በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ለፖላንድ የተሰጠ “ታላቅ ስጦታ”

ለፖላንድ የተሰጠ “ታላቅ ስጦታ”

ለፖላንድ የተሰጠ “ታላቅ ስጦታ”

ሐምሌ 6, 1525 ሆኸንዞለናዊው መስፍን አልብረሽት፣ የሉተራን እምነት የመንግሥት ሃይማኖት እንዲሆን አዋጅ አወጣ። በመስፍን ትተዳደር የነበረችው ፕራሻ የማርቲን ሉተርን ትምህርት በይፋ ለመቀበል የመጀመሪያዋ የአውሮፓ አገር ሆነች። በወቅቱ ፕራሻ የምትተዳደረው በፖላንድ ነበር።

አልብረሽት የምሥራቅ ፕራሻ መዲና የነበረችውን ኬኒዝበርግን የፕሮቴስታንት የባሕል ማዕከል ሊያደርጋት ፈልጎ ነበር። መስፍኑ በዚህች ከተማ ውስጥ ዩኒቨርሲቲ ያቋቋመ ሲሆን የሉተራን እምነት ጽሑፎች በበርካታ ቋንቋዎች እንዲታተሙ ድጋፍ ያደርግ ነበር። ከዚህ በተጨማሪም በአገሩ ውስጥ የሚኖሩት ፖላንዳውያን የተወሰኑ የቅዱሳን መጻሕፍት ክፍሎች በቋንቋቸው ሲነበብላቸው ማዳመጥ እንዳለባቸው የሚያዝ ድንጋጌ በ1544 አወጣ። ይሁንና በጊዜው በፖሊሽ ቋንቋ የተዘጋጀ መጽሐፍ ቅዱስ አልነበረም።

‘በዕለት ተዕለት ቋንቋ’ የተዘጋጀ ትርጉም

በመሆኑም አልብረሽት ለችግሩ እልባት ለመስጠት የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍትን በፖሊሽ ቋንቋ መተርጎም የሚችል ሰው ማፈላለግ ጀመረ። በ1550 ገደማ በጸሐፊነት፣ መጻሕፍትን በመሸጥና በሕትመት ሥራ ላይ ተሰማርቶ የነበረ ጃን ሱኩሉቱዚያ የተባለ ሰው ቀጠረ። ይህ ሰው ከሌፕሲግ ዩኒቨርሲቲ የተመረቀ ሲሆን የፕሮቴስታንቶችን ትምህርት በማስፋፋቱ የካቶሊክን ቤተ ክርስቲያን ማስቆጣቱ ይታወቅ ነበር። እንዲያውም በአንድ ወቅት ሃይማኖታዊ እምነቶቹን ለማስፋፋት ባደረገው ጥረት ምክንያት ለፍርድ ሊቀርብ ሲል ወደ ኬኒዝበርግ ከተማ ሸሽቶ ነበር።

ጃን ሱኩሉቱዚያ መጽሐፍ ቅዱስን በፖሊሽ ቋንቋ ለማዘጋጀት ከፍተኛ ጉጉት ነበረው። ሱኩሉቱዚያ ሥራውን ከተረከበ ከዓመት በኋላ የማቴዎስ ወንጌል የመጀመሪያ ቅጂዎች ለመታተም በቁ። ይህ እትም ለተወሰኑ ጥቅሶች አማራጭ ትርጉም የሚሰጡ ዝርዝር ማብራሪያዎችንና ጠቃሚ የኅዳግ ማስታወሻዎችን ያካተተ ነበር። ከዚያም ብዙም ሳይቆይ ሱኩሉቱዚያ የአራቱንም ወንጌሎች ሕትመት በበላይነት ይቆጣጠር ጀመር። በሦስት ዓመት ውስጥ ሁሉንም የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት ለማሳተም በቃ።

ተርጓሚው ትክክለኛ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ለማዘጋጀት ሲል የግሪክኛ መጻሕፍትን ያመሳክር ነበር። ከዚህም በተጨማሪ በ1551 እትም ላይ የሰፈረው መቅድም ተርጓሚው የላቲን ትርጉሞችንና “በሌሎች ቋንቋዎች የተዘጋጁ አንዳንድ የትርጉም ሥራዎችን ማመሳከሩን” ይገልጻል። ስተዲስ ኦን ዘ ፖሊሽ ላንጉጅ ኦቭ ሲክስቲንዝ ሴንቸሪ የተሰኘው መጽሐፍ ደራሲ የሆኑት ስታኒስላፍ ሮስፖንድ ይህን የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም “ማራኪና ጥሩ የሐሳብ ፍሰት ያለው” ሲሉ ገልጸውታል። ሮስፖንድ ቀጠል አድርገውም ተርጓሚው “በተራቀቁ ቃላት አልተጠቀመም” ከዚህ ይልቅ ፖላንዳውያን “በዕለት ተዕለት ሕይወታቸው በሚጠቀሙበት ቋንቋ” ለመተርጎም ጥረት አድርጓል ብለዋል።

