በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የተፈጥሮን ንድፍ ከማድነቅ ባሻገር ስለ ንድፍ አውጪው ተማር

የተፈጥሮን ንድፍ ከማድነቅ ባሻገር ስለ ንድፍ አውጪው ተማር

የተፈጥሮን ንድፍ ከማድነቅ ባሻገር ስለ ንድፍ አውጪው ተማር

ማይክልአንጀሎ ስለተባለው ጣሊያናዊ ሰዓሊና የቅርጻ ቅርጽ ባለሙያ ሲነገር ሰምተህ ይሆናል። የዚህን ሰው ሥራዎች የመጀመሪያ ቅጂ አይተህ ባታውቅም እንኳ ይህን ልዩ ተሰጥኦ ያለው ጣሊያናዊ “ድንቅና ተወዳዳሪ የሌለው የሥነ ጥበብ ባለሙያ” ብሎ ከጠራው የሥነ ጥበብ ታሪክ ጸሐፊ ጋር ሳትስማማ አትቀርም። ማይክልአንጀሎ ታላቅ ተሰጥኦ እንዳለው ማንም ሰው አይክድም። የማይክልአንጀሎን የሥነ ጥበብ ሥራዎች እያደነቀ ይህ ሰው የተዋጣለት የሥነ ጥበብ ባለሙያ መሆኑን አምኖ የማይቀበል ማን ይኖራል?

አሁን ደግሞ፣ በዙሪያችን ስላሉት እጅግ አስደናቂ የሆኑ ውስብስብና የተለያዩ ሕያዋን ፍጥረታት መለስ ብለህ አስብ። ዘ ኒው ዮርክ ታይምስ የተባለው መጽሔት አንድ የሥነ ሕይወት ሳይንስ ፕሮፌሰር የተናገሩትን በመጥቀስ “ንድፍ መኖሩን የሚያረጋግጡ ማስረጃዎች በሁሉም የሥነ ሕይወት ዘርፎች ላይ በጉልህ ይታያሉ” ማለቱ ተገቢ ነው። እኚህ ሰው አክለው “በሕያዋን ፍጥረታት ላይ የሚንጸባረቀው ንድፍ በአድናቆት እንድንዋጥ ያደርገናል” ብለዋል። ንድፍን አድንቆ ለንድፍ አውጪው እውቅና አለመስጠት ምክንያታዊ ነው?

በዙሪያው ያሉትን ነገሮች በትኩረት ይከታተል የነበረው ሐዋርያው ጳውሎስ ‘በፈጣሪ ፈንታ ፍጡርን ስለሚያከብሩና ስለሚያገለግሉ’ ሰዎች ተናግሯል። (ሮሜ 1:25 ዳርቢ) አንዳንዶች በስፋት ተሠራጭቶ የሚገኘው የዝግመተ ለውጥ ጽንሰ ሐሳብ ባሳደረባቸው ተጽዕኖ ምክንያት፣ ንድፍ ካለ ንድፍ አውጪ ሊኖር ይገባል የሚለውን ሐሳብ ለመቀበል አሻፈረኝ ብለዋል። ይሁንና የዝግመተ ለውጥ ጽንሰ ሐሳብ እውነተኛውን ሳይንስ ይወክላል? የቪየናው ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ሊቀ ጳጳስ የሆኑት ክሪስቶፍ ሼንቦርን የተናገሩትን ሐሳብ ዘ ኒው ዮርክ ታይምስ መጽሔት እንዲህ ሲል አስፍሮታል:- “በሥነ ሕይወት ላይ ንድፍ መኖሩን የሚያሳየውን ማስረጃ የማይቀበል ወይም የሚያጣጥል ማንኛውም አስተሳስብ መላ ምት እንጂ ሳይንስ ነው ሊባል አይችልም።”

ሳይንስ አበቃለት ማለት ነው?

