የሆሴዕ መጽሐፍ ጎላ ያሉ ነጥቦች
የይሖዋ ቃል ሕያው ነው
የሆሴዕ መጽሐፍ ጎላ ያሉ ነጥቦች
አሥሩን ነገዶች ባቀፈውና በስተ ሰሜን በሚገኘው የእስራኤል መንግሥት ውስጥ እውነተኛው አምልኮ ሙሉ በሙሉ ጠፍቶ ነበር ለማለት ይቻላል። በዳግማዊ ኢዮርብዓም የግዛት ዘመን እስራኤላውያን ቁሳዊ ብልጽግና አግኝተው የነበረ ቢሆንም ከእሱ ሞት በኋላ ያሉበት ሁኔታ እየተቀየረ ሄደ። ከዚያ ቀጥሎ የነበሩት ዓመታት ሽብርና ፖለቲካዊ አለመረጋጋት የነገሠባቸው ነበሩ። ከዳግማዊ ኢዮርብዓም በኋላ ከነገሡት ስድስት ነገሥታት መካከል አራቱ በሰው እጅ ተገድለዋል። (2 ነገሥት 14:29፤ 15:8-30፤ 17:1-6) በ804 ከክርስቶስ ልደት በፊት ገደማ የጀመረውና ለ59 ዓመታት የቀጠለው የሆሴዕ የነቢይነት ሥራ እስከዚህ የሁከት ዘመን የዘለቀ ነበር።
በሆሴዕ ትዳር ውስጥ የተከሰተው ሁኔታ ይሖዋ ለዓመጸኛው የእስራኤል ብሔር ያለውን ስሜት በግልጽ የሚያሳይ ነበር። የሆሴዕ መልእክት ዋነኛ ጭብጥ የእስራኤላውያንን ኃጢአት ማጋለጥና በእስራኤልና በይሁዳ መንግሥት ላይ የሚመጣውን የጥፋት ፍርድ ማወጅ ነው። ሆሴዕ በስሙ በተጠራው መጽሐፍ ውስጥ ለስለስ ያሉና በጥንቃቄ የተመረጡ እንዲሁም ጠንካራና ገላጭ የሆኑ ቃላትን አስፍሯል። የሆሴዕ መጽሐፍ በመንፈስ አነሳሽነት የተጻፈው የአምላክ ቃል ክፍል እንደመሆኑ መጠን መልእክቱ ሕያውና ዛሬም ቢሆን የሚሠራ ነው።—ዕብራውያን 4:12
“አመንዝራ ሴት አግባ”
ይሖዋ፣ ሆሴዕን “ሄደህ አመንዝራ ሴት አግባ” አለው። (ሆሴዕ 1:2) ሆሴዕ አምላክን የታዘዘ ሲሆን ከጎሜር ወንድ ልጅ ወለደ። ጎሜር ቀጥሎ የወለደቻቸው ሁለት ልጆች በምንዝር የተወለዱ እንደሆኑ ግልጽ ነው። እነዚህ ልጆች ሎሩሃማና ሎዓሚ የሚል ስም የወጣላቸው ሲሆን የስማቸው ትርጉም ይሖዋ ለእስራኤላውያን ምሕረት እንደማያደርግላቸውና ታማኝ ያልሆኑት ሕዝቦቹን እንደሚተዋቸው የሚጠቁም ነው።
ይሖዋ ዓመጸኛ ስለሆኑት ሕዝቦቹ ምን ይሰማው ነበር? ለሆሴዕ እንዲህ ብሎታል:- “እርሷ በሌላ ሰው የምትወደድ አመንዝራ ብትሆንም፣ አሁንም ሂድና ሚስትህን ውደዳት፤ ወደ ሌሎች አማልክት ዘወር ቢሉ[ም] . . . እግዚአብሔር እስራኤላውያንን እንደ ወደዳቸው አንተም እርሷን ውደዳት።”—ሆሴዕ 3:1
ቅዱስ ጽሑፋዊ ጥያቄዎችና መልሶቻቸው:-
1:1—ሆሴዕ ባገለገለባቸው ዓመታት በይሁዳ ይገዙ የነበሩትን አራት ነገሥታት በሙሉ በስም ሲጠቅስ ከእስራኤል ነገሥታት መካከል ግን የአንዱን ስም ብቻ ያሰፈረው ለምንድን ነው? ይህ የሆነው የአምላክን ምርጥ ሕዝቦች የመግዛት ሕጋዊ መብት ያላቸው ከዳዊት የትውልድ መስመር የተገኙ ነገሥታት ብቻ ስለሆኑ ነው። በይሁዳ ይገዙ የነበሩት ነገሥታት ከዳዊት የዘር ሐረግ የመጡ ሲሆን በሰሜናዊ የእስራኤል መንግሥት የነበሩት ግን ከዚህ የዘር ሐረግ የተገኙ አልነበሩም።
