በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

‘አባታችሁ መሐሪ ነው’

‘አባታችሁ መሐሪ ነው’

‘አባታችሁ መሐሪ ነው’

“አባታችሁ መሐሪ እንደሆነ ሁሉ እናንተም ምሕረት ማሳየታችሁን ቀጥሉ።”—ሉቃስ 6:36 NW

1, 2. ኢየሱስ ለጸሐፍትና ለፈሪሳውያን እንዲሁም ለተከታዮቹ የተናገራቸው ቃላት ምሕረት አስፈላጊ ባሕርይ መሆኑን የሚያሳዩት እንዴት ነው?

 በሙሴ በኩል ለእስራኤላውያን የተሰጣቸው ሕግ 600 የሚያህሉ ዝርዝር ደንቦችንና መመሪያዎችን ይዟል። እስራኤላውያን የሙሴን ሕግ መታዘዛቸው አስፈላጊ የነበረ ቢሆንም ምሕረት ማሳየታቸውም ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ነገር ነበር። ኢየሱስ ምሕረት ለማሳየት እምቢተኞች ለነበሩት ፈሪሳውያን ምን እንዳላቸው ተመልከት። አምላክ “ከመሥዋዕት ይልቅ ምሕረትን እወዳለሁ” ማለቱን በመጥቀስ ለሌሎች ምሕረት ባለማሳየታቸው ሁለት ጊዜ ገሥጿቸዋል። (ማቴዎስ 9:10-13፤ 12:1-7፤ ሆሴዕ 6:6) በምድራዊ አገልግሎቱ መገባደጃ አካባቢ ኢየሱስ እንዲህ ብሏቸዋል:- “እናንት ግብዞች የኦሪት ሕግ መምህራንና ፈሪሳውያን፤ ወዮላችሁ! ከአዝሙድ፣ ከእንስላልና ከከሙን ዐሥራት እየሰጣችሁ በሕጉ ውስጥ ዋነኛ የሆኑትን ማለትም ፍትሕን፣ ምሕረትንና ታማኝነትን ግን ንቃችኋልና።”—ማቴዎስ 23:23

2 በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው ኢየሱስ ምሕረት ማሳየትን ከፍ አድርጎ ይመለከት ነበር። ለደቀ መዛሙርቱ “አባታችሁ መሐሪ እንደሆነ ሁሉ እናንተም ምሕረት ማሳየታችሁን ቀጥሉ” ብሏቸዋል። (ሉቃስ 6:36 NW) በዚህ ረገድ ‘አምላክን ለመምሰል’ የምሕረትን ትክክለኛ ትርጉም ማወቃችን አስፈላጊ ነው። (ኤፌሶን 5:1) በተጨማሪም ምሕረት የሚያስገኘውን ጥቅም መረዳታችን ይህን ባሕርይ በሕይወታችን ይበልጥ እንድናንጸባርቅ ያነሳሳናል።

ለተቸገሩ ምሕረት ማሳየት

3. የምሕረትን ትክክለኛ ትርጉም ለመረዳት ወደ ይሖዋ መመልከት ያለብን ለምንድን ነው?

3 መዝሙራዊው እንደሚከተለው ሲል ዘምሯል:- “[ይሖዋ] ቸር ነው፤ ርኅሩኅም ነው፤ ለቍጣ የዘገየ፣ ምሕረቱ የበዛ። እግዚአብሔር [“ይሖዋ፣” NW] ለሁሉ ቸር ነው፤ ምሕረቱም በፍጥረቱ ሁሉ ላይ ነው።” (መዝሙር 145:8, 9) ይሖዋ “የርኅራኄ አባት፣ የመጽናናትም ሁሉ አምላክ” ነው። (2 ቆሮንቶስ 1:3) ምሕረት ማሳየት ሲባል ሌሎችን በርኅራኄ መያዝ ማለት ነው። ምሕረት ከአምላክ ባሕርይ ዋነኛ ገጽታዎች አንዱ ነው። ይሖዋ ምሕረት በማሳየት ረገድ የተወው ምሳሌና የሰጠን መመሪያዎች የዚህን ባሕርይ ትክክለኛ ትርጉም ለመረዳት ያስችሉናል።

4. ኢሳይያስ 49:15 ስለ ምሕረት ምን ያስተምረናል?

