በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በልጃችሁ ልብ ውስጥ የአምላክን ፍቅር መቅረጽ የምትችሉት እንዴት ነው?

በልጃችሁ ልብ ውስጥ የአምላክን ፍቅር መቅረጽ የምትችሉት እንዴት ነው?

በልጃችሁ ልብ ውስጥ የአምላክን ፍቅር መቅረጽ የምትችሉት እንዴት ነው?

ከይሖዋ አምላክ ጋር የቅርብ ዝምድና መመሥረት በጣም አስቸጋሪ በሆነበት ጊዜ ላይ እንገኛለን። (መዝሙር 16:8) አስቀድሞ በትንቢት እንደተነገረው የምንኖረው ‘በሚያስጨንቅ ጊዜ’ ውስጥ ነው። አብዛኞቹ ሰዎች “ከእግዚአብሔር ይልቅ ተድላን የሚወዱ” ናቸው። (2 ጢሞቴዎስ 3:1-5) አዎን፣ በዛሬው ጊዜ በዓለም ውስጥ ለአምላክ እውነተኛ ፍቅር ያለው ሰው ማግኘት በጣም አስቸጋሪ ሆኗል።

ልጃችን ለአምላክ ፍቅር እንዲኖረው ከፈለግን ትጋት የተሞላበት ጥረት ማድረግ ይኖርብናል። ልጆቻችን ለይሖዋ አምላክ ያላቸውን ልባዊ ፍቅር እንዲያሳድጉ መርዳት ይጠበቅብናል። ታዲያ ይህን ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው?

ግልጽ ውይይት ማድረግ

ልጆቻችን ለአምላክ ያላቸውን ፍቅር እንዲያሳድጉ መርዳት የምንችለው የራሳችን ልብ ለእሱ ባለን ፍቅር የተሞላ ከሆነ ነው። (ሉቃስ 6:40) መጽሐፍ ቅዱስ የዚህን አስፈላጊነት ሲገልጽ እንዲህ ይላል:- “አምላክህን እግዚአብሔርን [“ይሖዋን፣” NW] በፍጹም ልብህ፣ በፍጹም ነፍስህ፣ በፍጹም ኀይልህ ውደድ። ዛሬ የምሰጥህን እነዚህን ትእዛዛት በልብህ ያዝ። ለልጆችህም አስጠናቸው [“በልጆችህም ልብ ውስጥ ቅረጻቸው፣” NW]።”—ዘዳግም 6:4-7

የአምላክን ፍቅር በልጆቻችን ልብ ውስጥ መቅረጽ የምንችለው እንዴት ነው? በመጀመሪያ ደረጃ በልጃችን ልብ ውስጥ ያለውን ነገር ማስተዋል ይኖርብናል። ቀጥሎም ልጃችን በእኛ ልብ ውስጥ ያለውን በግልጽ እንዲያይ ማድረግ አለብን።

ኢየሱስ ክርስቶስ ከሁለት ደቀ መዛሙርቱ ጋር ወደ ኤማሁስ እየተጓዘ በነበረበት ወቅት በቅድሚያ ተስፋቸውንና የሚያሳስቧቸውን ነገሮች እንዲናገሩ አበረታቷቸዋል። ኢየሱስ ከቅዱሳን መጻሕፍት ላይ እየጠቀሰ አስተሳሰባቸውን እንዲያስተካክሉ የረዳቸው ጊዜ ሰጥቶ ካዳመጣቸው በኋላ ነው። ቆየት ብሎ ደቀ መዛሙርቱ ‘በመንገድ ሳለን፣ ሲያነጋግረን ልባችን እንደ እሳት ይቃጠልብን አልነበረምን?’ በማለት ተናግረዋል። ይህ ታሪክ የልብን አውጥቶ በግልጽ መነጋገር ሲባል ምን ማለት እንደሆነ ጥሩ አድርጎ ያሳያል። (ሉቃስ 24:15-32) የልጃችንን ስሜት መረዳት የምንችለው እንዴት ነው?