1:2-9—በእርግጥ ሆሴዕ አመንዝራ ሴት አግብቷል? አዎን፤ ሆሴዕ ያገባት ሴት በኋላ ላይ አመንዝራ ሆናለች። ነቢዩ ሆሴዕ ስለ ቤተሰብ ሕይወቱ የገለጻቸው ሐሳቦች በሕልም ወይም በራእይ የተመለከታቸው ነገሮች ስለ መሆናቸው የገለጸው ነገር የለም።
1:7—ይሁዳ ምሕረት ያገኘችውና ከጥፋት የዳነችው መቼ ነበር? ይህ ትንቢት ፍጻሜውን ያገኘው በ732 ከክርስቶስ ልደት በፊት በንጉሥ ሕዝቅያስ የግዛት ዘመን ነበር። በዚያን ወቅት ይሖዋ በአንድ መልአክ አማካኝነት 185,000 የጠላት ሠራዊትን በመግደል ኢየሩሳሌምን ከአሦራውያን ስጋት ነፃ አውጥቷታል። (2 ነገሥት 19:34, 35) በመሆኑም ይሖዋ ይሁዳን “በቀስት ወይም በሰይፍ ወይም በጦርነት ወይም በፈረሶችና በፈረሰኞች ሳይሆን” በአንድ መልአክ አማካኝነት አድኗታል።
1:10, 11—ሰሜናዊው የእስራኤል መንግሥት የወደቀው በ740 ከክርስቶስ ልደት በፊት ከነበረ፣ የእስራኤል ሕዝብ ከይሁዳ ጋር እንዴት ‘አንድ ሊሆኑ’ ይችላሉ? አይሁዳውያን በ607 ከክርስቶስ ልደት በፊት በምርኮ ወደ ባቢሎን ከመወሰዳቸው በፊት በሰሜናዊው የእስራኤል መንግሥት ይኖሩ የነበሩ በርካታ ሰዎች ወደ ይሁዳ ፈልሰው ነበር። (2 ዜና መዋዕል 11:13-17፤ 30:6-12, 18-20, 25) በግዞት ተወስደው የነበሩት አይሁዳውያን በ537 ከክርስቶስ ልደት በፊት ወደ ትውልድ አገራቸው ሲመለሱ ቀደም ሲል ከሰሜናዊው የእስራኤል መንግሥት ወደ ይሁዳ ሄደው የነበሩት እስራኤላውያን ልጆችም አብረዋቸው ተመልሰዋል።—ዕዝራ 2:70
2:21-23—ይሖዋ ‘ስለ ራሴ ስል [ኢይዝራኤልን] በምድሪቱ እተክላታለሁ፤ እምራታለሁ’ በማለት የተናገረው ትንቢት ምን ትርጉም አለው? ሆሴዕ ከጎሜር የወለደው የበኩር ልጅ ኢይዝራኤል ይባል ነበር። (ሆሴዕ 1:2-4) “አምላክ ዘርን ይዘራል” የሚል ትርጉም ያለው ይህ ስም፣ ይሖዋ ታማኞቹን ቀሪዎች በ537 ከክርስቶስ ልደት በፊት በመሰብሰብ ልክ እንደ ዘር በይሁዳ ምድር እንደሚዘራቸው የሚያመለክት ትንቢት ይዟል። ለ70 ዓመት ባድማ ሆና የቆየችው ምድር አሁን እህል፣ ጣፋጭ ወይንና ዘይት ይመረትባታል። በዚህ ትንቢት ላይ፣ እነዚህ መልካም ነገሮች ምድር ፍሬዋን እንድትሰጥ እንደሚጠይቁ እንዲሁም ምድር ሰማያትን ዝናብ እንዲጥሉ እንደምትለምን ተደርጎ ማራኪ በሆነ መንገድ ተገልጿል። ሰማያት ደግሞ አምላክ ዝናብ ያዘለ ደመናን እንዲልክ ይማጸናሉ። ይህ ሁሉ የሚደረገው ከግዞት የሚመለሱ ቀሪዎችን ፍላጎት ለማርካት ሲባል ነው። ሐዋርያው ጳውሎስና ጴጥሮስ ሆሴዕ 2:23ን የመንፈሳዊ እስራኤል ቀሪዎችን የመሰብሰቡን ሥራ ለማመልከት ተጠቅመውበታል።—ሮሜ 9:25, 26፤ 1 ጴጥሮስ 2:10
ምን ትምህርት እናገኛለን?