4 በኢሳይያስ 49:15 ላይ ተመዝግቦ እንደሚገኘው ይሖዋ “እናት የምታጠባውን ልጇን ልትረሳ ትችላለችን? ለወለደችውስ ልጅ አትራራለትምን?” ሲል ተናግሯል። እዚህ ላይ ‘መራራት’ ተብሎ የተተረጎመው የዕብራይስጥ ቃል ከላይ በተጠቀሰው በመዝሙር 145:8, 9 ላይ ከምሕረት ጋር ተያይዞ ከተሠራበት ቃል ጋር ተመሳሳይነት አለው። ይሖዋ ምሕረት እንዲያሳይ የሚያነሳሳው ስሜት የምታጠባ እናት ለልጇ ካላት ተፈጥሯዊ የርኅራኄ ስሜት ጋር ተነጻጽሯል። ምናልባትም ሕፃኑ ተርቦ ወይም አንድ ነገር ፈልጎ ይሆናል። በዚህ ጊዜ እናትየው በርኅራኄ ወይም በሐዘኔታ ስሜት ተነሳስታ ለልጇ የሚያስፈልገውን ታሟላለች። በተመሳሳይም ይሖዋ ምሕረት ለሚያሳያቸው ሰዎች እንዲህ ያለ የርኅራኄ ስሜት አለው።

5. ይሖዋ ከእስራኤላውያን ጋር በነበረው ግንኙነት “በምሕረቱ ባለጠጋ” እንደሆነ ያሳየው እንዴት ነው?

5 ለተቸገሩ ሰዎች መራራት አንድ ነገር ሲሆን እነሱን ለመርዳት እርምጃ መውሰድ ደግሞ ሌላ ነገር ነው። ይሖዋ፣ ከ3,500 ዓመታት ገደማ በፊት አምላኪዎቹ በግብጽ በባርነት ሲማቅቁ ምን እንዳደረገ ተመልከት:- “በግብፅ አገር የሚኖሩትን የሕዝቤን መከራ አይቻለሁ፤ ከአሠሪዎቻቸው ጭካኔ የተነሣ የሚያሰሙትንም ጩኸት ሰምቻለሁ፤ ሥቃያቸውንም ተረድቼአለሁ። ስለዚህም ከግብፃውያን እጅ ልታደጋቸውና ማርና ወተት ወደምታፈሰው ሰፊና ለም ወደ ሆነችው . . . ምድር ላወጣቸው ወርጃለሁ።” (ዘፀአት 3:7, 8) እስራኤላውያን ከግብጽ ነፃ ከወጡ ከ500 ዓመታት በኋላ ይሖዋ እንዲህ ሲል ያደረገላቸውን አስታውሷቸው ነበር:- “እስራኤልን ከግብፅ አወጣሁት፤ ከግብፃውያን እጅ ይጨቁኗችሁ ከነበሩት ከሌሎቹ መንግሥታት ሁሉ እጅ ታደግኋችሁ።” (1 ሳሙኤል 10:18) እስራኤላውያን ከይሖዋ የጽድቅ መሥፈርቶች ፈቀቅ ይሉ ስለነበር ብዙ ጊዜ ለመከራ ተዳርገዋል። እንደዚያም ሆኖ ይሖዋ ይራራላቸው የነበረ ሲሆን በተደጋጋሚም ከመከራ ታድጓቸዋል። (መሳፍንት 2:11-16፤ 2 ዜና መዋዕል 36:15) ይህ ታሪክ፣ አፍቃሪ የሆነው አምላክ ለተቸገሩ፣ አደጋ ላይ ለወደቁ ወይም በመከራ ውስጥ ላሉ እንደሚደርስላቸው ያሳያል። ይሖዋ “በምሕረቱ ባለጠጋ” ነው።—ኤፌሶን 2:4

6. ኢየሱስ ክርስቶስ ምሕረት በማሳየት ረገድ አባቱን የኮረጀው እንዴት ነው?

