በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

‘ከስግብግብነት ሁሉ ራሳችሁን ጠብቁ’

‘ከስግብግብነት ሁሉ ራሳችሁን ጠብቁ’

‘ከስግብግብነት ሁሉ ራሳችሁን ጠብቁ’

‘የሰው ሕይወቱ በሀብቱ ብዛት የተመሠረተ አይደለም።’—ሉቃስ 12:15

1, 2. (ሀ) በዛሬው ጊዜ ሰዎች ትኩረት የሚያደርጉባቸውን ነገሮች በተመለከተ ምን ታዝበሃል? (ለ) እንዲህ ዓይነቱ አመለካከት ምን ተጽዕኖ ሊያሳድርብን ይችላል?

 ብዙ ሰዎች የስኬት መለኪያ ወይም አስተማማኝ የወደፊት ሕይወት ለማግኘት ዋስትና እንደሆኑ አድርገው ከሚያስቧቸው ነገሮች መካከል ገንዘብ፣ ንብረት፣ ዝና፣ ዳጎስ ያለ ደመወዝ የሚያስገኝ ሥራና ቤተሰብ መመሥረት ይገኙበታል። ሀብታምም ሆነ ድሃ በሆኑ አገሮች ውስጥ የሚኖሩ ብዙ ሰዎች ትኩረት የሚያደርጉት በቁሳዊ ነገሮችና በስኬት ላይ ሲሆን እነዚህንም ለማግኘት ሲሯሯጡ ይታያሉ። በሌላ በኩል ግን እነዚህ ሰዎች ለመንፈሳዊ ነገሮች ምንም ፍላጎት ላይኖራቸው ይችላል፤ የተወሰነ ፍላጎት ቢኖራቸው እንኳ እሱም እየጠፋ ነው።

2 ይህ ደግሞ መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚከተለው በማለት አስቀድሞ የተናገረው ትንቢት ፍጻሜ ነው:- “በመጨረሻው ዘመን የሚያስጨንቅ ጊዜ [ይመጣል]። ሰዎች ራሳቸውን የሚወዱ ይሆናሉ፤ ገንዘብን የሚወዱ፣ . . . ከእግዚአብሔር ይልቅ ተድላን የሚወዱ ይሆናሉና። ሃይማኖታዊ መልክ አላቸው፤ ኀይሉን ግን ክደዋል።” (2 ጢሞቴዎስ 3:1-5) እውነተኛ ክርስቲያኖች እንደዚህ ዓይነት አመለካከት ባላቸው ሰዎች መካከል ስለሚኖሩ ይህ ዓይነቱን አስተሳሰብና አኗኗር እንዲከተሉ ሁልጊዜ ተጽዕኖ ይደረግባቸዋል። ዓለም እኛን ‘በራሱ መልክ ለመቅረጽ’ የሚያደርገውን ጥረት ለመቋቋም ምን ሊረዳን ይችላል?—ሮሜ 12:2 በጄ ቢ ፊሊፕስ የተዘጋጀው ዘ ኒው ቴስታመንት ኢን ሞደርን ኢንግሊሽ

3. ኢየሱስ የሰጠውን የትኛውን ምክር እንመለከታለን?

3 “የእምነታችን ጀማሪና ፍጹም አድራጊ” የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ በዚህ ረገድ ጠቃሚ ትምህርት ሰጥቶናል። (ዕብራውያን 12:2) በአንድ ወቅት ኢየሱስ፣ ለሕዝቡ መንፈሳዊነትን የሚያጎለብት ትምህርት እየሰጠ ሳለ አንድ ሰው በንግግሩ መሃል ገብቶ “መምህር ሆይ፤ ወንድሜ ውርስ እንዲያካፍለኝ ንገረው” በማለት ጠየቀው። ኢየሱስ በምላሹ ለሰውየውም ሆነ በቦታው ለተሰበሰቡት ሰዎች በሙሉ ጠንከር ያለ ምክር ሰጠ። ከስግብግብነት እንዲርቁ ከበድ ያለ ማስጠንቀቂያ ከመስጠቱም በላይ ይህንን የሚያጠናክር ትኩረት የሚስብ ምሳሌ ነገራቸው። እኛም ኢየሱስ በዚያ ወቅት የተናገረውን ነገር በቁም ነገር መመልከትና ይህንን ምክር በሕይወታችን ውስጥ ተግባራዊ በማድረግ እንዴት እንደምንጠቀም ማሰብ ይኖርብናል።—ሉቃስ 12:13-21

