ይሖዋን ማገልገል —ከምንም ነገር ጋር ሊወዳደር የማይችል ክብርና መብት
የሕይወት ታሪክ
ይሖዋን ማገልገል —ከምንም ነገር ጋር ሊወዳደር የማይችል ክብርና መብት
ዚራ ስታይገርስ እንደተናገረችው
በሙሉ ጊዜ አገልግሎት በታማኝነት አብሮኝ ያገለግል የነበረው ባለቤቴ በ1938 በሞት አንቀላፋ። በዚህም የተነሳ ባለቤቴ ከሞተ ብዙም ሳይቆይ የተወለደውን ሕፃንና አሥር ዓመት የሆነው ልጃችንን የመንከባከቡ ኃላፊነት በእኔ ላይ ወደቀ። እንደዚያም ሆኖ በሙሉ ጊዜ አገልግሎት የመካፈል ከፍተኛ ጉጉት ነበረኝ፤ ሆኖም ይህን ማድረግ የምችለው እንዴት ይሆን? በሙሉ ጊዜ አገልግሎት መካፈል እንዴት እንደቻልኩ ከመተረኬ በፊት ስለ ቀድሞ ሕይወቴ ጥቂት ልንገራችሁ።
ሐምሌ 27, 1907 በአላባማ፣ ዩናይትድ ስቴትስ ተወለድኩ፤ ብዙም ሳይቆይ ወላጆቼ እኔንና ሦስት ታናናሾቼን ይዘው ወደ ጆርጂያ ሄዱ። ከጥቂት ጊዜ በኋላ ወደ ቴነሲ የተዛወርን ሲሆን ቆየት ብሎ ደግሞ በታምፓ፣ ፍሎሪዳ አቅራቢያ መኖር ጀመርን። በ1916 እዚያው እያለን “የፍጥረት ፎቶ ድራማ” የተባለውን በድምፅ የታጀበ ተንቀሳቃሽ ምስል ተመለከትሁ። የፊልም ኢንዱስትሪ ገና መጀመሩ ስለነበር “ፎቶ ድራማውን” ሁሉም ሰው ወደደው!
ወላጆቼ መጠበቂያ ግንብንና ሌሎች መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችን በጉጉት ያነቡ ነበር። አባቴ እነዚህን ጽሑፎች ማንበብ ቢወድም በወቅቱ ከመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች (በዚያን ጊዜ የይሖዋ ምሥክሮች የሚጠሩበት ስም ነው) ጋር አይሰበሰብም ነበር። እናቴ ግን እኔን፣ ወንድሞቼንና እህቴን ወደ ስብሰባዎች ትወስደን ነበር። እንዲያውም ወደ ናይልዝ፣ ሚሺገን ከተዛወርን ብዙም ሳንቆይ በስብሰባዎች ላይ አዘውትረን ለመገኘት ስንል ወደ ሳውዝ ቤንድ፣ ኢንዲያና በባቡር ከ16 ኪሎ ሜትር በላይ እንጓዝ ነበር።
ሐምሌ 22, 1924 ራሴን ለይሖዋ መወሰኔን ለማሳየት ተጠመቅሁ። ከዚያ ብዙም ሳይቆይ እናቴ ሁኔታዎቿን አስተካከለችና ኮልፖርተር (በወቅቱ የሙሉ ጊዜ አገልጋዮች የሆኑ የይሖዋ ምሥክሮች የሚጠሩበት ስም ነው) ሆና ማገልገል ጀመረች። የእሷና የሌሎች ኮልፖርተሮች ግሩም ምሳሌነት እኔም በዚህ ሥራ የመካፈል ፍላጎት እንዲያድርብኝ አደረገ።
አጋር አገኘሁ
