በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ክፋት እስከ ዛሬ ያልተወገደው ለምንድን ነው?

ክፋት እስከ ዛሬ ያልተወገደው ለምንድን ነው?

ክፋት እስከ ዛሬ ያልተወገደው ለምንድን ነው?

መጽሐፍ ቅዱስ ‘[ይሖዋ] አምላክ በመንገዱ ሁሉ ጻድቅ እንደሆነ’ ይናገራል። (መዝሙር 145:17፤ ራእይ 15:3) ነቢዩ ሙሴ ስለ ይሖዋ ሲናገር እንዲህ ብሏል:- “ሥራውም ፍጹም ነው፤ መንገዱም ሁሉ ትክክል [“ፍትሕ፣” NW] ነው፤ የማይሳሳት [“ፍትሕን የማያጓድል፣” NW] ታማኝ አምላክ፣ ቀጥተኛና ጻድቅ አምላክም እርሱ ነው።” (ዘዳግም 32:4) ያዕቆብ 5:11 “[ይሖዋ] እጅግ ርኅሩኅና መሓሪ ነው” ይላል። አምላክ የክፋት መንስኤ አይደለም፣ ደግሞም ሊሆን አይችልም።

ደቀ መዝሙሩ ያዕቆብ እንዲህ ሲል ጽፏል:- “ማንም ሲፈተን፣ ‘እግዚአብሔር ፈተነኝ’ አይበል፤ ምክንያቱም እግዚአብሔር በክፉ አይፈተንም፤ እርሱም ማንንም አይፈትንም።” (ያዕቆብ 1:13) ይሖዋ አምላክ ሰዎችን በክፉ አይፈትናቸውም እንዲሁም መጥፎ ድርጊት እንዲፈጽሙ አይገፋፋቸውም። ታዲያ ክፋትና መከራ ለመኖሩ ተጠያቂው ማን ነው?

ክፋት ለመኖሩ ተጠያቂው ማን ነው?

ከመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎች አንዱ የሆነው ያዕቆብ ሰዎች ለክፋት መኖር በከፊል ተጠያቂዎች መሆናቸውን ገልጿል። ያዕቆብ እንዲህ ብሏል:- “እያንዳንዱ የሚፈተነው በራሱ ክፉ ምኞት ሲሳብና ሲታለል ነው። ምኞትም ከፀነሰች በኋላ ኀጢአትን ትወልዳለች፤ ኀጢአትም ካደገች በኋላ ሞትን ትወልዳለች።” (ያዕቆብ 1:14, 15) ሰዎች ተገቢ ባልሆነ ምኞት በመገፋፋት አንዳንድ ድርጊቶችን ይፈጽሙ ይሆናል። በተጨማሪም፣ የሰው ልጆች ኃጢአትን መውረሳቸው የሚያሳድርባቸውን ተጽዕኖ ከግምት ውስጥ ማስገባት ያስፈልጋል። ኃጢአት የሚያሳድረው ተጽዕኖ መጥፎ ምኞቶች እንዲያይሉ ስለሚያደርግ አስከፊ ውጤት ያስከትላል። (ሮሜ 7:21-23) የሰው ልጆች የወረሱት ኃጢአት ታላቅ መከራ ለሚያስከትሉ መጥፎ ድርጊቶች ባሪያ እንዲሆኑ ስለሚያደርጋቸው በእርግጥም በላያቸው ላይ ‘ነግሷል።’ (ሮሜ 5:21) ከዚህም በላይ ክፉ ሰዎች ሌሎችም እንደነሱ የክፋት ድርጊቶችን እንዲፈጽሙ ተጽዕኖ ያሳድራሉ።—ምሳሌ 1:10-16

