበሩ ታዋቂ ሰዎችን ታሪክ ያወቅኸው እንዴት ነው? ስለ እነሱ በማንበብ ሊሆን ይችላል። በተመሳሳይም የኢየሱስን አስተሳሰብ ማወቅ የሚቻልበት ዋናው መንገድ ስለ እሱ የተጻፈውን ታሪክ ማንበብ ነው።—ዮሐንስ 17:3
ስለ ኢየሱስ የሚናገሩ አራት ታሪካዊ ዘገባዎች ያሉ ሲሆን እነዚህም በማቴዎስ፣ በማርቆስ፣ በሉቃስና በዮሐንስ የተጻፉት ወንጌሎች ናቸው። እነዚህን ዘገባዎች በጥንቃቄ ማንበብህ ኢየሱስ የሚያስብበትን መንገድ፣ ውስጣዊ ስሜቱንና ነገሮችን ለማከናወን የሚገፋፋውን ስሜት እንድታውቅ ይረዳሃል። ስለ ኢየሱስ ባነበብከው ነገር ላይ ጊዜ ወስደህ ስታሰላስል ክርስቶስ ምን ዓይነት ሰው እንደነበር በአእምሮህ መሳል ትችላለህ። ራስህን እንደ ክርስቶስ ተከታይ አድርገህ የምትመለከት ቢሆንም እንኳ በዚህ መልኩ ማንበብህና ማሰላሰልህ “በጌታችንና በአዳኛችን በኢየሱስ 2 ጴጥሮስ 3:18
ክርስቶስ ጸጋና ዕውቀት” ማደግህን እንድትቀጥል ይረዳሃል።—ይህንን በአእምሯችን ይዘን ኢየሱስ መንፈሳዊ ሰው እንዲሆን የረዳው ምን እንደሆነ የሚያሳዩ አንዳንድ ሐሳቦችን ከወንጌል ዘገባዎች እንመልከት። ከዚያም ኢየሱስ የተወውን ምሳሌ መኮረጅ የምትችለው እንዴት እንደሆነ ራስህን ጠይቅ።—ዮሐንስ 13:15
መንፈሳዊነትና “የመንፈስ ፍሬ”
የወንጌል ጸሐፊ የሆነው ሉቃስ፣ ኢየሱስ ሲጠመቅ የአምላክ ቅዱስ መንፈስ እንደወረደበትና ኢየሱስም ‘በመንፈስ ቅዱስ እንደተሞላ’ ተናግሯል። (ሉቃስ 3:21, 22፤ 4:1) ኢየሱስ ደግሞ ለተከታዮቹ በአምላክ ቅዱስ መንፈስ የመመራትን አስፈላጊነት አስገንዝቧቸዋል። (ሉቃስ 11:9-13) እንዲህ ማድረጋቸው ይህን ያህል አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? የአምላክ መንፈስ የአንድ ሰው አስተሳሰብ ተለውጦ የክርስቶስ አሳብ እንዲኖረው የማድረግ ኃይል ስላለው ነው። (ሮሜ 12:1, 2) መንፈስ ቅዱስ አንድ ሰው እንደ “ፍቅር፣ ደስታ፣ ሰላም፣ ትዕግሥት፣ ቸርነት፣ በጎነት፣ ታማኝነት፣ ገርነት፣ ራስን መግዛት” የመሳሰሉ ባሕርያትን እንዲያፈራ ይረዳዋል። መጽሐፍ ቅዱስ “የመንፈስ ፍሬ” በማለት የሚጠራቸው እነዚህ ባሕርያት የመንፈሳዊ ሰው መለያ ናቸው። (ገላትያ 5:22, 23) በአጭር አነጋገር መንፈሳዊ የሆነ ሰው በአምላክ መንፈስ የሚመራ ነው።