1:2-9፤ 3:1, 2፦ ሆሴዕ የአምላክን ፈቃድ ለመፈጸም ሲል በትዳሩ በመጽናት ምን ያህል መሥዋዕት እንደከፈለ አስብ! እኛስ የአምላክን ፈቃድ ለመፈጸም ስንል የግል ምርጫዎቻችንን ለመተው ፈቃደኞች የምንሆነው እስከ ምን ድረስ ነው?
1:6-9፦ ይሖዋ ቃል በቃል የሚፈጸምን ምንዝር እንደሚጠላ ሁሉ መንፈሳዊ ምንዝርንም ይጠላል።
1:7, 10, 11፤ 2:14-23፦ ይሖዋ እስራኤልንና ይሁዳን አስመልክቶ የተናገረው ትንቢት ፍጻሜውን አግኝቷል። የይሖዋ ቃል ምንጊዜም መፈጸሙ አይቀርም።
2:16, 19, 21-23፤ 3:1-4፦ ይሖዋ ከልብ ንስሐ የሚገቡትን ይቅር ለማለት ፈቃደኛ ነው። (ነህምያ 9:17) እኛም ልክ እንደ ይሖዋ ከሌሎች ጋር ባለን ግንኙነት ርኅሩኆችና መሐሪዎች መሆን ይገባናል።
‘ይሖዋ የሚያቀርበው ክስ አለው’
ይሖዋ ‘በምድሪቱ በሚኖሩ ሰዎች ላይ የሚያቀርበው ክስ አለው።’ ለምን? ምክንያቱም በምድሪቱ ላይ ‘ታማኝነት፣ ፍቅር እንዲሁም አምላክን ማወቅ የለም።’ (ሆሴዕ 4:1) ከዳተኛ የሆኑት እስራኤላውያን ያጭበረብሩ፣ ደም ያፈሱ እንዲሁም ቃል በቃልም ሆነ በመንፈሳዊ ምንዝር ይፈጽሙ ነበር። የአምላክን እርዳታ ከመጠየቅ ይልቅ ‘አንድ ጊዜ ወደ ግብፅ ይጣሩ፣ ሌላ ጊዜ ደግሞ ወደ አሦር ዞር ይሉ ነበር።’—ሆሴዕ 7:11
ይሖዋ ‘እስራኤል ይዋጣል’ የሚል የፍርድ መልእክት አስተላልፏል። (ሆሴዕ 8:8) የይሁዳ መንግሥትም ቢሆን ከተጠያቂነት አያመልጥም። ሆሴዕ 12:2 ይሖዋ “በይሁዳ ላይ የሚያቀርበው ክስ አለው፤ ያዕቆብን እንደ መንገዱ ይቀጣዋል፤ እንደ ሥራውም ይከፍለዋል” ይላል። ይሁንና አምላክ “ከመቃብር ኀይል እታደጋቸዋለሁ፤ ከሞትም እቤዣቸዋለሁ” በማለት ቃል ስለገባ ተመልሰው እንደሚቋቋሙ ምንም ጥርጥር የለውም።—ሆሴዕ 13:14
ቅዱስ ጽሑፋዊ ጥያቄዎችና መልሶቻቸው:-
6:1-3—“ኑ፤ ወደ እግዚአብሔር [“ይሖዋ፣” NW] እንመለስ” በማለት የተናገረው ማን ነው? ታማኝ ያልሆኑት እስራኤላውያን ወደ ይሖዋ እንመለስ በማለት እርስ በርሳቸው ለመበረታታት ሞክረው ሊሆን ይችላል። ሁኔታው እንዲህ ከሆነ፣ ይህን ያደረጉት ንስሐ የገቡ መስለው ለመታየት መሆን አለበት። ምክንያቱም ፍቅራቸው ልክ “እንደ ማለዳ ጉም፣ እንደሚጠፋም የጧት ጤዛ” ለአፍታ ብቻ የሚቆይና ፈጥኖ የሚያልፍ ነው። (ሆሴዕ 6:4) በሌላ በኩል ግን ይህ ሐሳብ፣ ሆሴዕ ሕዝቡ ወደ ይሖዋ እንዲመለስ ያቀረበው ልመና ሊሆን ይችላል። ያም ሆነ ይህ አሥሩን ነገዶች ባቀፈውና በስተ ሰሜን በሚገኘው የእስራኤል መንግሥት ይኖሩ የነበሩት ዓመጸኛ ሰዎች እውነተኛ ንስሐ መግባትና ወደ ይሖዋ መመለስ ነበረባቸው።
7:4—አመንዝራ የሆኑት እስራኤላውያን “እንደሚነድ ምድጃ” የሆኑት በምን መልኩ ነበር? ይህ ንጽጽር የልባቸው ክፉ ምኞት ምን ያህል ከፍተኛ እንደነበር ያሳያል።
ምን ትምህርት እናገኛለን?