በ1925 በኢንዲያናፖሊስ፣ ኢንዲያና በተደረገ ትልቅ የአውራጃ ስብሰባ ላይ ከቺካጎ ከመጣው ከጄምስ ስታይገርስ ጋር ተዋወቅን። ጄምስ ቀናተኛ የይሖዋ አገልጋይ መሆኑ ወዲያውኑ ቀልቤን ሳበው። እኔ የምኖረው ከቺካጎ 160 ኪሎ ሜትር ገደማ ርቄ ስለነበር ከጄምስ ጋር መገናኘት ቀላል አልነበረም። በዚያን ጊዜ በዚህ ትልቅ ከተማ ውስጥ አንድ ጉባኤ ብቻ የነበረ ሲሆን ስብሰባዎች የሚካሄዱት ፎቅ ላይ በሚገኝ የኪራይ ቤት ውስጥ ነበር። ጄምስ እኔን በመንፈሳዊ ለማበረታታት ብዙ ጊዜ ደብዳቤ ይጽፍልኝ ነበር። በታኅሣሥ 1926 የተጋባን ሲሆን ከአንድ ዓመት ገደማ በኋላም የመጀመሪያ ልጃችን ኤዲ ተወለደ።
ከጥቂት ጊዜ በኋላ እኔና ጄምስ አቅኚ ሆነን አብረን ማገልገል ጀመርን። በሚሺገን፣ በሉዊዚያና፣ በሚሲሲፒ፣ በሳውዝ ደኮታ፣ በአይዋ፣ በነብራስካ፣ በካሊፎርኒያና በኢሊኖይስ በአጠቃላይ በስምንት ግዛቶች ያገለግልን ሲሆን እነዚያ ዓመታት በሕይወታችን ውስጥ በጣም የተደሰትንባቸው ጊዜያት ነበሩ። ጄምስ ሲታመም ግን ሁኔታዎች ተለዋወጡ።
በጄምስ መታመም የተነሳ የገንዘብ ችግር ስላጋጠመን በ1936 ወደ ቺካጎ ተመልሰን የይሖዋ ምሥክር ከሆነችው አማቴ ጋር መኖር ጀመርን። ጄምስ ሕመሙ እየባሰበት ሲሄድ በአንድ ካፊቴሪያ ውስጥ በቀን 1 የአሜሪካ ዶላር እየተከፈለኝ እሠራ ነበር፤ በዚህ ወቅት ሁለተኛውን ልጃንን እርጉዝ ነበርኩ። ተወዳጅ የሆነችው አማቴ ከሚያስፈልገን በላይ ምግብ ትሰጠን የነበረ ሲሆን በምላሹም ምንም ገንዘብ አትቀበለንም። ልታደርገው የምትችለውን ሁሉ አድርጋልናለች።
ጄምስ ኤንሰፍላይተስ በተባለ በአእምሮ ላይ ጉዳት በሚያደርስ ሕመም ለሁለት ዓመታት ከተሰቃየ በኋላ ሐምሌ 1938 ሞተ። ታምሞ በነበረበት ወቅት መኪና መንዳት ወይም ከቤት ወደ ቤት በሚደረገው አገልግሎት መካፈል ባይችልም ባገኘው አጋጣሚ ሁሉ ይመሠክር ነበር። ቤተሰባችንን በኢኮኖሚ ለመደገፍ ስል የሙሉ ጊዜ አገልግሎት አቋርጬ ለአጭር ጊዜ የሚቆዩ የተለያዩ ሥራዎችን እሠራ ጀመር።
ባለቤቴ ከሞተ ከስምንት ቀናት በኋላ ሐምሌ 30, 1938 ልጃችን ባቢ ተወለደ። በዚህ ጊዜ አማቴ፣ ነፃ ሕክምና ወደሚሰጥበት ጤና ጣቢያ እንድሄድ አልፈለገችም። ከዚህ ይልቅ የተሻለ ሆስፒታል ገብቼ የራሷ ዶክተር እንዲረዳኝ አደረገች። ከዚህም በላይ ወጪዎቼን በሙሉ ሸፈነችልኝ፤ ያሳየችኝን ክርስቲያናዊ ፍቅር ከልብ አደንቃለሁ።
ወደ ሙሉ ጊዜ አገልግሎት መመለስ
ባቢ 2 ዓመት እስኪያልፈው ድረስ ከአማቴ ጋር መኖር ቀጠልን፤ በዚህ ጊዜ ኤዲ የ12 ዓመት ልጅ ነበር። ሁኔታዎቼን ማስተካከል የሚጠይቅብኝ ቢሆንም ይሖዋን በሙሉ ጊዜ ለማገልገል የነበረኝ ከፍተኛ ፍላጎት አልቀዘቀዘም። በ1940 በዲትሮይት፣ ሚሺገን በተደረገው የአውራጃ ስብሰባ ላይ አቅኚዎች የሆኑ ባልና ሚስት የተዋወቅሁ ሲሆን እነሱም ወደ ሳውዝ ካሮላይና መጥቼ አቅኚ እንድሆን