6 ኢየሱስ ክርስቶስ በምድር በነበረበት ጊዜ ምሕረት በማሳየት ረገድ አባቱን በሚገባ ኮርጇል። ሁለት ማየት የተሳናቸው ሰዎች “ጌታ ሆይ፤ የዳዊት ልጅ ማረን!” እያሉ ሲለምኑት ምን ምላሽ ሰጣቸው? እነዚህ ሰዎች ኢየሱስ የዓይን ብርሃናቸውን በተአምር እንዲመልስላቸው እየተማጸኑት ነበር። ኢየሱስ እንደጠየቁት አደረገላቸው። ይሁንና ይህን ተአምር የፈጸመው ማድረግ ስለቻለ ብቻ አልነበረም። ከዚህ ይልቅ መጽሐፍ ቅዱስ “ኢየሱስም ራራላቸው፤ ዐይኖቻቸውንም ዳሰሰ፣ ወዲያው አዩ” ይላል። (ማቴዎስ 20:30-34) ኢየሱስ ርኅሩኅ መሆኑ፣ ማየት የተሳናቸውን፣ ጋኔን ያደረባቸውን፣ በሥጋ ደዌ በሽታ የተያዙትንና ልጆቻቸው የታመሙባቸውን ወላጆች ከችግራቸው እንዲላቀቁ ለመርዳት ተአምር እንዲሠራ አነሳስቶታል።—ማቴዎስ 9:27፤ 15:22፤ 17:15፤ ማርቆስ 5:18, 19፤ ሉቃስ 17:12, 13

7. ይሖዋ አምላክና ልጁ የተዉት ምሳሌ ምሕረት ስለማሳየት ምን ያስተምረናል?

7 ይሖዋ አምላክና ኢየሱስ ክርስቶስ የተዉት ምሳሌ ምሕረት ሁለት ገጽታዎች እንዳሉት ያሳያል። አንዱ፣ ችግር ላይ ለወደቁ ሰዎች መራራት ወይም ማዘን ሲሆን ሌላው ደግሞ ችግራቸውን ሊያቃልል የሚችል እርዳታ መለገስ ነው። ምሕረት ማሳየት ሁለቱንም ገጽታዎች ማንጸባረቅን ይጠይቃል። በቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ ምሕረት የሚለው ቃል በአብዛኛው የተሠራበት እርዳታ ለሚሹ ሰዎች ደግነት ማድረግን ለማመልከት ነው። ይሁንና ከፍርድ ነክ ጉዳዮች ጋር በተያያዘስ ምሕረት ማሳየት ምንን ይጨምራል? ተገቢ የሆኑ ነገሮችን አለማድረግን፣ ለምሳሌ ያህል ቅጣት ከመስጠት ወደኋላ ማለትን ይጨምር ይሆን?

ለኃጢአተኞች ምሕረት ማሳየት

8, 9. ዳዊት ከቤርሳቤህ ጋር ኃጢአት ከፈጸመ በኋላ የተደረገለት ምሕረት ምንን ይጨምራል?

8 ነቢዩ ናታን ለጥንቱ የእስራኤል ንጉሥ ለዳዊት ከቤርሳቤህ ጋር ምንዝር በመፈጸም መበደሉን ፊት ለፊት ከነገረው በኋላ ምን እንደተከሰተ ተመልከት። ንስሐ የገባው ዳዊት እንዲህ ሲል ጸለየ:- “እግዚአብሔር ሆይ፤ እንደ ቸርነትህ መጠን፣ ምሕረት አድርግልኝ፤ እንደ ርኅራኄህም ብዛት፣ መተላለፌን ደምስስ። በደሌን ፈጽሞ እጠብልኝ፤ ከኀጢአቴም አንጻኝ። እኔ መተላለፌን አውቃለሁና፤ ኀጢአቴም ዘወትር በፊቴ ነው። በውሳኔህ ትክክል፣ በምትሰጠው ፍርድም ንጹሕ ትሆን ዘንድ፣ አንተን፣ በእርግጥ አንተን ብቻ በደልሁ፤ በፊትህም ክፉ ነገር አደረግሁ።”—መዝሙር 51:1-4