በቅርቡ፣ በጉባኤ ውስጥ በምሳሌነት የሚጠቀሱ ትልልቅ ልጆች ወይም ሙሉ ሰው ወደ መሆን የተቃረቡ ልጆች ላሏቸው አንዳንድ ወላጆች በግልጽ መነጋገርን የሚመለከቱ አንዳንድ ጥያቄዎች ቀርበውላቸው ነበር። ለምሳሌ ያህል በሜክሲኮ የሚኖረው ግሌን አራት ልጆችን አሳድጓል። a ግሌን እንዲህ ብሏል:- “በወላጆችና በልጆች መካከል ጥሩ የሐሳብ ግንኙነት እንዲኖር ማድረግ ጥረት ይጠይቃል። እኔና ባለቤቴ ከልጆቻችን ጋር ጊዜ ለማሳለፍ ስንል እምብዛም አስፈላጊ ያልሆኑ ነገሮችን በመሥራት የምናውለውን ጊዜ ለመቀነስ ወሰንን። ልጆቻችን በአሥራዎቹ የዕድሜ ክልል ውስጥ በነበሩበት ወቅት ስለሚያሳስቧቸው ነገሮች በመጨዋወት ምሽቱን በሙሉ የምናሳልፍባቸው ጊዜያት ነበሩ። በምግብ ሰዓትም ቢሆን የሚያደርጉትን ጭውውት በመስማት ያሉባቸውን ችግሮች ማስተዋልና አብዛኛውን ጊዜም የተሳሳተ ዝንባሌያቸውን እንዲያስተካክሉ በደግነት መርዳት ችለናል። ብዙውን ጊዜ እንዲህ ማድረጋችንን እንኳ አያስተውሉም ነበር።”

በግልጽ መወያየት በልባችን ውስጥ ያለውን አውጥቶ መናገርን ይጨምራል። ኢየሱስ “መልካም ሰው በልቡ ከሞላው መልካም ነገር መልካሙን ያወጣል፤ . . . ሰው በልቡ ሞልቶ የተረፈውን በአፉ ይናገራልና” ብሏል። (ሉቃስ 6:45) ሦስት ልጆቹ በጃፓን ውስጥ በሙሉ ጊዜ አገልግሎት እየተካፈሉ የሚገኙት ቶሺኪ እንዲህ ብሏል:- “በይሖዋ የማምነው ለምን እንደሆነ ደጋግሜ እነግራቸው ነበር። ይሖዋ ስለ መኖሩ ጠንካራ እምነት ሊኖረኝ የቻለው እንዲሁም መጽሐፍ ቅዱስ ትክክለኛና ከሁሉ የተሻለ የሕይወት መመሪያ መሆኑን ከሕይወት ተሞክሮዬ የተገነዘብኩት እንዴት እንደሆነ አጫውታቸው ነበር።” በሜክሲኮ የምትኖረው ሲንዲ እንዲህ ብላለች:- “ባለቤቴ ከልጆቻችን ጋር አዘውትሮ ይጸልያል። ልጆቹ የሚያቀርበውን ልባዊ ጸሎት ማድመጣቸው ይሖዋ እውን እንዲሆንላቸው ረድቷቸዋል።”

ምሳሌነታችን የሚያሳድረው ከፍተኛ ተጽዕኖ

ልጆች ከምንነግራቸው ቃላት ይበልጥ አኗኗራችንን በመመልከት ይሖዋን ምን ያህል እንደምንወደው መገንዘብ ይችላሉ። ሰዎች ኢየሱስ ክርስቶስ፣ ለይሖዋ የሚያሳየውን ታዛዥነት በመመልከት ለአምላክ ያለውን ጥልቅ ፍቅር ማስተዋል ይችሉ ነበር። ኢየሱስ “እኔ አብን እንደምወድ ዓለም እንዲያውቅ አብ የሰጠኝን ትእዛዝ እየፈጸምኩ ነው” ብሏል።—ዮሐንስ 14:31 NW

በዌልስ የሚኖር ጋርዝ የተባለ አንድ የይሖዋ ምሥክር እንደሚከተለው ብሏል:- “ልጆቻችን ይሖዋን እንደምንወድና ነገሮችን እሱ በሚፈልገው መንገድ ለመሥራት እንደምንጥር መመልከት አለባቸው። ለምሳሌ ያህል፣ ልጆቼ አምላክ በሰጠን መመሪያ መሠረት ስህተቴን አምኜ ስቀበል ይመለከታሉ። አሁን እነሱም እንደዚያ ለማድረግ ይጥራሉ።”

ግሬግ የተባለ አንድ አውስትራሊያዊ እንዲህ ብሏል:- “ልጆቻችን እውነት በሕይወታችን ውስጥ ትልቅ ቦታ እንደያዘ እንዲገነዘቡ እናደርጋለን። ሥራን ወይም መዝናኛን የተመለከተ ውሳኔ ስናደርግ በቅድሚያ ክርስቲያናዊ ኃላፊነቶቻችንን ይነካብን እንደሆነ በጥሞና እናስባለን። ረዳት አቅኚ ሆና የምታገለግለው የ19 ዓመቷ ሴት ልጃችን እንዲህ ዓይነቱን አመለካከት በማዳበሯ ተደስተናል።”