ይሁን እንጂ ዋነኛው የክፋት መንስኤ ሰይጣን ዲያብሎስ ነው። በምድር ላይ ክፋትን ያመጣው እሱ ነው። ኢየሱስ ክርስቶስ፣ ሰይጣንን “ክፉው” እና “የዚህ ዓለም [ማለትም ከአምላክ የራቀው ኅብረተሰብ] ገዥ” ሲል ጠርቶታል። በጥቅሉ ሲታይ የሰው ልጆች የይሖዋ አምላክን መልካም መንገዶች ችላ እንዲሉ ለሚያሳድርባቸው መጥፎ ተጽዕኖ በመሸነፍ ሰይጣንን እየታዘዙ ነው። (ማቴዎስ 6:13፤ ዮሐንስ 14:30፤ 1 ዮሐንስ 2:15-17) በ1 ዮሐንስ 5:19 ላይ ‘መላው ዓለም በክፉው ሥር እንደሆነ’ ተገልጿል። እንዲያውም ሰይጣንና አጋንንቱ ‘ዓለምን ሁሉ በማሳት ወዮታ’ አስከትለዋል። (ራእይ 12:9, 12) በመሆኑም ለክፋት መኖር በዋነኝነት የሚጠየቀው ሰይጣን ዲያብሎስ ነው።

መክብብ 9:11 በሰዎች ላይ መከራና ሥቃይ እንዲደርስ ምክንያት የሆነውን ሌላ ነጥብ ሲገልጽ “ጊዜና ዕድል [“አጋጣሚ፣” NW] ግን ሁሉን ይገናኛቸዋል” ይላል። በአንድ ወቅት ኢየሱስ ክርስቶስ ግንብ ተንዶባቸው ስለሞቱ 18 ሰዎች ተናግሮ ነበር። (ሉቃስ 13:4) እነዚህ ሰዎች ሕይወታቸውን ያጡት በአጉል ሰዓት አጉል ቦታ ላይ በመገኘታቸው ነው። በዛሬው ጊዜም ተመሳሳይ ሁኔታ ሊያጋጥም ይችላል። ለምሳሌ ያህል፣ ከትልቅ ሕንፃ ላይ ተፈንቅሎ የወደቀ ጡብ በአንድ ተላላፊ መንገደኛ ላይ ጉዳት ሊያደርስ ይችላል። ታዲያ ለዚህ ነገር ተወቃሹ አምላክ ነው? በፍጹም። ይህ ሆን ተብሎ የተደረገ ሳይሆን እንዲያው በአጋጣሚ የተከሰተ ነገር ነው። አንድ የቤተሰብ አባል ቢታመም ወይም አባት ከልጆቹና ከሚስቱ በድንገት በሞት ቢለይ ሁኔታው ተመሳሳይ ነው።

በመሆኑም አምላክ የክፋት መንስኤ እንዳልሆነና በሰዎችም ላይ መከራና ሥቃይ እንደማያመጣ በግልጽ ለመረዳት እንችላለን። ከዚህ ይልቅ ክፋትንና ክፉ ድርጊት የሚፈጽሙትን ሰዎች የማስወገድ ዓላማ አለው። (ምሳሌ 2:22) እንዲያውም ከዚህ የበለጠ ነገር ያደርጋል። መጽሐፍ ቅዱስ፣ አምላክ በክርስቶስ አማካኝነት ‘የዲያብሎስን ሥራ የማፍረስ’ ዓላማ እንዳለው ይናገራል። (1 ዮሐንስ 3:8) በስግብግብነት፣ በጥላቻና በክፋት ድርጊት የተሞላው ይህ ሥርዓት በቅርቡ ይጠፋል። አምላክ መከራንና ሥቃይን በማስወገድ ‘እንባን ሁሉ ያብሳል።’ (ራእይ 21:4) ይሁንና ‘አምላክ እስካሁን ይህን ያላደረገው ለምንድን ነው? ክፋትና መከራ እስከ ዛሬ ድረስ ያልተወገደው ለምንድን ነው?’ ብለህ ትጠይቅ ይሆናል። ስለ አዳምና ሔዋን የሚናገረው የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ መልሱን ይሰጠናል።