4:1, 6፦ የይሖዋን ሞገስ ላለማጣት ከፈለግን ስለ እሱ ያለንን እውቀት ማሳደግና የምንማረውን ነገር ተግባራዊ ማድረግ ይኖርብናል።
4:9-13፦ ይሖዋ የሥነ ምግባር ብልግና የሚፈጽሙና በሐሰት አምልኮ የሚካፈሉ ሰዎችን ይቀጣል።—ሆሴዕ 1:4
5:1፦ የአምላክን ሕዝቦች የሚመሩ ሁሉ ሙሉ በሙሉ ክህደትን ማስወገድ ይኖርባቸዋል። ይህ ካልሆነ ግን አንዳንዶችን በሐሰት አምልኮ እንዲካፈሉ በማባበል ‘ወጥመድና መረብ’ ሊሆኑባቸው ይችላሉ።
6:1-4፤ 7:14, 16፦ ንስሐ እንደገቡ መናገር ብቻ ግብዝነት ከመሆኑም ባሻገር ከንቱ ነው። ኃጢአት የሠራ አንድ ሰው የአምላክን ምሕረት ማግኘት ከፈለገ ከልብ ንስሐ መግባቱን ማሳየት ይኖርበታል። ለውጥ አድርጎ ከፍተኛ ደረጃ ወዳለው እውነተኛ አምልኮ በመመለስ ይህንን ማሳየት ይችላል። ተግባሩ፣ ከአምላክ ከፍተኛ የሥነ ምግባር አቋም ጋር የሚስማማ መሆን አለበት።—ሆሴዕ 7:16 የአዲስ ዓለም ትርጉም የግርጌ ማስታወሻ
6:6 (NW)፦ አንድ ሰው ኃጢአት የመሥራት ልማድ ከተጠናወተው ለአምላክ ጽኑ ፍቅር ጎድሎታል ማለት ነው። የቱንም ያህል መንፈሳዊ መሥዋዕት ቢቀርብ ይህን ጉድለት መሸፈን አይቻልም።
8:7, 13፤ 10:13፦ “ሰው የሚዘራውን ያንኑ ያጭዳል” የሚለው የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓት እውነት መሆኑ ጣዖት አምላኪ በሆኑት እስራኤላውያን ላይ በደረሰው ሁኔታ ታይቷል።—ገላትያ 6:7
8:8፤ 9:17፤ 13:16፦ ስለ ሰሜናዊው መንግሥት የተነገሩት ትንቢቶች ፍጻሜያቸውን ያገኙት ዋና ከተማው ሰማርያ በአሦራውያን እጅ በወደቀችበት ጊዜ ነው። (2 ነገሥት 17:3-6) ይህም ይሖዋ የተናገረውን እንደሚያደርግና ቃል የገባውን እንደሚፈጽም እንድንተማመን ያደርገናል።—ዘኍልቍ 23:19
8:14፦ ይሖዋ ኢየሩሳሌምና ይሁዳ ባድማ እንደሚሆኑ አስቀድሞ በተናገረው መሠረት በ607 ከክርስቶስ ልደት በፊት በባቢሎን አማካኝነት ‘በይሁዳ ከተሞች ላይ እሳት ለቋል።’ (2 ዜና መዋዕል 36:19) የአምላክ ቃል በጭራሽ ሳይፈጸም አይቀርም።—ኢያሱ 23:14
9:10፦ እስራኤላውያን ራሳቸውን ለእውነተኛው አምላክ የወሰኑ ቢሆኑም እንኳ ‘ወደ ብዔልፌጎር በመጡ ጊዜ ለዚያ አሳፋሪ ጣዖት ራሳቸውን ለይተዋል።’ እኛም ከእነሱ መጥፎ ምሳሌ ትምህርት በማግኘት ራሳችንን ለይሖዋ ስንወስን የገባነውን ቃል ከማፍረስ መቆጠባችን ጥበብ ይሆናል።—1 ቆሮንቶስ 10:11
10:1, 2, 12፦ አምላክን የምናመልከው ከግብዝነት በራቀ ልብ መሆን ይኖርበታል። ‘ለራሳችን ጽድቅን ስንዘራ፤ [የአምላክን] ጽኑ ፍቅር ፍሬ እናጭዳለን።’