ልጆቻችን አምላክን እንዲያውቁ መርዳት

በደንብ የማናውቀውን ሰው ልንወደው ወይም እምነት ልንጥልበት አንችልም። ሐዋርያው ጳውሎስ በፊልጵስዩስ የሚገኙት ክርስቲያኖች ለይሖዋ ያላቸውን ፍቅር እንዲያሳድጉ ሲያበረታታቸው “ፍቅራችሁ በጥልቅ እውቀትና በማስተዋል ሁሉ በዝቶ እንዲትረፈረፍ እጸልያለሁ” በማለት ጽፎላቸዋል። (ፊልጵስዩስ 1:9) በፔሩ የሚኖረውና የአራት ልጆች አባት የሆነው ፋልኮኔርዮ እንዲህ ብሏል:- “ከልጆቼ ጋር መጽሐፍ ቅዱስን አዘውትረን ማንበባችንና ማጥናታችን እምነታቸውን አጠንክሮላቸዋል። ይህን ሳላደርግ በምቀርበት ጊዜ ለአምላክ ያላቸው ፍቅር ሲዳከም አያለሁ።” በአውስትራሊያ የሚኖረው ጋሪ እንዲህ ብሏል:- “ብዙ ጊዜ ልጆቼ የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች እየተፈጸሙ መሆኑን የሚያሳዩ ማስረጃዎችን እንዲያስተውሉ አደርጋለሁ። እንዲሁም የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች ተግባራዊ ማድረግ ያለውን ጠቀሜታ ጎላ አድርጌ እገልጽላቸዋለሁ። መጽሐፍ ቅዱስን በቤተሰብ ደረጃ በቋሚነት ማጥናታችን እምነታቸውን ለመገንባት የሚያስችል ቁልፍ ሆኖ አግኝቼዋለሁ።”

ልጆች ዘና ባለ ስሜት ሆኖም በአክብሮት የሚቀርብላቸውን ትምህርት በተሻለ መንገድ ሊቀበሉ ይችላሉ። (ያዕቆብ 3:18) በብሪታንያ የሚኖሩትና አራት ልጆችን ያፈሩት ሾውን እና ፖሊን እንዲህ ብለዋል:- “መጽሐፍ ቅዱስን በቤተሰብ ሆነን በምናጠናበት ወቅት ልጆቻችን ቢረብሹም እንኳ በጣም ላለመቆጣት እንጥራለን። ትምህርቱን በተለያየ መንገድ ለማቅረብ እንሞክራለን። አንዳንዴም ልጆቻችን የምናጠናውን ርዕስ እንዲመርጡ እናደርጋለን። በይሖዋ ድርጅት የተዘጋጁ ፊልሞችን እንጠቀማለን። አንዳንዴ ፊልሙን ወደኋላ በመመለስ አሊያም ለትንሽ ጊዜ ቆም በማድረግ ባየነው ነገር ላይ እንወያያለን።” በዚያው አገር የምትኖር ኪም የተባለች እናት እንደሚከተለው ብላለች:- “ልጆቼ ቆም ብለው እንዲያስቡ የሚያደርጓቸውን ጥያቄዎች ለመጠየቅ ስል ለቤተሰብ ጥናት በጥሩ ሁኔታ እዘጋጃለሁ። በጥናቱ እንደሰታለን፤ ብዙውን ጊዜም ከልባችን እንስቃለን።”

የጓደኛ ምርጫ

ልጆቻችን የአምላክ ወዳጅ በሆኑ ሰዎች መካከል ሲኖሩ ለይሖዋ ያላቸው ፍቅርና ለእውነተኛው አምልኮ ያላቸው አድናቆት በቀላሉ ሊያድግ ይችላል። ልጆቻችን የሚያንጽ ውይይትና ጭውውት ከሚያደርጉ ሰዎች ጋር እንዲወዳጁ ማድረግ ጥረት ይጠይቅ ይሆናል። ይሁንና እንዲህ ማድረጋችን የሚክስ ነው! ከዚህም በላይ ልጆቻችን አምላክን ማገልገልን የሙሉ ጊዜ ሥራቸው ካደረጉ የይሖዋ ምሥክሮች ጋር የሚገናኙበትን አጋጣሚ ማመቻቸት በጣም ጠቃሚ ነው። ብዙዎች ወደ ሙሉ ጊዜ አገልግሎት ሊገቡ የቻሉት ቀናተኛ ከሆኑ የአምላክ አገልጋዮች ጋር ወዳጅነት በመመሥረታቸው ነው። አሁን በሚስዮናዊነት የምታገለግል አንዲት እህት እንዲህ ብላለች:- “ብዙውን ጊዜ ወላጆቼ አቅኚዎችን ቤታችን ይጋብዟቸው ነበር። እነዚህ አቅኚዎች በአገልግሎታቸው ሁልጊዜ ደስተኞች ነበሩ፤ በመሆኑም እኔም እንደነሱ ወደዚህ የአገልግሎት ዘርፍ በመግባት አምላክን የማገልገል ፍላጎት አደረብኝ።”