አበረታቱኝ። በመሆኑም የ1935 ሞዴል የሆነች ፖንቲያክ መኪና በ150 ዶላር ገዛሁና ወደ ሳውዝ ካሮላይና ለመሄድ ተዘጋጀሁ። በ1941 ዩናይትድ ስቴትስ ወደ ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ስትገባ እኔና ሁለት ወንዶች ልጆቼ ወደ ደቡብ አቀናን፤ በዚያም እንደገና በሙሉ ጊዜ አገልግሎት መካፈል ጀመርኩ።
ወደ ሳውዝ ካሮላይና ስንዛወር መጀመሪያ የሄድነው
ወደ ካምደን ነበር፤ ቀጥሎም ወደ ሊትል ሪቨር ከዚያም ወደ ኮንዌይ አቀናን። በኮንዌይ እያለሁ አነስ ያለ ተጎታች ቤት ገዛሁ። የነዳጅ ማደያ ያለው አንድ ደግ ሰው ይህንን ተጎታች ቤት ማደያው አጠገብ እንዳቆምና በዚያ በሚገኘው ጋዝና ኤሌትሪክ አልፎ ተርፎም በመጸዳጃ ቤቱ እንድጠቀም ፈቀደልኝ። በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት ነዳጅ የሚከፋፈለው በራሽን ስለነበር ቤንዚን ማግኘት አልቻልኩም። በመሆኑም አንድ ያገለገለ ብስክሌት ገዛሁ። በ1943 ገንዘባችን በሙሉ በመሟጠጡ በአቅኚነት መቀጠል የምችል አይመስልም ነበር፤ በዚህ ወቅት ልዩ አቅኚ እንድሆን የተጋበዝኩ ሲሆን ይህም በየወሩ የወጪ መሸፈኛ እንዳገኝ አስቻለኝ። በእነዚህ ሁሉ ዓመታት ይሖዋ በጣም ረድቶኛል!በዚያን ጊዜ በኮንዌይ የሚኖር ሌላ የይሖዋ ምሥክር ስላልነበረ እኔም ሆንኩ ልጆቼ ብቻችንን አገልግሎት መውጣቱ አስቸጋሪ ሆኖብን ነበር። በመሆኑም በልዩ አቅኚነት አብራኝ የምታገለግል ጓደኛ እንዲላክልኝ የሚጠይቅ ደብዳቤ ጻፍኩ፤ በ1944 ኢዲት ዎከር የተባለች ግሩም ጓደኛ ተመደበችልኝ! ከኢዲት ጋር በተለያዩ ቦታዎች ለ16 ዓመታት አብረን አገልግለናል። የሚያሳዝነው ግን በጤና እክል ምክንያት ወደ ኦሃዮ ለመመለስ ተገደደች።
ልረሳቸው የማልችላቸው በረከቶች
ስለ እነዚያ ዓመታት ካሉኝ በርካታ አስደሳች ትዝታዎች መካከል በኮንዌይ ትኖር የነበረችው አልቤርታ አንዷ ናት፤ በ13 ዓመቷ የአካል ጉዳተኛ የሆኑትን አያቷንና ሁለት ታናናሽ ወንድሞቿን ትንከባከብ የነበረችውን ይህችን ወጣት ፈጽሞ አልረሳትም። አልቤርታ ያስተማርኳትን የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት በመውደዷ የተማረችውን ለሌሎች ለመናገር ትፈልግ ነበር። የአቅኚነትን አገልግሎት ከልቧ ታደንቅ ስለነበር በ1950 የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቷን እንደጨረሰች አቅኚ ሆነች። በአቅኚነት ማገልገል ከጀመረች ከ57 ዓመታት በላይ ቢያልፉም አሁንም በሙሉ ጊዜ አገልግሎት እየተካፈለች ነው!