ሰይጣን ያነሳው አከራካሪ ጥያቄ

አምላክ ክፋት እስከ ዛሬ ድረስ እንዲኖር የፈቀደበት ምክንያት በሰው ልጆች ታሪክ መጀመሪያ ላይ ከተፈጸሙት ክንውኖች ጋር የተያያዘ ነው። በዚያን ወቅት የተከሰተ አንድ ክንውን በፈጣሪ ላይ አከራካሪ ጥያቄ አስነስቷል። ይህ ጥያቄ ደግሞ ወዲያውኑ ወይም በቀላሉ መልስ የሚያገኝ አልነበረም። እስቲ የተከሰተውን ሁኔታ እንመርምር።

ይሖዋ አምላክ የመጀመሪያዎቹን ወንድና ሴት ፍጹም አድርጎ ከፈጠራቸው በኋላ በገነት ውስጥ አስቀመጣቸው። እነዚህ ሰዎች ከእንስሳት የተለዩ የሚያደርጋቸው ልዩ ስጦታ ማለትም የመምረጥ ነፃነት ተሰጥቷቸው ነበር። (ዘፍጥረት 1:28፤ 2:15, 19) መልካሙንና ክፉውን የመለየት ችሎታ ያላቸው እንደመሆናቸው መጠን አዳምና ሔዋን ፈጣሪያቸውን ለመውደድ፣ ለማገልገልና ለመታዘዝ መምረጥ አሊያም ከእሱ ተለይተው ራሳቸውን መምራትና ለመታዘዝ እምቢተኞች መሆን ይችሉ ነበር።

አዳምና ሔዋን ለእሱ ያላቸውን ፍቅር እንዲያሳዩ አጋጣሚ ለመስጠት ሲል እውነተኛው አምላክ አንድ ነገር እንዳያደርጉ አዘዛቸው። ለአዳም እንዲህ የሚል ትእዛዝ ሰጠው:- “በአትክልት ስፍራው ውስጥ ከሚገኝ ከማንኛውም ዛፍ ፍሬ ትበላለህ። ነገር ግን መልካምና ክፉን ከሚያሳውቀው ዛፍ አትብላ፤ ምክንያቱም ከእርሱ በበላህ ቀን በእርግጥ ትሞታለህ።” (ዘፍጥረት 2:16, 17) አዳምና ሔዋን የአምላክን ሞገስ ላለማጣት እንዲሁም ለእነሱም ሆነ ወደፊት ለሚመሠርቱት ቤተሰብ ጥቅም ሲሉ ከተከለከሉት ፍሬ ከመብላት መቆጠብ ነበረባቸው። ታዲያ የታዘዙትን ፈጽመዋል?

መጽሐፍ ቅዱስ በወቅቱ ምን እንደተፈጠረ ይነግረናል? ሰይጣን ዲያብሎስ በአንድ እባብ በመጠቀም ሔዋንን “በእርግጥ እግዚአብሔር፣ ‘በአትክልቱ ስፍራ ካሉ ዛፎች ከማናቸውም እንዳትበሉ’ ብሎአልን?” ሲል ጠየቃት። ሔዋን፣ አምላክ የሰጣቸውን ትእዛዝ በነገረችው ጊዜ ሰይጣን እንዲህ አላት:- “መሞት እንኳ አትሞቱም፤ ከፍሬው በበላችሁ ጊዜ ዐይናችሁ እንደሚከፈትና መልካምና ክፉን በማወቅ፣ እንደ እግዚአብሔር እንደምትሆኑ እግዚአብሔር ስለሚያውቅ ነው።” ከዚያም ሔዋን የዛፉ ፍሬ የሚጓጓ ሆኖ ስለታያት “ከፍሬው ወስዳ በላች።” አክሎም ዘገባው “ከእርሷም ጋር ለነበረው ለባሏ ሰጠችው፤ እርሱም በላ” ይላል። (ዘፍጥረት 3:1-6) በመሆኑም አዳምና ሔዋን የተሰጣቸውን የመምረጥ ነፃነት በአግባቡ ሳይጠቀሙበት ቀሩ እንዲሁም አምላክን ባለመታዘዝ ኃጢአት ሠሩ።