9 ዳዊት ከልብ ተጸጽቷል። ይሖዋ የዳዊትን ኃጢአት ይቅር ያለለት ሲሆን ዳዊትም ሆነ ቤርሳቤህ ይደርስባቸው የነበረውን ቅጣት አቅልሎላቸዋል። በሙሴ ሕግ መሠረት ሁለቱም ሞት ሊፈረድባቸው ይገባ ነበር። (ዘዳግም 22:22) የሠሩት ኃጢአት ካስከተለባቸው መዘዝ ሙሉ በሙሉ ማምለጥ ባይችሉም ሕይወታቸው ተርፎላቸዋል። (2 ሳሙኤል 12:13) የአምላክ ምሕረት ኃጢአትን ይቅር ማለትንም ይጨምራል። ይሁን እንጂ አምላክ ተገቢውን ቅጣት ከማስፈጸም ወደኋላ አይልም።

10. ይሖዋ በሚፈርድበት ጊዜ ምሕረት የሚያሳይ ቢሆንም ምሕረቱን በተሳሳተ መንገድ መረዳት የሌለብን ለምንድን ነው?

10 ‘ኀጢአት በአንድ ሰው [ማለትም በአዳም] በኩል ወደ ዓለም’ ስለገባና ‘የኀጢአት ደመወዝ ደግሞ ሞት’ ስለሆነ ሁሉም ሰው ሞት ይገባዋል። (ሮሜ 5:12፤ 6:23) ይሖዋ በእኛ ላይ በሚፈርድበት ጊዜ ምሕረት የሚያሳይ በመሆኑ ምንኛ አመስጋኞች ነን! ይሁንና የአምላክን ምሕረት በተሳሳተ መንገድ እንዳንረዳ መጠንቀቅ አለብን። ዘዳግም 32:4 ይሖዋን አስመልክቶ ሲናገር ‘መንገዱ ሁሉ ትክክል [“ፍትሕ፣” NW] ነው’ ይላል። በመሆኑም አምላክ ምሕረት በሚያሳይበት ጊዜ ፍጹም የሆኑትን የፍትሕ መሥፈርቶቹን ችላ አይልም።

11. ይሖዋ፣ ዳዊት ከቤርሳቤህ ጋር የፈጸመውን ኃጢአት በተመለከተበት ጊዜ ፍትሕ ያሳየው እንዴት ነው?

11 ዳዊትና ቤርሳቤህ ይደርስባቸው የነበረው የሞት ፍርድ ከመሻሩ በፊት ኃጢአታቸው ይቅር ሊባልላቸው ይገባ ነበር። እስራኤላውያን ፈራጆች ኃጢአትን ይቅር የማለት ሥልጣን አልነበራቸውም። በመሆኑም የዳዊትን ጉዳይ እንዲያዩት ተፈቅዶላቸው ቢሆን ኖሮ የሞት ፍርድ ከማስተላለፍ በቀር ሌላ አማራጭ አይኖራቸውም ነበር። ሕጉ ይህን እንዲያደርጉ ይጠብቅባቸው ነበር። ይሁንና ይሖዋ ከዳዊት ጋር የገባውን ቃል ኪዳን ግምት ውስጥ በማስገባት ኃጢአቱን ይቅር ለማለት የሚያስችል ሁኔታ ይገኝ እንደሆነ ለማየት ወሰነ። (2 ሳሙኤል 7:12-16) በመሆኑም “የምድር ሁሉ ዳኛ” የሆነውና ‘ልብን የሚመረምረው’ ይሖዋ አምላክ ጉዳዩን ራሱ ለማየት መርጧል። (ዘፍጥረት 18:25፤ 1 ዜና መዋዕል 29:17) አምላክ የዳዊትን ልብ በትክክል ማንበብና እውነተኛ ንስሐ መግባቱን መገምገም ችሎ ነበር። በመሆኑም ኃጢአቱን ይቅር ብሎለታል።

12 ኃጢአተኛ የሆኑት የሰው ልጆች ከአምላክ ምሕረት ተጠቃሚ መሆን የሚችሉት እንዴት ነው?