ተገቢ ያልሆነ ጥያቄ

4. ሰውየው በኢየሱስ ንግግር መሃል ጣልቃ ገብቶ ጥያቄ ማቅረቡ ተገቢ ያልነበረው ለምንድን ነው?

4 ይህ ሰው በኢየሱስ ንግግር መሃል ጣልቃ ገብቶ ጥያቄ ከማቅረቡ በፊት ኢየሱስ፣ ለደቀ መዛሙርቱና ለተሰበሰቡት ሰዎች ከግብዝነት ስለ መራቅና በድፍረት ለሰው ልጅ ስለ መመሥከር እንዲሁም ከመንፈስ ቅዱስ እርዳታ ስለ ማግኘት እየነገራቸው ነበር። (ሉቃስ 12:1-12) እነዚህ ሐሳቦች ደቀ መዛሙርቱ በቁም ነገር ሊመለከቷቸው የሚገቡ አስፈላጊ ትምህርቶች እንደሆኑ ጥርጥር የለውም። ሆኖም ኢየሱስ ራሳቸውን እንዲመረምሩ የሚያነሳሳ እንዲህ ያለ ትምህርት እየሰጠ ሳለ ሰውየው ጣልቃ ገብቶ ከቁሳዊ ንብረት ጋር በተያያዘ በቤተሰቡ መካከል የተፈጠረውን ውዝግብ ክርስቶስ እንዲፈታለት ጠየቀው። እኛም ከዚህ ክንውን ጠቃሚ ትምህርት ማግኘት እንችላለን።

5. ሰውየው ካቀረበው ጥያቄ አንጻር ስለ እሱ ምን ማለት እንችላለን?

5 “አንድ ሰው ሃይማኖታዊ ምክር እያዳመጠ እያለ የሚያስበው ነገር አብዛኛውን ጊዜ ማንነቱን ይጠቁማል” ይባላል። ኢየሱስ በጣም አስፈላጊ ስለሆኑ መንፈሳዊ ነገሮች በሚናገርበት ወቅት ሰውየው ቁሳዊ ጥቅም እንዴት ማግኘት እንደሚችል እያሰበ የነበረ ይመስላል። ግለሰቡ ውርሱን ለመካፈል ሕጋዊ መብት ይኑረው ወይም አይኑረው የተገለጸ ነገር የለም። ኢየሱስ በሰብዓዊ ጉዳዮች ረገድ ጥበበኛ ፈራጅ መሆኑ ስለሚነገርለትና ሥልጣን ስላለው፣ ይህ ሰው በዚህ ሊጠቀም ፈልጎ ሊሆን ይችላል። (ኢሳይያስ 11:3, 4፤ ማቴዎስ 22:16) ሰውየው ለኢየሱስ እንዲህ ዓይነት ጥያቄ ያቀረበበት ምክንያት ምንም ይሁን ምን ጥያቄው፣ ግለሰቡ ትክክለኛ የልብ ዝንባሌ እንዳልነበረው ይኸውም ለመንፈሳዊ ነገሮች አድናቆት እንደጎደለው ያሳያል። ታዲያ እኛስ ራሳችንን መመርመራችን አስፈላጊ እንደሆነ ይህ ሁኔታ አያሳይም? ለምሳሌ ያህል፣ በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ አእምሯችን እንዲባዝን መፍቀድ ወይም ከስብሰባው በኋላ ስለምናደርጋቸው ነገሮች ማውጠንጠን ቀላል ሊሆን ቢችልም እንዲህ ከማድረግ ይልቅ ትምህርቱን በትኩረት ማዳመጥና እንዴት በተግባር እንደምናውለው ማሰብ ይኖርብናል። በዚህ መንገድ በሰማይ ከሚኖረው አባታችን ከይሖዋ አምላክም ሆነ ከእምነት ባልንጀሮቻችን ጋር ያለንን ግንኙነት ማሻሻል እንችላለን።—መዝሙር 22:22፤ ማርቆስ 4:24