የተፈጸመው ሁኔታ ምን ያህል ከባድ እንደሆነ ተገንዝበሃል? ዲያብሎስ የተናገረው ነገር አምላክ ለአዳም ከሰጠው ትእዛዝ ጋር ይቃረናል። ሰይጣን አዳምና ሔዋን ክፉና መልካሙን ለመወሰን የይሖዋ እርዳታ እንደማያስፈልጋቸው በተዘዋዋሪ መንገድ ተናግሯል። በመሆኑም የሰይጣን ግድድር ይሖዋ ባለው የሰው ልጆችን የመግዛት ሕጋዊ መብት ላይ ጥያቄ አስነስቷል። በዚህም የተነሳ ሰይጣን ያስነሳው እጅግ ወሳኝ ጥያቄ ‘ይሖዋ የሰው ልጆችን የመግዛት መብት አለው?’ የሚለው ነው። ታዲያ እውነተኛው አምላክ ለዚህ ግድድር ምን ምላሽ ይሰጥ ይሆን?

በቂ ጊዜ ያስፈልጋል

ይሖዋ ሦስቱን ዓመጸኞች ማለትም ሰይጣንን፣ አዳምንና ሔዋንን ለማጥፋት የሚያስችል ኃይል አለው። አምላክ ከእነሱ የበለጠ ኃይል እንዳለው ምንም ጥርጥር የለውም። ይሁን እንጂ ሰይጣን ጥያቄ ያነሳው በይሖዋ ኃይል ላይ ሳይሆን በመግዛት መብቱ ላይ ነው። ይህ ጉዳይ የመምረጥ ነፃነት ያላቸውን ፍጡራን በሙሉ ይመለከታል። እነዚህ ፍጡራን አምላክ ካስቀመጣቸው ተፈጥሯዊ፣ ሥነ ምግባራዊና መንፈሳዊ መመሪያዎች ሳይወጡ የመምረጥ ነፃነታቸውን በአግባቡ ሊጠቀሙበት እንደሚገባ መገንዘብ አለባቸው። ካልሆነ ግን፣ አንድ ሰው የስበትን ሕግ ከግምት ውስጥ ሳያስገባ ከትልቅ ፎቅ ላይ ቢዘል ለከባድ ጉዳት መዳረጉ እንደማይቀር ሁሉ እነሱም አስከፊ ውጤት ይገጥማቸዋል። (ገላትያ 6:7, 8) የማሰብ ችሎታ ያላቸው ፍጡራን በሙሉ የአምላክን ትእዛዝ ችላ ብሎ በራስ መመራት የሚያስከትለውን መዘዝ ማየታቸው ጥቅም ያስገኝላቸዋል። ይህ ደግሞ ጊዜ ይጠይቃል።