10:5፦ ቤትአዌን (“የጉዳት ቤት” የሚል ትርጉም አለው) ቤቴልን (“የአምላክ ቤት” ማለት ነው) ለማንቋሸሽ የተሠጠ ስም ነው። በቤትአዌን የነበረው የጥጃ ጣዖት ወደ ባቢሎን በምርኮ በተወሰደ ጊዜ የሰማርያ ነዋሪዎች፣ ያመልኩበት የነበረውን ይህን ጣዖት በማጣታቸው በጣም አዝነዋል። ራሱን እንኳ ማዳን በማይችል በድን የሆነ ጣዖት መታመን እንዴት ያለ ሞኝነት ነው!—መዝሙር 135:15-18፤ ኤርምያስ 10:3-5
11:1-4፦ ይሖዋ ምንጊዜም ሕዝቡን የሚይዘው በፍቅር ነው። ለአምላክ መገዛት ፈጽሞ ከባድ ሸክም አይደለም።
11:8-11፤ 13:14፦ ይሖዋ፣ ሕዝቡ እውነተኛውን አምልኮ መልሶ እንደሚያቋቁም የተናገረው ቃል ‘በከንቱ ወደ እሱ አልተመለሰም።’ (ኢሳይያስ 55:11) እስራኤላውያን በ537 ከክርስቶስ ልደት በፊት ከባቢሎን ግዞት ነፃ የወጡ ሲሆን ቀሪዎቹም ወደ ኢየሩሳሌም ተመልሰዋል። (ዕዝራ 2:1፤ 3:1-3) ይሖዋ በነቢያቱ አማካኝነት ያስነገረው ማንኛውም ቃል ሳይፈጸም አይቀርም።
12:6 (NW)፦ ምንጊዜም ቢሆን ፍቅራዊ ደግነትንና ፍትሕን ማሳየት ብሎም ይሖዋን ተስፋ ማድረግ ቁርጥ ውሳኔያችን መሆን ይኖርበታል።
13:6፦ እስራኤላውያን ‘በጠገቡ ጊዜ ታበዩ፤ ከዚያም [ይሖዋን] ረሱ።’ እኛም የትዕቢት ዝንባሌ እንዳይጠናወተን ራሳችንን መጠበቅ ይኖርብናል።
የይሖዋ “መንገድ ቅን ነው”
ሆሴዕ “እስራኤል ሆይ፤ በኀጢአትህ ምክንያት ስለ ወደቅህ፣ ወደ አምላክህ ወደ እግዚአብሔር [“ይሖዋ፣” NW] ተመለስ” በማለት ተማጽኗል። ሕዝቡንም እንደሚከተለው በማለት ይሖዋን እንዲለምኑ አሳስቧቸዋል:- “ኀጢአታችንን ሁሉ ይቅር በለን፤ የከንፈራችንንም ፍሬ እንድናቀርብ፣ በምሕረትህ ተቀበለን።”—ሆሴዕ 14:1, 2
ንስሐ የገባ አንድ ኃጢአተኛ ወደ ይሖዋ መምጣት፣ በመንገዶቹ መመላለስና ለአምላክ የምስጋና መሥዋዕት ማቅረብ ይኖርበታል። ለምን? ምክንያቱም “የእግዚአብሔር [“የይሖዋ፣” NW] መንገድ ቅን ነውና፤ ጻድቃን ይሄዱበታል።” (ሆሴዕ 14:9) ገና ብዙ ሰዎች “በመጨረሻውም ዘመን በመንቀጥቀጥ ወደ እግዚአብሔርና [“ይሖዋና፣” NW] ወደ በረከቱ” እንደሚመጡ ማወቃችን ምንኛ ያስደስታል!—ሆሴዕ 3:5
[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የሆሴዕ የቤተሰብ ሕይወት ይሖዋ ከእስራኤላውያን ጋር የነበረውን ግንኙነት ያሳያል
[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ሰማርያ በ740 ከክርስቶስ ልደት በፊት ስትወድቅ አሥሩን ነገዶች ያቀፈው የእስራኤል መንግሥት ከሕልውና ውጪ ሆነ