12 ይሖዋ፣ የወረስነው ኃጢአት ከሚያመጣብን የሞት ቅጣት ነፃ የሚያወጣንን ዝግጅት በማድረግ ያሳየን ምሕረት ከፍትሑ ጋር የሚስማማ ነው። ይሖዋ የፍትሕ መሥፈርቶቹን ሳይጥስ ኃጢአታችንን ይቅር ለማለት እንዲችል ልጁን ኢየሱስ ክርስቶስን ቤዛ አድርጎ ሰጥቶናል። ይህም ከሁሉ የላቀው የምሕረት መግለጫ ነው። (ማቴዎስ 20:28፤ ሮሜ 6:22, 23) የወረስነው ኃጢአት ከሚያስከትልብን ቅጣት የሚታደገንን የአምላክን ምሕረት ለማግኘት ከፈለግን ‘በልጁ ማመን’ ይገባናል።—ዮሐንስ 3:16, 36

መሐሪና ፍትሐዊ አምላክ

13, 14. የአምላክ ምሕረት ፍትሑን ያለዝበዋል? አብራራ።

13 ከላይ እንዳየነው ይሖዋ ምሕረት ሲያሳይ የፍትሕ መሥፈርቶቹን አይጥስም። ይሁንና ምሕረቱ በሆነ መንገድ በፍትሑ ላይ ተጽዕኖ ያሳድራል? ምሕረት መለኮታዊውን ፍትሕ የሚያለዝብ ባሕርይ ነው? በፍጹም እንዲህ ማለት አይደለም።

14 ይሖዋ በነቢዩ ሆሴዕ አማካኝነት እስራኤላውያንን እንዲህ ብሏቸዋል:- “ለእኔ እንድትሆኚ ለዘላለም አጭሻለሁ፤ በጽድቅና በፍትሕ፣ በፍቅርና በርኅራኄም [“በምሕረትም፣” NW] አጭሻለሁ።” (ሆሴዕ 2:19) እነዚህ ቃላት ይሖዋ ምሕረት የሚያደርገው ፍትሕን ጨምሮ ከሌሎቹ ባሕርያቱ ጋር በሚስማማ መልኩ እንደሆነ በግልጽ ያሳያሉ። ይሖዋ “ሩኅሩኅ ቸር . . . ክፋትን፣ ዐመፅንና ኀጢአትን ይቅር የሚል በደለኛውን ግን ሳይቀጣ ዝም ብሎ [የማይተው]” አምላክ ነው። (ዘፀአት 34:6, 7) ይሖዋ መሐሪና ፍትሐዊ አምላክ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ ስለ አምላክ ሲናገር “እርሱ ዐለት፣ ሥራውም ፍጹም ነው፤ መንገዱም ሁሉ ትክክል [“ፍትሕ፣” NW] ነው” ይላል። (ዘዳግም 32:4) የአምላክ ፍትሕ ልክ እንደ ምሕረቱ ፍጹም ነው። አንዱ ባሕርይ ከሌላው የበለጠ ወይም የተሻለ አይደለም። አሊያም አንዱ ባሕርይ እንዲለዝብ ለማድረግ የሌላው ተጽዕኖ አያስፈልገውም። ከዚህ ይልቅ ሁለቱም ባሕርያት ያለ ምንም እንከን ተደጋግፈው የሚሠሩ ናቸው።

15, 16. (ሀ) መለኮታዊ ፍትሕ ጭካኔ የሚንጸባረቅበት አለመሆኑን የሚያሳየው ምንድን ነው? (ለ) ይሖዋ በዚህ ክፉ ሥርዓት ላይ ፍርዱን በሚያስፈጽምበት ጊዜ፣ እውነተኛ አምላኪዎቹ ስለምን ነገር እርግጠኛ መሆን ይችላሉ?