አከራካሪ ለሆኑ አንዳንድ ጉዳዮች እልባት ለመስጠት ጊዜ ያስፈልጋል የሚለውን ሐቅ ለመረዳት የሚከተለውን ምሳሌ መመልከት ይቻላል:- ሁለት አባወራዎች ማንኛቸው ጠንካራ እንደሆኑ ለማወቅ ፉክክር ገጠሙ እንበል። ይህ ጉዳይ ወዲያውኑ መልስ ሊያገኝ ይችላል። የሁለቱን ሰዎች ጥንካሬ በሚያነሱት ክብደት መለካት ይቻላል። ይበልጥ ከባድ የሆነውን ሸክም ማንሳት የቻለው ግለሰብ ከሌላኛው የበለጠ ጠንካራ ነው ሊባል ይችላል። ይሁንና ጥያቄው ‘የእነሱ ምላሽ ምንም ይሁን ምን ልጆቹን ከልብ የሚወደው አባት የትኛው ነው’ ወይም ደግሞ ‘ቤተሰቡን በደንብ የሚንከባከበው አባት ማንኛው ነው’ የሚል ቢሆንስ? ጥንካሬን ማሳየትም ሆነ ቃላት መደርደር ብቻውን ለእነዚህ ጥያቄዎች በቂ መልስ ሊሆን አይችልም። ለጥያቄዎቹ አጥጋቢ መልስ ለማግኘት ከተፈለገ በቂ ጊዜ መስጠት፣ ሁኔታዎቹን በጥንቃቄ መገምገምና ትክክለኛ ድምዳሜ ላይ መድረስ ያስፈልጋል።

ያለፉት ጊዜያት ምን ያሳያሉ?

ሰይጣን በአምላክ የመግዛት መብት ላይ ጥያቄ ካስነሳ ወደ 6,000 የሚጠጉ ዓመታት አልፈዋል። ታዲያ ታሪክ ምን አሳይቷል? ሰይጣን በአምላክ ላይ ያስነሳው ክስ ያሉትን ሁለት ገጽታዎች ተመልከት። ሰይጣን ለሔዋን “መሞት እንኳ አትሞቱም” በማለት ያለ አንዳች ኃፍረት ተናግሯል። (ዘፍጥረት 3:4) ይህ ፍጡር አዳምና ሔዋን የተከለከለውን ፍሬ ቢበሉ እንደማይሞቱ ሲናገር ይሖዋን ሐሰተኛ ነው ማለቱ ነው። ይህ በእርግጥ ከባድ ክስ ነው! አምላክ በዚህ ረገድ እውነተኛ አይደለም ከተባለ በሌሎች ነገሮች ላይስ እንዴት እምነት ሊጣልበት ይችላል? ይሁን እንጂ፣ ያለፉት ጊዜያት ምን ያሳያሉ?

አዳምና ሔዋን ለሕመም፣ ለሥቃይ፣ ለእርጅናና በመጨረሻም ለሞት ተዳርገዋል። መጽሐፍ ቅዱስ “አዳም በአጠቃላይ 930 ዓመት ከኖረ በኋላ ሞተ” በማለት ይገልጻል። (ዘፍጥረት 3:19፤ 5:5) ይህ አሳዛኝ ውርስ ለሰው ሁሉ የተዳረሰው ከአዳም ነው። (ሮሜ 5:12) ያለፉት ጊዜያት ሰይጣን “ሐሰተኛ፣ የሐሰትም አባት”፣ ይሖዋ ደግሞ “የእውነት አምላክ” መሆኑን አረጋግጠዋል።—ዮሐንስ 8:44፤ መዝሙር 31:5

ከዚህም በተጨማሪ ሰይጣን፣ ለሔዋን እንዲህ ብሏታል:- “ከፍሬው [እንዳይበሉ ከተከለከሉት ፍሬ] በበላችሁ ጊዜ ዐይናችሁ እንደሚከፈትና መልካምና ክፉን በማወቅ፣ እንደ እግዚአብሔር እንደምትሆኑ እግዚአብሔር ስለሚያውቅ ነው።” (ዘፍጥረት 3:5) ሰይጣን እንዲህ ያለ አሳሳች ሐሳብ በማቅረብ የሰው ልጆች ራሳቸውን የመምራት አጋጣሚ እንዳላቸው ገለጸ። በዚህ መንገድ ሰዎች ከአምላክ ርቀው ራሳቸውን ቢመሩ የተሻለ ሕይወት እንደሚኖራቸው በመጠቆም የመጀመሪያዎቹን ባልና ሚስት አሳታቸው። ይሁን እንጂ ሰይጣን ያቀረበው ሐሳብ እውነት ነው?

