በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

‘ባረጁ ጊዜ ያፈራሉ’

‘ባረጁ ጊዜ ያፈራሉ’

‘ባረጁ ጊዜ ያፈራሉ’

በሜድትራንያን አካባቢ የሚኖሩ አብዛኞቹ ሰዎች ግቢያቸው ውስጥ የተምር ዛፎችን ይተክላሉ። እነዚህ ዛፎች በውበታቸውና በሚያፈሩት ጣፋጭ ፍሬ ይታወቃሉ። ከዚህም በላይ ከመቶ ለሚበልጡ ዓመታት ያለማቋረጥ ፍሬ ይሰጣሉ።

የጥንቷ እስራኤል ንጉሥ የነበረው ሰሎሞን የአንዲትን ውብ ሱላማጢስ ልጃገረድ ቁመና ከዘንባባ ዛፍ ጋር አመሳስሎታል። (ማሕልየ መሓልይ 7:7) ፕላንትስ ኦቭ ዘ ባይብል የተሰኘ መጽሐፍ እንዲህ ብሏል:- “የተምር ዛፍ በዕብራይስጥኛ ‘ትዕማር’ በመባል ይጠራል። . . . ይህ ዛፍ በአይሁዳውያን ዘንድ የግርማ ሞገስና የውበት ተምሳሌት ተደርጎ የሚታይ ከመሆኑም ባሻገር አብዛኛውን ጊዜ ስሙ ለሴቶች መጠሪያነት ያገለግል ነበር።” ለምሳሌ ያህል ውብ የሆነችው የሰሎሞን እህት ስሟ ትዕማር ነበር። (2 ሳሙኤል 13:1) አንዳንድ ወላጆች አሁንም ድረስ ይህንን ስም ለሴት ልጆቻቸው ያወጣሉ።

በዘንባባ ዛፍ የተመሰሉት ውብ የሆኑ ሴቶች ብቻ አይደሉም። መዝሙራዊው እንዲህ ሲል ዘምሯል:- “ጻድቃን እንደ ዘንባባ ይንሰራፋሉ፤ እንደ ሊባኖስ ዝግባም ይንዠረገጋሉ። በእግዚአብሔር ቤት ተተክለዋል፤ በአምላካችንም አደባባይ ይንሰራፋሉ። ባረጁ ጊዜ እንኳ ያፈራሉ፤ እንደ ለመለሙና እንደ ጠነከሩም ይኖራሉ።”—መዝሙር 92:12-14

አምላክን በታማኝነት የሚያገለግሉ አረጋውያን ውብ ከሆነው የዘንባባ ዛፍ ጋር የሚያመሳስሏቸው ብዙ ነገሮች አሏቸው። መጽሐፍ ቅዱስ “ሽበት የክብር ዘውድ ነው፤ የሚገኘውም በጽድቅ ሕይወት ነው” ይላል። (ምሳሌ 16:31) አረጋውያን በዕድሜ መግፋት ሳቢያ ጉልበታቸው ቢደክምም፣ የአምላክ ቃል የሆነውን መጽሐፍ ቅዱስን አዘውትረው በማጥናት መንፈሳዊ ጥንካሬያቸውን እንደያዙ መቀጠል ይችላሉ። (መዝሙር 1:1-3፤ ኤርምያስ 17:7, 8) ታማኝ አረጋውያን የሚናገሯቸው ማራኪ ቃላትና መልካም ምሳሌነታቸው ለሌሎች ከፍተኛ የብርታት ምንጭ ከመሆን ባሻገር ከዓመት እስከ ዓመት ፍሬ ማፍራታቸውን ይቀጥላሉ። (ቲቶ 2:2-5፤ ዕብራውያን 13:15, 16) አረጋውያንም ልክ እንደ ዘንባባ ዛፍ በስተ እርጅናቸው ፍሬ ማፍራት ይችላሉ።