በ1951 እኔና ኢዲት በጣም ጥቂት የይሖዋ ምሥክሮች በሚኖሩበት በሮክ ሂል፣ ሳውዝ ካሮላይና ለአጭር ጊዜ እንድናገለግል ተመደብን። ከዚያም ወደ ኤልበርተን፣ ጆርጂያ ተዛውረን ለሦስት ዓመታት ካገለግልን በኋላ ወደ ሳውዝ ካሮላይና የተመለስን ሲሆን በዚያም ከ1954 እስከ 1962 ቆይቻለሁ። በዋልሃላ ሳገለግል በገጠራማው አካባቢ ብቻቸውን የሚኖሩ የመስማት ችግር ያለባቸው ኔቲ የተባሉ አንዲት አረጋዊት አገኘሁ። መጽሐፍ ቅዱስ ሳስጠናቸው አረጋዊቷ ከመጽሐፉ ላይ አንድ አንቀጽ ካነበቡ በኋላ በገጹ ግርጌ ላይ የሚገኘውን ለአንቀጹ የተዘጋጀውን ጥያቄ አመለክታቸዋለሁ፤ እሳቸውም መልሱን ከአንቀጹ ያሳዩኛል።
ኔቲ ያልገባቸው ነገር ሲኖር ጥያቄያቸውን ወረቀት ላይ ያሰፍሩልኝና እኔም መልሱን እጽፍላቸው ነበር። ጊዜ እያለፈ ሲሄድ ኔቲ ለመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ያላቸው አድናቆት ስላደገ በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ መገኘትና ከቤት ወደ ቤት ማገልገል ጀመሩ። ኔቲ ከቤት ወደ ቤት የሚያገለግሉት ብቻቸውን ሲሆን እኔም ብዙም ሳልርቅ እከታተላቸዋለሁ፤ አብዛኛውን ጊዜ እርዳታ ቢያስፈልጋቸው ለመሄድ እንድችል ከመንገዱ ባሻገር እሆናለሁ።
በዋልሃላ እያለሁ አሮጌዋ መኪናዬ መሥራት አቆመች። በዚህ ወቅት በ100 ዶላር የምትሸጥ መኪና ባገኝም ገንዘብ አልነበረኝም። በንግድ ሥራ ላይ የተሠማራ አንድ ወንድም 100 ዶላር አበደረኝ። ከዚያ ብዙም ሳይቆይ እህቴ፣ አባታችን ሲሞት በባንክ ያስቀመጠው ጥቂት ገንዘብ እንደነበረ ማወቃቸውን የሚገልጽ ያልጠበቅሁት ደብዳቤ ላከችልኝ። ወንድሞቼና እህቴ በዚህ ገንዘብ ምን ቢያደርጉበት እንደሚሻል ከተነጋገሩ በኋላ ሁሉም ለእኔ እንዲላክ ተስማሙ። ገንዘቡ 100 ዶላር ነበር!
ከልጆቼ ጋር በአቅኚነት ማገልገል
ኤዲና ባቢ ልጆች እያሉ ሁልጊዜ አብረውኝ ከቤት ወደ ቤት ያገለግሉ ነበር። በዚያን ጊዜ በአጠቃላይ ሲታይ ሰዎች ዕፅ አይወስዱም፤ የሥነ ምግባር ብልግናም በዛሬው ጊዜ እንደሚታየው አልተስፋፋም ነበር። ኑሯችን ቀላል እንዲሆን ማድረጌና በስብከቱ ሥራ ላይ ማተኮሬ
በአሁኑ ጊዜ ወላጆች፣ ልጆቻቸው የይሖዋ አገልጋዮች እንዲሆኑ ለመርዳት ሲጥሩ የሚገጥሟቸውን አብዛኞቹን ችግሮች ለማስቀረት አስችሎኛል።ኤዲ፣ በካምደን በሚገኝ ትምህርት ቤት እስከ ስምንተኛ ክፍል ከተማረ በኋላ ከእኔ ጋር በአቅኚነት ማገልገል ጀመረ። ለተወሰኑ ዓመታት አብረን በአቅኚነት በደስታ ስናገለግል ከቆየን በኋላ በብሩክሊን ኒው ዮርክ በሚገኘው የይሖዋ ምሥክሮች ዋና መሥሪያ ቤት የማገልገል ፍላጎት አደረበት። በዚያም ከ1947 እስከ 1957 ያገለገለ ሲሆን በ1958 የቀድሞ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዬ የነበረችውን አልቤርታን አግብቶ አብረው በአቅኚነት ማገልገል ቀጠሉ። በ2004 በአቅኚዎች የአገልግሎት ትምህርት ቤት ሦስታችንም አንድ ላይ ስንካፈል ምን ያህል እንደተደሰትን መገመት ትችላላችሁ!