6. ኢየሱስ፣ ሰውየው የጠየቀውን ነገር ያላደረገለት ለምን ነበር?

6 ሰውየው እንዲህ ያለ ጥያቄ እንዲያቀርብ የገፋፋው ምንም ይሁን ምን ኢየሱስ ፍላጎቱን አላሟላለትም። ከዚህ ይልቅ “አንተ ሰው፤ በእናንተ ላይ ፈራጅ ወይም ዳኛ ያደረገኝ ማነው?” በማለት መለሰለት። (ሉቃስ 12:14) ኢየሱስ ይህንን ሲል ሕዝቡ በደንብ ስለሚያውቀው ነገር እየተናገረ ነበር፤ በሙሴ ሕግ መሠረት በከተሞቹ ውስጥ እንደነዚህ ባሉ ጉዳዮች ላይ የሚፈርዱ ዳኞች ይሾሙ ነበር። (ዘዳግም 16:18-20፤ 21:15-17፤ ሩት 4:1, 2) በሌላ በኩል ግን ኢየሱስ ትኩረት ያደረገው ይበልጥ አስፈላጊ በሆኑ ጉዳዮች ይኸውም ስለ አምላክ መንግሥት እውነት በመመሥከርና ለሰዎች ስለ ይሖዋ ፈቃድ በማስተማር ላይ ነበር። (ዮሐንስ 18:37) እኛም ተራ የሆኑ ጉዳዮች ትኩረታችንን እንዲሰርቁት ከመፍቀድ ይልቅ የኢየሱስን ፈለግ በመከተል ጊዜያችንንና ጉልበታችንን ምሥራቹን ለመስበክና ‘ሕዝቦችን ደቀ መዛሙርት ለማድረግ’ እንጠቀምበታለን።—ማቴዎስ 24:14፤ 28:19

ከስግብግብነት ራሳችሁን ጠብቁ

7. ኢየሱስ ምን ማስተዋል የተሞላበት ሐሳብ ሰጥቷል?

7 ኢየሱስ የልብን ሐሳብ የማወቅ ችሎታ ስላለው ግለሰቡ እንዲህ ያለ ጥያቄ ማቅረቡ ከበድ ያለ ችግር እንዳለበት የሚጠቁም መሆኑን ኢየሱስ ተገንዝቦ ነበር። በመሆኑም ኢየሱስ፣ ሰውየው የፈለገውን ነገር ለማድረግ ፈቃደኛ አለመሆኑን በመግለጽ ብቻ ሳይወሰን ሰውየው እንዲህ ዓይነት ጥያቄ እንዲያቀርብ ያነሳሳውን ምክንያት እንዲህ በማለት ገልጿል:- “የሰው ሕይወቱ በሀብቱ ብዛት የተመሠረተ ስላልሆነ፣ ተጠንቀቁ፤ ከስግብግብነትም ሁሉ ራሳችሁንም ጠብቁ።”—ሉቃስ 12:15

8. ስግብግብነት ምንድን ነው? እንዲህ ያለው ባሕርይስ ወደ ምን ሊመራ ይችላል?