በታሪክ ዘመናት ሁሉ የተለያዩ መንግሥታት ተፈራርቀዋል። የሰው ልጆች አሉ የተባሉትን ሁሉንም ዓይነት አገዛዞች ሞክረዋል። ይሁንና በሰው ልጆች ላይ አሰቃቂ ነገሮች በተደጋጋሚ ጊዜያት ደርሰዋል። አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊ ከዛሬ 3,000 ዓመታት ገደማ በፊት ‘ሰው ሰውን የሚገዛው ለመጕዳት ነው’ ወደሚል ምክንያታዊ መደምደሚያ ደርሷል። (መክብብ 8:9) ነቢዩ ኤርምያስ ‘ሰው አካሄዱንም በራሱ አቃንቶ ሊመራ አይችልም’ ሲል ጽፏል። (ኤርምያስ 10:23) ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በሳይንስና ቴክኖሎጂ መስክ የተገኙት ስኬቶች የዚህን አባባል እውነተኝነት ውድቅ ማድረግ አልቻሉም። ያለፉት ጊዜያት ከላይ የተጠቀሱት ሁለት አስተያየቶች እውነት መሆናቸውን አረጋግጠዋል።

ምን ለማድረግ አስበሃል?

አምላክ የፈቀደው ጊዜ ሰይጣን፣ በይሖዋ የመግዛት መብት ላይ ያስነሳው ክስ ሐሰት መሆኑን አረጋግጧል። የአጽናፈ ዓለሙ ሉዓላዊ ገዥ ይሖዋ አምላክ ብቻ ነው። በተጨማሪም ፍጥረታቱን የመግዛት መብት ያለው ሲሆን አገዛዙም ከሁሉም የተሻለ ነው። በአምላክ አገዛዝ ሥር ለዘመናት የኖሩት መንፈሳዊ ፍጥረታት ይህን እውነታ ሲገልጹ እንዲህ ብለዋል:- “ጌታችንና አምላካችን ሆይ፤ ክብርና ሞገስ፣ ኀይልም ልትቀበል ይገባሃል፤ አንተ ሁሉን ፈጥረሃልና፤ በፈቃድህም ተፈጥረዋልና፤ ሆነዋልምና።”—ራእይ 4:11

በአምላክ አገዛዝ ላይ ስለተነሳው ጥያቄ ምን ይሰማሃል? አምላክ አንተን የመግዛት መብት አለው ቢባል ትስማማለህ? ከሆነ፣ የይሖዋን ሉዓላዊነት አምነህ መቀበል ይኖርብሃል። ይህን ለማድረግ በቃሉ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙትን አስደናቂ እውነቶችና ምክሮች በሁሉም የሕይወትህ ዘርፍ በተግባር ማዋል ይገባሃል። ‘አምላክ ፍቅር ስለሆነ’ ሕግጋቱና ትእዛዛቱ ለፍጥረታቱ ካለው ፍቅር የመነጩ ናቸው። (1 ዮሐንስ 4:8) ይሖዋ መልካም የሆነውን ማንኛውንም ነገር አያስቀርብንም። በመሆኑም ቀጥሎ የተጠቀሰውን የመጽሐፍ ቅዱስ ምክር ልብ ማለት ያስፈልግሃል:- “በፍጹም ልብህ በእግዚአብሔር [“በይሖዋ፣” NW] ታመን፤ በራስህ ማስተዋል አትደገፍ፤ በመንገድህ ሁሉ እርሱን ዕወቅ፤ እርሱም ጐዳናህን ቀና ያደርገዋል።”—ምሳሌ 3:5, 6

[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

መጽሐፍ ቅዱስን በማጥናትና ትምህርቶቹን በሥራ ላይ በማዋል የአምላክን አገዛዝ መምረጥህን ማሳየት ትችላለህ

[በገጽ 4 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]

© Jeroen Oerlemans/Panos Pictures