ከበርካታ ዓመታት በፊት ባቢ ትንሽ ልጅ እያለ፣ በቋሚነት መጽሐፍ ቅዱስን ወደማስጠናቸው ሰዎች በመኪና መሄድ እንድችል በቂ ነዳጅ እንዳገኝ ይሖዋ እንዲረዳኝ ሲጸልይ የሰማሁበትን ቀን አልረሳውም። ባቢ በሕይወቱ ሙሉ ለአገልግሎት ፍቅር እንዳለው ያሳየ ሲሆን ለረጅም ዓመታትም በአቅኚነት አገልግሏል። የሚያሳዝነው ባቢም ከቤተሰቡ ጋር በተያያዘ አሳዛኝ ሁኔታ አጋጠመው። በ1970 ባለቤቱ መንታ ልጆቻቸውን ስትወልድ ሕይወቷን ያጣች ሲሆን ሕፃናቱም ሞቱ። ከባለቤቱ ጋር ከተጋቡ ገና ሁለት ዓመት እንኳ አልሞላቸውም ነበር። እኔና ባቢ ሁልጊዜም የኖርነው በአንድ አካባቢ ሲሆን በጣም እንቀራረባለን።
አሁንም በአቅኚነት ማገልገል
በ1962 በለምበርተን፣ ኖርዝ ካሮላይና ውስጥ በሚገኝ ጉባኤ የተመደብኩ ሲሆን ከ45 ዓመታት በኋላም በዚህ ጉባኤ ውስጥ እያገለገልኩ ነው። በ80ዎቹ ዓመታት ውስጥ ሆኜም እንኳ መኪናዬን እነዳ ነበር። በአሁኑ ወቅት በአቅራቢያዬ ካሉት የይሖዋ ምሥክሮች መካከል አንድ ቤተሰብ ወደ ጉባኤና አገልግሎት ይወስደኛል።
ለመራመድ የሚያግዝ ድጋፍና ተሽከርካሪ ወንበር ቢኖረኝም ያለ ምንም እርዳታ መሄድ ስለምችል አንዱንም መጠቀም አያስፈልገኝም። ጥሩ ጤንነት ስለሰጠኝ ይሖዋን አመሰግነዋለሁ፤ ዓይኔ እንኳ ትንሽ የደከመው በቅርቡ ነው። በጣም ካልታመምኩ በስተቀር ከጉባኤ ስብሰባዎች በፍጹም አልቀርም። አቅመ ደካማ ለሆኑ ለረጅም ጊዜ ያገለገሉ አቅኚዎች በተደረገው ዝግጅት በመጠቀም አሁንም አቅኚ ሆኜ እያገለገልሁ ነው።
በአቅኚነት ከ70 ለሚበልጡ ዓመታት በማገልገሌ ይሖዋ በሕይወቴ ሁሉ እንደረዳኝ አፌን ሞልቼ መናገር እችላለሁ። a መቼም ቢሆን በጣም ጎበዝ ወይም ፈጣን ሠራተኛ እንዳልነበርኩ አውቃለሁ፤ ሆኖም ይሖዋ ምን መሥራት እንደምችልና ምን መሥራት እንደማልችል ይገነዘባል። ይሖዋ ጥረት እያደረግሁ መሆኔን ስለሚረዳልኝና ስለተጠቀመብኝ በጣም አመሰግነዋለሁ።
ሁሉን ነገር የሰጠን ይሖዋ በመሆኑ የምንችለውን ያህል በተሟላ መልኩ እሱን ማገልገል አስፈላጊ እንደሆነ ይሰማኛል። አቅሜ እስከፈቀደ ድረስ አቅኚነትን ማቆም አልፈልግም። ይህ አገልግሎት እንዴት ያለ ግሩም መብት ነው! ይሖዋ ለዘላለም እንዲጠቀምብኝ ጸሎቴ ነው።
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
a እህት ስታይገርስ መቶ ዓመት ሊሞላት ሦስት ወራት ሲቀሯት ሚያዝያ 20, 2007 ምድራዊ ሕይወቷን አጠናቃለች። ለበርካታ ዓመታት በታማኝነት ያከናወነችው አገልግሎት የሚያበረታታን ከመሆኑም በላይ በሰማይ ሽልማቷን መቀበሏ ያስደስተናል።
[በገጽ 13 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
እኔና ባለቤቴ ኮልፖርተሮች ሆነን ስናገለግል በዚህ መኪና እንጠቀም ነበር
[በገጽ 14 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በ1941 ከልጆቼ ጋር
[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በቅርቡ ከኤዲና ከባቢ ጋር