8 አንድ መዝገበ ቃላት ስግብግብነት የሚለውን ቃል “ሀብት ወይም ንብረት አሊያም የሌላን ሰው ንብረት ለማግኘት ከመጠን በላይ መመኘት” በማለት ፈቶታል። ስግብግብነት የማይረካ ፍላጎትን፣ ስስታምነትንና ምናልባትም የሌሎችን ንብረት መመኘትን የሚያካትት ሲሆን እንዲህ ዓይነት ባሕርይ ያለው ሰው የሚመኘው ነገር አስፈልጎት ላይሆን ይችላል፤ እንዲህ ማድረጉ በሌሎች ላይ ስለሚያሳድረው ተጽዕኖም አያስብም። ስግብግብ የሆነ ሰው አንድ ነገር ለማግኘት ያለው ፍላጎት አስተሳሰቡንና ድርጊቱን ሙሉ በሙሉ እንዲቆጣጠረው ስለሚፈቅድ ይህ ነገር አምላኩ ይሆናል። ሐዋርያው ጳውሎስ ስስታም የሆነ ሰው ከጣዖት አምላኪ ጋር እኩል መሆኑን እንደገለጸ ልብ በል፤ እንዲህ ያለው ሰው ደግሞ የአምላክን መንግሥት አይወርስም።—ኤፌሶን 5:5፤ ቈላስይስ 3:5

9. ስግብግብነት በምን መንገዶች ሊገለጽ ይችላል? አንዳንድ ምሳሌዎች ስጥ።

9 ኢየሱስ “ከስግብግብነትም ሁሉ” እንድንርቅ ማስጠንቀቁ ትኩረት የሚስብ ነው። ስግብግብነት ብዙ ገጽታዎች አሉት። ከአሥርቱ ትእዛዛት መካከል በመጨረሻ ላይ የሰፈረው ሕግ፣ ስግብስብነት የሚገለጽባቸውን አንዳንድ መንገዶች እንደሚከተለው በማለት ይዘረዝራቸዋል:- “የባልንጀራህን ቤት አትመኝ፤ የባልንጀራህን ሚስት ወይም የእርሱን ወንድ አገልጋይ ሆነ ሴት አገልጋይ፣ በሬውንም ሆነ አህያውን ወይም የእርሱ የሆነውን ማናቸውንም ነገር አትመኝ።” (ዘፀአት 20:17) መጽሐፍ ቅዱስ፣ አንዳንዶች ስግብግብ በመሆናቸው ከባድ ኃጢአት እንደሠሩ የሚገልጹ በርካታ ምሳሌዎች ይዟል፤ እነዚህ ፍጥረታት ስግብግብነታቸው የተገለጸው በተለያዩ መንገዶች ነበር። የእሱ ያልሆነውን ነገር በስግብግብነት የተመኘው የመጀመሪያው አካል ሰይጣን ሲሆን እሱም ለይሖዋ ብቻ የሚገባውን ክብር፣ ሞገስና ሥልጣን ለማግኘት ፈለገ። (ራእይ 4:11) ሔዋን ደግሞ ራሷን የመምራት መብት ለማግኘት የተመኘች ሲሆን ይህንን እንደምታገኝ በማሰብ መታለሏም የሰውን ዘር ለኃጢአትና ለሞት ዳርጎታል። (ዘፍጥረት 3:4-7) ከጊዜ በኋላ አጋንንት የሆኑት አንዳንድ መላእክት፣ ‘በሥልጣን ስፍራቸው’ ባለመርካታቸው ለእነሱ የማይገባውን ነገር ለማግኘት ሲሉ ‘መኖሪያቸውን ትተዋል።’ (ይሁዳ 6፤ ዘፍጥረት 6:2) ከዚህም በተጨማሪ በለዓምን፣ አካንን፣ ግያዝንና አስቆሮቱ ይሁዳን አስቡ። እነዚህ ሰዎች ባሏቸው ነገሮች ረክተው ከመኖር ይልቅ ቁሳዊ ነገሮች ለማግኘት ከመጠን በላይ መመኘታቸው ኃላፊነታቸውን አላግባብ እንዲጠቀሙበት ያደረጋቸው ሲሆን ይህም ጥፋት አስከትሎባቸዋል።

10. ኢየሱስ “ተጠንቀቁ” በማለት የሰጠውን ምክር ተግባራዊ ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው?