ኢየሱስ በምድራዊ አገልግሎቱ ወቅት የመንፈስ ፍሬ ተብለው የተገለጹትን ባሕርያት አሳይቷል። ኢየሱስ በኅብረተሰቡ ዘንድ ዝቅ ተደርገው የሚታዩ ሰዎችን የያዘበት መንገድ እንደ ፍቅር፣ ቸርነትና በጎነት ያሉት ባሕርያት እንዳሉት በግልጽ ያሳይ ነበር። (ማቴዎስ 9:36) ለምሳሌ ያህል፣ ሐዋርያው ዮሐንስ የዘገበውን አንድ ክንውን እንመልከት። ታሪኩ፣ ኢየሱስ “በመንገድ ሲያልፍም ከተወለደ ጀምሮ ዐይነ ስውር የሆነ ሰው አየ” ይላል። የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ሰውየውን ያዩት ቢሆንም እንደ ኃጢአተኛ ቆጥረውት ነበር። ደቀ መዛሙርቱ “ኀጢአት የሠራ ማን ነው? እርሱ ራሱ ወይስ ወላጆቹ?” ብለው ጠየቁ። ጎረቤቶቹም ቢሆኑ ስለ ሰውየው ሲያስቡ የሚመጣላቸው ለማኝ መሆኑ ብቻ ስለነበር “ይህ ሰው ተቀምጦ ሲለምን የነበረው አይደለምን?” ብለዋል። ኢየሱስ ግን ይህን ዐይነ ስውር የተመለከተው እርዳታ እንደሚያስፈልገው ግለሰብ አድርጎ ስለነበር ዐይነ ስውሩን ካነጋገረው በኋላ ፈወሰው።—ዮሐንስ 9:1-8
ይህ ክንውን ስለ ክርስቶስ አስተሳሰብ ምን ያስተምርሃል? በመጀመሪያ ደረጃ ኢየሱስ ዝቅ ተደርገው የሚታዩ ሰዎችን ከመናቅ ይልቅ ርኅራኄ አሳይቷቸዋል። በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ ሰዎችን ለመርዳት ቅድሚያውን ወስዷል። ታዲያ ኢየሱስ የተወውን ምሳሌ እየተከተልክ እንዳለህ ይሰማሃል? ኢየሱስ ለሰዎች ያለው ዓይነት አመለካከት በማዳበር የሰዎች ሕይወት እንዲሻሻልና የወደፊቱ ጊዜያቸው ብሩህ እንዲሆን ለማድረግ ትጥራለህ? ወይስ ታዋቂ ለሆኑ ሰዎች በማዳላት ዝቅ ተደርገው የሚታዩትን ትንቃለህ? ኢየሱስ ለሰዎች ያለው አመለካከት ካለህ የእሱን ምሳሌ እየተከተልክ ነው ማለት ይቻላል።—መዝሙር 72:12-14
መንፈሳዊነትና ጸሎት
ኢየሱስ ዘወትር ወደ አምላክ ይጸልይ እንደነበር የወንጌል ዘገባዎች ይነግሩናል። (ማርቆስ 1:35፤ ሉቃስ 5:16፤ 22:41) በምድራዊ አገልግሎቱ ወቅት ለጸሎት ጊዜ ይመድብ ነበር። ደቀ መዝሙሩ ማቴዎስ “ሕዝቡን ካሰናበተ በኋላም [ኢየሱስ] ለመጸለይ ብቻውን ወደ ተራራ ወጣ” በማለት ጽፏል። (ማቴዎስ 14:23) ኢየሱስ በሰማይ ከሚገኘው አባቱ ጋር በዚህ መንገድ መነጋገሩ ጥንካሬ እንዲያገኝ ረድቶታል። (ማቴዎስ 26:36-44) በዛሬው ጊዜም መንፈሳዊ የሆኑ ሰዎች ከአምላክ ጋር የሚነጋገሩባቸውን አጋጣሚዎች ለማግኘት ይጥራሉ፤ ምክንያቱም እንዲህ ማድረጋቸው ከፈጣሪያቸው ጋር ያላቸውን ግንኙነት እንደሚያጠናክርላቸውና አስተሳሰባቸው ይበልጥ የክርስቶስን አሳብ እንዲመስል እንደሚረዳቸው ያውቃሉ።