ይህን ፕሮጀክት ያስተባበረው ሱኩሉቱዚያ ቢሆንም ተርጓሚው እሱ እንዳልነበር ማስረጃዎች ይጠቁማሉ። ታዲያ የትርጉም ሥራውን ያከናወነው ምሑር ማን ነው? ተርጓሚው ስታኒስላው ሙርዚሂኖቪስኪ የተባለ ወጣት ሲሆን ሱኩሉቱዚያ ይህን አስቸጋሪ ሥራ እንዲሠራለት በቀጠረው ጊዜ ዕድሜው በ20ዎቹ መጀመሪያ ላይ ነበር።

ሙርዚሂኖቪስኪ የተወለደው በአንዲት አነስተኛ መንደር ውስጥ ሲሆን ዕድሜው ሲደርስ አባቱ የግሪክኛና የዕብራይስጥኛ ቋንቋዎችን እንዲያጠና ወደ ኬኒዝበርግ ላከው። ከዚያም ሙርዚሂኖቪስኪ፣ በጀርመን ዊትንበርግ ዩኒቨርሲቲ የገባ ሲሆን ከማርቲን ሉተር ጋር የተዋወቁትም በዚያ ሳይሆን አይቀርም። ይህ ወጣት ተማሪ የፊሊፕ ሜላንግተንን ትምህርት በጥሞና ማዳመጡ የግሪክና የዕብራይስጥ ቋንቋዎችን ጠንቅቆ እንዲያውቅ እንደረዳው ጥርጥር የለውም። ሙርዚሂኖቪስኪ ወደ ጣሊያን በመሄድ ተጨማሪ ትምህርት ከተከታተለ በኋላ ወደ ኬኒዝበርግ ተመልሶ መስፍን አልብረሽትን ማገልገል ጀመረ።

ማርያ ኮሶቫስክ የተባሉ ጸሐፊ፣ ዘ ባይብል ኢን ዘ ፖሊሽ ላንጉጅ በተሰኘው መጽሐፋቸው ላይ እንዲህ በማለት ተናግረዋል:- “ሙርዚሂኖቪስኪ ትጉህና ስኬታማ ሠራተኛ ነበር። ሆኖም የሌሎችን ትኩረት ወደ ራሱ ለመሳብ፣ ትልቅ ሥልጣን ለማግኘት አሊያም በትርጉም ሥራው የመጀመሪያ ገጽ ላይ ስሙ እንዲሰፍር እንኳ አልፈለገም።” በእርግጥም ይህ ወጣት ችሎታውን አስመልክቶ ሲጽፍ “የላቲንንም ሆነ የፖሊሽን ቋንቋ በጥሩ ሁኔታ አልጽፍም” ብሏል። ሙርዚሂኖቪስኪ እንዲህ ቢሰማውም ፖላንዳውያን የአምላክን ቃል እንዲያገኙ ለማድረግ መሣሪያ ሆኖ አገልግሏል። የሥራ ባልደረባው የሆነው ሱኩሉቱዚያ ያዘጋጁትን የትርጉም ሥራ ለፖላንዳውያን የተሰጠ “ታላቅ ስጦታ” ሲል ገልጾታል።

ሌላው ታላቅ ስጦታ

በፖሊሽ ቋንቋ ከተዘጋጀው ከዚህ መጽሐፍ ቅዱስ በኋላ ሌሎች በርካታ ትርጉሞች ወጥተዋል። በ1994፣ የአዲስ ዓለም የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት ትርጉም፣ እንዲሁም በ1997 መላው የአዲስ ዓለም ቅዱሳን መጻሕፍት ትርጉም በፖሊሽ ቋንቋ ወጥተዋል። እነዚህን የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች ያዘጋጁት ሰዎች የሌሎችን ትኩረት ወደ ራሳቸው መሳብ የማይፈልጉ ከመሆናቸውም ሌላ የአምላክን ቃል ትክክለኛነቱን በጠበቀ ሁኔታና በ16ኛው ክፍለ ዘመን ይነገር በነበረው ቋንቋ ሳይሆን በዛሬው ጊዜ በሚነገረው ቋንቋ ለማስቀመጥ የተቻላቸውን ያህል ጥረዋል።

በዛሬው ጊዜ መጽሐፍ ቅዱስ በሙሉም ሆነ በከፊል ወደ 2,400 በሚያክሉ ቋንቋዎች ተተርጉሟል። የአምላክን ቃል ትክክለኛ ትርጉም በራስህ ቋንቋ ማግኘት ከቻልክ የይሖዋን መመሪያ የምታገኝበት ከሁሉ የላቀ ትልቅ ስጦታ አግኝተሃል ማለት ነው።—2 ጢሞቴዎስ 3:15-17

[በገጽ 20 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

“አዲስ ኪዳንን” በፖሊሽ ቋንቋ ላዘጋጀው ለስታኒስላው ሙርዚሂኖቪስኪ የቆመ የመታሰቢያ ሐውልት

[በገጽ 21 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በስታኒስላው ሙርዚሂኖቪስኪ የተተረጎመው ማቴዎስ ምዕራፍ 3

[ምንጭ]

Dziȩki uprzejmości Towarzystwa Naukowego Plockiego