10 ኢየሱስ ስግብግብነትን አስመልክቶ በሰጠው ምክር ላይ “ተጠንቀቁ” ማለቱ እንዴት የተገባ ነው! እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው? ሰዎች፣ ራሳቸው ስግብግብ እንደሆኑ ማመን ስለሚከብዳቸው ነው። ሐዋርያው ጳውሎስ “የገንዘብ ፍቅር የክፋት ሁሉ ሥር ነው” በማለት ተናግሯል። (1 ጢሞቴዎስ 6:9, 10) ደቀ መዝሙሩ ያዕቆብም በውስጣችን መጥፎ ምኞት ‘ከተፀነሰ በኋላ ኀጢአት እንደሚወለድ’ ገልጿል። (ያዕቆብ 1:15) ከኢየሱስ ምክር ጋር በሚስማማ መልኩ ‘ከስግብግብነት ሁሉ ራሳችንን መጠበቅ’ እንድንችል ልባችን በምን ላይ እንዳተኮረ በመመርመር ‘መጠንቀቅ’ ይኖርብናል።

የሀብት ብዛት

11, 12. (ሀ) ኢየሱስ ከስግብግብነት ስለ መራቅ ምን ማስጠንቀቂያ ሰጥቷል? (ለ) የኢየሱስን ማስጠንቀቂያ መስማት የሚኖርብን ለምንድን ነው?

11 ራሳችንን ከስግብግብነት እንድንጠብቅ የሚያነሳሳን ሌላም ምክንያት አለን። ኢየሱስ “የሰው ሕይወቱ በሀብቱ ብዛት የተመሠረተ” አለመሆኑን እንደተናገረ ልብ እንበል። (ሉቃስ 12:15) ሰዎች፣ ደስታና ስኬት ከሀብትና ከብልጽግና ጋር የተቆራኙ እንደሆኑ በሚያስቡበት ብሎም ፍቅረ ንዋይ በተስፋፋበት በዚህ ዘመን፣ ኢየሱስ ከላይ የተናገረው ሐሳብ በቁም ነገር ሊታሰብበት ይገባል። ኢየሱስ እንዲህ ብሎ ሲናገር፣ አንድ ሰው የቱንም ያህል የተትረፈረፈ ቁሳዊ ሀብት ቢኖረው ትርጉም ያለውና የሚያረካ ሕይወት ማግኘቱ የተመካው በእነዚህ ነገሮች ላይ እንዳልሆነ መግለጹ ነበር።

12 ይሁን እንጂ አንዳንዶች በዚህ ሐሳብ አይስማሙ ይሆናል። ቁሳዊ ንብረቶች የተደላደለና አስደሳች ሕይወት ለመምራት ስለሚያስችሉ ሕይወት ይበልጥ ትርጉም ያለው እንደሚሆን ይናገሩ ይሆናል። በመሆኑም የሚፈልጓቸውን ቁሳዊ ነገሮች እንዲሁም የኤሌክትሮኒክ ዕቃዎችና ሌሎች ንብረቶች ሁሉ ለመግዛት በሚያስችሏቸው ሥራዎች ይጠመዳሉ። እነዚህ ነገሮች ሕይወታቸው የተደላደለና ስኬታማ እንዲሆን የሚያደርጉ ይመስላቸዋል። ሆኖም እንዲህ የሚያስቡ ሰዎች ኢየሱስ የተናገረው ቁም ነገር አልገባቸውም።

13. ስለ ሕይወትና ቁሳዊ ንብረቶች ሊኖረን የሚገባው ሚዛናዊ አመለካከት ምንድን ነው?