ኢየሱስ በአብዛኛው ረዘም ላለ ጊዜ ይጸልይ ነበር። (ዮሐንስ 17:1-26) ለምሳሌ ያህል፣ ሐዋርያቱ የሚሆኑትን 12 ሰዎች ከመምረጡ በፊት “ሊጸልይ ወደ ተራራ ወጣ፤ ሌሊቱንም ሁሉ ወደ እግዚአብሔር ሲጸልይ አደረ” የሚል ዘገባ እናገኛለን። (ሉቃስ 6:12) መንፈሳዊ የሆኑ ሰዎች የግድ ሌሊቱን ሙሉ ባይጸልዩም የኢየሱስን ምሳሌ ይከተላሉ። በሕይወታቸው ውስጥ ከበድ ያሉ ውሳኔዎችን ከማድረጋቸው በፊት፣ መንፈስ ቅዱስ መንፈሳዊነታቸውን ሊያሻሽል የሚችል ውሳኔ ለማድረግ እንዲረዳቸው ስለሚፈልጉ ሰፋ ያለ ጊዜ ወስደው ወደ አምላክ ይጸልያሉ።
ከዚህም በላይ ኢየሱስ ያቀረባቸው ጸሎቶች ከልብ የመነጩ ነበሩ፤ እኛም በዚህ ረገድ ልንመስለው ይገባል። ሉቃስ፣ ኢየሱስ ከመሞቱ በፊት ባለው ምሽት ላይ እንዴት እንደጸለየ ሲገልጽ እንዲህ ብሏል:- “እጅግ ተጨንቆም በብርቱ ይጸልይ ነበር፤ ላቡም እንደ ደም ነጠብጣብ ወደ ምድር ይፈስ ነበር።” (ሉቃስ 22:44) ኢየሱስ ከዚያ በፊትም አጥብቆ ይጸልይ የነበረ ቢሆንም በዚህ ወቅት በምድራዊ ሕይወቱ ካጋጠሙት ሁሉ የሚበልጥ ከባድ ፈተና ስለተደቀነበት “በብርቱ” ጸልዮአል፤ ጸሎቱም ተሰምቶለታል። (ዕብራውያን 5:7) መንፈሳዊ አመለካከት ያላቸው ሰዎች የኢየሱስን ምሳሌ ይከተላሉ። ከባድ ፈተናዎች ሲያጋጥሟቸው መመሪያና እርዳታ እንዲሁም መንፈስ ቅዱስ ለማግኘት ወደ አምላክ “በብርቱ” ይጸልያሉ።
ኢየሱስ የጸሎት ሰው እንደነበረ ግልጽ ነው፤ በመሆኑም ደቀ መዛሙርቱ በዚህ ረገድ እሱን ለመኮረጅ መፈለጋቸው ምንም አያስደንቅም። በዚህም የተነሳ “መጸለይን አስተምረን” ብለው ጠይቀውት ነበር። (ሉቃስ 11:1) በተመሳሳይም በዛሬው ጊዜ መንፈሳዊ ነገሮችን ከፍ አድርገው የሚመለከቱና በአምላክ ቅዱስ መንፈስ ለመመራት የሚፈልጉ ሰዎች ለአምላክ በሚያቀርቡት ጸሎት ረገድ የኢየሱስን ምሳሌ ይኮርጃሉ። በመሆኑም እውነተኛ መንፈሳዊነትና ጸሎት የማይነጣጠሉ ነገሮች ናቸው።
መንፈሳዊነትና ምሥራቹን መስበክ
በማርቆስ ወንጌል ላይ ኢየሱስ በርካታ ሕመምተኞችን እስከ ምሽት ድረስ እንደፈወሰ የሚገልጽ ዘገባ እናገኛለን። በነጋታው ገና ጎህ ሳይቀድ ብቻውን ሆኖ እየጸለየ ሳለ ሐዋርያቱ መጡና ብዙ ሰዎች እየፈለጉት እንደሆነ ነገሩት፤ እነዚህ ሰዎች ለመፈወስ ፈልገው ሊሆን ይችላል። ሆኖም ኢየሱስ “ከዚህ ተነሥተን በአቅራቢያ ወዳሉት መንደሮች እንሂድ፤ እዚያም ልስበክ” አላቸው። ከዚያም እንዲህ ያለበትን ምክንያት ሲገልጽ “የመጣሁት ለዚሁ ነውና” ብሏል። (ማርቆስ 1:32-38፤ ሉቃስ 4:43) ኢየሱስ ሰዎችን መፈወሱ አስፈላጊ እንደሆነ ቢሰማውም ዋነኛ ተልእኮው ስለ አምላክ መንግሥት ምሥራች መስበክ ነበር።—ማርቆስ 1:14, 15
