የአንባቢያን ጥያቄዎች
የአንባቢያን ጥያቄዎች
ንጉሥ ሳኦል፣ ዳዊት የእሱ አገልጋይ እንዲሆን ቀደም ሲል ልኮ ያስጠራው ቢሆንም ዳዊት ጎልያድን ከገደለ በኋላ “አንተ ወጣት፣ የማን ልጅ ነህ?” ብሎ የጠየቀው ለምን ነበር?—1 ሳሙኤል 16:22፤ 17:58
ቀላል የሆነው መልስ፣ ሳኦል ዳዊትን መጀመሪያ ባገኘው ጊዜ ቆይታቸው አጭር ስለነበር ረስቶት ይሆናል የሚል ነው። ሆኖም ይህ ሊሆን አይችልም፤ ምክንያቱን በ1 ሳሙኤል 16:18-23 ላይ የሚገኘው ዘገባ እንደሚያሳየው ንጉሥ ሳኦል ወደ ዳዊት ሰዎችን ልኮ ካስመጣው በኋላ በጣም ስለወደደው ጋሻ ጃግሬው አድርጎታል። በመሆኑም ሳኦል ዳዊትን በደንብ አውቆት መሆን አለበት።
አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሑራን፣ በ1 ሳሙኤል 17:12-31 እና ከ17:55 እስከ 18:5 ላይ ያሉት ዘገባዎች፣ በሁለተኛው መቶ ዘመን ከክርስቶስ ልደት በፊት በተጠናቀቀው ሰብዓ ሊቃናት በተባለው የዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት ግሪክኛ ትርጉም የተወሰኑ ቅጂዎች ላይ ስለማይገኙ እነዚህ ጥቅሶች በኋላ ላይ የተጨመሩ እንደሆኑ ይናገራሉ። ይሁን እንጂ እነዚህ ጥቅሶች ተዓማኒነት ባላቸው ሌሎች የዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት ጥንታዊ ቅጂዎች ላይ ስለሚገኙ በእነዚህ የሰብዓ ሊቃናት የተወሰኑ ቅጂዎች ላይ ብቻ ተመሥርቶ እዚህ መደምደሚያ ላይ መድረሱ ጥበብ አይደለም።
ሳኦል፣ በመጀመሪያ አበኔርን ከዚያም ራሱን ዳዊትን ስለጠየቀ ለማወቅ የፈለገው የዳዊትን አባት ስም ብቻ እንዳልነበረ ከሁኔታዎቹ ለመረዳት ይቻላል። ዳዊት፣ ጎልያድን ያሸነፈ ታላቅ እምነትና ድፍረት ያለው ሰው መሆኑን ሲመለከት ሳኦል እንዲህ ዓይነቱን ወጣት ማን እንዳሳደገው ለማወቅ ፈለገ። ሳኦል፣ የዳዊት አባት የሆነው እሴይ ወይም ሌሎች የቤተሰቡ አባላት እንደ ዳዊት ዓይነት ድፍረትና ጀግንነት እንደሚኖራቸው በማሰብ ከጦር ሠራዊቱ ጋር እንዲቀላቀሉ ፈልጎ ሊሆን ይችላል።
አንደኛ ሳሙኤል 17:58 ዳዊት፣ “እኔ የአገልጋይህ የቤተ ልሔሙ ሰው የእሴይ ልጅ ነኝ” በማለት የሰጠውን አጭር መልስ ብቻ የያዘ ቢሆንም ከዚያ በኋላ ያለው ሐሳብ ረዘም ያለ ውይይት አድርገው ሊሆን እንደሚችል ይጠቁማል። ይህን በማስመልከት ካርል ካይል እና ፍራንዝ ዴሊትሽ የተባሉ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሑራን የሰጡትን የሚከተለውን ሐሳብ ልብ በል:- “[1 ሳሙኤል 18:1] ‘ከሳኦል ጋር የሚያደርገውን ንግግር እንዳበቃ’ ማለቱ ሳኦል ከዳዊት ጋር ስለ ቤተሰቡ ረዘም ያለ ውይይት እንዳደረገ ያሳያል።”
ከዚህ አንጻር፣ ሳኦል “አንተ ወጣት፣ የማን ልጅ ነህ?” ብሎ የጠየቀው የዳዊትን ማንነት ሳይሆን ስለ አስተዳደጉ ለማወቅ ፈልጎ ነው ብለን መደምደም እንችላለን።
[በገጽ 31 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ሳኦል ዳዊትን የማን ልጅ እንደሆነ የጠየቀው ለምን ነበር?