13 ኢየሱስ፣ ብዙ ሀብት ማካበት ትክክል ነው ወይስ አይደለም በሚለው ሐሳብ ላይ ከማተኮር ይልቅ የሰው ሕይወት “በሀብቱ ብዛት” ማለትም ባሉት ነገሮች ላይ የተመሠረተ እንዳልሆነ ማጉላቱ ነበር። ለመኖር ወይም በሕይወት ለመቀጠል ብዙ ነገር እንደማያስፈልገን ሁላችንም እናውቃለን። ለመኖር የሚያስፈልገን ጥቂት ምግብ፣ ልብስና መጠለያ ብቻ ነው። ሀብታሞች እነዚህ ነገሮች በብዛት ያሏቸው ሲሆን ድሆች ግን የሚያስፈልጓቸውን ነገሮች ለማግኘት ይለፋሉ። እንዲህ ዓይነት የኑሮ ልዩነት ቢኖርም ሲሞቱ ሁሉም እኩል ይሆናሉ። (መክብብ 9:5, 6) በመሆኑም ሕይወት ትርጉም ያለው መሆኑ አንድ ሰው በሚያገኘው ንብረት ላይ ብቻ የተመካ አይደለም፤ ሊሆንም አይገባም። ኢየሱስ ስለ ምን ዓይነት ሕይወት እየተናገረ እንዳለ ስንመረምር ይህ ሐሳብ ግልጽ ይሆንልናል።

14. ከላይ በተጠቀሰው የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ ላይ ከሚገኘው ‘ሕይወት’ ከሚለው ቃል ምን ትምህርት ማግኘት እንችላለን?

14 ኢየሱስ “የሰው ሕይወቱ በሀብቱ ብዛት የተመሠረተ” እንዳልሆነ ሲናገር በሉቃስ ወንጌል ላይ ‘ሕይወት’ ለሚለው ቃል የገባው የሚለው የግሪክኛ ቃል የአንድን ሰው አኗኗር ሳይሆን ሕይወትን ራሱን የሚያመለክት ነው። a ኢየሱስ ይህን ሲናገር፣ ሀብታም ወይም ድሃ ብንሆን አሊያም ኑሯችን የተንደላቀቀ ወይም ከእጅ ወደ አፍ ቢሆንም፣ ምን ያህል ዕድሜ እንደምንኖር መወሰን አሊያም ነገ እንኳ በሕይወት መኖራችንን ማወቅ እንደማንችል መግለጹ ነበር። ኢየሱስ በተራራው ስብከቱ ላይ “ለመሆኑ ከእናንተ መካከል ተጨንቆ በዕድሜው ላይ አንዲት ሰዓት መጨመር የሚችል አለን?” ብሎ ነበር። (ማቴዎስ 6:27) መጽሐፍ ቅዱስ፣ “የሕይወት ምንጭ” ይሖዋ ብቻ እንደሆነና ለታማኞቹም በሰማይም ሆነ በምድር “እውነተኛ የሆነውን ሕይወት” ወይም “የዘላለም ሕይወት” ሊሰጥ የሚችለው እሱ ብቻ መሆኑን በግልጽ ያሳያል።—መዝሙር 36:9፤ 1 ጢሞቴዎስ 6:12, 19

15. ብዙዎች በቁሳዊ ነገሮች ላይ የሚታመኑት ለምንድን ነው?