15 የይሖዋ ፍትሕ ጭካኔ የሚንጸባረቅበት አይደለም። ፍትሕ በአብዛኛው ሕጋዊ መንገድ መከተልን ያመለክታል፤ ፍርድ ደግሞ ብዙውን ጊዜ በኃጢአተኞች ላይ ተገቢውን ቅጣት ማስፈጸምን ይጠይቃል። ይሁንና የአምላክ ፍትሕ፣ መዳን የሚገባቸውን ሰዎች ሕይወት መታደግንም ይጨምራል። ለምሳሌ ያህል፣ በሰዶምና ገሞራ ይኖሩ የነበሩት ክፉ ሰዎች በጠፉበት ጊዜ የእምነት አባት የሆነው ሎጥና ሁለት ሴት ልጆቹ በሕይወት ተርፈዋል።—ዘፍጥረት 19:12-26

16 ይሖዋ በዚህ ክፉ ሥርዓት ላይ ፍርዱን በሚያስፈጽምበት ጊዜ፣ ‘ልብሳቸውን በበጉ ደም አጥበው ያነጹት እጅግ ብዙ ሕዝቦች’ ከጥፋት እንደሚድኑ እርግጠኞች መሆን እንችላለን። እነዚህ እውነተኛ አምላኪዎች በዚህ መንገድ “ከታላቁ መከራ” በሕይወት ይተርፋሉ።—ራእይ 7:9-14

ምሕረት ማሳየት ያለብን ለምንድን ነው?

17. ምሕረት እንድናሳይ የሚያነሳሳን ዋነኛ ምክንያት ምንድን ነው?

17 በእርግጥም ይሖዋና ኢየሱስ ክርስቶስ የተዉት ምሳሌ የምሕረትን ትክክለኛ ትርጉም ለመረዳት ያስችለናል። ምሳሌ 19:17 “ለድኻ የሚራራ ለእግዚአብሔር ያበድራል፤ ስላደረገውም ተግባር ዋጋ ይከፍለዋል” በማለት ምሕረት እንድናሳይ የሚያነሳሳንን ወሳኝ ምክንያት ይገልጻል። ይሖዋ አንዳችን ለሌላው ምሕረት በማሳየት የእሱንና የልጁን ምሳሌ ስንከተል ይደሰታል። (1 ቆሮንቶስ 11:1) ከዚህም በላይ ምሕረት ማሳየታችን ሌሎችም በአጸፋው በርኅራኄ ዓይን እንዲመለከቱን ያነሳሳቸዋል።—ሉቃስ 6:38

18. ለሌሎች ምሕረት ለማሳየት መጣር ያለብን ለምንድን ነው?

18 ምሕረት ሌሎች በርካታ መልካም ባሕርያትን አጣምሮ ይዟል። ሞገስ ማሳየትን፣ ፍቅርን፣ ደግነትንና ጥሩነትን ያካትታል። ምሕረት ለማሳየት የሚያንቀሳቅሰን ዋነኛ ባሕርይ ርኅራኄ ወይም የሐዘኔታ ስሜት ነው። አምላክ ምሕረት በሚያሳይበት ጊዜ የፍትሕ መሥፈርቶቹን አይጥስም። ይሁን እንጂ ይሖዋ ለቁጣ የዘገየ ሲሆን ኃጢአተኞች ንስሐ እንዲገቡ የሚያስችላቸው በቂ ጊዜ በመስጠት ይታገሳል። (2 ጴጥሮስ 3:9, 10) በመሆኑም ምሕረት ከትዕግሥት ጋር የተቆራኘ ነው። ምሕረት የአምላክ መንፈስ ፍሬ የሆኑትን ጨምሮ ሌሎች በርካታ ግሩም ባሕርያትን የሚያካትት በመሆኑ፣ ምሕረት ማሳየት እነዚህን ባሕርያት ለማዳበር የሚያስችል አጋጣሚ ይከፍትልናል። (ገላትያ 5:22, 23) በእርግጥም ለሌሎች ምሕረት ለማሳየት መጣራችን በጣም አስፈላጊ ነው!