እውነት ነው፣ የልጆቻችን አመለካከት ጥሩም ሆነ መጥፎ ተጽዕኖ ሊደረግበት ይችላል። በመሆኑም መጥፎ ባልንጀርነት የሚያስከትላቸው አደጋዎች ልጆቻችንን የማሳደግ ችሎታችንን ይፈታተናሉ። (1 ቆሮንቶስ 15:33) ወጣቶች ይሖዋን ከማይወዱና ከማያውቁ እኩዮቻቸው ጋር ወዳጅነት ከመመሥረት እንዲቆጠቡ ማስተማር ጥበብ ይጠይቃል። (ምሳሌ 13:20) ቀደም ሲል የተጠቀሰው ሾውን እንዲህ ብሏል:- “ልጆቻችንን አብረዋቸው ከሚማሩት ልጆች ጋር እንዴት ተግባብተው መሥራት እንዳለባቸውና ግንኙነታቸው ከትምህርት ቤት ያለፈ መሆን እንደሌለበት አስተምረናቸዋል። ልጆቻችን ከትምህርት ሰዓት ውጪ በሚደረጉ እንቅስቃሴዎች ወይም ስፖርታዊ ጨዋታዎች መካፈል የሌለባቸው ለምን እንደሆነ ተገንዝበዋል።”

ልጆችን ማሠልጠን ያለው ጥቅም

ልጆቻችን ስለሚያምኑባቸው ነገሮች ለሌሎች እንዲናገሩ በማሠልጠን ለአምላክ ያላቸውን ፍቅር በማሳየት እንዲደሰቱ ልንረዳቸው እንችላለን። በዩናይትድ ስቴትስ የሚኖረው ማርክ እንደሚከተለው ብሏል:- “ልጆቻችን በመደበኛው አገልግሎት በሚካፈሉበት ጊዜ ብቻ ሳይሆን በማንኛውም ጊዜ ስለሚያምኑባቸው ነገሮች ለሌሎች መናገር እንደሚችሉ ሆኖ እንዲሰማቸው ለማድረግ እንጥራለን። በመሆኑም ለመዝናናት ብለን ወጣ ስንል፣ ለምሳሌ ያህል ወደ መናፈሻ፣ ወደ ባሕር ዳርቻ ወይም ወደ ጫካ ስንሄድ መጽሐፍ ቅዱስና መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችን እንይዛለን። በኋላም በዚያ ለምናገኛቸው ሰዎች ስለምናምንባቸው ነገሮች እንነግራቸዋለን። ልጆቻችን እንዲህ ባለው ሁኔታ መደበኛ ባልሆነ መንገድ መመሥከራቸው እጅግ ያስደስታቸዋል። እነሱም ስለሚያምኑባቸው ነገሮች በመናገር ከሰዎቹ ጋር በምናደርገው ውይይት ይካፈላሉ።”

አረጋዊው ሐዋርያው ዮሐንስ ብዙ ሰዎች ለአምላክ ያላቸውን ፍቅር እንዲያሳድጉ ረድቷል። እነዚህን ሰዎች አስመልክቶ ሲጽፍ “ልጆቼ በእውነት የሚመላለሱ መሆናቸውን ከመስማት የሚበልጥ ደስታ የለኝም” ብሏል። (3 ዮሐንስ 4) እኛም ልጆቻችን ለአምላክ ያላቸውን ፍቅር እንዲያሳድጉ የምንረዳቸው ከሆነ ተመሳሳይ ደስታ እንደምናገኝ ጥርጥር የለውም።

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

a አንዳንዶቹ ስሞች ተለውጠዋል።

[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ከእምነት ጋር ስለተያያዙ ጉዳዮች በግልጽ መነጋገር ጥረት ይጠይቃል

[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ልጆቻችሁ ለአምላክ ያላቸውን ፍቅር እንዲገልጹ አሠልጥኗቸው

[ምንጭ]

Courtesy of Green Chimneys Farm