ይሁን እንጂ፣ ፈጣሪ መኖሩን የሚያሳየውን ማስረጃ መቀበል “ምርምርን እንደሚገታ” ሆኖ የሚሰማቸው ሰዎች አልጠፉም። በኒው ሳይንቲስት መጽሔት ላይ የወጣ አንድ ርዕስ ይህን መሰሉን ፍርሃት አስመልክቶ “‘ንድፍ አውጪ አለ’ የሚለው አስተሳሰብ የማይነቃነቅ ጋሬጣ ስለሆነበት ሳይንስ ገደብ የሌለው ምርምር የሚደረግበት መስክ መሆኑ አክትሞለታል” ብሏል። በእርግጥ ይህ ስጋት መሠረት ያለው ነው? በፍጹም። እንዲያውም እውነታው የተገላቢጦሽ ነው። እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው?

አጽናፈ ዓለምም ሆነ በምድር ላይ የሚገኙት ሕያዋን ፍጥረታት የተገኙት እንዲያው በአጋጣሚና በዝግመተ ለውጥ ነው ብሎ ማመን ሰዎች ትርጉም ያለው መልስ ለማግኘት ከመጣር ወደኋላ እንዲሉ ያደርጋቸዋል። በሌላ በኩል ግን በዙሪያችን ያሉትን ነገሮች የሠራው ከፍተኛ የማሰብ ችሎታ ያለው አካል መሆኑን አምኖ መቀበል፣ በተፈጥሮና በግዑዙ አጽናፈ ዓለም ላይ የተንጸባረቀውን ጥበቡን እንድንመረምር ያነሳሳናል። ለምሳሌ ያህል የሥነ ጥበብ ታሪክ ምሑራን “ሞና ሊዛን” የሳለው ሊዮናርዶ ዳ ቪንቺ መሆኑን ማወቃቸው የአሳሳል ስልቱንና ሥዕሉን ለመሥራት የተጠቀመባቸውን ቁሳቁሶች ለማወቅ ምርምር ከማድረግ አላገዳቸውም። በተመሳሳይም ንድፍ አውጪ አለ ብሎ ማመን፣ ውስብስብ ስለሆኑት ንድፎቹና የፍጥረት ሥራዎቹ ዝርዝር ሁኔታዎችን ለማወቅ ምርምር ከማድረግ ሊያግደን አይችልም።

መጽሐፍ ቅዱስ ተጨማሪ ምርምር እንዳናደርግ እንቅፋት ከመሆን ይልቅ ለሚነሱብን ሳይንሳዊም ሆኑ መንፈሳዊ ጥያቄዎች መልስ ለማግኘት ምርምር እንድናደርግ ያበረታታናል። በጥንት ዘመን ይኖር የነበረው ንጉሥ ዳዊት ታላቅ ጥበብ በተንጸባረቀበት አካሉ ላይ ካሰላሰለ በኋላ “ግሩምና ድንቅ ሆኜ ተፈጥሬአለሁና አመሰግንሃለሁ፤ ሥራህ ድንቅ ነው፤ ነፍሴም ይህን በውል ተረድታለች” ብሏል። (መዝሙር 139:14) እንዲያውም ፈጣሪ፣ ኢዮብን “የምድርን ስፋት ታውቃለህን?” በማለት እንደጠየቀው መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። (ኢዮብ 38:18) ይህ አባባል ምርምር ከማድረግ መታቀብ እንዳለብን የሚጠቁም አለመሆኑ ግልጽ ነው። ከዚህ በተቃራኒ ታላቁ ንድፍ አውጪ ሰዎች በእጁ ሥራዎች ላይ ምርምር እንዲያደርጉ ግብዣ አቅርቦላቸዋል። በተጨማሪም ነቢዩ ኢሳይያስ “ዐይናችሁን አንሡ፤ ወደ ሰማይ ተመልከቱ፤ እነዚህን ሁሉ የፈጠረ ማን ነው?” ብሎ በመጻፍ በዙሪያችን ያሉትን ፍጥረታት ስለሠራው አካል ያለንን እውቀት እንድናሳድግ ጋብዞናል። ኢሳይያስ 40:26 በመቀጠል አጽናፈ ዓለምን ለመሥራት እጅግ ታላቅ ኃይል ያስፈልጋል የሚለው ሐቅ ትክክል መሆኑን ያረጋግጣል። ይህ ሐቅ ደግሞ ከሳይንስ ግኝቶች ጋር ይስማማል።