ዛሬም ቢሆን ስለ አምላክ መንግሥት መስበክ፣ የክርስቶስ አስተሳሰብ ያላቸው ሰዎች ተለይተው የሚታወቁበት ምልክት ነው። ኢየሱስ ተከታዮቹ ሊሆኑ ለሚፈልጉ በሙሉ የሚከተለውን ትእዛዝ ሰጥቷቸዋል:- “ስለዚህ ሂዱና ሕዝቦችን ሁሉ . . . ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው፤ ያዘዝኋችሁንም ሁሉ እንዲጠብቁ አስተምሯቸው።” (ማቴዎስ 28:19, 20) ከዚህም በተጨማሪ ኢየሱስ “ለሕዝብ ሁሉ ምስክር እንዲሆን፣ ይህ የመንግሥት ወንጌል በዓለም ሁሉ ይሰበካል፤ ከዚያም መጨረሻው ይመጣል” በማለት አስቀድሞ ተናግሯል። (ማቴዎስ 24:14) የስብከቱ ሥራ የሚከናወነው በመንፈስ ቅዱስ ኃይል እንደሆነ የአምላክ ቃል ስለሚነግረን በዚህ ሥራ በቅንዓት መካፈል እውነተኛ መንፈሳዊ ሰው ተለይቶ የሚታወቅበት ምልክት ነው።—የሐዋርያት ሥራ 1:8
በዓለም ዙሪያ ለሚገኙ ሰዎች ስለ አምላክ መንግሥት የሚናገረውን መልእክት ለመስበክ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች በአንድነት ጥረት ማድረግ ያስፈልጋቸዋል። (ዮሐንስ 17:20, 21) በዚህ ሥራ የሚካፈሉት ሰዎች መንፈሳዊ አመለካከት ሊኖራቸው የሚገባ ከመሆኑም በላይ በዓለም ዙሪያ በደንብ የተደራጁ መሆን ይኖርባቸዋል። አንተስ የክርስቶስን ፈለግ በመከተል የአምላክን መንግሥት ምሥራች በዓለም ዙሪያ የሚሰብኩት እነማን እንደሆኑ መለየት ትችላለህ?
መንፈሳዊ ሰው ለመሆን የሚያስችሉህን ብቃቶች እያሟላህ ነው?
እርግጥ ነው፣ እውነተኛ መንፈሳዊ የሆነን ሰው ለመለየት የሚያስችሉ ሌሎች ምልክቶችም አሉ፤ ሆኖም አንተ እስካሁን የተገለጹትን ብቃቶች እያሟላህ ነው? ይህንን ለማወቅ እንደሚከተለው በማለት ራስህን ጠይቅ:- ‘የአምላክ ቃል የሆነውን መጽሐፍ ቅዱስን ዘወትር አነባለሁ? ባነበብኩት ነገር ላይስ አሰላስላለሁ? የመንፈስ ፍሬን በአኗኗሬ አሳያለሁ? የጸሎት ሰው ነኝ? በዓለም ዙሪያ የአምላክን መንግሥት ምሥራች ከሚሰብኩት ሰዎች ጋር ለመተባበር እፈልጋለሁ?’
ራስህን በሐቀኝነት መመርመርህ የመንፈሳዊነትህን ጥልቀት ለማወቅ ሊረዳህ ይችላል። “ሕይወትና ሰላም” ማግኘት እንድትችል አሁኑኑ አስፈላጊ የሆኑትን እርምጃዎች እንድትወስድ እናበረታታሃለን።—ሮሜ 8:6፤ ማቴዎስ 7:13, 14፤ 2 ጴጥሮስ 1:5-11
[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]
የመንፈሳዊነት መለያ ምልክቶች
◆ የአምላክን ቃል መውደድ
◆ የመንፈስ ፍሬ ማፍራት
◆ ወደ አምላክ አዘውትሮ ከልብ የመነጨ ጸሎት ማቅረብ
◆ የአምላክን መንግሥት ምሥራች ለሰዎች ማካፈል
[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
መጽሐፍ ቅዱስ ‘የክርስቶስን አሳብ’ ለማወቅ ይረዳሃል