በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የአንዲት እናት እምነት ያጋጠማትን አሳዛኝ ሁኔታ ለመቋቋም ረድቷታል

የአንዲት እናት እምነት ያጋጠማትን አሳዛኝ ሁኔታ ለመቋቋም ረድቷታል

የአንዲት እናት እምነት ያጋጠማትን አሳዛኝ ሁኔታ ለመቋቋም ረድቷታል

“ይህን ደብዳቤ እያነበባችሁ ከሆነ የተደረገልኝ ቀዶ ሕክምና አልተሳካም ማለት ነው፤ በሞት ስላንቀላፋሁ ከአሁን በኋላ አብሬያችሁ አልኖርም።”

ከላይ ያለው ሐሳብ፣ ካርመን የተባለች አንዲት የይሖዋ ምሥክር እናት 25, 19 እና 16 ዓመት ለሆናቸው ሴቶች ልጆቿ የጻፈችው ደብዳቤ የመክፈቻ ቃላት ነበሩ። የሚያሳዝነው፣ ቀዶ ሕክምናው ባለመሳካቱ ካርመን በሞት አንቀላፋች።

ሦስት ልጆቿን ይህን በመሰለ አሳዛኝ ሁኔታ ትታ መሄዷ አንጀት የሚበላ ነው። ሆኖም ይህች እናት በይሖዋና እርሱ በሰጠው ተስፋ ላይ የነበራት ጠንካራ እምነት ይህን አሳዛኝ ሁኔታ እንድትቋቋም የረዳት ሲሆን ውስጣዊ ሰላምም እንደሰጣት ልብ ከሚነካው ደብዳቤዋ በግልጽ ማየት ይቻላል። ለልጆቿ የጻፈችላቸው ደብዳቤ እንዲህ ይላል:-

“በመጀመሪያ ከልብ እንደምወዳችሁ ልነግራችሁ እፈልጋለሁ። . . . አንዲት እናት እንዲኖሯት የምትመኛቸው ዓይነት ጥሩ ልጆች ናችሁ፤ በጣም እኮራባችኋለሁ።

“አምላክ ተስፋ የሰጠው አዲስ ዓለም እስኪመጣ ድረስ ከእናንተ ጋር ለመኖር እፈልግ ነበር፤ . . . ይሁንና ሁኔታዎች እንደዚያ አልሆኑም፤ አሁን ያላችሁን ታማኝነት ይዛችሁ መቀጠል እንድትችሉ አምላክ እንዲረዳችሁ በጸሎት ጠይቄዋለሁ። . . . ብዙ ፈተናዎችን ጸንተን አልፈናል፤ ይሖዋም ፈጽሞ አልተወንም። . . . ስለዚህ በድርጅቱ በኩል በሚሰጠው መመሪያ መታመናችሁንም ሆነ ከጉባኤው እንዲሁም ከሽማግሌዎች ጋር መተባበራችሁን ቀጥሉ። አቅማችሁ የሚፈቅደውን ያህል ዘወትር በስብከቱ ሥራ ተካፈሉ፤ እንዲሁም ሁሉንም ወንድሞች ውደዱ።

የምንለያየው ለጊዜው ነው። . . . ለሠራኋቸው ስህተቶች፣ ሳልረዳችሁ ለቀረሁባቸው ጊዜያት ወይም ምን ያህል እንደምወዳችሁ ላልተናገርኩባቸው ወቅቶች ሁሉ ይቅር እንድትሉኝ እለምናችኋለሁ። . . . እያንዳንዳችሁ የራሳችሁ ፍላጎት እንዳላችሁ አውቃለሁ። ይሖዋም ይህን ከእናንተ በላይ ስለሚያውቅ የሚያስፈልጋችሁን ሁሉ ያሟላላችኋል፤ እንዲሁም ላሳያችሁት ጽናት ሁሉ ይክሳችኋል።

በአዲሱ ዓለም ውስጥ ለመኖር ያላችሁን ግብ ፈጽሞ አትርሱት፤ እዚህ ግብ ላይ ለመድረስ የምታደርጉትን ጥረት ቀጥሉበት። እስከ መጨረሻው ድረስ ታማኝ እንድትሆኑ ይሖዋ ያበርታችሁ፤ አብዝቶም ይባርካችሁ። . . . ውድ ልጆቼ አትዘኑ። እወዳችኋለሁ!”

አሳዛኝ ክስተት ማንኛውንም ሰው በየትኛውም ጊዜ ሊያጋጥመው ይችላል። በጥንት ዘመን የኖረው ንጉሥ ሰሎሞን “ጊዜና ዕድል [“አጋጣሚ፣ NW] ግን ሁሉን ይገናኛቸዋል” በማለት ጽፏል። (መክብብ 9:11) ይሁን እንጂ በአምላክ ላይ ጠንካራ እምነት ያላቸው ሰዎች ሐዋርያው ጳውሎስ እንደሚከተለው በማለት የተናገረው ዓይነት ተስፋ ሊኖራቸው ይችላል:- “ሞትም ይሁን ሕይወት፣ . . . የትኛውም ፍጥረት፣ በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ካለው ከእግዚአብሔር ፍቅር ሊለየን አይችልም።”—ሮሜ 8:38, 39፤ ዕብራውያን 6:10