እርግጥ ነው፣ ፍጥረትን አስመልክቶ ለሚነሱ ጥያቄዎች ሁልጊዜ በቀላሉ መልስ ማግኘት አይቻልም። በከፊል ይህ የሆነበት ምክንያት፣ የመረዳት ችሎታችን ውስን ስለሆነና ስለምንኖርበት ዓለም ያለን እውቀት የተሟላ ባለመሆኑ ነው። ኢዮብ ይህን በደንብ ተገንዝቦ ነበር። ኢዮብ ምድራችንን ያላንዳች ድጋፍ በሕዋ ላይ ያቆመውንና ውኃ ያዘሉ ዳመናዎችን ከምድር በላይ ያንጠለጠለውን ፈጣሪን አወድሶታል። (ኢዮብ 26:7-9) ያም ሆኖ እነዚህ አስደናቂ ነገሮች ‘የፈጣሪ ሥራ ዳር ዳር’ ብቻ መሆናቸውን አስተውሏል። (ኢዮብ 26:14) ኢዮብ በዙሪያው ስላለው ዓለም ይበልጥ መማር ይፈልግ እንደነበር ምንም ጥርጥር የለውም። ዳዊትም ቢሆን “እንዲህ ያለው ዕውቀት ለኔ ድንቅ ነው፤ ልደርስበትም የማልችል ከፍ ያለ ነው” ብሎ መጻፉ የአቅም ገደብ እንዳለበት አምኖ መቀበሉን ያሳያል።—መዝሙር 139:6

ፈጣሪ አለ ብሎ ማመን ለሳይንስ እድገት እንቅፋት አይሆንም። ስለ ቁስ አካልም ሆነ ስለ መንፈሳዊ ነገሮች የተሟላ እውቀት ለማግኘት የሚደረገው ምርምር መቋጫ የሌለውና ዘላለማዊ ነው። እውቀት በማካበቱ የሚታወቅ በጥንት ዘመን የኖረ አንድ ንጉሥ ‘[አምላክ] በሰዎች ልብ ዘላለማዊነትን አኖረ፤ ይሁን እንጂ ከመጀመሪያ እስከ መጨረሻ ያደረገውን ማወቅ አይችሉም’ በማለት በትሕትና ጽፏል።—መክብብ 3:11

አምላክ ‘ክፍተት መሙያ’ ነው?

አንዳንድ ሰዎች፣ ‘አምላክ’ ለአንድ ጉዳይ ሳይንሳዊ ማብራሪያ መስጠት ሳይቻል ሲቀር እንዲሁ ያለ ቦታው የሚጠቀስ፣ ተጨባጭነት የሌለው ‘የመፍትሔ ሐሳብ’ ነው የሚል ተቃውሞ ያነሳሉ። በሌላ አባባል እነዚህ ሰዎች ንድፍ አውጪ መለኮታዊ አካል አለ የሚለው ሐሳብ ሰዎች ነገሮችን በምክንያታዊነት ማስረዳት ሲሳናቸው የፈጠሩት ‘ክፍተት መሙያ’ ነው ማለታቸው ነው። ይሁንና እዚህ ላይ ክፍተት ናቸው የተባሉት ነገሮች ምንድን ናቸው? እንዲያው እዚህ ግባ የማይባሉና ብናውቃቸውም ሆነ ባናውቃቸው ለውጥ የማያመጡ ጥቃቅን ጉድለቶች ናቸው? በፍጹም። ከዚህ ይልቅ በዳርዊን ጽንሰ ሐሳብ ላይ ትልቅ ለውጥ የሚያመጡ ሰፋፊ ክፍተቶች ናቸው። እነዚህ ክፍተቶች ከሥነ ሕይወት ጥናት ጋር በተያያዘ የዝግመተ ለውጥ ጽንሰ ሐሳብ በቂ ማብራሪያ ያላገኘላቸው መሠረታዊ ሐሳቦች ናቸው። እንደ እውነቱ ከሆነ የዝግመተ ለውጥ ጽንሰ ሐሳብ አራማጆች ተጨባጭ ማስረጃ የሌለውን የዳርዊንን ጽንሰ ሐሳብ፣ ሳይንስ ማረጋገጫ ሊያገኝላቸው ላልቻሉ ነገሮች ‘ክፍተት መሙያ’ አድርገው ይጠቀሙበታል።

በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሰው ፈጣሪ ‘ክፍተት መሙያ’ አይደለም። ከዚህ ይልቅ በፍጥረት ሥራዎች ውስጥ የእሱ እጅ የሌለበት ነገር የለም። መዝሙራዊው “አንተ የሕይወት ሁሉ ምንጭ ነህ፤ ከአንተም ብርሃን የተነሣ ብርሃን እናያለን” በማለት የይሖዋ የፍጥረት ሥራ ሁሉን አቀፍ መሆኑን ተናግሯል። (መዝሙር 36:9 የ1980 ትርጉም) ይሖዋ ‘ሰማይንና ምድርን፣ ባሕርንም፣ በውስጣቸውም የሚኖሩትን ሁሉ መፍጠሩ’ በሚገባ ተገልጿል። (የሐዋርያት ሥራ 4:24፤ 14:15፤ 17:24) በመጀመሪያው መቶ ዘመን ይኖር የነበረ አንድ አስተማሪ አምላክ ‘ሁሉን ፈጥሯል’ ብሎ ለመጻፍ የሚያስችል አጥጋቢ ምክንያት ነበረው።—ኤፌሶን 3:9

ከዚህም በተጨማሪ፣ አምላክ “የሰማያትን ሥርዐት” ማለትም ቁስ አካልና ኃይል የሚመሩበትን የተፈጥሮ ሕግጋት ፈጥሯል። ሳይንቲስቶች እስካሁን ድረስ በእነዚህ ሕግጋት ላይ ጥናት በማካሄድ ላይ ይገኛሉ። (ኢዮብ 38:33) አምላክ ያወጣቸው ንድፎች የተሟሉና ዓላማ ያላቸው ከመሆናቸው ባሻገር ምድር የተለያዩ ዝርያዎች ባሏቸው አስደናቂ ሕያዋን ፍጥረታት እንድትሞላ ያወጣውን ዓላማ ከግብ ለማድረስ የሚረዱ ናቸው።

ንድፍና የማመዛዘን ችሎታ

በመጨረሻም፣ የማመዛዘን ችሎታን አስመልክቶ የሚነሳውን ጥያቄ መመርመራችን ጥሩ ይሆናል። የሳይንስ ጽሑፍ አዘጋጅ የሆኑት ጆን ሆርገን የተለያዩ ሳይንሳዊ ጽንሰ ሐሳቦች ያላቸውን ተአማኒነት አስመልክተው ሲናገሩ “የተገኘው መረጃ አጠራጣሪ በሚሆንበት ጊዜ መመሪያ ለማግኘት የማመዛዘን ችሎታችንን መጠቀማችን የሚያሳፍር ነገር አይደለም” ብለዋል።

ሕይወት የተገኘው እንዲያው በአጋጣሚ ወይም ምንነታቸው በማይታወቅ ኃይሎች ነው ብሎ ማሰብ ምክንያታዊ ነው? የዝግመተ ለውጥ ጽንሰ ሐሳብ ሰፊ ተቀባይነት ያገኘ ቢሆንም እንኳ ሳይንቲስቶችን ጨምሮ በርካታ ምሑራን ከፍተኛ የማሰብ ችሎታ ያለው ፈጣሪ መኖሩን ያምናሉ። አንድ የሳይንስ ፕሮፌሰር እንዳሉት ከሆነ አብዛኛው ሕዝብ “ሕይወት በንድፍ የተሠራ ነው የሚል ጠንካራና ምክንያታዊ የሆነ አስተሳሰብ አለው።” ብዙዎች እንዲህ ብለው የሚያምኑት ለምንድን ነው? በርካታ ሰዎች ሐዋርያው ጳውሎስ “እያንዳንዱ ቤት የራሱ ሠሪ አለው” በማለት ከገለጸው ሐሳብ ጋር ሙሉ በሙሉ ስለሚስማሙ ነው። (ዕብራውያን 3:4) ከዚያም ጳውሎስ “ነገር ግን ሁሉን የሠራ እግዚአብሔር ነው” የሚል ምክንያታዊ መደምደሚያ አቅርቧል። ከመጽሐፍ ቅዱስ አመለካከት አንጻር ሲታይ፣ አንድ ቤት ንድፍ አውጪና የሚገነባው ሰው ሊኖረው ይገባል ብለው እያመኑ ውስብስብ የሆነ አንድ ሕዋስ እንዲሁ በአጋጣሚ ተገኘ ብሎ ማሰብ ምክንያታዊ አይደለም።