“ምሕረት የሚያደርጉ ደስተኞች ናቸው”

19, 20. ምሕረት በፍርድ ላይ የሚያይለው ከምን አንጻር ነው?

19 ደቀ መዝሙሩ ያዕቆብ ከሌሎች ጋር ባለን ግንኙነት ሁልጊዜ ምሕረት ማሳየት የሚኖርብን ለምን እንደሆነ ሲናገር “ምሕረት በፍርድ ላይ ያይላል” ብሏል። (ያዕቆብ 2:13ለ) ያዕቆብ እዚህ ላይ እየተናገረ ያለው አንድ የይሖዋ አገልጋይ ለሌሎች ስለሚያሳየው ምሕረት ነው። ምሕረት በፍርድ ላይ ያይላል ሲባል፣ አንድ ሰው ‘ስለ ራሱ ለአምላክ መልስ በሚሰጥበት ጊዜ፣’ ይሖዋ ግለሰቡ ለሌሎች ምሕረት ማሳየቱን ግምት ውስጥ በማስገባት በልጁ ቤዛዊ መሥዋዕት አማካኝነት ይቅር ይለዋል ማለት ነው። (ሮሜ 14:12) ዳዊት ከቤርሳቤህ ጋር ለፈጸመው ኃጢአት ምሕረት ያገኘው እሱ ራሱ ለሌሎች ምሕረት የሚያሳይ ሰው ስለነበር መሆን አለበት። (1 ሳሙኤል 24:4-7) በሌላ በኩል ደግሞ “ምሕረት ያላደረገ ሁሉ ያለ ምሕረት ይፈረድበታል።” (ያዕቆብ 2:13ሀ) “ርኅራኄ የሌላቸው” ወይም ምሕረት የማያደርጉ ሰዎች አምላክ “ሞት ይገባቸዋል” ብሎ ከፈረደባቸው መካከል መፈረጃቸው ምንም አያስደንቅም!—ሮሜ 1:31, 32

20 ኢየሱስ በተራራው ስብከቱ ላይ “ምሕረት የሚያደርጉ ብፁዓን [“ደስተኞች፣” NW] ናቸው፤ ምሕረትን ያገኛሉና” ሲል ተናግሯል። (ማቴዎስ 5:7) እነዚህ ቃላት የአምላክን ምሕረት የሚፈልጉ ሁሉ ለሌሎች ምሕረት ማድረግ እንዳለባቸው በግልጽ ያሳያሉ! የሚቀጥለው ርዕስ በዕለት ተዕለት ሕይወታችን ምሕረት ማሳየት የምንችለው እንዴት እንደሆነ ያብራራል።

ምን ትምህርት አግኝተሃል?

• ምሕረት ምንድን ነው?

• ምሕረት በምን መንገዶች ይንጸባረቃል?

• ይሖዋ መሐሪና ፍትሐዊ አምላክ የሆነው በምን መንገድ ነው?

• ለሌሎች ምሕረት ማሳየት ያለብን ለምንድን ነው?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 21 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ይሖዋ ለተቸገሩ ሰዎች የሚያሳየው ርኅራኄ እናት ለልጇ ካላት የመራራት ስሜት ጋር ይመሳሰላል

[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ኢየሱስ ከፈጸማቸው ተአምራት ስለ ምሕረት ምን እንማራለን?

[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ይሖዋ ለዳዊት ምሕረት ባሳየው ጊዜ የፍትሕ መሥፈርቶቹን ጥሷል?

[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

አምላክ ኃጢአተኛ ለሆኑ የሰው ልጆች ያሳየው ምሕረት ከፍትሑ ጋር የሚስማማ ነው