15 ኢየሱስ የተናገረው ሐሳብ ሰዎች ስለ ሕይወት ያላቸው አመለካከት በቀላሉ ሊዛባ እንደሚችል ይጠቁማል። ሀብታምም ይሁኑ ድሃ ሁሉም ሰዎች ፍጹም ባለመሆናቸው ዞሮ ዞሮ መጨረሻቸው አንድ ነው። በጥንት ዘመን የኖረው ሙሴ እንዲህ በማለት ተናግሯል:- “የዕድሜአችን ዘመን ሰባ ዓመት፣ ቢበዛም ሰማንያ ነው፤ ከዚያ በላይ ከሆነም ድካምና መከራ ብቻ ነው፤ ቶሎ ያልፋልና፤ እኛም ወዲያው እንነጕዳለን።” (መዝሙር 90:10፤ ኢዮብ 14:1, 2፤ 1 ጴጥሮስ 1:24) በዚህም የተነሳ ከአምላክ ጋር ጥሩ ዝምድና ያልመሠረቱ ሰዎች ብዙውን ጊዜ፣ ሐዋርያው ጳውሎስ “ነገ ስለምንሞት፣ እንብላ፣ እንጠጣ” በማለት የተናገረው ዓይነት አመለካከት ያንጸባርቃሉ። (1 ቆሮንቶስ 15:32) ሌሎች ደግሞ ሕይወት አስተማማኝ እንዳልሆነና ቶሎ እንደሚያልፍ ስለሚሰማቸው ቁሳዊ ንብረት በማካበት ሕይወታቸው ዋስትና እንዲኖረውና የተረጋጋ እንዲሆን ለማድረግ ይጥራሉ። ምናልባትም ብዙ ቁሳዊ ነገሮች ማካበት ሕይወታቸውን ይበልጥ አስተማማኝ ሊያደርገው እንደሚችል ይሰማቸው ይሆናል። ሀብትና ንብረት፣ አስተማማኝ ሕይወትና ደስታ ያስገኛሉ የሚል የተሳሳተ አስተሳሰብ ስላላቸው እነዚህን ነገሮች ለመሰብሰብ አለረፍት ይባክናሉ።—መዝሙር 49:6, 11, 12

አስተማማኝ ተስፋ

16. የአንድ ሰው ሕይወት ትርጉም ያለው መሆን አለመሆኑ የሚመዘነው በየትኞቹ ነገሮች አይደለም?

16 አንድ ሰው ጥሩ ኑሮ ካለው ማለትም ምግብ፣ ልብስ፣ መጠለያና ሌሎች የቅንጦት ዕቃዎችን እንደ ልብ ማግኘት የሚችል ከሆነ ሕይወቱ ይበልጥ የተደላደለ ሊሆን ወይም የተሻለ ሕክምና ሊያገኝ ይችላል፤ ይህ ደግሞ ዕድሜውን በተወሰኑ ዓመታት ሊያራዝምለት እንደሚችል አይካድም። ይሁን እንጂ እንዲህ ያለው ሕይወት ይበልጥ ትርጉም ያለውና አስተማማኝ ነው? ሕይወት ትርጉም ያለው መሆኑ የሚመዘነው፣ በአንድ ሰው ዕድሜ ርዝመትም ሆነ ባሉት ቁሳዊ ነገሮች ወይም በገንዘቡ ሊያገኝ በሚችላቸው ነገሮች አይደለም። ሐዋርያው ጳውሎስ በእነዚህ ነገሮች ከመጠን በላይ መታመን ጉዳት እንዳለው ተናግሯል። ጳውሎስ ለጢሞቴዎስ እንዲህ በማለት ጽፎለታል:- “በዚህ ዓለም ባለጠጎች የሆኑት እንዳይታበዩ፣ ደስም እንዲለን ሁሉን ነገር አትረፍርፎ በሚሰጠን በእግዚአብሔር እንጂ አስተማማኝነት በሌለው በሀብት ላይ ተስፋ እንዳያደርጉ እዘዛቸው።”—1 ጢሞቴዎስ 6:17

17, 18. (ሀ) ከቁሳዊ ንብረቶች ጋር በተያያዘ ልንኮርጃቸው የሚገቡን ግሩም የሆኑ ምሳሌዎች የትኞቹ ናቸው? (ለ) በሚቀጥለው ርዕስ ላይ ኢየሱስ የተናገረውን የትኛውን ምሳሌ እንመለከታለን?