መጽሐፍ ቅዱስ ንድፍ አውጪና ፈጣሪ የለም ብለው ስለሚያምኑ ሰዎች ሲናገር “ሞኝ በልቡ፣ ‘እግዚአብሔር [“ይሖዋ፣” NW] የለም’ ይላል” ብሏል። (መዝሙር 14:1) እዚህ ላይ መዝሙራዊው በፈጣሪ መኖር ያላመኑ ሰዎችን ገሥጿቸዋል። አንድ ሰው ጽንፈኛ በመሆን በራሱ አስተሳሰብ ይመራ ይሆናል። ጠቢብና አስተዋይ የሆነ ሰው ግን የፈጣሪን መኖር በትሕትና አምኖ ይቀበላል።—ኢሳይያስ 45:18

አስተዋይ ለሆኑ በርካታ ሰዎች ታላቅ ንድፍ አውጪ እንዳለ የሚያሳየው ማስረጃ የሚያጠራጥር አይደለም።

ንድፍ አውጪውን ማወቅ ትችላለህ

ራሳችንን የንድፍ ውጤት አድርገን የምንመለከት ከሆነ “የተፈጠርነው ለምንድን ነው? የሕይወታችን ዓላማስ ምን ይሆን?” ብለን መጠየቃችን አይቀርም። እነዚህን ለመሳሰሉት ጥያቄዎች ሳይንስ ብቻውን አጥጋቢ መልስ አይሰጥም። ይሁን እንጂ እነዚህ መሠረታዊ ጥያቄዎች አሳማኝና አጥጋቢ መልስ ይሻሉ። በዚህ ረገድ መጽሐፍ ቅዱስ ጠቃሚ እርዳታ ያበረክታል። መጽሐፍ ቅዱስ ይሖዋን ፈጣሪ ብቻ ሳይሆን ዓላማና ለሚሠራቸው ነገሮች ሁሉ አሳማኝ ምክንያቶች ያሉት አምላክ እንደሆነ አድርጎ ይገልጸዋል። ቅዱሳን መጻሕፍት አምላክ ለሰው ልጆች ያለውን ዓላማ የሚገልጹ ሲሆን ብሩህ የወደፊት ተስፋም ይዘዋል።

ይሁንና ይሖዋ ማን ነው? ምን ዓይነት አምላክ ነው? የይሖዋ ምሥክሮች ታላቁ ንድፍ አውጪያችንን ይበልጥ እንድታውቀው ሊረዱህ ፈቃደኞች ናቸው። ስለ ስሙ፣ ስለ ባሕርያቱና ከሰው ልጆች ጋር ስላለው ግንኙነት መማር ትችላለህ። የአምላክን ድንቅ ንድፎች ማድነቅ ብቻ ሳይሆን ንድፍ አውጪ በመሆኑ ክብር ልንሰጠው የሚገባን ለምን እንደሆነ በቃሉ በመጽሐፍ ቅዱስ አማካኝነት ትማራለህ።—መዝሙር 86:12፤ ራእይ 4:11

[በገጽ 4 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ማይክልአንጀሎ

[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ንድፍ አውጪ አለ ብሎ ማመን ከእውነተኛ ሳይንስ ጋር ይስማማል

[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የተለያዩ ዝርያዎች መኖራቸውና ሕያዋን ፍጥረታት ከአካባቢያቸው ጋር ለመላመድ የሚያደርጉት ለውጥ፣ እጅግ የረቀቁ ልዩ ልዩ ንድፎች ስለመኖራቸው ማረጋገጫ ናቸው

[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ንድፍ ካለ፣ ንድፍ አውጪ ሊኖር ይገባል