17 ሀብት ‘አስተማማኝነት ስለሌለው’ በሀብት ላይ ተስፋ ማድረጉ ጥበብ የጎደለው እርምጃ ነው። የእምነት አባት የሆነው ኢዮብ እጅግ ባለጠጋ የነበረ ቢሆንም ድንገተኛ አደጋ በደረሰ ጊዜ ሀብቱ ምንም ሊፈይድለት አልቻለም፤ ያለውን በአንድ ጀንበር አጣ። ኢዮብ ያጋጠመውን መከራና ችግር በሙሉ እንዲቋቋም የረዳው ከአምላክ ጋር የነበረው ጠንካራ ዝምድና ነበር። (ኢዮብ 1:1, 3, 20-22) አብርሃም የነበረው ቁሳዊ ሀብት ይሖዋ የሰጠውን አስቸጋሪ ተልእኮ እንዳይቀበል እንቅፋት እንዲሆንበት አልፈቀደም፤ እንዲህ በማድረጉም “የብዙ ሕዝቦች አባት” በመሆን ተባርኳል። (ዘፍጥረት 12:1, 4፤ 17:4-6) እነዚህና ሌሎች ምሳሌዎች ልንኮርጃቸው የሚገቡ ናቸው። ወጣትም ሆንን አረጋዊ በሕይወታችን ውስጥ ይበልጥ አስፈላጊ የሆነውና ተስፋ የምናደርግበት ነገር ምን እንደሆነ መመርመር ይኖርብናል።—ኤፌሶን 5:10፤ ፊልጵስዩስ 1:10

18 በእርግጥም፣ ኢየሱስ ስግብግብነትንና ስለ ሕይወት ተገቢ አመለካከት መያዝን አስመልክቶ የተናገረው ሐሳብ አስፈላጊና ትምህርት ሰጪ ነው። ኢየሱስ ከዚህም በተጨማሪ ሞኝ ስለነበረ አንድ ሀብታም ሰው የሚገልጽ ትኩረት የሚስብ ምሳሌ ተናግሯል። በዛሬው ጊዜ ይህ ምሳሌ በእኛ ሕይወት ውስጥ ተግባራዊ ሊሆን የሚችለው እንዴት ነው? እኛስ ከዚህ ምሳሌ ምን ልንማር እንችላለን? የሚቀጥለው ርዕስ ለእነዚህ ጥያቄዎች መልስ ይሰጠናል።

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

a “ሕይወት” ተብሎ የሚተረጎመው ሌላው የግሪክኛ ቃል ባዮስ ነው። በቫይን የተዘጋጀው ኤክስፖዚተሪ ዲክሽነሪ ኦቭ ኦልድ ኤንድ ኒው ቴስታመንት ዎርድስ እንደሚገልጸው ባዮስ የሚለው ቃል “የሕይወት ዘመንን፣” “አኗኗርን” እንዲሁም “መተዳደሪያን” ያመለክታል።

መልስህ ምንድን ነው?

• ኢየሱስ፣ ያዳምጡት ከነበሩት ሰዎች አንዱ ያቀረበለትን ጥያቄ ለማሟላት ፈቃደኛ አለመሆኑ ምን ትምህርት ይሰጠናል?

• ከስግብግብነት ራሳችንን መጠበቅ ያለብን ለምንድን ነው? ይህን ማድረግ የምንችለውስ እንዴት ነው?

• ሕይወት የተመካው በቁሳዊ ንብረቶች ላይ አይደለም የምንለው ለምንድን ነው?

• ሕይወት ትርጉም ያለውና አስተማማኝ እንዲሆን የሚያደርገው ምንድን ነው?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ኢየሱስ የሰውየውን ፍላጎት ያላሟላለት ለምን ነበር?

[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ስግብግብነት ለጥፋት ሊዳርግ ይችላል

[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

አብርሃም ለቁሳዊ ነገሮች ተገቢ አመለካከት እንዳለው ያሳየው እንዴት ነበር?